ሞት በታወጀባቸው አማሮች ይሁንባችሁ - ፋኖዎች
ይህን መልእክቴን ስሙኝ!
ይነጋል በላቸው
Ethiopian
Semay
6/12/25
ዛሬ ስለፋኖ የሰማሁትን ባልሰማ ደስ ባለኝ፡፡ በመሠረቱ የሰማሁት ቀድሞም የማውቀውን ግን ችግሩ በጊዜ ሂደት ሊቀረፍ ይችል ይሆናል በሚል ተስፋ ሰምቼ እንዳልሰማሁ አልፈው የነበረውን ነው፡፡ አዲስ ነገር የለም፡፡ አሁን ግን በዛ፡፡ እጅ እጅ አለ፡፡ ትግስታችንንም ተፈታተነ፡፡
ዛሬ ከተለያዩ ሰዎች ጋር አመሸሁ፡፡ ተመሳሳይ መረጃ ቃረምኩ፡፡ ማሳደር አልፈለግሁም፡፡ ቤቴ እንደገባሁ መጻፍ ጀመርኩ፡፡ ምን ላድርግ? ዛሬ እንጂ ነገ የኔ ላይሆን ይችላል፡፡ አድሮ መገኘት ብርቅ እየሆነ በመጣበት አሳሳቢ ዘመን ነገ ለዛሬ ሩቅ ናት፡፡
አማራው በአንዳንድ የፋኖ አመራሮች በሚደርስበት በደልና ጭቆና ክፉኛ እየተበሳጨ ነው፡፡ በብዙ የገጠር ሥፍራዎችም አማራው ብልጽግናን እስከመደገፍ እየደረሰ እንደሆነ መስማት ጀምረናል፤ ይህ ክስተት አደገኛ ነው፡፡ “የሞኝ ሙርጥ ካላንድ ቀን አይበልጥ” ይባላል፤ ከሁለት ዓመት በላይ አንዳቸው ከአንዳቸው እምብዝም በማይሻሉ አማራጮች መካከል ሆኖ መደቆስና ከሁሉም ዓይነት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች መገለል የሚፈጥረው ብሶት ከባድ ነው፤ አያድርስ እንጂ አንዳንዴ መምረጥ የሌለብንን መጥፎ አማራጭ ሳይቀር ሳንወድ በግዳችን እንድንመርጥ የምንገደድበት ሁኔታ ውስጥ ራሣችንን ልናገኝ እንችላለን፡፡
መከላከያ በጭካኔው አንዴውኑ ይታወቃል፡፡ በፋኖ ውስጥና በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱ ወሮበሎችና አጋሰሶች ደግሞ ሕዝቡን እያራቆቱትና እየገደሉትም ነው፡፡ አማራው እየደረሰበት የሚገኘው ባለሁለት ስለት መከራና ስቃይ ተነግሮ አያልቅም፡፡
ፋኖ ትግል እንደጀመረ ታጋዮቹ ከፍተኛ የውጊያ ሞራል ነበራቸው፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥም የአቢይን ዘረኛ ኦሮሙማ ጥለው ኢትዮጵያን ከወደቀችበት አዘቅት ለማንሣት ከፍተኛ ጉጉትና ወኔውም ነበራቸው፡፡ የዛሬውን አያድርገውና ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ትግሉ ሜዳ የጎረፉት ታጋዮች ፍላጎት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነበር፡፡ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩም በዚያች በፈረደባት የትግርኛ ተረት “ለምጣዲ ሲባል ዐይጧ ትለፍ” ብለው ታጋዮች እየተቻቻሉ ብዙ ጊዜ አለፈ፡፡ እየቆዬ ግን ነገር መበላሻሸት ጀመረና በዚህ አስጠሊታ ሂደት ብዙ ጀግኖችንና ብዙ ሀብት ንብረት በሤራና በተንኮል አጣን፡፡ ራስ ወዳድነት የነፃነት ትግሉን አጠየመው፡፡
የብልጽግና
ተላላኪው ብአዴን ፋኖን ሠርጎ ገባበት፡፡ አቢይ ገንዘቡን እየረጨ ፋኖን ከአናት እስከ ታች መከፋፈሉን ቀጠለ፡፡ ዐረመኔው አቢይ
አህመድ ሰይጣናዊ ተልእኮውን ለመወጣት በዓለም አቀፍ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይላት ሁሉን አቀፍ እገዛ ተንተርሶ ፋኖ ላይ መላ ትኩረቱን
አደረገ፡፡ አቢይ ከሰይጣንም በላይ የረቀቀ
የጥፋት አምባሳደር ነው፡፡ የአቢይ ተፈጥሯዊ ዋና ችሎታ ደግሞ ሰዎችን በገንዘብ መደለልና መከፋፈል ነው፡፡ የሰው ደም
ካልጠጣ እንቅልፍ የማይወስደው አቢይ ትግሬና አማራ ላይ ዘመተ፡፡ ከዚያም…
ቆዩኝማ፡፡ ከዚያም … የሚለውን ከመቀጠሌ በፊት ስለአንድ ምግብ አሠራር ልናገር፡፡
ማዮኔዝ የሚባል ምግብ አለ፡፡ ከዕንቁላል፣ ከዘይት፣ ከአቼቶ ወይም ሎሚና መሰል የምግብ ግብኣቶች የሚዘጋጅ ለተለያዩ የምግብ ዝግጅቶች ለምሣሌ ለሣንዱዊች መሥሪያነት የሚውል ነው፡፡ ማዮኔዝ ሲሠራ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል - ከፍተኛ፡፡ በየደረጃው የሚጨመሩ ግብኣቶችን እየጨመሩ በዊስከር (መምቻ ሽቦ) ያለማቋረጥ በፍጥነት መምታት ያስፈልጋል፡፡ እየተመታ እያለ አንድ ነገር ከጎደለበት ወይም ዙሩን ጠብቀው ካልመቱት እየለደለደና እየፋፋ የመጣው ማዮኔዝ ባልታሰበ ቅጽበት ወደቀጭን ፈሣሽነት ተቀይሮ ሊሟሽሽና ድካማችን ሁሉ መና ሆኖ ሊቀር ይችላል፡፡ ያኔ ያ ሁሉ ዕንቁላልና ሌላ ሌላው ግብኣት ሁሉ ጥቅም የለውምና ይደፋል፡፡ ፋኖም እንደማዮኔዙ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ “ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ…” እንዳይሆን፡፡
ከዚያም አቢይ አማራንና መላዋን ኢትዮጵያ በጭቃ ጅራፉ መግረፉን ተያያዘው፡፡ በጦርነት፣ በቤት ፈረሳ፣ በኑሮ ውድነት፣ በየቀኑ በሚታወጅ አጓጉል መመርያና ደምብ፣ … ሕዝብን እንደጊንጥ ይነድፍ፣ እንደጅብም ይሰለቅጥ ያዘ፡፡ በዚያም ምክንያት የቻለ ጫካ ገባ፤ ያልቻልን እዚሁ በቁማችን ሲዖልን መለማመድ ያዝን፡፡
ወንድሞቼ፣ በእንግሊዝኛው የቃል አጠቃቀም “momentum” የሚባል ነገር አለ - አንድን ነገር ለማከናወን ምቹ ጊዜ ወይም አጋጣሚ፡፡ “momentum”ን አለመጠበቅ ወይም በአግባቡ አለመጠቀም ለማያንሰራራ ጉዳት ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ የአእምሮ መጫጫትን ተከትሎ የሚከሰትን ውስልትናን ካልተከላከሉ ደግሞ ለዚህ ዓይነቱ አደጋ መዳረጉ የሚጠበቅ ነው፡፡
የእስካሁኑን ችግራችንን አጢኖ ከአሁን በኋላ ላለው አምላክ ይቅር ካላለን የፋኖ ነገርም ወደዚያ እያመራ ነው፡፡ የሚሰማው ሁሉ አስደንጋጭ ነው፡፡ ስንትና ስንት በአመራር ደረጃ የነበሩ ፋኖዎች በአዲስ አበባ በኩል ወደ ዐረብ ሀገር እየተሰደዱ ነው፡፡ ለምን ይዋሻል? አንዱ ተስፋ ቆርጦ ወይም በበላይ አመራር ተናዶ ከትግሉ ወጣ ማለት ግን ትግሉ ተስተጓጎለ ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡ ወላድ በድባብ ትሂድ እንጂ አማራ የሰው ዕጥረት የለበትም፤ ችግሩ ጥራት ያለው ሰው የማግኘቱ ጉዳይ ነው - በሆዱ የማያስብ ሰው ያለማግኘት ጣጣ አሁን ላይ እያስጨነቀን ይገኛል፤ ዘመናችን ሆድ የነገሠበት ሆነና ተቸገርን፤ኅሊና ጠፋ፡፡
በወራት ሊያልቅ ይችል የነበረው የፋኖ ትግል አሁን ጉድባ ውስጥ ገብቶ መከራችንን እያበላ ያለው የይሉኝታ ገመድ አስሮን በጊዜው እውነቱን ባለመናገራችንና ችግሩን የሚፈታ ኃይል በማጣታችን ነው - ፋኖ በበርካታ ዞኖች ብዙ መሬት መያዙን አጥቼው አይደለም፤ ግን አንድ ቢሆንና የሚታማበትን ሁሉ በቶሎ ቢያስተካክል ኖሮ አሁን በዚህ መልክ አይገኝም ነበር፡፡ መድኃኒት ሳይገኝለት ተሸፋፍኖ የሚቀመጥ ቁስል ወደካንሠርነት ይለወጥና ለአካል ጉድለት ወይም ለኅልፈት ያጋልጣል፡፡ ወደዚያ ደረጃ ሳንደርስ የፋኖን ነገር መፍትሔ መስጠት ይገባል እያልኩ ነው - ያለፈው አልፏል፡፡ ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራም፡፡
ፋኖ ከፈለገ እርስ በርስ መጎሻመጡን ትቶና በጎጥና በሸጥ መለያየቱን ዕርም ብሎ በአንድነት ቢነሣ ድሉ የሱ ነው - ጥርጥር የለውም፡፡ እንዳሁኑ ከቀጠለ ግን እዚህ ላይ አቢይ ቀደም ሲል የተናገረው እውነቱን ነው - ሺህ ዓመትም አይሳካለትም፡፡ መጽሐፉ “እርስ በርሷ የተከፋፈለች መንግሥት አትጸናም” የሚለው ለዚህ ትልቅ ዋቢ ነው፡፡ ሰው ነኝ የሚል ፍጡር እንደሰው ማሰብ አለበት፡፡ሰው ከሰውነት ተራ ከወጣ አቢይ አህመድን ሆነ ማለት ነው - ጎራው ቢለያይም፡፡
እናም አሁን ላይ በተለይ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራምና እውነቱን እንናገራለን፤ ፋኖ በመንደርና በቀበሌ ተከፋፍሎ የትም አይደርስምና በአፋጣኝ መላ ይፈልግ፡፡ የአንድ የሰባተኛ ክፍል ምሩቅ ዕብድ ሰውዬ መጫወቻ ሆኖ በተለይ የአማራን ሕዝብ መሣቂያና መሣለቂያ አያድርገው፡፡ ይህ ሲባል ግን የኢትዮጵያ ነፃነት ይቀራል ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከፋኖም ከብልጽግናም ከሕወሓትና ከኦነግም በፊት ነበረችና በዚህ ሃሳብ አይግባን፡፡ ይህን በሚገባ አውቃለሁ፤ የነፃነቷን በቅርብ መበሰርም ከማንም ባላነሰ እረዳለሁ፡፡ ሳይታለም በተፈታ ነገር መከራከር አያስፈልግም፡፡ ይህን የምለው ደግሞ ለመጽናናትም ሆነ ለማጽናናት ብዬ አይደለም፤ ዕድሜ ለሰጠው በቅርቡ የሚታይ ስለሆነ እንጂ፡፡
አቢይ ሰሞኑን ለአንዲት ጋዜጠኛ ከሰጠው ውሽከታው መረዳት የቻልኩት ራሱ ቅስሙ በከፍተኛ ደረጃ መሰበሩን ነው - አለሁ ለማለት ያህል ነው ክልጂቷ ጋር 2200 ሰው በቀጥታ ሥርጭት እንደተከታተለው የተነገረለትን እንጨት እንጨት የሚልና የጠነዛ ቃለ ምልልስ የሰጠው፡፡ በቁሙ ሞቷል፡፡
ከቀደመ ታሪክ አኳያ ፋኖነት ትግል በማኮላሸት አይታወቅም፡፡አሁን ከምናያቸው ፋኖዎች ጥቂት የማይባሉት ግን ለማይጠረቃ ሆዳቸውና ለሥጋዊ ፍላጎታቸው ሲሉ ብዙ ደባ እየፈጸሙ እንደሆነ በግልጽ እየተረዳን ነው፡፡ ሁሉም ሊሆኑ አለመቻላቸው የአጋጣሚ ጉዳይ እየሆነ ይመስላል፡፡ እንጂ ብዙ አመራሮች በሚዘርፉት ገንዘብ በየከተሞች ፎቅ እየሠሩ እንደሆነ በስፋት ይነገራል፡፡ ጦርነቱን እንዲያፋፍሙና ወደ ድል ማማ እንዲጓዙ የፋኖ አርበኞች ሲጠይቁ አዛዦቹ እንደሚያስቆሟቸውና አርፈው እንዲቀመጡ እንደሚያደርጓቸው እንሰማለን፡፡ ብዙ አመራሮች ፋኖን ወይም ፋኖነትን የቢዝነስ ማዕከላቸው አድርገውታል፡፡ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡
ሕዝብ እያለቀ፣ አገር እየወደመ፣ ዜጎች በያሉበት ሞት ተፈርዶባቸው በየቀኑ እየተረሸኑ፣ የእርሻ ሥራና አዝመራ መሰብሰብ እየተስተጓጎለ፣ ትምህርትና ህክምና ቆሞ ምድረ በዳነት እየተስፋፋ በዚህ መሃል በራስ ጥቅም መታወር ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት ነው፡፡አንድ ሰው የሚያደርገው መልካምም ሆነ መጥፎ ድርጊት ደግሞ ምንም እንኳን ጊዜ ቢፈጅም መሰማቱና በአደባባይ መታወቁ አይቀርም፡፡
እናም
ብዙ የፋኖ መሪዎች ጭንቅላታቸውን ሆዳቸው ውስጥ ወትፈው የሀብት ክምችት ላይ እንደተሰማሩ ይነገራልና ከዚህ ዕኩይ ምግባራቸው ቢታቀቡ
የመጀመሪያ ተጠቃሚዎቹ ራሣቸው ናቸው - ይህ እንግዲህ በፋኖ ስም ሰው እያገቱና በቡድን ሆነው እየዘረፉ ሀብት የሚያከማቹትን የለየላቸው
ሽፍታና ወንበዴዎችን ሳይጨምር ነው፡፡
የጦርነቱ መራዘም እንደሚጠቅማቸው የተረዱ ፋኖዎችና ለጠላት በገንዘብ የተገዙ ባንዳዎች የነፃነት ትግሉን እያዘገዩት መሆናቸው በስፋት ይነገራል፡፡በዚያም ምክንያት የምንጠብቀው ትንሣኤያችን እንደግመል ሽንት ወደኋላ እየተጎተተ በውጤቱ ሆዳሙ ብአዴንና ትብታባሙ አቢይ አህመድ ለጊዜውም ቢሆን እየቀናቸው መሆኑ በግልጥ ይታያል፡፡ ይህም ሁሉ በብልኆች እየተመዘገበ ነው፡፡ ምድረ ከርሳም በቅርቡ ዋጋውን እንደሚያገኝም ይህ ጸሐፊ በሚገባ ይገነዘባል፡፡
ፋኖነትን ከታሪክ እናውቃለን፡፡ ለመስዋዕትነትና ለድል እንጂ ለሀብት ክምችትና ለዘረፋ ወይም ለሥልጣን ሽሚያ የተዘጋጀ ፋኖ በታሪክ አይታወቅም፡፡ ለታሪክ ግንባታ እንጂ ሀገርን ለማፍረስና ለባንዳነት የተሠለፈ ፋኖ አሁን በምናየው መጠንና ድፍረት በታሪክ አልታዬም፡፡ አሁን ግን አእምሮ ጠፋና በኦሮሙማ ሞትና ዕልቂት የታዘዘበትን አማራ ባወጣ ሸጦ የግል ሀብት ለማግበስበስና በዘምቦ ተባርቆ ለሚገኝ ሥልጣን ለመዘባነን የሚፈልግ ፋኖ ተፈጠረ - ይህ ዓይነቱ መሠሪ የሕጻን አንሻን ዕድል ያግኝ፤ የኢሳይያስ በላይ ዕጣ ፋንታ ይድረሰው፡፡ የፕሮፌሰር አሥራት አሣዛኝ ዕድልም አይለፈው፡፡ በየትኛውም ጎራ ያሉ የደም ነጋዴዎች ሁሉ ጥቁር ውሻ ይውለዱ፡፡ ትግሉ በሆዳሞችና በቅጥረኞች ባይሰነካከል ኖሮ በአራት ጠቅላይ ግዛትና በመላዋ ኢትዮጵያ የሚገኝ አማራና የአማራ ፋኖ ደጋፊ በኅብረትና በቅንጅት ቢሠራ የኢትዮጵያ ችግር በጥቂት ወራት ውስጥ ዕልባት ባገኘ ነበር - ሕወሓት የተጋሩን አእምሮ በመርዘኛ ፕሮፓጋንዳው ባያኮላሽ ደግሞ የኢትዮጵያ የአሁኑ ችግር በአንድና ሁለት ሣምንታት ውስጥ መፍትሔ ባገኘ፡፡ ግን ምን ይደረጋል “እባብ የልቡን አይቶ እግሩን ነሣው” እንደተባለው የየዋሃንን ቀልብ ለመሳብ በሚመስል ሁኔታ ለቁጥር በሚያታክት የኮር፣ የዕዝ፣ የክፍለ ጦር፣ የብርጌድ፣ የሻለቃና መሰል ወታደራዊ የዕዝ ሰንሰለት እየተጠራ ያለው ፋኖ ይህን የበሰበሰና የገማ የአቢይ ኦሮሙማ በቀላሉና በአጭር ጊዜ ሊደመስስና መናገሻ ከተማዋን ሊቆጣጠር ሲችል ወገቡን እንደተመታ እባብ እዛው ጫካ ውስጥ እየተጥመለመለ ይገኛል፡፡
ዐይን የገባው ይመስላል፡፡ ዐይን ውስጥ መግባት መጥፎ ነው - “የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ…” የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ አቢይ ሥልጣን ላይ ያለው በአማራ አለመተባበር ነው፡፡ አቢይ ወንበሩን የሚያስጠብቀው ኦርቶዶክስንና አማራን እንዲያጠፋላቸው ከላኩት ዓለም አቀፍ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይላት ሁለንተናዊ ድጋፍ በተጓዳኝ ጭካኔን ማዕከሉ ባደረገ ሸሩና ሤራው ነው፡፡ ለወርም ይሁን ለዓመት ከአሁን በኋላ አቢይ ሥልጣን ላይ የሚቆዬው ሰሜነኞች ከኅብረት ይልቅ ልዩነትን የሙጥኝ ብለው እስከቆዩ ድረስ ብቻ ነው፡፡
ወደዋናው ነጥብ ስንገባ ወሬ የሚያምረው የቡና ተርቲብ ላይ ነውና ከወሬ ይልቅ ተግባር ላይ እናተኩር፡፡ በወሬ ጠላት አይጠፋም፡፡ በሰበር ዜና ብዛትም ተጨባጭ ድል አይገኝም፡፡ እውነቱን ተናግሮ እመሸበት ማደር ይባላልና እውነቱን መነጋገር ደግ ነው፡፡ እኔ ይህን አልኩ፡፡ ይህን ደግሞ እንወቅ - በፋኖም ውስጥ ይሁን በብልጽግናና በብአዴን ውስጥ ያለ ተምችና ነቀዝ ሁሉ ዋጋውን ሊከፈል የቀረን ጊዜ እጅግ በጣም አጭር ነው፡፡ የጨለማው ግዝፈት የሚጠቁመን የብርሃንን መቃረብ ነው፡፡ እናም ወደኅሊናችን በፍጥነት እንመለስ፡፡
ለማጠቃለል ያህል ሁሉም ሌባና አጭበርባሪ የትም ይሁን የት መታወቁን ይወቅ፡፡ ከሕዝብ ዐይንና ጆሮ ተደብቆ የሚቀር አንዳችም ነገር የለም፡፡ ለሆዱ የተገዛና ነፃነትን የሚያዘገይ የመጨረሻ ዋጋውን እንደሚያገኝ ይገንዘብ፤ እሱ ባያገኝ ዕዳውን ለዘር ማንዘሩ አስተላልፎ ሁለት ሞቶችን ይሞታል፡፡
ስምና ዝና ብቻውን አያዋጣም፡፡ “አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ደርግ ከመሣፍንቱ፣ ወያኔ ከደርግ፣ ኦሮሙማ ከወያኔ፣ ፋኖ ከወያኔና ከኦሮሙማ ካልተማሩ ሁለ ነገራችን ውኃ ቢወቅጡ እምቦጭ ነው፡፡ በዚያ ላይ በሕዝብ ተሣትፎ የማይመጣ መንግሥት ሕዝብ ላይ መሞላፈጡ የነበረና ያለ ነውና በሀገራችን ትንሣኤ የሕዝብ ድርሻ ከፍ ሊል ይገባል፡፡
ከልምድ እንደምንገነዘበው በአንድ ወገን ብቻ የሚገኝ ነፃነት በአብዛኛው የዚያን ወገን ፍላጎት ብቻ የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ሁሉም የየድርሻውን አስተዋፅዖ ያበርክት - በተኩስም፣ በገንዘብም፣ በሃሳብም፣ በመረጃም፣ በሞራልና በሌላ ሌላ የተቻለ ነገር ሁሉ፡፡ ከእሳት ወደ እሳት እየተላለፍን መኖር የለብንም፡፡
ግን ግን የአንድን ወፈፌ ሰው ወንበር ለማስጠበቅ የሚከሰከሰውን የሀገር ሀብትና ገንዘብ አስባችሁት ታውቃላችሁ? “ደመወዜ ያንሰኛል” እያለ የሚቀልድብን አቢይ የሚያሠራቸውን በትሪሊዮኖች የሚገመቱ የቤተ መንግሥትና የሪዞርት/መናፈሻ ፕሮጀክቶችን ትተን ለወንበሩ ጥበቃና ለጦርነት የሚያወጣው ብቻውን ለኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን ያለብዙ ማጋነን ለአፍሪካ ሀኪሞችና መምህራን በቂ ደሞዝ ሊሆን የሚችል ነበር፡፡
የሀገሪቱ አጠቃላይ የፀጥታና የመከላከያ ሠራዊት ሁሉ ሪፓብሊካን ጋርድ በለው፣ ደኅንነት በለው፣ ፖሊስ በለው፣ ደምብ “አስከባሪ” በለው፣ … ሁሉም ቀን ከሌት የሚኳትነው የሰውዬውን ወንበር ለመጠበቅ ነው፡፡ ሰሞኑን ለምሣሌ 50 ሺህ ፖሊስ አዲስ አበባ ላይ ተራግፎ እኛኑ መውጫ መግቢያ እያሳጣን ነው፡፡ መከላከያም እንደዚሁ አዲስ አበባን አጨናንቋታል - ሁሉም የአእምሮ ህመሞች የተከማቹበትን የአንድ ዕብድ ወንበር ለመጠበቅ ነው ይሄ ሁሉ ግርግር፡፡
ይሄ
ሁሉ ወጪ ለሀገር ልማትና ለዜጎች ሥራ ፈጠራ ቢውል ኖሮ የት በደረስን! ጀምበር ወጥታ በገባች ቁጥር ነጋ ጠባ የሚደረግ ወንበር ጥበቃ አይሰለችም? ሠራዊቱስ ሰባት ዓመት
ሙሉ - ኧረ ከዚያም በላይ - ለአንድ ዕብድ ማጎብደድ አያንገሸግሸውም? ምን ዓይነት ሰው ሰጠን ግን!!
Ethiopian
Semay - Photo and phighlits are added by Ethiopian Semay

No comments:
Post a Comment