ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ
አገሬ አዲስ
Ethio Semay
The Two Famous Narcissists Power Monger Twins Hitler & Abiy Noble Prize winners (Posted Ethio Semay) |
እኛ ኢትዮጵያውያን ነገራትን የምናይበትና የምንገመግምበት ብሎም የምናነጣጥርበት እውቀትና
ችሎታ ባለቤቶች ነን።እነዚህ ችሎታዎች በዩኒቨርሲቲ ተምረን ያገኘናቸው ሳይሆን ከዕድሜና ከተመክሮ ያካበትናቸው ግሩም ድንቅ እሴቶቻችን ተረትና ምሳሌ፣ቅኔ፣ሰምና ወርቅ ተረባ፣ለክፉም ሆነ ለደግ፣ለምስጋናም ሆነ
ለነቀፋ ስሜታችንን የምንገልጽባቸው ቃለ ምህዳሮቻችን ናቸው።
ይህም “ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ ” የሚለው አባባላችን ለእራሱና ለቤተሰቡ ብሎም
ለተወለደበት ሃገርና ማህበረሰብ ብዙም ሳይጨነቅ፣እዬጎዳም ለራሱ ክብርና ዝና ብሎም ጥቅም ለውጭ ወይም ለጎረቤት ደፋ ቀና የሚለውን
አስመሳይ ለመግለጽ የምንጠቀምበት አባባላችን ነው።
ዶር አብይ አህመድ በምዕራቡ ዓለም
የኖቤል ሽልማት የ2012 ዓም ወይም በፈረንጆቹ 2019 የሰላም ተሸላሚ ሆኖ ተመርጥዋል።ኢትዮጵያዊ ለዚህ አወዛጋቢ የሽልማት ዕድል
በመብቃቱ ደስ ቢለንም የስጦታው ምክንያት ግን በአንድ ገጹ ብቻ በታዬ መልኩ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።ለሰላም የሠሩና የሚሰሩ ሰዎች
ላበረከቱት መልካም አስተዋጽኦ እውቅና ማገኘታቸው ተገቢና ትክክል ነው።
ዶር አብይ አህመድ ለሽልማቱ የበቁት
ዋናው ምክንያት በነጮቹ መንግሥታት ድጋፍና እርዳታ ከኢትዮጵያ የተገነጠለችውን ኤርትራን እውቅና በመስጠትና ሰፍኖ የነበረውን ውጥረት
ከዛም በላይ የምዕራቡ መንግሥታት በሰላም ማስከበሩ ስም ያሰፈሩት ጦር ሃይልና የሚያወጡት ወጭ ስለቀረላቸው፣በአፍሪካ ውስጥ ለሚያካሂዱት
ሰላማዊ ወረራ የተመቻቸ የፖለቲካ ድባብ እንዲሰፍን ጥረት በማድረጉ ነው።ሰላም ከተባለ በቅድሚያ አንድ መሪ በሃገሩ ውስጥ ሰላምና
መረጋጋት እንዲፈጠር የዛ ጦስ ምክንያት የሆነውን ለማጥፋት ሲነሳና
በተግባር ሲያሳይ መሆን ነበረበት።የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ መሪ ኔልሰን ማንዴላ በአገራቸው የነበረውንና ሊኖርም የሚችለውን
ዘረኛ ስርዓት በሰላማዊ መንገድ ማሶገዳቸውና ቅራኔውን በመፍታታቸው፣ቅርሾ ሳይኖር አገራቸው በይቅርታ መርከብ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ
እንድትሸጋገር በማድረጋቸው ነበር።ይህ ሥራቸው እውነትም ለሰላም ሽልማት ያበቃቸዋል።ከዚያ በፊትማ በሸላሚዎቹ አሸባሪ ተብለው
27 ዓመት በሮቢን ደሴት እስር ቤት ውስጥ ሲማቅቁ ማን ዞር ብሎ አያቸው? የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ትግል የሌላውን ሀገር ሕዝብ ድጋፍ
በማግኘቱና ዓለም አቀፋዊ መልክ እዬያዘ ሲመጣ ሁኔታው ከእጅ ሳይወጣና
በዘረኛ የደቡብ አፍሪካ ነጮች ላይ የበቀል ክንድ ሳይዘረጋ ኔልሰን ማንዴላን በመፍታት ከሞላ ጎደል የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ሕዝብ
መብቱን እንዲያገኝ ሳይወዱ በግድ ያደረጉት ስምምነት ነው።ያም ቢሆን የኔልሰን ማንዴላና የሌሎቹ ታጋዮች ቆራጥነት ባይኖር ኖሮ ለዛም
ለመብቃት አይቻልም ነበር።
ወደ እኛው ዶር አብይ አህመድ ስንመለስ
እርግጥ ነው ከመለስ ዜናዊና ከሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ሲነጻጸር የተለዬ ነው።ሆኖም ግን በአቀራረብና በስልት ከመለዬት ሌላ የሚመራበት
ሕገመንግሥት፣ለሥልጣን የመጣበት አካሄድ፣የሚወክለው የጎሰኞች ስብስብ የሆነው ኢሕአዴግ ተመሳሳይ በመሆኑና በዚህም ተመሳሳይ ስርዓት
የአገራችን አንድነት ፣ሰላምና የሕዝብ መብት የተጠበቀበት ባለመሆኑ፣በሚሊዮን
የሚቆጠር እትዮጵያዊ በማንነቱ ሲፈናቀል፣ሲገደል ፣ሲዋከብ የታዬበት ጊዜ ቢኖር በዶር አብይ ዘመነ መንግሥት ነው። አሁንም ተቃዋሚና
ተች ይታሰራል፣ይዋከባል፤አሁንም ዶር አብይ በቅርበት በሚያዬው በአዲስ አበባ ከተማ ሳይቀር ሕዝብ ይፈናቀላል።ውሎ መግባት የሚያጠራጥርበት
ሁኔታ የሰፈነ ነው።አሸባሪ የቄሮ መንጋ እንደፈለገ የሚቦርቅበትን ስርዓትና የፖለቲካ ቡድን የሚመራ ሰው የሰላም አባት ተብሎ መሰዬሙ
የሰላምን ትርጉም ያዛባል ብቻ ሳይሆን ይክዳል።
የኖቤል ሸላሚዎቹ የሚያዩትና የሚያምኑበት
ዋናው መለኪያቸው የእነሱ ጥቅም ተጠብቋል፣ሊጠበቅ ይችላል ወይስ አልተጠበቀም ከሚል ስሜት ነው።ለዚያ የቆመ መሪ የራሱን ሕዝብ ቢጠብሰው
አይሸታቸውም።ዶር አብይ አህመድ ከኖቤል ሽልማት ውጭ በዬአረብ አገሩና በሌሎችም አገሮች እውቅናና ሽልማት ተችሮለታል፤ይህ የኖቤል
ሽልማት የመጀመሪያው አይደለም።በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰበሰበው ሽልማት በተሸላሚነት ክብረወሰን የሰበረ የመጀመሪያው መሪ ሳያደርገው
አይቀርም።መታዬት ያለበት ሽልማቱ ከነማንና ለምን ተሰጠ የሚለውን ነው።አረቦቹ በንግድና በኢንቨስትመንት ስም ሕዝብ የተነፈገውን
የመኖሪያና የታሪክ ቅርስ ያረፈበትን ቦታ የፈለጋቸውን ያህል እንዲይዙ በማድረጉ ሲሆን በምዕራቡ በኩል ደግሞ በኔዎሊበራል የፖለቲካ
ጉዞ የገሪቱን በግልባላይዜሽን ሽፋን እንዲቆጣጠሩ በር ስለከፈተላቸው ነው።ለገበያ የወጡትን የአገሪቱን አንጡራ ሃብቶች ለመቀራመት ዕድል ስለሰጣቸው የምስጋና መግለጫ አድርገውታል። የኢትዮጵያ ሕዝብማ እርስ በርሱ የሚተላለቅበትን የጎሳ ፖለቲካ የኢሕአዴግን
ካምፕ ኦፒዲኦን(ኦዴፓ) ወክሎ እያተራመሰው ነው።አሸባሪ የሆኑትን የራሱን ጎሳ የቄሮ መንጋ ከማሰርና ከመቅጣት ይልቅ ተጠቂዎቹን ለምን አለቀሳችሁ ብሎ እያሸማቀቀና ድምጻቸውን
ለማሰማት አደባባይ እንዳይወጡ በማፈን ተግባር ላይ ተሰማርቱዋል።ይህ አድራጎቱ ነው “ ለቤት ቀጋ ለውጭ አልጋ ” የሚያሰኘው።
“እዬዬም ሲደላ ነው” ምንም እንኳን መሠራቱ አስፈላጊ ቢሆንም ከጊዜውና ከቅደም ተከተሉ አኳያ ሲታይ አሁን በዬቦታው የሚከናወነው የፓርክ ሥራና
ምረቃ ለአስገንቢው አካል ወይም ግለሰብ ከመታሰቢያነቱ ባሻገር ጊዜውን የጠበቀ አይደለም።”ለስሙዋ ሙዳይ ሰፋች”ይባላል።የኢትዮጵያ ሕዝብ የምዝናናበት ፓርክ ይከፈትልኝ ሳይሆን የጠዬቀው በሰላም ወጥቼ የምገባበት፣በፈለኩት
የአገሬ መሬት ላይ ሰርቼና ንብረት አፍርቼ የምኖርበት፣ልጆቼ በሰላምና በደስታ የሚያድጉበት፣እርሃብና ድህነት ተወግዶ ስደት የሚቆምበት
ሥርዓት ይኑር ነው።በጎሳ ተዋረድ የቆመው ስርዓትና ክልል፣የዚያም መሳሪያ የሆነው አፋኙና ከፋፋዩ “ሕገመንግሥት” ይወገድልኝ ነው።አልፈናቀል፣የመኖሪያ ቤቴ በላዬ ላይ እየፈረሰ ቦታዬን አልነጠቅ፣በጎሳ ማንነቴ አልጠቃ፣ኢትዮጵያዊነቴ
ይከበርልኝ ነው ያለው። ይህንን ያላስከበረ መሪ የሰላም አባት ተብሎ መሸለሙ ለሰላም ስድብ ነው።የሰላምን ዋጋ ማሳጣት ነው።በአገር
ውስጥ ሰላም ሰፍኖ ለሕዝብ ካልጠቀመና ካልበጀ የጥቂቶች ሰላም ማግኘት ብቻውን ለሽልማትና ለሙገሳ
አያበቃም።ይህንን ያላካተተ የሰላም ሽልማት ከትንሽ ቤተሰብ ውስጥ ያለ መተሻሸትና መሞጋገስ ነው።የምዕራብ አገሮች መተሻሸት!
መሪዎቻችን ከማስመሰል ወደ መምሰል
ደረጃ ተሻግረው በኢትዮጵያ ሕዝብና በታሪክ የመከበርንና የመወደድን ጸጋ ያገኙ ዘንድ እመኝላቸዋለሁ።”ከባዳ የጎረሱት በሶ ይወጣል
ደም ጎርሶ” የሚባለው አባባልም እንዳይከሰትባቸው እርምጃቸውን በቅጡ እንዲያጤኑትና ለጊዜያዊ ውዳሴ እንዳይንበረከኩና እጅ እንዳይሰጡ
አደራ እላቸዋለሁ።
ኢትዮጵያ በሕዝቡዋ አንድነትና ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
አገሬ አዲስ
Posted Ethiopian Semay
No comments:
Post a Comment