መፈንቅለ መንግስትና ሕዝባዊ አልገዛም ባይነት ሁለቱ አስፈላጊ ናቸው
ጌታቸው ረዳ
(Ethio Semay)
ኢትዮ ሰማይ
10/22/2021
መፈንቅለ መንግሥት በኢትዮጵያ
አንጀት አርስ ሞጋች በታጣበት በዚህ ፈታኝ ዘመን እምዬ ኢትዮጵያ አምጣ የወለደችልንን ወጣቱ ብርቅየው ኢትዮጵያ ወዳጄ አቻምየለህ ታምሩ ስለ መፈንቅለ መንግሥት አላስፈላጊነት ያተተበትን ጽሑፍ ትናንት አንብቤው ነበር። መልእክቱ መቶ በመቶ ከእውነተኛ ስጋት የመነጨ እና እኔም ስጋቱን የምጋራው ብሆንም በሰጠው አገላለጽ ግን የማልስማማባቸው ነጥቦች አሉ።
መጀመሪያ የወንድሜን አቻምየለህ እምነት ልጥቀስ።
እንዲህ ይላል፡
“ኢትዮጵያ ጠንካራና ብሔራዊ ስሜት ያለው ማዕከላዊ መንግሥት፣ ያልተከፋፈለና ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ስምሙ የሆነ የአገር መከላከያ ሠራዊት ሲኖራት በታሪኳ ያጋጠሟትን ችግሮች ሁሉ በድል ስትወጣ ኖራለች። በተቃራኒው ደካማና ብሔራዊ ስሜት በሌለው ማዕከላዊ መንግሥት ላይ ስትወድቅ፤ የተከፋፈለና ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ስምምነት የሌለው የመከላከያ ሠራዊት ሲኖራት ደግሞ የታሪካዊ ጠላቶቿ ሲሳይ ስትሆን ኖራለች። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲከፋፈል፣ መፈንቅለ መንግሥት እንዲያደርግና ለአመራሩ አልታዘዝም ብሎ ስዒረ መንግሥት እንዲሞክር ሌት ተቀን ሲወተውቱ የሚውሉ የፋሽስት ወያኔ አጋሰሶች ኢትዮጵያ የጠላቶቿ ሲሳይ እንድትሆን ተግተው የሚሰሩ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አገር በቀል ወኪሎች ናቸው።” ይላል።
በጣም የሚያወያየን ነው።መጀመሪያ ከላይ የተጠቀሰው የመጀመሪያው መስመር አልስማማም። ምክንያቱም “አሁን ያለው መንግሥት ጠንካራ እና ብሔራዊ ስሜት ያለው መንግሥት የለም። ስለሆነም ድሮ በድል ስትወጣ ነበረች እንጂ አሁን በድል መውጣት አልቻለችም። ለዚህ ምክንያት የሆነው፤ ‘ጠንካራ እና ብሔራዊ ስሜት ያለው መንግሥት’ ስላለሆነ ነው። ይህ የወያኔ ወራሽ የሆነው ኦሮሙማው መንግሥት “ጠንካራ ብሔራዊ ስሜት” አለው ከተባለ ማየት እሻለሁ።
ወንድሜ አቻም እንዳለው “በተቃራኒው ደካማና ብሔራዊ ስሜት በሌለው ማዕከላዊ መንግሥት ላይ ስትወድቅ፤ የታሪካዊ ጠላቶቿ ሲሳይ ስትሆን ኖራለች“። አዎን ፤ ለዚህም ነው አብይ የሚመራው ስርዓት ዘረኛ እና አገራዊ አስተዳደራዊም ይሁን የማጥቃትም ሆነ የመከላከል ጦርነት ለመምራት ብቃት የጎደለው፤ ካንገት በላይ አኖህላሊ ቃላቶችን መደርደር እንጂ በጠንካራ ብሔራዊ ስሜት ያልተቃኘ ስለሆነ፤ ገንጣዮችና ሽብርተኞች የፈለጉት ሕዝብ ሲያርዱ፤ በርካታ ከተሞች ሲያወድሙ፤ከባድ ከባድ ድፍረቶች ሲፈጽሙ፤ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ”መናፈሻ ፓርክ እየሄደ ብስክሌት ሲነዳ ፎቶ ሲነሳ ይውላል። ስለዚህም አገራችን የጠላቶቿ ሲሳይ ሆናለች።
የመጀመሪያው ወሳኝ መመዘኛ የሆነው “ጠንካራ ብሔራዊ/አገራዊ/ ስሜት” የለውምና የመመዘኛው ፈተና ወድቋል (እያየነውም ነው)። ሁላችንም ባመንበት በተወሰነ ደረጃ ጦርነቱ መደገፍ አስፈላጊ ነበርና፤ መጀመሪያ አካባቢ ደግፈነውም ነበር። እያደረ ግን ፤ ከላይ በቁንጮ የተቀመጡ የጦር አመራሮች ‘ተንኮል የበዛበት፤ ተጠያቂነት የሌለው፤ ማፈግፈግ ሲደረግ’ ለምን እንዳፈገፈገ ግልጽ ያልሆነ፤ ቢገለጽም እውነትን ያልተከተለ አታላይ ምክንያት በማቅረብ በብዙዎቻችንም ሆነ በየከተማውና በየገጠሩ የሚኖሩ ኗሪዎች አመኔታ አጥቷል።
በርካታ ሉኣላዊ ድምበሮች በውጭ ወራሪዎች ተደፍረዋል፤ ተነጥቀዋል። ሉኣላዊነትዋ ለጥቃት አመች ሆናለችና በማንኛውም ረገደድ መወገድ የግድ ነው።
መፈንቅለ መንግሥት መደረግ አለበት የምለው የኔ አስተሳሰብ “ጁንታ” ተብሎ ከሚጠራው ገንጣይ ፋሺሰት ቡድን ደጋፊዎች የኔ “መፈንቅለ መንግሥት” አመኔታ ይለያል። አቻም እንደሚለው “የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አልተከፋፈለም” የሚል እምነት ካለን ፤ ያልተከፋፈለው ሰራዊት የስርዓቱ አገልጋይ ከሆነ “አልፈየደም ማለት ነው”። ምክንያቱም ሰርዓቱ ብሔራዊ ውርደት ያመጣ አገሪቱ የጠላቶች ሲሳይ እየሆነች እያየ ይህ “አልተከፋፈለም” አንድ ነው የተባለው ሰራዊት የአንድነቱ
“ፋይዳው ምንድ ነው?”
በነገራችን ላይ መፈንቅለ መንግሥት ሲካሄድ አብይ ብቻ ሳይሆን “ይህ ውርደት እያከናነበን ላለው መሪ “ለማገልግል እና ለመከላከል በሙሉ ልባችን ከጎኑ ቆመናል”
የሚሉትን የነቀዙ ወታደራዊ አዛዦችን እነ ‘ብርሃኑ ጁላም ሆኑ እነ ባጫ ደበሌን ለሕግ ማቅርብን’ የሚጨምር መፍንቅለ መንግሥት ቢደረግ ምንም የሚመጣ ነገር የለም። ወያኔን ማሸነፍ ሲያቅተን አንድ አገር ወዳድ ከትግሬም ይሁን ከሌላ በቡድን ወታደር መፈንቅለ መንግሥት ቢያካሂድ እንመኝ ነበር። ሌሎች ግን ስጋት ነበራቸው። ተፈነቀለ ግን የተፈራው አልደረሰም። የተፈራው በከፊል ሊደርስ ቢችልም አብይ እና አሽከሮቹ “በወቅቱ እርምጃ መወሰድ የሚገባቸው እርምጃዎች ባለመውሰዳቸው፤ ለጦርነት ተዳርገናል። ይህ የሆነው “የአባትና የልጅ” ፍቅር አልቆ “ሲሻኮቱ” ጊዜ ወስዶ 'Frankenstein's monster' አይነት ታሪክ (ፈጣሪው በፈጠረው ሲበላ) ያመጣው ሰበብ ነው።
ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሲደረግ “ሳበው-ወጥር” ይኖራል? አዎ። ግን ድምበሮች በሱዳን ተይዘዋል፤” የጦር አዛዦች “ሱዳኖቹ
ወንድሞቻችን ናቸው ውግያ ውስጥ አንገባም” ሲሉ ተደምጠዋል። ከሚገባ በላይ ውድመት እና “አፍግፍግ” እያለ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙርከኞች የወያኔ ሲሳይ እንዲሆኑ” ከፈቀደ ይህ አልተከፋፈለም እየተባለ ያለው ሰራዊት ፣ መፈንቅለ መንግሥት እንዲያደርግና ለአመራሩ አልታዘዝም ብሎ
ስዒረ መንግሥት እንዲሞክር ጥሪ ካልተቀበለ ብሔራዊ ስሜቱን የሚገልጸው ለአንድ መሪ ነኝ ብሎ በሁለት ምላስ ለሚናገር መሪ ወይስ ለአገሪቱ ድህንነት?
ለአመራሩ አልታዘዝም ብሎ ስዒረ መንግሥት እንዲሞክርበት ቢደርግ ከዚህ ውርደት ማውጣት የሚችሉ ወታደራዊ ቡድኖች ስርዓቱን ቢቆጣጠሩ የተሻለ እንጂ የከፋ ውርደት አይመጣም። ብሔራዊ ስሜት አላቸው የምንል ከሆነ ፤ከነዚህ ውስጥ የወጡ ወታደሮች መስመር ማስያዝ ለምን አይቻላቸውም?
ስለ መፈንቅለ ምንግሥት ስናገር ስለ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ነው፤ ስለ ሕዝባዊ አመጽ ሳወራ ደግሞ አሜሪካ ውስጥ “በፕረዚዳንት ትርማፕ” ወቅት የታየው “የሃብታሞች መደብ ያቀነባበሩት ፋሺስታዊ/አናርኪሳዊ” ሲቪላያዊ መፈንቅለ መንግሥት ሳይሆን “ኢትዮጵያዊ ፍቅር’ በታጠቁ ፤ ፍትህ ባጡ ክፍሎች የተቀነባባረ “ሕዝባዊ አልገዛም” ባይነት አመጽን ነው እያልኩ ያለሁት። ወታደራዊ አመጹን ከጠላነው ሕዝባዊ አመጽም አያስፈልግም እያልን ነው። በጦርነት የምናሳብብ ከሆነ፤ ይህ ጦርነት ማለቂያው መቸ ነው? የሚለው ብንጠይቅ መልስ ካለ እንጠብቃለን። መሪዎቹ ጦርነቱን ይፈለጉታል።የኩሊዎች መንግሥት ሁሌም ጦርነትን “ለሥልጣናቸው ማቆያ” ስለሚያደርጉት “ጦርነቱ ሊቆም አይፈልጉም”። ስለዚህ ችካል ውስጥ ገብተን ተቸከልን ማለት ነው።
የመፈንቅለ መንግሥት አስፈላጊነት ስሜት
ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲ ትተዳደራለች በምትባለዋ ቄሳራዊት አሜሪካ የሚኖሩ ኗሪዎችዋ በጣም ብዙ አሜሪካውያን የአኗኗራቸውን መንገድ ለመጠበቅ 'መፈንቅለ መንግስት' ወይም 'ኃይል' ሊያስፈልግ ይችላል ብለው ያምናሉ። አምና በ2020 ሎስ አንጀለስ ታይምስ የተባለ ታዋቂ ጋዜጣ ባሳተመው ዘገባ በ 2017 የዳሰሳ ጥናት ውስጥ ከ 4 ቱ የአሜሪካ መልስ ሰጭዎች አንድ (1) “ብዙ ወንጀል ሲኖር” ወይም “ስርኣቱ በቁርቁዝና ሲበሰብስ” ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት “ትክክለኛ” ስልት ነው የሚሉ ዜጎች አሉ፡ በማለት ጥናቱን ያቀረቡት የቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት “ኤልሳቤት ጄ ዘክሜስተር” ተናግረዋል።
ዜጎች መፈንቅለ መንግሥት እንደ አማራጭ ለመውሰድ የተገደዱበት ምክንያቱም ይላል በ2019 የተደረገ ሌላ የምርምር ማዕከል “የሕዝብ አስተያየት እንደሚያሳየው 60% የሚሆኑት የአሜሪካ ምላሽ ሰጪዎች ዲሞክራሲያቸው በሚሠራበት መንገድ “አልረኩም”። ይላል። ስለሆነም ከ4ቱ 1 አንዱ የተጠቀሰው አማራጭ ያልሆነውን ያልተለመደው አማራጭ መንገድ እንዲከሰት የሚፈልጉ ሰዎች አሜሪካ ውስጥ ተከስተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አሜሪካ ውስጥ ከተደረገው ጥናት በይበልጥ መፈንቅለ መንግሥት ቢከሰት የሚሰጉ ዜጎች እንዳልሆኑ እገምታለሁ።አገሪቱ በቀውስ እየታመሰች ባለችበት የጦርነት ወቅት መፈንቅለ መንግሥት ወታደሩን ይከፋፍላል የሚሉ ስጋቾች አሉ። ሊኖር ይችል ይሆናል። ስጋቱን ለማመን ግን የተደረገ አርግጣኛ ዳታ ግን የለም። የማከብረው ወዳጄ የምጣኔ ሃብት እና የታሪክ ተመራማሪ ሊቁ ወጣት አቻምየለህ ታምሩ በጽሁፉ ላይ ያልተብራራ ለስጋቱ ምንጭ ይኖሮው ይሆናል። ይህ ለወደፊቱ የሚታይ ይሆናል።
መፈንቅለ መንግሥቱን የሚፈልጉ ”ጁንታዎች” ብቻ እንደሆኑ ያቀረበው መስመር ብስማማም (ጁንታ እንኳን መፈንቅለ መንግሥት አገሪቴ ብትፈፈርስም ደንታ ስለሌላቸው ምንም ቢሉ ቢሉ የሚጠበቅ ነው) የስዒረ መንግሥት ንቅናቄ ፍላጎት ግን “ጁንታው ቡድን”
ብቻ የተወሰ ፍላጎት አይደለም:፡ ጁንታ ካልሆኑት አንዱ እኔው ሁለት አማራጮችን ለማየት እሻለሁ።
የፋሺሰቱ ስርዓት ለማስወገድ “መፈንቅለ መንግስትና ሕዝባዊ አልገዛም ባይነት” ከሁለቱ ሌላ አማራጭ የለም። “በወያኔ ትግራዋይነት” ቅኝት እና “በኦሆዴድ ኦነግ ኦሮሙማ” ቅኝት ሹማሙንት አጋፋሪነት ‘ምርጫ’ ተብሎ ለ30 አመት የተደሰኮረለት “ምርጫ” የት እንዳደረስን ስላየነው በፋሺሰቶች አስተባባሪነት የሚደረግ ምርጫ “ቦምብን ለህጻናት ማስታቀፍ” ስለሆነ አማራጭ ሆኖ አልተገኘም።
በምርጫ አሸነፈ የተባለለት የ2014 ዓ.ም የነገሰው አዲሱ ንጉሳችን “ንጉሥ አብይ አሕምድ”
አንግሳኛለች ለሚላት “ኢትዮጵያ” የሰጣት አበርክቶ “የአዲስ አባባ ሕዝብ ከሸርሙጦች የተደቀሉ የሸርሙጦች ልጆች ናቸው” የሚሉ የቀወሱ ዕብዶች እና ኢትዮጵያ ትፍረስ የሚሉ፤ ለሦስት ሺሕ አመት እንገዛችሗለን የሚሉ አማካሪዎቹ እና አማራን በመጨፍጨፍ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በጭፍጨፋ እየተካፈሉ ያሉ የጨፍጫፊ ድርጅት መሪዎች ፓርላማ ውስጥም ይሁን ከፍተኛ የመንግሥት ሹመት ተሹመው “ኢትዮጵያ ምን ታመጪ!” ብሏታል።
በዛ ሳያቆም ወያኔ የከፈተው ጦርነት ፤ ተዋጊው ጦር እንዲያፈገፍግ ተደርጎ መጨረሻ ላይ ከትግሬ የተነሳው የሽብር ሃይሉ ‘ጎንደርን ወሎን እና ዓፋርን’ ደፍሮ በመግባት ከተሞችን እና ገጠሮችን በመቆጣጠር ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ዝርፍያ፤ ውድመት እና ግድያ እንዲፈጸም ያደረገ መንግሥት በምርጫ ስም ምንሊክ ቤተመንግሥት ገብቷል።
ያም ሆነ ይህ ወያኔ ለ27 አመት ኦሮሙማ ለ3 አመት፤ በመፈንቅለ መንግሥት መጥተዋል። ስለዚህ በመፍንቅለ መንግሥት የመጡት እነዚህ ሁለቱ ፋሺሰት ቡድኖች፤ እንደ ዕድል ለፈጣሪ አይሳነውም እና (እንደ ሚባለው) አገር ወዳድ የሆኑ ከጦር ሃይሉ ውስጥ በትኣምር ቢገኙና ቢፈነግሉት “በምን ዕድላችን ባገኘነው” ያሰኛል።
እኔም ሆንኩኝ ወንድሜ አቻምየለህ አሁን ያለው ስርዓት ፋሺሰት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በኦሮሙማ ቅኝት በመቀየስ ኢትዮጵያ ባመዳከም ወደ ኦሮሞነት ለመቀየር የሚታይ መስመር ዘርግቶ “ጠላት” ብሎ ያሰመረበትን “አማራ” ከኢትዮጵያ ምድር ለማስወገድ የራሱ ወወታደሮች እና ድርጅት በጨፍጨፋው እንዲሳተፉ እንዳደረገ ከጸረ አማራ ድርጅች መሪው አንዱ “ጀ/ል ከማል ገልቱ” በዩቱብ ቀርቦ መስጢሩን ይፋ አድርል። አቻም ይህንን ያውቃል።
ይህ ብቻ ሳይሆን “የጭፍጨፋው መሪ” ሻሸመኔ ውስጥ ትምህርት ቤቶች/፤ ሆቴሎች፤ሕክምና መስጫ ህንጻዎች ቤተክርስተያናት እና ምዕመናን ፈርሰው ፤እሳት ጋይተው እና ታርደው የአማራና የክርስትያን ንብረት ሲዘረፍ “የከተማው ከንቲባ ሺመልስን ዕርዳታ እንዲልክለት ሲጠይቀው” የሰጠው ምላሽ ፡ “አርፈህ ተኛ” ብሎኛል ሲሉ “ከንቲባው” ተናግረዋል። እንዲህ ያለ ግልጽ ጭፍጨፋና ጸረ አነድነት አንዲካሄድ ያደረገው ማን ነው? የኦሮሞን “ክልል” ለማስተዳዳር በንጉሡ የተሾመው ሰው “ጭፍጨፋ እንዲካሄድ ሲፈቅድ” ይባስ ብሎ አገር እመራለሁ የሚለው አብይ አሕመድ ሻሸመኔ እንደነደደች በአገር የየዜና ማሰራጫዎች እና
ለም አቀፋዊ የዜና ማዕከሎች ሲዘግበው እያያና እየሰማ
“ኢትዮጵያ ምን ታመጪ!” ብሎ
“አንጦጦ ተራራ ሄዶ ‘የህጻናት ብስክሌት እየነዳ’ ፎቶ ሲነሳና ደስታውን ሲገልጽ ነበር”። ሺመልስ አዱኛ ከ አንድ ወር ተኩል “ጀሮ-ዳባ” ቆይታ ወደ ሻሸመኔ ሄዶ ሲለፍልፍ ነበር የሚል ዜና ሰማን።
እንዲህ ያለውን ጸረ ኢትዮጵያ መሪ ያወም “በፋሺሰትነት” የተመደበ ሥርዓት በሕዝብ አመጽም ይሁን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ቢወገድ ኢትዮጵያ የምትጎዳው ምንድ ነው?
የሚቀራትስ ምንድ ነው? አብይ አሕመድ ድሮ የኦነግ ከዚያም የወያኔ ኩሊ የነበረ ዛሬ ደግሞ የኦነግ መሪዎች ኩሊ ነው። ኩሊ ራሱን ያልቻለ ተላላኪ ማለት ነው።
ፋሺሰት ሙሶሎኒ የኩሊዎች ስብስብ ነበር። ኦሮሙማ ያቀፈው ተሿሚም ብዙዎቹ በግድያ በጭፍጨፋ፤ በሌብነት፤ በዘረኝነት፤በአጭበርባ ባሕሪ የተዘፈቁ ኩሊዎች ናቸው። ስለዚህ ይህ የኩሊ ስብስብ በመፈንቅለ መንግሥት ቢወገድ ሕዝቡ ምንም አይጎዳም። ይልቁኑ መፈንቅለ መንግሥቱ አራማጆች ከተለያዩ ነገዶች የተወጣጡ ሆነው “ጦሩ” ለአገሪቱ ተገዥ እንዲሆን ማስተባበር የሚችሉ “አገር ወዳድ ወታደራዊ ቡድኖች” መፈንቅለ መንግሥት ቢያካሂዱ ተመራጭ ነው።
የሚያስፈልገው፤ ማለትም መሪን ማስወገድ የሚችሉት መፈንቅለ መንግሥት የሚመራው (ወይወንም የሚያካሂደው ቡድን) የጋርዮሽ ፍላጎትና ትብብር ሲኖር ነው ይላሉ በዚህ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት።-
ማንኛውንም መፈንቅለ መንግሥት ስኬታማ ለማድረግ ይቻላል፤ ይላል “የመፈንቅለ መንግሥት ተማራማሪ የሆነው የአሜሪካ ባህር ኃይል ጦር ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር “The Strategic Logic of Military
Coups” የሚል መጽሐፍ ደራሲ ሕንዳዊው “ናውኒሃል ሲንግ” Naunihal Singh ይህንን ስልት “የማስተባበር ጨዋታው” (coordination
game) ማወቅ ብቻ ነው፡ ይላል።
አብይ አሕመድ የመፈንቅለ መንግሥት ውልድ መሆኑን እናውቃለን። ወያኔ 17 አመት የፈጀበት በብረት መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ ነገሠ። ከወላጁ ወያኔ ወደ ልጁ አብይ የተሸጋገረ ውርስ ነው። እርግጥ ነው ለመፈንገል ሲሞከር ሰበብ አይታጣውም።
መሪዎች ሥልጣናቸው ሲነካ “መፈንቅለ መንግሥት” በማካሄድ እነሱን መልሶ የሚያስቀምጥ አመጸኛ ቡድን ያዘጋጃሉ። አብይ እራሱ በዚህ ተዘጋጅቶ እንደነበር እናውቃለን (ዛሬም ተዘጋጅቶ ይሆናል)።
ታስታውሱ እንደሆነ ጥቂት ኮማንዶዎች ቤተመንግሥት ድረስ መጥተው “መፈንቅለ መንግሥት” ላማካሄድ ሞክረውብኝ ነበር ባለው አንደበቱ “ከሥልጣኔ ብወገድ መፈንቅለ መንግሥቱን ያካሄዱትን ወታደሮች የሚገዳደር “ከቡራዩ ከ,,.. ከ… ወዘተ..” በፈረስ እየጋለበ መጥቶ የሚፋለም ወጣት (ኦሮሞ ማለቱ ነው) አለኝ ሲል መፍንቅለ ምንግሥቱን በሌላ መፈንቅለ መንግሥት ላመስቆም ዝግጁ እንደነበር እራሱ ነግሮናል። አሜሪካው ትራምፕም እንዲሁ ነበር ያደረገው።
ይህንን አስመልክቶ አንድ ጋዜጠኛ ለፕሮፌሰር “ናውኒሃል ሲንግ” እንዲህ ጠይቆት ነበር፡
በዋሽንግተን ውስጥ የሆነው ነገር አሳሳቢ ነው፡ ግን መፈንቅለ መንግሥት አይደለም። ያንን ልዩነት ማስረዳት ይችላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር “ናውኒሃል ሲንግ” መልስ፣-
ችግሩ ፕሬዚዳንቱ የሞራል ስልጣን ስለሰጣቸው ነው ፣ እዚህ እያየን ያለነው አመፅ ፣ በመንግሥት ላይ ኃይለኛ አመፅ ተብሎ በተሻለ ይገለጻል። አመፅ ነው ግን መፈንቅለ መንግስት አይደለም።” ይላል።
አብይ አሕመድም በተመሳሳይ “የዘር ጨፍጫፊ ነብሰ ገዳጥ ሽብርተኞች” ከተማ ሲያቃጥሉ አማራውን በገፍ በተከታታይ ሲጨፈጭፉ…ጉራጌና የጋሞ እናቶች ክርስትያን አባቶችን ሲያርዱ.. “አልሰማሁም አላያሁም.. ስለችግር አታውሩ ስለ ስንዴ መዝራት አውሩ” እያለ ሽብርተኞችን ስለሚያበረታታ አገሪቱ ወደ ከፋ ጭለማ ገፍትሯታል። ለ30 አመት የደደቡ ወጣት ምሁራንም ንጉሡን አጅበው ካቢኔው ላይ ተቀላቅለውለታል። እንዲሁ “የሆነ ሆኗል እንቀጥል” ይላሉ። ይህንን አስመልክቶ ከላይ የተጠቀሰው ህንዳዊ አሜሪካ ፖለቲከኞች እንዲህ የሚሉትን ይኮንናቸዋል “ፖለቲከኞች ከ 300 ዓመታት በፊት ስለ ተከሰተው ችግር የሚያወሩ እንጂ አሁን እየሆነው ስላለው ችግር ግድ ሳይላቸው “እርሱን ተውት ይልቁንም ወደፊት መጓዝ አለብን” እያሉ ሲናገሩ ታደምጣለህ። ያ ሁሉ የሚያስጨንቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ይላል።
ስለሆነም አብይ አሕመድ ስለተደረገው አታለቃቅሱ እያለ ሲያሾፍ፤ መፈንቅለ መንግሥት ቢደረግበት ወይንም ሕዝባዊ አመጽ ተደርጎ “አትገዛንም ከሥልጣን ውረድ” ካልተባለ በምን ስልት ሊወገድ ይችላል?
አፍሪካ ውስጥ ዛሬም “ጊኒ እና ማሊ…” የሚደረጉ ወታደራዊ ኩዴታዎች ሕዝቡ ሲደግፍ እንጂ ሲቃወም አላየንም።፡ምክንያቱም ሕዝቡ መርሮታል፤ አማራጭ የለውም!! ምሁሩ ተፈትኖ ወድቋል። በቃ!!!
አስረዱኝ? እኔ እየተከራከርኩ ያለሁት መስመር ‘እምባ በሚያነቡ፤ ተከብበናል ድረሱልን ብለው ደራሽ አጥተው ስለ ታረዱ የመንግሥት ያለህ ብለው ጮኾው አማራጭ ስላጡ ዜጎች ምርጫ ነው እያወራሁ ያለሁት። ጥይት ተርከፍክፎባቸው ቢላዋ አንገታቸው ያረፈባቸው የሞቱንም መናገር ባይችሉም ፤ እስኪ ጫካ ውስጥ ተከብበው ድረሱል እያሉ ያሉ በህይወት ያሉትን ሴቶች እና ወጣት ወንዶች፤ እናቶች እና ህጻናት ጠይቁዋቸው ምን አንደሚሉ! አብይ በመፈንቅለ መንግሥት ከሚወገድ እኛ እንታረድ ብለው አይሉም። የኔን ሃሳብ አይጠሉትም። “የመንግሥት ያለህ!! አብይ የት አለህ?!!! ብለው ለሚጮኹት ጠይቃችሁ እኔ ስለማቀርበው መፍትሄ ምን አንደሚሉዋችሁ ጠይቋቸውና መልሱን ፈልጋችሁ ንገሩኝ!!
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ
(ኢትዮ ሰማይ)
No comments:
Post a Comment