Thursday, June 10, 2021

የትግራይ ህፃናት ለውጊያ የመመልመሉ ዓለም አቀፍ የወንጀል ድርጊት በህ.ወ.ሓ.ት. ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ ድረገጽ ዋና አዘጋጅ) 6/10/2021

 

 


 

የትግራይ ህፃናት ለውጊያ የመመልመሉ ዓለም አቀፍ  የወንጀል ድርጊት በህ.ወ.ሓ.ት.

ጌታቸው ረዳ

(ኢትዮ ሰማይ ድረገጽ ዋና አዘጋጅ)

6/10/2021


በፎቶግራፍ አዘጋጅቼ እንድትመለከትዋቸው የለጠፍኳቸው እነኚህ ፎቶዎች ወያነ ሥልጣኔን ተነጠቅኩ ብሎ በማኩረፉ አስቀድሞ ያቀደውን “ሃገረ ትግራይ” የምትባል አዲስ አገር እመሰርታለሁ በማለት ድሮ ሲያደርገው እንደነበረው ህጻናትን አስታጥቆ ወደ ጦርነት ያሳተፋቸው ታዳጊ ወጣቶች ናቸው።

                       “በነፃነት ስም በትጥቅ ግጭት የህፃናት ተሳትፎ” 

ብዙዎቻችሁ እንደ ወዳጄ ግደይ ባሕሪሹም ነፃነት የሚል ቃል ስትሰሙት ይዘገንናችሗል የሚል ግምት አለኝ። የ “ጠራናፊት ትግራይ” (ሗላ ኢዲዩ የተባለው) ድርጅት መሪ እና ዋና መስራች የነበረው ወዳጄ ግደይ እንዲህ ይላል፡ “ ነፃነት የሚሉት ቃል ትርጉሙን ከአገሬ ሁኔታ ጋር ባገናዝበው ከቶውኑም ላልሰማው ዘገነነኝ። “ነፃነት ፤ ነፃነት፤ አሥር ጊዜ ነፃነት” ፤ቃሉ ቢደጋገም አገሬ ውስጥ ተገልብጦ “ባርነት” ተሰራበት። ኣእምሮአቸው ተገልብጦ ያነ’ብ አንደሆነ አላውቅም እንጂ፤እንዴት ለነፃነት ትርጉም ከዓለም ሕዝብ የነፃነት ትርጉም ጋር ላለማመሳሰል፤ ሰልጥነውበት (ሰይጥነውበት) በሌላ ተርጉመውት እንደሆነ አይገባኝም።” ይላል ድሮ ጸረ ወያነ ሲወጋ የነበረ “የጦር መሪ” አርበኛው ተዋጊ ወዳጄ “ግደይ ባሕሪሹም”።

እውነት ነው። እኔ እራሴ ገና እጅግ ወጣት በነበርኩበት ወቅት 17 አመት አላረፍኩም፤ 27 አመት አላረፍኩም አሁንም 3 አመት አላረፍኩም። ነጻነት የሚባል አልተገኘም፡ አላየሁም።  እንደተመለከታችሁት ለ27 አሁን ደግሞ ለ3 አመት ጠቅላላ 30 አመት ሙሉ የሰማነው ቃላት ግደይ እንዳለው “ነፃነት ፤ ነፃነት አሥር ጊዜ ነፃነት” ፤የሚል ተደጋጋሚ ቃል ነው። በተግባር ላይ ሲውል ግን ነፃነት ሳይሆን “ጥቂቶች በነፃነት የሚንደላቀቁበት ፤ ለብዙሃኑ ግን ሲኦል የሆነበት ፤ በዓለም ውስጥ ያልታየ ፤ ያንድ አገር ልጆችን የሚያጋድል፤አገር የሚያፈረስ ሆኖ አግኝተነዋል።  ዛሬ ወየኔ በነፃነት ሲንደላቀቅባትና ሚሊዮኖች ሲገርፍና ሃብት ሲያግበሰብስበት የነበረበትን ሥልጣኑን ሲነጠቅ፤ ምስኪን የትግራይ ታዳጊ ወጣቶች ለእሳት እያጋፈጣቸው ዳግም ዓለም አቀፍ ወንጀል በመፈጸም ላይ ነው።

በ17 አመቱ የወያነ ትግራይ የትጥቅ ትግል የስንት ወጣት ህይወትና ኑሮ እንደበላ በቅርብ የምናውቀው እኛ የትግራይ ተወላጆች ነን። በተለያዩ የትግራይ አውራጃዎች ሲኖሩ የነበሩ የራሴ እጅግ በርካታ ዘመዶቼ ፤ለምሳሌ የኔ ታናሽ ወንድም ምናልባትም  በ 12 ወይንም በ 13 አመት ዕድሜው ወደ ወያኔ ተቀላቅሎ በጦርነት “እዛው አድጎ” በጥይት ተመትቶ ፤ ኑሮውና ትምህርቱ ተጓጉሎ፤ ወያኔ ሥልጣኑን ከያዘ በሗላ ግን የት ወድቅህ ብሎ ዞር ብሎ ሳያየው፤ በዘመዶች እርዳታ ኑሮውን ሲገፋ፤ የወያኔ የመሪዎች ልጆች ግን በሃብት ተንበሽብሸውና ትምህርት ተምረው ፤ ግማሹ እውጭ አገር እየኖሩ የተደላደለ ህይወት በመኖር ላይ ይገኛሉ።

አሳዛኝ የሚያደርገውና እጅግ የሚያስቆጣኝ ነገር ቢኖር አንድ ነገር አለ።  የወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ህይወት ለጥቂቶች መሪዎችና ዘመዶቻቸው መጠቀሚያ እንዲሆኑ “ግፋ በለው” እያሉ እውጭ አገር ሲኖሩ የነበሩ የ17 አመት “የማሌሊት አገልጋዮች”፤ ዛሬም ከዚያ ማፈሪያ ድርጊታቸው ሳይታቀቡ፤ ያንን እየደገሙ ያሉ ከጦርነቱ ርቀው እሳት የሚጭሩ የትግራይ ምሁራን እና ጀሌዎቻቸው ለትግራይ ታዳጊ ህጻናት ሞትና ስደት የታሪክ ተጠያቂ ወንጀለኞች መሆናቸው አንባቢዎች እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ።  

እነዚህ ህፃናት ባየሁ ቁጥር የወንድሜን ትዝታ ዓይኔ ላይ ሲደቀንብኝ እያዘንኩ ዛሬም እንደ ወንድሜ የመሳሰሉ ታዳጊ ወጣት ህፃናት ከትምህርት ርቀው “አካለ ስነኩላን ለመሆን” ወያኔ ወደ እሳት ሲማግዳቸው ማየት የተረዳሁት ነገር ቢኖር፤ ድሮ የፈፀመው ‘ህፃናትን ማስታጠቅ’ ወንጅሉ በዓለም አቀፍ ሕግ ሳይጠየቅበት በመኖሩ፤ ዛሬ ያንን የዓለም መንግሥታትና የሰው ልጆች መብት ተሟጋቾች ተቋማት ቸልተኝናትና “ተባባሪነት” ስላየ ወያኔ ይህንን ወንጀሉን እንደገና ደግሞታል።

የባሰ የሚያደርገው ደግሞ ፤ እንደ “አሶስየትድ ፕሬስ” እና ‘ሲ ኤን ኤን እና አልጀዚራ’ ወዘተ… የመሳሰሉ “በዜና ዘገባ” ስም ወደ ትግራይ በመሄድ ነገር እያባባሱ “በትጥቅ ግጭት የህፃናት ተሳትፎ”  በዓይናቸው እያዩና እየዘገቡትም ቢሆን “ለተባበሩት መንግሥታት ከማመልከትና ከመጠቆም ይልቅ” የሚያዩትን “ዓለም አቀፍ ጥሰት” ለደሞዛቸው ማስገኝያ ብቻ እስከጠቀማቸው ድረስ ጉዳያቸው አይደለም።

የነዚህ የዜና ማሰራጫ ባልደረቦች ችልተኝነታቸው ወደር የለውም። በ19ኛዎቹ “ላይቤሪያ አፍሪካ ውስጥ ያየነቻው እናቶች የሚደፍሩ የሽምቅ ተዋጊ ታጣቂ ህፃናት” የትግራይ ወጣት ህፃናትም “በከተማና በገጠር ጦርነቶች እየተሳተፉ በሽብር ተሰማርተው፤ ሰው እንዲያፍኑ፤አድርጉ ተብሎ ሲታዘዙ “ሰው እንዲገድሉ” ፤ “ማሕበረሰብ እንዲያስጨንቁ” ወንጀል እንዲፈጽሙ ተመልምለው በዓይናቸው እያዩ” ያንን ሕሊና ቢስነት በጊዜው እንዲቆም ተጽእኖ የማያደርጉ የዜና ማሰራጪያዎች በሰለማዊ ሰልፍ ተቃውሞ እንዲደርሳቸው ለዓለም ማሳወቅ ተገቢ ነው። የሚገርመው ነገር የህጽናቱን በጦርነት መሳተፍና በጥይት ተመትተው ሲያነክሱ እያዩ፤ ያንን ሳያሳስባቸው “ቸል” ብለውት “ስለ ጦርነቱ በማን አሸናፊነት ባጭር ጊዜ እንደሚያልቅ ሲተነብዩ መስማት” እጅግ ይገርማል። 

እነዚህ በፎቶግራፉና በቪዲዮው የምታይዋቸው ፈረንጆች “ቻይለድ ሶልጀር” ብለው የሚጠርዋቸው ወጣት ተዋጊዎች ሕሊናቸው ያላደገና የሳሳ ስለሆነ “አድርጉ የሚባሉትን” ብቻ ያደርጋሉ። ህጻንታና ታዳጊ ወጣች ለመታዘዝ ቀላል ስለሆኑ  በአክረራሪ ሃይሎች የሚፈጸሙ ግድያዎች ብዙዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት ለሽብር ድርጊት በማሰማራት፤ ሌሎችን በመግደል እስከ  ራስን የማጥፋትን ትልዕኮ ጨምሮ የሚደረግ የዘመናዊ ጦርነት ክስተት መጠቀሚያ ሆነዋል ፡፡ ታስታወሱ እንደሆነ ጦርነቱ ከመቀስቀሱ ጥቂት ቀን ሲቀረው ይመስለኛል፤ “ማይካድራ ከተማ” ውስጥ ‘ጦር ካምፕ’ አጠገብ  ”ቡና/ሻይ” በመሸጥ የምትተዳደር አንዲት ወጣት ልጃገረድ በቪዲዮ ያደረገቺው ቃለመጠይቅ ላይ  የታወቁ አንድ ጀኔራል (ስማቸወን ዘነጋሁኝ) ሻይ ውስጥ መርዝ ጨምራ አንደድትገድላቸው በወያኔዎች ተጠይቃ ሸሽታ አምቢ ብላ ድርጊቱን እንዳልፈጸመችና ምስጢሩ እንደከሸፈ ተናግራለች። ወጣቶች ያልበሰሉ ስለሆነ ወያኔዎች ለወንጀል ድርጊት ቅድሚያ የሚመርጥዋቸው “ማንጁስ” (ጩጬ) የሚልዋቸውን እነዚህን ህፃናትን ነው።

                ወያኔ ውስጥ ያየነው የ17 አመት ትግላቸው ያየነው ትዝብት

 ወያኔዎች በትግል ወቅት ለሐላፊዎች ብቻ የተመደቡ “ሴት” ልጆች ነበሩ። ብዙዎቹ እንደ ተዋጊዎች ፣ ምግብ ሰሪዎች ፣ አስተላላፊዎች ፣ ሰላዮች ወይም ለወሲባዊ ዓላማዎች ያገለግልዋቸው ነበር ፡፡ ሱዳን ውስጥ ብዙ ወጣት/ኮረዳ/ ሴቶች በሴተኛ አዳሪነት ተመልምለው የሚሰሩትን ገንዘብ ለድርጅቱ ገቢ ሲያደርጉ የነበሩ በርካታ ሴቶች በተባበሩት መንግሥታት “እስክሪነር ኦፊሰር” ሆኝየ ስሰራ  ይህንን ምስጢር የነገሩኝ ሴቶች ነበሩ።

ከዚያም አልፎ የሱዳን ወታደሮችን በማማለል፤ ወንጀል ፈጽመው የታሰሩ የወያኔ አባሎች ካሉ ከሱዳን ባለሥልጣናትና ወታደሮች ወሲብ በመፈጸም ያስፈትዋቸው ነበር። በስለላም የተሰማሩ ነበሩ። ሁሉም ወጣት ቆነጃጅቶች ናቸው።

ወዳጄ ግደይ እንዲህ ይላል፦

“የሱዳን ሕዝብ የዋህ ሕዝብ ነው። ብቻውን አይበላም። ነገር ግን የሱዳን ባለሥልጣኖችን ክፋት ያስተማርናቸው እኛው ነን። መጀመሪያ ሲያስተናግዱን እና ወደ መጨረሻ ሲሸኙን አንድ አይነት አልነበረም። ከማንዳን (ኮለኔል) እስሌማን እና ሻምበል ፈዱልን ባየንበት ዓይን፤ በሗላ “ኒመሪ” ሲገለበጥ አብረው የተገለበጡት  እነ ዛቢጥ (ሞታለቃ) አሲር እና ሰው (ፈላሻ) ሲሸጥ የተያዘው ኮለኔል ዳኒኤልን ማወዳደር አንችልም። እንደነ ወያነ ትግራይ ለነ ‘ዛቢጥ አሲር’ እና መሰሎቹ  ዓለም ነበሩ።  እኛ ለጉቦ የሚሆን ገንዘብ ቢያልቅብን በግመል መግረፊያ አለንጋ ጀርባችን እንደ ገጣባ አህያ እስኪላጥ ድረስ ነበር የሚገሸልጡን። ለነ ዛቢጥና መሰሎቹ ግን ወያኔዎች ገንዘብ ቀርቶ የልጃገረድ (ኮረዳ) ጉቦ በማቀበል የሰው ልጅ በስደት የቁም ስቃይ እንዲያልፍ አደረጉት። በማለት ወያኔዎች ለፖለቲካ መጠቀሚያቸው በማድረግ ኮረዳ ልጃገረዶች የሱዳኖች የወሲብ ማርኪያ አንዳደረጉዋቸው ሱዳን ውስጥ የነበረን ሰዎች ትውስታውን ያስታውሳል።

 

 ወያኔ ከመመስረቱ በፊት ሱዳን አገር ሲኖር የነበረ መኮነን በተባለ የሱዳን ቋንቋ አጣርቶ የሚናገር እኔንም ጭምር “ሱዳን ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት ሊያደረጉ ከመጡት ከአይሁዲ ሰላዮች አንዱ ነው'' ብሎ ያሳሰረኝ” የወያኔ ቀንደኛ አባል  በእነ መኮነን አገናኝነትና ጉቦ ሰጪነት “በአንቼ ጠርሙስ አረቄ” ጉቦ ናላው የዞረው "ዛቢጥ  (መቶ አለቃ) አሲር" ወዳጄ ግደይ በሕሪሹም ከላይ እንደገለጸው  ብዙ ሰው ገረፈ፤ በወያኔዎች አዘጋጂነት ብዙ ሴት የደፈረና የወያኔ ተቃዋሚዎችን አስሮ ያንገላታና ያሳፈነ፤ በመጨረሻ እርሱም ቀኑ ደረሰና ፕሬዚዳንት ኒሜሪ ሲገለበጥ አብሮ ተገለብጦ “እባካችሁ ደብቁኝ” እያለ ኢትዮጵያዊያንን ሲማጸን ተሰማ።

 ዛሬ ወያኔዎችም የነ "ዛብጥ አሲር" ዕጣ እነሱም በተራቸው ደርሷቸው ሲገርፉ የነበሩ ወያኔ ያሰማራቸው ግበረሰዶማዊያንና ገራፊ ነብሰገዳይ የነበሩ ወንጀለኞች ወደ ትግራይ ጫካ በመሸሽ ገበሬውን ደብቁን እያሉ "የሽምቅ ተዋጊ ጥገኝነት" ጠይቀው ወጣቱ እንዲከላከልላቸው እያደረጉ ነው።

ያ እንዳይበቃ ወያኔዎች ድሮ ሲፈፅሙት የነበረው በዓለም አቀፍ የተከለከለውን ወጣቶችን በጦርነት ውስጥ የማሳተፍ ወንጀላቸው ዛሬም እነሆ ለሁለተኛ ጊዜ ሕግ በመጣስ አገር በመገንጠል ኢትዮጵያን የተማረ ወጣት ለማሳጣት የወጣቶች መጻኢ ዕድል እንዲበላሽ እያደረጉ ነው።

“Children, Not Soldiers” “ሕፃናት እንጂ ወታደሮች አይደሉም!!!”

በመጨረሻም  “Children, Not Soldiers” “ሕፃናት እንጂ ወታደሮች አይደሉም” የሚል በ2014 ዓ.ም የነበረው በደቡብ ሱዳን፤ በኮንጎ፤በቻድ፤ በየመን፤አፍጋኒስታን፤ በኒየማር እና በሶማለያ ….. ወዘተ…. የተካሄደው በየ አገራቱ የተካሄዱት ዓለም አቀፍ ዘመቻ ዛሬ በድጋሚ “ትግራይ ውስጥ” እንዲካሄድ አስፈላጊ ነው የሚል ሃሳብ ስላለኝ፤  በወያኔዎች የታጠቁ የሽምቅ ተዋጊ ታዳጊ የትግራይ ወጣቶች በተባበሩት መንግሥታት “በዩኔስኮ” ጥረት በኩል ከጦርነቱ ተስበው እንዲወጡ ለማድረግ የተማራችሁ ክፍሎች እና የሕግ ባለሞያዎች ይህ ሃሳብ እንድትጋሩኝ አሳስባለሁ።

                                                       


ጽሑፉን “ሼር” በማድረግ በመቀባበል ለብዙ አንባቢዎችና ምሁራን እንዲደርስ የበኩላችሁ  ሃገራዊ ሃላፊነታችሁ “ሼር” በማድረግ ተወጡ።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ (Ethio Semay)

 

No comments: