ዶ/ር ጸጋ መላኩ
ኢትዮጵያን ለምን ጠሉ?
ሰመረ አለሙ
Ethiopian Semay
2/12/2026
ከላይ ምስላቸው የሚታየው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ታላቁ ዶ/ር ኢንጀነር ቅጣው እጅጉና ኢትዮጵያዊ መሆናቸው በእጅጉ ያንገሸገሻቸው
ዶ/ር ጸጋ መላኩ ናቸው፡፡ በወ/ሮ ጸጋ በኩል የተለየ ማብራሪያ ቢሰጠውም
ሁለቱም ለተሻለ ህይወት ወደ ባህር ማዶ ያቀኑ የኢትዮጵያ ልጆች ነበሩ፡፡ ነብሱን ይማረውና ቅጣው እጅጉ በህይወት በነበረበት ዘመን
ከግል ኑሮው በላይ ስለ ሃገሩ ኢትዮጵያ የሚብሰከሰክ መልካም ዜጋ ነበር፡፡ በኑሮ ደረጃውም ልጅ ቅጣው እጅጉ ከወ/ሮ ጸጋ በላይ በአሜሪካ ቁሳዊ ጥቅሞች ተመቻችቶለት በታላቅ እንክብካቤ የሚኖር የተዋጣለት ሳይንቲስት ነበር፡፡ ይህ ወንድማችን በአንድ ወቅት የወያኔን መንግስት ለመጣል ሃይል አቀናጅቶ
ከፍተኛ ጥረት አድርጎም ነበር በዚህ የተከፋው ቴዎድሮስ ጸጋዬ የርእዮት
ሚዲያ ባለቤት አፍቃሪ ኢትዮጵያ በመሆኑ ጥርስ ነክሶበት ሲያብጠለጥለውም ነበር፡፡ ዶር ኢንጅነር ቅጣው እጅጉ ቢሮ በቀኙ የኢትዮጵያ
ባንዲራ በግራው ደግሞ የተቀማጠለ ኑሮ የሰጠችውን የአሜሪካን ባንዲራ በማቆም ለሃገሩ ያለውን ክብር አሳይቷል፡፡
ስለ ፎቶግራፉ በዚህ መልኩ ካብራራን በኋላ በቅርቡ አስተዋዩ፤ሞጋቹ ትንታጉ ጋዜጠኛ ተክለ ሃይማኖት አዳነ ወደ ሃገረ
እስራኤል አቅንቶ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷን ዶር ጸጋ መላኩን አነጋግሮ ነበር፡፡ ተ/ ሃይማኖት ጥያቄውን ሲሸክፈው 1/ ኢትዮጵያ ውስጥ
የቀሩ ቤተ እስራኤላውያን እርሶ ይህንን ወምበር ከያዙ በኋላ ጉዳያችን መንቀሳቀስ አቁሟል እያሉ ቅሬታቸውን ያሰማሉ 2/ የኢየሩሳሌም ይዞታችን የዴር ሱልጣን ገዳም ሊፈርስ መቃረቡንና በዚያ የሚኖሩት ገዳማውያንም መንገላታቸውን 3/ ኢትዮጵያ
በኖሩበት ዘመን የኢትዮጵያ ትዝታቸውንና 4/ በቱርክ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የዋሃቢ ሰው በእስራኤል ጉዳይ የሰጠውን ግንዛቤ እንዴት
ይመለከቱታል የሚል ይገኝበታል፡፡
ጋዜጠኛ ተክሌ የስልጣን ርቀቱን ጠብቆ ብዙ የሚያውቀውን ለራሱ ይዞ እሳቸው ብቻ የሚሰጡትን መልስ ሳይሞግት እንዳለ አስተላልፎልናል፡፡ አንዳንዴ ብቻ ወ/ሮዋ ገደብ ሲጥሱ እርምት ለማድረግ ቢሞክርም ሴትዮዋ መናገርና የራሳቸውን ሃሳብ ከማስተጋባት ውጭ የሌላውን ስለማያዳምጡ አንዳንዴም ከጥያቄው ጋር ያልተገናኘ መልስ በመስጠታቸው አድማጭ ይፍረድ በማለት ቃለ መጠይቁን እንዳለ አቅርቦታል።
https://www.youtube.com/watch?v=YgI
ወ/ሮ ጸጋ ኢትዮጵያ በሚኖሩበት ጊዜ የምድር ሲኦል ይኖሩ እንደነበር መገለል ይደርስባቸው እንደ ነበር በተጨማሪም ሸክላ ሰሪ ፤ ካይላ፤ ቡዳ ፤ፈላሻ ይባሉ እንደነበረና መሬት መግዛት እንደማይፈቀድላቸው ከፕሮፌሰር ሃይጋ የተጋቱትን ከፈረንጅ መጽሃፍ አንብበው መበደላቸውን ቱግ ግንፍል እያሉ ሲያወሩ ሰማናቸው፡፡ አንባቢ ሴትዮዋ ኢትዮጵያን ሲለቁ 16 አመታቸው መሆኑን ከግንዛቤ ይውሰድ፡፡ ያሳዝናል እንደሳቸው በዶክትሬት ደረጃ የተማረ ነገርን በጥልቀት ሳያገናዝብ የፕሮፌሰር ሃይጋን የማጠብ ፖለቲካ ሳያላምጥ የበላበትን ወጭት መስበሩ በእጅጉ ያስተዛዝባል ፡፡ እውቁ ኢትዮጵያዊ መንግስቱ ለማ በሎንዶን ሲማር በህመም ምክንያት ሆስፒታል ገብቶ አንዱ መደዴ እንግሊዝ ልብስ የለበስከው አየር ማረፊያው ላይ ወደ እንግሊዝ ስትመጣ ነው፤ ሃገርህ ዛፍ ላይ ነበር ተንጠልጥለህ የምትኖረው ይህንን አስረዳን በማለት በመቶ በሚቆጠሩ መደዴ የእንግሊዝ ህሙማን ወጥረው ቢጠይቁት ነገሩ ገርሞት "ከየት ልጀምረው ብሎ ጥልቅ ሃሳብ ውስጥ የገባውን ያህል ለወ/ሮ ጸጋም ለመመልስ ከየት ልጀምር ብሎ በእጅጉ ያስጨንቃል፡፡ መንግስቱ ለማ ግን ቆፍጣና ኢትዮጵያዊና የተዋጣለት ምሁር በመሆኑ የተጠየቀውን አንዱንም ሳይክድ እነዛን መደዴ እንግሊዞች በምሁራዊ ትንተና አላዋቂነታቸውን አረጋግጦ ኢትዮጵያን አስከብሮ ታሪካዊ ተልእኮውን ተወጥቶ ነበር ወደ ውድ ሃገሩ የተመለሰው፡፡
በጎንደር፤በጎጃም፤በወሎ፤በሸዋ፤በከፋ፤በትግራይ፤በአሩሲ፤በሲዳሞ፤በሃረር፡፡ አንዱ አንዱ ላይ መቀለዱ
የታወቀ ነበር ያም ካለመማር የመጣ እንጅ ቂም ታስቦ ታልሞ ሌላውን
ለማቁሰል በኢንስቲቱሽኖች የተባለ አባባል አልነበረም፡፡ ጋዜጠኛው
እራሱ በቤተ ሰቡ ሳይቀር የደረሰበትን በደል ከዚህ በፊት አቅርቦልናል እሱም ከግንዛቤ ማጣትና ባለመማር ነው በማለት ነገሩን ቂም
ሳይቋጥርበት አልፎታል፡፡ ጎጃሜ ቡዳ ነው እየተባለ በዘፈን ሳይቀር ይቀለዳል ወ/ሮዋም ይህን ነገር ያውቃሉ ወይም ከቤተሰባቸው ይሰማሉ፡፡ጎጃሜ
ግን ሃገሩ ኢትዮጵያ ላይ እንዲህ ተባልኩ ብሎ የጥላቻ ሰይፉን እንደ ወ/ሮ ጸጋ አልመዘዘም ስቆ ያልፈዋል እንጅ፡፡ እንደ እውነቱ
ከሆነ ከቤተ እስራኤላውያኑ በላይ በትግሬ፤በአማራ፤በኦሮሞ፤በደቡብ ይቀለዳል እንደውስ ማን የማይቀለድበት ጎሳ አለ? ህብረተሰባችን ባለመማሩ አርሶ የሚያበላውን ገበሬ አፈር ገፊ፤ ማረሺያውን የሚሰራለትን ቀጥቃጭ፤ ሸምኖ የሚያለብሰውን ሸማኔ፤ ፍቆ አቅማዳ የሚሰራለትን ፋቂ ሌላም ሌላም ስም ሲሰጠው ኑሯል፡፡ ባለውለታውን በዚህ መልኩ የሚጠራ ህብረተሰብ ባለመማሩ አላዋቂ
ካለመሆኑ በስተቀር ምን ምክንያት ሊሰጥበት ይችላል? ቤተ እስራኤላውያን ነን ብለው ራሳቸውን የጠሩት በዚህ ልክ ተበድለው ነበር
ወይ? ዛሬ አገራችን እስራኤል በሚሉት አገር ከዚህ ያነሰ መገለል አልደረሰባቸውም ወይ? በእርግጥ በየስርአቱ ከገዥዎች ጋር እንደ ዶር ጸጋ የሚሞዳሞዱ ይህ መገለል ላይደርስባቸው ይችላል፡፡ ወሮ ጸጋ እንዳናውቅ ቢያድበሰብሱትም በሃገረ እስራኤል በትውልደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን
ላይ የሚደርሰው በደል በመላው አለም የሚገኙ ሚዲያዎችን ቀልብ ስለሚስብ በየእለቱ እየሰማነው ነው፡፡ እንደውም ይህ ጽሁፍ ሲዘጋጅ ቤተ እስራኤላውያን ላይ የሚደርሰውን በደልና
አድልዎ አስመልክቶ የእስራኤል ፓርላማ ውይይት ያደርጋል ዶር ጸጋ የማገጃ ትእዛዝ ካላወጡበት በስተቀር፡፡ዶር
ጸጋ አክቲቪስት ሁነው የእስራኤልን ፓርላማ ደጅ ይጠኑ የነበረው ቆሻሻ ነው ተብሎ በተደፋው በኢትዮጵውያን ደም ምክንያት
መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ ቤተ እስራኤላውያን ከጠቅላላው የእስራኤል ህዝብ በንጽጽር በግምባር ላይ ከሚሰለፉ የእስራኤል ወታደሮች
ከፍተኛውን ቁጥር ሲይዙ ሞታቸውም በዚያው ልክ ያሻቅባል ይህ ዶር ጸጋን አያሳስብም ባላቸው ንክኪ ልጆቻቸው ወደ ውጊያ ስላማይሄዱ፡፡
በኦፊሰር ደረጃ ያሉ እጅግ በጣም ጥቂቶችና ለንጽጽርም የሚበቁ አይደሉም፡፡ ወ/ሮ ጸጋ ማርች 15 2023 ለኪኔሴቱ ባደረጉት ንግግር
ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ቤተ እስራኤላውያኑ በቂ መተዳደሪያ ያለ ማግኘታቸው፤በመንፈሳዊ
አባቶቻችዉ ላይ የሚደርሰው ንቀት፤በቂ የሆነ ህክምና ያለማግኘት፤ልጆቻቸው የከፍተኛ ትምህርት እድል ያለማግኘት፤የሚመደቡበት የትምህርት
ዘርፎች ወደፊት በቂ መተዳደሪያን የማያገስገኝ መሆኑ በመግለጽ ነበር፡፡ እንደውም በ2022 በሃላፊነት ሰራ የተመደቡት 2% መሆናቸውንና
በትምህርት ረገድ ከፍተኛ መድሎ እንደተደረገባቸው ዛሬ በጣም ሰልጥነናል በሚሏት እስራኤል ላይ እየተደረገባቸው መሆኑን በሪፖርታቸው
ገልጸዋል፡፡ ስምና አዲስ ማንነትን የመቀየሩን ነገር ከግምት ሳንከት ማለት ነው፡፡ የአረብና ሌሎች ወደ እስራኤል የፈለሱት ቤተ
እስራኤላውያን ቀድሞ የነበራቸውን ስምና ማንነት ሲይዙ ከኢትዮጵያ የሚሄዱት ግን አዲስ ስም ወጥቶላቸዋል አዲስ የሃይማኖት ስልጠናም
ተቀብለዋል፡፡ኢትዮጵያ ግን በልጆቿ መሃል ልዩነት ሳታደርግ በድህነቷ እኩል አስተናግዳቸዉ ነበር የኢትዮጵያ በደሏ ደሃ መሆኗ ነው ደሃ እናት ደግሞ ለምን ደኸየች ተብላ በጠላትነት
ልትታይ አይገባትም፡፡
ከ9 ወር በፊት እዚሁ እግረኛው ሚዲያ ላይ ብርቱካን የተባለች መልከ መልካም ወገናችን በትግራይ "ቡዳ ነሽ" ፤ "ወደ ጅብነት ትቀየሪያለሽ" ሌላም ሌላም እያሉ መቆሚያ መቀመጫ አሳጥተውኛል"<<ከትግራይ-አውጡኝ>> በማለት ተማጽኖዋን ለኢትዮውጵያውያን አቅርባለች፡፡ መረጃውም እነሆ።
https://www.youtube.com/watch?v=tgpLyHmkBdg
ብርቱካን ምንም እንኳን የኦርቶዶክስ ተከታይ ብትሆንም ልጅሽን ክርስትና አናነሳውም፤ ልጆችሽም ከልጆቻችን ጋር አይማሩም ተብላ በሚያሳዝን ሁኔታ የተገለለች ወጣት ነች፡፡ ብርቱካን ፈላሻ ሁና አይደለም ይህ ሁሉ መገለል የደረሰባት፡፡ ለዚህ ተጠያቂው የትግራይ ህዝብ ሳይሆን እንደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገር የእውቀትና የግንዛቤ ችግር በማህበራችን መንሰራፋቱ ነው፡፡ እስቲ ወደ ወሮ ጸጋ ህይወት እንመለስ ወ/ሮ ጸጋ ጎንደር በልጅነታቸው ብስክሌት እየጋለቡ የምድር መንግስተ ሰማያት ይኖሩ የነበር ሲሆን ቤተሰባቸው በጎንደር ቤት ንብረት ያላቸው ነበሩ አባታቸውም በወቅቱ ለሌሎች ህልም በሆነው በመብራት ሃይል ተቀጥረው ይሰሩ ነበር፡፡ ወሮ ጸጋ መበደላቸውን ያወቁት ከቤተሰባቸው ሳይሆን በሰሚ ሰሚ ከፈረንጆቹ ነበር፡፡ ብዙ ጎንደሬዎች ከቤተ እስራኤላውያን ጋር ተጋብተው በፍቅር እየኖሩ ነው ከቤተ እስራኤላውያንም ለመጋባት ከፍተኛ ፍላጎትም እንዳለ ጋዜጠኛ ተክሌ በቦታው ተገኝቶ የአይን ምስክርነቱን ቢሰጥም ሴትዮዋ ለመስማት ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ቤተ እስራኤላውያኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በውትድርና፤ በአስተዳደር፤ በትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ነበሩ የወ/ሮዋ በሬ ወለደ ተረት አንድም ተጨባጭነት ያለው ማስረጃ ሊቀርብለት አይችልም ከአፈ ታሪክ በዘለለ፡፡
ዶር ጸጋ አንዱ አምርረው ከገለጹት በላይና ሊረሱት ያልቻሉት ፈላሻ እየተባሉ መጠራታቸውን ነው ይገርማል በዚያው ቃለ ምልልስ ማንኛውም ቤተ እስራኤላዊ ህልሙና
ጸሎቱ ከ2500 አመት በፊት ከመጣባት ከፈለሰባት ሃገሩ ወደ እስራኤል መመለስ ነው ብለውናል፡፡ ይህ የዶ/ር ጸጋ ማብራሪያ የሚያሳየውና
ዶር ጸጋም የተቀበሉት ከውጭ ፈልሰው የመጡ መሆናቸውን ነው፡፡ ታዲያ ይህ ስም በሌሎች ሲጠራ ወንጀል መሆኑ ምኑ ላይ ነው? በእርግጥ
ይህንን ስም አንወደውም ተብሎ ስምን መለወጥ ይቻላል የጥል መንስኤ
ግን መሆኑ አግባብነት የለውም ፡፡ (በጌምድር ወደ ጎንደር፤ ጋላ ወደ ኦሮሞ፤ አሩሲ ወደ አርሲ፤ሀረር ወደ ሃረሪ ተለውጧል ሌላም
ሌላም)፡፡ ቤተ እስራኤላውያን ኢትዮጵያ በነበሩበት ጊዜ በእኩልነት አንዱ ከአንዱ ሳያንስ የሚኖርበት በመሆኑ ዶር ጸጋና ቤተሰቦቻቸው
ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ በላይ የቅንጦት ኑሮ መኖራቸውን አባባላቸው
የፈጠራ መሆኑን አሳይቷል፡፡ ማሳያውም " እናቴን ነገ ወደ ኢትዮጵያ ልንሄድ ነው ብዬ አሁን ብደውልላት ልዘጋጅ
እንኳን አትለኝም ለኢትዮጵያ ካላት ፍቅር የተነሳ" በማለት ኢትዮጵያ ያለመበደሏን አረጋግጠውልናል፡፡ በእርግጥ ወያኔ
ከገባ በኋላ ሂደው ቢሆን ኑሮ በጎሳዬ ተበደልኩ ብለው ሊነግሩን ይችሉ ነበር የወቅቱ ፋሽን በመሆኑ፡፡ እንደዛም እንዳንል ጌታቸው
ረዳ የ TPLF መሪ ሁኖ ወደ እስራኤል ተጉዞ እንዳነጋገራችውም እናውቃለን፡፡ እንደ ወ/ሮ ጸጋ ገለጻ ጀርመን ካደረሰባቸው በላይ ኢትዮጵያውያን ያደረሱባቸው በደል ይበልጣል ባይ
ናቸው፡፡ የኢትዮጵያውያን መልካምነት ግን በእናታቸው በኩል ተንጸባርቋል፡፡
ዮዲት ጌዴዎን የአይሁድ እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰችው ጥፋትና ሰቆቃ ጀርመን በሚኖሩት አይሁዳውያን ላይ
ከደረሰው ይበልጥ እንደሆን እንጅ የሚተናነስ አልነበረም መልካሙ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን በዚህ ቂም አልያዘም ተፈጥሮውም አይደለም፡
ዶር ጸጋ የእስራኤል ወዳጅ ናቸው ብሎ ፣መገመት ይከብዳል፡፡ በውነት ለቤት እስራኤሎች ከኢትዮጵያውያን በላይ ወዳጅ
ከየት ይመጣል? 80% ያህል ኢትዮጵያዊ ለእስራኤል በአንድም ሆነ በሌላ ስስ ልብ አለው፡፡ " የእስራኤል ወዳጇ ለኔም ወዳጄ ነው ቤተኛ መሆኔ ታዲያ ምኑ ላይ ነው?'
እያልን እንዳላዜምን እኝህ ሰው በእብሪት ጉድ ሰሩን ፡፡ ወሮ ጸጋ የወደፊት ህልማቸውን ሲጠየቁ ለጊዜው ከነኳታር ጋር ተስማምተናል ሳውዲ አረቢያና የተለያዩ ቦታዎች በነጻነት
መሄድ ነው የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል ኢትዮጵያ ግን ዝርዝራቸው ውስጥ አልተካተተችም፡፡ ወሮ ጸጋ ኑሮና ታሪክ ብዙ አስተምሮናል ቁሚያለሁ
ያለ በእግዚአብሄር የቆመ ነው አሜሪካ አውሮፓን አላውቅህም ብላዋለች ነገ ነገሮች ምን አቅጣጫ እንደሚይዙ የሚያውቅ ፈጣሪ ብቻ ነው
አይበለውና ለጥቂት ሰከንድ እስራኤልን ከአሜሪካ ነጥለው ይመልከቷት፡፡ ባለፈው በኢራን የሚሳዬል ውርጅብኝ ሲወርድ ባንድ እግራችን
እየቆምን ነበር ምህላ ያደረስነው ዛሬ እርሶ ግን ይህ የመከራ ጊዜ ያለፈ ሲመስሎት ገደብ በሌለው እብሪት ያብጠልጥሉናል፡፡ እንደ እርሶ አይነት ፖለቲከኛ ለእስራኤል ጠላት እንጅ ወዳጅ አያበዛላትም
መሰረተ ኢትዮጵያውያን ለሚቀጥለው የፓርላማ ምርጫ ይህን ነገር ከግምት ይከታሉ ብለን እናምናለን፡፡
ወሮ ጸጋ ወደ እስራኤል የወሰዶት የእምነትም የመገፋትም ምክንያት አይደለም ኢትዮጵያ ደሃ አገር በመሆኗ ጥሩ ኑሮን ፍለጋ በማለም ነው፡፡ እኔም ሃገሬን ጥዬ ወደ አሜሪካ የተሰደድኩት
የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ነው እኔም ዜግነቴን ቀይሪያለሁ ሃገሬ በነበርኩበት ጊዜም መናጢ ደሃ ነበርኩ ሃገሬ ካላት በላይ ልትሰጠኝ ስለማትችል
ዛሬ ላይ እንደ እርሶ ኢትዮጵያን ሳብጠለጠል አልውልም እንደውም ሃሳቤና መንፈሴ ከኢትዮጵያ ተሰፍቶ ከእንቅልፍ የምባንንበት ጊዜም
አለ ስለ መጭው ዘመኗ በማሰብ፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የሚጎርፈው ቤተ እስራኤል እንደ እኔና እንደእርሶ መልካም ኑሮን ፍለጋ
ነው፡፡ በሊቢያ፤ በየመን፤በሱዳን፤በሳውዲ አረቢያ ነብሱን አስይዞ
ተዋርዶ የሚጎርፈው የተከበረው ኢትዮጵያዊ በተመሳሳይ ምክንያት ምክንያት
ኑሮን ለማሸነፍ ነው ማለባበስና ምክንያት መደርደር አያስፈልግም፡
በአውሮፓና በአሜሪካ እጅግ ብዙ የሃገሩ አይሁዳውያን ይኖራሉ በኢትዮጵያውያኑ ልክ እራሳቸውን ለአደጋ ሰጥተው ወደ እስራኤል ለውትድርና
ግልጋሎትና ለመኖር ሲጓዙ አላየንም ምክንያቱም እስራኤል ሊያገኙ ከሚችሉት
ጥቅም በላይ ባሉበት አገር ስለሚያገኙ ነው፡፡ በተቃራኒው ብዙ እስራኤላውያን ወደ አውሮፓና አሜሪካ ይጎርፋሉ( ይፈልሳሉ የሚለውን ቃል ላለመጠቀም ነው
እንዳያስቆጣዎት)፡፡ በቃለ ምልልሶ እንዳስተዋልነው ያቀረቡት ሃተታና ምክንያት ሁሉ ውሃ የሚቋጥር አይደለም ምሁራዊ ትንታኔዎም እጅግ
ቀላላ ነው፡፡ ዛሬ አለም እርሶ ኢትዮጵያን ሲለቁ የነበረበት ዘመን አይደልም የመረጃዎች ፍሰት በእጅጉ ጨምሯል ምናልባትም እዛው
እስራኤል ውስጥ ሁነው እርሶ ያልደረሱበት ዜናዎች የኢትዮጵያ ወጣቶች እጅ ሊደርስ ይችላል የእውቀት ሞኖፖሊነትም ስላበቃ ሌላውን
አሳንሶ ማየት አላዋቂነት ነው፡፡
ወ/ሮ ጸጋ ከእስራኤል ባለስልጣን ጋር በተለያየ ሁኔታ መገናኘታቸውና ፎቶ መነሳታቸው እራሳቸውን እንደ ነጮች ሳይመለከቱ አልቀሩም፡፡ ወሮ ጸጋ እርሶ እስከ ቤተሰብዎ ጠቅልለው ስለመጡ እርሶ ያገኙትን እድል ኢትዮጵያ ለቀሩት ቤት እስራኤላውያን አይነፈጓቸው ጥረትም ያለማድረግዎን ፍንጭ ሰጥተዋል ከ3 ትውልድ በላይ አናመጣም የሚሉት ለኢትዮጵያውያኑ አይሰራም እዚህ ከ3 ትውልድ በላይ ስላልተጨፈጨፋችሁ፡፡ በኢየሩሳሌም ስላለው ይዞታችን የግብጽ ነው ብለው ቃሎን ስለሰጡ ምን ማለት እንችላለን አፍቃሪ ኢትዮጵያ የፓርላማ አባል ሲመጣ ጉዳዩን ህይወት ይዘራበት ይሆናል፡፡ የፓለስታይኑ እስላሙ ንጉስ ይዞታችንን ሲያጸኑልን በሳለሃዲን ጊዜ ኢትዮጵያውያን ተጓዦች ልዩ ጥበቃ ተደርጎላቸው ወደ እምነት ቦታቸው ሲጓዙ በነ ዶር ጸጋ መላኩ የስልጣን ዘመን ይዞታችን መነጠቁ ልብ ያደማል ጊዜ ይፍረደው፡
በመጨረሻም ለእስራኤል መራጭ ህዝብ በተለይም ቤተ እስራኤላውያን
ወሮ ጸጋን በዚያ ወምበር ያስቀምጥካቸው አንተ ነህ ሴትዮዋ አፈትልኳቸው እንደገለጹት ክፉ የኢትዮጵያ ጥላቻ አላቸው
ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን በዚያ ለሚኖሩት ቤተ እስራኤላውያንም ክብርና ፍቅር የላቸውም በዚያ ያላችሁ ወገኖቻችን ኢትዮጵያ አገራችሁ ነች ኢትዮጵያ መሸሻችሁ ነች
ዶር ጸጋ ግን በዚህ ወምበር እስከተቀመጡ ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላችሁ
ቁርኝት መፋቁ አይቀሬ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ለናንተ ያለው ፍቅር
ወደር የለውም ነገር ግን እናንተን በዶር ጸጋ አይን ካያችሁ አትራፊ አትሆኑም፡፡ በእርግጥ እንደ ወንድማችን ዳጊ መሰለኝ ወደ ፓርላማ
ሲገባ የእናቱን ጉልበት የሳመው፤እነ ዶር አምባሳደር አብረሃም ንጉሴ አይነቱን በወሮ ጸጋ አይነት ማየት ቢከብደንም በዚህ ሃላፊነት
የሚሰሩ ሰው ያደረሱት ጥፋት በእናንተው ካልሆነ በሌላ ሊፋቅ አይችልም፡፡ የሴትዮዋ ኢትዮጵያን ጥላቻ የጀመረው ከፕሮፌሰር ሃይጋ ትምህርት ይሁን ወይም የትግሬ ራዲዮ በሚሰሩበት
ጊዜ ወይም ደግሞ ጌታቸው ረዳ የ ቲ ፒ ኤል ኤፍ መሪ ሁኖ በጎበኛቸው
ጊዜ ትክክለኛ ምንጩን ለጊዜው ማወቅ ቢከብደንም ወደፊት መድረሳችን ግን ጥርጣሬ የለውም፡፡ በነገራችን ላይ የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ የዘር
ሃረጉ ከአይሁድ እምነት ተከታዮች ቤተሰቡ ይመዘዛል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ሰመረ አለሙ semere.alemu@yahoo.com

No comments:
Post a Comment