Friday, May 22, 2026

አበቤች አደኔ አብይና ዝናሽ ሆይ እንደ ዛጉዌው መስራች እንደ ንጉሥ መራ እልፎችን እቤታችሁ ለማኖርና ለመቀለብ ፈቃደኞች ናችሁ? ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay 5/22/26

 

አበቤች አደኔ አብይና ዝናሽ ሆይ እንደ ዛጉዌው መስራች እንደ ንጉሥ መራ እልፎችን እቤታችሁ ለማኖርና ለመቀለብ  ፈቃደኞች ናችሁ?

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay

5/22/26

ዛሬ የምንመለክተው ጉዳይ “መጽዋች እና ተመጽዋች” በሕግ አውጥቶ ድሆችን እንደ ቆሻሻ እያየ ከጎዳና እየለቀመ እስር የሚያስገባ (social cleansing) አብይ አሕመድ እና የሱ ታማኝ የሆነቺው በሰው ሰራሽ ውበት የምትዋብ እና የሞዴል  ልዕቶች የማይለብሱዋሸው በውድ ልብሶችና ሽቶዎች የምትሽቀረቀረው የአዲስ አበባ ውቢትዋ አበቤች አደኔ ለድሃ ማሕበረሰብ ያላቸው ጥላቻን እንመለከታለን።

ምንም እንኳ አብይ አሕመድ ለመለመን ይተፈቀደለት ፥ ለማኝ እና ልመናም እንደሚሳካለት የልመና ባለሞያ መሆኑን ሳይሸማቀቅ ቢነግረንም ፤ በሚገርም ነገር ‘ልመና ለአብይ ሲፈቀድ  “አዱንያ አልሆን ብላቻቸው” የዕለት ጉርሻ አጥተው ለሚለምኑ እና ለሚመጸውቱ መጽዋቾች ግን አብረው እንደሚቀጡ አዲስ አዋጅ ተግባር ላይ እየዋለ እንደሆነ በዚህ በተለጠፈው የቪዲዮ እና የድምጽ ማስረጃ ማረጋገጥ ይቻላል ።

 ሳምንቱን አበቤች አደኔ በድሆች ሕይወት ስታሾፍ ሰምተናታል። በዚህ ቪዲዮም ታደምጠዋታላችሁ። በዚህ Ethio forum ዘገባ የሥርዓቱ ጨኻኝነተ እና ንቅዘት ባስገራሚ ማስረጃ ዘግቦ አሳይቶናል (ምስጋና ይግባው!) 

 የሃገራችን ሕዝብ እስላምም ክርስትያንም ይሁን ታዋቂ ሃይማኖቶችን የማይከተል በየዋህ ባሕሪ በመነሳሳት ይሁን የሃይማኖቱን ሕግጋቶች ተከተለው ለታረዙ ድሆች “ልብስ” ለተራቡ “ምግብ” የሚመጸውቱ መጽዋቾች እና ተመጽዋቾች ፣ (የኦነጉ መሪ ሌንጮ ለታ «የኦሮሞዎች መንግሥት) እያለ የሚጠራው «አብይ አሕመድ የሚመራው የኦሮሞዎች መንግሥት» በሕግ ይቀጣል። መጽዋቾች እና ተመጽዋቾችን ለመቅጣት ሰላዮችን መድቦ እየተከታተለ ፤ ከገንዘብ ቅጣት ጀምሮ ንግድ ቤቶችን እሰከማሸግ/ እሰከመዝጋት/ የሚደርስ ሕግ አጽድቆ እየቀጣቸው ይገኛል።

ይህም የነገረችን ለሥርዓቱ ከሚሸቅሉ ሎሌዎች አንድዋ ከላይ ከነ አበቤች አደኔ ፎቶ ጋር የምታይዋት «አለምፀሃይ ጳውሎስ” የተባለች “barbaric” የአዋጁ ምሕረት-የለሽነትና ጭካኔ  ታሪክ ይታዘበኛል ሳትል ፣ሳትሸማቀቅ “ጀርመኖች በ1933 ለድሆች እና ለቤት-አልባዎች ሲያደርጉት የነበረው ዓይነት እስራት፤ቅጣትና ንቀት በኩራት ነግራናለች።

የኦሮሙማው ቡድን  ወደ ሥልጣን ከመጣበት የመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ ውሸት እና መቀደድ የማንነቱ መገለጫ ባሕሪ እንደነበር በሂደት አይተናል። ልምድ አደረጉትና ቅጥ ያጡ ዋሾች እና ከራባት ያጠለቁ ጤናማ የሚመስሉ የአእመሮ በሽተኞችን ከየቦታው ለቃቅሞ እየሾመ ሲዋሹለት ምቾት ሰጣቸዋል። እንዲህ ያሉ ሰዎች የስነ ልቦና ሊቃውንት Mythomania ይሏቸዋል።

ዛሬ የምንመለከተው የአብይ አሕመድ የወንጀል ተጋሪዋ  አበቤች አደኔን ነው።የሕከምና ባለሞያ ዶክተሮች በኑሮ ውድነት በደሞዝ ማነስ የተመጣጠነ ምግብ ቀርቶ በቀን አንድ ቀን ብቻ እየበላን በርሃብ ተሰቃይተናል እያሉ ሲጮሁ አበቤች አደኔ ደግሞ ድሆችን ወደ መመገቢያ ማእክላት ሂዳችሁ “እጃችሁን ታጥባችሁ” የተመጣጠነ ምግብ ተመገቡ እያለች የምትቀልደውን ቀልድዋን አይተን ፣ አብይን ዳብሰን ከዚያም ወደ 12ኛው ክ/ዘመን ንጉሥ እና የድሆች አያያዝን እንመለከታለን።

አበቤች አደኔ ለድሆች ያላት ግሃዳዊ ጥላቻ ከማሳይተዋ በፊት ጥላቻና ውሸት የጀመራት ገና ሥልጣን ላይ ከመውጣትዋ በፊት ቢሆንም ሥልጣን ስትይዝ ግን ድብቅ ጥላቻዋ በግሃድ የወጣው የግምሩክ ሐላፊ ሆና ስትሾም የአማራ ነገድ ሰራተኞች እያባረረች በምትኩ ኦሮሞዎችን ስትቀጥር ከዚያም ጥላቻዋ ወደ ትግሬዎች ዞሮ “ትግርኛ ተናጋሪዎች እንዲጨፈጨፉና እንዲለቀሙ (ቱ ቢ ሃንትድ) ሆን ብላ በማቀድ ‘’ሓጫሉን የገደሉት ትግርኛ ተናጋሪዎች ናቸው” ማለትዋ ሳይበቃ ‘’ ፥ (ፍንፍኔ ውስጥ) ትግሬዎችን ፈቅደንና ወድደን ብናኖራቸው ጠገቡ’’ የምትለን የኦሮሙማው ኢንትርሃሙዌ ቡድን አባል አበበች አደኔ ፡ ሰሞኑን አዲሰ አበባ ውስጥ ሰላሉ ርሃብተኞች እንዲህ ስትል ተናግራለች፡

«አዲስ አበባ ላይ ጎዳና ላይ ወጥቶ ምግብ የሚያስለምን ምንም ምክንያት የለም። አዲሰ አበባ ውስጥ እንደው እውነቱን ለመናገር አዲሰ አበባ ላይ ጎዳና ላይ የሚያስወጣ ምክንያት በአሁኑ ሰዓት  የለም ወደ ምገባ ማእከላት ውስጥ ጎራ ብሎ ትኩስ ፥ ንጹህ እና የተመጣጠነ ምግብ  መመገብ የሚቻልበት ከተማ ሆኗል።ማረፊያ የሌላቸው ደግሞ ቤታቸው ነው፡ ማረፊያቸው ነው። ርቧቸው ምግብ በልተው አረፍ ብለው እርስ-በርሳቸው ተወያይተው የሚሄዱበት ቤታቸው ነው። ስለዚህ በየጎዳና ላይ የዕለት ጉርሻቸው የሚለምኑ ወገኖቻችን ሁሉ መልእክት ለማስተላለፍ እወዳለሁ። “በከተማ ውስጥ የተገነቡ የምገብ ማዕከላትን በመሄድ እጃችሁን ታጥባችሁ በንጽሕና መጥታችሁ መመገብ ትችላላችሁ። የሚያስፈልገው ሰው ከየት እንድየት መጣህ የሚለው ማንም ሰው የለም።” ተላለች ስትቀደድ፡

የሚገርመው፤ ጉልበታቸው ለደከመ አረጋዊያን ፤ ዕርጉዞች፤ ህጻናት እና አካለ ስንኩላን አድራሻ ወዳልተገለጸላቸው የመመገቢያ ጣቢያዎች «ማጓጓዣ አዘጋጅታ የሚያመላልሳቸው አብቶቡስ እና ታከሲ ያዘጋጀችላቸው ይመስል እየሄዳችሁ ተመገቡ ትላለች”።

አንድ መንግስት የድህነትን መዋቅራዊ መንስኤዎችን ከማንሳት ይልቅ የበጎ አድራጎት ገጽታ በመፍጠር ድሆችን ሕጋዊ እና ኢ-ሕጋዊ ድሆች” በሚል ደረጃ በመሰየም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ በዚህ ዓለም ተሰምቶ የማያውቅ የድሆች ዓይነት ስም እያወጣ በዘር መድለዎ እና በቤት ግንባታ ሽፋን ድሆችን ከተጠለሉበት መኖርያቸው እያፈረሰ ፥ ከሥራቸው እያፈናቀለ፤ መናፈሻ ፓርክ ሰራሁላችሁ እያለ ሲያሟርት ወደ ጎዳና እንዲወጡ ያደረጋቸው ተፈናቃዮችና  ድሆች ፣ የሚያስለምን ምክንያት ምን እንደሆነ አላውቅም ትላለች (እያወቀች)።

አለቃዋም እንዲሁ«ከብት የሚግጠው የጓሮ ቅጠል እጁ ላይ ይዞ እያሳየ)» ሃገራችን  ችግር ውስጥ ሰላለች በርሃብ ከመሞት ይህንን ቀጠል ሸምጥጣችሁ ጨው ጨምራችሁ ፥ ካስፈለገም ትንሽ ዘይት ጨምራችሁበት ለ7 ሰው መመገብ ትችላላችሁ፡ እያለ “በሕዝብ ሕይወት” ቀልድ ይሰራል።

እንደመታውቁት ተምረው የመቅጠርያ ባጀት ስለታጣ  መንግሥት ባጀት የለኝም ሰላላቸው ፤ ሥራ ያጡ 1500 ሃኪሞችና በርካታ ነርሶች ስራ የላቸውም ሲል አዲስ ዘመን እንደዘገበ እናስታሳለን።

ስራ ላይ ያሉ የሕክምና ባለሞያዎችም ደማዛችን  ለኪራይ ፥ ለምግብና ለመጓጓዣ ሰለማይበቃን ቁርስ በልተን ምሳ ሳንበላ ውለን በመከራ እየስራን ነው ፤ በማለት ሥራ ያጡ እና የተራቡ ሃኪሞች በሚል የጻፍኩትን አስታውሱ።በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠ/ምኒስተር ነኝ የሚለን የኦነግ ሸኔው ሰው አብይ አሕመድ እሮሮአቸው ሲያቀርቡለት ምን እንዳላቸው ላስታውሳችሁ።

የብዙ ሰው ልብ በሐዘን የነካቺው አንዲት የልብ ቀዶ ጥገና ስፕሻሊስት፡

«እባካችሁ አትግፉን (don't push us) ሀገራችንን ማገልገል እንፈልጋለን»  ስትል፣

አብይ አሕመድ ደጎሞ እኔም የ IT ባለሙያ ነኝ ወደ ውጪ መውጣት አቅቶኝ አይደለም ሀገሬን ላገልግል ብዬ ነው። እኔም ለሃገሬ እያገለገልኩ ነው አሞኝ እንኳ አሞኛል ሳልል እሰራለሁ፡ የሕክምና ሙያ ከምንም አይበልጥም» አላቸው።

ሃቁ ግን አብይ ከድሮ ጀምሮ ወደ ሥልጣን ሳይመጣ ከኋላ የራስ ቅል  (ጭንቅላቱ) ላይ እባጭ (ዒጥ) ስለነበረው ፤ ያችን ሥልጣኑን ተጥቅሞ ወደ ውጭ አገር በመሄድ ቀዶ ጥገና አድርጎ ታክሞ እንደመጣ እሱ ቢክድም ፎቶውን ከማየት ነው። እንዲያውም አዲሰ አበባ ውስጥም “ለአምላክ ምስጋና እና ፍቅር” በሚል ታክሞ መምጣቱን ሕዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ አድርጎ  ትርጉሙን ሳያውቅ ሕዝቡን ሸውዶታል።

ከተማችንን አዲስ አበባን ለማስዋብ ስንል ባለሃብቶችን ኑ ግቡና አግዙን እያልን ስንት በጀት እያፈሰስን ባለንበት ሰዓት እናንተ ሐኪሞች "ብር" "ብር" አትበሉ ሕክምናን ብር ማግኛ አርጋችው አትስሩ ፡ስትመረቁ በገባችሁት ቃል መሠረት አርፋችሁ ሥሩ! አላቸው።

«ብርን አስባችሁ ከመጣችሁ አታስቡት ፡ ኢትዮጽያ በአሁኑ ወቅት ተመንዝሮ የማያልቅ ተስፋ እንጂ ብር የላትም፡ ምናልባት ለዘይትና ሽንኩርት 500ብር  እንጨምርላቹ ይሆናል።» ሲል ቀለደባቸው።

በሬ እየታረሰበት ሥጋውም እየተበላ ቆዳውም  ለጅማት ክር እየዋለ ይሄ ሁሉ ሲደረግበት ምንም ነገር አይናገርም… ሐኪምም እንደዚ በሬ ነዉ መሆን ያለበት...!"

እያለ በሕኪሞች ላይ ከቀለደ በኋላ አንድ ሓኪም በጻፈው መጣጥፍ ላይ እንዲህ ያለውን ላስነብባችሁ እና ወደ ጉዳያችን እናምራ፤

አብይ ለሐኪሞች እንዲህ አላቸው

ሰሞኑን ሐኪሞች ስላኮረፋችሁ ለኩርፊያችሁ የሚሆን ምሳ ብሉና ቤተ-መንግስቱን ጎብኝታችሁ ወደ ሥራ ሂዱ” አለን። ይላል አንድ ሐኪም። በማስቀጠልም

...ብቻ ብዙ ብዙ ነገር ተብለናል ፣ መሪያችን ባደባባይ ባሪያ መሆናችንን በድጋሚ ሲያበስረን እጅጉኑ አመመኝ።ሲል በቁጭት ለሕዝብ አስረዳ።

ሓኪሞች ሳይቀሩ ለሽንኩርት መግዣ በማጣት በሚሰቃዩባት አገር የባንቱስታዋ ከንቲባ አበቤች አደኔ ደግሞ ወደ ጎዳና ያስወጣቻቸው ድሆች “ኑ የተመጣጠነ ምግብ ተመግቡ” እያለች ታሾፋለች።

በ11 እና 12ኛው ክ/ዘመን የነበሩት መንግስታቶቻችን ስለ ድሆች አያያዝ እና የምግብ ማዕከላት ጉዳይ እንመልከት

የዛጉውዌ ሥርወ መንግሥት የንጉሥ መራ ተከለኃይማኖት የድሆች አያያዝ እና አመጋገብ ከመመልከታችን በፊት የሚክተሉት እንግዳ ቃላቶች ትርጉማቸውን እንመልከት

መጀምርያ የዘመኑ ቃላቶች እና ትርጉማቸውን እነሆ፡

 እልፍ(እልፍ ማለት የግዕዙ “ቁጥር ማለት ሳይሆን- ችግረኛ ሰው፤ ጧሪ እና ደጋፊ የሌላቸው ማለት ነው

 እልፍ አውል- እልፍ አውል ማለት ብዙ ሕዝብ የሚያውል፤ የሚረዳ የሚመግብ ማለት ነው።

እልፍ አስከባሪ--  እልፍ አስከባሪው እናት እና አባታቸው የማይጦሩትን ሰዎች እየተዘዋወረ እየመዘገበ ለቅጣት የሚያቀርብ ክፍል ነው።

ሐሰሴ ፍትሕ - ፍርድ አስፈጻሚ- ፍትሕ ሚኒስተር /ፍርድ አሳሽ /ፈታሽ/ መርማሪ/አጣሪ ማለት ነው

አበጋዝ - በመራ ተ/ሃይማኖት ዘመን  የተቋቋመ “በሐሰሴ ፍትሕ ሠራዊት” ስር የነበረ - ዋና ሥራው የሕዝብ መብት ሲደፈር ፥ገዢዎች ያለ አግባብ  በደል ሲፈጽሙ፤ክፉ ቀን ሲመጣ፤ድርቅ፤አንበጣ በአገሪቱ ላይ ችግር ሲደርስ ፤ ሕዝቡ ሳይጎዳና ርሃብ ሥር ሳይሰድ በአጭር የሚቀጭበትን መንገድ የሚያደርግ።

 ዶሚና የተባለ ደግሞ’ “የሰላም ዘበኛ’’ የመንግሥት ግብር በየወረዳው ሲሰበስብ ሕዝቡን ያለአግባብ እንዳይበደል መቆጣጠር ነው።  “አበጋዝ ከቱርክ የተገኘ ስም ነው” ብለው ቀ/ዳማዊ ኃለስላሴ “ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ” በሚለው መጽሐፋቸው  በምዕራፍ 15 ላይ ‘’ቃሉ የተገኘው ቱርክ ሐረር ሲገባ ያመጣው ቃል ነው ቢሉም ፡ ንጉሡ ወይንም አማካሪዎቻቸው ተሳስተዋል። ይህ ቃል በ12ኛ ከ/ዘመን የነበረ በዘመኑ የተጻፉ የግዕዝ መጽሕፎቶች እንደተገኙ (አሁን እኔ ለዚህ መጣጥፍ የተጠቀምኩት መጽሐፍ ደራሲ ይገልጻሉ)። ደራሲውም ከታች አስቀምጣለሁ።

ጉሮጉሮኒንደር- በመራ ተክለሃያምኖት ዘመን ሐሰሴ ፍትሕ (ፍርድ አስፈጻሚ) የፍትሕ  ሚኒስተር የነበረ የከፋ አውራጃ (የአናርያ) ተወላጅ በቆዳ ቀለሙ “ጥቁር ሰው ነበር። በመራ ተክለሃያምኖት ለካም እና ለኩሽ ሰዎች (በቆዳ ቀለም) እየለየ ሥልጣን በመስጠቱ ከጠያይም ኢትዮጰያዊያን የካም እና የኩሽ (የአናረያ እና የመረዌ) ዘሮች ካልሆኑ ሲማዊያን ነን የሚሉ ወደ ጥንት ቦታቸው እንዲመለሱ እና የዓረብ ዘር ሆነው እስልምና የሚከተሉ ዓረቦችም አገራቸው እንዲገቡ፤ ሲማዊያን  ነን የሚሉትም  ከሥልጣን ተገልለው ኢትዮጵያዊያን ሆነው እሰላምና እመነት የሚከተሉ ካሉ ከሃያምኖት ወገኖቻቸው ጋር አብረው እንዲሄዱ ፥ ይህንን አንፈጽምም ካሉ ተጠምቀው ኢትዮጵያ አገራቸው  ሰለሆነች አርሰው የርስት ተካፋይ ሆነው  እንዲኖሩ በመደረጉ፤ በዚህ ላይ ከዮዲት ዘመን ጀመሮ በሃይማኖት ግጭት ሰለተፈጠረ ሰላም ደፍርሶ በመታየቱ።

ጉሮጉሮኒንደር ይህንን በማየት የቀለም እና የሃይማኖት ልዩነት ማድረግ ለሃገሪቱ ሰላም እና ባሕል መረጋጋት ጠንቅ ሰለሆነ ይህንን ማስቀረት አለብን ብሎ እሱ ሲሾም፤ጥቁሮችን ከየቦታው (ከመርዌ -ሱዳን) ሳይቀር በማስመጣት ከቀያዮች እና ጠያይም ኢትዮጵያዊያን ጋር ቀላቅሎ ሠራዊት የመሰረተ በንጉሡ እና በሕዝብ የተወደደ ሰው ነበር። (ስለ ጉሮጉሮኒንደር አስገራሚ የፍትሕ ሰው መሆን ሌላ ቀን እመለስበታለሁ) ዘመኑ ከመላው ኢትዮጵያ የመጡ ሰዎች የገነቡት አስተዋጽኦ መሆኑን ላሰምርበት እሻለሁ። ሥራውና ግንባታው የአገው ብቻ ፥ የአማራ ብቻ የትግሬ ብቻ.... ወዘተ... የሚሉ ደናቁርት ትንሽ መቆጠብ ያስፈልጋል።

አሁን ወደ ድሆች እንግባ፡

ንጉሥ መራ ተክለሃይማኖት ላስታ ውስጥ የተወለደ ነው። መራ በመጀመሪያ የአክሱማዊው የንጉሥ ድል ናኦድ (ጸረ ዮዲት ጉዲት ወገኖች ላይ ከባድ እርምጃ የወሰደ ንጉሥ) የጦር መሪ (በዘመኑ አጠራር “መሪ ፈረሰኛ የሰላም ዘበኛ” ነበር። ከዚያም የድል ናኦድ ልጅ መሶበ ወርቅን አገባ። ቆይቶም አማቹን ገልብጦ የዛግዌ ሥርወ መንግሥት መስርቶ የሰለሞንን ቤት ገለበጠ።

 ይሀ ንጉሥ ጧሪ እና ደጋፊ የሌላቸው “እልፎችን” ድሆችን እንዴት ይረዱ እንደነበር ያዋቀረው ልዩ የሆነ አስገራሚ አያያዝን እንመልከት።

ከላይ እንደተመለከትነው “እልፍ” ማለት ቁጥር ሳይሆን ችግረኛ ሰው/ሰዎች ማለት ነው። እነዚህ እልፎች «እልፍ አስከባር» በሚባል የችግረኞች እንባ ጠባቂ ድርጀት ችግራቸው እየታየ ዕርዳታ እንዲያገኙ ያደረጋል። ዕርዳታ የሚያገኙበት ቦታ ደግሞ “እልፍ አውል” በሚባል የመመገቢያ እና የዕርዳታ ቦታ ነው። እልፍ አስከባሪም ይሁን እልፍ አውል፤ ሁለቱም “በሐሰሴ ፍትሕ” (በፍትሕ ሚኒስቲር) ቁጥጥር ሥር የሚካሄዱ የዕርዳታ ዘርፎች ናቸው።

የእልፍ አውል ዋና ተግባር ወይንም የሥራ ድርሻ፤ ልጅ የሌላቸው መካኖች በበሽታ ወይንም እርጅና ምክንያት መሥራት ያልቻሉ ችግረኞችን መጦር፤ ከሥራ የተገለሉ በሽተኞች ፥ ጧሪ ከሌላቸው መደገፍ፤ ወላጆቻቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩና ዘመድ የሌላቸው ሕፃናትን መደገፍ ነው።

ጎረሞሶች ሆነው ሥራ ጠል ከሆኑ ይመረመሩና ወደ ፀጥታ አስከባሪነት ተመልመለው ይገባሉ። ጎረምሶች ሆነው ሥራ በማጣት ሲነከራተቱ የሚበሉት ካጡ ማቆያ ስፍራ ይሰጣቸውና  እና እንደ እየ የስራ ችሎታቸው እየታየ ህንጻ ሥራ ወይንም እርሻ እና ንግድ ከሆነም አጋሰሶች እየተሰጣቸው እንዲሰማሩ ይደረጋል።

ጧሪ እና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያን እና ልጅ እግሮች ከሆኑ ግን እልፍ አስከባሪው ችግረኞችን እየተዘዋወረ በመሰብሰብ በተሠሪነት  እየገቡ እንዲቀለቡ ያደርጋል። ችግረኞችን የሚቀበለው ሰው ምግባቸውን፤ልብሳቸውንና ንጽህናቸውን የማሟላት ግዴታ አለበት። ተሠሪ የሚቀበለው ድሀው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ከንጉሠ ነገሥቱ ጀምሮ እሰክ ተራው ወታደር ያለውም ነው።

 ንጉሠ ነገሥቱ ሁለት ድርሻ አለው። አንዱ ከሕዝቡ የበለጠ ድርሻ ተሰጥቶት ተነቃናቂ ያልሆኑ እሰከ 300 የሚሆኑ ችግረኞችን ይቀልባል፥ ያለብሳል። በራሥ እና ደጃዝማች ማዕረግ ያሉት ደግሞ በቋሚነት አሥር ሰው በየቤታቸው ይዘው ሲቀልቡ፣ ከዚህ በተጨማሪ በተራ ሲደርሳቸው አንድ እልፍ (አድ ችግረኛ ሰው) ለወር ይቀልብ እና ለተረኛ ያዛውራሉ።

ከፊታውራሪ እሰክ ባላምባራስ ማዕረግ ያላቸው በነዋሪነት ሦስት ሰው ይይዙና በተረኛነት አንድ እልፍ ሰው ለስደስት ቀን ቀልበው ለተረኛ ያስተላለፋሉ።-

እልፍ አስከባሪው ቤተመንግሥት ያሉትን ሳይቀር በመልካም አያያዝ ወይንም በችግር ላይ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በየጊዜው ቁጥጥር  ያደርጋል። በቋሚነት የተቀመጡትም ሆነ በወር ተራ የሚዞሩት ደህንነታቸው፥ ንጽሕናቸው፥ ልብሳቸው ፥ ምግባቸው እንደምን እንደሚሰራላቸው በመመርመር ጉድለት ያገኙበት ሰው ካዩ  ጉድለቱ ሰለሚያስጠይቅ በመልካም ሁኔታ የተረከቡትን ሰው ተነከባክበው ይይዙት እንደነበር በግዕዝ የተጻፉ የመዛግብት መረጃዎችን ያመላክታሉ።

እልፍ አስከባሪው እናት እና አባታቸው የማይጦሩትን ሰዎች እየተዘዋወረ በማጣራት ከአጽመ እርስት እንዲነቀሉ ያደርጋል። ከእርስቱ የተነቀለው ለጌታ ብያድርም ተቀባይነት የለውም። እናትና አባቱ ያልጦረ ሰው ፤ አሽከርነት አስገብቶ የተገኘ ማንኛውም ሰው ንብረቱ ተወርሶ ለመንግሥት ገቢ ይደረግበታል።የተወረሰው ንብረትም ድሆች እንዲረዱበት ይደረጋል።

ከዚህ የሥራ ከፍል ሌላ በሐሰሴ ፍትሕ ስር የሚተዳደሩ ብዙ የሕዝብ መብት አስከባሪ ቅርንጫፎች እንደነበሩ በታሪክ ስፍሯል።

አበጋዝ ፦ይህ ሹም በመራ ተክለሃይማኖት ዘመነ መንግሥት የተቋቋመና በሐሰሴ ፍትሕ ሠራዊት ስር የነበረ ነው። የሥራ ድርሻው የሕዝብ መብት ሲደፈር ፥ ገዢዎች  ያለአግባብ በደል ሲፈጽሙ ፥ርሃብን እና ድሕነተን ይሚያመጣ ከፉ ቀን ሲመጣ ፥ድርቅ አንበጣ በአገሪቱ ላይ ችግር ሲደርስ ሕዝቡ ሳይጎዳና ርሃቡ ስር ሳይሰድ በአጭሩ የሚቀጭበትን መንገድ መሻት ነው።

ሌላው በአበጋዝ ሥር የሚታዘዝ የሥራ ክፍል «ዶሚና» የሚባለው የሰላም ዘበኛ ነው። ሃላፊነቱም በወረዳ ውስጥ ያለውን ሕዝብ ግብር በወቅቱ እንዲገብር ማድርግ፥ መልከኛው ሕዝብም “”በግብርም ሆነ በሌላ የተንኮል ዘዴ እንዳይበደለውና ጎዳና ወጥቶ ደህይቶ እንዳይለምን የበላይ ሆኖ መቆጣጠር ነው።

 አበጋዙ ዶሚና የሚሰራውን እና የሰጠውን ጥናት ከዶሚና እየተቀበለ በሕዝብ ላይ የሚደረሰውን ከፈተኛም ይሁን ዝቅተኛ በደል ለአውራጃው አበጋዝ ያቀርባል። አውራጃውም ለበላይ አበጋዝ ያቀርብና እና ለሐሰሴ ፍትሕ ያቀርባል።”

ከዶሚና በታች ደግሞ «ገራዳ» የተባለው አካል አለ። ገራዳ ከዶሚና በታች ሆኖ የሕዝቡን ምሬት ይሁን አቤቱታ እና በደል ለዶሚና ያቀርባል።እነዚህ ክፍሎች በዘመነ መራ ተክለኃይማኖት  የነበሩ አሰራሮች እና ስሞች እንደነበሩ  በልዩ ልዩ የግዕዝ መጻሕፍት ውስጥ ሰፍሮ  ይገኛል።

ሕ ማጣት ለድህነት ምክንያት ከሆኑት አንዱ በመሆኑ በዚህ ንጉሥ ዘመን ከላይ የጠቀስኩት  «ጉሮጉሮኒንደር» የተባለው የናራ (ዛሬ አርሲ) ተወላጅ የነበረ የሰላም ጠባቂ የፍትሕ ሰው የድህነት መክንያት ፍትሕ ማጣት እንደሆነ ሰለገባው ፍትሕ እንዲሰፍን ከመኳንንቱ ጋር በመጋጨት ንጉሡ ሕጎቹን እና አሰራሩን እንዲለውጥ ያሳምነው ነበር።

ምንጭ፤

ጥንታዊ የኢትዮጰያ የሰላም ጥበቃ ታሪክ ከቅራት - እስከ ዘምናዊ ፖሊስ (ከአእምሮ ንጉሤ) ደራሲውም በመላ የኢትዮጰያ ገዳማት በመሄድ ያገኙዋቸውን ሦስት የግዕዝ መጻሕፍትን እንደ ምንጭ ይጠቅሳሉ።

እንግዲህ ከላይ እንዳያችሁት በ12ኛው ዘመን እልፎችን (ድሆችን) ከንጉሡ ጀምሮ ከተራ ሕዝብ ድረስ የተቸገሩትን በወረፋ እና በቋሚነት እንዲመግብ ይደረግ እንደነበር እና ወላጆቻቸውን አንጦርም ብለው ወላጆች ለልመና የዳርጉ ልጆች ንብረታቸው ይወረስ እንደነበር አይተናል።

   «በርሃብ ልናልቅ ነው ደሞዝ ጨምሩልን»ብለው ለጮሁ የኢትዮጵያ ሓኪሞች «ሰሞኑን ሐኪሞች ስላኮረፋችሁ ለኩርፊያችሁ የሚሆን ምሳ ብሉና ቤተ-መንግስቱን ጎብኝታችሁ ወደ ስራ ሂዱ እያለ ለተሳለቀባቸው አብይ አሕመድም ይሁን “የሰጠናችሁ ዳቦ ብቻ እየገመጣችሁ ፖለቲካ ሳታወሩ ተኙ” የምትለን ለሚስቱ “ለፓስተር ዝናሽ ታያቸው እና ለአበቤች አደኔ” የማቀርብላቸው ጥያቄ “እንደ ዛጉዌው መስራች እንደ ንጉሥ መራ እልፎችን እቤታችሁ ለማኖርና ለመቀለብ  ፈቃደኞች ናችሁ?

‘‘የለማኝ ልጅ’’ ከንቲባዋና ሚኒስትሯ|ETHIO FORUM

https://youtu.be/HEMMglhpdmQ?si=TXU1-bO9_7EBzCCJ


ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay

 

 

 

 

No comments: