Saturday, August 2, 2025

የእነ ደቂቀ ተወለደምድኅንና የነ ጎበዜ ጎሹ ግፍስ ምን ልትለው ነው? መልስ ለጽንፈኛው የትግራይ ብሔረተኛ አስራት አብርሃም ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay 8/2/25

 

የእነ ደቂቀ ተወለደምድኅንና የነ ጎበዜ ጎሹ ግፍስ ምን ልትለው ነው?

መልስ ለጽንፈኛው የትግራይ ብሔረተኛ አስራት አብርሃም

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay 8/2/25

ባለፈው ትችት ላይ አስራት አብርሃም ማን እንደሆነ ገልጫለሁ። አስራት አብርሃ (ከአገር በስተጀርባ መፅሐፍ ደራሲ) ነው። ሰውየው ሕሊናው የጨለመበት እልም ያለ የታወረ ጸረ አምሐራ ዘረኛና ፤  ኢትዮጵያም ፈርሳ ማየት የሚሻየዓረና ፓርቲ አባል የነበረ ፤ በምኒሊክ ሴራ ንጉሣችን ዮሐንስ መተማ ከተሰዋ ወዲህ ፤ የነበረን ሥልጣን ነፃነትና ክብር ተነጥቀን በሸዋዎች ተገዛን፡ የትግራይ ሰዎች ሥም በአማርኛ ሆነ፡ የሚል “የሀገረ-ትግራይ” አክራሪ አቀነቃኝ ነው

ሰሞኑን ደግሞ በትግርኛ ፡ በገጸመጽሐፉ ላይ (በፌስቡኩ) ላይ “የቂቀ ኢስጢፋኖስ ተከታዮች የተለየ የእምነት ስርዓት ስላላቸው የተጨፈጨፉት ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም ወይ? ኢትዮጵያ ወደ 700 አመታት በትግሬዎች ላይ ያላሳረፈቺው ብትርና ጭቆና የለም  ወይ? ትግራይ እኮ የነፃነት ሃገር፤ የማንም ሃይማኖት አክባሪ “ሃር” ነች” በማለት በኢትዮጵያ ላይ የለመደበት ክሕደትና “እኩይ” ጥላቻውን ለመግለጽ፡ ዶ/ር ገብረየሱስ በሚባል ኢትዮጰያዊ የትግራይ ተወላጅ ላይ “ኢትዮጰያዊ ነኝ” ሰላለ ብቻ በሰውየው ላይ የማጠልሸት ዘመቻ አድርጓል።

ዶከተር ገ/የሱስ “ኢትዮጰያዊነቴን” ድሮም አሁንም ጥንትም ነገም የሚቀጥል ማንነቴ ነው፡ ኢትዮጵያ የነፃነት ቀንዲል/ምልክት ነች።” ብሎ በማለቱ፤ ጽንፈኛው አስራት አብርሃም ክፍል ፩ ክፍል ፪ ብሎ ለ ዶ/ር ገብረየሱስ በሰጠው መልስ ውስጥ ሃይማኖትን በሚመለከት ከላይ የጠቀሰኩት ነጥብ ይገኝበታል።

አስራት አብርሃም ትግራይ የተለያዩ የሃየማኖት እምነት ተከታዮች መብት አክባሪ ኢትዮጰያ ግን የማታከበር አድርጎ ትግራይ የገነት ምድር አድርጎ ለመሳል በጽንፈኝነት ባሕሪው በዶክተሩና በኢትዮጵያ ሃገራችን ላይ ሊያላግጥ ሞክራል። ሃቁ ግን ተቃራኒው ነው።

አሁን የማሳያችሁ፤ ጽንፈኞቹ የደበቁትና ሊነሳ የማይፈልጉትን የ19ኛው ክ/ዘመን የትግራይ ፕሮተስታንት (አንዳንድ ሰዎች በዘጠኝ መለኮት የሚያምኑ “ቅባቶች” ናቸው ፤ ጸረ ምንኩሰናም ናቸው ይልዋቸዋል) ግፍና ስቃይ በትግራይ ምን ይመስል እንደነበር እንመለከታለን።

 “ደቂቀ ተወለደምድኅን ወያኔዎች የደበቁት የፕሮተስታንት ታሪክ በትግራይ - ደራሲ ጌታቸው ረዳ (ሕዳር 2005 ዓ.ም ) የሚል መጽሐፌን አንብቡ፤ ያላገኛችሁት ካላችሁ አሜሪካ ውስጥ በጣም ጥቂት ቅጂዎች ይገኛሉ አሁንም መግዛት ትችላላችሁ።

ተወለደመድኅን ገብሩ እና ጎበዜ ጎሹ የዓድዋ (ማይ ሚሻን) ሰው ሲሆኑ ሁለተኛው ሰው ደግሞ የማሕበረዴጎይ (አክሱም) ሰው ናቸው። ሁለቱም ሰዎች የታወቁ የኦርቶዶከሰ ቀሳውስት ኖሮው በስዊድን ሚሲዮኖች ሰባኪዎች ምክንያት ለሕክምና ወደ ኤርትራ ሄደው ወደ ከኒሻ (ፕሮተስታንት) የተለወጡ ናቸው። በዚህ አዲሰ እምነታቸው ሕዝብን ለማሳመንና ለመመልመል/ለማስተማር/ ትግራይ ውስጥ በተለይ ዓድዋ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነ “የኢቫንጀሊካል መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት” መሰረቱ።

በመሰረቱበት ወቅት የነዚሀ ሰዎች የመብት ረገጣ እና ጥቃት ለማወቅ ባደረግኩት ጥናት መጽሐፌ ውስጥ ከሰፈረው ጥቂቱን ላስነብባችሁ እና በዚህ አጋጣሚም አስራት አብርሃም በንጉሠ ነገሥት ዘርአ ያዕቆብና ደቂቀ እስጢፋኖስ የተደረገው የሃየማኖት ክርክር የነገድ (የዘር) ነክ እንዳልሆነና በማስረጃ ምን ይመስል እንደነበር፤ ያላወቀ ከሆነም በዛው መጽሃፌ ውስጥ “የአፄ ዘርአ ያቆብና የአባ እስጢፋኖስ ክርክር የሸዋና የትግሬ ጸብ አልነበረም” የሚል በገጽ-97”  ያሰፈረኩትንና ክቡር ፕሮፍሰር ጌታቸው ኃይሌ መጽሐፌን አንብበው ያከሉበትን ምሁራዊ ትንተና አስተያየት እንዲመለከተው እመክራለሁ።

ወደ ፕሮተስታንቶቹ ሁኔታ ልመለስና ይህንን አሰቃቂ የእምነት ረገጣ በትግራይ ብሔረተኞች ትርጉም “ነፃነት” ተበሎ ይተረጎም ይሆን? የሚል እኔም ለአስራት አብርሃም ልጠይቅ።

ለማንኛውም ገፉ ምን የምስል ነበር?

ከመጽሐፌ ልጥቀሰላችሁ፤

ለሕዝብ ክፍት ሆኖ በደወል የተጠራው ችሎት

በግንቦት 1915 ዓድዋ ከተማ ውስጥ የሚገኙት አምስቱ የቤተክርስትያን ገዳማት ኗሪዎች ወደ መሃል ገበያ እንዲሰበሰቡ የአዋጅ ደወል አስተጋቡ። ወደ ችሎቱ ያልሄደ ኗሪ እንደ “ጸረ ማርያም” ተቆጥሮ እርምጃ እንደሚወሰድበት ታወጀ።ስለሆነም የአዋጁን ደወል የሰሙ ኗሪዎች ፀሐይ ወደ መውጫዋ ስትቃረብ ጉዟቸው የዕለቱ ችሎት ይሰማል ወደተባለው ወደ ከተማዋ መሃል ገበያ አቀኑ።

ዓድዋ ከተማ ማሃል ገበያ ላይ በተባለው ቀን እና ሰዓት ሕዝቡ ጢም ብሎ አረጋዊ፤ ወጣት፤ሴት እስላም፤ ክርስትያን ሳይለይ በሙሉ ገበያውን አጥለቀለቀው። 27ቱ ሃይማኖት ነክ ተከሳሾች እና ማሕበራዊ ነክ ወንጀል የፈጸሙ ተራ ወንጀለኞች ጋር ተደምረው በጠቅላላ 44 እስረኞች ጥንድ፤ለጥንድ በሰንሰለት በእግረ ሙቅ ታስረው ክፍት ችሎት ወደ እሚሰማው ቦታ በጠባቂዎች ተይዘው ወደ ገበያው እንዲመጡ ተደረገ። የሕዝቡ ብዛት ከመጠን በላይ ስለሆነ እነሱን ገፈትሮ ወደ ችሎቱ ለመድረስ ጠባቂዎቻቸው ከሕዝቡ ጋር ከባድ ትግል ገጠሙ። ተመልካቹ እስረኞቹን ለማየት አንዳንዱ ካብ ላይ፤ እወንዝ ባሻገር ላይ ባሉት ጉብታዎች፤አጥሮች ላይ ተንጠላጥለው ይመለከታሉ። በቅርብ ርቀት የተሰገሰገው ተመልካችም  እነሱን ለማየት አንገቱን እያሰገገ/እየተንጠራራ/ እርስ በርስ ይገፋፋል።

እስረኞቹም አንዳንዶቹ እምባ ያቀራሉ፤አንዳንዱም ለጠላት ደስ አይበለው ካንገት በላይ ፈገግ እያሉ ይስቃሉ። እንደምንም ብለው ዘበኞቹ ከሕዝቡ ጋር ተጋፍጠው ማስገቢያ በመክፈት እስረኞቹን ወደ ችሎቱ ፊት ወደ ማሃል አስገቧቸው።

በጣም የሚያስፈራው እና እንዲህ ብታደርግ “ወዮልህ” በማለት ሕዝቡን የሚያስጠነቅቁ አስፈሪ “የምቀጫ ቁሳቁሶች” ተቀምጠው እመሃል ይታያሉ። እገበያው ላይ ካለው መጠነኛ ዛፍ የተንጠለጠለ አለንጋ እና ረዢም ጅራፍ እና ፈንተት ብሎ በተዘጋጀው ልዩ ጠረጴዛ ላይም አስፈሪ “የሰላ ቢላዋ” ይታያል። ቁሳቁሶቹ የሚያስተላልፉት  መልዕክት ከጥንት ተያይዞ የመጣውን  የወላጆቻቸው ሃይማኖት የሚያራክሱ ሰዎች ከተገኙ የሚደርስባቸው ዕጣ ፈንታ የሚቀጡበት በግልጽ በሚታዩት በነዚህ አስፈሪ የማሰቃያ (የመቅጫ ዕቃዎች) እንደሆነ ኗሯዎቹ እንዲያዩት ለማስጠንቀቅ የተቀመጡ ዕቃዎች ናቸው።

በአባታቸው (በደጃዝማች ገብረስላሴ) ፈንታ ተወክለው ችሎቱን ለመምራት የተሰየሙት ሹም ደጃዝማች ተ/ሃይማኖት ገብረስላሴ  ወደ ጠረጴዛው ታጅበው ተቀመጡ። ሕዝቡም የሳቸውን እና የተከሳሾቹን ድመፅ ለማድመጥ ያመቸው ዘንድ በተቻለው መጠን ወደ ፊት ወደ ችሎቱ ለመጠጋት አርስበርሱ ክፉኛ እየተገፋፋ ነው። እማሃል ከተቀመጡት ደጃዝማቹ ጋር ግራ እና ቀኝ ከተሰየሙት መኳንንት ፤ ካህናት ፤ ታዋቂ የአገር ሽማግሌዎችና ሊቃውንት አብረው ተቀምጠዋል።

ቀደም ብለው በመጀመሪያው ችሎት የተገኙት አራቱ ምስክሮችም ተገኝተዋል። የክሶቹ ዓይነትም ያው ናቸው።በመጀመሪያ ለጥያቄ ቃላቸው እንዲሰጡ የቀረቡ ተከሳሾች ዋናዎቹ አለቃ ተወልደመድህን ገብሩ፤ጎበዜ ጐሹ፤ገዛኸኝ ወልደገሪማ እና ተሰማ እንግዳ ነበሩ። “መመሪያችሁ ምንድ ነው? የሚለው ለሁሉም የቀረበላቸው ጥያቄ ነበር። እኛ የምንመራው በቡሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን ትምህርት ነው፡ በማለት ሁሉም ተመሳሳይ መልስ ሰጡ።በችሎቱ የነበሩ ሊቃውንት አንዳንድ ጥያቄ አቅርበው ሲከራከሯቸውም አቋማቸው ሳያዛቡ ጠንከር ብለው የመጸሕፍት ጥቅስ እየጠቀሱ ተከራከሯቸው።

ክርክሩ በእንደዚህ ያለ የክርክር ሂደት እየቀጠለ ሳለ “ቄስ ወልደገሪማ እንደ ቄስነትዎ ቤተክረስትያን ውስጥ በቅዳሴ ስርዓት የማርያምን ስም እያወደሱ ሲቀድሱ በሌላ ጎን ደግሞ ተቃራኒውን ያምናሉ፡ ይህ እምነትዎ አልተጋጨም ወይ? ለሚለው ከዳኞቹ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ እንዲሰጡ ሲጠየቁ፡ አለቃ ተወልደመድኅን ጣልቃ በመግባት፡ “እንዴ ቅዱሳን መላእክትም እኮ ያመሰግኗታል፤ቅዱስ ኤፍሬምም አመስግኗታል፤ አባቶች እንደሚያመሰግኗት እና እንደሚያከብሯት ሁሉ እኛም እንዲሁ እናመሰግናታለን፤እናከብራታለን ነገር ግን እናንተ እንደምታምኑት “ፈጣሪያችን ነች፤ አዳኛችን ነች፤አማላጃችን ነች፤ ብለን አናምንም።”(269)

ደጃዝማች ተክለሃይማኖት ገብረስላሴ ወደ ሌላኛው ተከሳሽ ወደ አለቃ ጐበዜ ዞር ብለው፤

 “አንተ ሕዝባችንን የፈረንጅ ቱልቱላ እና ተከታይ ለማድረግ ከምትቀበለው የሚሲዮናውያን እና የጀርመኖች ገንዘብ ለሕዝበ እየበተንክ ስብከት ውስጥ ገብተሃል። ሲሉ ጮኹባቸው።

ጐበዜም “ለሕዝብ የምበትነው የገንዘብ አቅምም ሆነ ምንጭ የለኝም።ቢኖረኝ ኖሮ ወደ ትሪፖሊ እየተጋዙ የሚሄዱትን ምሲኪኖች ገንዘቡን በሰጠኋቸው፤ ራሳቸውን አሰማርተው ኑሯቸው የሚያሸንፈበት የግብርና ወይንም የንግድ የመረዳጃ ተቋም በከፈትኩላቸው ነበር፤ ሆኖም አቅሙ የለኝም።” ሲሉ መልስ ሰጡ።

የደጃዝመች ገ/ብረስላሴ ልጅ የሆኑት ደጃዝማች ተ/ሃይማኖት ዘመናዊ ቀመስ ትምህርት ጣሊያን አገር ድረስ ሄደው የተማሩ ስለሆኑ የአለቃ ጎበዜ ጎሹ መልስ እንደ ድፍረት ስለቆጠሩት “አንተ የምታደርገው ለልዩ ተግባር ነው። ወደ ትሪፖሊ ሚሄዱት አበሾች በየወሩ የሚቀበሉት 100FRCs ፍራንክ ነው። አንተ የምትሰጣቸው ገንዘብ ግን 3FRC ነው።ይሄ ደግሞ ሆን ብለህ ለተነሳህበት ዓላማ ለማሳካት ሕዝብን ለማሳሳት የምታደርገው ዘዴ ነው፡” አልዋቸው።

ጎበዜም “ክቡር ሆይ እኔ ጀርመኖች ስለተባለው ጉዳይ የማውቀው ነገር የለኝም። ሆኖም እየተወቀስኩ ያለሁበትን በገንዘብ የመደለል ጉዳይ 3 ሰልዲ (ሰልዲ የጣሊያን ነሃስ /ኮፐር ‘የብረት’ ገንዘብ ነው። 1 ሰልዲ 1/20 የጣሊያን ሊሬ ነው) ከኔ የተቀበለ ሰው የለም።ካለም ይቅረብ እና እቀጣለሁ።በማለት መልስ ሰጡ።

ክርክሩ ተሰምቶ እንዳበቃ ዳኞቹ ውሳኔ ላይ ለመድረስ እርስ በርሳቸው በመወያየት ላይ እንዳሉ አንድ መልእክተኛ ከሩቅ እየተጣደፈ ወደ ችሎቱ መሃል በመንድርደር የቴሌግራም መልእክት ይዞ በመምጣት ለምክትል ገዢው ለደጃዝማች ተ/ሃይማኖት ገ/ስላሴ ሰጣቸው። የቴሌግራሙ መልእክት አንብበው ካጠገባቸው ጋር ካሉት ሾመኞች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ፤ ፊታቸውን ቀና አድርገው ወደ ተከሳሾኩ ፊት ለፊት ትኩር ብለው እያዩ “እንደ እኔ፤ እንደ እኔ ፍላጎት እና ስልጣን ቢኖረኝ ኖሮ ሳር ጎጆ ውስጥ ሁልሽንም አስገብቼ እሳት ነበር የምለቅባችሁ!” …“ሆኖም የበታች ባለ ስልጣን ስለሆንኩ የበላይ ባለስልጣን ለምክር እና ውሳኔ በቴሌግራም በጠየቅኩት መሰረት የተሰጠኝ መልስ በነፃ እንዳሰናብታችሁ ስለታዘዝኩ ፍርዱ ተዘግቷል፤ሂዱ!” በማለት በቁጣ ተከሳሾቹን እዛው ትተው ከችሎቱ ተነሱ።

ቴሌግራሙም ከወላጅ አባታቸው ከአዲስ አበባ ከደጃዝማች ገ/ስላሴ የተላከው ትዕዛዝ የሚለው “በሃይማኖት ጭቅጭቅ ውስጥ አትግባ፤ ተከሳሾቹን አሰናብታቸው።” ነበር መልእክቱ የሚለው። ሆኖም ተከሳሾቹ እንዲሰናበቱ በቃል ቢነገርም በተግባር ግን ሳይፈቱ ቀርተው እንደገና ጥንድ፤ጥንድ ሆነው ለሁለት በሰንሰለት ታስረው ወደ ነበሩበት እስር ቤት ተወሰዱ

ወደ እስር እንደተመለሱ፤ ምግብ ይዘውላቸው ወደ እስር ቤቱ የመጡት ባሻይ መድሃኔም የጸረ ማርያም ተባባሪ ነህ ተብለው በሰንሰለት ታስረው ወደ እስር ቤት አብረው ከጓደኞቻቸው ጋር ተቀላቀሉ።እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ እነ የማነ ብርሃን አበራ የተባሉት እና ሌሎች የማይ ሚሻን ኗሪዎች ስድስት ሰዎች እየተለቀሙ ታሰሩ።ልጅ ተድላ ነጋሲ የተባሉትም ወንድ ልጆቻቸው እና የሴት ልጃቸው ወንድ ልጅ አስመራ ሚሲዮን ትምህርት ቤት እንዲማሩ ልከሃል ተብለው ወደ እስር አስገቧቸው።አንዳንዳንዶቹም እየሸሹ ራቅ ወዳለ ቦታ እየሄዱ ተሸሸጉ።ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሌሎች የሚጠረጠሩ ሰዎችም እንዲሁ ወደ እስር ቤት እየተለቀሙ ታሰሩ።ምንጠራው እየተጧጧፈ ሲሄድ ወታደሮቹ ወደ ታሰሩ እስረኞች መኖርያ ቤት በመሄድ ያገኙትን ምግብ፤ንብረት እና ገንዘብ ዘረፏቸው።

የእስረኞቹ ቤተሰብ የሆኑት ሴት ፤ህፃን፤ሽማግሌ መጠለያ እና ለደህንነታቸው ሲሉ እንዲያጠሏቸው ፈቃደኞች ወደ ሆኑ ርህሩህ በጎ አድራጊ ጎረቤቶች እና ዘመድ አዝማድ መኖርያ ቤት ዘንድ እየሄዱ መጠለል እና መሸሸግ ጀመሩ።አንዳንዶቹ ማስጠጋታቸው ችግር እንደሚያመጣባቸው ቢያውቁም በድፍርት ተባበሯቸው።

ሁተኛ ዙር ችሎት

በሚቀጥለው ዓርብ እስረኞቹ እንደዘወትሩ በሰንሰለትና በገመድ ተጠፍረው ወደ ምክትል አገረ ገዢው ቤተመንግሥት መኖርያ ግቢ ለምርመራ ቀረቡ። ወደ አገረ ገዢው መኖርያ ታስረው በእግር ሲጓዙ አላፊ አግዳሚ ሕዝቡ ከብቦ ይሳለቅባቸው እና ያመናጭቃቸው ነበር።እስረኞቹ ወደ ግቢው ከገቡ በኋላ ሕዝቡ የግቢው አጥር በመጣስ ሆ! ብሎ በነቂስ በመግባት “እነዚህ ጸረ ማርያም ምንም ምሕረት አያስፈልጋቸውም፤ መገደል ነው የሚገባቸው።” እያሉ በጩኸት ግቢውን ማወክ ጀመሩ።ዘበኞቹ በስንት ግብግብ እና ድብድብ ሕዝቡን እየገፉ በመከራ ከግቢው እንዲርቅ አደረጉ።

በምርመራው ሂደት አለቃ አዛርያስ በዋስ እንዲፈቱ ተደረገ። አለቃ አዛርያስ በስቅለተ ዓርብ ከአለቃ ጐበዜ ቤት በመሄድ ከሚሲዮናውያኑ ፈረንጆች ጋር ሆነው ጠጅ ሲጠጡ ነበር፡ ተብለው መከሰሳቸው ይታዋሰል።ጎበዜ ቤት ሄዶ ጠጅ ሲጣጣ አይቻለሁ የሚል የዓይን እማኝ ስላልተገኘ ለጊዜው በዋስ እንዲለቀቁ ሆነ።

አቶ ወልደስላሴ የተባሉ ሃብታም ነጋዴም እንደዚሁ አራት ልጆቻቸው በሚሲዮኖች ት/ቤት በግዴታ አስመዝግበሃል ተብለው ተከስሰው ሲጠየቁ........... እያለ ወደ አስከፊው “ከሕብረተሰቡ መገልለ” መኖርያ ቤቶቻቸው በድንጋይ መወገር ግርፋትናስደት” መጽሐፉ ወደ ሰፊው ዝርዝር ይወስደናል። ችግሩ በዓድዋና በአከሱም ብቻ አላቆመም በመላ ትግራይ ውስጥም የተደረገ ግፍ ነው።

 ታዲያ አስራት “የአፄ ዘርአ ያዕቆብ አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቹ ትግሬ በምሆናቸው ጨፈጨፋቸው” እያለ ያለተፈጸም ታሪክ ሲያጣምም ይህ ትግራይ ውስጥ የተደረገው ድርጊት በምን ዓይነት በፃንት ይገልጸው ይሆን? በመሰረቱ አባ እስጢፋኖስ እንዲቀጡ የጠየቁት የትግሬ አበምኔቶች ናቸው። ነጻ ሲባሉም ተመልሰው ሀደው ዋልድባ ቢታቀቡም ትግሬዎቹ እዛ ደረስ ሄደው መኖርያ ቤታቸውን አቃጠሉባቸው። በዶ/ር መስከረም ለቺሳ የተጻፈ  “ደቂቀ እስጢፋ -ታላቁ ዓመጽ ሲጋለጥ (2016 ዓ.ም) ያሳተመቺውን አስገራሚ መጽሐፍ የአባ እስጢፋኖስ ምንነትና በዝርዝር በሕዝብ ጀሮና ዓይን ተሰምተውና ተነብበው የማያውቁ ታሪኮችን ማንበብ ይጠቅማል። አፄ ዘርአ ያዕቆብ አባ እስጢፋኖስን “እስጢፋ” (ሰይጣን) ይላቸዋል። አባ እስጢፋኖስ የአክሱማዊው ቅዱሰ ያሬድ ማኅሌትን እንደሚቃወሙና “ደብረ ጽዮን የሚባል ነገር የለም” ይሉ እንደነበር ዶ/ር መስከረም በሰፊው አብራርታለች። መጽሐፉን ግዙና በታነቡት በደቂቀ እሰጢፋኖስ የነበራቸሁ አስተሳሰብ በማስረጃ ይቀይረዋል።

ማጠቃለያ

ይህ ምጽሐፍ ስጽፍ እምቴ የተዋኅዶ ኦርቶዶክስ አማኝ ፤ የሰው ለጆች የፈጠረ የእየሱስ እናት ናት ተብላ የምትታመን እትብቴም በአክሱም አፈር የተቀበረ ፤ ተጠምቄ፤ ጽዮን ጉያ ውስጥ ታቅፌ ያደግኩ ቤትየም ከጽላቱ በስተጀረባ ሆኖ ሲቀደስና ሲደወል ቀንም ሌሊትም ሳደምጥ ቅብአ ሜሮን እየተቀባሁ ዕጣንዋን እያሸተትኩ ያድግኩ እንጂ “ፕሮተሰታንት” (ከንሻ) እንዳልሆንኩ ለመግለጽ እወዳለሁ። ይህንን ለመጻፍ ያስነሳኝ እንደ አስራት አብርሃም የመሳስሉ ጸረ አምሐራ የትግራይ አክራሪ ብሔርተኞች ያለመታከት በመጽሐፍ መልክም በንግግርም “ከትግራይ እናቱ የተወለደው ንጉሥ ዘርአ ያዕቆብን አምሐራ ፤ ትግራይ የሚጠላ” እያሉ በሃይማኖት አሳብቦ የትግራይ አማንያንን የጨፈጨፈ “የሸዋ አምሐራ ነው” እያሉ ሲዋሹ ስለተመለከትኩ ነው ይህንን “ወያኔዎች የደበቁት “ትግሬዎች በትግሬዎች ላይ የፈጸሙት የእምነት ረገጣ ለማሳየት “ደቂቀ ተወለደምድኅን ወያኔዎች የደበቁት የፕሮተስታንት ታሪክ በትግራይ - ደራሲ ጌታቸው ረዳ (ሕዳር 2005 ዓ.ም )” የሚል መጽሐፍ ለጽፍ የተገደድኩበት መነሻ የትግራይ ፋሺስቶች አደብ እንዲገዙ ለማሳሰብ ስል ነው።

መልካም ቅዳሜና ዕሁድ ይሁንላችሁ!

ጌታቸው ረዳ

 

No comments: