አፄ ዮሐንስ አፄ ምኒልክ ሊቀ መርዓዊ እና አፈወርቅ ገብረየሱስ
መልስ ለታሪክ ምሁር ነኝ ባዩ አቶ ተሰፋኪሮስ አረፈ
ከጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay
8/11/25
ሰሞኑን በራኸ ሾው (ከፍታ) በሚባለው የተገንጣዮች ሚዲያ ላይ ፤ በሁለት ተከታታይ ክፍሎች
የቀረበው በዓይነቱ ለየት ያለ ሞቅ ያለ ውይይት ፤ በግጭት አፈታት ተመራማሪው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር በኢትዮጵያዊው የትግራይ
ተወላጅ ዶ/ር ገብረየሱስ ተኽሉ መካከልና የታሪክ ምሩቅ ነኝ በሚል “በአቶ ተስፋኪሮስ አረፈ” የነበረው ውይይት ሕሊናየን ከሳቡኝ
ውይይት ቀዳሚው ነበር። ይህ ጉዳይ ባለፈው ሰሞን ነካክቸው የነበረው ከውይይቱ የታዘብኩት ቀጣይ ክፍል ነው።
ተሰፋኪሮሰ አረፈና መሰል “የሃገረ ትግራይ ሪፑብሊክ” ለመመስረት ከሚጥሩ የትግራይ ተገንጣዮች
ያስታወሰኝ ነገር ፤‘ኤርትራኖች
በኢትዮጵያ የኖሩበትን የምዝበራ ስልታቸው ያስታውሰኛል። ኤርትራኖች አዲሰ አበባ ውስጥ እየኖሩ የግንጠላ ደጋፊዎች ሆነው ኢትዮጰያን
ሲያፈርሱና ሲበዘብዟት እንደነበረው ሁሉ ፤ ይህ ሰውና በመቶዎቹ የሚቆጠሩ አዲሰ አበባ ከተማም ይሁን ትግራይ ውስጥ በኢትዮጵያዊያን
ግብር ከፋዮች የተገኘ ሕክምናም ባንክ አግለገሎት ትራንስፖርት ይሁን ነዳጅና መብራት ልክ እንደ ሃገርኛው
ተጠቃሚ ሆነው ወፍራም ደሞዝ እይተከፈላቸው በምቾት እየኖሩ ከሚገኙት ተገንጣዮች አንዱ ነው።
ይህ ሰውና አምሳያዎቹ ኢትዮጰያዊ አይደለሁም «ሃገሬ ትግራይ ነች»
እያሉ ኢትዮጵያን ለማውደም “በኦነጋዊው ኦሮሙማው አብይ አሕመድ ተባባሪነት ትግራይን የመገንጠል አጀንዳው ያለምንም ስጋት እንዲያካሂድ የተፈቀደለት
ሃገሬ በማይላት በሚጠላት ኢትዮጵያ
ውስጥ ጥገኝነት ሳይጠይቅ አዲሰ አበባ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር «ሕገወጥ ስደተኛው» ሃይለኪሮሰ አረፈ
እና ከኢትዮጰያዊው የትግራይ ተወላጅ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ገብረየሱስ ተኽሉ ጋር
ያደረገው ውይይት ኢትዮጰያዊያን ትግሬዎች ያደምጥን ሁሉ ተገርመናል ።
መጀመሪያ ስለ ሰውየው የመወያየት “ዶማጎግ” ባሕሪው ቃላት ቢያጥሩኝም ባጨሩ ልግለጽና ወደ ርዕሱ እገባለሁ።
አቶ ተሰፋኪሮሰ አረፈ ፤- ተወያዩን ለማሳነስ እንዳልተገራ ጨቅላ ማንም ሳይጠይቀው ከምንም ተነስቶ አስተናጋጀዋን እርማት አድርጊ እኔ የታሪክ ምሁር ነኝ እርሱ የስነጽሑፍ መምህር ነው የታሪክ ምሁር አይደለም እያለ በሚገርም ጨቅላነት የሚንጠራራ ፤ እጅግ ሲበዛ “እኔ ብቻ ልናገር” የሚል የተከራካሪውን ሰዓት የሚሻማ ስግብግብ ፤ ውይይቱ ሁሉ “የእንዳ ረማሚ” (የድሮ የመቀሌ ተማሪዎች ሻይ ቤት) ክርክር የሚያስመስለው ፤ የዋለልኝ መኮንን አድናቂና የሃገር አፈራሽነት ስካር የተጠናወተው ፤ ኢትዮጵያን “ሰልቃጭ” እያለ የሚግልጻት፤ ኢትዮጵያን በማበሻቀጥ ስሜቱን የሚያረካ፤ እንደኔው የተገረመው ተከራካሪው ዶ/ር ገብረየሱስ በተሰፋኪሮስ አጉል ኩፎሳ ከመገረሙ የተነሳ “እኔ እና አንተ ከእነ Enno Littmann ምሁራዊ ዓይን በጣም እጅግ እሚንቶች የሆንን ፤ የነሱ ተማሪዎች እንጂ በታሪክ ዕውቀት እኩል አይደለንምና የጠቀስኩልህን የነዚህ ሊቃውንት ምርምር ሥራ ነው» ብሎ ሲለው « በፍጹም አላንስም፤ እኔ ከነሱ አላንስም” እያለ ከታላቁ ጀርመናዊው Enno Littmann የጥንት ቅርሶችን ለማጥናት የጀርመን ሊቃውንቶችን ቡድን መርቶ ብ1897 ወደ ትግራይ ወደ አክሱም እና ኤርትራ መጥቶ ሰለ ሃውልቶቹም ሆነ ሰለ የትግሬ ቋንቋ ተአምራዊ ትርጉሞችን የገለጠልን ዓለም አቀፍ ሊቅ ራሱን እኩል በማድረግ የረባ የታሪክ ዕውቀት ሳይኖሮው ራሱን በከንቱ የሚቆልል ይህ ትንሽ ሰው በሚገረም ሁኔታ ታዘብኩት።
በጨዋ ደምብና በምሁራዊ ሙግት ያስገነዳው ኢትዮጵያዊው መሁር ዶ/ር ገብረየሱስ ተኽሉ ሳላደንቀው
አላልፍም እያልኩ፤ አሁን የተስፋኪሮስ የምኒሊክ ጥላቻውና ውሸት በቀጥታ ልግባ።
አቶ ተስፋኪሮሰ እንዲህ ይላል።
«ትግራይ ውስጥ አፄ ምኒልክ የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት
ሲሉ ትግራይ ወንድ እንዳይበቅልባት የወንድ ብልት እንዲሰለብ በማዘዝ ፤ ሴቶች ብቻ ቀርተው “የትግራይ ትወልድ እንዲመክን” ሆን ብለው “ጀነሳይድ ፈጽመዋል” በማለት ሲከሳቸው፤ ለውንጀላው መከራከያ ማስረጃ አድረጎ የጠቀሳቸው
ሰው ደግሞ ከዚህ ከታች የምንመለከታቸው በዘመኑ የነበሩ ፤ የዓይን ምስክርነታቸው በእጅ ጽሑፍ ጽፈው ናፖሊ (ጣሊያን አገር) ሲኖሩ
የጻፉት የዓድዋ ተወላጅ የሆኑት የደብተራ ፍስሐ አብየዝጊ መጽሓፋን
ነው።
እውነታው ግን የደብተራ ፍስሐ አብየዝጊ መጽሐፍ የሚለው ተቃራኒው ነው። ይህንን በሚመለከት
መጽሐፌ ላይ ተርጉሜ የጠቀስኩትን እንመልከት
እንዲህ ይላል።
“የአፄው ጋላዎች ብልት በመስለብ ሱሰኞች ነበሩ እና ሰውን እየሰለቡ መፎከር ጀመሩ። ንጉሡም
መሳሪያ ሳይማርክ “ገዳይ“ብሎ የፎከረ ሰው ወዮለት! በማለት አዋጅ አወጁ። ቢሆንም ስለ ሕልፈተ ትግራይ ልብ ላለው ብዙ አሳዝኗል።
እነኚያ የቤገምድር አማራዎች ግን በጣም ይቆጩ እና ያዝኑ ነበር።” ታሪኽ ኢትዮጵያ (፻፴፱-፻፵-(139-140)-(ትርጉም ጌታቸው
ረዳ - ኢትዮ ሰማይ- “የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” መጽሐፍ)
“በዛችው አምባ መሽገው ብዙ የሸዋን ሠራዊት የገደሉት 7 የትግራይ ተዋጊዎች መከላከላቸውን
ቀጠሉ። ምሽጉ በድንጋይ በደምብ የተገነባ ሆኖ ከአፋፉ ምሽግ ደጃፍ ላይ ወራሪዎቹን በዘዴ ለመሳብ ሆን ብለው ሰዎቹ አስቀድመው እህል
እና ጓዝ እቃ ከምረውበታል።
ሲተኰስባቸው ዝም ብለው አድፍጠው ይቆዩ እና አማራዎቹ እየተጠጉ እህሉን እና ዕቃውን ዓይተው
ለመጎተት ወደ ዳገቱ ጫፍ ሲጠጉ፤ የጥይት ዶፍ በማውረድ ከገደሉ ወደ ታች እየወደቁ ብዙ ሰው ጎዱባቸው።ይህ እንደሰሙ ንጉሡ ወደ
ስፍራው በመሄድ ሲመለከቱት አብሯቸው የነበረ ‘ኢልግ’ የተባለ የኢስፏፀራ መድፈኛ መድፉን አነጣጥሮ ዳገቱ ላይ የተገነባው ምሽግ
ላይ በመተኮስ አፈራረሰው። ከዚያ በኋላ ነፍጠኞቹ ነፍጣቸውን ወደ ታች ጣሉት። ንጉሡም “ደግ ሰው” ነበሩ እና
“ተው አትቶኩስባቸው”
በማለት እንዳይተኩስ አገዱት። ከዚያ በኋላ ንጉሡ 7ቱ ታጣቂዎች በራሳቸው መታጠቃቸው ብዙ አዘኑ።” (ታሪኽ ኢትዮጵያ ትርጉም ጌታቸው ረዳ - ኢትዮ ሰማይ- “የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው
ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” መጽሐፍ )
ደብተራ ፍስሐ በጻፉት ጥንታዊ የእጅ መጽሐፍቸው
ላይ እንዳነበባችሁት ነፍጠኞቹ ነፍጣቸውን ወደ ታች ጣሉት። ንጉሡም “ደግ ሰው” ነበሩ እና “ተው አትቶኩስባቸው” ያሉትን ንጉሡ
ዘር ጨፍጫፊ ሳይሆኑ የንጉሡ ደግነት የመሰከሩላቸውን ደግነት “ተስፋኪሮስ” ጀነሳይደር” ብሎ ሲወነጅላችው፡
ከዚያም የትግራይን ወንድ በመስለብ ወንጅሎ ስማቸውን አጠፋ።
የዓይን ምስከሩ የሚሉት “የአፄው ጋላዎች ብልት በመስለብ ሱሰኞች ነበሩ እና ሰውን እየሰለቡ መፎከር ጀመሩ። ንጉሡም
‘መሳሪያ ሳይማርክ “ገዳይ“ብሎ የፎከረ ሰው ወዮለት! በማለት አዋጅ አወጁ።” በማለት ተዋጊ ያልሆነን ሰው “እንዳትነኩ” እንዳትገድሉ፤
ብለው አዋጅ ያስነገሩና በደብተራ ፍስሐ “ደግ” ነጉሥ እንደነብሩ የተመሰከረላቸው አፄ ምንሊክን በመጥላት ታሪክ አንብቦ መረዳት ያቃተው የታሪክ መምህር አቶ ተሰፋኪሮስ ንጉሡን
በዘር ማጥፋት መወንጀሉ አስገራሚ ነው።
ከላይ በዓን ምሥከርነት ደብተራ ፍስሐ ያዩት አፄ ምንሊክ ትግራይን ለማስገበር በዘመቱበት ወቅት አፄ ምንሊክ ያሳዩት ደግነትና ለሠራዊታቸው የሰጡት ማስጠንቀቂያ አይተናል። አሁን ደግሞ
በራሳቸው በደብተራ ፍስሐ መጽሐፍ አፄ ዮሐንስ ጎጃም በተባለ የጎጃም ሰው እና ሕዝብ ላይ የፈጸሙት የጥላቻና የዘር ጭፍጨፋ የመሰከሩበትና
እራሳቸው ንጉሡም ቆይተው የተፀፀቱበትን እንመልከት።
ከዚያ በፊት ግን አቻምየለህ ታምሩ እንዲህ ያስቀመጠውን ከተስፋኪሮስ ለምኒሊክ ውንጀላና ለዮሐንስ
ወገናዊነት ውዳሴውን ለማነጻጸርም እንዲመቸን ተስፋኪሮስም ይሁን የሞተው መምህር ገብረኪዳንና መሰሎቻቸው ጎንደር ውስጥ ዘጌ ገጠር
የተወለዱት እውቁ ደራሲና የጣሊያን ተቀጣሪ የነበሩት ደራሲ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ ምኒልክን በማድነቅ “የትግራይን ሕዝብ
በጅምላ
“ችግር ያባረረው ትግሬና ባሩድ የሸተተው አውሬ አንድ
ናቸው። እንደ ቡኽር በሄትም እየዘለለ ሸዋ ለመግባት አልቦዝን አለ።”
እያሉ ሕዝብን ተሳደቡ ብለው የሚጨሱበት ስድባቸው ፤ ተሰፋኪሮስ በዚህ ውይይት የአፈወርቅ ገብረየሱስ ተናገሩ የተባሉበትን ስድብ ምን እንዳሉ ባይጠቅስም በደፈናው ስማቸውን በመጥቀስ ሁሉም አማራ እንደሚወክል አድርጎ ተስፋኪሮስ ያቀረበው ልቅሶ (ከላይ ለማነጻጸር እንዲመችኝ የጠቀስኩት ስድባቸው) የትግሬ ጥንት ጸሐፍቶችም ስለ ጎጃም ሕዝብ ምን ብለው እንደጻፉ እንመለከታል።
በመጀመሪያ
አቻምየለህ ታምሩን ልጥቀስ፤-
« የዐፄ ዮሐንስ የዜና መዋዕል ጸሐፊያቸው ሊቀ መርዓዊ የዐፄ ዮሐንስን የጎጃም ዘመቻ ሲገልጹ
«ወሖረ ሀገረ በላዕተ ሰብእ እምብሔረ ጎጃም» ሲሉ ነበር የጻፉት። ይህን የዐፄ ዮሐንስ የዘር ማጥፋት ዘመቻና አላማው ወደ አማርኛ
ሲመለስ «[ጃንሆይ] ወደ ሰው በላው [ቡዳው] አገር ወደ ጎጃም ዘመተ» ማለት ነው።” የላል አቻም።
ከዚች ቀን ጀምሮ ይህንን ማስረጃ ካቀረብኩ በኋላ አፈወርቅ ገብረየሱስ (አማራዎች) ትግሬን ሰደበ እየተባለ በትግራይ ምሁራን የሚለቀሰው ልቅሶ ከዛሬ ጀምሮ ይህንን አቻነት መሰዳደቡን ተመልከቶ እንደሚቆም እመክራለሁ።
በመቀጠል እንዲህ ይላል አቻምየለህ ታምሩ፦
« የዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ሊቀ መርዓዊ እንደነገሩን ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን ለማጥፋት ሁለት ጊዜ በዘመቱበት ወቅት «ሴቱን ጡቱን ወንዱን ብልቱን
አይተርፈኝም» ብለው አዋጅ አስነግረው ነበር።» ይላል የታሪክ አጥኚው
አቻምየለህ ታምሩ።
በማከልም አቻም እንዲህ የላል፤
«ክርስቲያን ናቸው፤ ለሃይማኖታቸው ሲሉ ሞቱ እየተባለ የሚነገርላቸው ንጉሠ ነገሥት በጎጃም የሚገኘውን ታቦት ሁሉ ከየመንበሩ እየበረቀሰ በየሜዳው እንዲጣልና ቤተ ክርስቲያኖች ሳይቀሩ እንዲቃጠሉ አደረጉ። አድማጭ ልብ ማለት ያለበት ለሃይማኖታቸው ሞቱ እየተባለ የሚነገርላቸው ዐፄ ዮሐንስ ደርቡሽ በኢትዮጵያ ላይ ያደረገውን ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠልን እርሳቸውም እንዳደረጉት ነው። ከዚህ የምንረዳው በኢትዮጵያ ታሪክ በኢትዮጵያ መንግሥትነት ተሰይሞ ቤተ ክርስቲያን የደፈረው፣ የዘረፈው፤ ያቃጠለውና ታቦቱን ሜዳ ላይ የጣለው የመጀመሪያው ወያኔ እንዳልሆነ ነው። ወያኔ ወደ ኢትዮጵያ መንበገ ሥልጣን ከመምጣቱ አንድ መቶ አመት በፊት በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትነት የተሰየሙት ዐፄ ዮሐንስ ልክ ደርቡሽ ጎንደርና ጎጃም ገብቶ ቤተ ክርስቲያን እንዳቃጠለው ጎጃምን በወረሩበት ወቅት ቤተ ክርስቲያንን ደፍረዋል፤ ዘርፈዋል፤ አቃጥለዋል፤ ታቦቱን ሜዳ ላይ ጥለዋል" ሲል በማስረጃ አሳይቷል።
እራሳቸው አፄ ዮሐንስም 3 ወር ሙሉ በጎጃም ሕዝብ ላይ ጭፍጨፋ እንደፈጸሙ ያመኑብትን ደብዳብይ ነጥበዋን ብቻ ላስቀመጥ፡ እንዲህ ሲሉ አመኑ፤-
"በእኔም በድኃውም ኃጢአት እንደሆነ አይታወቅም ጎጃምን ሳጠፋው ከረምሁ። ተጻሕፈ በዳሞት ሰፈር። አመ ፭ወ፮ ለኅታኅሣሥ በ፲ወ፰፻፹፩ ዓመተ ምሕረት።" ሲሉ አመኑ፤-
እንግዲህ! በዚህ የዐፄ ዮሐንስ ደብዳቤ በግልጽ እንደተቀመጠው የጎጃም ድሃ ያለ ጥፋቱ «ሳጠፋው ከረምሁ» ብለው በራሳቸው አንደበትም ነግረውናል።
በተጨማሪም ከላይ የደብተራ ፍስሐ ምስክርነት ያጣመመው የተሰፋኪሮሰ ውሸት አሳይቻለሁ። አሁን ደግሞ የትግራይ መሁራን የሸሸጉት የዐፄ ዮሐንስ አራተኛ የጎጃምን ሕዝብ «ሴቱን ጡቱን ወንዱን ብልቱን አይተርፈኝም» ብለው ያወጁት የዘር ዕልቂት በደብተራ ፍስሐ አብየዝጊ ምስክርነት እንደገና ልጨምር፦
እንዲህ ይላሉ፡
ከገጽ ፻፲፱ (119) እስከ ገጽ ፻፳ (120) ላይ ደብተራ ፍስሐ ጊዮርጊስ አብየዝጊ “ታሪኽ ኢትዮጵያ” በሚል 1899 ፈረንጅ (1891 ዓ.ም በትግርኛ ቋንቋ በእጅ ጽሑፍ የጻፉት መጽሓፋቸው) አጼ ዮሐንስ በጎጃም ሕዝብ ላይ ያደረሱትን 3 ወር ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ እንዲህ ይገልጹታል፦ “ወደ አማራ አገር ገሠገሡ። ከሁሉም ነገር የጎጃሜው ክዳት አንጀታቸው አብግኖአቸው ነበርና እሱም (ንጉሡም) ጎጃም መግባታቸው ስመቶ ነበርና መግባታቸውን ሰምቶ ወደ አምባ ሄዶ ተሸሸገ። ንጉሡም በሠራዊታቸው እንዲከበብ አደረጉት። እዛው መሸጉና ጎጃምን እልም አድርገው አጠፉት። ጎጃም የከሐዲ አገር ነው ተብሎ “ጎጃም የተባለ ሁሉ” እንደ ከንቱ ነገር “እየታየ” ይገደል ነበር። (ገጽ ፻፲፱ (119) እስከ ገጽ ፻፳ (120) ላይ ደብተራ ፍስሐ ጊዮርጊስ አብየዝጊ “ታሪኽ ኢትዮጵያ” በሚል 1899 ፈረንጅ 1891 ኢትዮ ዘመን አቆጣጠር በትግርኛ ቋንቋ በእጅ ጽሑፍ የጻፉት መጽሓፋቸው። (ትርጉም ጌታቸው ረዳ -ኢትዮ ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ)
ወደ ዝርዝሩ ከመግባቴ በፊት
ልታተኩሩባት የምፈልጋት የገለጽዋት ዋና ነጥብ፤ የትግርኛው ጽሑፋቸው እንዲህ ይነበባል፡
ትግርኛ
“ንጎጃም ፡ ሕልም ፡ አቢሎም
፡ አጥፍእዋ። ካሐዳይ ፡ ሃገር ፡ እዩ ፡ ተባሂሉ ፡ ጎጃመታይ ፡ ከምከንቱ ነገር ፡ ይቅተል ፡ ነበረ።” የደራሲው እጅ ጸሑፍ አጣጣል ልክ እንደታተመው አቅርቤዋለሁ።
አማርኛ ትርጉም
«ጎጃምን እልም አድርገው
አጠፉዋት። ጎጃም የከሐዲ አገር ነው ተብሎ “ጎጃም የተባለ ሁሉ” እንደ ከንቱ ነገር “እየታየ” ይገደል ነበር።»
የሚለው ስንመለከት “ጎጃም የተባለ ሁሉ” እንደ ሰው ፍጡር ሳይሆን እንደምን ተቆጥሮ ይገደል ነበር አሉ? እንደ “ከንቱ ነገር” ተቆጥሮ ይገደል ነበር።
እዚህ ላይ አፄ ዮሐንስ
በጎጃም እና አፄ ምኒልክ በትግራይ ውስጥ ምን አደረጉ የሚሉ ነገሮችን በማስረጃ አሳይቻለሁ።
የትግራይ አክራሪ ብሔረተኞች
ትግራይ ውስጥ አፄ ምኒልክ የትግራይን ሕዝብ ለማጥፋት ሲሉ ትግራይ
ወንድ እንዳይበቅልባት የወንድ ብልት እንዲሰለብ በማዘዝ ፤ ሴቶች ብቻ ቀርተው ትወልድ እንዲመክን “ጀነሳይድ ፈጽመዋል” በማለት
ተሰፋኪሮሰ አረፈና መሰል “ተገንጣይ ቡድኖች” አፄ ምኒልክን በዘር ዕልቂት የውሸት ክስ እየፈጠሩ አዲሱን የትግራይን ትውልድ ማሳሳታቸው
ታሪክ ላይ ጉዳት እያደረሱ ስለሆነ አዲሱ ትውልድ ከነዚህ ሰዎች መርዛማ ቅስቀሳ እንዲርቅ እመክራለሁ።
ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay
8/11/25

No comments:
Post a Comment