ነፋስን የዘሩ ዐውሎ ነፋስን ያጭዳሉ
Ethiopian Semay
ጌታቸው ረዳ
10/18/2026
የፋሺስቶች መንጠርራት በመጨረሻ ለምን በውርደት ይጠናቀቃል?
የምንነጋገረው ሰለ ወያኔ፣ ስለ ኦነግ ስለ የጎጃሙ ፋኖ እና ስለ አብይ አሕመድ አክራሪ ኦሮሙማዊነት እና መሰል ፋሺስታዊ ርዕዮተ-ዓለም የሚከተሉ የፋሺስት ቡድኖችን ነው። ወያኔን ስንመለከተት እንደ ሙሶሎኒ ከከፍተኛ ማማ ወደ አፈር እንዴት እንደተንከባለለ በዓይናችን እያየን ነው። በወቅቱ ሰሚ ያጣን
ቢሆንም ፤ ይህ እንደሚከሰት በጣም በጣት የምንቆጠር ሃያሲያን ተንብየን ይነበረው ክስተት ከብዙ አመታት በፊት ነው።
በውርደት የመጠናቀቁ ምክንያት የሆኑት እራሱ የሚከተላቸው አቀጣጣይ ቢጋሮቹ ናቸው። ምክንያቱም ዋና ዋና ምሰሶዎቹ—እጅግ ከፍተኛ የሆነ ትምክሕት የሞላበት ብሔርተኝነት፣ ፍጹም አምባገነንነት እና ቀጣይነት ያለው መስፋፋት (ሄጂመኒ) ለውደቀቱ ምክንያቶች ናቸው።
ፋሺዝም የሚገነባው የማይሸነፍ እና ስህተት የማይሰራ መሪ እና ድርጅት አለን የሚል ቅዠት ውስጥ ስለሚተበተብ ውስብስብ እውነታዎች ጋር ሰለሚጋጭ ሲጋጭ የግድ ይፈራርሳል።
ወያኔን ስንመለከት በዓይናችን የምናያቸውና ያየናቸው በታሪክም ሆነ በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ፣ በበርካታ ሥር-ነቀል ጉድለቶች ምክንያት ከፍተኛ ውርደት ተከናንበዋል፡-
1. ወያኔዎችም ሆኑ የጎጃም ፋኖ የሚመሩት የፋኖ መሪዎች እነሱ ከበቀሉት ምድር የወጣ መሪ የማይሳሳት መሪ አለን የሚለው አፈ-ታሪክ እና አስከፊው እውነታ ስንመለከት፤ በተለይ በጎጃም ምድር በዘመነ ካሴ፤ በትግሬ ምድር መለስ ዜናዊን ስንመለከት ባንድ ግለሰብ ዙርያ የሚመለክ ድርጅትን እናያለን። ተከታዮቻቸው ይህንን ሂስ ሲመለከቱ መቀበል ዳገት ይሆናባቸዋል፤ ወደ ስድብም ይሽቀዳደማሉ።
ምንያቶቹን እንመልከት፡
እነኚህ ድርጅቶች በከፍተኛ ትምክሕትና በልዩ የፍጡርነት ስብዕና የተገነቡ መሪዎች ናቸው ተብለው ስለሚመለኩ ተከታዮቻቸውም ለኛ መዳኛ የተላከ መሪ ነው ብለው እንዲያምኑት ስለሚደረግ ፋሺዝም ሲገነባ በአንድ ግለሰብ ዙሪያ በሚገነባ አምልኮ (cult of personality) ላይ ስለሚያተኩር፤ ተከታዮቹ መሪውን ዓለምን ያናገረ ተአምር ሰሪ አድርገው ይቀበሉታል።
ይህም ሲሆን ድርጅቱ የሚፈጽማቸው ስሕተቶች ሲከሰቱ ተቃውሞ እንደ ወንጀል ስለሚቆጠር፣ መሪው/ድርጅቱ/ ማንኛውንም አጥፊ ውሳኔ ሲወስን ተከታዮቹ ከመሪው ውሳኔዎች ጋር ይስማማሉ። ይህ ሁኔታ ወደ አስከፊ ስትራቴጂካዊ ስህተቶች ሰለሚመራ —ለምሳሌ ወያኔ ማሸነፍ የማይቻልባቸው ጦርነቶች ውስጥ በመግባቱ ያልጠበቀው የጥንካሬ ገጽታው ከፈተኛ የሰው ሕይወት ኪሳራ እና መንግሥት በነበረበት 27 አመት በጥናት የገነባውንየትግራይ ምጣኔ ሃብት ወድሟል።
2. ስለሆነም የወያኔ ፋሺዝም ቀጣይነት ያለው ጦርነት አስፈላጊነትን ይከተላል፤
ፋሺስታዊ ርዕዮተ-ዓለም ሰላምን እንደ መበስበስ እና መቀዛቀዝ ምልክት አድርጎ ሰልሚመለከተው፤ ህልውናውን ለማስረዳትም የማያቋርጥ ትግል እና መስፋፋት ያስፈልገዋል። ይህ ባሕሪው ወደ ጠበኛ እና «ጦር አውርድ» የማስፋፋት ትዕይንት ዳርጎታል።
በሚገርም ሁኔታ የወያኔ ፋሺዝም እውነተኛ ፋሺስት መሆኑን የምናይበት መለኪያ በክልሉ ያከማቸው ይፋ እና ድብቅ ሀብት ለቀሰቀሰው ጦርነት በመጠቀም መላው ዓለም እና ጎረቤቶቹ በእርሱ ላይ እንደተነሳ አድርጎ በመሳል ተቀናቃኞቹንም «በጠመንጃየ የተማረኩ ምርኮኞቼ የነበሩና ያንበረከክሁዋቸው ናቸው» እያለ እራሱን በመካቡ ያልጠበቀው ሙሉ ወታደራዊ ሽንፈት እና በውርደት የመንበርከክ እጣ ፈንታ ገጥሞታል።
3. በሕዝቡ ላይ የሚደርስ የስነ-ልቦና ድንጋጤ
ፋሺስታዊ ቡድኖች ህዝባቸውን «ለዓለም የበላይነት የታጨ "የላቀ" ልዩ
ዘር እንደሆኑ» እንዲያምኑ ለማድረግ ለአመታት ይሰሩባቸዋል/አይተናልም።ሕዝቡ የጠበቀው የበላይንት ሲያጣ፣ ቃል ከተገባው ክብር እና ከተሸነፉ በኋላ ከሚገጥመው አስከፊ እውነታ መካከል ያለው ልዩነት፣ ጥልቅ የሆነ የብሔራዊ ውርደት እና የመክዳት ስሜት ስለሚፈጥር፤ ተከታዮቹ መሪውን ወደ መክዳት ወይንም መልሶ «መሪውን ወደ
መብላት» ያመራል።
በታሪክ ውስጥ ይህ አዝማሚያ በቤኒቶ ሙሶሊኒ እና በአዶልፍ ሂትለር ዕጣ ፈንታ በግልጽ ታይቷል፤ የእነሱም አገዛዞች የሺህ ዓመት ክብርን ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ግን በአጠቃላይ ወታደራዊ ውድቀት፣ በግዛት መከፋፈል እና በአመራራቸው ላይ በደረሰ የህዝብ ውርደት ተጠናቀዋል። የወያኔ ዕጣ ፈንታ በተመሳሳይ ቢጠናቀቅም፤ የአብይ አሕመድ ኦሮሙማ ፋሺስታዊ አጅንዳም ከዚህ አይለይም፤ ምልክቱም እያየን ነው።
የየአብይ አሕመድ ኦሮሙማ ፋሺስታዊ ሂደትም ስንመለከት፤ ፋሺስቶች ሊፈርሱ ሲሉ የሚታየው ገጽታ
እያሳየን ነው። ይኸውም፤
የውስጥ ተቋማት መፍረስ
ብቃትን መሰረት ያደረገ አሰራርን፣ ገለልተኛ ፍርድ ቤቶችን እና ሙያዊ ተቋማትን በፓርቲው ላይ በሚደረግ ፍጹም ታማኝነት በመተካት፣ ልክ በወያኔ መንግሥት እንዳየነው የአብይ አሕመድ ፋሺዝምም የመንግስትን መዋቅሮች ከውስጥ ሲቦረቡረው እና ሲያዳክመው እያየን ነው። በሂደት ለወድፊቱ ትልቅ ቀውስ ሲከሰት፣ ሙሰኛ እና ብቃት የሌለው ቢሮክራሲ ሁኔታውን መቆጣጠር ስለማይችል፣ ነገሮች ወደ ትርምስ እና ውድቀት ያመራሉ። ወያኔ የወደቀበት ሂደት የአብይ አሕመድ ኦሮሙማም እየደገመው ይገኛል።
ለዚህ ነው "ነፋስን የዘሩ ዐውሎ ነፋስን ያጭዳሉ" የምለው ። – ይህ ጥቅስ ለፋሺስት አገዛዞች በተደጋጋሚ የሚጠቀስ የታወቀ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ሲሆን፣ ሌሎችን ለመቆጣጠር የሚጠቀሙበት የኃይል እርምጃና ጥቃት በመጨረሻ ተመልሶ እነርሱኑ እንደሚያጠፋቸው ያመለክታል።
ጌታቸው ረዳ

