Thursday, February 5, 2026

ለአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እኔም የምለው አለኝ! ይኄይስ አእምሮ 2/5/26 Ethiopian Semay

ለአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) እኔም የምለው አለኝ!

ይኄይስ አእምሮ

2/5/26

Ethiopian Semay

በቀጣዩ ዐረፍተ ነገር የምለውን ለማለት በርግጥም የተወሰነ ጥናትና ምርምር አስፈላጊ መሆኑ አይካድም፡፡ [ይሁንና] ካነበብኩትም፣ ከሰማሁትም፣ ፈጣሪየ ረዘም ያለ ዕድሜ ሰጥቶኝ በሕይወት ተሞክሮየ ከታዘብኩትም፣ በተለይ ደግሞ ያለፉት ስምንት ዓመታት የአቢይ አህመድ ጭራቃዊ አገዛዝ አእምሮየን ካሸከመው ሥነ ልቦናዊ ቀውስና አእምሯዊ ህመም በመነሳት “በዓለማችን ታሪክ እንደአማራ ጠላት የበዛበትና በዚያም ምክንያት እንደአማራ የተበደለ ሕዝብ (ነገድ) የለም” የሚል ግለሰብኣዊ ምሥክርነት ብሰጥ ስህተቴ ያን ያህል ለከፉ የሚሰጥ አይመስለኝም፡፡ የአማራ ጠላት እንደመብዛቱ እስካሁን አለመጥፋቱ ደግሞ የፈጣሪ ጣልቃ ገብነት እንዳለ መገመት አይከብድም፡፡ ለምን ቢባል ሌሎች መሰል ነገዶች ጠፍተዋልና፡፡ አማራ ግን ትንሣኤው እንደተጠበቀ ሆኖ እየተንጠራወዘም ቢሆን አለ ለማለት ያህል እስካሁን አለ፡፡

የአማራ ጠላቶች ቆጥረው አይዘለቁም፡፡ ጭንቅላቱ በውጭ ሀገር ሆኖ በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ ዓለምን እየገዛ የሚገኘው የአፍራሹ ኃይል ምድራዊ ወኪል (Ambassador of the Negative Energy) አንደኛው ሲሆን ሁለተኛውና የዚህ ኃይል የሀገር ውስጥ ታዛዡ ደግሞ በዚሁ አሉታዊ ኑባሬ ተኮትኩቶና በመርዛማ ትርክት አንጎሉ ተሞልቶ ያደገውና አንዱ አንዱን እየተካ የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥትን ሲቆጣጠር በሚገባ የምናውቀው ዘረኛና ሆዳም ትውልድ ነው፡፡ እነዚህ ዋነኞቹ የአማራ ጠላቶች ሲሆኑ ከዋና ጠላትነት ባልተናነሰ የአማራን ከርሰ መቃብር እየቆፈረ አማራን በመጨረስ ላይ የሚገኘው ደግሞ ከአማራው አብራክ የወጣ ሆዳምና ባንዳ አማራ ነው፡፡ የአማራ ክልል ሚሊሻና አድማ በታኝ ከመከላከያ ጋር ጥምር ጦር በሚል መጠሪያ ተባብሮ ፋኖን በመውጋት የራሱን አጥፊ ኦሮሙማን ሲታደግ ይታያችሁ፡፡

ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ነጥብ ዙሪያ ትንሽ ተጨማሪ ነገር ማለት አስፈላጊ ነው፡፡ በቅድሚያ ግን በክርስትና ሃይማኖቴ አንድ ትልቅ አስተምህሮ ያለው ክስተት ባስታውስ ደስ ይለኛል፡፡ እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር እንደሰው ሲመላለስና ተልእኮውንም ጨርሶ በስቅላት ሕይወቱን ለሰው ልጆች ሲገብር ለዚያ ኹነት ያበቃው ይሁዳ የሚባል የራሱ ደቀ መዝሙር መሆኑ ነው፡፡ ገንዘብ ያዥ የነበረው ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር አበደና ጌታውን በ30 አላድ ሸጠ፡፡ ጉንጩን በመሳም አሳልፎ ከሸጠውና እንዲሰቀል ካደረገው በኋላ ግን ተፀፀተና የሸጠበትን ገንዘብ ሳይበላው ራሱን ሰቅሎ ሞተ፡፡ አማራን የከዱ አማሮች ሁሉ ክርስቶስ “የሰውን ልጅ አሳልፎ የሚሰጥ የወፍጮ መጅ ባንገቱ ላይ ታስሮ ወደ ባሕር ቢጣል ይሻለዋል” ሲል ያ ሆዳም ገብጋባ፣ ያ የዲያቢሎስ ልዑክ ይሁዳ መዳረሻው ሲዖል እንጂ ገነት እንደማይሆን በግልጽ እንደተናገረ ሁሉ እነዚህ አማራን የከዱ አማሮችም በታሪክ ጥቁር መዝገብ ስማቸው ሰፍሮ ወደፊት ለሚነሱ ከሃዲዎች መቀጣጫ እንደሚሆኑ አንጠራጠርም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡

አማራን ገባ ብለን ማየቱ ስለአማራ ጠላት አማራዎች መጠነኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስችለናል፡፡

በአማራ ስም የሚነግደው አማራ ነኝ ባይ እጅግ ብዙ ነው፡፡ በመሠረቱ አማራነት ክፍት ነው - በተለያዩ ምክንያቶች፡፡

አንደኛ - አማርኛ ቋንቋ ባለቤትነቱ አማሮች ተብለው ለተፈረጁት ዜጎች ብቻ የተተወ ሣይሆን የገዢዎችም ቋንቋ ነው፡፡ ገዢዎች ደግሞ ከየትኛውም ነገድ ወይም ብሔር/ብሔረሰብ የሚመጡ ናቸው - አማራውም፣ ትግሬውም፣ አገውም፣ ኦሮሞውም … ኢትዮጵያን እየተፈራረቀ ገዝቷል፡፡ ስለዚህ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አማርኛ ባለቤት አልነበረውም - ግን ያስገድል መጀመሩ ከጊዜ ወደጊዜ ግንዛቤ እያገኘና አማርኛን በአፍ መፍቻነት የሚናገሩ ተጠቂዎችም የአክራሪ ዘረኞች ዒላማ እየሆኑ መጡ፡፡

ሁለተኛ - አማራ የሚባለው ነገድ ከአካባቢና ከክፍለ ሀገር ልጅነት ባለፈ በጎሰኝነትና በዘረኝነት እንዲሁም በአንድ ቋንቋ ተናጋሪነት የፍረጃ ደዌ የተለከፈ ባለመሆኑ ከሁሉም የኢትዮጵያ ነገዶች ጋር ተዋልዷል፤ ተካብዷል፡፡ ስለዚህም በዘረኝነት ልክፍት ተጠምዶ በወንዝና በሸንተረር ራሱን አጥሮ የጋራ መሰባሰቢያ ጎሣዊ ማንነት ሊፈጥር አልቻለም፡፡ ይህም አንዱ የችግሩ መንስዔ ነው፡፡

ሦስተኛ - በብዙ የመቶኛ ስሌት “ጥርት ያለ” አማራ የሚባለውን ዜጋ ከዜሮ በላይ እስከሚገኙ ጥቃቅን የመቶኛ ሥሌቶች ድረስ “በአባቴ እናት ትግሬ ነኝ፤ በሴት አያቴ አባት ኦሮሞ ነኝ” የሚለውን ሰው ሁሉ አማራ በአማራነት ይቀበላል፤ አማራ የመሳብና የማቀፍ እንጂ የመግፋትና እደጅ አቁሞ አጥንትና ደም የማጣራት ጠባይ የለውም፡፡ ስለሆነም ይህ ለማንም እጅግ የተለጠጠ አማራዊ ክፍተት ለአሰለጦችና ለጠላቶቹ ቦርቃቃ መግቢያ በር እየከፈተ አማራን አስጠቅቶታል፤ እያስጠቃውም ነው፡፡ አማራ የአማራነትን ነገዳዊ የማንነት ሥልጣን የመስጠት ወይ የመንፈግ መብት እንደሌለው ይገነዘባል፡፡ ሌሎች ግን ይህ መብት እንዳላቸው ይሰማቸዋል ብቻ ሣይሆን ተግባራዊ ሲያደርጉም ይስተዋላል፡፡ ለምሣሌ አንድ ሰው ኦሮሞ ነኝ ቢልና ኦሮምኛ ቋንቋንም ከኦሮሞ ነኝ ባዩም በበለጠ ጥንቅቅ አድርጎ ቢናገር ዘር ማንዘሩንና የትውልድ አካባቢውን ተናግሮ በተገቢው መንገድ እንዲጣራና ትክክለኛ ኦሮሞነቱ እንዲታወቅ ካልተደረገ በስተቀር ባህሉንና ቋንቋውን በማወቁ ብቻ ከታወጀው ጄኖሣይድ አይተርፍም፡፡ ለዚህ ነባራዊ እውነት የወለጋ አማራ-ኦሮሞዎች ኅያው ምሥክር ናቸው (ከዚህ ነጥብ አኳያ ትግሬዎች እንደሚሻሉ እኔ አውቃለሁ)፡፡ አማራ ግን አማርኛን ሁሉም ስለሚናገረው መልክህ ጠቆረ ቀላ፤ ቁመትህ ረዘመ አጠረ፣ ሰውነትህ ከሳ ወፈረ … አማራ ነኝ ካልክ አማራ ነህ - አበቃ፡፡ ሁሉም ነገ ጥርግርግ ብሎ ወደማይቀረው ቤቱ ሊጓዝ አሁንና ዛሬ አንተ አማራ ሆንክ አልሆንክ ለአማራ ጉዳዩ አይደለም፡፡ በሦስት ቀናት የሚፈርስ ሰውነት በነዚህ ምድራዊ ልዩነቶች ሲናከስና ሲበላላ ይታያችሁ፡፡ ይህም አንደኛው አማራን የሚያስጠቃ ነጥብ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ስንሞት እኮ ቋንቋም በለው ሃይማኖት፣ ሀብት በለው ንብረት አብሮ አይሄድም፡፡ በምን ዓይነት ድንቁርና ውስጥ እንደምንኖር ሳስበው ይገርመኛል፡፡

 አምስተኛ - ራሱን በአማራነት የተቀበለ ዜጋ ሳይቀር ለሆዱ ተገዝቶ ከአማራ ጠላቶች ጋር በማበር አማራን ለማጥፋት ይሰማራል፡፡ ለዚህ ትልቁ ምሣሌ አቢይ አህመድ ራሱ ነው፡፡ ብዙ ሰው አቢይን በኦሮሞነት ነው የሚያውቀው፡፡ ግን ስህተት ነው፡፡ አቢይ በኦሮሞ ላይ ማሾፉ እንዳለ ሆኖ እናቱ ወሎዬና አባቱ አማራ ወይም ጋሞ እንደሆነ ይነገራል - ቅንጣት ኦሮሞነት የለበትም፡፡ ምንም እንኳን ተበርዘን ተከልሰን አንድኛችንን ከሌላኛችን በመልክና በቁመት መለየት ብንቸገርም የአቢይ መልክ ሲታይ ግን ይበልጥ የሚቀርበው አማራ ወደሚባሉት ኢትዮጵያውያን ነው ወይም ይመስለኛል፡፡ የሥልጣን ወንበሩን በምንም ዓይነት መንገድ ለድርድር የማያቀርበው አቢይ ግን የመጣበትን ነገድ ክዶ ኦሮሞ በመምሰል አማራን እያጠፋ ይገኛል፤ ነገ ኬንያ ውስጥ ሌላ ዕድል ቢሰጠው ኪኩዩ ነኝ ብሎ እነሉዎንና ካሊንጂን፣ እነካምባና ሉያን ከማጥፋት አይመለስም፡፡ የቆረበው በጥፋት ነውና፡፡ ይህ የሰንበት ጽንስ አቢይ አህመድ መላውን አማራ ሳይቀብር የአእምሮ ዕረፍት እንደማያገኝ ሁሉም የሚመለከተው ወገን ካልተረዳ አደጋው በ60 ሚሊዮን አማራ ብቻ ተወስኖ እንደማይቀር መታወቅ አለበት፡፡ ለማንኛውም አማራነትንና ኢትዮጵያዊነትን የካዱት እነተመስገን ጥሩነህና ዳንኤል ክብረትም ሆኑ ሌሎቹ በአእምሮ የቀነጨሩና ለሆዳቸው ሲሉ ለአጋንንቱ ዓለም ያደሩ በላዔሰቦች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ የፍርድ ቀናቸውም  በብርሃን ፍጥነት እየመጣ ነው፡፡ አፋብን ከዚህ አንጻር ብዙ ይጠበቅበታል፡፡ ራሱን ግን በደምብ ይፈትሽ!!

በላይኛው አካሄድ ከተጓዝኩ መቆሚያ የለኝምና ወደተነሳሁበት ላምራ፡፡

1. አማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ከፍ ሲል በአጭሩ ያስቀመጥኩትን እውነታ በማጤን የትግል ሥልቱን በአስቸኳይ ይለውጥ፡፡ ለውጦም ትግሉን ከአማራ ክልል አሁኑኑ ያውጣ፡፡ አለበለዚያ በዚህ መልክ ከቀጠለ አማራ ክልል ይጠፋል፤ የትም ሥፍራ የሚገኝ አማራም ያልቃል፡፡ አሁን ራሱ አማራ አለ ማለት በማንችልበት ሁኔታ ተቋማቱና ኢኮኖሚው እየወደሙበት ነው፡፡ የተነሱበት ጠላቶች ዋና ዓላማ አማራን መጨረስ ብቻ ሳይሆን የአማራ ነው የተባለ ነገርን ሁሉ እንስሳትንና ዛፎችን ጭምር እየረመረሙ አማራን ባዶ ማስቀረት ነው፡፡ የፋኖ ትግል ከአማራ ክልል ካልወጣ የአማራ ችግር በቶሎ ዕልባት አያገኝም፡፡ አቢይ እንደሆነ የማይነጥፈውን የኢትዮጵያ ሰብኣዊና ቁሣዊ ሀብት ስለተቆጣጠረ የሚያሰማራው ሰውና ድሮን የሚገዛበት ገንዘብ እስኪያጥረው ድረስ ለመቆየት ማሰብ ጅልነት ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ይቀራል እንጂ አቢይ የሚያሰልፈው ወታደርና የሚተኩሰው ጥይት ወይም የጦር መሣሪያ ግብኣት ሊያጣ አይችልም፡፡ ሺህ ዓመት እዋጋለሁ የሚለው እዚህ ላይ እውነቱን ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝብ አታስጨርሱ፤ ሀብት ንብረት አታስወድሙ፤ በቶሎ ከአማራ ክልል ውጡ፡፡ አቢይን አደህይቼ አራት ኪሎን እይዛለሁ ማለት ቅዠት ነው፡፡

 አቢይ የሚቀናጣበትንና ጦርነት የሚያካሂደበትን ገንዘብ በፍጹም አያጣም፡፡ እደግመዋለሁ ከአማራ ክልል ቶሎ ውጡ!! አቢይ አማራን ለማጥፋት የሚተባበረው የውጭ ኃይልም እንደዚሁ እጅግ ብዙ ነው፡፡

2. ውስጣችሁን አጥሩ፡፡ “ሳል ይዞ ስርቆት፤ ቂም ይዞ ጸሎት” የለም፡፡ እርስ በርስዋ የተከፋፈለች መንግሥትም አትጸናም፡፡ ስለዚህ አንድ ሁኑ፡፡ ላልተጨበጠ ሥልጣንም አትራኮቱ፡፡ ገና ነው፡፡ ምኑም አልተያዘም፡፡ ለተረት ከአማራ በላይ ያለ አይመስለኝም - “የምትስቅ ሴትና የሚነቃነቅ ዛፍ” የምትሉት እናንተው ናችሁ፡፡ የምትስቅ ሴት ሳቀችልኝ ስትል እያሾፈችብህ ሊሆን ይችላልና ያኔ መጠንቀቅ ነው፡፡ የሚነቃነቅ ዛፍም ከአሁን አሁን ተነቀለልኝ ስትል ውሸቱን ነው - ሊያደክምህ፡፡ ይህን ምሣሌ ወደፋኖ ስናመጣው አንድ ሺህ ወታደር ተሰማርቶብህ ስምንት መቶውን ስትማርክና ሃሴት ስታደርግ በማግስቱ ሃምሣ ሺህ ወታደር ይለቀቅብሃል፤ ምክንያቱም አቢቹ የሰው ችግር የለበትማ! አንተ ጦሩን ማርከህ የምታቀምሰው ስታጣ፣ አንተ በየቀኑ መከላከያን እየገደልክ ጣትህ ሲዝል፣ አንተ የሞተን በመቅበር አቅልህን ስትስት … አቢዩ ግን የሀገሪቱ ተጨባጭ ችግሮች ምንም ሳይመስለው በብልጭልጭ ኮሪደር ዓለምን እያታለለ የሥልጣን ዕድሜውን ያራዝማል፡፡ ይህንንም ሂደት እንኳን አቢይና መንጋው ከፋኖ አመራሮች ውስጥም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የሚወዱት አይጠፉም፡፡ ጦርነቶች የድሃ ጠላቶች እንጂ የባለጌዎች መፈንጫ የሀብት ምንጭ ናቸው፡፡

ልጆቻቸውን በመቶ ሚሊዮኖች ወጪ እየዳሩና ውጭ ሀገር አንቀባርረው እያስተማሩ የሚገኙ ጄኔራሎችና ሚኒስትሮች ዕድሜያቸው በአሥራዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የሚገኙ የድሆች ልጆችን ግን ከትምህርት ቤት እያፈሱ ያለበቂ ሥልጠናና ያለበቂ ደሞዝ ወደሞት ቀጣና ያሰማራሉ፡፡ በሀገራችን የተንሰራፋው ይህን መሰሉ ግፍ ያሳብዳል፡፡ የኑሮ ውድነቱና መፈናቀሉ፣ ቤት ፈረሳውና ለከት የለሽ ቀረጥና ግብሩ፣ ሙስናውና ሌላ ሌላው መከራና ስቃይማ ሆድ ይፍጀው፡፡ ኢትዮጵያ እግዚአብሔርም የረሳት የምንዱባን ምድር ሆናለች፡፡ እንጸልይ፡፡ ምህላም እንያዝ፡፡

3. በሰበር ዜናዎች ተሰላችተናል፡፡ ሰበር ዜና ጥሩ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎች እርግጥ ነው ይኖራሉ፡፡ ሲበዛ ግን ይሰለቻል፤ ማርም ሲበዛ ይመራል ይባላል አይደል? ሦስትና አራት ዓመት በዘለቀ ሁኔታ በጥቃቅን ሰበር ዜናዎች የሚሊዮኖችን ተስፋ ለማለምለም መሞከር እየቆዬ የሚያመጣው አሉታዊ ጎን ለጥገናም አዳጋች ነው፡፡ ከፋኖ ጎን ቆመው በወፌ ቆመች ወፌ ቆመች ትግሉን በተለያዩ መንገዶች ለመደገፍ የሚተጉ ሚዲያዎችን በዚህ አጋጣሚ ባመሰግን ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን በጎመን የተደለለ ሆድ አቀበት ላይ ቢለግም ጥፋቱ የማን እንደሆነ ይታወቃልና ከዚህ ዓይነቱ አካሄድ ቆጠብ ማለቱ አይከፋም፡፡ ለአብነት ያህል ቀደም ሲል የነበረው የሕዝብ ብሩኅ ተስፋና ጉጉት የተሞላበት ጥባቆት (expectation) አሁን ከሞላ ጎደል የለም፡፡ የሰነፉ እረኛ ታሪክ ለስንተኛ ጊዜ እንደሆነ አላውቅም አሁንም በግልጽ እየተስተዋለ ነው - እውነቱን ተናግሮ እመሸበት ማደር መልካም ነውና አንወሻሽ፡፡ ሕዝቡ ሰፍ ብሎ ፋኖን የሚጠብቅበት ጊዜ ነበር፤ ነበር ስል አሁን የለም ማለቴ ግን አይደለም፡፡ የጠቀስኩት ሰነፉ እረኛ በጎቹን ቀበሮ በላብኝ እያለ በመጮህ መንደርተኛውን ሁሉ በውሸት ሲያሯሩጥ ቆይቶ በሦስተኛው ዙር የቀበሮ መንጋ መጥቶ በጎቹን ሲያረትምለትና ያነዜ ቢጮህ ማን ይድረስለት? እንደዚያ ነው የኛ ነገር እየሆነ ያለው፡፡ ፈረንጅ ምን ይላል? አንብብልኛ! “Hit the iron when it is hot.” ለዚህ አማርኛም አይሰንፍም - “ዱላ ይዞ እባብ…” ይለዋል፡፡ ዱላ ይዘሃል - አጠገብህ እባብ አለ፡፡ እስኪነድፍህ ምን አስጠበቀህ? በያዝከው ዱላ መቀጥቀጥ ነዋ! (እማሬያዊ ፍቺው ነው)

4. አምባገነናዊነት የራስን መቀበሪያ ጉድጓድ ከማቃረብ ውጪ ምንም እንደማይፈይድ ፋኖም ሆነ የፋኖ ቤተሰብ ይገንዘብ፡፡ ቀን ሰጠኝ ብሎ፣ አንድን ነገር የማድረግና ያለማድረግ ዕድል እጄ ላይ ወደቀ ብሎ ኢፍትኃዊና ኢሞራላዊ ነገር ማድረግ ይዋል ይደር እንጂ ወደባለቤቱ መዞሩ ገሃድ እውነት ነው፡፡ ለዚህ ብዙ ሩቅ ሳንሄድ እኔ እንኳን በቅርበት የማውቃቸውን ደርግንና ወያኔ/ኢሕአዴግን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ሕዝብን ልትንቅ፣ ድሃን ልትጠየፍ፣ ደካማን ልታንኳስስ ትችላለህ፡፡ የሥራህን የዞረ ድምር ግን ከታሪክና ከሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ተረዳ፡፡ ጉልበትና ኃይል ይከዳሉ፡፡ ዝናና ባለጸግነት እንደጉም ይተናሉ፤ እንደጤዛም ይረግፋሉ፡፡… ስለዚህ ፋኖ አንድ መግለጫ ከማውጣቱ በፊት በቡድን ሆኖ በደምብ ይምከርበት፡፡ አስፈላጊ ከሆነም ከሽማግሌዎችና ከጤናማ የሃይማኖት አባቶች ጋር ይወያይበት፡፡ ከአፍ ከወጣ አፋፍ ነው፡፡ አሸናፊው ፍቅርና መተሳሰብ እንጂ ኃይልና ጉልበት አይደለም፡፡ ቆም ብሎ የመከረ፣ ታገስ ብሎ ያማከረ ብዙ ወንዞችን ይሻገራል፤ ብዙ ተራሮችንም ይወጣል፡፡ ብልኅነት ጀብደኝነትን ይገራል፤ አስተዋይነት ዘመን ተሻጋሪ ስብዕናን ያላብሳል፡፡ ለዚህም ነው ጥበብን የተጎናጸፉ ዜጎች በትውልዶች መካከል በበጎ አርአያነት የሚታወሱት፡፡ ኔልሰን ማንዴልን አስብ፤ ማኅተመ ጋንዲንና ማዘር ተሬዛን አስታውስ፡፡

ዙሪያ ጥምጥም መሄዱን ጋብ ላድርገውና አንድ ሰሞነኛ አውነት ልናገር፡፡ በዚያን ሰሞን ፋኖ በሚዲያዎች ላይ ያወጣው መግለጫ በበኩሌ አላስደሰተኝም፡፡ እቤታቸው ጎመን ሰልችቷቸው ለወጥ ያለ ነገር ባገኝ ብለው ጓደኛቸው ቤትም ሲሄዱ ያው ጎመን ሲቀርብላቸው “በየት ዞረሽ ቀደምሽኝ” ያሉትን የአለቃ ገ/ሃናን ታሪክ ነው ያስታወሰኝ፡፡ ይህን ስል በግሌ መግለጫውን አልደገፍኩትም ለማለት አይደለም - በብዙ ጎኑ የምደግፈው ነው፡፡ ነገር ግን በድርጅታዊ አቋምነት በዚያ መልክ አይወጣም፡፡ ከአንድ አባል እንደግል አስተያየት ቢቀርብ ምንም ባልነበረ፡፡ ብዙ ውዝግብ ማስነሳቱንም ታዝቤያለሁ፡፡ ያኔ ታዲያ የሚመለከተው አካል ብቅ ብሎ ማብራራትና እንዳስፈላጊነቱም ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው በዝምታ ነው የታለፈው፡፡ የትኛው ማኅበረሰብ ነበር “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” ያለው? አዎ፣ ለኔ ብሎ የቆመ ስለኔ ፍላጎትና ድምጽ ግድ ካልሰጠው የኔ አይደለም ማለት ነው፡፡ አይደገም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በትኅትናው የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል - ራሱን ዝቅ አድርጎ፡፡ ሩቅ ሳልሄድ እንደ አስቴር በዳኔ አገላለጽ “ውድ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አቢይ አህመድ እንኳን ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አቅርበው የለም አንዴ?” (ቀለደችብን አስቱ) ወይ ኢትዮጵያ፡፡ የማንሰማው እኮ ላይኖር ነው፡፡

5. ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ የትውልድ አካባቢ፣ ወዘተ. ምንም ማለት አይደሉም፡፡ ከሁሉም ሰው ወይም ሰውነት ይበልጣል፤ ቀጥሎም የአንዲት ሀገር ዜግነት፡፡ ስለሆነም እነዚህን ነገሮች ለባለቤቱ ማለትም ለግለሰቡ መተው እንጂ ተቋማዊ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፤ ፋኖ በመሣሪያና በሰው ብዛት ብቻ ሳይሆን በዕውቀትና በጥበብም ታላቅ ከፍታ ላይ መገኘት አለበት - በራሳቸውና በቅርብ ሰዎቻቸው ላይ ሳይቀር ትክክለኛ ፍርድ የሚሰጡት የነአፄ ምኒልክ፣ የነአፄ ቴዎድሮስ ዘር አይደለም እንዴ? አንድ ሰው ደረቱ ላይ ያሻውን ያህል መጠን ያለው መስቀል ቢያንጠለጥል፤ የጨረቃን ወይ የቀይ መስቀልን ምስል ትከሻው ላይ ቢያስቀምጥ፣ የሰው ቀርቶ የወፍ ቋንቋ ቢናገር መብቱ ነው - የሰውን መብት እስካልነካ ድረስ፡፡ በሌላ በኩል ግን የአንድ ተዋጊ ሠራዊት ሥነ ሥርዓትና ደምብ ሊኖረው ይገባልና በዚያን መሰሉ ሁኔታ በመተዳደሪያ ደምብና በተቀረጸ ህግና ሥርዓት መዳኘት አግባብ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ መሥሪያ ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ወዘተ. በዚህ መሠረት የሚገዙ ስለመሆናቸው እንረዳለንና አባላትም ለደንቦች ተገዢ መሆን እንደሚኖርባቸው ይገንዘቡ፤ ለተቋማዊ ህግና ደምብም ይገዙ፡፡ ፋኖ አሁን ባለበት ደረጃ እንደነዚህ ያሉ ልዩነቶችን በጥበብና በአስተዋይነት በሆደ ሰፊነትም ጭምር ማለፍ እንጂ ወደኃይል እርምጃ መሄድ ራሱን ይጎዳዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ ከአቢይ ልዋስና “መግደል መሸነፍ ነው” እያልኩ ነው፡፡

6. ፋኖ ጥይት ማባከን ያለበት ጠላቱ ላይ እንጂ በቅጣት መልክም እንበለው በብቀላ ወይም በሌላ መንገድ ወገኑ ላይ መሆን የለበትም፡፡ ግድያ እርኩሰት ነው፤ ግድያ ከሰው ማነስ ነው፤ ግድያ ከእንስሳዊነትም በታች ነው፡፡ ግድያ በምንም መልኩ አንድን ችግር ያባብስ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም፡፡ በጦር ግምባር የሚታየው መገዳደልም አማራጭ በመጥፋቱ እንጂ የሚመረጥ ሆኖ አይደለም፡፡ በግድያ የሚፈታ ችግር ያለ ይመስላል እንጂ እንደኔ በጭራሽ የለም፡ግድያ የጫጫን አእምሮ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ምሉዕ የምናደርግበት ሰይጣናዊ እርምጃ ነው፡፡ ስለዚህ ፋኖ የውስጥ ችግሩንና አለመግባባቱን በውይይትና በሽምግልና እንጂ በግንፍለተኝነት ወደጥይት ካመራ ትግሉ ከመጀመሩ ከሸፈ ማለት ነው - ለውስጣዊ ግድያዎች ነው እንዲህ እምቧዘራፍ የምለው፡፡

ኦህዲድን በህልምም በእውንም የምንገድለው እኮ እኛን ካልገደለ እንቅልፍ እንደማይወስደው ስለምናውቅ ነው፤ በስድስቱም አቅጣጫዎች ሌላ የተሻለ አማራጭ ብንፈልግ ምንም በማጣታችን ነው እነሱን ካልገደልን እኛ መኖር እንደማንችል አምነን ከኦሮሙማ ጋር የምንዋጋው፡፡ ስንሻው አምባቸውን መግደሉ ግን የቂልነት መጨረሻ ነው፡፡ ሥልጣን እንደሆነ ይደረስበታል፡፡ ዝናና ታዋቂነት እንደሆነ በራሱ ጊዜ እኛኑ ፈልጎ ይመጣል፡፡ ሳይቀመጡ እግርን መዘርጋትን ምን አመጣው? ለመፈንገል? ገና ምኑም ምኑም ሳይጨበጥ ለሥልጣን መራወጥና ለበላይነት መሟሟት በተለይ ሥልጡን ከሚባለው አማራ በጭራሽ አይጠበቅም፡፡ “ለዚህ ለዚህማ ምናለችኝ ጣቴ” ተብሎ እንዳይተረትብንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ከአይተ ሐጎስ አንዳችም ነገር ያልተማረው ኦቦ ገመቹ ምን እያደረገና በዚያም ምክንያት በጫካም በከተማም ምን እየደረሰበት እንደሆነ ምንም እንዳይገባው አቶ ደስታ ጆሮውን በጨርቅ ጠቅጥቆ ራሱን ካደነቆረ እግዜር ይሁነን ከማለት ውጪ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? ወንበሪቱ ደግሞ ፈርዶባት አንዲት ብቻ ናት፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠረው የፋኖ ሠራዊት አባላትና በሺዎች የሚቆጠሩ የፋኖ አመራሮችን ልትሸከም ቀርቶ ልታስጠጋቸው አትችልም፡፡ ከዚህ አኳያ ራሳችንን ለትዝብት መዳረግ የለብንም፡፡ አለበለዚያማ ከጮርቃው አቢይ በምን ተሻልን? እናም ፋኖዎች ጊዜ አታባክኑ፤ ራሳችሁን አስተካክሉና በቶሎ ኑልን፤ እኔም ፍቼ ወይም ሸኖ ድረስ መጥቼ በደስታ እቀበላችኋለሁ፡፡ ለዛሬ ይብቃኝ፡፡ እንደሁኔታዎች አስገዳጅነት መመለሴ ግን አይቀርም፡፡

Ethiopian Semay 

No comments: