ሞት የነጠቀን የሊቃውንት ሁሉ ሊቅ ጌታቸው ኃይሌ
ከጌታቸው ረዳ
ሳንሆዘ ካሊፎረኒያ
Ethiopian Semay
6/13/2021
በፈረንጆች ዘመን በዲሰምበር
10/2021 የፕፌሰር ጌታቸው ኃይሌን ከዚህ ዓለም መሰናበት ዜና የሰማሁት በፌስቡክ
ውስጥ በፎቶግራፍ የተሸኘች አጭር ጽሑፍ ነበረች፤ “መልካም ዕረፍት” የምትል። ልቤ በማዘኑ ፌስቡኬን ሳልዘጋ ኮምፕዩተሬን ዘጋሁት
እና ለደቂቃዎች በዝምታ ተዋጥኩኝ።
ክቡር ፕሮፌሰር ሲጠሩኝ “ሬር በርድ/ Rare Bird/ (ብርቅዬ ወፍ) ብለው ነበር የሚጠሩኝ። በፖለቲካ ትግል ዘመኔ ከተዋወቅኳቸው ታላላቅ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች መካካል መምህሬና ወዳጄ ዶ/ር አለሜ እሸቴ (ነብስ ይማር) አሁንም በቅርብ የማነጋግራቸው ወዳጆቼ ወዳጄ ግርማ በቀለ፤ ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ (አምስተርዳም ኗሪ የሕክምና ዶ/ር እና ሳይኪያትሪሰት) እንዲሁም ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድሃንየ (ኤርትራዊ ብረይመን ዩኒቨርሲቲ ጀርመን ፕሮፌሰር) የፖለቲካ መድረክ ካስተዋወቀኝ በርካታ ምሁራን መካካል ናቸው።
ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ጋር ተከታታይ ግንኙነት እናደርግ ነበር። ግራ የሚያጋቡ
የግዕዝ ቃላቶች ትርጉም ስፈልግ እሳቸውን እጠይቃለሁ። “ግዕዝ በቀላሉ” የሚል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ኋላም አሻሽለው ያሳተሙት
መጽሐፍ ልከውልኝ አንብበውና እፈትንሃለሁ ብለውኝ ለማጥናት ጀምሬ ሳይፈትኑኝ ተሰናበቱኝ። እጅግ አዘንኩ።
ለመጨረሻ የተለዋወጥነው አሳዛኙ የኢመይል መልዕክት በ Dec 17, 2020 6:16 am የጻፉልኝ ነበር። እንዲህ ይላል።
Greetings
Thu, Dec 17, 2020 6:16
am
Getatchew Haile (email address deleted for
privacy)
To Getachew
Reda
ሰላም ውድ አቶ ጌታቸው:
እንደምን አለህ? እኔ ከአልጋ መውጣት የማይችል ሕመምተኛ ሆኛለሁ: ግን የሚምታታውን
የእርስ በርስ ግጭት ዜና በተቻለ መጠን እከታተላለሁ: አንተንም አስባለሁ: ስሜትህና ግምገማህ እንዴት ነው? መጨረሻው ምን ይሆን
ይመስልሃል?
ጌታቸው ኃይሌ
Sent from my
iPhone”
የሚል ነበር። እኔም ልቤ በሃዘን
በተሰበረ መልስ “ ልቤ ብርቱ ሓዘን ተሰምቶታል ፤ ህመምዎ ምንድነው?” የሚል ጥያቄ እና ስለ ወያኔዎች ወደ ጫካ መኮብለል ያለኝን
አስተያየት ለማወቅ ስለጠየቁኝ የኔ መልስ ሰጥቻቸው፤ከዚያ ወዲያ ድጋሚ ብጠይቅ መልስ ላገኝ አልቻልኩም። እንደሚሰናበቱን ነብሴ ይነግረኝ
ስለነበር እጅግ ነበር ስሰጋ የነበረው። የማይቀረው “ሞት” ከሚወድዋትና ከታቀፉባት ከኢትዮጵያ ጉያ ነጠቃቸው።
እሳቸው “ደቂቀ እስጢፋኖስ”
የሚል መጽሐፋቸው በ1996 ሲጽፉ እኔ ደግሞ “ደቂቀ ተወልደመድኅን” የሚል መጽሐፍ በ2005 ዓ.ም ስጽፍ
ከመታተሙ በፊት አስተያየት እንዲሰጡኝ ቅጁን ልኬላቸው የተሰማቸው አድናቆት ሰፊ አስተያያት የጻፉትን ከመጽሐፉ ውስጥ እንዲታተም
አድርጌአለሁ።
መጽሐፉ በበርካታ ኢትዮጵያዊያን
የፕሮተስታንት ተከታዮች የተነበበ ነው። መጽሐፉ ስጽፍ እኔ የተዋህዶ አማኝ ብሆንም ወያኔዎች ስለ ደቂቀ እስጢፋኖስ የትግራይ ምሁራን
በመጽሐፍ መልክና በፕሮፓጋንዳም በርካታ ውሸት ስላሰራጩ እኔም አማራውን መውቀስ ትታችሁ የራሳችንን ጉድፍ ቅድሚያ እንመልከት በሚል፤
በአጼ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን የነበሩ የጉንዳጉንዲ/ገራዓልታ የትግራይ ተወላጅ
አባ እስጢፋኖስ የተባሉ “ልጆቻችን መጥፎ ስብከት እየሰበከ ወደ እርሱ እንዲሰልሉ ፀረ እምነታችን የሆነ
ትምህርት እያስተማራቸው ነው” በሚል ልጆቻቸው እንዲያስተምሩላቸው የላኩ ወላጆች የተፈጠረው ከፍተኛ አለመግባባት (ጸብ) በመጠናከሩ
በኢኚህ መነኩሴና የትግራይ ሰዎች የተፈጠረ ፀብ መፍትሔ ፍለጋ ለዳኝነት ከትግራይ ወደ ሸዋ ደብረብርሃን ከተማ ወደ ንጉሥ ዘርአ
ያዕቆብ ሄደው ንጉሡ እራሱ ያስቻለው ችሎት በተሰማው ክርክርና አለመግባባት ምክንያት “ለማርያምም ሆነ ለንጉሡ” አንሰግድም በሚል
ጸንተው ስለተከራከሩ፤ በእሳቸው እና በተከታዮቻቸው የተወሰደው “ጨካኝ ቅጣት” ተላለፈ።
አባ እስቲፋኖስ እና ተከታዮቻቸው “ትግሬዎች ስለሆኑ” የሸዋው አማራው ዘርአ
ዕቆብ የጀመረው “ጸረ ትግሬ” አስተዳዳር ይኼው እስከዛሬ ድረስ አለ ፤እያሉ የወይን ጋዜጠኛ የነበረው ሙሉጌታ ደባልቀው እና ”ምንኩስና
በኢትዮጵያ ዛሬ እና ትላንት” ደራሲ ካሕሳይ ገ/እግዚአብሔር (ገጽ 17-75) የመሳሰሉ የትግራይ ጸሐፍት “በደቂቀ እስጢፋኖስ” የተላለፈው ቅጣት ሸዋዎች
“ትግሬን ስለሚጠሉ ነው” እያሉ “የሃሰት ውንጀላ በመፈልሰፍ” መጽሐፍት
ጽፈው አዲሱን ትውልድ ስለመረዙት እኔም የትግራይ ተወላጆች የተለየ እምነት ስለተከተሉት የትግራይ ሰዎች፤ በራሳቸው በትግራይ ሕዝብ
እና አገረ ገዢዎች ፍርደገምድል ምክንያት ከ1910 እስከ 1954 ዓ.ም የደረሰባቸው የሃይማኖት ጥሰት፤ መገረፍ እና መሰደድ መጨረሻም
ከትግራይ የተባረሩበትን የትግራይ ፍርድ በንጽጽር የጻፍኩት መጽፍ ላይ ፕሮፌሰር ከፍተኛ አድናቆት የጻፉልኝ ከመጽሐፉ ቀንጭቤ ላስነብባችሁና
ክቡር ፕሮፌሰር የማይረሳውን ዕውቀታቸውና ውለታቸውን በዚህ ልደምድም።።
ቅድሚያ ግን እግረመንገዳችሁ
ሃለቃ ተወልደመድህን ገብሩና ጎበዜ ጎሹን ላስተዋውቃችሁ።
ሃለቃ ተወልደመድህን ገብሩ (ዓድዋ) ጎበዜ ጎሹ (አክሱም- ናዕዴር) ሁለቱም
የታወቁ የተዋህዶ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ቀሳውስት የነበሩ በኋላ በ1900 አካባቢ ሕክምና ፍለጋ ወደ ኤርትራ ከሄዱ በኋላ ሁለቱም
ባገኙት የሕክምና ክትትልና ጠቀሜታ ተንተርሶ ሚሲዮናዊያኖቹ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ዕምነት እና ካላቸው የራሳቸው እምነት ጋር እያመዛዘኑ
ሲታከሙ ቆይተው በስብከቱ ስለተማረኩ ሁለቱም ሃይማኖታቸውን ለውጠው ወደ ዓድዋ እና አክሱም ተመልሰው ያደረጉት አስገራሚ ሕዝባዊ
የሃይማኖት ክርክር የሚገርም ነበር። በዚህ ወቅት ማለትም በ1909
የትግርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጽፈው ከ1910 እስከ 1954 ትግራይ ውስጥ በሕዝቡና ዓድዋ ውስጥ በነበሩ የደጃዝማች ዘውዴ
ገብረስላሴ ባርያጋብር ወንድም በሆኑት ደጃዝማች ተ/ሃይማኖት ገብረስላሴ ባርያጋብር (የደጃች ገብረስላሴ ባርያጋብር ልጅ) የደረሰባቸው
የሃይማኖት መድልዎ “ግፍ” ያሳለፉት አሰቃቂ ግርፍትና እስራት እንዲሁም ከትግራይ የመባረር ዕጣ ደርሶባቸው አዲስ አበባ ድረስ ሄደው
(በንግሥት ዘውዲቱና አጼ ሃይለስላሴ ወቅት አቤቱታቸውን አቅርበው) ትግራይ ሕዝብ እና በትግራይ ገዢዎች ያላገኙትን ድጋፍና ፍትሕ ሸዋ ሄደው ፍትህ
አግኝተዋል።
“ደቂቀ ተወልደመድኅን- ወያኔዎች
የደበቁት የፕሮተስታንቶች የስቃይ ታሪክ በትግራይ” የሚል መጽሐፍ በፈረንጆች 2005 ዓ.ም ስጽፍ በመጽሐፌ ላይ አስተያየት እንዲሰጡበት
የጠየቅኩቸው ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እንዲህ ብለው ያሰፈሩት አስተያየት የማልረሳው ስለሆነ እነሆ ከመጽሐፌ ቀንጭቤ ላስነብባችሁ፡
እንዲህ ይላል፤
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
ኮሌጅቪል፥ ሚኒሶታ፥ ሚያዝያ
27 ቀን 2003 ዓ.ዓ.ም.
ለውድ አቶ ጌታቸው ረዳ
መምህር ገብረ ኪዳን ደስታ
"የትግራይ ሕዝብና የትምክሕተኞች ሴራ" በሚለው መጽሐፉ ያጣመመውን የኢትዮጵያ ታሪክ ያስተካከልክበትን፥
"ይድረስ ለጎጠኛው መምህር" የሚል ርእስ የሰጠኸውን መጽሐፍ ሳደንቅ፥አሁን ደግሞ አቶ ሙሉጌታ ደባልቀው
"የህ.ወ.ሓ.ት. የትጥቅ ትግል" በሚል ርእስ ያሳተመውን
ሌላ የፕሮፓጋንዳ መጽሐፍ በመቋቋም ላይ መሆንክን ስትነግረኝ ስላንተ ያለኝ አድናቆት መገረምን እስከተለልኝ። ድረ-ግጾችን ስጎበኝ
ድርሰቶችህን የማላገኝበት ጊዜ የተወሰነ ነው። በዚያ ላይ፥ በጎበኙት ቊጥር አዲስ ነገር፥ አዲስ ዕውቀት-የማይታጣበትን
www.ethiopiansemay.blogspot.com ታካሂዳለኽ።"ይድረስ ለጎጠኛው መምህር" ያልከውን መጽሐፍ ሳነብ፥
የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነትና ገናና ታሪክ ለማስከበር ይህን ያህል የምትሠዋውን ጊዜ የምታገኘው ሰውነትክን እንቅልፍ እየነፈግኸው መሆን አለበት። መረጃዎች እየሰበሰቡና
ሦስት ቋንቋዎች (አማርኛ ትግርኛ እንግሊዝኛ) እያፈራረቁ መጻፍ ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ የማይገምት ያለ አይመስለኝም። ትውልዶች
አልፈው ትውልዶች ሲተኩና ለሀገራችን በቀውጢ ቀኗ እነማን ደረሱላት ብለው ሲጠይቁ "ከአክሱም ጌታቸው ረዳ" የሚል
ማንም ሊፍቀው የማይችል መልስ ያገኛሉ።
የአቶ ሙሉጌታ መጽሐፍ ከመምህር
ገብረ ኪዳን መጽሐፍ ጋር ሲነፃጸር የሁለቱ ዓላማና የሚተቿቸው አርእስት አንድ ዓይነት ቢሆኑም አንዳንድ እውነት ነገር ስላለበት
አንባቢን የማጭበርበር ችሎታ አለው። በፕሮፓጋንዳ ረገድ ሲታይ ጎጂነቱም በዚያው መጠን ለመሆን ስለሚችል፥ "የትግራይ ሕዝብና
የትምክሕተኞች ሴራ" ደራሲን በጫረው እሳት ልብሱን አቃጥለህ በአደባባይ ራቁቱን እንዳቆምከው፥በ"የህ.ወ.ሓ.ት.
የትጥቅ ትግል" ደራሲ ላይም ተመሳሳይ አደጋ ስትጥልበት ለማየት
ቸኩያለሁ።
አቶ ሙሉጌታ ስለ ደቂቀ እስጢፋኖስ
የዘገበውን ስሕተት እንዳርምለት ያቀረብክልኝን ጥያቄ በደስታ በመቀበል፥
የሚያስፈልጉትን አንቀጾች ከዚህ በታች አቀርባለሁ። ወደዚያ ከመሄዴ በፊት ግን መምህር ገብረ ኪዳንን በአደባባይ እርቃነ-ሥጋውን
አቆምከው ላልኩት አንድ ሁለት ምሳሌ ልጥቀስ። የመጀመሪያው፥ ጎሰኞቹ በቀላጤያቸው በመምህር ገብረ ኪዳን ብዕር ከትግራይ ሕዝብ በቀር
የኢትዮጵያ ሕዝብ፥ በተለየ አምሐራው፥ ፈሪ ነው፣ ጠላት ሲመጣ ይሸሻል ለሚሉት ሽለላ ማስተባበያ ገጽ 92-3 ላይ የሰጠኸው የብፁዕ
አቡነ ጴጥሮስ የሰማዕትነት ታሪክ ነው።
[ጳጳሱን፣] "መላው ያገሪቱ ሕዝበ ክርስቲያን [ለኢጣሊያ አገዛዝ]
እንዲሰግድ . . .አድርግ የፈለግከውን እንፈጽማለን" ሲሏቸው፣ "አገሬ እና ሕዝቤ ለሰላቶ እንዲሰግድ አልፈቅድም"
ስላሉ ግምባራቸውን ለፋሽስት ጥይት ሰጥተው የክብር መሥዋዕትና የሃይማኖት ስነምግባር ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ይህ ታሪክ በወያኔ
ጸሐፊው በገብረኪዳን አንዲት ቅጠል ገጽ አልተቸረውም። ጳጳሱ የትግራይ ሰው [ስላልሆኑ] ቢሆኑ ኖሮ እነገብረኪዳን ደስታ ስለሳቸው
ታሪክ ብቻ ብዙ መጻሕፍትና ፕሮግራሞች በሰሩ ነበር። ሆኖም ዘረኝነት እጅግ ስለሚጫናቸው የአማራውን ኅብረተሰብ ጉድለት እና ደካማ
ጎኑን ብቻ እየጫሩ ጎሳን ማናናቅ እና ማበላለጥ በዘረኛነት ቅስቀሳ መጠመድ ሞያቸው አድርገውታል።”
ሁለተኛው የትግራይ ሕዝብ እንደ
አማሮች ከጠላት ጋር አይተባበርም፤ አማሮች ከሓዲዎች ናቸው የሚሉትን የሞኞችን ሞኝነት ለማጋለጥ ገጽ 91-92 ላይ የሰጠኸን የቅድስት
አክሱም ጽዮን ካህናት ጀኔራል ግራዚያኒን እንዴት እንደተቀበሉት የታሪክ ምዝገባ ነው።
ጣሊያን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አገራችን በወራሪነት በመጣችበት ወቅት (በ1928
ዓ.ዓ.ም.) የአክሱም ቀሳውስትና ዲያቆናት ጽላተ ሙሴንና የጥንት ነገሥታትን ዘውዶች ተሸክመው በወረብ በሽብሸባ እየዘመሩ . .
"ጀኔራል ግራዚያኒን
እናክብር" እያሉ ከቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ከመቅደሱ ሰገነት ጀምሮ እስከ ደጀ-ሰላሙ (አፄ ዮሐንስ ከግብፅ የማረኩት መድፍ
የተቀመጠበት በር) ድረስ እስኪወጣ "ንሴብሖ" እያሉ ተቀብለው ሸኝተውታል። ይሄንን መረጃ ለማየት የሚፈልግ
"You Tube" በተባለው የኦድዮ--ቪድዮ (መልእክተ-ስእል) ህዋ ሰሌዳ (ኢንተርኔት) መድረክ ገብቶ
Graziani-Italians in Axum Ethiopia ወይንም(http://www.youtube.com/watch?v=_20tOa8C6VU)
ብሎ በመጻፍ ማየት ይችላል። . . . እንዲህ ያለውን ድርጊት የአንኮበር ቀሳውስት ቢያደርጉት ኖሮ ወያኔዎች ስለ ሁኔታው አራግበው
አይጠግቡም ነበር።”
ታሪኩን ከታሪክ መጻሕፍት አንብቤዋለሁ፤
በ"You Tube" መኖሩን ግን አላወኩም ነበር። ካህናቱ "ንሴብሖ" ብለው የዘመሩት የእስራኤል
ልጆች ፈርዖንና ሠራዊቱ ቀይ ባሕር ሲሰጥሙ ለአምላካቸው ምስጋና ሲያቀርቡ የዘመሩት መዝሙር ነው። የአክሱም ካህናት ይኽንን መዝሙር
የዘመሩት፥ "የኢትዮጵያን ንጉሥና ሠራዊቱን ደምስሰህ እንኳን የኢጣሊያን አገዛዝ አመጣህልን" ሲሉ ነው። የጠቀስኩት
ሌሎች ካህናት አያደርጉትም ብዬ የአክሱምን ካህናት ለማሳጣት ሳይሆን ድርጊቱን "የአንኮበር ቀሳውስት ቢያደርጉት ኖሮ ወያኔዎች
ስለ ሁኔታው አራግበው አይጠግቡም ነበር" ያልከው ከልቤ ስለገባ ነው። "ይድረስ ለጎጠኛው መምህር" ከዳር
እስከ ዳር በተመሳሳይ ማስረጃና ትንተና የተሞላ ነው። ጎሰኞቹ ኤርትራን ለማስገንጠል የፈጸሙትን ብሔራዊ ወንጀል እንደመዘገብከው
ለማንበብ የሚፈልግ "ጽናቱን ስጠኝ" ብሎ ጸልዮ መጀመር ይኖርበታል።
የአቶ፡ሙሉጌታ ደባልቀውጋላህቲ
ሠጊ ("የህ.ወ.ሓ.ት. የትጥቅ ትግል" 1967-83 ዓ.ም.) አንድ በፕሮፓጋንዳ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ
ጸሐፊ ያቀነባበረው መጽሐፍ ነው። ለምሳሌ በአማርኛ በአዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ ስለ አቢሲኒያ ይጽፋል። አቢሲኒያ የሚባል ቃል ወይም
ስም በአማርኛ የለም። ታዲያ በአማርኛ በሚጻፍ መጽሐፍ ውስጥ ለምን ገባ? የሚከነክን ጥያቄ ነው። አቢሲኒያ ፈረንጆች እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ ድረስ ስለ ሀገራችን ሲጽፉ
ኢትዮጵያን የሚጠሩበት ስም ነው። ዓረቦች "ሐበሻ" የሚሉት ስም ነው። እኛም "አበሻ" እንላለን፤
ግን "አበሻ" የምንለው አገሪቷን ኢትዮጵያን ሳይሆን፥
ሕዝቧን ነው። ዛሬ ዛሬ እየቀረ ሄደ እንጂ፥ "አበሻ ነህ?"፤ "አበሻ ነሽ?" ብሎ መጠየቅ
የተለመደ ነበር። ዛሬም ቢሆን "ያበሻ ልብስ"፤ "ያበሻ ምግብ" እንላለን። ግን "አቢሲኒያ ነን" አንልም።
አቶ ሙሉጌታ ደባልቀው አቢሲኒያ የሚለውን ስም ያለምክንያት አልተጠቀመበትም። ከኢትዮጵያ መገንጠል
የሚፈልጉ ሰዎችን ለመርዳት ነው። ተገንጣዮቹ የመጀመሪያው እርምጃቸው ሊገነጥሉት በሚፈልጉት ቦታ ላይ የሰፈሩትን ሰዎች
"አበሾች አይደላችሁም" ማለት ነው። ግን "አበሾች አይደላችሁም" ከማለት፣ "የአቢሲኒያ
ሰዎች አይደላችሁም" ማለቱ ለዓላማቸው ያመቻል። ለምሳሌ የኦሮሞ ነፃነት ግምባር (የኦነግ) ካድሬዎች የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው
የሐበሻ ሕዝብ የተለየ መሆኑን ለማሳየት "አበሻ" በማለት ፈንታ አቢሲኒያ ነው የሚሉት። የዚህ ሁሉ ጠንቅ ምዕራባውያን ደራሲዎች ስለ ኢትዮጵያ ሲጽፉ
ጥንቃቄ ማጓደላቸው ነው። ሐበሻ ወይም Abyssinia የኢትዮጵያውያን ሁሉ መጠሪያ ሆኖ ሳለ ምዕራባውያን ደራሲዎች ለትግሬዎቹና ለአማሮቹ ብቻ ይሰጡታል።
ሌሎቹን ከዚህ ስም ያሶጧቸዋል።
እንዲያውም፥ ከዚህ አልፈው ይሄዳሉ፤ በተለየ ኦሮሞዎቹንና አገዎቹን
ቋንቋቸው አማርኛ ወይም ትግርኛ ስላልሆነ በዘር ሌላ ሕዝብ ያደርጓቸዋል። አብዛኛው የትግሬ ሕዝብ ምንጩ አገው፤ አብዛኛው የአማራ
ሕዝብ ምንጩ አገውና ኦሮሞ መሆኑን፤ እንደ ግዕዝ ሥነ ጽሑፍ፥ እንደ
ሥዕል፥ ያለው The Abyssinian Civilization የሚሉት
ከሞላ ጎደል የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዋፅኦ መሆኑን እየዘነጉ፥
Abyssinians የሚሏቸው የትግሬዎችና የአማሮች ብቻ
ቅርስ ያደርጉታል። የፈረንጅ ቃል ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የሚወዳደር የሚመስላቸው ሰዎች እነሱን እየጠቀሱ ራሳቸውን
The Abyssinian Civilization ለሚሉት ለአባቶቻቸው ሥልጣኔ ባዳ ያደርጋሉ።
አቶ ሙሉጌታ ደባልቀው ስለ
"አቢሲኒያ" ሲጽፍ "አቢሲኒያን" የማይላቸውን ኢትዮጵያውያን ከአማሮች ብቻ ሳይሆን ከትግሬዎችም
እንደሚያለያያቸው እያወቀ ስለሆነ፥ ይህ ሰው "አክሱም፥ ላሊበላ፥
ጎንደር ምናቸው ነው” ያለው አቶ መለስ ዜናዊ በአንድነታችን ላይ ዘመቻቸውን ማቀነባበራቸው ግልጽ ነው። ይህ ሰው "የአክሱም
ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው” ያለው አቶ መለስ ዜናዊ በአንድነታችን
ላይ ዘመቻቸውን ማቀነባበራቸው ግልጽ ነው።
አጅሬ "የህ.ወ.ሓ.ት.
የትጥቅ ትግል" ደራሲና ነጭ አምላኪዎች ይህ ችግር በማህላችን እንዳሉ ያውቃል። ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው
ባለው ችግር ገብቶ ሕዝብ ለማበጣበጥ በአማርኛ ሲጻፍ ተብሎ የማይታወቀውን አቢሲኒያ የሚለውን ስም ይጠቀምበታል፤ የረቀቀ የፕሮፓጋንዳ
እርምጃ ነው። በዚያው አያይዞ አጼ ምኒልክ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ያደረጉትን ዘመቻ ጭፍጨፋ ይለዋል። ረቂቁ ተንኮል የተዘመተባቸውን
የልጅ ልጆች ለማስቆጨትና የመገንጠልን ሐሳብ እንዲገፉበት ለማድረግ ነው።
"ነጭ አምላኪዎች"
የሚባለው አነጋገር ሐሜት እንዳይደለ በአንድ ምሳሌ ላሳይ፤ አባ ባሕርይ የሚባሉ ሊቅ ስለ ኦሮሞዎች ያደረጉትን ጥናት "ዜናሁ
ለጋላ" የሚል ስም ሰጥተውት ሲኖር፥ ብዙ ፈረንጆች አንዳንዶቹ ትርጒሙን፥ አንዳንዶቹ እናቱን ከነትርጒሙ አሳትመውታል። ያንን
በኋላ የመጡ የኦሮሞን ታሪክ ጸሐፊዎች (ኦሮሞዎቹ ሳይቀሩ) በአድናቆት ሲጠቅሱት ኖረው እኔ እናቱን ከአማርኛና ከእንግሊዝኛ ትርጒሜ
ጋር ባሳትመው ዓይናቸው ቀላ፤ የማይታመን ተቃውሞ አነሡ። መጽሐፉ ከሰው እጅ እንዳይገባ የተቻላቸውን ያህል ጣሩ፤ እኔንም ለመግደል
እንዳቀዱ ነገሩኝ። ጭፍጨፋ የሚባለውም በመሠረቱ ያመነውንና የተማረከውን በግፍ ሲገድሉትና ሲያሠቃዩት እንጂ፥ በጦርነት ጊዜ ሁለቱ
ወገኖች የሚገዳደሉት ቢበዛ "ተጨፋጨፉ" ይባላል እንጂ፥ "ጭፍጨፋ" አይባልም። በአጼ ምኒልክ ዘመቻዎች
ያመነውና የተማረከው አንዳች ጉዳት እንደደረሰበት የሚያስረዳ ሰነድ የለም። ደራሲው ስለ እንዲህ ያለ ጭካኔና ሰላማዊ ሕዝብ ጭፍጨፋ ለማስነበብ ከፈለገ ስለ ጨካኝ ነገሥታት ዘመቻ ይጻፍልን።
ጭፍጨፋ ማለት እሱና ግብር
አበሮቹም "ይድረስ ለጎጠኛው መምህር" በሚባለው መጽሐፍህ
ውስጥ ወደ አማርኛ ተርጒመህ ገጽ 313-363 የቀዳኸውን የአቶ ገዛኢ ረዳን ቃለ መጠይቅ ያጋለጠው ነው። የሰፈራቸው ሰዎች እነ
አቶ ገዛኢ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግምባር ሰዎችን ለምን "ከሲኦል ወደ መሬት የሰው ልጅ ለመከራ እንዲዳርጉ የወረዱ
አጋንንት" እንደሚሏቸው ቃለ መጠይቁ አሳይቶናል።
ጭፍጨፋ ማለት እነዚህ ጸሐፊዎችና
ግብር አበሮቻቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ እኩልነት ይሟሟቱ የነበሩትን የኢሕአፓን ልጆች አሲምባ ላይ ከተኙበት የፈጸሙባቸው ጭካኔ ነው።
በእጃቸው ላይ ምን ያህል ደም እንዳለ የማናውቅ መስሏቸው ወንጀላቸውን ለሌሎች ለመስጠት ወይም እናንተም እንደኛ ወንጀለኞች ናችሁ
ለማለት በወንጀል አድራጊነታቸው ላይ ለሌሎች ወንጀል ፈጣሪዎች ሆነዋል። “ግ.ሓ.ት (ግምባር ሓርነት ትግራይ) በተባለው ሌላው የትግራይ
ነፃ አውጪ ብሔረተኛ ቡድንም ላይም እርቅ እናድርግ ብለው ሌሊት ተኝተው እንዳለ የፈጸሙባቸው ጭካኔም የወያኔው ታጋይ የነበረው አቶ
አስገደ ገብረስላሴ “ጋህዲ” በተባለው መጽሐፉ አጋለተው ሰነድ ምስክር ነው።” (ከደራሲው የተጨመረ) ለማን፣ ማን እንዲያምናቸው
ይሆን እብለት የሚያዥጎደጉዱት? የሀፍረትና የይሉኝታ መንፈስ ሽው ብሎባቸው ቢሆን ኖሮ፥ እንኳን ታሪክ ሊጽፉ ሰው ቀና ብለውም አያዩም
ነበር። ያዳናቸው ይሉኝታ ቢስ መሆናቸው ነው። እድሜ ለይሉኝታ ቢስነት ይበሉ።
ደቂቀ እስጢፋኖስ፤
አሁን የተጣመመውን የደቂቀ
እስጢፋኖስን የሰማዕትነት ታሪክ እንዳስተካክል ወደጠየቅከኝ ወደ ዋናው ጥያቄህ ልምጣ።………… በማለት ሰፊ ማብራሪያ ጽፈዋል።
የፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ሕልፈተ
ሞት ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ጉዳት ነው።
ነብስ ይማር!!!!! ለቤተሰብ
መጽናናት ይስጥ!! እጅግ አዝኛለሁ!!
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ
No comments:
Post a Comment