Thursday, August 29, 2019

ዘረኝነት ትልቁ ዕብደት - (ከሰሞኑ አንኳር አሣዛኝ ክስተቶች ጥቂቶቹ) ምሕረት ዘገዬ (mz23602@gmail.com) Posted at Ethio Semay


ዘረኝነት ትልቁ ዕብደት - (ከሰሞኑ አንኳር አሣዛኝ ክስተቶች ጥቂቶቹ)
ምሕረት ዘገዬ (mz23602@gmail.com) 
Posted at Ethio Semay
ብዙ የዕብደት ዓይነቶች አሉ፡፡ ከያዙ የማይለቁ፣ ከሰው ወደ ሰው ወይም ከእንስሳ ወደ እንስሳ የሚተላለፉ፣ ልብስ እያስወለቁ መለመላን የሚያስኬዱ፣ ጥሩ ልብሶችን እያስለበሱ አእምሮን ግን የሚያስቱ፣… የዕብደት ዓይነቶች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ከሁሉም ዕብደቶች በክፉነቱና ሳይገድል እንደማይለቅ በህክምና ታሪክ የተዘገበው ግን የውሻ ዕብደት ነው፡፡ የውሻን ዕብደት መቶ ፐርሰንት ዕብደት ይሉታል የተማሩቱ፡፡

በዘመናችን ግን ያን የውሻ ዕብደት በዕጥፍ የሚያስከነዳ ሌላ ዓይነት ዕብደት ተከስቶ ሀገርና ሕዝብን ጉድ እያሰኘ ነው፡፡ እሱም ዘረኝነት ነው፡፡ መድኃኒት የሌለውና የይሉኝታና ሀፍረት ገመዶችን በጣጥሶ በመጣል ሰውን መሣቂያና መሣለቂያ የሚያደርግ ነው የዘረኝነት ዕብደት፡፡ ዘረኝነት በተራው የብዙ ነገሮች መባቀያ ነው - ለምሣሌ ለሙስና፣ ለድንቁርና፣ ለታኅተ-እንስሳዊ ባሕርያት ወዘተ.፡፡ ዘረኝነት የሁሉም ነውሮች፣ ወንጀሎችና ኃጢኣቶች መፍለቂያ ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን በሽታ እንኳን ለወዳጅ ለጠላትም አይስጥ፡፡

በዚህ አሳሳቢ ወቅት ወያኔ የሰቀለውን ማውረድ አቅቶን በጭንቀት እየዋለልን እንገኛለን፡፡ ወያኔ የወለደውና ላለፉት 30 እና 40 ዓመታት ሀገራችንን ሲያምሳት የኖረው የዘረኝነት ዕብደት እጅግ ተላላፊ እንደመሆኑ ሀገራችንን ጫፍ እስከ ጫፍ ወርሮ እንደሰደድ እሳት እያንገበገባት ነው፡፡ ካለ ፈጣሪ ዕርዳታም የሚቆም አይመስልም፡፡ ስለሆነም በተለይ  በገዳማትና በዋሻዎች ዘግታችሁ የምትገኙ የእግዚአብር ሰዎች ለዚህች በሞት አፋፍ ላይ ሆና ለምታቃስትና ለምታጣጥር ሀገር አጥብቃችሁ ጸልዩ፡፡ ክፉን ያርቅልን እንጂ ሀገራችን ለይቶላት እንደሦርያና ኢራቅ ከሆነች መመለሻው ከባድ ነው፡፡ እነጃዋር እንደሆኑ እሳቱን ከለኮሱ በኋላ ጃዝ ያሏቸው ሰዎች ይወስዷቸውና በሞቀ ቤት ያሯቸዋል - ይህ ግልጽ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በሁለትና በሦስት ዜግነት እንደሚቀማጠሉ እናውቃለን፡፡ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የቆረጠ ሰው የቢሊዮን ዶላር ሎተሪ እንደወጣለት ይቆጠራል፡፡ የዋናው ሣጥናኤል ቢሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ይመስለኛል፡፡ በሰው አምሣል የተፈጠሩ ሰይጣኖች በሰዎች መሀል እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱትም በዚህችው ጉደኛ ሀገራችን ይመስለኛል፡፡ ማንኛውም ህገ ልቦናና ህገ መሬት ወሰማይ የሚጣስባት ብቸኛ ሀገርም ትመስለኛለች፡፡

አንዳንድ ሰሞነኛ የዘረኝነት ልክፍት ውጤቶችን እንመልከት፡፡ (ብዙዎቹ በሚዲያ የተነገሩ እውነተኛ መረጃዎች ናቸው፡፡) 

1.     ባለፉት ሁለት ቀናት ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ፡፡ ልደታ መሀል ከተማ ላይ፡፡ ለአካባቢው እንግዳ የሆነ አንድ አሽከርካሪ መቆም በማይፈቀድ ቦታ አቁሞ ሰው ይጠብቃል፡፡ ወዲያው ከመቆሙ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ይመጣና ሰላምታ ከሰጠው በኋላ በኦሮምኛ ያናግረዋል፡፡ ሹፌሩ ግራ ይጋባና “ኧረ ኦሮምኛ አልችልም የኔ ወንድም!” ይለዋል፡፡ ትራፊክ ፖሊሱም በቅጽበት - “ባንድ አፍ!” እንደምንለው ዓይነት በግሩም አማርኛ “ኦሮምኛ ካላወቅህማ የሚያግባባን ሌላ ነገር አለ” በማለት በወገቡ የያዘውን የደምብ ተላላፊዎች መቅጫ ወረቀት አውጥቶ ግጥም አድርጎ ይጽፍበታል፡፡ ቢለምነው … ቢለምነው… በአቡየ በጂዮርጂስ ቢለው ወይ ፍንክች! በዘረኝነት ደዌ ተለክፎ አብዷላ! እነጃዋርና እነበቀለ ገርባ ምን ሲሰሩ ከረሙና! እነሕዝቅኤል ጋቢሣ ምን ሲተክሩ ቆዩና! ያቺ የኦሮምኛዋ መግቢያ ወገንን መለያ ኮድ መሆኗ ነው፡፡ ለዚህም ደርሰናል! አዲዮስ ኢትዮጵያ፡፡

በበኩሌ ሰውዬው አይቀጣ አልልም፡፡ ችግሩ ሰውዬውን ያስቀጣው ደምብ መተላለፉ ሳይሆን ኦሮሞ አለመሆኑ ወይም አለፍ ሲልም ኦሮምኛን መናገር አለመቻሉ ብቻ ነው፡፡ “የሚያግባባን ሌላ ነገር አለ” የሚለው የዘረኝነት ደዌ መገለጫ ብዙ ነገር ይጠቁመናል፡፡ የአዲስ አበባና የፌዴራል ተብዬው የሥራ ቋንቋ አማርኛ ሆኖ ሳለ ኦሮምያን ገና ከአሁኑ ያለ ዐዋጅና ያለማስጠንቀቂያ በዚህ መልክ ወደ አዲስ አበባ አስገብቶ ሕዝብን ማወክና በማንአለብኝነት እስከዚህ ድረስ በግልጽ ማዳላት ምን ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል አይገባኝም፡፡ የሚመለከተው አካል ይህን ወጥ ረገጥነት ቢመለከተውና ነገሮች ከቁጥጥር ሳይወጡ ዕልባት ቢበጅላቸው መልካም ነው፡፡ ለኦሮሞም ሕዝብ ይህ ነገር የሚጠቅመው አይመስለኝም፡፡ ወያኔዎች በልበ ድፍንነት ያደረጉት የዘረኝነት መድሎ ሁሉ ዛሬ ለጸጸትና እንደፈሳች ዝንጀሮ ለመገለል እንደዳረጋቸው ሁሉ ይህ ዓይነቱ ኦሮሟዊ ፈር የለቀቀ አሠራርም ይዋል ይደር እንጂ እየተለመደ በመጣው የጋራ አገላለጽ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በነገራችን ላይ ያ ኦሮምኛ ያልቻለ ሰው እኮ ኦሮሞም ሊሆን ይችላል፡፡ ኦሮምኛን አለመቻል በራሱ ኦሮሞነትን ሊከለክል አይችልም፡፡ አማርኛ የማይችሉ ብዙ አማሮች አሉ፤ ትግርኛ የማይችሉ ብዙ ትግሬዎች አሉ፤ ኦሮምኛ የማይችሉ ብዙ ኦሮሞዎች አሉ፡፡ ቋንቋ በዘር የማይተላለፍና በመልመድ ወይም በመማር የሚገኝ ማኅበረሰብኣዊ ዕሤት ነው፡፡ ይህን ሃቅ ያለማወቅ ችግር ነው እነበቀለንና ሕዝቅኤልን አሳውሮ ገደል እየከተታቸው ያለው፡፡ እነሱም ያሣዝናሉ፡፡ ቀድሞ አለመለከፍ ነው እኮ እናንተዬ፡፡

2.    አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ወጥቷል አሉ፡፡ በዚያ ፍኖተ ካርታ አማርኛ ቋንቋ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች በሁሉም ክልሎች እንደሚሰጥ ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ እንደ አማራ እኔን አስደንግጦኛል፡፡ መሆን የሌለበትና የአክራሪዎችን ፍላጎት ያላገናዘበ ነው፡፡ “የበላችው ያስገሳታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሳታል” እንደሚባለው ለዚህ ለተገፋ የአማራ ሕዝብ ሌላ ችግር የሚፈጥር ነገር ነው፡፡ እነሕዝቅኤልንና ጃዋርን የመሰሉ “የሀገር መሪዎችን” አናት ላይ አስቀምጦ የፈለገውን ያህል ጠቃሚ ሃሳብ ቢሆንም ይህን መሰል ድፍረት ማሳየት ለቅጽፈት ነው፡፡ ይሄውና ከትግራይ ጫፍ እስከ ወለጋ ጫፍ እየተሰማ ያለው ሮሮም የዚሁ ደምብ ውጤት ነው፡፡ በደናቁርትና በዕብዶች በተሞላች ሀገር ውስጥ እንዲህ ያለ ለ110 ሚሊዮን ሕዝብ ቤዛና መድኅን ሊሆን የሚችል መመርያ ማውጣት ስህተት ነው፡፡ ቢያንስ ጊዜው ገና ነው፡፡ መሆኑ ግን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደሀገር መቀጠል ካለባት አንድ የጋራ መግባቢያ አስፈላጊ ነው - ያ የጋራ መግባቢያ ደግሞ ኦሮምኛ ወይም ሱማሊኛ ወይም ጉራግኛ ወይም ሃዲይኛ… እንጂ ኪሱዋሂሊ ወይም ቤንጋሊ ሊሆን አይችልም፡፡ በአማርኛ ጥላቻ ያበዱ ሰዎች አብዛኛውን የፖለቲካ ልጓም በተቆጣጠሩበት ሁኔታ ይህን ደምብ ማውጣት እነሱን ብቻ ሣይሆን እኔን መሰል የዋሆችንም ቢያስደነግጥ ትክክል ነው፡፡ እነሱ የሚፈልጉት የጨረባ ተዝካር ዓይነት የኳስ አበደች ሀገራዊ ሁኔታን ነው፡፡ የነሱ ህልምና ምኞት ኢትዮጵያን ባቢሎን ማድረግ ነው፡፡ ግን በሁለት ተቃራኒ ዓለማት ተሰንቅረው የሚሰቃዩም ይመስሉኛል፡፡ ለሥልጣንና ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሲሉ ኢትዮጵያን ይፈልጓታል፡፡ አማራን ስለሚጠሉ ደግሞ የኢትዮጵያን ኅልውና አይፈልጉም፡፡ ግራ ተጋብተው ግራ አጋቡን፡፡


ጃዋርና ጃዋራውያን እንግሊዝኛንና አማር|ኛን አጣርተው ይናገራሉ፡፡ በዚህም ተጠቀሙ እንጂ አልተጎዱም፡፡ አንድ ኃይል መጥቶ “ የምትጠሉት ከሆነ እንግዲያውስ ይህን ቋንቋ ከአእምሯችሁ ጓዳ እሰርዛለሁ!” ቢላቸው ተንበርክከው እያለቀሱ ይለምናሉ፡፡ አንድ ሰው የሚጠቀምበትን ነገር ሌላ ሰው እንዳይጠቀምበት መከልከል ደግሞ ንፉግነትና የለዬለት ምቀኝነት ነው፡፡ በመሠረቱ ከ87 ሀገራዊ ቋንቋዎች መካከል ይሰጠው በነበረውና አሁንም እየሰጠ ባለው አገልግሎት ምክንያት አማርኛን ከሌሎች ለይቶ የሀገሪቱ ዜጎች እንዲያውቁት ማድረግ እሰየው የሚያስብል እንዲያውም ዘግይቷል የሚያሰኝ እንጂ እንደዚህ ቡራ ከረዩ የሚያስብል አልነበረም፡፡ እነሱ ራሳቸው አማራ ከሚባለው የሚጠሉት ዘር እንዳልተወለዱና ቋንቋውንም ጥርት አድርገው እንደማይናገሩ የተልእኳቸው አንዱ አካል አማራንና አማርኛን ማጥፋት ስለሆነ ብቻ እየሠሩት ያሉትን የዕብድ ሥራ ይሠራሉ፡፡ በየትም ሀገር ያልተመዘገበ ዕብደት በመሆኑ ጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ቢመዘግበው ደስ ይለኛል፡፡ ኢሬቻና አሸንዳየን ከማስመዝገብ ይልቅ ይሄኛው ይመዝገብልን፡፡ የትግራዮቹ ማፈሪያዎች የሰጡት ተቃውሞ ደግሞ ያስቃል፡፡ “አማርኛና ትግርኛ ስለሚመሳሰሉ ልጆቹ ይደነጋገራሉ፡፡” ብለዋል አሉ፤ ጉድ ያለው ገንፎ አድሮ ይፋጃል፡፡ ይህን ፍኖተ ካርታ የነደፉ ሰዎች የቸገረ ቢቸግራቸው እንጂ ለአማራ ወይም ለአማርኛ ባላቸው ፍቅር አይደለም ለአማርኛ ቦታ እንዲሰጠው ያደረጉት፡፡ የቋንቋን ጥቅም እንዳለማወቅ የመሰለ ድንቁርና የለም ወገኖቼ፡፡

3.    ሰሞኑን ጠ/ሚንስትሩ የተገኘበት አንድ የምሁራን ስብሰባ ነበር አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መቼስ ማፈሪያው እየበዛ ተቸግረናል፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ አንዱ አሻቃባጭና እወደድ ባይ “ምሁር” ይነሳና “ላለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ መሪ አልነበራትም፡፡ አሁን መሪው ሲገኝ ሕዝብ በተራው ጠፋ፡፡” ይህ አነጋገሩ ጠ/ሚኒስትሩን በቁም የሚገድል ነው፡፡ በሀገራችን እየተሠራ ያለውን የዘር መድሎና በአንድ ነገድ ላይ ያነጣጠረ የዘር ፍጅት ለምንከታተል ወገኖች የዚያ ምሁር ተብዬ አሽቃባጭነት ለሀገሪቱም ለሕዝቡም ለጠሚው ለራሱም ትልቅ ስድብ ነው፡፡ ሰዎች በስብሰባዎችና በማኅበራዊ ግንኙነቶች ወቅት የሚናገሩትን ነገር በደምብ ቢያስቡበት ለእንደዚህ ዓይነት ውርደትና ቅሌት አይዳረጉም ነበር፡፡ ከመናገራችን በፊት ደጋግመን ብናስብ ይልበጥ ተጠቃሚዎቹ እኛው ነን፡፡

4.    እነጃዋር አማርኛን ባለመናገር ይተባበሩን፡፡ እነሱ በአማርኛ በተናገሩ ቁጥር በሀፍረት እየተሸማቀቅሁ አለቅሁ፡፡ የነፍጠኛ ቋንቋ፣ የቅኝ ገዥ ቋንቋ፣ የሚጠሉትን ሕዝብና ሀገር ቋንቋ እየተናገሩ ሥነ ልቦናቸውን መጉዳት የለባቸውም፡፡ ዓለማችን የማንም ያልሆኑና ማንም በባለቤትነት የመጠየቅ መብት የሌላቸው ከሰባት ሽህ አንድ መቶ በላይ ቋንቋዎች አሏት፡፡ እነዚህ ዕብዶቻችን የያዛቸው በሽታ እስኪወስዳቸው ድረስ አማርኛን ሳይጨምር ከነዚያ ልሣናት ለምሣሌ እግሊዝኛን ወይ ዐረብኛን መጠቀም ይችላሉ፡፡ አማርኛን ግን በሚወዱት ይሁንባቸውና ይተውልን፡፡ አማርኛን የሚጠላ ሁሉ በዚህ አጋጣሚ ከጭንቅላቱ እንዲያወጣው በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ የምትጠላውን ነገር አለመጠቀም ይመረጣል፡፡ ኦሮምኛን የሥራ ቋንቋ ማድረግ ከተፈለገ ደግሞ ይቻላል፡፡ አማሮችንና አማርኛን ከማሰቃየት በደፈናው ፓርላማን ሰብስቦ በአንድ ጭብጨባ መወሰን ነው - የኛ ዕንቅልፋም ፓርላማ ደግሞ በዚህ አይታማም፤ በቃ፡፡ ከዚያም እንዳመጣብን እኛ ሽማግሎቹም ብንሆን ተምረን “አካም ቡልቴ ነጉማ” ማለት አያቅተንም፡፡ … ነገ ጧት የምናፍርባቸው ብዙ ዝግንትል ቅሌቶች አሉ(ብ)ን፡፡
5.    ይሄ “አዲስ አበባ የማን ናት?” የሚሉት የጅሎች ጥያቄ ደግሞ ያስገርማል፡፡ ለመሆኑ “ናይሮቢ የማን ናት?” “ቡዡምቡራ የማን ናት?” “ሆኖሉሉ የማን ናት?” “ኒውዮርክ የማን ናት?” “ዋሽንግተን ዲሲ የማን ናት?” ሲባል ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? ምን ዓይነት ገልቱነት ነው ወደ ሀገራችን የገባው? ለኬ እውነቱን ነው “ና አልመታህም” ቢለው “ ‹ና አልመታህም›ን ምን አመጣው?” ብሎ አጥብቆ የሸሸው - አንዱ፡፡ ይሄ ጅልነታችንስ ያስጠላልና እንተወው፡፡ ለሰሚም ግራ ነው፡፡ “ይህች መኪና የማን ናት?” “ያ መኪና የማን ነው?” “ያቺ ቆንዦ የማን ምሽት ናት?” ቢባል ያስኬዳል፡፡ የሚሊዮኖችን መኖሪያ የማን ነው ብሎ መጠየቅ? ከዚያም በሚቃረኑ መልሶች እሰጥ አገባ ውስጥ ገብቶ በከንቱ መጨቃጨቅና ሥራ መፍታት? አሻ! ይህንን ዘመንስ ከአምስት ዓመታት በላይ ኮማ ውስጥ እንደከረመው ኤሪየል ሻሮን በሰመመን ማለፍ ነበር! ኢትዮያ ስትነሳ ደግሞ መነሳት፡፡ ይሄን ዕድል ማን ያገኘዋል!

6.   “የጨነቀው እርዝ ያገባል” ይባላል፡፡ የባሰበትም እመጫት፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወያኔዎችና የነሱ ፍጡራን የሆኑ “-ፓ”ዎች ወዳስኮረፉት ሕዝብ ልብ የገቡ እየመሰላቸው በዓላትን በከፍተኛ ወጪ በድምቀት ማክበርና በዩኔስኮና በመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ኹነቶችን መዝጋቢ ድርጅቶች ማስመዝገብን ሥራየ ብለው ተያይዘውታል፡፡ ይሄ ማስመዝገብ የሚሉት ፈሊጥ ደግሞ ቅጥ አምባሩ እየጠፋ ነው፡፡ የውሸት ሣቁንም፣ ዕንቅልፉንም፣ የከንፈርና ጆሮ ትልትሉንም፣ የመጠጥ ገልባጭነቱንም፣ የምግብ አግበስባሽነቱንም፣ አጭርና ረጂም ቁመቱንም… ምኑንም ምኑንም መመዝገብ የለመደው ጊነስ ቡክ ይሁን ዩኔስኮ የኛንም ኢሬቻ ሊመዘግብ እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ መመዝገብ መቼም አይሰለቸውም፡፡ አስመዝጋቢው ካላፈረ መዝጋቢው አያፍርምና የመሽኒያችንንም መጠን ትልቅነትና ትንሽነት ከነወርድ ስፋቱ መዝግብልን ካልነው ይመዘግባል፡፡ ፈረንጅ ምን ገዶት! እያሾፈብህ ይመዘግብልሃልኝ - ሊያስቅብህ፡፡

የሆኖ ሆኖ እነዚህ አሸንዳየና ኢሬቻ የሚሏቸው ነገሮች እጅግ እየተጋነኑ ነው - ለጤና አይመስልም፡፡ በሀገራችን ሁሉም ነገር ወደ ፖለቲካነት እየተለወጠ (politicized, even over-politicized እየሆነ) ብዙ ነገር በ“እነሱ”ና በ“እኛ” መካከል በሚፈጠር ቅራኔ ስለሚወጠር ችግሮች እየተባባሱ ነው፡፡ ከፖለቲካ ውጪ መኖር አልቻልንም - የሀገራችን ፖለቲካ ደግሞ ከሌሎች ሀገሮች በባሰ የዮሐንስ ራዕዩ 666 ሆኖብናል፡፡ ከፖተለክን እንኖራለን - ካልፖተለክን አንኖርም ወይም አነስ ሲል መኖር ይቸግረናል፡፡ የጭንቀት ዘመን፡፡ፖለቲካ ደግሞ የፖለቲከኞችን ጥቅምና ፍላጎት እንጂ ሀገር አያውቅም፡፡ ሃቀኛ ፖለቲከኛ ሆድ እንጂ ሀገር የለውም፡፡ የሥልጣንና የዝና፣ የሀብትና የገንዘብ ፍቅር እንጂ የወገንና የሀገር ፍቅር አለው ተብሎ እምብዝም አይገመትም፡፡ በመሆኑም አንድም ቀን ተወስተው የማያውቁ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ዕሤቶች ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል እጅግ እየተጋነኑ ሥራ አስፈቺ እየሆኑ ነው፤ መንገድ በመዝጋትም የጉዞ መጨናነቅን በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡ ብዙ ወጪም አላቸው፡፡ የሀገሬ ሙስሊም “ሸርተት ያረጋቸውና ሸሬላን ያበዛሉ” ይላል፡፡ ማሰብ ቀድሞ ነው፡፡ መጥኖ መደቆስም ቀድሞ ነው፡፡ አሁን ሁሉ ነገር ከመስመር ከወጣና ከተበለሻሸ በኋላ አሸንድየና ሶለል ቢሉት፣ በጣዖታዊ የግምባር ላይ ደም ቅብ የዛፎችን ቆሌ ባዲገዝ ቢለማመኑ፣ በጨምበላላ ሰበብ መስክ ላይ ቢያረግዱ ዋጋ የለውም፡፡ ሀገር የሚተዳደረው በዕውቀትና በጥበብ እንጂ በስሜትና ውዥንብርን በማስፈን በሚከሰት ግርግር አይደለም - ግርግር ለቀጣፊ ብቻ ነው እሚመች፡፡

ከዚህ በተያያዘም ኢሬቻን በአዲስ አበባ ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁን እየሰማን ነው፡፡ በግሌ ደስ ይለኛል፡፡ የወንድሞቼ በዓል የራሴውም ነው፡፡ ከ150 ዓመታት በፊት እዚህ አዲስ አበባ ይከበር ነበር ተብሏል፡፡ መረጃ አላየሁም፡፡ ይሁን እንመነው፡፡ ግን ለምን አሁን? አሁን ምን ተገኝቶ ነው ከደብረ ዘይት ወደ አዲስ አበባ ሊዛወር የቻለው? ገና ለገና ኦህዲድ/ኦዴፓ/ኦነግ ሥልጣን ስለያዙ? በዓሉ ሲከበርስ ውኃው ከየት ሊመጣ ነው? ጊዜያዊ ኩሬና ሐይቅ በመስቀል አደባባይ ለመሥራት ታስቦ ይሆን? የሰውን ልጅ ከንቱነትና ተመፃድቆ ሳስበው ግርም ይለኛል፡፡ ያቺን የተማሪውን ደብተር የምታበለሻሽ መጨረሻዋ ግን ያላማረ ኮራጅ ጦጣ ታሪክ አስታወሳችሁልኝ? የዚህን ኦሮሟዊ ፖለቲካ ጉዞ መጨረሻ ማየት ናፍቆኛል፡፡ ደግነቱ በቅርብ ሩጫውን የሚጨርስ ይመስለኛል፡፡ “ካነጋገር ይፈረዳል፤ ካያያዝ ይቀደዳል፡፡” ይላል ብሂሉ፡፡ የፖለቲካው ነጸብራቅ የሆነው የኑሮ ውድነቱ ብቻ ኦህዲድን በታትኖ ይጥለዋል፡፡ “ቱ!” ‹ምሕረት ምን አለ!› በሉ፡፡

በመሠረቱ አንድን ነገር ማድረግ ስለቻልክ ብቻ አታደርግም ወይም አታድርግ፡፡ እንደዚያ ከሆነ ከምክንያትና ከዕውቀት ወጥተህ የስሜትህ ተገዢ ሆነሃል ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል ኒውስዊክ መጽሔት ላይ ያነበብኩት አንድ ጽሑፍ አሁን ትዝ አለኝ፡፡ ጋዜጠኛው ሣይንቲስቱን እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል - “ወንድን ወደ ሴት ለውጦ እንዲወልድ ማድረግ ይቻላል ወይ?” ሣይንቲስቱም እንዲህ ሲል መለሰ “አዎ፣ በትክክል ይቻላል፡፡ ግን ለምን? ምን አስገደደንና እንዲህ እናደርጋለን? ሴቶቻችን ‹እምቢዬው፣ አንወልድም› ቢሉን ግዴለም ይሁን ይባላል…”፡፡ ሌላም የቅርብ ጊዜ ታሪክ ትዝ አለኝ፡፡ ቻይና ኅዋ ውስጥ በ800 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የነበረቻትን ሣተላይት “አሜሪካንን ሳታስፈቅድ” ከምድር ወደ ሰማይ በሚወነጨፍ ሚሣይል አደባየቻት፡፡ በቻይና የ‹ፐርፌክሽን› ጥበብ ዓለም ጉድ ተሰኘ፡፡ አሜሪካ ግን አበደች፡፡ የውሽማ ሞት አስተኔ ሆነባት - አያለቅሱት ወይ አይተውት፡፡ እናም አለች - “ክብርት ቻይና ሆይ! እንደዚያ ማድረግ እንደምትችይ እናውቃለን፤ ማወቃችንንም እንደምታውቂ እናውቃለን፡፡ እናም ይህን አሁን ለምን እንዳደረግሽ ማብራሪያ እንድትሰጭን እንፈልጋለን፡፡” አያድርስ እኮ ነው! ቻይኒትም ጊዜ አልፈጀችም፡፡ እንዲህ ስትል ወዲያውኑ መግለጫ አወጣች፡፡ “ቺን ቺንጓም ቹ ቻይኗቹኑንሃም ዱምቹንግ አሜሪክቹም ዱችኑግ ቺን ቿ…” በእንግሊዝኛው አሸንዳ አልፎ ወዳማርኛው ሲተረጎም “ ይህ የቻይና እንጂ የአሜሪካ ጉዳይ ስላልሆነ ምንም ዓይነት ማብራሪያ ለማንም አንሰጥም፡፡ ‹ሥራ ፈቶች!›”፡፡ ቻይንኛ ይችላል ብላችሁ ደግሞ አሟርቱብኝ አሉ፡፡ ሲያምረኝ ይቅር፡፡ በእግረ መንገድ ግን ማድረግ መቻልን ለማሳወቅ የሚኬደውን ርቀት መገንዘቡ አይከፋም እላለሁ፡፡ ቻይናና ኦነግ ማነው ኦህዲድ ግና ሲመሳሰሉ!

“ዘራፍ እኔ ወንዱ!
የሞተ ፈረስ ጋላቢ፤
የደረቀ ወንዝ ተሻጋሪ፤
ትኋን ገዳይ በርግጫ፤
ቁንጫ ገዳይ በጠበንጃ...
ዘራፍ ዘራፍ እትትትት....” እያለ የሚፎክር አጎት ነበረኝ፡፡

ደስ ሲል! በሞተች ሀገር ላይ የፈለጉትን ቁማርና ሰኞ ማክሠኞን መጫወት ማን ያቅተዋል? ወያኔስ በተንጋለለችዋ ኢትዮጵያ ከሩቅ የሚገማ ሰይጣናዊ የመርገምት ሽንቱን ሲያርከፈክፍባት 27 ዓመታትን ዘልቆ የለምን? ቀን ነው፡፡ ለሁሉም ቀን አለው፡፡ ቀን ይሰጣል፤ ቀን ይነሳል፡፡ ቀንን በአግባቡ አለመጠቀም ግን ሞኝነት ነው - ከሞኝነቶች ሁሉ ላቅ ያለና በኋላ የሚያስቆጭ ሞኝነት ለዚያውም፡፡

ኢሬቻ መስቀል አደባባይ ይቅርና አንዋር መስጊድና ሥላሤ ካቴድራል ውስጥም ይከበር ቢባል ዕድሜ ሁሉንም ሥልጣን በእጁ ላስገባው ኦነግ ማለትም ኦዴፓ የማይቻለው ነገር የለም - ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እኚህ ሁለትም አንድም የሆኑ ድርጅቶች ያምታቱኛልኝ፡፡ እንግዲህ ይህንና ከዚህም በላይ ማድረግ መቻሉ ከታወቀ ያን በዓል በተለመደበት ቦታ ቢያከብሩ ከትዝብት ይድናሉ ባይ ነኝ፤ የሀገርን አድባር እስከዚህ እየተዳፈሩ መፈታተን የኋላ ኋላ መዘዝ አለው፡፡ መዘዝም ባይኖረው ከፍ ሲል እንደገለጽኩት በቀትረ ቀሊልነት ያስፈርጅና ለትዝብት ይዳርጋል፡፡

“ሸማ በየፈርጁ ይለበሳል” ይባላል፡፡ አማረብኝ ብለህ በሱሪህ ላይ ቡታንታህን አጥልቀህ ቢሮ አትገባም፡፡ አሳዳሪው ነኝ ብለህ አሽከርህ ጭንቅላት ላይ አትጸዳዳም፡፡ ነውርም፣ ኃጢኣትም፣ ወንጀልም ነው፡፡ ልክህን ማወቅ ብልኅነት ነው፤ ጥፋትህን ሰው ላይነግርህ ይችላል - በመፍራት ወይም በማክበር ወይም በይሉኝታ ወይም ሥራህ እንዲያጋልጥህና በጊዜ ሂደት እንድትዋረድ ብሎ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሣ ሰዎች ጉድህን ላይነግሩህ ይችላሉ፡፡ አንተ ግን ጎበዝ ሁንና ደካማና ጠንካራ ጎንህን ዕወቅ፡፡ ከዚያም ለራስህ ቀይ መስመር አብጅ፡፡ ሰዎች ቀይ መስር እስኪያበጁልህና እስኪያዋርዱህ አትጠብቅ፡፡ ደግመህ ላታገኛት የምትችላትን ፀሐይህን በቅጡ ተጠቀምባት እንጂ አታባክናት፡፡

ታውቃለህ - አክሱም ጽዮን የምትከበረው በለመደባት በአክሱም ነው፤ ግሸን ደብረ ከርቤ ስትከበር የሚያምርባት በግሸን ተራራ ላይ ነው፤ ቁልቢ ገብርኤል ሲከበር ደስ የሚለው በቁልቢ ነው (ነፍስ ይማር ኦነግ እንዳስገደላቸው የተነገረላቸው የደብሩ አበምኔት)፡፡ አየህ - “አባት ሳለ አጊጥ፣ ጀምበር ሳለ ሩጥ” የሚለውን ብሂል አለወጉ መተግበር ቢያንስ የትዝብትን ዕዳ ያስከትላል፡፡ በዚህች የኦነግ ውሳኔ ከንፈሩን ያላንሻፈፈና አፉን በመዳፉ አፍኖ ያልሳቀ አሽሟጣጭ ቢገኝ እቀጣለሁ፡፡ አይ… እውነቴን ነው… ይች ፍየል ከመድረሷ… ዓይነት ነገር በዛች፡፡ ታላቁ የኦሮሞ ሕዝብ በዚህ አይታወቅም፡፡ ኢትዮጵያን በንግሥናም ይሁን በፕሬዝደንትነትና በጠ/ሚኒስትርነት ከሌሎች ወንድምና እህቶቹ ጋር ኢትዮጵያን እየገዛና እያስተዳደረ እዚህ ያደረሰ ኦሮሞ ዛሬ ገና ሥልጣን ላይ እንደወጣ ለማስመሰል የሚደረገው የደምባሮችና የአክራሪዎች ሩጫ ሊገታ ይገባዋል፡፡ የልጆች ጨዋታ አታድርጉት፡፡ እዚህ ሊነገሩ የማይገባቸው ብዙ ነውሮችን የሚፈጽሙ ጊዜ ሰጠን ያሉ ኦነጎችና ኦህዲዶች አሉና ሃይ ይባሉ፡፡ ዕዳ እያከማቹ መሆናቸው ይነገራቸው፡፡ ዕዳውን ደግሞ እነሱ ወይም ቀጣይ ትውልዳቸው የሚከፍለው እንጂ አየር ላይ ተንሣፍፎ የሚቀር አይደለም፡፡ ለሁላችንም አስተዋይ ልቦና ይስጠን፡፡
Posted at Ethio Semay

Tuesday, August 27, 2019

የኦሮሞ ልጆች የጫካ አገዛዝ ሕግ እና እናቶች በፖሊሶች የመደብደብ ጉዳይ ጌታቸው ረዳ የኢትዮ ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ 08/27/2019


የኦሮሞ ልጆች የጫካ አገዛዝ ሕግ እና እናቶች በፖሊሶች የመደብደብ ጉዳይ
ጌታቸው ረዳ የኢትዮ ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ
08/27/2019
ርዕሱ አሁን ለሚገዛን  ሥርዐተ አልባው የኦሮሞዎቹ ሥርዓት እንደሚስማማ ሰየምኩት እንጂ ርዕሱ “የጫካ ልጆች የአገዛዝ ሕግ” በሚል ርዕስ እንደ አገራችን ዘመን አቆጣጠር በ1995 ዓ.ም በገጽ 13 “ዜጋ” በሚባል መጽሔት አዲስ አበባ ካሳተምኩት ጽሑፌ የወሰድኩት ነው።

ይህ ተመሳሳይ ርዕስ የወሰድኩበት ምክንያት በጠቀስኩት አመተምሕረት አዲስ አባባ ከተማ ውስጥ በልደታ ቤተክርስትያን ምእመናን እና በወያኔው ፓትርያሪክ መካካል ከሕዳር 9/1995 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጠረ ውዘግብና ግጭት አስመልክቶ የታየው የፖሊሶች ጭካኔ በማመሳሰል ትናንት አንድ ወዳጄ አንድ የጠገበ የአብይ አሕመድ የአዲስ አበባ ፖሊስ አንዲት አዛውንት ከልጃቸው ጋር ያለ ምሕረት እንደ አውሬ ምድር (እባብ) ራስ ራሳቸውን በዱላ ሲቀጠቅጣቸው የሚያሳይ ቪዲዮ ስመለከት ከላይ የጠቀስኩትን በልደታ ቤተክርስትያን ውስጥ የወያኔ ፖሊሶች (በ1995) ያሳዩት የጭካኔ እርምጃ በእኚህ አዛውንት እናት ላይ ያየሁት ግፈኛ ዱላ ስለታወሰኝ ርዕሱ እና ድርጊቱ ተመሳሳይ ሆኖ በማግኘቴ  “የጫካ ልጆች የአገዛዝ ሕግ”  ከሚለው ጽሑፌ በመውሰድ “የኦሮሞ ልጆች የጫካ አገዛዝ ሕግ እና እናቶች በፖሊሶች የመደብደብ ጉዳይ” (አብይ/ኦነግ)” ብየ ርዕሱን ለወጥ አድርጌ ተጠቅሜበታለሁ።


መጀመሪያ ትናንት አዲስ አባባ ከተማ በአንድ ጥጋበኛ የአብይ አሕመድ ፖሊስ ባልደረባ በእናት አዛውንት እና በልጃቸው ላይ ያወረደው በጫካ ሕግ የተመራ አስነዋሪ የድብደባ ግፍ ከመተቸቴ በፊት በ1995 ዓ.ም የታየው የልደታ ቤተክርስትያን ምዕመናን እና የጫካ ልጆች (የወያኔ) ፖሊስ ግፍ በመዘርዘር ሁለቱም ተመሳሳይነታቸውን ለማሳየት በመጀመሪያ ስለ ልደታ ምዕመናን ምን እንደተደረገ ላስታውሳችሁ። ከዚያም ወደ ዛሬው ወደ ኦሮሞዎቹ አስተዳደር እንመለከታለን።

ወደ ዝርዝሩ ከመግባቴ በፊት ባጭሩ የጭቅጭቁ መነሻ በሕዝቡ የተወደዱ እና የተከበሩ የልደታ አስተዳዳሪ የነበሩት ተነስተው በወያኔ ካድሬ አስተዳዳሪ ለመተካት (ከምክንያቶቹ አንዱ) በሃገረ ስብከት ጽ/ቤት እና በአባ ጳውሎስ (የወያኔ ፓትርያሪኩ) ትዕዛዝ ሲተላለፍ የልደታ ምዕመናን ውሳውን ፖለቲካዊ በመሆኑ አንቀበልም ብለው ተቃውሞ ባመሰማታቸው የወያኔው ፓትርያሪኩና የመለስ ዜናዊ አሽከር ፖሊሶች የደረጉትን ጭካኔ ባጭሩ እንዲህ ነበር።

መሳሪያ የታጠቀ ሃይል ቤተክርስትያኒቱን ወረራት። እንደ አንድ የጣሊያን ወራሪ ጠላት ወደ ውስጥ ቤተ መቅደሱ በመግባት በእናቶች እና አዛውንቶች ላይ ብትር መሰንዘር ጀመሩ። ሕዝቡ ለጸሎት አብርቶ  ይዞት የነበረውን ቅዱስ ጧፍ  እንደያዘ ነበር በፖሊስ ብትር እየተደበደበ ከቤተክርስትያኒቱ እንዲወጣ የተደረገው። ያ እንዳይበቃ ወታደሮቹ እየተንደረደሩ በእርግጫ እና በቆመጥ እየደበደቡ ሕዝቡን ከመሬት ላይ እየጣሉ በጫማቸው እየረገጡ ይደፈጥጡት ነበር። ከዚያ በላ ነበር ዜጋ በተባለው ወርሓዊ መጽሔት ላይ ያንን ዜና ስሰማ “የጫካ ልጆቹ የአገዛዝ ሕግ” በሚል የጻፍኩት።

በዚያ ጽሑፌ ላይ ትንሽ ላስታውሳችሁ። የጫካ ልጆቹ ሕግ ምን እንደሆነ ከታች እስከ ላይ ያሉት የሚመሩበት መመሪያቸው ጭካኔ እና ግፍ ስለሆነ ከተማ ላይ የሚፈጸሙት ግፍ አሁን ደግሞ የአማልከቶች ቤት ሳይቀር እንዴት እየደፈሩ እንዳሉ ተመለክቱ። ስል የሚከተለውን በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆና የቪ ኦ ኤ ዘጋቢ የነበረቺው  ሔለን መሓመድ ያስተላለፈቺውን ዘገባ ጥቅስ ባጭሩ ጠቅሼ የነበረውን ዘገባ ላስንብበቻሁ እና ወደ ሕግ አልባው የኦሮሞዎቹ የነ አብይ አሕመድ ፖሊስ ያደረገው ግፍ እንመለከታለን።

“ሕዝቡ መጮህ ጀመረ፤ እያለቀሰ ስሞታውን ያሰማል።ርክክቡ ከተፈጸመ በላ ሁኔታው የተረጋጋ መሰለ። ከጥቂት ደቂቃ በላ ብረት ቆብ ያጠለቁ፤ ጋሻ ያነገቡ ፖሊሶች ወደ ቤተክርሰትያኒቱ ቅጥር ግቢ በሁለት መርሰዲስ ተጭነው በመግባት ሕዝቡ ሳይሆን ፖሊሶቹ ፀጥታውን አደፈረሱት። ሁለት ስቪል የለበሱ ግለሰቦች አንድ 16 አመት የሚሆነው ታዳጊ ወጣት ጠምዝዘው ሲደበድቡት አይቻለሁ።

ወጣቱ ራሱን ለማዳንና ለማስለቀቅ በሚታገላቸው ጊዜ አንደኛው ፖሊስ ከወገቡ ሽጉጡን በማውጣት ጭንቅላቱ ላይ ከመደገኑ ባሻገር በሽጉጡ መያዣ ጭንቅላቱን ፈጠፈጠው። ሌሎች 6 ፖሊሶች ተጨምረውበት በአጠቃላይ ለ’8’ ሆነው ታዳጊውን ወጣቱን በአሰቃቂ  ሁኔታ ከደበደቡት በላ፤ከሌሎች መሰሎች ጋር በመኪና  ጭነው ወረዳ ሃያ ሁለት ፖሊስ ጣቢያ ወሰድዋቸዋል።” የሔለን መሓመድ ዘገባ ለቪ ኦ ኤ አዲስ አበባ”።

እንዲህ ነበር የወያኔ ፖሊሶች ጭካኔ እስከ ቤተመቅደስ ድረስ እየገቡ እናቶችን አረጋውያንን ህጻናትን ሲደበድቡ ታሪክ የዘገባቸው። ዛሬ ደግሞ ትናንት እንድ የቅርብ ወዳጄ የላከልኝ ቪዲዮ-ተመለከትኩ። https://www.facebook.com/100035912120492/videos/142737860266617/ ሁኔታው አዲስ አበባ “ዋርካ ትሬዲንግ ሃውስ” በሚል የንግድ በራፍ ላይ ሁለት የታጠቁ ፖሊሶች (ኦሮሞ ፖሊሶች እንደሆኑ በስፋት ተነግሯል) አንደኛው ጋጠ ወጥ ፖሊስ “ጦር ሜዳ” ያለ እስከሚመስለው ድረስ በያዘው ክለሽንኮቭ ጠመንጃ ጥይት ወደ ሰማይ በመተኮስ ጀግንነቱን ለማሳየት በባዶ ሜዳ ላይ እና ባዶ እጁ ሆኖ ቆሞ ሲመለከተው በነበረው የአካባቢው ተመልካች ሕዝብ ፊት እየተወጣጠረ በኩራት ሲንጎማለል ይታያል። አንደኛው ጋጠ ወጡ ፖሊስ ደግሞ አንድ ታዳጊ ወጣት በካቴና ሁለት እጁን አስሮ መሬት ላይ ጥሎ  በዱላ ሲነርተው አጠገቡ የቆሙት እናት የልጃቸውን ያለ ሕግ መደብደብ አንጀታቸው አላስችሎ በሎአቸው በመቃወም ከድብደባው ሊያስጡልት ሲታገሉ ‘ጋጠ-ወጡ’ ፖሊስ እሳቸውን በመዳፈር ገፍትሮ ሊጥላቸው እና ሊደበድባቸው ሲሚከር እሳቸውም ልጃቸውን ለማስጣል ሲታገሉ ጋጠ ወጡ ፖሊስ እኚህን አያቱን የሚያክሉ አዛውንት እንት ሲያንገላታቸው ይታይል።

በጣም የሚያስደንግጠው ትዕይንት ያልተገሩት እና ያልሰለጠኑት የአብይ አሕመድ የጫካ ልጆች የኦሮሞ ፖሊሶቹ ጋጠ ወጥነት ያስገረምን ሳይበቃ እዛው ቆመው አካባቢውን ዙርየውን ከብበው ይህ ግፍ እና ድብደባ ሲፈጸም ቆመው የሚመለከቱ በጣም በርካታ ጎልማሶች ፖሊሱን ከመቃወም እና ልጁን ከድብደባ ከማስጣል ይልቅ ልጃቸውን ከመሞት ለማዳን ሲታገሉ የነበሩትን እናት “በሃይል ጎትተው ከልጃቸው በማስራቅ” ፖሊሱ በልጁ ላይ ተጨማሪ ድብደባ እንዲፈጸምበት ለፖሊሱ ዕድል በመስጠት “ተባባሪ ሆነው” መታየታቸውን ኢትዮጵያውን ዜጎች የዘቀጡ አሳፋሪ ማሕበረሰቦች ሆነው ያየሁበት አጋጣሚ ነው።

በዜግች ግብር ተሰብስቦ ደሞዙን የሚከፍሉት ተቀጣሪ ፖሊስ አንድን ዜጋ በካቴና እጆቹን ጠፍሮ ሲደበድበው እና አዛውንት እናቶችን ሲደብድብ ከዚያም አልፎ እንደ ጀብድ ተቆጥሮ ጥይት ወደ ሰማይ እየተኮሱ ሰላማዊ ሕዝብን የሚረብሹ በአፍሪካ መዲና የሚታዩ የጫካ ፖሊሶችን መቃወም ሕዝቡ እንዴት ያቅተዋል። ታስታውሱ እንደሆን ከ26 አመት በፊት ሎስ አንጀለስ አሜሪካ ውስጥ “ራድኒ ኪንግ” የተባለ ጥቁር በፖሊሶች ተከብቦ መሬት ላይ ጥለው እጆቹን በካቴና አስረው ያለ ምሕረት ሲቀጠቅጡት በታየው ቪዲዮ የተነሳ ጥቁሮች በንዴት ተነሳስተው የሎስ አንጀለስ ማዕከላዊውን ከተማ የሱቅ እና ንግድ እንዲሁም መንግሥታዊ ህንጻዎችን አንዳለ በእሳት እንዳጋዩት ይታወሳል። እንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያውያን ለ28 አመት አንደ አህያ የለመድነውን ድብደባ ከምንም ሳንቆጥር አናቶች ሲደበደቡ ልጆቻቸው አብረው ሲደበደቡ እያየን ያለ መቃወማችን ምስጢሩ ዛሬም ሊገባኝ አልቻለም።

የትግሬዎቹም ሆነ የኦሮሞዎቹ አፓርታይድ አገዛዝ አዲስ አባባ እና አካባቢዋ ጋጠወጥ ፖሊሰቻቸው አስማርተው አዲስ አባባን ልክ እንደ ሞንሮቪያ (ላይቤሪያ) የጋንጎች (ሞብ) አስተዳደር ሕዝቡ በስርዓተ አልባ ዘራፊዎች እና በሕጋዊ ታጣቂ ፖሊሶች እየተረበሸ የሰቀቀን ኑሮ እያሳለፈ ነው። ከሦስት አመት በፊት ኦሮሞ “ክልል” ውስጥ አንዲት አዛውንት  እናት ፖሊሶች ልጃቸውን ገድለውባቸው ሲያበቁ እናትየዋ በልጃቸው ሬሳ ጎን ቁጭ ብለው ሲያለቅሱ ማልቃሳቸው የተመለከቱ ጋጠ ወጥ ኦሮሞ ፖሊሶች እናትየዋን በዱላ መደብደባቸውን በ ቪ ኦ ኤም ሆነ በራሴው ባሳተምኩት መጽሐፍ በሰፊው በታሪክ የተመዘገበ ነው። ዛሬም በአፓርታይዱ አብይ አሕመድ ዘመን እናቶች በፖሊሶች መደፈራቸውን እና መደበብደባቸውን አልቆመም። አሳዛኙ ግን ተቃዋሚው እና ኗሪው ይህንን ግፍ እየተመለከተ አይቶ አንዳለየ የመሆኑ አስደንጋጭ እና አስገራሚ ምስጢር እንዴት እንፍታው? ፔቲሽን ማዘጋጀት የምትችሉ ሰዎች እባካችሁ ይህንን ግፍ ለአዲስ አበባ ፖሊስ እና ፍትሕ አሰፍናለሁ ብላ ለምታወራው የአብይ አሕመድ የፍትሕ ሚኒሰትርዋ ወ/ሮ ማዓዛ አሸናፊ ጽ/ቤትዋ ድረስ የተቃውሞ ደብዳቤ በመጻፍ በሁለቱ ፖሊሶች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው አቤቱታችንን እንላክ።ይፈጸማል ወይ? ያ ሌላ ጉዳይ ነው። ግን ለታሪክ እናስመዝግብ። ሁላችንም የየበኩላችን ትንሽ ትንሽ ብንሰራ ግፉ እንዲህ ስር አይሰድም ነበር። በተልይም በፌስ ቡክ ያላችሁ እህቶችና በሴቶች መብት ቆመናል ለምትሉ የሴቶች ማሕበሮች የእናቶችን ግፍ ማስቆም ይጠበቅባችሗል። አብረን እንጩህ ! ድማጻችሁን አስሰሙ!! ቪዲዮውን ለመመልክት ይህንን በፌስ ቡክ የተለጠፈውን ይመልከቱ።
አመሰግናለሁ ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ Ethio Semay)          




Tuesday, August 20, 2019

ትንቢትን በሤራና በግድያ ማስቀረት አይቻልም! ትንቢቱ ደረሰ (ከአዲስ አበባ) Posted at Ethio Semay


ትንቢትን በሤራና በግድያ ማስቀረት አይቻልም!
ትንቢቱ ደረሰ (ከአዲስ አበባ)
Posted at Ethio Semay
የባህር ዳሩን የአማራ ባለሥልጣናት ጭፍጨፋ አስመልክቶ ሄኖክ የሽጥላ በዩቲዩብ ያቀረበውን ሀተታ ተከታተልኩ፡፡ እነአቢይና ወያኔዎች ይህን ግድያ ማቀነባበራቸውን በፊትም የምንጠረጥረው ነገር ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደተገለጸው የአማራ ጠላቶች እጅግ ከመብዛታቸውም በተጨማሪ አንዳንድ ወፍዘራሾች “ከናካቴው የለም” የሚሉትን ይህን ጎሣ በማጥፋት ረገድ ሁሉም ይተባበራሉ -- እነሱ ራሳቸው የማይስማሙና እንደዐይጥና ድመት አጥፊና ጠፊ  ሆነውም ቢሆን - ቤንዚንና እሳት ሆነውም ቢሆን በአማራ ላይ ያላቸው አቋም ግን አንድ ነው - ይህንን የኢትዮጵያ አለኝታ ነገድ ከሥሩ መንግሎ ማጥፋት፡ - ትልቅ ምክንያትም አላቸው - እርሱ ወደ ሥልጣን ከመጣ እንደልባቸው የሚዘባነኑበት በሙስናና በዘረፋ የሚገኝ የሀገር ሀብት፣  ለየደናቁርት የጎሣ አባሎቻቸው እንደገና ዳቦ እንዳፈተታቸው የሚያቃርጡት የይስሙላው የፌዴራል ሥልጣን አይኖርም፤ “ወርቃማ ጊዚያችን ይህች ናት!” ብለው ስለሚያምኑ ይህን የኳስ አበደች ዘመን በፍቅር ይወዱታል - በዚህ ዘመን የሚመጣባቸውን ሁሉ ግም ለግም እየተረዳዱ “አንድ ሰውና አንድ ጥይት” እስኪቀራቸው ይዋጉታል፡፡ ለዚህም ነው “በህገ መንግሥታችን አንደራደርም” በሚል እንደ አሠርቱ ትዕዛዛት ጉያቸው ውስጥ ወትፈው ያን ከሽንት ቤት ወረቀትነት ያነሰ ዋጋ ያለውን ሕወሓታዊ ሠነድ ጣዖታዊ ቤተ መቅደሳቸው ውስጥ አኑረው የሚፎክሩበት፡፡

 አማራ ካልጠፋላቸው ዕንቅልፍ የሚባል በዐይናቸው አይዞርም፡፡ እነዚህ የአማራ ጠላቶች የትግራይ ወያኔዎችና የኦሮሞ ኦነጋውያን ናቸው፡፡ እነዚህን የሚያሰማሩ የአዲሱ ዓለም ሥርዓት አዋላጅ የሆኑት ኢሉሚናቲዎችም መዘንጋት የለባቸውም (The so called  Illuminati who are by now at the(ir) peak to form the New World Order after destroying nearly 80% of the world’s population....)፡፡ እነዚህን ፍናፍንት ዜጎች በአማራ ጠላትነት እያነሳሱና እያደራጁ፣ በበጀትና በዘመናዊ ጦር መሣሪያም እያጠናከሩ፣ ዘመናዊ የሣተላይት መረጃ እየመገቡ በኢትዮጵያ ላይ ጃዝ ብለው ይለቋቸዋል፡፡ ይህም ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ የፈዘዝነውም ሆነ የተበታተንነው ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ አንድ ያልሆነውም ሆነ በትንሹም በትልቁም የምንንነታረከው ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ብዙ ሆነን ሳለ ጥቂት የሆንነው፣ ኃያል ሆነን ሳለ ደካማ የሆንነው፣ ሀብታም ሆነን ሳለ ድሃ የሆንነው፣ አንበሣ ሆነን ሳለ ከዝንጀሮም ያነስነው ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ይህን ካልኩ ዘንዳ የትንቢቱን ፍጻሜ ልንገርህ፡፡ የምታውቁትን ነገር እንደአዲስ በመቁጠር “ያበጠው ይፈንዳ” በሚል  ብሂል ቆዳየን አላዋድድም፡፡ እውነቱ ግን ይሄው ነው፡፡ ጠላቶችም መከራቸውን የሚያዩትና ከዳር እዳር ኅብረት ፈጥረው አማራንና የአማራን ብቸኛ መመኪያ ኢትዮጵያን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የሚራወጡት የመጨረሻውን ትንቢት እነሱም ስለሚያውቁና ያንን የማይቀር ትንቢት የቀለበሱ መስሏቸው ነው፡፡ ይህን እያስገመገመ በመምጣት ላይ የሚገኝን ገሃድ እውነት መናገር ድፍረት ሊመስል ይችላል፡፡ ግን ምንም ማድረግ አልችልም፡፡

አማራ ማንሠራራቱ ዕንቅልፍ እንደነሳቸው ገልጸናል፡፡ እነአሣምነው እየተጓዙበት የነበረው ሀገርን የመፍጠር እንቅስቃሴ እነአቢይንና አክራሪ ኦሮሞዎችን፣ አክራሪ ትግሬዎችን፣ ከየጎሣው ያሉ ሆዳምና ነቀዝ ዜጎችን በጠቅላላው ዕረፍት ነስቷቸው ነበር፡፡ ስለዚህም ያንን ግልጽ የግድያ ዘመቻ ካላንዳች ይሉኝታና ሀፍረት በመፈንቅለ መንግሥት ሰበብ ማካሄድ ነበረባቸው - ያ “ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ” የምንለው የኢሉሚናቲዎች ጭምብልም ከጎናቸው ስለሆነ ማንንም አይፈሩም፤ አያፍሩምም፡፡ “የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር” ይባላል፡፡ እነአቢይ የሚገድሉትን ሁሉ ከገደሉና መረጃ ካጠፉ በኋላ ያን ከእውነት የራቀ ነገር መደስኮራቸው በሕዝብ ንቃተ ኅሊና ላይ ጢባጢቤ ከመጫወታቸውም በላይ የነሱን ማይማዊ ዕብሪት አጉልቶ ያሳያል፡፡ አክራሪ ኦሮሞዎች በከሚሴና በቤንሻንጉል ጉሙዝ በኩል ሊሠሩት ያቀዱትንና የጀመሩትንም አማራን በጎጥና በሸንተረር የመከፋፈል እንዲሁም በሳል አመራር የማሳጣት እንቅስቃሴ እነአሣምነው ቀድመው ነቅተውባቸው ሊያከሽፉባቸው በመነሳታቸው በአማራ ልሂቃንና አመራሮች ላይ ያ ሁሉ ውርጅብኝ ወረደ፡፡ መሆን ስለነበረበት ነው የሆነው ብለን በአርምሞ እንቀበለዋለን፡፡ አንድ መሆን ያለበት ነገር ደግሞ ይዘገያል እንጂ ከመሆን አይዘልም፡፡ አሁን እንደምንሰማው ያ በአክራሪ ወያኔዎችና ኦህዲድ/ኦነጎች የተጠነሰሰ ዘመቻ “ዘመቻ ቅንጸላ” ይባል ነበር፡፡

ቅንጸላ ምን ማለት እንደሆነ በውል አላውቀውም፡፡እንደሚመስለኝ  ግን “ማምከን፣ ማስቀረት፣ መቀምጠል፣ ማጉደል፣ ማክሸፍ...” ሳይሆን አይቀርም፡፡ የአማራን ትንሣኤ ለማስተጓጎልና እስከወዲያኛው ለመቅበር የተደረገ ሙከራ እንደሆነ ወዲያና ወዲህ ከሚያቅነዘንዛቸው ዕረፍት ያጣ ተግባራቸው መገንዘብ ይቻላል፡፡ አሁን አሁንማ ይሠሩትን አጥተዋል፡፡

ይህ አማራን የማጥፋት ሁለገብ ዘመቻ በነአቢይ አህመድ ይመራ እንጂ አንዳንድ ሆዳም የብአዴን አባላትም የጥፋት ዘመቻውን መተባበራቸው የታወቀ ነው፡፡ ዱሮውንም ሆዳም ፍቅር አያውቅም፡፡ ሆዳም ሚስቱንም፣ ልጁንም፣ አባቱንም፣ እናቱንም ለገንዘብና ለጥቅም አሳልፎ ይሸጣል፡፡ ይሁዳ ጌታውን በ30 አላድ እንደሸጠ ሁሉ የባሰበት ሆዳም አማራም አማራን አይሸጥም ተብሎ አይታሰብም፡፡ የአማራ መከራ የበዛው የራሱ ልጆች ሳይቀሩ ከታሪካዊው ጠላቶቹ ጋር በመተባበር ለከርሳቸው ሲሉ ስለሸጡት ነው፡፡ ያለ ነው፡፡ ወደፊትም ይህን መሰሉ አስቀያሚ ክህደትና ሽርሙጥና አይቀርም፡፡ ዋጋቸው ግን በሠፈሩት ቁና ልክ ይሠፈራል፡፡ እንጂ ለክህደት ለክህደትማ እነክፍሌ ወዳጆንና ገነት ዘውዴን ማን ይረሳቸዋል?

ዘመቻ ቅንጸላ ያደረገውን አድርጎ ለጊዜው የተሣካ ይመስላል፡፡ በዚያም ምክንያት በአማራው አካባቢ አሁን ለጊዜው መፍዘዝ ይታያል፡፡ ግን በዚህ መልክ አይቀጥልም፡፡ ምክንያቱም ትንቢቱ ደርሷልና፡፡ ንግርት ቢዘገይ እንጂ አይቀርም፡፡

ይህ ነው ትንቢቱ፡፡ መጀመሪያ ከሰሜን የመጡ አንበጦች ኢትዮጵያን እንደተምች ይወሯታል፡፡ ወርረውም እስከ አጥንቷ ይግጧታል፡፡ መሣሪያ ከትከሻቸው የማይወርድ እረኞች በሽምብራ ዛፍ ሥር ተቀምጠው ጠማማ ፍርድን ይሰጣሉ፡፡ እህል በሸሃኔ ይሠፈራል፡፡ ቀጣና ይበዛል፡፡ ርሀብና መከራ ይናኛል፡፡ ትልቅ ሰው ይዋረዳል፤ ትንሽ ሰው ይከበራል፡፡ በመጨረሻቸው ግን እነዚያ ጉዶች እንደጢስ በንነው፣ እንደጤዛ ረግፈው ይጠፋሉ፡፡ ይህን አሁን አይደለም እኛ የምንለው፡፡ ከልጅነታችን ጀምሮ በ50 እና 60ዎቹ ዕድሜ የምንገኝ ሁሉ የምናውቀው የቅርብ ዘመን ትውስታ ነው፡፡

ቀጥሎ ፊጋ ከብቶች ባዶውን በረት ይወርሳሉ፡፡ ለተወሰነ ጊዜም ባዶ ያገኙትን በረት እውነት መስሏቸው እምቡር እምቡር ይሉበታል፡፡ ዕውቀትና ጥበብ ባለፈበት መንገድ ያላለፉ የለዬላቸው ነፈዞች ናቸው፡፡ መሪያቸው ሃይማኖት የለውም፡፡ አለው ቢባልም ማስመሰያ እንጂ ከአንጀት አይደለም፡፡ ዕድሜው ከሦስት ዓመታት አያልፍም፡፡ የነሱም የመጨረሻ ዕጣ ልክ እንደአንበጣዎቹ ይሆንና ባላሰቡትና ባልጠበቁት ሁኔታ አከርካሪያቸውን ተመትተው ወደ ታሪክ ትቢያነት ይለወጣሉ፡፡ ያንን ጊዜ አንተ ወይም አንቺና እኔ ላናየው ብንችልም የማይቀር ስለመሆኑ ግን የዮዲትና የግራኝ አህመድ ወይም የመንግሥቱና የመለስ karmic  መጻሕፍት  ምሥክሮቼ ናቸው፡፡ ይህ እውነት መሃላ የማያሻው አጠቃላይ እውነት ነው፡፡

በመጨረሻው መጨረሻ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ተጠራርተውና ኃይላቸውን አስተባብረው ኢትዮጵያን ይረከባሉ፡፡ በነሱም የኢትዮጵያ የቀድሞ ክብር ይመለሳል፡፡ ያም ጊዜ እጅግ ቀርቧል፡፡ይህን እውነት መናገር ማንንም አይጎዳም፤ ለማንምም የሥጋት መንስኤ ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም የምሥራች ነው፡፡ ለወፍ አራሾች ግን መርዶ ነው፡፡ (ባይገርምህ እናትና ልጅም ተገናኝተው ጥጃዋ ከእህትና ወንድሞቿ ጋር የእናቷን ጡት የምትጠባበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ምን ያስቅሃል?)


እነዚህ የአሁኖቹ ከንቱዎችና ጌቶቻቸው ወያኔዎች ግን ትልቅ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ የነሱን የዓመታት መርዝ ለመንቀል ብዙ ትግልን ይጠይቃል፡፡ ብዙ ሕዝብ መስዋዕት ይሆናል፡፡ የደም ጎርፍ የማናመልጠው ዕዳችን ይሆናል፡፡ “ለኃጥኣን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል” እንዲሉ ነውና ብዙ አሣር ያገኘናል፡፡ መስዋዕቱን ለመቀነስ እንዲቻል (ትንቢትን ማስቀረት ባይቻልም) ወደ ፈጣሪ ተመልሰን በፆምና በጸሎት ብዙ መድከም ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያ ቃል የተገባላት ምድር ናት፡፡ ጠላቶቿ ቀበርናት ሲሉ አፈሯን አራግፋ የምትነሣ፣ ገደልናት ሲሉ የምትድን ልዩ ሀገር እንደሆነች በተደጋጋሚ አስመስክራለች፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን ብዙ ዕልቂት ቢኖርም ከህመሟ ተፈውሳ በሚተርፏት ጥቂት ዜጎች ልዕልናዋን እንደገና ታስከብራለች፡፡ አራሙቻዎችም ተጠራርገው የጨለማው ንጉሥ ግዛት ወደሆነው ወደ መጡበት መቀመቅ ይወርዳሉ፡፡

   
በየከተሞች የሚታየው የሴቴኒዝም እምነትም በነፃነታችን ቶሎ አለመምጣት ላይ የበኩሉን ጽላሎት ማሳረፉ አይቀርም፡፡ ከጥግ እስከጥግ የቆሸሸውና በዘረኝነት፣ በሙስናና በድንቁርና የተበከለው ቤተ መንግሥታችን ብቻ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንንና የእምነት ቤቶችን በጥቅሉ ሰይጣን ስለተቆጣጠራቸው እውነተኛ እረኞች የሉንም፡፡ ሰይጣን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስያንን ጨምሮ የእስክንድርያዋንና የኢትዮጵያዋን ኦርቶዶክስ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተቆጣጥሯል፡፡ ልጅ እየወለደ በድብቅና አንዳንዴም ልክ እንደቫቲካኑ የ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንድ ሊቀ ጳጳስ (ፖፕ ሮድሪጎ) በማንአለብኝነት በግልጽ የሚያሳድግ ፓትርያርክና ጳጳስ ባለባት ሀገራችን ውስጥ የእግዚአብሔር በረከትና ጥበቃ በቀላሉ ይገኛል ማለት ቀልድ ነው፡፡ በዚህ ዘመን መዳን ከባድ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግፍና በደል እየተሠራ እያለ አንድም የሃይማኖት አባት በግልጽ ወጥቶ አይቃወምም፤ ቂጡ ላይ ቁስል ያለበት ውሻ እንደልቡ አይጮህም፤ ፈስ ያለበትም ዝላይ አይችልም፡፡ “አባቶቻችን”ም በጠባያቸው ሰይጣናዊነት የተነሣ ፀጋ እግዚአብሔር ጎድሏቸዋልና በጎቻቸውን ተኩላና ቀበሮ ሲቦተራርፍ፣ ሀገርን ማንም ወስላታና ወለፈንዴ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ሲጫወትባት ትንፍሽ አይሉም፡፡ ምክንያቱም በሆነ ነገር አፋቸው ተሸብቧል፡፡ ለነፍሳቸው ያደሩ እንደነ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ አባቶች ሞታቸው ሰማዕትነት እንጂ ተራ ዓለማዊ የሥጋ ሞት እንዳልሆነ ስለሚረዱ እውነትን መስክረው በጥይት ተደብድበው ሞተዋል፡፡ አሁን ግን የምዕመናንንና የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ ገንዘብ እየዘረፉ፣ በዘረኝነት አሮንቃ እየዳከሩና በሴሰኝነት የወሲብ ንዳድ እየነፈሩ ስለነፍስና ስለሀገር ማሰብ የማይቻል በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን በቅርጽ እንጂ በይዘት የለችም - የምለው ሀሰት ቢሆን ጌታ ይፍረድብኝ (ባይባልም አንዳንዶችን ደስ እንዲላቸው ግዴለም ልበለው)፡፡ ድንጋይ ይክባሉ እንጂ አእምሮ ላይ የሚሠሩት አንዳችም ነገር የለም፤ የነሱ የራሳቸው አእምሮም ባዶ ቀፎ ነው፡፡ አብዛኛው ካህንና ደብተራ ዐይኑ የሚጎለጎለው፣ መረዋ ድምጹ የሚጎላው፣ ቅኔውና ወረብ ሽብሸባው የሚሠምረው ገንዘብ ላይ ነው፡፡ ከሁለት ሰዓት የዐውደ ምሕረት ስብከት ውስጥ 30 እና 40 ደቂቃው ብቻ በተግባር ለማይተረጎም ሃይማኖታዊ ቃል የሚውል ሆኖ ሌላው ገንዘብ ስጡ ላይ ነው - መስጠት ብቻውን ያጸድቅ ይመስል፡፡ “ብዙ አየን” አለች አሉ ቦለቅያ፡፡



እንግዲህ እውነቱ እንዲህ ነው፡፡ ሴቴኒዝምን እንዋጋ፡፡ ዝርዝሩን መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው( Romans 1:18-32, Leviticus 20:13, 1 Corinthians 6:9-10, 1 Timothy. 1:9-10)፡፡ ነገር ግን ይህ የጨለማ ዘመን በቶሎ እንዲነጋ ለማድረግ የእውነት ዘገርን እንጨብጥ፡፡ ከላይ እስከታች የሠፈነውን ሙስና እንዋጋ፡፡ በመደበኛ ገቢያችን መኖርን እንለማመድ፡፡ በልጆች አእምሮ ላይ ብዙ እንሥራ፡፡ እንደሀገርም እንደሕዝብም እየጠፋን ነውና ከተሳሳተ መንገድ በቶሎ እንመለስ፡፡ ከሰሞነኛ ቅሌታችን ብጠቅስ ለምሣሌ - ፈተናን እየሠረቅንና በመምህራን እያሠራን መልስ በመበተን ትውልድን ከማደደብ በላይ ምን ወንጀል አለ? በምግብና በልብስ እንዲሁም በሌሎች የንግድ ዕቃዎች የሚሠራውን ፌክና አሻጥር አናንሳው፡፡ የጀሦና የሴጋቱራን እንጀራ፣ የቀይ ሸክላ በርበሬንና የሞራ ቅቤን  መመገብ ለምደን ሰው መሆን ቢያቅተን በርግጥም አይፈረደብንም፡፡ የምንገርም ሆነናል እኮ .... ሀገርና ሕዝብ በ30 ዓመታት ውስጥ ብቻ መጥፋት የሚችሉ ተራ ነገሮች ናቸው ማለት ነው?



ከነአቢይ አህመድ የሕይወት መመርያ ቀጣዩን ለአብነት ያህል እንመልከት፡-

Politics has nothing in common with moral. The ruler who is governed by the moral is not a skilled politician, and is therefore unstable on his throne. He who wishes to rule must have recourse to both cunning and to make believe. Great national qualities, like frankness and honesty, are vices in politics, for they bring down rulers from their thrones more effectively and more certainly than the most powerful enemy. (Source: Secret Societies and their Power in the 20th Century, by Jan Van Helsing)


ለዚህ ነው የሁሉም ችግር ማስወገጃ መንገዳቸው ውቃው ሆኖ የቀረው፡፡ ሰው ሰው የማይሸት ፖለቲካና ሃይማኖት፣ ከምክንያት ይልቅ ከራስ ወዳድነትና ከስግብግብነት ጋር የተቆራኘ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተራክቦ ገጥሞን ወደ ሮቦትነት እየተለወጥን ነውና ጨርሰን ሳንጠፋ እንምከር፤ እንነጋገር፤ ለዚሁ ጉዳይ መድረኮችም ይዘጋጁ፡፡ የኑሮ ውድነቱንም ለማብረድ ወደ ሰውነት እንመለስ፡፡ ሰውነት እጅጉን ርቆናል፤ ናፍቆናልም፡፡




Monday, August 19, 2019

በሰይጣን ግዛትም ሥላሤዎች አሉ – እንተዋወቃቸው፡ – ወልደ ማርያም ዘገዬ (posted at Ethio Semay)


በሰይጣን ግዛትም ሥላሤዎች አሉእንተዋወቃቸው፡ወልደ ማርያም ዘገዬ (posted at Ethio Semay)
በፈረንጅኛው Trinity ባማርኛው ሥላሤ አብን (the Father) ወልድንና (the Son) መንፈስ ቅዱስን (the Holy Spirit) ይይዛል፡፡ በምሥጢረ ሥላሤ ትምህርት ሥላሤዎች አንድም ሦስትም ናቸው፡፡ አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራፂ በሚል አገባብ ይታወቃሉ፡፡ ይህ እንግዲህ በሥነ መለኮት ወይም ቴዎሎጂ ሃይማኖታዊ የዕውቀት ዘርፍ የሚተነተን ነው፡፡
እስካሁን ባለው የሥነ መለኮት ትምህርት ፀላዔ-ሠናያት የሆነው ሣጥናኤል እምቅድመ ፍጥረተ አዳም ወሔዋን ዘመን  ጀምሮ ከእግዚአብሔር መንግሥት በጠባዩ መማረጥ ሳቢያ ከገነተ ሰማይ ወደ ደይነ ምድር መወርወሩንና መሰል ሰብኣዊና ረቂቅ ፍጡራንን ወደ ግዛቱ ከመጠቅለሉ ውጭ እንደ እግዚአብሔር መንግሥትሥላሤየሚባል ሥነ ተፈጥሮ የለውም፡፡ ሰይጣን በልማድ እንደምናውቀው የክፋት ምንጭና የብልግናዎች ሁሉ ቁንጮ መሆኑን ነው፡፡ ሣጥናኤል፣ ጋንኤል (ሲበዛ አጋንንት) ዲያብሎስ፣ ሉሲፈር ወዘተ. በሚባሉ የክትና የሠርክ ስሞች የሚታወቀው ሰይጣን የሞት፣ የስደት፣ የጠብ፣ የግጭት፣ የስቃይ፣ የመከራ፣ የርሀብ፣ የበሽታ፣ የዕልቂት፣ የድርቅተምሣሌትና ዋና መንስዔ እንደሆነ የሁላችን ግንዛቤ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች የሰይጣንን ኃይል ለተለያዬ ዓላማ ይጠቀማሉ፡፡ ገንዘብና ሥልጣን ለማግኘት ሲባል ከትንሽ ገንዘባዊ መስዋዕትነት እስከሰው ነፍስ ጭዳነት ለሰይጣንና አጋፋሪዎቹ በማቅረብ ብዙ የሀብትና የሹመት ደረጃዎችን የሚወጡ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ የሁሉም መጨረሻ ግን አያምርም፡፡ አንድ መዋቲ ሰው ደግሞ በሰይጣን ከሚያልፍለት በእግዚአብሔር ደጅ በድህነት ኖሮ ቢሞት ይሻለዋል፡፡ የሰው ወርቅ አያደምቅም፡፡ …. ሰይጣን ብድርን ሲያስከፍል በነፍስ እንጂ በቁስ አይደለም፡፡ ሰዎች ይህን ቢረዱ ከሚታየው የሰው ለሰው መጨካከን ከዕጥፍ በላይ ይቀንስ ነበር፡፡
ከዚህ ተፈጥሮው በመነሣትም በግብርም በአስተሳሰብም እርሱን የሚመስሉ ፍጡራን ከሰዎችም ሆነ ከሌሎች እንስሳት ሲገጥመንሰይጣንእንላቸዋለን፡፡ ዓለማችን እጅግ ብዙ የሰይጣን ምሣሌዎችንና ቀጥተኛ ወኪሎችን አስተናግዳለች፡፡ እነዚህ ሰይጣናት (devil-incarnates) የንጹሓን ዜጎችን የዕለት ከዕለት ሰላም ከማወክ አልፈው ለበርካታ ጦርነቶችና ግጭቶች መንስኤ በመሆን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የዓለማችን ዜጎች ዕልቂት ዋነኛ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ከነዚህ ሰይጣናዊ ሰዎች ሂትለርን ከጀርመን፣ ሙሶሊኒን ከጣሊያን፣ መለስን ከኢትዮጵያ እዚህ ላይ በዋቢነት ብንጠቅስ አይበዛባቸውም፡፡ እነዚህ ከሞታን ሠፈር የምናስታውሳቸው የአጋንንት ወኪሎች ናቸው፡፡ የዓለማችን ቅርጽ እንዲህ ማስጠሎ የሆነው የነዚህሰዎችአሉታዊ ሚና ጎልቶ በመውጣቱ ነው፡፡ ጊዜያቸውም ስለሆነ፡፡
በአሁኑ ወቅት በሕይወት እየኖሩ ሰይጣንን በሚያስከነዳ ክፋትና ተንኮል ሀገርንና ሕዝብን እንደዶሮ እየገነጣጠሉ የሚገኙ የሰይጣን ልጆች ደግሞ በየሀገሩ አሉ፡፡ እንደኢትዮጵያ ግን በሌሎች አይበዙም፡፡ ኢትዮጵያ መንግሥትም ባለቤትም ስለሌላት በተለይ በአሁኑ ወቅት እነዚህ የአጋንንት ውላጆቸ እንደልባቸው እየፈነጩ ይታያሉ፡፡ የዘመንን ፍልስፍናዊ ቅኝት በሚገባ መጠቀም ማለት እንደነሱ ነው፡፡ ከነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹና ይህን ካምፕ በፊታውራሪነት የሚመሩት የሚከተሉትኢትዮጵያውያንናቸው፡፡
1.    ሕዝቅኤል ጋቢሣ (ፕሮፌሰር ይሉታል)
2.    በቀለ ገርባ
3.    ጃዋር ሞሀመድ

እነዚህ ናቸው በሀገራችንየሰይጣን ሥላሤዎች ናቸውያልኳቸው፡፡ አንድም ሦስትም እየሆኑ ሀገርንና ሕዝብን ለማጨራረስ ቀን ከሌት  ያለ አንዳች መታከት የሚባዝኑት የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላቶችን ማወቅ ተገቢና ወቅታዊም ነው፡፡ እነሱም ይህን አያጡትም፡፡
ሕዝቅኤል ጋቢሣ ሌላው ሁሉ ቀርቶ የአብራኩ ክፋይ የሆነች ልጁ ከዩኒቨርስቲ በቅርቡ ተመርቃ በኢትዮጵያ ባንዲራ ስትደምቅበት የሰይጣን ሽንት የሆነው እርጉም አባቷ ግን የሚሠራው ሁሉ የልጁን ሀገር ድራሽ ማጥፋት ሆነ፡፡እበት ትል ይወልዳልይባላል፡፡ የዚህን የሰንበት ጽንስ ዕኩይ ተግባር እኔ ልቅርና አባቱ ሰይጣን ራሱ ዘርዝሮ አይጨርሰውም፡፡ የሚናገረውና የሚጽፈው ሁሉ እንዳንዳች ነገር የሚቆንስና የሚገለማ ነው፡፡ በምን ቀን ይህን መሰሉ የአጋንንት መንፈስ እንደተጣባው አይታወቅም፡፡ ዘመድ አዝማድ ቢኖረው የሰውዬው ደዌ ብዙዎችን ሳይበክልና የጋራ መኖሪያችንን ሳያወድም ክፍል ተቆጥሮለት ወደ ታወቀ ጠበል ወስዶ ማስጠበል ነበር፡፡
በቀለ ገርባ የሚሉት በሽተኛ ደግሞ አለ፡፡ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ በማፈንገጥኦሮሞ ወንድ ከኦሮሞ ሴት ውጭ ከተኛ ዘሩን እንዳጠፋ ይቆጠራል…” ብሎ ሲናገር ቅንጣት የማያፍር ጥቁር ሰይጣን ነው፡፡በኦሮምኛ ካላናገሯችሁ ምንም ዕቃ አትሽጡላቸው፣ነጋቲ ቡላበሏቸውየሚልና ግም ነጭ ጭቃ አናቱ ላይ ተሸክሞ የሚዞር በሰው አምሳል የተፈጠረ የለዬለት ጋኔን ነው፡፡ ለስሙ የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ መምህር ነው፡፡ ግን የቋንቋና ማኅበረሰብን ዕድገትና ዘፈቀዳዊ ግንኙነት አያውቅም፡፡ ቋንቋ ባሕርያዊ እንዳልሆነም የማይረዳ ገልቱ ነው፡፡
ጃዋር እንኳን ከሰይጣንም በላይ ነው፤ ሰይጣን ቢሞት የሚተካው አልጋ ወራሹ ጃዋር መሆን አለበትሰይጣን የሚሞት ከሆነ፡፡ እንደሚታማውና መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ይህ ጋንኤል ኢትዮጵያን ለመበታተን እንደ ግብጽ ባሉ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች የተመለመለና በብዙ ሚሊዮን ዶላር ተገዝቶ ሥራውን በስኬት እየተወጣ ያለ ጎልማሣ ነው፡፡ ይህ ሰው እስካለ ድረስ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ገና ብዙ ፍዳ ያገኛቸዋል፡፡ (ይህ አባይ የሚሉት ወንዝ ምነው ጋና ወይ ካሜሩን ውስጥ በሆነ! ጠቅሞ ላይጠቅመን አሣራችንን አበላን አይደል?) የተከፈተለት ሚዲያ ከፌዴራል መንግሥት በግልጽም በድብቅም ድጋፍ እንደሚያገኝ ከመነገሩም በተጨማሪ የላኩት ኃይሎች ስለገንዘብ ምንም እንዳያስብና እንዳይጨነቅ ዋስትና የገቡለት ይመስላል፡፡ ለዚህም ሣይሆን አይቀርም እንደኢሳት ያሉ ጣቢያዎች ነጋ ጠባ የገንዘብ ዕርዳታ በመለመን ሥራ ሲጠመዱ የጃዋር ኦኤምኤን (OMN) ግን እንኳንስ ገንዘብ ሊለምን ለሠራተኞቹ የሚከፍለው ደሞዝ ራሱ ከማንም ጋር የማይወዳደርና ሥራ አስኪያጁ ጃዋርም ጥይት በማይበሳው እጅግ ውድ መኪና የሚንፈላሰስ፣ ወፍ ከሰማይ በሚያወርዱ ሥልጡን ኮማንዶዎች ከሀገሪቱ /ሚኒስትር በበለጠ የሚጠበቅና ተሰሚነቱና ተፅዕኖውም ከማንም በላይ የሆነው፡፡ ይህን ሁሉም ያውቃል፡፡ ክርስቲያን ታደለ የሚባል የአብን ምክትል /መንበር(?) ወዶና ፈቅዶ ያልተወለደበት አማራነት ወንጀል ሆኖበት በጎሣዊ ማንነቱ ሰበብ ከበርካታ መሰሎቹ ጋር ተይዞ ሲታሰርና ሲሰቃይ ጃዋር ግን ሲዳማን ከደቡብ ለመገንጠል በግልጽ ዐዋጅ ዐውጆ ለብዙ ሕዝብ ዕልቂትና ለንብረት ውድመት ዋነኛ ተጠያቂ መሆን ሲገባው ማንም ዝምቡን እሽ አላለውምየሚገርም የነገሮች ሂደት፤ በታሪክ የሚያስጠይቅ ልዩ ኦህዲዳዊ የአስተዳደር ዘይቤ፤ በታሪክ ማኅጸን የተረገዘው ህግ ሲወለድ እስከሞት ሊያስቀጣ ለሚችል ከፍተኛ ወንጀል የሚዳርግ በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ ሸውራራ ኦነጋዊ መንግሥት የተተከለበት አስደናቂ ዘመን፡፡ ይህ የሚያሳየው የፌዴራል መንግሥት ተብዬው የኦህዲድ ባለሥልጣናትም  ጃዝ ብሎ ጃዋርን በላከው ኃይል ተፅዕኖ ሥር መውደቃቸውን ነው፡፡ እንጂ በአንድ ሀገር ውስጥ የተለያየ ሕገ መንግሥትና አስተዳደር ያለ በሚያስመስል ሁኔታ አማራውን እያጠቁ ኦሮሞው አገር ምድሩን እንዲቆጣጠርና ጽንፈኞች ያሻቸውን እንዲያደርጉ ፈረሱም ሜዳውም ባልተለቀቀላቸው ነበር፡፡ ይህ አሣፋሪ ዘመን ማለፉ አይቀርም፡፡ ሲያልፍ ግን ብዙ ጠባሳ እንዳይጥል አእምሮን ከአሁኑ በቅጡ መጠቀም ይገባል፡፡ በዱባ ጥጋብ የሚፈነጥዝ ዘረኛና ሤረኛ ሁሉ ቆም ብሎ የማሰቢያ ጊዜው አሁን መሆኑን መረዳት አለበት፡፡እዩኝ፣ እዩኝ” “ደብቁኝ፣ ደብቁኝ እንደሚያስከትል ከወዲሁ ካልተረዳን ዛሬ ትናንትን እንዳልሆነ ሁሉ ነገም ዛሬን አይሆንምና ቢያንስ ለመጪው ትውልዳችንና ለልጆቻችን በማሰብ ከፈረሰኛ የስሜት ደንገላሣ ወጥተን በጥሞና እናስብ፡፡ እነደቻሣና ኩምሣ እየሰማችሁኝ ነው? ከነሐጎስና ገረግዚሃር ካልተማራችሁ ከማን ልትማሩ ትፈልጋላችሁ? ዕደጉ እንጂ! እኛምወፌ ቆመችእንበላችሁ፡፡ እንደቀጨጫችሁ አትቅሩብን፡፡ የናንተ ማደግና መለወጥ ለጋራ ቤታችን ወሳኝ መሆኑን ተገንዘቡ፡፡
ስለ አጋንንታዊ ሥላሤዎች ይችን ታህል ካወራን ለዛሬ ይብቃኝ፡፡ እምነታችንን አጥብቀን እንራመድ፡፡ ለአጋንንት መድኃኒቱ የእምነት ጽናት ነውና በፈጣሪ ብቻ እንታመን፤ ለርሱም ችግራችንን እንንገረው፡፡ መሥራት ያለብንንም እንሥራ፡፡ ዝም ብለን ግን አንቀመጥ፡፡