Monday, November 11, 2019

ከ ቀሲስ አስተርአየ ፓትርያርክ፦የአኩስም ሊቀ ጳጳስ እና የደብረ ሊባኖስ እጨጌ አዲስ አበባ ኢትዮጵያጥቅም
ት 29 ቀን 2ሽ 11 ዓ/ም 
 ከ
 ቀሲስ አስተርአየ

ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ፦የአኩስም ሊቀ ጳጳስ እና የደብረ ሊባኖስ እጨጌ፦
         አዲስ አበባ 
      ኢትዮጵያ

ብጹዕ ወቅዱስ ሆይ!  

ቋሚ ሰው ለሞተ ወገኑ “በረደህ ላልብስህ፡ ዘቀዘቀህ ላንተርስህ፤ ራበህ ላጉርስህ፤  አይልም። የሚሰጠው እንባ ብቻ ነው። በመንበረዎ ተቀምጠው በአረመኔወች ለታረዱ ልጆቼዎ የሰጧቸውን እንባ ተመለከትኩ።  

 ከቅኔው ቆጠራ ብንን ብየ ራቡ ሲሰማኝ፤ ከደጃፍ ቁሜ በእንተ ስማ ለማርያም ስል ድምጼን ሰምታ ደረቷን እየደቃች እኔን ይራበኝ እያለች ከልጆቿ ሳትለይ ያስተማረችኝ ርኅሪት እናት መታረዷን ስሰማ፤ ከመንደር እስክወጣ ድረስ ተናካሽ ውሻውን እየተከላከለልኝ “ተሜ አይዞህ በርትተህ ተማር” እያለ ያስተማረኝ አባ ወራ ጭንቀቱን መከራውን  ከባህር ማዶ ሆኜ ስሰማ እኔም ቅዱስነተዎ ያነቡትን እንባ ተጋራሁ።

ለቅዱስነተዎ  አላቃሽም አነጋጋሪም አጽናኝም ብጹአን አቡኖች በአካባቢዎ  አሉሉዎ። ከውቅያኖስ ማዶ ላለሁት ለኔ ግን በደስታም ሆነ ይህን በመሰለ አሰቃቂ ዘመን በመጻህፍቶቻቸው አማካይነት የከበቡኝ አማካሪወቼና የሚያጽናኑኝ እነ ቅዱስ ጳውሎስ፤ እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፤ እነ ቅዱስ ቄርሎስና በዝክረ ሊቃውንት መጽሐፋቸው እነ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ብቻ ናቸው።

ባሁኑ ጊዜ ብትኖሩ ምን ትሉ፡ ምንስ ታደረጉ ነበርብየ ከላይ የጠቀስኳቸውን አባቶች በመጻሕፍቶቻቸው አማካይነት ጠየኩ።  ከሰፊው ምክራቸው  የመረዳት አቅሜ የፈቀደለኝን ጨልፌ ከዚህ በታች እገልጻለሁ።

ቅዱስ ጳውሎስ ፋታ ሳይሰጥ የቀጠለውን መከራ “ወኢረከብነ ወኢአሐተኒ ዕረፍተ ለነፍስነ ወበኩሉ አኅመመነ በአፍአኒ ቀትል ወበውስጥኒ ፍርሀት“ 2 ቆሮ 7፦5 እያለ ከዘረዘረ በኋላ፤ መልእክቱን እንዲጽፍ የተገደደበት ምክንያት ”ወዘኒ ዘጸሀፍኩ ለክሙ አኮ በእንተ ዘገፍአ ወዘተገፍአ ዳእሙ ከመ ይትዐወቅ  ከመ ጽህቅሙ በእብቲአነ በቅድመ እግዚአብሔር”2ኛ ቆሮ 7፡12ማለትም፦ይህችን ጦማር የጻፍኳት ስለ በዳይና ተበዳይ ለመናገር አይደለም። የደረሰው መከራ ያስከተለው ጭንቀት ነው“ እያለ የተሰማውን እንደገለጸ፤   እኔም የቅዱስነተዎን እንባ እንዲፈስ ያደረገውን  ዘግናኝ መከራ በዚህች ልፋፍ አማካይነት እንድጋራ ወገንነቴና ባብነቱ ትምህርት ያሳለፍኩት ትዝታየ አሰገደደኝ።     

ችግሩን ፈጥሮ አሸካሚም ተሸካሚውም ሰው ነው፤ የችግሩ ፈችም ከእግዚአብሔር በታች ከቅዱስነተዎ ጀምሮ በተገቢው ቦታ የተሰለፈው ሰው ነው።  ይልቁንም ”የዘመድ ቄስ እየፈታ ያለቅስ“ እንዲሉ ባእዳን ቄሶች ካልሆን በቀር፤   ችግር ፈች ነኝ እያለ በየጎጡ ተሰልፎ  ከሚንጫጫው ይልቅ፤ የችግር ፈችነቱ ኃላፊነት በእኛ በቄሶች ላይ እጅግ ይከብዳል። ከሁሉም በላይ ደግሞ  “ከመ ንፍታህ ዘኢይትፈታህ” የሚለውን በጥልቅ ተገንዝቦ በመንበረ ፓትርያርካችን ላይ በተቀመጠ እንደ ቅዱስነተዎ ባለው ላይ እጅግ በጣም በጣም በጣ ይከብዳል።  

ሰው የደረሰበትን መከራና ችግር ለመግለጽ ቃል ሲያጥረው ሊያደርገው የሚችለው እንባ ማፍሰስና መቃተት ብቻ ነው። በዚህ መዛኝና አስተዛዛቢ ፈተና ልናደርገው የሚገባንን  በቤተ ክርስቲያናችን ቋንቋና ብሂል ለመግለጽ ስቃትት፤ ምናልባት በዳህጸ ልሳንም ሆነ፤ በዳህጸ ብእር ለቅድስናዎ የማይመጥን ቃል ቢገኝ ይቅርታ እየጠየኩ፤ ቅዱስነትዎ ያለብዎትን ግዴታና ሀላፊነት፤ እኛም ካህናት ነን የምንል መንፈሳውያን ልጆቸዎ በያለንበት አሁን ማድረግ የሚገባንን በየአንቀጹ ለመግለጽ እሞክራለሁ።  

                         የተፈጸመው ችግር
አሁን በህዝባችንና በቤተ ክርስቲያናችን የሚፈጸመው አረማዊ ጭፍጨፋና የነዋየ ቅድሳት ቃጠሎ በቀዳማዊው ኢህአዲግ ዘመን በአገር ውስጥና በሊብያ ከተፈጸመው ግድያና ስደት እጅግ የባሰ፤  አገራችን ልትሸከመው ካቋሟ በለይ የሆነ መከራ ነው።

ዓለምንም እጅግ ከማስጨነቁ የተነሳ የሮማ ካቶሊክን ፖፕ ፍራንስስን ካሉበት መንበር ላይ ሆነው የዋይታ  ድምጻቸውን ለዓለም እንዲያሰሙ አስገደዳቸው። 

" መንግስቱ በፍርድ ቤት የታሰረ ሰውን ጨለማ ቤት አስቀምጡ፣ ግረፉ ይላል እንዴ? አይልም። መግረፍ ጨለማ ቤት ማስቀመጥና አካል ማጉደል የኛ የኢህዲግ አሸባሪነት ተግባር ነው" በማለት የተናገሩትጠቅላይ ምስንስቴር ዓቢይ፤   ራሳቸው በጉያቸው ታቅፈው የያዙት ሰው፤ ተመልካቹን ያሳዘነ መከራ በህዝባቸው ሊፈጽም፤ በሌላ ሰውና በሌላ አገር ህዝብ ላይ ይፈጸማል ብለን አላሰብንም ነበር።

ራሳቸው ጠቅላይ ምንስተሩ “መግረፍ ጨለማ ቤት ማስቀመጥና አካል ማጉደል የኛ የኢሀዲግ አሸባሪነት ተግባር ነው" ብለው ከገለጹት በላይ ጨለማ ቤት ማስቀመና አካል ማጉደሉ እጅግ እየባሰና እየከፋ ሄዶ፤ የኛን ሰውነት ብቻ ሳይሆን የደቂቀ አዳምን ሰውነት በመናጥ ላይ ነው። “ለእመ ሀልቀ ሰብእ ሱዑ ሰብአ” ማለትም፦ የምትሰዋው እንስሳ ቢያልቅብህ ሰው ሰዋ” በሚል በአረማዊ አምልኮና መርሖ የሚመራው የነጁዋር መሀመድ ቡድን አገራችን ውስጥ ሰርጎ በመግባት ወገኖቻችንን እያረደ ህንጻ ቤተ ክርስቲያንን ሲያቃጥል ከማየት ምን የከፋና ዘግናኝ ክፉ ነገር በዚህ ምድር ይኖራል?

ጠቅላይ ምኒስተር ዓቢይ ይህን ትእዛዝ የሰጠውን አረመኔ ቡድን ለህግ ያቀረቡልናል ብለን ስንጠብቅ፤ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ” እያሉ ከተናገሩት ጋራ የሚቃረን። ይልቁንም “መግረፍ ጨለማ ቤት ማስቀመጥና አካል ማጉደል የየአህዲግ የአሸባሪነት ተግባር ነው” ብለው የተናገሩትን የራሳቸው መንግሥት እጅግ አልቆና አግዝፎ በተግባር እያሳየን ነው።  

ህዝባችን ኢትዮጵያዊ ሆኖ የኖረው ኑሮ ተክዶበት፤  “አገር ናት” ብለው የገለጿት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ተክዳ በመቃጠል ላይ ሳለች፤  ግድያውንና መቃጠሉን  አደበስብሰው፤ የገዳዩንና የተገዳዩን ቁጥር በማይታመንና በማይመጥን ቀመር  አካክሰውና አወራርደው አቀረቡልን። ገዳይንም ተገዳይንም ደርበው በመክሰስ ለተፈጸመው በደል ተጠያቂ አልባ በማድረጋቸው የአመራራቸውን ብቃት ከጥያቄ ላይ ጥሎታል።  

  ሳያፍር ሳይፈራ አረመኔአዊ ትእዛዝ እየሰጠ ይህን ሕዝብ አስጨፍጫፊ ግለሰብ፤ በክብር ጠባቂ ዘበኛ እያሳጀቡ፤ በመንግሥታቸው ጉያ አቅፈው ይዘው ከተከሳሽነትንና ከተወቃሽነት ነጻ ባደረገው ንግግራቸው በደሉንና ተጠያቂነቱን በራሳቸው መንግሥት ላይ ጭነውታል።  

“በትረ ጽድቅ ወበትረ መንግስትከ አፍቀርከ ጽድቀ ወአመጻ ጸላእከ” የሚለውን ሊቃውንት አበው አባቶቻችን ተርጉመው እንዳስተማሩን፤ ትክክለኛ መንግስት እውነትን የሚወድ ሸፍጥ የሚጠላ ነው። የአንድ አገር መንግሥት በዘመኑ የተከሰተውን ሁሉ በጽድቅ ሚዛን እየፈተሸ ህዝቡን ያለ አድለዎ ማገልገል ይጠበቅበት ነበር። ይሁን እንጅ ጠቅላይ ምንስቴር ዓቢይ የመንግሥትነትን ሀላፊነት ለመወጣት ከመጣር ይልቅ፤” 50 ኦሮሞ 20 አማራ 10 ጉራጌ 2 ስልጤ 1 ማንነቱ ያልታወቀ እያሉ የተናገሩት ነገረ ዘርቅ ”አህያየን የሰረቃት ሌባ የአህያየ አፈለላጊ ሲሆን አህያየን እንዴት ላገኛት እችላለሁ“ የሚለውን የባላገሩን የትዝብትና የነቀፋ ንግግር እንደ ዘውድ በራሳቸው ላይ ደፋባቸው።

የተናገሩትን ስላቅ ሰምቼ በዙሪያቸው ያሉት ሰዎች በህዝባችን ላይ የሚፈጽሙትን ዘግናኝ ያረመኔ ተግባር ስመለከት  ነቢዩ ኤርምያስን “አሳዳጆቻችን ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣኖች ሆኑ። በተራሮች ላይ አሳደዱን በምድረበዳ ሸመቁብን”ሰቆ 4፡19እያለ እንዲጮህ ካስገደደው ሰቆቃ ባልይ ሆነብኝ።

”ነፍስ መግደልን ተንኮልን ክፉ ጠባይን የተሞሉ፡ የሚያንገላቱ ምህረት ፍቅር የሌላቸው ውል የሚያፈርሱ የማያስተውሉ እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ህግ እያወቁ እነዚህን ሁሉ ክፉ ተግባሮች ፡ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሚያደርጉትን ያበረታታሉ” ሮሜ 1፡30የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ ምስክርነት ተፈጻሚነት ያገኘ መሰለኝ ።

በቀዳማዊው ኢህአዲግ ዘመን የተፈጸመውን ግፍና በደል አሁን ከሚፈጸመው ጋራ ሳነጻጽረው፤ ኢትዮጵያ ገብቶ  በሜንጫና ገጀራ ቁረጡ ብሎ ያስተላለፈው የአረመኔው ጁዋር ተግባር ሊብያ ላይ በወገኖቻችን አይሲስ ከፈጸመው ተግባር እጅግ ይልቅ ከፋ ሆነ።

ኢትዮጵያ ያለፈችበት የ27ን የመከራ ዘመን ሳስበው፤  እራሳቸው ጠቅላይ ምንስቴር ዓቢይ በህዝብ ደህንነት ተሰልፈው ከሰማይ ንስር ይልቅ ፈጣን በመሆን ለአቶ መለሰ አገልጋይ በሆኑባት ቅጽበት እንደ ጀመረ ተገነዘብኩ።  ራሳቸው ፈጣሪ የሚሉት እግዚአብሐር መውጫውን ይስጣቸው ብየ ትኩረቴን በዚህ ዘመን ወዳለነው ካህናት አዞራለሁ።  

እኛ በዚህ ዘመን የምንገኝ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳውያን መሪወች በዘመናችን እንደምናያቸው እንዳንድ ሰርጎ ገቦች በደመቀበት ጎራ የምንሰለፍ ጥቅም አሳዳጆች ካልሆን በቀር በሰላሙ ጊዜ “ከመ ናእምር ወንለቡ ወንጠይቅ መጠነ ትምህርትከ  ቅድስት ዘተነበት በላዕሌነ ይእዜኒ እምኀቤሁ። በከመ ተመሰለ ብከ ኦ ርእሰ ሕይወት ከማሁ ለነኒ ረስየነ ድልዋነ ንትመሰል ኪያሁ” (ስርአተ ቅዳሴ) እያልን የምናነበውን መተግበር ይኖርብን  ነበር። ማለትም፦ ርእሰ ህይወት የሆንከን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ቅዱስ ጳውሎስ አንተን እንደመሰለና፤ በመከራ ጊዜ ህዝቡን በእግዚአብሂር  እመኑ ማለት ብቻ ሳይሆን፤ ከህዝቤ በፊት የመከራውን ገፈት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ” እንዳለ፤ እኛም እንደሱ በህዝብ ላይ የመጣ መከራ ህዝቡን ሲጨርሰው ከማየት ከህዝብ በፊት ለመሞት የበቃን አድርገን ማለት ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ የራሱን ሀዋርያዊ ድርሻ እየገለጸ ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉት ላይ የሚሰነዘርወን ነቀፋ እየገታ “ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉ ሰወች ላይ መፍረድ ምን አግዶኝ፤ እግዚአብሔር ይፍረድ። እናንተስ በውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ፍረዱ”  (1ቆሮ 5፡12አለ። እኛም እሱን ምሳሌ በማድረግ፤ ለጥፋት የተሰማሩትን እነጀዋርን የፈጠራቸው አምላክ ከአውሬነት ወደ ሰውነት ይመልስላቸው እያልን፤ ትኩረታችንን ወደ ራሳችን ቤት በመመለስ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ካህናት ያለብንን ግዴታና ሀላፊነት ለመግለጽ እሞክራለሁ።

የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት በዚህ ወቅት ያለብን ግዴታና ሀላፊነት

ቤተ ክርስቲያናችን የክርስቶስ መልእክተኛ ስለሆነች ያለባት ሀላፊነት ሰማያዊና ምድራዊ ነው። ለሰማያዊውና ለምድራው ህግጋት ትጠነቀቃለች። በበለጠና በጠለቀ ትኩረትና ጥንቃቄ ቅድሚያ የምትሰጠው ግን ለሰማያዊው ህግ ነው። ይህ ሰማያዊው ህግ ነቢዩ ኤርምያስ እግዚአብሄር ጽድቃችን ነው ብሎ የተናገረው ነው  (ኤር 23፡6) ።

ቤተ ክርስቲያን በምድር እስካለች ድረስ የምድሩን ህገ መንግሥት እያከበረች እንዲከበር ታስተምራለች። ይሁን እንጅ ከሁሉም ይልቅ ጽድቅን እንድታስቀድም በጌታዋ በክርስቶስ ታዝዛለች። ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያን ከምንግሥት ይልቅ እጽፍ ድርብ ሰማያዊና ምድራዊ ሀላፊነት አለባት ማለት ነው።

ይህን እጽፍ ድርብ ስርአት ራሱ ክርስቶስ ስላደረገው፤ ቤተ ክርስቲያንም እንድትከተለው እነ ቅዱስ ቄርሎስ “ንህነሰ ንተሉ ሥርአተ ወህገ ከመ ክርስቶስ አምሳሊነ እንዘ አምላክ ውእቱ ናሁ ኮነ ስብአ ወኢወጽአ ግሙራ እምስብሀተ መለኮቱ ። ወለእመኒ ኮነ ውስተ ክፍል እምነ ፍጡራን ውእቱሰ ይትሌዐል ላዕለ ኩሉ ፍጥረታት። እንዘ ሐጋጌ ሕግ በመለኮቱ ናሁ ኮነ መትሕተ ሕግ ወነበረ በዘቦቱ ሐገገ ” (ቄርሎስ ሃ. ም .70፡ቁ 4) እያሉ አስተምረዋል።

ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ በጥምቀቱ ላወጃት ጽድቅ የበለጠ ትኩረት እየሰጠች፤ እግዚአብሔር ፍጥረቱን ሁሉ ቢወድም  የሚያተኩርበት ተቀዳሚ ነገሩ በአርያው የፈጠረው ሰው እንደሆነ ታስተምራለች። ለመለኮት ከሰው የበለጠና የላቀ ቁም ነገር የለውም። በኦርቶዶክስ ስነ መለኮት ትምህርት ትእግስት  ትልቅ ቦታ ቢኖራትም፤ የእግዚአብሄር ቁም ነገሩ ሰው ሲሻር ሲደመሰስ ትእግስት ወደ ቁጣ ትለወጣለች።   

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን ተልእኮ ፤ ክርስቶስ ባወጀው ጽድቅ እየተመራን ከጽድቅ ወደ ኋላ የቀረውን ወደ ጽድቅ ለማድረስ ሳናሰልስ እንድንታገል ክናናለች። ይህች ጽድቅ የምትባለው የክርስቶስ መመሪያ  ከሰማይ በታች ከተዘረጉት በዓለም ካሉት ሁሉ በላይ እጅግ የተለየች እና የላቀች ናት። መሪወቻችንን ቅዱሳንና ብጹዓን እያልን እንድንጠራቸው ያስተማረችንም ብጽዕናቸውና ቅድስናቸው ከዚህች ክርስቶሳዊት ጽድቅ ጋራ ከሁላችን በላቀና በጠለቀ ሁኔታ የተጣበቁ ናቸው ብላ ነው። እነሱም በዚህ ስም ስንጠራቸው ደፍረው ወይ የሚሉን ከሁላችንም እጅግ በላቀ ሁኔታ ከዚህች ጽድቅ ጋራ የተጣበቁ መሆናቸውን እያረጋገጡ ነው።

እንኴን ብጹአንና ቅዱሳን  የሚባሉ አቡኖቻችን፤ በዚህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ክህነታዊ ንክኪ ያለንና በጥምቀት የተባበረን ሁሉ በክርስቶስ የምንመራ የዚህች ክርስቶሳዊት ህግ ( ጽድቅ) ተሳታፊወች ነን። በምግባራችን ቅድስና ከምድራዊ ህግ ክስና ወቀሳ በላይ ሆነን፤ ዛሬ በቅድስት ኢትዮጵያ አገራችን የተከሰቱትን አረማውያን ካሉበት ህገ አረሚ ተላቀው፤ የዚህ ጽድቅ ተሳታፊ እንዲሆኑ ልናደርጋቸው በተገባ ነበር።  

እኛ ካህናት በቤተ ክርስቲያናችን ነገረ መለኮት ሀተታ በብዙ ምሳሌዎች የምንገለጽ ነበርን። ከብዙ ምሳሌወች ሁለቱን ዓይንነትንና ቀንድነትን ብቻ  ባጭር ባጭሩ ለመግለጽ እሞክራለሁ።
ሊመጣ ያለውን መከራ አስቀድመን አይተን በመንፈሰ ትንቢት  ህዝባችንን እናስጠነቅቅ ዘንድ፤   አዕይንተ እግዚአብሔር ተብለን ነበር።  አዕይንተ እግዚአብሔርን ትርጉም ሳንረዳ፤ ቃሉ ሲባል ሲነገር ስለሰማን ብቻ፤  ሳንሆንና ሳንበቃ አማናውያን የእግዚአብሄር ዓይኖች በመምሰል በየአውደ ምህረቱ እርስ በርሳችን ስንሞካከሽበት የሚመለከተን ህዝብ እየታዘበን ነው።  የሚመጣውን መከራ ከህዝብ በፊት አስቀድመን አይተን ለህዝብ ልናካፍል ይቅርና፤ ህዝብ በመከራው እሳት እየተለበለበ ሳለ  “ሰማይ ስሚ ምድርም አድምጭ፤ መሰረቶችሽም ይንቀጥቀጡ” እያለን ቤተ ክርስቲያናችንን በሚመጥናት ብሶቱን ለፈጣሪና ለተፈጥሮ ማሰማት አቃተን።

በመጽሐፈ ቅዳሴያችን እንደምናነበው፤ ክርስቶስ በመሰቀል ላይ በነበረበት ቀውጢ ሰአት፦“ገአረ ኢየሱስ በህማሙ ወጸርሀ ኀበ አቡሁ። ወእንዘ ሀሎ ህየ ጸርሀ ኀበ አዳም ገብሩ ወኀበ ኩሎሙ ደቂቁ”(205-6)። ድምጹን ለሰማያዊ አባቱ ለእግዚአብሔር አሰማ።  በዚያው ቅጽበትም በመሬት ላለው ለደቂቀ አዳም አሰማ።

ቤተ ክርስቲያናችንም ወደ እግዚአብሄር “ፍታህ ሊተ እግዚኦ ወተበቀል በቀልየ” እያለች መጮኋዋን ሳታቌርጥ፤  “ንዑ ትርአዩ ዘንተ ቅስፈተ እለ ትሳተፉ ሕማመ ቢጽክሙ ወእለ ትትዌከፉ ሕማመ ፍቁራኒክሙ” 275 ቁ 40። እያለች ማለትም፦ “በዓለም ያለህ ደቂቀ ዓዳም ሆይ!  በኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ላይ የሚደርሰውን መታረድ መገረፍ መቃጥል መሰደድ መገረፍ መሰቃየት ተመልከት” እያለች እነ ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪን የጀመሩትን ክስ ማጠናከር አለባት።

ህዝቧን ጨካኝ አረመኔ  እንደበግና እንደ ፍየል ሲያርድ በማየታችን ልንገታውና ልንውጠው የማንችለው እንባችን ቢፈስ፤ ማንም አልፎ ሀጅ የሚያደርገው የተፈጥሮ ጠባይ ነውና  ቅዱስ ጳውሎስ “ኢከውነኒ ምዝጋና” ካለው የተለየ አይሆንም። 

ልጆቿና ባሏ ከፊቷ ታርደውባት፤ ቤቷ ተቃጥሎባት ከአመድ ላይ ቁጭ ብላ  እንደ ምታለቅስ እናት፤ እናቱን አባቱን ወንድሙን እህቱን አጥቶ ቀኑ ጨልሞበት እንደ ሚያለቅስ ህጻን ልጅ ቁጭ ብለን ማልቀስ ፈጽሞ አይመጥነንም።  የናቶችን እና የህጻናቱ ድርሻ የሆነውን ቁጭ ብሎ ማልቀስ እኛ ከወሰድነው ክህነቱ የሚጠይቀንን ተልእኮ ለማን ልንሰጠው እንችላለን? የቤተ ክርስቲያናችንን ሰማያዊና ምድራዊ ተልእኮ በአግባቡ ያልተረዱ ወገኖች ፓትርያርኩ በመንበራቸው ላይ ቁጭ ብለው አለቀሱ እያሉ የናቶችንና የህጻናቱን ድርሻ ለኛ እየሰጡ በየሚዲያው የሚለቁትን ስመለከት ከተልእኴችን በታች ያወረዱን መሰለኝ። “ብክይዎ ወላህውዎ እለ ታፈቀርዎ” እንዲል ለምንወደውና ለምናፈቅረው ሰው ማልቀስ ሰባዊ ባህርያችን ቢያስገድደንም፤ በተረጋጋ መንፈስ ተጽናንተን ችግሩን ለመወጣት መንገድ የሚያሳይ ባለመሆኑ ለኦርቶዶክስ ልጆች አንገታችንን እንድንደፋ አድርጎናል። ቁጭ ብሎ ማልቀስ የእግዚሀብሔር አይንነታችን ከማጥፋት ሌላ ትርፍ የለውምና።

ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታና ህዝባችን እንዴት እንደታዘበን ተረደተን፤ እራሳችንን እንድንታዘብ ይረዳን ዘንድ ከምንገለጽባቸው ብዙ ምሳሌወች ሁለቱን ብቻ እንድንቃኛቸው እፈልጋለሁ። እነዚህ ምሳሌወች ቀንድነትና ዓይንነት ናቸው።

ቀንድ ለቅዱሳን ከብቶች መከላክያቸውና ኃይላቸው ነው።  እግዚአብሄር ለሙሴ “ኢይፈቅድ ትኩን ዘነመ አላ ርእሰ”ዘዳ 28፡44) እንዳለው እኛ ካህናት ለህዝባችን ተከላካይ ቀንዶች ነበርን። ይልቁንም አቡኖች።

  የቀንድነታችን ቀንድ ደግሞ ፓትርያርካችን ነበሩ። አሁን በዚህ ዘመን ያለን ካህናት ግን ቀንድ ልንሆን ይቅርና ከአካሉ ተቆርጦ የወደቀ ጅራት እንጅ በአካል ላይ ያለ ጅራት እንኳ መሆን አልተቻለም።  

ስለቀደሙ አባቶቻችን ቀንድነት ብዙሰዎ ጽፈዋል።ከብዙወቹ አንዱ Iris Habib el Masri የተባሉ የታሪክ መዝጋቢ “The sheep of Ethiopia have been delivered from the hyenas of the west by the doctrines of st. Cyril the great” (The story of the copts page 262) ብለው እንደመሰከሩት፤ የቀደሙ አባቶቻችን ቀንድነታቸው የሚደነቅ ነበር።

ቴወዶስዮስ የሚባለው ሊቅ “ወንህነሂ ዓዲ ተወከፍነ ትምህርታቲሁ ቅድስተ ዘዝኩ ቀርን መንፈሳዊ ቅዱስ ቄርሎስ”ሃ አ ም 83፡ 33እያለ ከገለጸው ከቅዱስ ቄርሎስና ከቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቀንድነት ይልቅ እጅግ ኃያል ተከላካይ ነበር።

በዚህ ዘመን ያለን እኛ ግን “የደከሙትን እጆች አበርቱ የላሉትንም ጉልበቶች አጽኑ ። ፈሪ ልብ ላላቸው እነሆ አምላካችሁ በበቀል ብድራትን ለመክፈል መጥቶ ያድናችኋልና በርቱ አትፍሩኢሳ 35፡4ለማለት እንኴ ተስኖን እነ እስክንድር ነጋ፤ እነ ተመስገን ደሳለኝ እና ሌሎችም የመሳሰሉት ቀደሙን።

ቀደሞ ይህን በመሰለ አስከፊ ፈተና ውስጥ ኢትዮጵያ ስትወድቅ ሊቃውንቱና ቀሳውስቱ  ይደማመጡ ነበር። አቡኖችም ከቀሳውስቱና ከሊቃውንቱ የሚሰሙትን ድምጽ ገሸሽ በማድረግ ተዘዝልለው አይቀመጡም ነበር። በመንበራቸው ቁጭ ብለው እንደ ሰላሙ ጊዜ “ወደፈተና አታግባን ” እያሉ መጸለያቸውን “ፈኑ እዴከ ወንአ አድህነነ” በሚለው  ተክተው፤  መነኮሳት ከገዳማቸው፤ ባህታውያን ከዋሻቸው፤ ቀሳውስ ከመቅደሶቻቸው እንዲወጡ አድርገው ጠላትን በግንባር ቀደም በመፋለም በህዝብ ላይ የሚደርሰውን የመከራ ገፈት ቀማሾች  ነበሩ።

ከህገ ኦሪት ገና ላልደረሱ አረማውያን ወደ ህገ ኦሪት እንዲደርሱ አሰርቱ ቃላት የተጻፉበትን ጽላት ተሸክመው ከቤተ መቅደስ በመውጣት ከውጭ የሚመጡትን ወራሪወች  ሲዋጉ ኖረው ነበር ። እኒህን የመሳሰሉ ቅዱሳን ቀንዶች የነበሯት ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ ሰው በላ አረመኔ  በቤተ መቅደሷ ሰተት ብሎ ገብቶ አካሏን እየጨፈጨፈ ነው።   

ከቀድሞው መከራ በከፋ መከራ ውስጥ በምትገኘው ቤተ ክርስቲያናችን ያለነው መንፈሳዊ ሰወች፤ የቀደሙ መንፈሳውያን አባቶች ካደረጉት ፍልሚያ የበለጠ መፋለም ሲጠበቅብን፤ ቁጭ ብለን ከማልቀስና በተለመደው ስብከታችን ህዝቡን ከማደንዘዝ በቀር የቀደሙ አባቶችንን መተካት አልቻልንም።  ቤተ ክርስቲያናችን  በምድራዊና በሰማያዊ ህግጋት አንጻር ያላትን አቋም ልንገልጽላት አቅም አልባ ሆነን ተገኘን።  

በሕግ አንጻር የቤተ ክርስቲያናችን አቋም

የአብነቱ መምህራን አባቶቻችን ባንድምታው እንዳስተማሩን፤ ያንድ አገር መንግሥት እራሱ በህዝቡ ላይ በሚፈጽመው በደልና ጭቆና ራሱን አይክሰስ እንጅ፤  እያወቀም  ሆነ ሳያውቅ በመንግሥቱ ከለላ ያሉትን ወገኖች የሚያስደበድብ የሚያስፈጅ ከሆነ፤ ቤተ ክርስቲያናችን በመበደል ያለውን ወገኗን ወክላ “በህግ ልትፈርድ በመንበር ላይ ተቀምጠህ ሳለህ ያለ ህግ ስላስመታኀኝ የተለሰንክ ግድግዳ ነህ”የሐዋ 23፡3ብላ መንግሥትን የመፋለም መብት አላት። ግዴታም አለባት።

ክፉ የሚሰሩትን ሰዎች የሚፈራና በክፉ አድራጊዎች የተናቀ መንግሥት በኢትዮጵያ መኖር እንደሌለበት ቤተ ክርስቲያናችን በድፍረት ባትናገር ያመራር ችግር ገጥሟታል ማለት ነው  (ሮሜ 13፡3። በደካማ መንግሥት ንዝህላልነትም ሆነ በሸረኝነት በመታረድ ላይ ያለውን ወገኗን ቤተ ክርስቲያናችን ወክላ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ”ሞት የሚገባውን ነገር አድርጌ ከሆነ ከሞት ልዳን አልልም” (የሐዋ 25፡11እያለች ድምጿን ከፍ አድርጋ መናገር አለባት።

ቅዱስ ጳውሎስ “የቀረበብኝ ክስ  ከንቱ እንደሆነ እየታወቀ ለገዳዮች አሳልፎ ይሰጠኝ ዘንድ ማንም አይችልም” ብሎ  ወደ ቄሣር ይግባኝ ብያለሁ እንዳለ፤ ጠቅላይ ምንስቴር ዓቢይ በደል የፈጸመውን ጁዋርን ወደ ህግ ለማቅረብ ባንድም ሆነ በብዙ ምክንያት ከፈሩ ወይም አቅም ካነሳቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ይግባኝ እንድትል የህግ ምሁሩ የቅዱስ ጳውሎስ መርሆ በምሳሌነቱ ያስገድዳታል።

ጠቅላይ ምንስቴር ዓቢይ ጁዋርን በህግ ፊት ማቅረብ ሲገባቸው፤ የተፈጸመውን  ወንጀል አደበስብሰው፤ የገዳዩንና የተገዳዩ ቁጥር በማይታመንና በማይመጥን ቀመር  አካክሰውና አወራርደው በማቅረባቸው፤ ለተፈጸመው በደል ተጠያቂ አልባ አድርገውታል።  ገዳይንም ተገዳይንም ደርበው በመክሰሳቸው የተፈጸመውን በደል ተጠያቂ አልባ ከማድረጋቸው ባሻገር፤  በህዝብና በህግ ላይ  እጽድርብ ደባ ፈጽመዋል ብላ ቤተ ክርስቲያን ያላንዳች ማቅማማት የመገሰጽና የመክሰስ መብቷን ልትጠቀም ይገባታል።

ጠቅላይ ምንስቴሩ በመንግስታቸው ሰወች መገደላቸውን መስክረዋል፤ ተገዳይ እንዳለ ካመኑ ገዳይና አስገዳይ እንዳለ ግልጽ ነው። የፈሰሰው ንጹህ ደም ያለፍርድ ተደብስብሶ ቢታለፍ፤ የበለጠ መቅሰፍት አስከትሎ  በህዝብ ደም ኢትዮጵያ ከዳር እስከዳር አኬልዳማ ከመሆኗ በፊት፤ ቤተ ክርስቲያን  ጽፋ ባስቀመጠችው ሕጓ የጠቅላይ ምንስቴር ዓቢይን መንግስት እፋረድሀለሁ እያለች የመፋለም እጽፍ ድርብ ሀላፊነት አለባት።  

  በፍትሐ ነገሥቷ “ወለዘሂ አገበርወ ከመ ይቅትል ለእመ ኮነ ዘአገበሮ መኮንን ውእቱ ላዕለ አልቦ ዕዳ በላዕሌሁ። ወለእመ ኮነ ካልእ አዛዚ ሥሉጠ ላእለ ተአዛዚ ይደሉ ኩነኔሁ ላዕለ አዛዚሁ። ወእመሰ ኢኮነ ሥሉጠ በላዕሌሁ ወኢይፈርህ እምኔሁ ይደሉ ከነኔሁ ላእለ ተአዛዚ”(አንቀጽ 47፡ 1ሽ678) የሚል አንቀጽ አለ። ይህም ማለት፦ “አንድ ሰው በሌላ ሰው ተገፍቶ ሰው  ቢገድልና ተገፋፍቶ የሚፈጽመው ግድያ የሚያስከትለውን ፍርድ የመገመት አቅሙ ከገፋፋው ሰው እውቀት በታች ከሆነ  ግድያውን ያስፈጸመው አካል ፍርዱን ይቀበላል። ነገር ግን ገዳዩ  የሚያስከተልውን ፍርድ ለመገመት የእውቀት አቅሙ  እንዲገድል ካዘዘው በላይ  ከሆነ ራሱ ገዳዩ ፍርዱን ይቀበላል” ይላል።

ሕጔን ከዓለሙ ህግ ጋራ አቆራኝተውና አጣጥመው በህዝቧና በነዋየ ቅድስቷ ላይ የደረሰውን ጥቃት ለዓለም ማቅረብ የሚችሉትን የህግ ሊቃውንት ልጇችን መሰብሰብና ሃይላቸውን አጠናክረው ከጎኗ እንዲሰለፉ ብታደርግ ከወቀሳና ከከሰሳ ያድናታል።  

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነብ ሁሉ ሊረዳው የሚችለው በሀዲስ ኪዳን ውስጥ ሌላም አንቀጽ አለ “ሞት የሚገባው በደል በፈጸመ ሰው ላይ፤ በአድልዎ ሞት ቢፈረደበት ቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ሆና እንድትፋለም ሃላፊነት እንዳለባት ሁሉ፤ ሞት የሚገባውን በደል በፈጸመ ሰው ላይ የሞት ፍርድ ተበይኖበት የክሱ ፋይል እንዲዘጋ በመንግሥት ላይ ተጽእኖ ታሳድራለች1ኛ ዮሐንስ 5፡16። በደለኛው በሕግ ስር ወድቆ ሞት ከተበየነበት በኋላ እንደሞተ ይገመታል። የሞቱ ፍርድ ተበይኖ የክሱ ፋይል ከተዘጋ በኋላ፤ በተበየነበት ሰው ላይ ሞቱ ተግባራዊ እንዳይሆን፤  ወደ ምህረት እንዲለወጥ ቤተ ክርስቲያናችን ለምህረት የመታገል ግዴታ አለባት።

ጠቅላይ ምንስቴር ዓቢይም፡ ፍትህን ለመደበቅ በውስጣቸው የሸመቀ ሸፍጥ ከሌለባቸው፤ በአገራችን የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አቻ ላቻ አድርገው የደም ድምጽ ክስ እንዲቀጥል ከማድረግ ትልቅ ፤ ራሳቸው “ስንሳሳት ገስጹን” እንዳሉ ስህተታቸውን ተገንዝበው፤ ቤተ ክርስቲያናችን ፍትህ እንዲፈጸም በምታደርገው ጥረት ቢተባበሩ ለራሳቸው መንግሥት ቢጠቅም እንጅ የሚጎዳ አይደለም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት በያለንበት አሁን ማድረግ የሚገባን

የድሮ አባቶች ይህን የመሰለ መከራ ሲገጥማቸው እንዴት ተሻገሩት ብለን ታሪካቸውን ስንቃኘው በሰላሙ ጊዜ ቆመውም ተቀምጠውም ተኝተውም “ወደፈተና አታግባን” የሚለውን ቁጭ ብለው እያለቅሱ እንዳላሳለፉት መረዳት እንችላለን።   በፈተናው ከገቡ በኋላ የመለያየትን የጸብ ግድግዳ ለማፈረስ ክርስቶስ ኃይሉን የገለጸበትን በልባቸው የተሳለውን የመስቀል አርማ በእጃቸው ጨብጠው “እለ ይትመነደቡ ታድህን፤ ወለእለ በመዋቅህት ጽኑአን ዘምስሌሆሙ ትሄሉ” የሚለውን ጸሎት ተግባራዊ ለማድረግ በሚገደሉትና በሚገድሉት ወገኖች መካከል በመገኘት እኛን ሳትገድሉና ሳታርዱ ህዝባችንን ልታርዱ አትችሉም በማለት ክህነታዊትና ወገናዊነት ሀላፊነታቸውን እየተወጡ  አለፉ።

ተፈትኖ ያለፈው ቅዱስ ዮሀንስ አፈወርቅ መንፈሳውያን መሪወች ፈተና ሲገጥማቸው በፍጹም እምነትና ቆራጥነት መከራውን እንዲጋፈጡ “እምከመ ወደቅን ውስተ ግበ ፍትወት ወነበርነ ውስተ ህማመ ጽልመት  ዘገብረ ዓለም።  ይደለወነ ናንቃዕዱ በዓቢይ ገአር፤. . .   ይደልወነ ናንስእ ህሊናነ ምስለ እደዊነ” (ተግሳጽ 22እያለ መከረ። ማለትም፦ ምርጫ በሌለው ፈተና ውስጥ ስንገባ በጨለማ ቤት ሲዘጋብን፤ ከተጻፈው ሳንወጣ ከገባንበት ፈተና ከተዘጋብን ጨለማ ለመላቀቅ ያለንን ሁሉ አቅም መጠቀም አለብን ማለት ነው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በአንጾኪያ ከተማ ሰዎች ላይ ግፈኞች ከጫኑባቸው መከራና ጭንቅ ለማላቀቅ መሪወችን እየተፋለመ የከተማውን ህዝብ አንቀሳቅሶ የፖለቲካ መሪወችን እንዳንበረከ፤ እኛም ይህን አብነት ተከትለን አረመኔወች በህዝባችን አንገት ላይ የሰነዘሩትን ሰይፍ ከእጃቸው ጥለው፤ ንስሀ ገብተው  በአርያው ለፈጠረው እግዚአብሄር እንዲበረከኩ በምናደርገው ጥረት፤ የዓለምም ህዝብ ይተባበረን ዘንድ ፖፕ ፍራንስስኮ ከዚህ ቀደም ያሰሙልንን ድምጽ እንዲቀጥሉ፤ ሌሎችም ተሰሚነት ያላቸው ሁሉ አካላት  እንዲተባበሩን ሳንታክት ጥሪያችንን ማሰማት አለብን።

በነገራችን ላይ ዮሐንስ “አፈወርቅ” የሚለውን ቅጽል በህዝብ የተጎናጸፈው ስለጻፈ። ወይም ንስሀ ግቡ እያለ ህዝቡን በሰበከበት ወቅት አልነበረም። የአንጾኪያ ህዝብ በግፍ አገዛዝ ተይዞ በተጨነቀበት ወቅት ህዝቡን እየመራ አስጨናቂወችን ስለተፋለመ ነበር።

ካቅም በላይ የሆነ ከባድ መከራ ሲመጣ ክንዶቻችን እንደሚዝሉ በሙሴ ከተከስተው ተገንዝበናል። ዓይኖችን ለመግለጽ ሽፋፍቶች እንደሚከብዱ ከሐዋርያትም ተረደትናል። በነሱ የደረሰው መጫጫን በኛም እንደሚደርስብን ተገንዝበን፤ የተጫጫነንና የከበደን ፈንቅለን በሚገደለው ንጹህ ህዝብና በሚገለው አረማዊ መካል የመቆም ግዴታ አለብን። በህዝብ ላይ ይህን የመሰለ አሰቃቂ መከራ እየተካሄደ ተዘልሎ መቀመጥ ትእግስትን አያሳይም።

ያዕቆብ ዘስሩግም ተዘልሎ ኖሮ መከራ አንዣቦ  ሲመጣ  ቁጭ ብለው ለሚያለቅሱ ሰወች የሚከተለውን ብሏል።  “አሜሃ ይከውን ኀዘን ዘኢይበቁዕ ኀዘን።  ይከውን ዘኢይበቁዕ ኀዘን፤ ይከውን  ዘኢይበቁዕ አውያት፤ ይከውን ዘኢይበቁዕ ገአር፤  ይከውን ዘኢይበቁዕ ብካይ፤ ወይውህዝ አንብእ ከመ ማየ ክረምት ዘአልቦ ማህለቅት” (ዘስሩግ ገጽ 356፡ ቁ96)። ይህም ማለት፦ ተዘልሎ ኖሮ መከራ ሲመጣ  ማዘን ምሾ ማውረድ ማልቀስ እንባ ማጉረፍ አይጠቅምም”

ቀድሞ በደረሰበት መከራ ሳይበገር መፋለሙን ያላቆመውም ቅዱስ ጳውሎስ “በድካም አብዝቼ በመገረፍ አብዝቼ በመታሰር አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንኩ። በብትር ተመታሁ በድንጋይ ተወገርኩ በወንዝ ፍርሀት  በወንበዴወች ፍርሀት በወገኔ በኩል በአህዛብ ፍርሀት በከተማ ፍርሀት በምድረ ፍርሀት በውሸተኞች ወንድሞች ፍርሀት ነበረብኝ በድካምና በጣር እንቅልፍ በማጣት  በራብና በጥም በእርዛት የደረሰብኝን ሳልቆጥር ለቤተ ክርስቲያን እጨነቃለሁ 2ኛ ቆሮ 11፡23᎗29እንዳለው  መታሰር መፈታት ሳይሰለቻቸው በየመንገዱና በየደረሱበት የሚገጥማቸውን ዛቻና ማስፈራራት እየተቋቋሙ አሁንም ለህዝባቸው በመጨነቅ ያሉትን  ምሳሌወች ያላሳጣን እግዚአብሄር ይባረክ።  

የግላቸውን ጥቅምና ክብር ጤንነትና ድሎት ሳይመርጡ “የፍትህ ያለህ” እያሉ የሚጮኹትንና፤ “የግድያው ጀማሪና ትእዛዝ ሰጭው ማን እንደሆነ ሳይገልጹ የሟቾች መንደር መጥቀሱ ከአስፈላጊነቱ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እየገለጹ፤ ለብሄሩ ለመንደሩ ብቻ የሚያስብና የሚያዘነብል የሚያዳላ ከአውሬ እንደማይሻል እየተናገሩ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በጠቅላይ ምንስቴሩ ብቻ መተማመን ጠቃሚ አይደለም ብለው የተናገሩትን ወገኖች በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰገን አላልፍም።

 እነዚህና የመሳሰሏቸው “እስከሞት የታመንክ ሁን” ብሎ ክርስቶስ የተናገረውን ለመፈጸም በያሉበት ሆነው የሚታገሉ ዓለም ያላወቃቸው ለኛ መፈራረጃ ያደረጋቸው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቃቸው ብዘዎች አሉን።   

የገጠመን ጠላት “ብእሲ አብድ ይጠፍዕ እዴሁ ወይትሀሰይ ለርእሱ እንዘ ይትሀበይ ሕቢተ ለዓርኩ፤ መፍቀሬ ጋእዝ ይትፌሳህ በባእስ ወጽኑዕ በቅፈተ ልብ ኢይዳደቅ ሠናየ” (ምሳሌ 17፡18  ማለትም፦ በኃጢአት ስካር ነፍዞ፤ በሚፈጽመው በደልና ግፍ ደምብዞ፤ በገደለው ሬሳ ላይ ቆሞ የሚያጨበጭብ እጅግ ጨካኝ አረመኔ ነው። ኃጢአት ባደነደነው  ልቡ እርሱ በርሱ እየተጔተተ ዋስና ምስክር እየሆነ በመደጋገፍ በግፍ ላይ ግፍ በበደል ላይ በደል በመፈጸም ላይ እስካሁን ባደረገው ተጸጽቶ የማይመለስ የኢትዮጵያን ህዝብ ጨርሶ የሚያጠፋ ነው።

የፈሰሰው ደም ያለፍርድ ተደብስብሶ ቢታለፍ፤ የበለጠ መቅሰፍት አስከትሎ በህዝብ ደም ከዳር እስከዳር ኢትዮጵያን አኬልዳማ ስለሚያደርጋት ለቤተ ክርስቲያን ያላት  አማራጭ ቁጭ ብላ በማልቀስ ብቻ ሳትወሰን፤ ድምጿን ከቤተ መቅደስ ውጭ አውጥታ ለአምላክና ለዓለም እያሰማች፤ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በነበረበት ቀውጢ ሰአት ያደረውን ማድረግ ይኖርብናል።

በመጽሐፈ ቅዳሴያችን እንደምናነበው፤ ፦“ገአረ ኢየሱስ በህማሙ ወጸርሀ ኀበ አቡሁ።  . . . .  “ወእንዘ ሀሎ ህየ ጸርሀ ኀበ አዳም ገብሩ ወኀበ ኩሎሙ ደቂቁ”(205-6)።  ድምጹን ለሰማያዊ አባቱ ለእግዚአብሔር አሰማ። በዚያው ቅጽበትም በመሬት ላለው ለደቂቀ አዳምም አሰማ። ቤተ ክርስቲያናችንም ወደ እግዚአብሔር የምታሰማውን ድምጽ ሳታቋርጥ በዓለም ላለው “ንዑ ትርአዩ ዘንተ ቅስፈተ እለ ትሳተፉ ሕማመ ቢጽክሙ ወእለ ትትዌከፉ ሕማመ ፍቁራኒክሙ” 275 ቁ 40። እያለች “በዓለም ያላችሁ ሰው የሆናችሁ ሁሉ፤ በኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ላይ የሚደርሰውን መታረድ መገረፍ መቃጠል መሰደድ መገረፍ መሰቃየት ኑና ተመልከቱ” እያለች  ዲያቆን ዮሴፍ በዴንቨር ከተማ ፤ ዶክተር መሀሪ በኢሮፕ ሆነው የጀመሩትን ክስ በግንባር ቀደም ልትመራው ይገባታል።

በውስጥም በውጭ ለተበተነው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ወገኗም እንደ ነቢዩ  ኢሳይያስ “የደከሙት  እጆች ይበርቱ የላሉትንም ጉልበቶች ይጽኑ ። ፈሪ ልብ ያላችሁም፤ አምላካችሁ በበቀል ብድራትን ለመክፈል መጥቶ ያድናችኋልና በርቱ አትፍሩ”ኢሳ 35፡4) እያለች መበርታትና ማጠነካከር  አለብን።

መሰብሰብን መነቃቃትንና መመካከርን አጥብቆ የሚጠይቅ ከዚህ ዘመን የከፋ ስለሌለ  እርስ በርሳችን እየተያየን እንድንቃቃ እንድንመካከር  በዓለም ለተበተን ልጆቿ መንፈሳውያን ካህናትም ከነ ዲያቆን ዮሴፍ ተፈሪ ጋራ እንድንሰበሰብ እንድንነቃቃ እንድንመካከር ቅዱስ ፓትርያርኩ ሊጎተጉተን ይገባል።

በዚህ ዘመን ያለን ካህናት ቤተ ክርስቲያናችን የገጠማትን ፈተና፤ ከክርስትናችን ጋራ ባልተጋጨ መንገድ ለመወጣት እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ከመፋለም ይልቅ፤ በየአጥቢያችን ተከልለን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣውን ህዝብ በሰላም ጊዜ እንደምናደርገው “ንስሀ ግቡ አልቅሱ” እያልን  መሸኘት በዚህ ወቅት ያለችው ቤተ ክርስቲያናችን የምትቀበለው አይደለም።

ዛሬ ቤተ ክርስቲያንች ከገባችበት ፈተና እንድትወጣ  የሚጠበቅብንን ሳንወጣ ይህ እድል ቢያመልጠን፤ የሰውነቱን ገበና የሚሸፍንበት አጥቶ ነጠላ የሚለምነውን ሰው፤  ነጠላ ሳይሰጥ ሂድ ልበስ ይሙቅህ፤ የሚጎርሰው አጥቶ የሚለምንንም ምንም ነገር ሳይሰጥ ሂድ ብላ ጥገብ ከሚል ግብዝ የተለየን ልንሆን አንችልም። ይህ ባህርይ ህዝበ ክርስቲያንን ከሚያርደውና ቤተ ክርስቲያን ከሚያቃጥለው አረመኔ የተለየ አለመሆኑን ቅዱስ ያዕቆብ “አንተ ግብዝ በተግባር የማይገለጥ እምነት ነፍስ የተለየችው በድን እንደሆነ አታውቅም?  (ያዕ 2፡16᎗20ብሎ ገልጾታል።

በተረፈ “ደምረነ ምስለ እለ ይድህኑ” አጥፍተው ከሚጠፉ ሸፍጠኞች ንክኪ ጠብቀህ፤  ራሳቸው ድነው ሌላውን ለማዳን ከሚጥሩት የእምነትና የተግባር ከሆኑት ወገኖች ጋራ ደምረን“  በሚለው በሊጦኑ ጸሎታችን ይህችን ጦማር እደመድማለሁ።

በዓለም ዙሪያ ከተበተኑት ከቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አእጹቅ ልጆቿ አንዱና ደካማው ልጇ ቀሲስ አስተርአየ
ትድረስ፦
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
ለኢፊድሪ ፕሬዝደንት ክብርት ሣሕለ ወርቅ ዘውዴ
ለኢፊድሪ ጠቅላይ ምኒስተር ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ
ለኢፊድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሊቃውንት ጉባዔ
ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራንና ተማሪወች
ለሰዋሰዎ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መምህራንና ተማሪወች
ለማህበረ ቅዱሳን ድርጅት ጽቤት
አዲስ አበባ
Saturday, November 9, 2019

ታላቅ ሕዝብ በታላቅ ተራራ ላይ ቆሜ ማመስገኔ የሚጠሉኝ ካሉ ለኢትዮጵያ እንግዶች ናቸው! ከጌታቸው ረዳ (Ethio Semay ኢትዮ ሰማይ)


ታላቅ ሕዝብ በታላቅ ተራራ ላይ ቆሜ  ማመስገኔ የሚጠሉኝ ካሉ ለኢትዮጵያ እንግዶች ናቸው! ከጌታቸው ረዳ (Ethio Semay ኢትዮ ሰማይ)
Amhara the guardian of Orthodox Christianity in Ethiopia
ከታች ያለው ቪዲዮ ተመለከቱ! ትግሬዎች በጠላትነት የፈረጅዋት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ አማራው እንዴት እንደተንከባከባት ይህንን ቪዲዮ እንድታዩ እጋብዛችለሁ።

አማራው “ተዋህዶ ኦርቶዶክሰ ቤተክርስትያንና አማርኛ ቋንቋን” ጠብቆ አሁን እስካለነው ድረስ ተጉዞኣል። አሳዛኙ የዘመናችን ክስተት ግን ከምፅአተ-አክሱም “የቤጃ ወረራ በላ” በትግሬነት የተከሰቱት ትግሬዎች”  በ1967 ዓ.ም ወደ ጫካ በመሄድ ‘ኦርቶዶክስ ክርሰትናን፤ ባለ ሦስት ሕብር ሰንደቃላማችንን እና አማርኛን’ በጠላትነት ፈርጀው ዳግም ‘ምፅአተ -ኦርቶዶክስ’ ለማምጣት የተነሱ “የወያኔ ትግሬዎች” በስብሓት ነጋ አንደበት የተነገረና በድርጅቱም በተግባር የተከናወነ በማስረጃ ያለ ህያው ምስክር ነው። እኔ ከትግራይ መወለዴ “እስመ ኢአቀቡ ቃለከ” (ቃልህን አልጠበቁምና፤ግብዞችን አይቼ አዘንሁ” (መዝሙር 117) እንድል ተገድጃለሁ። እኔው ራሴ ትግሬ መሆኔን አስጠላኝ ብላችሁ ይገርማችሁ ይሆናል፡ ለዚህ ምክንያት አለኝ። እነ ስብሓት ነጋን እነ መለስ ዜናዊን የሚያሞግስ ተሸክሞ የሚሄድ ማሕበረሰብ ትግራይ ለመግለጽ ቃላት አበድሩኝ!

ትንሽ ተስፋ እየሰጠኝ የመጣ ነገር ቢኖር፤ ዛሬ፤ ዛሬ በቅርቡ ያየሁት አዲስ ክስተት ‘ሴቱም ወንዱም ልብሱም፤አንገቱም ግምባሩም በተዋበ መስቀል ያጌጠው አማራን እያዩ” ትግሬዎች አንገታቸው ላይ መስቀል ማንጠልጠል መጀመራቸው የነ ሰብሓት ነጋ አማራን እና ኦርቶዶከስን አከርካሪው ሰበርነው የሚለው ጥላቻቸው ቦታ እያጣ መምጣቱ የሚበረታታ ነው። መገንዘብ ያለብን ሕዝብን በሚምበለበል የምድረበዳ እሳት አሻግሮ የኢትዮጵያን ሰንደቅና ሃይማኖትዋን መሠረተ ድንጋይ አንዋሪው አማራው ዛሬም ሃያሉ ምድረበዳ ፊቴ ላይ ተጋርጦበታል። ሁሉም እንደልብስ ያረጃሉ እሱ ግን እንደ ጥንቱ ምድረደባውን በድል ይሻገራል ብል አልተሳሰትኩም። ይህንን ታላቅ ሕዝብ በታላቅ ተራራ ላይ ቆሜ  ማመስገኔ የሚጠሉኝ ካሉ ለኢትዮጵያ እንግዶች ናቸው።
አመሰግናለሁ ጌታቸው ረዳ (Ethio Semay)
EOTC TV CHANNEL ደብረ ሐዊ መካነ ምሥዋር(ሊታይ የሚገባ የቅዱስ ያሬድ ገዳም)ሊያመልጦት የማይገባ ዘጋቢ ፊልም


Thursday, November 7, 2019

ለሯጩ ኃይሌ ገብረሥላሴ መልስ (ከጌታቸው ረዳ -ኢትዮ ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ) (Ethio Semay) (Nov. 7, 2019)


ለሯጩ ኃይሌ ገብረሥላሴ መልስ (ከጌታቸው ረዳ -ኢትዮ ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ)
(Ethio Semay) (Nov. 7, 2019)
Getachew Reda author and Editor Ethio Semay
ተፈጥሮ አድሎአቸው በብርና በዶላር ብዛት ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቶአቸው አላስኖር አላስቀምጥ ብሎአቸው ፖለቲካውን ሳይካኑበት ለኢትዮጵያ ጠ/ሚኒሰቴርነት እወዳደራለሁ ሲሉ ከነበሩት የፋሺስት ድርጅት መሪ አድናቂዎች ከነበሩት መካከል አንዱ ሯጩ ኃይሌ ገብስላሴ ነው። ዛሬም መፈትፈቱን አላቆመም።

ትዝ ይላችሁ እንደሆነ በራሴው መጽሐፍ “የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” በሚለው መጽሐፌ ውስጥ ኃይሌ ገብረሥላሴ የተናገረውን በመግቢያየ ላይ ጠቅሼው ነበር እንዲህ ብሎ ስለ ዲሞክራሲ የተናገረውን፡

ልጥቀስ፤
““ በኔ እይታ ዲሞክራሲ  ለአፍሪካ ቅንጦት ነው!” ይላል እንግሊዙ ኃይለ ገብረሰላሴ እንዲህ በማለት “Everything we talk is about democracy, democracy. I know for me it is a little bit too luxurious. Democracy is too luxurious for Africa.”(ባለ ጊዜው  አትሌት ኃይለ ገብረስላሴ ሲሞላቀቅብን የተናገረው)  ምንጭ የጌታቸው ረዳ መጽሐፍ “የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው? ገጽ 8

ሰሞኑን ፌስ ቡክ ልከስስ ነው ብሎ ይቦርቃል። እስኪ ምን እንዳለ እንመልከት፦እንዲህ ይላል
”ፌስ ቡክ (የማሕበራዊ ትስስር ገጾች)በኢትዮጵያ ውስጥ እያደረሱት ያለውን ጥፋት የኢትዮጵያ መንግሥት የማይከስ ከሆነ ጌስ ቡክ ፣ክሴ አይቀርም።ሐገር እየተጎዳ ሕዝብም እየሞተ ነው ብሎ ተናግሯል።.. ሌላ አገር የተፈጠሩ እዚህ አገር እንደተፈጠሩ፤ሌላ አገር የጠቆረጡ እጆችና እግሮች ምስሎች እዚህ አገር እንደተቆረጡ ፤ሌለ አገር የተቃጠሉ ቤቶችና ንብረቶች እዚህ አገር እንደተቃጡሉና እንደወደሙ እያስመሰሉ ለጣጠፍውና  አሰማምሮ ማቅረብ ዋጋ ያስከፍላል።”
ሲል ባለ ሃብቱ ፖለቲከኛ ሯጩ ሃይለ ግበረሥላሴ በማያውቀው ፖለቲካ ገብቶ ዛሬም መፈትፈቱን አላቆመም።    
መጀመሪያ አማራውን ማሕበረሰብ የጨፈጨፈው አንተ ስቅስቅ ብለህ ያለቀስክለት ያንተው ንጉሥ ፋሺስቱ መለስ ዜናዊን መክሰስ ሲኖርብህ ዛሬ አንተ ስለ “ሕዝብ ጭፍጨፋና ሰላም አሳቢ” ሆነህ ብቅ ማለትህ የሚመሰገን ቢሆንም የተደረገውን አልተደረገም እያልክ ከአብይ አሕመድ ውሸት ጋር መጣመርህ የሚገርም ዘመን ነው። ለመሆኑ እንዳንተው ያሉ ለነ መለስ ዜናዊ ለፋሺሰቶችና ለጸረ አማራዎች ስቅስቅ ብለው እምባቸውን የሚያፈስሱ አሞጋሾችን በየትኛው ፍርድ ቤት እንክሰሳችሁ?

 እናነት ሙዚቀኞች እና ራጮች ምናለ በማታውቁበት ፖለቲካ ባታቦኩና ነገር ባታበላሹብን? ዛሬ ደግሞ ፌስቡክን እከሳለሁ ብለህ ስትጮህ በጣም ነው የገረመኝ። ብርሃኑ ነጋም በሎሌዎቹ ዝቶ ነበር። አብይ አሕመድም ተነፋፍጦብን ነበር።
የሚገርመው እዛው አንተ ካለህበት አገር አዲስ አበባ ውስጥ ተቀምጠው ነፍጠኛን ሰበርነው፤አዲስ አባባ ኦሮሞ ተቆጣጥሮታል’ የሚሉ እነ ሽመልስ አብዲሳ አስከ አብይ አሕመድ ጀምሮ ለማ መገርሳ፤እና ጃዋር፤ አማርኛ ከሚናገር ጋር እንዳትጋቡ፤ የሚለው በቀለ ገርባ፤ እንዲሁም “በአዲስ አባባ ዙርያ ጎጃሜዎችን አምጥተው ካሰፈሩ በላ ሕገ ወጠው ቤቶችን እንዳይፈርሱ እያሉ ሲከላከሉ የነበሩ ነፍጠኞች ማንነታቸው በውል ስለተለየ፤ የነፍጠኛ ሥርዓት ባለቤቶች መሆናቸው ስለታወቀ ከዚህ በኋላ ሒሳብ እናወራርዳለን” ብሎ በግልጽ የተናገረ ታየ ደንዳአ የመሳሰሉ ጸረ አማራዎች ሃይለ ገብረስላሴ ለምን አልከሰስካቸውም? ወይንም ለምን አንተ መንግሥት ተብየው “ሥርዓተ አልባው መንግሥትህን” ፌስቡክ ካልከሰሰ እኔ ፌስቡክ እከሳለሁ የምትለውን መንግሥትህን ለምን የተጠቀሱትን ጽንፈኞች አልከሰስካቸውም ብለህ አልጠየቅክም?
ያውም ወንጀለኞቹ ጸረ አማራ ኦነጎች እነ ሌንጮ ለታ፤ እንዲሁም ከጥቂት ወራት በፊት 3000 አመት አማራውን እንገዘዋለን ብሎ በግልጽ የተናገረ ጭፍን ጠባብነትና ትምክሕረተኝነት የተናወጠው ‘ሌንጮ ባቲ’ (ባለፈው ሰሞን አብሮ ከአብይ ጋር ወደ ሩስያ የሄደው የዛሬው የአብይ አሕመድ አማካሪ) ፤ ከማል ገልቹ (ሰሞኑን ነፍጠኛ እያለ የተናገረው ሰምታችል) የመሳሰሉትን በጠቅላላ “ኦፒዲኦ” የተባለው የቄሮ ጽንፈኛ አንቀሳቃሽን ሳትከስ ለዝና ብለህ ወደ ፌስቡክ ማትኮር “የብብትዋን ትታ የቋጡን” ያሰኛል።

አንተ ባለህበት አዲስ አበባ ከተማ አብረውህ ባንድ ከተማ የሚኖሩትን ከላይ የጠቀስኳቸው ዘረኞች ምላሳቸው አሞርሙረው የሚናገሩት ተደብቀው ሳይሆን ወይንም  “ፒያሳ መሃሙድ ጋ ጠቢቂኝ!” ደራሲ ጋዜጠኛ ‘መሐመድ ሰልማን’ እንዳለው ሚስጢረኛ ተሳሳሚዎች የሚሳሳሙበት “ኢንትር ላንጋኖ” ፤ “ትሬይን ሃውስ” ፤ “ቢግ ትሪ” ፤”ጊቤ” ፤”ቬሮኒካ” በሚባሉ ፒያሳ ውስጥ የሚገኙ ድብቅ መሰሳሚያ ቤቶች ውስጥ ሆነው ሳይሆን ጸረ አማራ የሆነ  ሕዝብ ለሕዝብ የሚያፋጀውን ማኒፌስቶአቸውና ንግግራቸው ያሰራጩት ፤ ተደብቀው ሳይሆን “በግልጽ በአደባባይ” የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀሮ እና ዓይን እያየ እየሰማ በጽሑፍና በንግግር ያሰራጩት አደገኛ መልዕክት አልሰማህም። ታዲያ ምነዋ ወንድም ኃይለ ግበረስላሴ እጉያህ ያሉትን እነ አብይ፤ እነ ለማ፤ እነ በቀለ ገርባ ሺመለስ እና ታየ ደንዳአ፤ጃዋር መሐመድ፤ በቀለ ገርባ እና መሰሎቹን ሳትከስ ወደ አሜሪካ አነጣጥረህ ፌስ ቡክን ለመክሰስ ምን አነሳሳህ?

ለመሆኑ  ፌስ ቡክ ያሉትን ዘረኞች እጅ እግር ሳይቆረጥ ከሌላ አገሮች የተፈጸመውን አጅና አንገት “በቆርጦ ቀጥል ቴክኒክ እያሰማመሩ” የተቆረጠውን የሌችን አገሮች ጭካኔ አገር ውስጥ እንደተደረገ አስመስለው እየለጠፉ ሕዝብን ለሕዝብ የሚያጋጩ የፌስ ቡክ  ኢትዮጵያውያንን እከሳቸዋለሁ የምትለው ቅዠት እውነት አንተ አገር ውስጥ ነው የምትኖሮው? የተደረገው አታውቅም?

 ለመሆኑ ሌላውን ልተወው እና “ሁለት ፕሮቴስታንቶች ሁለቱም እህትማማቾች ጡታቸው ተቆርጦ የሰውነት ክፍላቸው እንኳ በጽንፈኞች ሜንጫ ቁርጥርጥ ተደርገው መገደላቸውን ከዓይን ምስክሮችና ከሥፍራው የሸሹ እማኞች ሲናገሩ አልሰማህም? አከላቶቻቸው ተሰብስቦ በስንት መከራ ነብሳቸውን ሳያድኑ ለሞቱት ነብሳት ሲሉ ተሸሽገው ኦርቶዶክሶች አልቀበርዋቸውም? ጆሮህ እዛ ደርሶ ለምን ተደፈነ? የዓለም ኦሎምፒክ ሩጫ ስትመለከት ወይስ  የዓብይን ውሸት ስታዳምጥ አመለጠህ?   
ለፋሺስት መሪዎች የሚያለቅስና የሚያሞግስ ሕሊና የተሸከሙ፤ አገር ውስጥ የሚደረገውን አልተደረገም የሚሉ ሞራለ ቢስ ሁላ ገንዘብ ስላለው ብቻ እንዳመጣበት መፈትፋት ያስነውራል።  ጌታቸው ረዳ (ከኢትዮ ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ)

Wednesday, November 6, 2019

ሁላችሁም ጫ በሉና አድምጡኝማ! አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ) (Ethio Semay ኢትዮ ሰማይ ድረገጽ የተለጠፈ)


ሁላችሁም ጫ በሉና አድምጡኝማ!
አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)
(Ethio Semay ኢትዮ ሰማይ ድረገጽ የተለጠፈ)
ባለ ሁለት ምላሱ አብይ አሕመድ (ባንድ ራስ ሁለት ምላስ)
" የአቢይ የንግግር “ፊያቶ” እንዲህ አልነበረም፡፡ ትንታግ ምላሱ ጉሮሮው ውስጥ ሲወተፍ አይተናል፡፡ አንዲት ቃል ለማውጣት ሴኮንዶችን ፀጥ ረጭ ሲል ታዝበናል፡፡ ፊቱ በረዶ ሲዘንብበት አስተውለናል፡፡ የምናውቀው ግርማ ሞገሱ ከድቶት ሁለመናው ጥላቢስ ሲሆን በበኩሌ አይቻለሁ፡፡ የክፋት መጨረሻው እንደዚህ ነውና አልገረመኝም - የርሱ ግን ፈጠነብኝ፡፡ አለወትሮው ቃላትን ሲደጋግምና ሲንተባተብ ተመልክተናል፡፡ የደም ዋጋ ገና ከዚህ በላይ ብዙ ያስከፍለዋል፡፡"……  ከጽሑፉ የተወሰደ. ሙሉውን ከዚህ በታች ያንብቡ…

የሀገራችን ጉዳይ እንደሰሞኑ የተንተከተከበት ወቅት ኖሮ አያውቅም፡፡ በፍጹም!
ምክርን አትናቁ፡፡ ከየትም ቢመጣ ገምቢ ሃሳብንና አስተያየትን መቀበል የበሳል ሰው ምልክት ነው፡፡ ባይጠቅማችሁ አትጎዱበትም፡፡ ይህን አስተያየት የሚጽፍላችሁ ሰው የዛሬ 30 ዓመት ጀምሮ ስለሀገሩ እጅግ ብዙ ነገሮችን ሲጠቁም ነበር፡፡ ያኔ ስለሀገር ይጽፉ ከነበሩ ታላቆቹ አንዱ - ዳንዴው ሰርቤሎ (ጋሽ ግርማ ፈይሣ)  - በቅርቡ ወደማይቀርበት አገር ሄደ፤ ሌሎቹ ተስፋ ቆርጠው ወይም ለሥጋቸው አድልተው መጻፍን እርግፍ አድርገው ትተውታል ወይም በገዛ ፈቃዳቸው ጡረታ ወጥተዋል፡፡ ይህ ሰው ግን “ጉዱን አያለሁ” ብሎ እስካሁኒቷ ቅጽበት ቀጥሏል፡፡ ያኔ በዚህ ሰውዬ የወጣትነት ዘመን ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ የነበረ አቢይ የተባለ የአሁን ጎልማሣ ሳይመጣ ሰውዬው ብዙ ደክሟል፡፡ ወሮታ ክፈሉኝ እያለ አይደለም አሁን፡፡ እያለ ያለው “እባካችሁን ጆሮ ስጡኝ!” ነው፡፡ ይህ ሰው ከጻፋቸው ወደ አንድ ሽህ የሚጠጉ መጣጥፎች ውስጥ የተወሰኑትን ብንፈትሽ ከሚጽፋቸው ነገሮች በጣም ብዙዎቹ በተግባር መታየታቸውን ማመሳከር ይቻላል፡፡ አሁንም ጆሮ እናውሰው፡፡ ዓይነተኛውን የዕድሜ ዘመኑን ላባካነበት ሌላው ቀርቶ የሚለውን በመስማት እንካሰው፡፡

ዶ/ር አቢይ ደክሞታል፡፡ ትንፋሹ እየተስለመለመች ናት፡፡ በኔ ግምት በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ብዙና ሊታመኑ የማይችሉ በታሪክ አስወቃሽ ድርጊቶችን በመፈጸሙ እነዚያ ዕኩይ ድርጊቶች በህልሙም በእውኑም እየመጡ ሰላሙን ስለሚነሱትና በርሱ ዕውቅና ወይም ትዕዛዝ የተገደሉ በተለይም የአማራው አመራሮች ነፍሳት ዕረፍት እያሳጡት በመሆናቸው በጣም እየተጨነቀና በአካልም በመንፈስም ክፉኛ እየዛለ ይገኛል፡፡ ከሰሞኑ ጃዋርን ነፃ ለማውጣት ካደረገው ከንቱ ንግግር የተረዳሁት ይህንንና ብዙ ሌላም ነገር ነው፡፡

የአቢይ የንግግር “ፊያቶ” እንዲህ አልነበረም፡፡ ትንታግ ምላሱ ጉሮሮው ውስጥ ሲወተፍ አይተናል፡፡ አንዲት ቃል ለማውጣት ሴኮንዶችን ፀጥ ረጭ ሲል ታዝበናል፡፡ ፊቱ በረዶ ሲዘንብበት አስተውለናል፡፡ የምናውቀው ግርማ ሞገሱ ከድቶት ሁለመናው ጥላቢስ ሲሆን በበኩሌ አይቻለሁ፡፡ የክፋት መጨረሻው እንደዚህ ነውና አልገረመኝም - የርሱ ግን ፈጠነብኝ፡፡ አለወትሮው ቃላትን ሲደጋግምና ሲንተባተብ ተመልክተናል፡፡ የደም ዋጋ ገና ከዚህ በላይ ብዙ ያስከፍለዋል፡፡ የነአምባቸው ደም፣ የነአሣምነው ደም፤ የነሰዓረ ደም... የውሻ ደም አይደለም፤ የዶሮ ነፍስ አልያዙም፡፡ እነዚህ ውድ ዜጎች በዚህ ሰው ምክንያት ጭዳ መሆናቸውን ለመረዳት ከስድስተኛው ስሜታችን ሩቡን ያህል ብቻ እንዲሠራ ማድረግ በቂ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ በተለይ በአሁኑ ቅጽበት ምሥጢር አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር ግልጽ ነው፡፡

እንግዲያውስ እንዲህ እናድርግ፡፡ እንዲህ የምናደርገውም የትንቢቱን ቃል ለማለዘብ እንጂ ትንቢትን ማስቀረት ወይ ማስለወጥ ስለሚቻል አይደለም፡፡ ሁሉንም አይተን የሚበጀንን እንይዝ ዘንድ መለኮታዊ ፍርጃ እንደተጣለብን መገንዘብ ብልኅነት ነው፡፡

ሁሉም ሰው ወደ ፈጣሪው ይጸልይ፡፡ በፈጣሪ ፈቃድ ወያኔዎች ዳር ይዘው  በሁሉም ረገድ እነሱን የተኩና በነሱም የሰለጠኑ አቢይንና ወንድሙን የመናዊውን ጃዋርን ተመስሎ የመጣብን ውርጅብኝ ከባድ ነው - እያስገመገመ ያለው አደጋ ከነሦርያና ሩዋንዳም ይከፋል፡፡ በሀገራችን ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ክስተት ሰሞኑን ብልጭ ብሎ ንጹሓን ዜጎች - ሕጻናትና አእሩግ በሽተኞች ሣይቀሩ - እንደበሬ ታርደዋል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በተከናወነ ድራማ “ተከብቤያለሁ” ብሎ በማኅበራዊ ሚዲያ የድረሱልኝ ጥሪ ማቅረብና ባሌ ውስጥ የምትገኝ የአምስት ዓመት ዕድሜ ሕጻን መታረድ በምን ሊገናኙ እንደሚችሉ ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡

ይህ ነገር የሃይማኖት ጉዳይ እንዳይመስላችሁ፡፡ ይህ ጉዳይ እንደሚተረክልን የዘረኝነት ጦስ እንዳይመስላችሁ፡፡ ኢትዮጵያን ድራሹዋን የማጥፋት ጉዳይ ነው፤ የሚባለው ሁሉ ሽፋን እንጂ እውነተኛ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህ ሤራ ዓለም ኣቀፍ ነው፡፡ ከፈለጋችሁ ከአባይ ወንዝም አገናኙት ወይም ከአይገበሬው የሀበሾች ነጭን የማሸነፍ ጀግንነት ወይም እውነተኛ የክርስቶስ የማዕዘን ራስ ሊሆን ከሚጠበቅበት የኦርቶዶክስ እምነትም ጋር አያይዙት ይህች ሀገር በኢሉሚናቲዎች ጥርስ ከገባች ዘመን የላትምና ይህ ክስተት ኢትዮጵያን ከነታሪኳ ለማየት ካለመፈለግ የሚመነጭ የምዕራባውያን ታላቅ ሤራ ውጤት ነው፡፡ የቀን ከሌት ህልማቸው ይህችን አገር ማጥፋት በመሆኑ ምን ጊዜም ምቹ ሁኔታን መፍጠር ባይቻላቸው ራሱ እስኪፈጠርላቸው በጉጉት ሲጠብቁ ኖረዋል፡፡ አሁን ደግሞ በጣም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ አቢይን የመሰለ ፀረ ኦርቶዶክስና ጃዋርን የመሰለ ፀረ እስልምና ጉዶች በኢትዮጵያ ምድር ግዘፍ ነስተው ሁሉንም ነገር ተቆጣጥረዋል - የሚቃረኑ ለመምሰል የሚጥሩት ትያትር ሁሉ ፋይዳቢስና በቀላሉ የሚነቃበት እየሆነም ተቸግረዋል፡፡ ድራማቸው ሁሉ ሳይተውኑት ጭምር የሚታወቅና ምን ሊተውኑ እንደሚችሉ ሳይቀር የሚተነበይም ነው፡፡ ታሪካዊ ጠላቶቻችንም ከነዚህ የውስጥ ምንደኞች ጋር በመተባበር ውዱንና የክቱን የኖቤል ሽልማታቸውን ሣይቀር ለዚህ ጦርነታቸው አውለው በማታለልም፣ በማፍዘዝም፣ ጠና ሲል ደግሞ በጦር መሣሪያም ጭምር ይህችን ሀገር ለማጥፋት ክተት ዐውጀዋል፡፡ ያፈነገጠ ፕሮቴስታንቲዝምና የሆሊውድ/ቦሊውድ ፊልምና ሙዚቃ ኢንዱስትሪዎችም የዘመቻቸው አካላት ናቸው፡፡ አዲስ ነገር አልነገርኳችሁም፡፡ “ስንቶቻችን ይህንን እናውቃለን?” የሚለው ግን መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቻችን ስንታይ አዚም የተጣለብን ይመስል ስለማንኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ሳንጨነቅ ተጋድመን ዕንቅላፋችንን እንደቃለንና፡፡

አማራና ኦሮሞ፣ ትግሬና ጉራጌ አንባባል፡፡ ይህን የሤረኞች መከፋፈያ እንተወው፡፡ መተማመንን መፍጠርና በጋራ መታገል ይህችን አገር ከተደገሰላት የመከራ ዶፍ ይታደጋታል፡፡ በትንሹ በትልቁም አንደናገጥ፡፡ የሚሆነው ሁሉ ሊሆን እንዳለው እንመን፡፡ ከእስካሁኑ የተመሰቃቀለ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወታችን ግን እንማርና በአፋጣኝ እንስተካከል፡፡ ምክንያቱም ጊዜ የለንም፡፡ እንሩጥ!

ጥሩ ጥሩ ኦሮሞዎች፣ ጥሩ ጥሩ ትግሬዎች፣ ጥሩ ጥሩ አማሮች.... እየተሰባሰባችሁ እየተመካከራችሁ እየተፈቃቀራችሁ ለሥልጣንና ለገንዘብ ያላችሁን ፍቅር እየተዋችሁ በአንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ሀገርን ለማዳን ጥረት አድርጉ፡፡ ገንዘብም ሆነ ሥልጣን የሚጠቅመን ሀገር ስትኖር ነው፡፡ በአሁኑ ሁኔታችን ቢሊዮን ብርም ዓለምን የሚያስገዛ ሥልጣንም ዋጋ የላቸውም፡፡”ቀድሞ የመቀመጫየን” ብላለች ዝንጀሮ፡፡

በተለይ ብአዴን ወይም አዴፓ ራሱን ያጥራ፡፡ ይህ ሕዝብ ነገ ግልብጥ ብሎ ቢወጣ የመጀመሪያው ተጠቂ አዴፓ ነውና በቶሎ ወደ ትክክለኛ ቦታው ይመለስ - ኖሮት ወደማያውቀው ትክክለኛ ቦታ፡፡ ውስጡን ያጽዳ፡፡ በሕወሓትና ኦህዲድ የተሰገሰጉበትን የሁለት ዓለም መዥገሮች ይመንጥር - አሁኑኑ፡፡ እውነቱን ለመናገር ነገ ጊዜ የለንም፡፡ የነገሮች ፍጥነት በሚገርም ሁኔታ ብርሃናዊ ሆኗል - እጅግ ፈጣን!

መሆን ያለበት ባይቀርም ወደ ፈጣሪ ካለቀስንና ፍቅርንና መተዛዘንን ከተላበስን የመከራ አዝመራው ሊቀንስልን ጊዜውም ሊያጥርልን ይችላል፡፡ በየከተማው ያለው አሥረሽ ምቺው ይቅር፡፡ ከፈጣሪ መንገድ የወጡ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በቶሎ እንዲመለሱ እንምከር፤ በህግ አግባብም እናስተካክላቸው፡፡ ቅጥ ያጣውን ገንዘብ ወዳድነታችንን ልጓም እናብጅለትና ሙስናን ከደም ዝውውራችን እናውጣው - አንዱና ትልቁ ጠላታችን እርሱም ነውና፡፡ በእውነተኛው ገቢያችን  ብቻ ለመኖር ጥረት እናድርግ፡፡  ዳንኪራና ጮቤ እንዲሁም ከተፈጥሮ ህግጋት የወጣ መጥፎ ምግባር ሶዶምንና ገሞራን ምን ያህል ድምጥማጣቸውን እንዳጠፋቸው እናስታውስ፡፡ አሁን ጊዜው የሱባኤ ነው:፡ በሙስሊሙም በክርስቲያኑም የሱባኤና የቱበታ ወቅት ይሁን፡፡ በጽኑ እምነትና በንጹሕ ልብ ተጠይቆ ፈጣሪ እምቢ ብሎ አያውቅም፡፡

የእነ አቢይ ልጆች እነሥራኤል ዳንሣ ሕዝቡን ከምዕራብ አፍሪካ በተገዛ መተትና ድግምት እንዴት እያፈዘዙትና ወኔውንም ገንዘቡንም እየሰለነቡት እንደሆነ እየታዘብን ነው፡፡ የነዚህ አጋንንት ግብር በጠባብ አዳራሽ ተወሰኖ ቢቀር ብዙም ባልከፋ - “ወደሽ ከተደፋሽ ...” እንዲሉ ነውና፡፡ ግን ያ ዓይነቱ አንደርብ የምኒልክን ቤተ መንግሥት በግላጭ ተቆጣጥሮ በአዶ ከብሬ የቁጭ በሉ ትብታቡ ኢትዮጵያን ገደል እየከተታት መሆኑ ከማሳሰብም በላይ ነውና ሁላችንም ወደየኅሊናችን ተመልሰን ይህች ሀገር በትንሽ መስዋዕትነት መፍትሔ የምታገኝበትን ዘዴ እንፈልግ፡፡ ግዴለሽነት ብዙ ዋጋ ያስከፍላልና ከሰው ሳይሆን ከራሳችን እንጠብቅ፡፡ በሌሎች መስዋዕትነት ነፃ መውጣት እንደአካሄድ የሚቻል ቢሆንም እኛ ያልተሳተፍንበት ነፃነት በዘራፊ ወንበዴ ሊቀማና ያልተፈለገ አቅጣጫ ሊይዝ እንደሚችል ከተሞክሮ እንማር፡፡ በረባ ባልረባው አንከፋፈል፤ ቂምም አንያያዝ፡፡ በሃሳብ መከፋፈልና ቂም መያያዝም እኮ የሚያምረው በቅድሚያ የጋራ ሀገር ስትኖር ነው፡፡ በተገኘህበት ሊያርድህ ሜንጫና ሠይፍ ይዞ ወዳንተ እየተመመ ያለ የጥፋት ሠራዊት ከጎንህ አስቀምጠህ “የዛሬ ስንት ዓመት እንዲህ ብለኸኝ፤ ያኔ እንዲህ ብለሽኝ... እ?... ካንቺ ጋራ ?... ካንተ ጋራ? ... እስላምና አማራ! ‹አሄሄ! ‹የወጋ ቢረሣ የተወጋ አይረሣ!› አሉ!› ...” መባባሉ የመርገምት እንጂ የአስተዋይነት ምልክት አይደለም፡፡ እየኖሩ እንጂ እየሞቱ መወቃቀስ ለጠላት ካልሆነ ወገኔ ነው ለምትለውና ወገንህ ሊሆን ለሚጠበቅበት ለሚገባውም ሰው አይጠቅምም፡፡ በቃኝ እባክህን፡፡ ለቀና የሃሳብ ልውውጥ - martyrof2011@gmail.com