Tuesday, April 30, 2013

ጎዳና ተዳዳሪው የወታደራዊ መረጃ ኮሎኔል






 ጎዳና ተዳዳሪው የወታደራዊ መረጃ ኮሎኔል



ከኢትዮጵያ ሰማይ ዝግጅት፡ (Ethiopian Semay)
 
ክዚሀ በታች የቀረበው ልብን የሚያደማ አሳዛኝ የአንድ አርበኛ ኢትዮጵያዊ ከፍተኛ ወታደራዊ መኰንን ታሪከ ሲሆን፤ “ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ” በሚል ስያሜ እራሱን የሚጠራ ቡድን፤ የኢትዮጵያን ሕልውና ጠፍረው ያቆዩዋት ኢትዮጵያዊ ገመዶች በጸረ ኢትዮጵያዊነቱ እና በተካነበት የጠላት ቅጥረኛነቱ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም በቀድሞ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሠራዊት አባሎች እና ቤተሰቦቻቸው ህይወት ላይ ባዕድ አንኳን አይፈጽመውም ከሚባልበት አሰቃቂ የብተና፤የግድያ፤የማጥፋት እና የክብር መዋረድ መጠን በላያቸው ላይ በማን አለኝነት በለስ ቀንቶት ሕገወጥ ሥልጣኑን ተጠቅሞ በነዚህ ዜጎቻችን ላይ የፈጸመውን ወንጀል እና ጭካኔ ታነብባላችሁ። ፍርዱ ለአንባቢ እና ለታሪክ ቀርቧል። ታሪኩን አቀነባብሮ ዜጎች አንዲየውቁት ያደረገው   በኢትዮጵያ ሰማይ ድረ ገጽ እና በአንባቢዎች ስም አመሰግናለሁ።
ጌታቸው ረዳ (www.ethiopiansemay.blogspot.com)
 


you can contact the producer if there is any help you can to assist the hero, the present homeless Colonel Kasahun Tirfye. I hope the producer don't mind, me for  giving away his email to the public. fikirbefikir@gmail.com
 
እንደ አለመታደል ሆኖ ከቅርብ የታሪካችን ዘመን እንኳን ብንነሳ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ የሆነ፣ ብሔራዊ ስሜት ያለው፣ ጠንካራ የሆነ ሕዝባዊ መሠረት ያለው የመከላከያ ኃይል ለመፍጠር እየተደረገ የነበረውና አሁንም እያየነው ያለው ሙከራ መንግሥት በተለዋወጠ ቁጥር ሂደቱ የሚንገዳገድና የሚገታ ነው፡፡

በአገሪቱ ዘመናዊ የመከላከያ ኃይል በመገንባት ረገድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያደረጉት ጥረት ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካና ኮርያ ልሣነ ምድር የዘለቀ ብቃቱንና ጥንካሬውን ያስመሰከረ፣ የኢትዮጵያዊነት ከፍተኛ ስሜት፣ ኩራትና ወኔ ያለው የመከላከያ ኃይል ሠራዊት ሊፈጥሩ መቻላቸውን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ፡፡

ይሁን እንጂ የዘውዱን ሥርዓት የገረሰሰው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት አገሪቱ ገንዘቧንና ጥሪቷን አፍስሳ ያስተማረቻቸውን የጦር መኮንኖች በአንድ ጀምበር ረሽኖ በጉድጓድ ውስጥ እንደ ፍግ ሲከምራቸው እንደምንም አልቆጠረውም ነበር፡፡ በሚሊተሪ ሳይንስ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከፍተኛ የሆነ እውቀትን የቀሰመ፣ በወታደራዊ ዲሲፕሊን ይህ ቀረው የማይባልና የማይታማው ሠራዊት ዕድል ፈንታው፣ ጽዋ ተርታው እንደ ጉድፍ ተጠርጎ የትም መጣል ነበር፡፡

ኮሎኔል ካሳሁን ማእከሉን በበጎ ፈቃደኝነት የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች፣ እንዲሁም አንዳንድ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ማእከሉን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶች የሚያመጡላቸው መጻሕፍትና ጋዜጣዎች የአልጋቸውን ራስጌና ግርጌ ከበውት ነበር ያየኹት፡፡ ኮሎኔል በአሁን ሰዓት እነዚህ ሰዎች ያመጡላቸውን መጽሐፍት በማንበብ ተጠምደዋል፡፡


‹‹ኮዳ ትራሳቸው›› የሚል ስምና ዝናን ያተረፉትን፣ ከጥንት ከአባቶቻቸው የተረከቧትን ኢትዮጵያን፣ የእናት አገራቸውን ዳር ድንበር በደማቸውና በአጥንታቸው ለማስከበር ዱር ቤቴ ብለው በምንም ዋጋ ሊተመን የማይችል ክቡር መሥዋዕትነት የከፈሉትን የጦር መኮንኖች ደርጉ በተለያየ ጊዜ አድኃሪና ፊውዳል፣ ፀረ ሕዝብና ፀረ አብዮተኛ በሚል በአብዮታዊ እርምጃ ስም ረሸናቸው፡፡ ከደርግ የጭካኔ ሰይፍ ያመለጡትም በግፍ ተሰደዱ፡፡ ሌሎቹም በሰሜን ተራሮችና በረሃዎች ለእናት ምድራቸው ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው መሥዋዕት ሆነው በክብር አለፉ፡፡




ከደርግ ሠራዊት ጋር 17 ዓመታት ያህል ተዋግቶ በለስ የቀናው ባለተራው ኢህአዴግም ደርግ የተማመነበት፣ አፍሪካን ጭምር ያሠጋል የተባለውን ግዙፍ ሠራዊት ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሲያሸነፍና ሠራዊቱም እንዳልሆነ ሁኖ ሲበተን፣ የደርግ ሠራዊት ዕድል ፈንታ የሆነው በየሜዳው ላይ ልብሱንና ማእረጉን አንጥፎ መለመን ነበር፡፡ ቤተሰቤ፣ ልጆቼ፣ ሚስቴ፣ ዘመዶቼና ወገኖቼ ሳይል በረሃ ለበረሃ፣ ቆንጥር ለቆንጥር፣ ገደል ለገደል የተንከራተተው ሠራዊት በስተመጨረሻም ዕድሉ ያማረ አልሆነለትም ነበር፡፡



የትላንትናው የከፍተኛ ወታደራዊ መረጃና ደህንነት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት፣ የዛሬው ባለ ታሪክ የጎዳና ተዳዳሪ ኮሎኔል በጃንሆይና በደርግ መንግሥት ከሶማሊያ የጦር ግንባር እስከ ኤርትራ- ኡምሃጁር፣ ከረን፣ ተሰነይና ናቅፋ የጦር ግንባሮች የተሳተፉ ናቸው፡፡ እንዲሁም በመከላከያ ሚኒስቴርና በማእከላዊ እዝ ከፍተኛ የወታደራዊ ደህንነትና መረጃ መኮንን በመሆንም የሰሩ ናቸው፡፡ እኚህ መኮንን ከባለቤታቸው ሞት በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል በጎዳና ተዳዳሪነት ቆይተዋል፡፡ እኝህ ኮሎኔል ካሣሁን ትርፌ ይባላሉ፡፡ከኮሎኔል ጋር ስለ አጠቃላይ ሕይወት ታሪካቸውና እንዴት ለጎዳና ሕይወት ሊበቁ እንደቻሉ አውግተናል፡፡


ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ የተወለዱት በሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ከተማ 1939 .. ነው፡፡ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፄ ዘርዓያዕቆብና በኃይለ ማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ የሆነ ውጤት ያስመዘገቡት 17 ዓመቱ ወጣት ካሳሁን ትርፌ በጊዜው የላቀ ውጤት ያመጡ ልጆች ወደሚላኩበት ወደ ሐረር የጦር አካዳሚ ለሦስት ዓመት ወታደራዊ ስልጠና ተላኩ፡፡ በወቅቱ በሐረር አካዳሚ ወታደራዊና አካዳሚያዊ ሥልጠና ጎን ለጎን የሚሰጥበት ደረጃውን የጠበቀ ተቋም እንደነበር ያስታውሳሉ፡



ኮሎኔል ካሳሁን ስለ ሐረር የጦር አካዳሚ ትምህርት ቤት የትምህርት አሰጣጥ ጥራት፣ ብቃትና በአካዳሚው ስለነበራቸው ቆይታ ሲያጫውቱኝ፣ ከሚሊታሪ ሳይንስ ውጭ እንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋ፣ ከሳይንስ ትምህርቶችም ሂሳብና ፊዚክስ፣ ከሶሻል ደግሞ ኢኮኖሚክስ፣ ኅብረተሰብና የታሪክ ትምህርት ጭምርም ይሰጥ እንደነበር አጫውተውኛል፡፡

ኮሎኔል በዘመናቸው ከእርሳቸው ጋር የነበሩትን ሰልጣኝ ተማሪ ጓደኞቻቸውንና መምህራኖቻቸውን ሲያስታውሱም፣ ከፍተኛ የሆነ ኢትዮጵያዊ ስሜትና ወኔ ያላቸው፣ በሚሊታሪ ሳይንስና በወታደራዊ ዲሲፕሊን የታነጹ፣ ለአገርና ለወገን ክብር ተቆርቋሪ የሆኑ፣ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ ኮሎኔል ከሐረር አካዳሚ ተመርቀው ከወጡ በኋላ በምክትል መቶ አለቅነት በጊዜው በተሰጣቸው ወታደራዊ ግዳጅ መሠረት ለሁለት ዓመት አገልግሎት ለመስጠት ወደ ኦጋዴን ነበር የሄዱት፡፡ በዛም የአንበሳው ክፍለ ጦር 22 ሻለቃ ጦርን ተቀላቀሉ፡፡ በኦጋዴን የሁለት ዓመት ወታደራዊ ግዳጃቸውን ከጨረሱ በኋላም በወታደራዊ መረጃና ደህንነት ትምህርት ስፔሻላይዝ ለማድረግ ወደ ሆለታ ገነት አካዳሚ ገቡ፡፡

በሆለታ አካዳሚ ለአንድ ዓመት ስልጠና የወሰዱት ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ ከዚህ በኋላ ዋና ሥራቸው የነበረው የወታደራዊ መረጃና ደህንነት ሥራ ነበር፡፡ ኮሎኔል ከሆለታ ገነት ስልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ዳግመኛ ወደ ኦጋዴን ገላዲ በመመለስ 3 ሻለቃ ውስጥ በመረጃ መኮንንነት ማገልገል ጀመሩ፡፡ 1966 . መጨረሻ አካባቢም ወደ ሐረር ክፍለ ጦር መምሪያ በመሔድ የክፍለ ጦሩ ሴኩሪቲ ኦፊሰር በመሆን ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡

በአገሪቱ የለውጥ ንፋስ እየነፈሰ በነበረበት በዛን ወቅት በአገራችን ምስራቃዊ ክፍል ያለችው ሶማሊያ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት የደፈጣ ጥቃት በማድረግ ትንኮሳ ታደረግ እንደነበር አስታወሱኝ፡፡ ሶማሊያውያን በዲፕሎማሲው መስክ የግዛት ይገባኛል ጥያቄቸውን ለአፍሪካ አንድነትና ለዓለም አቀፉ መንግሥታት በማሳወቅ በኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር ታላቋ ሶማሊያን የመፍጠር ቅዠታቸውን ዕውን ለማድረግ ሩጫውን ተያያዙት፡፡


ከአሜሪካና ከራሺያ ባገኙት ከፍተኛ የሆነ የጦር መሳሪያ እርዳታ 1966 አብዮትና ለውጥ በኋላ ሶማሊያ በምስራቅ አገራችን ክፍል እስከ ኦጋዴንና ሐረር ድረስ ዘልቃ በመግባት የደፈጣ ጥቃት ሰነዘረች፡፡ ይህ የሶማሊያ ጥቃት በለውጥ ግርግርና ገና አለመረጋጋት ላይ ለነበረችው ኢትዮጵያና የደረጉ መንግሥት እንደ ዱብዳ ነበር ይላሉ ኮሎኔል፡፡

በወቅቱ ኮሎኔል ካሣሁን በሐረር ግንባር የነበረው ጦር ያለውን ኃይል ሁሉ አስተባብሮ የሶማሊያን ወራሪ ኃይል ተቋቁሞ ለመመከት ችሎ ነበር፡፡ በኋላም ደርግ በክተት ዘመቻ ለሦስት ወራት ያሰለጠናቸው የሚሊሻ ሠራዊት ከሶሻሊስት ወዳጅ አገሮች ከየመንና ከኩባ በተገኘ የጦር መሳሪያ እርዳታና ወታደራዊ ኃይል ድጋፍ የሶማሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን ጀግኖች አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ዳግም ላያንሰራረራ፣ አክርካሪውን ተመትቶ በመጣበት እግሩ ሽንፈትን ተከናንቦ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡ የዚያድባሬ ታላቋን ሶማሊያን የመፍጠር ከንቱ ምኞትም የቁም ቅዠት ሆኖ ቀረ፡፡

ኮሎኔል በዚህ ጦርነት ወቅት ዋና ሥራቸው የነበረው የጦር መረጃ መሰብሰብና የአየር ላይ ቅኝት በማድረግ የጠላትን እንቅስቃሴና የማጥቃት እርምጃ ቀድሞ ለወገን ሠራዊት መረጃ ማቀበል፣ ለሠራዊቱ የማጥቃትና የመከላከል እቅድ መንደፍ ነበር፡፡ የሶማሊያው ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት በድል ከተደመደመ በኋላ ኮሎኔል በሐረር ከቤተሰባቸው ጋር ለጥቂት ሳምንታት ቆይተው ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የኤርትራ የጦር ግንባር ተላኩ፡፡

ኮሎኔል ይህ ወደ ኤርትራ ያደረጉትን ረጅም ጉዞአቸውን ሲተርኩ፣ ከሐረር ተነስተው መቀሌ ከደረሱና በመቀሌ ለጥቂት ሳምንታት ቆይታ ካደረጉ በኋላ የሰሜኑ ጦርነት በመፋፋሙና እየገፋ በመምጣቱ የተነሣ ከመቀሌ ተነስተው ኡምኻጁርን፣ ተሰነይን፣ ባሬንቱ አልፈው ወደ አቁርደት ገቡ፡፡ በአቁርደትም በተለያዩ የወታደራዊ መረጃ ሥራዎችን በመሥራትና ጦሩን በማጠናከር ሥራ ለሦስት ወራት ከቆዩ በኋላ 3ኛውን ክፍለ ጦር በመቀላቀል በከፍተኛ መሥዋዕትነት ከረንን ከሻቢያ አስለቀቁ፡፡

የሻቢያ ጦር ከከረን ሽንፈቱ በኋላ የመሸገው በናቅፋ ተራራ ላይ ነበር፡፡ ያን ደም እንደ ጎርፍ የተንዠቀዠቀበትን፣ የሰሜን ተራሮች፣ የኢትዮጵያ ምድር በደም አበላ የተመታበትንና ምድሪቱ አኬል ዳማ የሆነችበት፣ የአንድ እናት ማኅፀን ክፋዮች በገዛ ደማቸው በዋኙበት በሰሜኑ የጦር ግንባር ያሳለፉትን መሪር ትዝታ ወደኋላ ሄደው አስታወሱት፡፡ ከከረኑ የጦር ግንባር በኋላ ኮሎኔል እንባ ባቀረረ ዓይናቸው አተኩረው እያዩኝ፣ ቀጣዩና ወሳኙ ጦርነት የተካሄደው በናቅፋ ግንባር ነበር አሉኝ፡፡

ይህ በናቅፋ የጦር ግንባር የተካሄደውን እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነትና እልቂት የየትኛው ደራሲ ብዕር፣ የየትኛው የጥበብ ሰው ብሩሽ፣ የትኛውስ ደራሲ ምናብ በትክክል ሊተርከው፣ ሊስለው ይችል ይሆን በማለት ኮሎኔል ወደዛ ተወዳዳሪ የሌለው ወደሚመስለው የሰሜኑ ግንባር የእልቂትና የፍጅት የጦር አውድማ ሕሊናቸውን በትዝታ ሰደው ለጥቂት ደቂቃዎች በዝምታና በትካዜ ውስጥ ሆነው ቆዩ፡፡

በኮሎኔሉ እንደ መርግ በከበደ ዝምታቸውና ትካዜያቸው ውስጥ በሰሜን ተራራ የወደቁ የኢትዮጵያ የማኅፀኗ ክፋዮች፣ የውድ ልጆቿ የደም ጩኸታቸው፣ በተራረሮቿና በሜዳዎቿ የተከሰከሰው አጥንቶቻቸው፣ ለእናት ምድራቸው ዳርድንበር መከበር ደማቸውን ከቀይ ባሕር ጋር የቀላቀሉት የእልፍ ኢትዮጵያን ጀግኖች ታሪክ በዛች ቅጽበት በአእምሮዬ ጓዳ ይመላለስ ገባ፡፡

የእነ አሉላ አባ ነጋ፣ የእነ አፄ ዮሐንስ፣ የምኒልክ፣ የጣይቱ፣ የእነ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ የእነ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ የኤርትራውያኑ ወጣቶች የእነ አብረሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም ወኔና ጀግንነት፣ እስከ ሮም አደባባይ የዘለቀው የኤርትራዊው የዘርዓይ ደረስ የኢትዮጵዊነት ብሔራዊ ኩራት፣ ወኔና ጀግንነት፣ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ለአንድ እናት ምድራቸው ለእማማ ኢትዮጵያ ከከፈሉት በደም ቀለም ከተጻፈው የመሥዋዕትነት ታሪካቸው ጋር ለአፍታ መነጋገር ያዝኩ፡፡

ኮረኔሉ እንደ መርግ ከከበደ የዝምታቸው ዓለም፣ ከገቡበት ከትካዜያቸው ባሕር ተመልሰው ቀና ብለው አዩኝ፡፡ እኔም ከተፋጠጥኩበት የአገሬ የተዥጎረጎረ ታሪክ እውነታ ትውስታዬን ተሰናብቼ ወደ ኮሎኔል ካሣሁን ትረካ ተመለስኩ፡፡ ኮሎኔል በናቅፋ ጦር ግንባር የነበረው ጦርነት እጅግ ከባድና ብዙ እልቂት የተፈጸበመት ነበር አሉኝ፡፡ ወደኋላ በትዝታ ተጉዘው ያን ዘግናኝና አስከፊ እልቂት እያስታወሱ፡፡
በዚህ በናቅፋ ግንባር ከሻቢያ ጋር በተደረገ ትንቅንቅ ኮሎኔል ዘጠኝ ቦታ መመታታቸውንና እስካሁንም ድረስ በክንዳቸውና በታፋቸው ላይ ያለው ጥይት አለመውጣቱን በሰውነታቸው ላይ ቀረውን ጠባሳ እያሳዩኝ የናቅፋ ግንባር የጦርነት ውሎአቸውን ልብን በሚነካ ሁኔታ መተረካቸውን ቀጠሉ፡፡

የሻቢያ ሠራዊት ከናቅፋ ሰንሰለታማና ሹል ተራራ ላይ ሆኖ በኢትዮጵያ ጦር ማዘዣ ጣቢያ ላይ በከፈተው መጠነ ሰፊ ማጥቃትና የከባድ ጦር መሳሪያ ድብደባ በዚህ ግንባር የጦሩ አዣዥ የነበሩትና በጦር ሠራዊቱ ውስጥ እጅግ የሚከበሩትና ተወዳጅነት የነበራቸው ጄኔራል ይልማ ግዛው ጭንቅላታቸውን ተመትተው በናቅፋው የጦር ግንባር መሞታቸውን የነገሩኝ ከባድ ሐዘን በተጫነው የሰቀቀን ድምፅ ነበር፡፡

ኮሎኔል ካሳሁን የቅርብ የሥራ ባልደረባቸውና ወዳጃቸው የነበሩትን፣ በናቅፋ የጦር ግንባር የተሠዉትን የኮሎኔል መርሻ አድማሱን ሞት ሲተርኩልኝ ፊታቸው ላይ መረበሽና ጥልቅ ሐዘን እየተነበበት ነበር፡፡ የቅርብ የሥራ ባልደረባዬና ወዳጄ / መርሻ ከሻቢያ በተተኮሰ የሞርታር ጥይት ነበር ከወገቡ በላይ ተቆርጦ ደሙ ከላይ እየተንጠባጠበ በአየር ላይ ግማሽ አካሉ እየተንሳፈፈ ነፍሱ ያለፈችው አሉኝ፤ በዛ ፃእረ ሞትና የእልቂት መናፍስት የናኙበት በሚመስለው የናቅፋው ጦር ግንባር የሆነውንና የደረሰውን ዘግናኝ እልቂት ኮረኔሉ ሊያስታውሱት ባይወዱም በዓይነ ሕሊናቸው ተመላለሰባቸው በጦሩ ውስጥ ከነበሩት 12 ከፍተኛ መኮንኖች መካከል ተመትተው በተአምር የተረፉት እሳቸው ብቻ መሆናቸውን አጫወቱኝ፡፡ በእርግጥም ይላሉ / ያን የእልቂ ቀን ሲያስታውሱት፡- ቀን በኢትዮጵያ ጦር ላይ ለእልቂት የታዘዘ የመቅሰፍትና የመዓት ቀን ነበር የሚመስለው፡፡ የናቅፋ ግንባር በርካታ የደርግ የዘመቻ ካድሬዎችና መኮንኖች ያለቁበት ግንባር ነበር፡፡ ናቅፋአሉ ኮሎኔል ሐዘንና ትካዜ በዋጠው ድምፀት… !!

ኮሎኔል በናቅፋ ግንባር ከተመቱ በኋላ ወደ አስመራ እቴጌ መነን ሆስፒታል በመሄድ በህክምና እርዳታ ከቆዩ በኋላ ለተጨማሪ ህክምና እና ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው ለማገገም እንዲችሉ ፈቃድ አግኝተው ወደ ሐረር ነበር የተጓዙት፡፡ ከሐረር መልስም ወደ አዲስ አበባ መጥተው 1972 .. በማእከላዊ የመረጃ መምሪያ መኮንን ሆነው ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡ በማእከላዊም እስከ 1978 .. ድረስ መቆየታቸውን ነግረውኛል፡፡


1978 የበላይ አለቆቻቸውና አንዳንድ የደረግ ካድሬዎች በመሰረቱባቸው ክስ የተነሣ የጦር ወንጀለኛ ተብለው በዓለም በቃኝ እስር ቤት እንዲታሰሩ ተወሰነባቸው፡፡ ኮሎኔል ያን ጊዜ ሲያስታውሱት እጅግ ከባድና ፈታኝ ወቅት ነበር ይላሉ፡፡ ኮሎኔል በወቅቱ የተወነጀልኩት በሐሰት ነው በሚል ተደጋጋሚ ይግባኝ በማሰማታቸው ከሁለት ዓመት መራር የእስር ጊዜ በኋላ በነፃ እንዲወጡ ተደረገ፡፡


ኮረኔሉ ከእስር እንደተለቀቁም አለቃቸው ጄኔራል ኃይሉ /ሚካኤል እንደገና ወደ ኤርትራ ሰሜን ግንባር ሄደው በአልጌና እንዲያገለግሉ ነበር ያዘዟቸው፡፡ ‹‹ይህን የበላይ አለቃዬን ውሳኔ የምቀበለው አለመሆኔን ለጄኔራሉ በድፍረት ነገርኳቸው፡፡ እሳቸውም መልሰው ይህን ውሳኔ የማትቀበል ከሆነ ሥራህን በፈቃድህ እንደለቀቀክ ይቆጠራል፡፡ ከፈለግህ ሃምሳ ዓመት ሲሞላህ ጡረታህን ማስከበር መብትህ ነው›› በማለት በኃይለ ቃል ተናግረው እንዳሰናበቷቸው ይናገራሉ፡፡


ኮሎኔል ካሳሁን ለአለቃቸው ለጄኔራል ኃይሉ እኔ ገና በልጅነቴ 17 ዓመቴ ጀምሬ በውትድርና ዓለም በምስራቅና በሰሜን የጦር ግንባር በረሃ ለበረሃ ተንከራትቼ አገሬን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ያገለገልኩ ወታደር ነኝ፡፡ በዛ ላይ ዘጠኝ ቦታ ተመትቼ የቆሰልኩ ነኝ፡፡ በእስር ቤትም ውስጥ እያለኹ ባጋጠመኝ የአእምሮ ጭንቀት የተነሣ አእምሮዬ በትክክል አይሰራም ቢሉም ሰሚ አላገኙም፡፡ የነበረኝ ዕድል አሉ ኮሎኔል የነበረኝ ዕድል ለመከላከያ / ይግባኝ ማለት ነበር፡፡


መከላከያ / ጄኔራል ኃይለ ጊዮርጊስ የህክምና ቦርዱ የፃፈውን የህክምና ወረቀቴን ካዩ በኋላ 1981 .. ጡረታ ተብዬ ከሠራዊቱ አሰናበቱኝ፡፡ ከዛ በኋላ የጤናቸውን ሁኔታ እየተከታተሉ የተለያዩ መጻሕፍትን የመተርጎም ሥራ ውስጥ ገቡ፡፡ በዚህ ሥራ ውስጥም እያሉ እንደገና ደርግ አባት ጦሮችን ለዘመቻ ክተት ሲጣራ በካራማራ ክፍለ ጦር ወታደራዊ መረጃ መኮንን ሆነው ተመደቡ፡፡ ግንቦት 19 ቀን ለሥራ ትፈለጋለህ ወደ አዲስ አበባ ተብዬ እንደመጣሁ ነበር በማግሥቱ ግንቦት ሃያ ወያኔ አዲስ አበባን የተቆጣጠረው ይላሉ፡፡


የወያኔ ኃይል አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ የመከላከያ ኃይሉን ዳግም ሲያዋቅር አንዳንድ የጦር መኮንኖችን እንድናግዛቸው ባደረጉልን ጥሪ መሠረት እስከ 1987 . ድረስ ደርግ ይሰጠን የነበረውን ደመወዝ እየከፈሉን የኢሕአዴግን ሰራዊት የማደራጀት ሥራ በመሥራት በመከላከያ / መቆየታቸውን ኮሎኔል ካሳሁን ነግረውኛል፡፡ በወቅቱ የመከላከያ / የነበረው ጄኔራል ጻድቃን /ተንሣይ እኛን ለጦራቸው ሲያስተዋውቀን የተናገረው ነገር አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል፡፡


እንዲህ ነበር ያሉት ጻድቃን፣እኛ የምናውቀውና የተካንነው የጫካ ውጊያን ነው፣ ከእነዚህ ሰዎች ደግሞ ሚሊታሪ ሳይንስ ምን እንደሆነ በሚገባ መማር ይገባናልበማለት ከጦራቸው ጋር እንዳስተዋወቋቸው ኮረኔሉ ያስታውሳሉ፡፡

1987 .. በኋላ ኮሎኔል ሙሉ ጡረታቸውን ይዘው ከመከላከያ ተሰናበቱ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ መጻሕፍት ትርጉምና ወደ ግሉ ፕሬስ ነበር ፊታቸውን ያዞሩት፡፡ የተለያዩ ከውጭ አገር የሚመጡ ዜናዎችን በመተርጎም፣ የወቅቱን ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ የሚወጡ ጽሑፎችን በመተርጎም በታሪክ፣ በዓባይ፣ በኢትኦጵ፣ በማኅበራዊና በፍቀር ነክ መጽሔቶችና ጋዜጦች በነበሩት በቸኮሌት፣ በጣዕመ ፍቅር፣ ሆሊውድ ላይ በጸሐፊነትና በተረጓሚነት መሥራታቸውን ያስታውሳሉ፡፡


በተለይ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በስፋት ይጽፉ በነበሩት በሚኒልከ፣ በዓባይ ጋዜጣ ላይ በሰፊው መስራታቸውንና ከምርጫ 97 በኋላ እነዚህ ጋዜጣዎች በመዘጋታቸውና አንዳንዶቹም ባለቤቶቻቸው በመታሰራቸው አንዳንዶቹም ከአገር በመሰደዳቸው ምክንያት ከነጻ ፕሬስ ወጥተው በመጻሕፍት መተርጎም ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ነግረውኛል፡፡ ኮሎኔል በዚህ የመጽሐፍ መተርጎም ሥራ ላይ እስካሁን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጠኑ ረጃጅም ከሃያ በላይ የሚሆኑ የልቦለዶ ሥራዎችን ለሌሎች ሰዎች በመተርጎም ለገበያ ማብቃታቸውን ይናገራሉ፡፡


ኮሎኔል ባለቤታቸው ከብዙ ህመምና ስቃይ በኋላ ከዚህ ዓለም ከሞት ከተለየዋቸው በኋላ፣ ከባለቤታቸው ዘመዶች ጋር መግባባት በመጥፋቱ እንዲሁም አእምሮዋቸው በመረበሹና ጤናቸው በመቃወሱ በጃን ሜዳ ከሚገኘው ቤታቸው ወጥተው በአዲሱ ሚካኤል አካባቢ ከአንድ ዓመት በላይ በጎዳና ተዳዳሪነት እንዳሳለፉ አጫወቱኝ፡፡ በደጃች ገነሜ ትምህርት ቤት አጥር ስር ሰዎች በሠሩላቸው እንደነገሩ በሆነ የላስቲክ መጠለያ ውስጥ ነበር ኮሎኔልን ያገኘናቸው፡፡

የአካበቢው ሰው ምንም እንኳን ስለማንነታቸው ባያውቅም በዕድሜዬ አረጋዊ መሆናቸውን እያዩ በማዘን ምግብ፣ ልብስና ገንዘብ በመስጠት ይረዷቸው እንደነበር ያታውሳሉ፡፡ በጎዳና ላይ በነበሩበት ጊዜ ኮሎኔል ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ ጭንቀትና መረበሽ እንደነበረባቸውና በየቀኑም በርካታ ሲጋራዎችን ያጨሱ እንደነበር በመኝታቸው አካባቢ የተጣለው የሲጋራ ቁጥራጭና በርካታ የሲጋራ ባኮዎች ምስክር ናቸው፡፡

ኮሎኔል ከአስከፊው የጎዳና ሕይወት በኋላ በቅርቡ የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ማእከል ባደረገላቸው ድጋፍ ወደ ማእከሉ ገብተው እንክብካቤ እያገኙ ነው፡፡ ኮሎኔል ካሳሁን ከነርቭ በሽታና በጎዳና ላይ ሳሉም ከነበራቸው ያልተመቻቸ ሕይወት የተነሣ በእግራቸው መሄድ አይችሉም፣ እናም የሚንቀሳቀሱት በዊልቸር ነው፡፡ በማእከሉ ተገኝቼ ሳያቸው ኮሎኔል የተጎሳቆለ ፊታቸው ተመልሶ፣ የነተበና የቆሸሸ ልብሳቸው ተለውጦ፣ ፊታቸው ላይ ደስታና ፈገግታ እየተነበበ ወንበር ላይ ተቀምጠው መጽሐፋቸውን እያነበቡ ነበር፡፡


ከጎዳና ሕይወት ወደ ተሻለ መጠለያ፣ ምግብ፣ ልብስና ሰብአዊ ፍቅርና እንክብካቤ ወደሚያገኙበት ወደእዚህ ዓይነት ማእከል በመምጣታቸው ኮሎኔል በእጅጉ ደስተኛ ናቸው፡፡ ኮሎኔል እንደነገሩኝ ማእከሉን በበጎ ፈቃደኝነት ከሚያገለግሉ የአማኑኤል ሆስፒታል የሳይካትሪስት ነርሶች ሙያዊ ምክርና እገዛ ማግኘታቸው ጥሩ የሆነ ስሜትን እንደፈጠረባቸውም አጫውተውኛል፡፡

እንዴት ነዎት? ስላቸው ‹‹ወንድሜ አሁን ደህና ነኝ፤ አእምሮዬም በጣም ደህና ነው፡፡ እንደበፊቱ ወደ ንባብና ትርጉም ሥራዬ እየገባሁ ነው›› በማለት እያነበቡት ያለውንና በእጃቸው የያዙትን ‹‹Among the Russians›› የሚል መጽሐፍ አሳዩኝ፡፡ እንዴት ያለ ግሩም መጽሐፍ መሰለህ በሚል የአድናቆት ቃል እያነበቡት ስላለው መጽሐፍም አወጉኝ፡፡

ባለፈው ሳምንት ‹‹አፍሪካን ኔግሮስ›› የሚል አንዲት ከአፍሪካ በባርነት ተሸጠው ከሄዱ ቤተሰብ የተወለደች አፍሪካ አሜሪካዊት ሴት የሕይወት ታሪኳን የተረከችበትን መጽሐፍ በተመስጦ አንብበው እንደጨረሱትም ነገሩኝ፡፡

‹‹ኮሎኔል ካሳሁን በቅርቡ በራሴና በመቄዶንያ ድርጅት ስም የሚታተም መጽሐፍ ለመተረጎም ዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ አንዳንድ ነገሮችን እንድታግዘኝ ስለምፈልግ እንዳትጠፋ›› አሉኝ ፈገግ እያሉ፡ አልጠፋም ኮሎኔል ብቅ እላለኹ ብያቸው ተጨባብጠን ተለያየን፡፡ ኮሎኔል ወደፊት የሕይወት ታሪካቸውን ለመጻፍ እንደሚፈልጉና ለዚህም የሌሎች ኢትዮጵያን ወገኖቻቸውን ድጋፍና እገዛ እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል፡፡ ወደፊት ኮሎኔል ካሳሁን የሕይወት ታሪካቸውን የሚተርክ መጽሐፍ ጽፈው እንደሚያስነብቡን አንዳንች እርግጠኝነት በልቤ ውስጥ እየተሰማኝ ተሰናበትኳቸው፡፡

ሰላም! ሻሎም!

Reproduced- at Ethiopian Semay (wwww.ethiopiansemay.blogspot.com) Getachew Reda