Wednesday, February 26, 2025

አጼ ምንሊክንና አጼ ቴዎድሮስን ለማወደስ “አጼ ዮሐንስን እና ኋይለሥላሴን” ማሳነስ “አጼ ዮሐንስ ለማወደስ ሁሉንም ነገሥታት ማሳነስ” እየጎላ የመጣ የዘመኑ የጥላቻ ጠንቅ መቆም አለበት ጌታቸው ረዳ


አጼ ምንሊክንና አጼ ቴዎድሮስን ለማወደስ “አጼ ዮሐንስን እና ኋይለሥላሴን” ማሳነስ “አጼ ዮሐንስ ለማወደስ ሁሉንም ነገሥታት ማሳነስ” እየጎላ የመጣ የዘመኑ የጥላቻ ጠንቅ መቆም አለበት

ጌታቸው ረዳ

2/26/25

ይህ መልዕክት ኢትዮጵያን ነገሥታት በየዘመናቸው ያደረጉት የሃገር ግንባታና ኢትዮጵያ ብለው ሰይመው ዓለም በአንክሮ የሚመለከታት አስገራሚት ሃገርና ባሕል ያስረከቡን እነዚያ ነገሥታቶቻችን በቅጡ ላልተረድዋቸው የዘመኑ ወጣት ትውልድ ነው መሠረታዊ መልዕክቴ።

ወጣቱ በተለይም ከ50 አመት ወዲህ ወጣት ኢትዮጵያዊያን በነዚህ ነሥታት ያላቸው ነገሥታቱን የማይመጥን አረዳድ መነሻው በጥላቻ የሰከሩ የኤርትራ፤ የትግሬ፤ የኦሮሞ፤ የደቡብ “ናዚያዊ” ምሁራን ባሰራጩት የጥላቻ ቅስቀሳ ነው።

 ሰሞኑን በአንድ የወደጄ ግብዣ ተጋብዤ ለተጋባዡ ሲደመጥ የነበረው ግጥም እጅግ የሚገርም የግጥም ርቀትና ችሎታ ቢሆንም የታዘብኩት ነገር ቢኖር ሃገር ወዳድነት፤ባሕል አክባሪነት፤ አመራርና አርበኛነት በሚመለከት ያለፉት ነገሥታት ስማቸው ሲነሳ ማለትም <<ቴዎድሮስን ዮሐንስን እንዲሁም በላይ ዘለቀን> ተደጋግመው ሲወደሱ ምስኪኑ ዮሐንስም ሆኑ አሉላ ወይንም ኋይለሥላሴ አንዳቸውም ስማቸው አልተወሳም።

ሁሉም ነገሥታቶቻችን አገር ሲያቀኑ እንደዘመናችን “የዘር፤የነገድ ፖለቲከኞች” ሳይሆኑ የኢትዮጵያ አምላክን ፤ ሃገርና ኢትዮጵያዊነትን በማተኮር ብቻ በነበራቸው የዘመኑ ዕውቀትና አስተያይ እየተመሩ እኔ ልገንባ እኔ ልገንባ እያሉ ለግዛት ቢጣሉም ዞሮው በጋብቻ አንድነታቸውን በማጎልበት እስከ እነ ብዙ “ድክመታቸው” አስገራሚ መሪዎች ነበሩ።

ባሳዛኝ ሁኔታ ግን የዘመኑ ትውልድ ነገሥታቱን <<እገሌ ንጉሥ የኛ ነው እገሌ፤ ደግሞ የነዚያ ነው>> በማለት ነገሥታቱ እኔ የእናንተው ንጉሥ ነኝ እገሌ ንጉሥ ደግሞ የናንተ አይደለም የእነ እገሌ ነው እያሉ ባላስተዳደሩበት ዘመንና ሁኔታ ፤ ዛሬ “ንጉሥ እገሌ የኛ ፤ ያ ደግሞ የነዚያ>> እያሉ ነገሥታቱ ባልተናገሩትና ባልሰሩት ስነምግባር ፤ ነገሥታቱን በዘር እና በተወለዱበት አካባቢ እየመደቡ ዘረኞችና ወገንተኞች በማስመሰል “አንዱን ንጉሥ ሲያሞግሱ አንዱን እንደ ጠላት መድበው ሲያሳንስዋቸውና ሲወነጅልዋቸው ማየት ተቀባይነት እያገኘ ልማድ ሆኖ ከመጣ በጣም ቆይቷል። ባለንበት ዘመን ባሁኑ ሰዓት ነገሥታቶቹ ያስተዳደሩትና ሃገር ያቀኑትን ያህል ማስተዳዳር ያልቻሉ የዘመኑ ፖቲከኞች ባመጡት የነገድ ፖለቲካ ሰለባዎች (ቪክቲሞች) የሆኑት ሃገር ያቀኑና ያስረከቡን ነገሥታቶቻችን ሆነው ማየት እጅግ ያማል።

 እኔ እስከማስታውሰው ለምሳሌ ዓ.ም በዘነጋሁት አመት የኢሕአፓ ወጣቶች በዓል ዋሺንግተን ውስጥ ሲከበር የተነበበው “የግጥም መድረክ” ቴድሮስንና ምንሊክ ሲወደሱ፤ ዮሐንስን እየዘለሉ ወደ ሌሎቹ እያሞገሱ አንድም ነገር ስለ አጼ ዮሐንስ አላነሱምና እኔም “ለምን? ብየ ተገረምኩኝ።ከዚያ በፊት በተለያዩ ገጣሚዎች ኢንተርኔት ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ሲሰራጭ ሳይ ስለነበር፤ ግጥም ላነበቡት ደብዳቤ ጽፌላቸው ለምን ሌሎቹን ነገሥታት ሲወሱ ዮሐንስ ምን በድለዋችሁ ነው? ብየ ድረገጾች ላይ አሰራጭቼው ተለጠፈ። “ባለማወቅ ስለሆነ ለወደፊቱ ዕርማት እናደርጋለን” ፤ የሚል መልስ ተሰጠኝ። ነገሩ ከስሕተት የመነጨ እንዳልሆነ ቢረዳኝም እናርማለን ስላሉ ግን ደስ አለኝ።

በመቀጠል ቮረኒካ መላኩ በሚል ስም የሚጽፍ የአምሐራ ተወላጅ ምሁር ‘ትግሬዎች ዮሐንስ በወደቁበት መሬት <<መተማ>> ላይ ስለ ክብራቸው ሐውልት ይቁምላቸው ብለው ሲወተውቱ (ትግሬዎቹ ትግራይ ውስጥ እንኳ በወቅቱ ሃውልት ባያቆሙላቸውም)፤ ቮረኒካ መላኩም ሐውልቱ ለአምሐራ ሕዝብ ለጨፈጨፈው ጨፍጫፊው ለዮሀንስ ሳይሆን ለቴዎድሮስ ሐውልት መቆም አለበት የሚል ንትርክ ሲገባ እኔም በወቅቱ <<ለዮሐንስ ሐውልት ከተነፈገው፤ ለቴዎድሮስም ለምኒሊክም ለሃይለስላሴም አይገባቸውም!>> ለጸረ ትግሬዋ ለቬሮኒካ የተሰጠ መልስከጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) በሚል አንድ ትችት ጽፌ ነበር።በዚያ ጽሑፍ ቴዎድሮስ ከዮሐንስ ባልተናነሰ የጭካኔ ሥራ መስራታቸው ጠቅሼ ሁለቱም ዕኩል በጎና መጥፎ ማሕር ስላላቸው በፍትሕ ዓይን ሁሉም ነገሥታት የኛ ናቸውና እናክብራቸው። በማለት ድክመትና ጥንካሬአቸው በሁሉም ነገሥታት መኖሩ እያወቅን በሞቱት ቅዱሳን (ሃገር ያቀኑ) ነገሥታቶቻችን በነገዳቸው ስንጎነታትላቸው ማየት የክፉ ዘመን ማሳያ ምልክት ነውና ይቁም አልኩኝ።

 ነገሥታቶቹ በዚህ ጨዋታ እየተቧደኑ ባልነበሩበት አሰላልፍ ፤ ነገሥታቱን በየነገዳቸውና በሃይማኖታቸው እየለዩ ንጉሥ እገሌ “የኛ”” ንጉሥ እገሌ ደግሞ “ጠላት” እያሉ ወዳጅና ጠላት አድርገው እንደ ጅብ የሚናጠቁባቸው እነማን ናቸው ብለን ብንጠይቅ የዘመኑ ወጣት ትውልድ (ምሁሩ) ኦሮሞዎች፤ ትግሬዎች እና አምሐራዎች ናቸው። የዚህ ሰበብ ደግሞ “ምሁራኖቹ ባመጡት “አቦዳደን” ያልተማረው ብዙሃኑ እነሱን እያዳመጠ በቀደዱለት ጎርፍ እየጎረፈ መሆኑን ሳይ የታሪክ አረዳዱ አሳሳቢ ያደርገዋል”።

ተራ በተራ እንሂድበት

አሁን ደግሞ ወደ ሙዚቃ ዘፋኞች ልውሰዳችሁ

ያመናል በለው የሚል በ2018 (በፈረንጅ) የተዘፈነ በሚሊዮኖች አድማጭ የተቀባበሉት አጼ ዮሐንስን ያገለለ ዘረኛ ሙዚቃን እንመለከት፡

ዘፋኙ አየነው አረጋ (ሻሎን)

ገጣሚ ትንሳ አድማሱ

ዳይረክተር ሔኖክ አለማዮህ (ዘ-ሐበሻ ድረገጽ ባለቤት)

እንዲህ ይላል፤

<<ያመናል በለው እትነሳም ወይ

ያመናል በለው ያመናል በለው!

ኦሮሞ ሲነካ ያመናል በለው!

አማራ ሲነካ ያመናል በለው!

ደቡቡ ሲነካ ያመናል በለው!

ቤንሻንጉል ሲነካ ያመናል በለው!

ተደፍረውበታል ባንዴራና አገሩ!

የእምየ ምንሊክ የነ ቴዎድሮስ!

የነ ንጉሥ ጦና የበላይ ዘለቀ!....>>

እያለ ብዙ አካባቢያዊ ጀግኖች ሲያሞግስ አገርን ያቀኑ ብዙ የውጭ አገር ቅኝ ገዢዎችን የተፋለሙ ዮሐንስን ግን ጭራሽ እንደነበሩም ንጉሥ እንደነበሩም አላስታወሳቸውም። ይህ ሙዚቃ ሲቀነባበር ወያኔዎች በሥልጣን ስለነበሩ ወያኔዎች የንጉሥ ዮሐንስ ልጆች አድርገው በመውሰድ ትግሬው እንዳለ ያገለለ የተቀነባባረ ንጉሡን ከሃዲና ጸረ ኢትዮጵያ ወይንም የተጠቀሱት “ያመናል በለው የተባለላቸው ነገዶች” ዮሐንስ የበደልዋቸው አድርገው በማቅረብ የተቀነባበረ ጸረ ዮሐንስ ዘረኛ ሙዚቃ ነበር። በዚህም ብዙ በወቅቱ ተቺቻለሁ። ከዚያ ተከትለው የመጡ እስካሁን ድረስ ያሉ ቪዲዮ ሙዚቀኞችና ዘፋኞች የየአካባቢ ነገሥታቶቻቸውና አርበኞች በማመጎስ የተጠመዱ ናቸው።

ካቆምንበት እንቀጥል:-

በትግሬ በኩል ያሉት ዘረኞችም እንመልከት:-

አጼ ዮሐንስን ቅዱስ አድረገው እሳቸውን ብቻ እያወደሱ የተቀሩት የኢትዮጵያ ነገሥታትን የሚዘልፉና የሚወነጅሉ እነማን ናቸው? መልሱ <<ፋሺቶቹ የትግሬ ምሁራን 99.9% >> ናቸው።

አጼ ምንሊክና ቴዎድሮስን እያወደሱ አጼ ዮሐንስን ስማቸው እንዲዘለል የሚያደርጉ ቦታቸውንና ልፋታቸውን የሚያሳንሱና የሚወነጅሉዋቸውስ እነማን ናቸው? የአምሐራ ጠባብ ነገዳዊያን ምሁራን። 

የሚገርመው ሌላው ስልት ደግሞ “የትግሬ ተወላጅ ነገሥታትን ስም አላነሱም እንዳይባሉና ዮሐንስንም ለማሳነስ ሲፈልጉ” ንጉን ትተው የጦር መሪ የሆኑት በንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ የተሾሙት “ራስ አሉ አባ ነጋን ይጠቅሳሉ”። የንጉሠ ነገሥት ምኒሊክን የጦርና የዲፕሎማሲ ጠበብትነት ክብርና ዝና ለማሳነስ ሲፈለግም ለባለቤታቸው ለንግሥት ጣይቱ በመስጠት የማወደስ ሜላ መጠቀም ሌላው ጸረ ምኒሊክነት ታዝቤአለሁ። 

እነዚህስ እነማን ናቸው? አሁንም “ነገዳዊያን አምሐራዎችና የወያኔ ትግሬና ኤርትራዊያን (Eritrea and Ethiopia The Federal Experience 1997-ደራሲ ተከስተ ነጋሽን ከመምህሬና ወዳጄ ዶ/ር ዓለሜ እሸቴ (ነብስ ይማር) ጋር ማሕደር በተባለ ድርገጽ አዳሚነት አውሮጳ ውስጥ ስለ የዓድዋ ጦርነትና የመሳሰሉት ጉዳዮች ሲወያዩ "ዶ/ር ተከስተ ነጋሽ" ንጉሠ ነገት ምንሊክን “ሰካራም” በማለት ባለቤታቸው ጣይቱን የጦር መሪና ዓድዋ ጣሊያንን ያሸነፈች ጀግኒት የሚለው በራሴ ድረገጽ ተለጥፎ ታገኙታላችሁ።) የትግሬ ምሁራንም ይህ ስልት ሆን ብለው ንጉሡን ለማሳነስ ይህንን ስልት ይጠቀሙበታል።  

ወገንተኛነትን የማጠናከር በሽታው በነዚህ ብቻ አልተወሰነም፡ ንጉሥ ዮሐንስ ከእስልምና ጋር ሸካራ ግንኙነት ስለነበራቸው፤ እሳቸውን ለመቃወም ሲሉ እስላማዊ ምሁራኖች “ግራኝ አሕመድን” የነጻነታቸው ታጋይ እና አገር አቅኚ ብለው መጽሐፍትን መጻፍና ሐውልቶች በማቆም (ሶማሊያም ኢትዮጵያም ውስጥ) ሕብረተሰቡን ክርሰትና እና አስልምና ወደ እሚል ወደ እማያልቅ ብጥብጥ ለመውሰድ የጣሩ አሉ።ከዚያም አልፈው የትግሬን ሕዝብ ለመጥላት ሲፈልጉ ዮሐንስን በማስታከክ ጥላቻቸው ሲያራግቡ እናያለን።

ኦሮሞ እና አምሓራ ምሁራንም የበላይ ዘለቀን ዝና ለመቀራመት የኛነው የኛ ነው ሲጓተቱ አይተናል። እንደማሳያ ይህንን እንመልከት፡

ኢኮኒመስቱና ተመራማሪው አቻምየላህ ታምሩ (ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የትጥቅ ትግል የጀመሩት በኢትዮጵያ ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ለመመስረት ነው ሲባል ሰማሁ ልበል? በሚል ርዕስ በMarch 1, 2017) እንዲህ ብሎ ነበር፡-

<<ጉምቱው ኢትዮጵያዊ የወላይታው ልጅ አቶ ታዲዮስ ታንቱ አንድ ወቅት አብረን እንጽፍበት በነበረው አዲስ ታይምስ መጽሄት ላይ እንዲህ ብለው ነበር፤

«ምኒልክ ድሮ በህይወት እያሉ ከነበሯቸው ጠላቶች በላይ በአሁኑ ወቅት በርካታ ጠላቶች አሏቸው። አክሱም ሆቴል ውስጥ ለመቁጠር የሚታክቱ በርካታ ምኒልክን የሚሰድቡ መጽሃፍቶች ተመርቀዋል። የምኒልክን ታሪክ ለማንቋሸሽ ብዙ እየተሰራ ነው። ይህን ለመከላከልም ታሪካችንን ማወቅ አለብን። ታሪካችንን ሰው እንዳይሰርቀን መጠበቅ አለብን። ታሪካችንን ለልጆቻችን ካላስተማርን 80 90 አመት በኋላ ህወሀት አድዋን ያሸነፈው መለስ ዜናዊ ነው ይለናል።>> አቶ ታዲዎስ ታንቱ እውነት አላቸው። የአቶ ታዲዮስ ንግርት ዛሬ በኛ ዘመን እየተተረጎመ እንደሆነ እያየነው ነው። በጭካኔ ወደር የሌለው ወያኔ ዛሬ ደግሞ ግፈኛ ታሪኩን በፈጠራ ታሪክ እያጨማለቀ ነው።>> - ይልና በመቀጠል ፤ ጎጃም ቢወለድም በላይ ዘለቀ ኦሮሞ ነው? በማለት አግራሞቱን አንዲህ ይተነትናል፡

<<ጀግናው በላይ ዘለቀለፈው ሰሞን «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» የሚል ግጥም ያለው አዲስ ዘፈን ተለቆ ነበር። የግጥሙ «ኃሳብ» ባለቤት የእውቀት ጾመኛው ተስፋዬ ገብረዓብ ነው። ተስፋዬ ገብረዓብ ከሁለት ዓመታት በፊት በተካነበት የእባብ ልቡ እየተሳበ «በላይ ዘለቀ ኦሮሞ ነው፤ ሙሉ ስሙም በላይ ዘለቀ ላቀዉ ቂልጡ አያኖ ገልገሊ ይባላል» ሲል በሬ ወለደ ጻፈ። ተስፋዬን ተቀብለው የኦነግ «ዶክተሮች» የወዲ ገብረዓብን ፈጠራ በስፋት አስተጋቡ። እኔ ሁልጌዜ የሚገርመኝ የኦነግ «ዶክተሮች» ተስፋዬ ፈልስሞ እንካችሁ የሚላቸውን ሸቀጥ «ምንጭህ ከምንብለው ሳይጠይቁ እንደወረደ መቀበላቸው ነው። ተስፋዬ የወያኔ ፕሮጀክቶች የሆኑትን «የቡርቃ ዝምታን» እና «ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድን» የጻፈው በዚህ መልክ በበሬ ወለደ ነበር። ለነገሩ ሳይመረምር የሚያስተጋባ ተቀባይ ስላለው ለምን ይጨነቃል። በዚህም የተነሳ በተስፋዬ ልብ ወለድ ኦሮሞ የሆነው በላይ ዘለቀ በኦነጋውያን ዘንድ ቅቡል ሆነ። ግጥምም ተጻፈና «ጎጃም ቢወለድም በላይ ኦሮሞ ነው» ተብሎ ተዘፈነለት።የበላይ አባትም ሙሉ ስማቸው ዘለቀ ላቀው አለሙ እንጂ ተስፋዬ ገብረዓብ ፈልስሞ ለኦነጎች እንዳስተማረው«ዘለቀ ላቀዉ ቂልጡ አያኖ ገልገሊ» አይደለም።

ዘለቀ ላቀው አለሙ የንጉስ ተክለ ኃይማኖት የቢቸና ሹምና በኋላ የንጉስ ተክለ ኃይማኖት የልጅ ልጅ የሰብለ ወንጌል ኃይሉ ተክለኃይማኖት ባል የልጅ እያሱ አንጋች ሆነው ነበር። ኦሮሞነቴን «በህግ አስከብሬያለሁ» የሚለው ተስፋዬ ገብረዓብ የበላይን አስከሬን በሞገሳ ባህል መሰረት ኦሮሞ አድርጎት ካልሆነ በስተቀር በህይወት የነበረው በላይ ዘለቀ እውነተኛ ታሪክ ይህ ከላይ የቀረበው ነው።>> በማለት ኦሮሞዎች በላይ ዘለቀ “ኦሮሞ” ነው፤ የኛ ነው የሚል አዲስ ቅስቀሳ እያስነሱ መጽሐፍ በማሳተም ጭቅጭቅ በማስነሳታቸው አቻምየለህ የሰጣቸው መልስ ነው። ይህ ሁሉ የሚያሳየን “ወያነ” የተባለ ጸረ ሃገር ቡድን ወደ ሥልጣን ከወጣ ወዲህ ሁሉም በየነገዱ ጀግናን እና ንጉሥን እየመረጠ የኔ ነው ፤ የኛ ነው፤ ወደ ማለቱ ሲገባ ማየት እጅግ አስገራሚ ዘመን ነው።

አንዳንዶቹም አጼ ዮሐንስን ለማሳነስ ንጉሡ የእስማኢል ነገድ ነኝ ይላል በማለት ያልተባለውን እየፈጠሩ ታሪክ ሲያበላሹ አይተናል።

ለምሳሌ ተስፈ ገብረአብ የተባለው ኤርትራዊ ባንዳ (ከዚህ ዓለም በፈጣሪ ትዕዛዝ አታስፈልግም ተብሎ በ54 አመቱ ከመሰናበቱ በፊት)የአፄ ዮሐንስ ማኅተም በሚል ርዕስ በፈረንጅ 2018 በድገጼ እንድለጥፈው ልከውልኝ የነበረው ሊቀ ሊቃውንቱ ነብስ ይማር ፕሮፌሰር ጌታቸው ይሌ ጠቃሚ ጽሑፍ ላስነብባችሁና ልሰናበት።

እንዲህ ይላሉ፡

<<ንቄ ያለፍኩትን ርእስ እንድመለስበት ኅሊናየ አስገደደኝ ጉዳይ። ጉዳዩ የአፄ ዮሐንስን ማኅተም ይመለከታል። የምጽፈው ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚጥረው ኤርትራዊው ተስፋየ ገብረአብ በአማርኛ በጻፈው መጽሐፉ ያደረገውን የታሪክ ማዛነፍ ለማቃናት፣ነው። በአማርኛ ሲጽፍ በኢትዮጵያ መኖር ኤርትራውያንንም እንደሚጠቅም ልብ ያላለው ይመስላል። ለመጽሐፉ የኢትዮጵያን ገበያ ባይፈልግ በአማርኛ አይጽፍም ነበር። ይኸንን አስፋፍቶ መተቸትን ለሌላ ጊዜ ላድርገውና፥ በአሁኑ መጽሐፉ ውስጥ ካሰፈራቸው  እኩይ ትችቶች አንዱን ጠቅሼ ላስተባብል። እንዲህ ይላል፤-

”አዲስ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አጤ ዮሃንስ ራሳቸውን “የጽዮን ንጉስ” ብለው ይጠሩ ነበር። በማህተማቸው መካከልም ዘውድ የደፋ አንበሳ ነበረ። የሸዋ መሳፍንት እንደሚያደርጉት ራሳቸውን ከሰሎሞናዊ ዘር ጋር የማቆራኘት ዝንባሌ ግን አልነበራቸውም። የአጤ ዮሃንስ የዘር ግንድ በቀጥታ ከአጤ ፋሲል ጋር የተያያዘ ነው። የፋሲል (የልጅ ልጅ – አምስተኛ ትውልድ የሆነችው) መና እስራኤል አያታቸው ናት። የአጤ ዮሃንስ ማህተም ላይ በአረብኛ የሰፈረው ጽሁፍ፣ “ንጉሰነገስት ዮሃንስ፣ ንጉሰ ጽዮን ዘኢትዮጵያ፣ ዘምነገደ እስማኤል” ይላል። “እስማኤል ማነው?” የሚል ጥያቄ ሲነሳ የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ አብርሃም አጋር ከተባለች ገረዱ ወለደው የተባለው ልጅ ስሙ እስማኤል ነበር።

የአቡነ ተክለሃይማኖት (ተክልዬ) የስጋ ዘመድ ይኩኖ አምላክ ዘሩን ቆጥሮና ተርትሮ ንጉስ ሰሎሞን ላይ ሲያደርስ፤ አጤ ዮሃንስ ደግሞ ተሸዋ ተረት ጋር ለመፎካከር በሚመስል መልኩ ከዚያም በላይ ርቀው የዘር ግንዳቸውን እስማኤል አብርሃም ላይ አደረሱት። አጤ ዮሃንስ ህጋዊ ሚስት ሃሊማ ሙስሊም ነበረች። አጤ ዮሃንስ ራሳቸውን ከአምላክ ጋር ለማገናኘት የእስማኤልን ሃረግ የተከተሉበት፣ ህጋዊ ሚስታቸውን ከሙስሊም ቤተሰብ የመረጡበት ስነ ልቦናዊ ምክንያት ምን እንደሆነ አይታወቅም። “ዘእምነገደ እስማኤል” የሚል ጽሁፍ የያዘውን የአጤ ዮሃንስን ማህተም ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ አስተውሎ ትርጓሜ የሰጠው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ነበር። ፍቅሬ ቶሎሳ እውነተኛ ታሪክ ውስጥ ልቦለድ የሚቀላቅል ግዴለሽ ታሪክ ጸሃፊ ቢሆንም የማህተሙን ፎቶግራፍ ስላተመልን መረጃውን እንቀበለዋለን።” ይላል

አሁን ደግሞ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ስለ አፄ ዮሐንስ ማኅተም ምን እንዳለ እንይ፤

“አጼ ዮሐንስ 4ተኛ ለአግአዚ-ሰሎሞናዊ ሐረጉ የሚጨነቅ አልነበረም። በዚህም ምክንያት እንደሌሎቹ አግአዚ-ሰሎሞናዊ ነገሥታት በማህተሙ ላይ “ድል አድራጊው የይሁዳ አንበሳ” የሚል ጽሁፍ አላስቀረፀም። ሆኖም ራሱን የጽዮን ንጉስ ብሎ ይጠራ ነበር፤ በማሕተሙ መካከልም ዘውድ የደፋ አንበሳ ነበረው።

የአጼ ዮሐንስን ማሕተም ይመለከቷል፡ ማህተሙ የአረብኛ ጽሑፍ ነበረው። ጽሑፉ “ንጉሠ ነገሥታት ዮሐንስ ንጉሠ ፅዮን ዘ ኢትዮጵያ፥ ዘ አምነገደ እስማኢል” የሚል ነበር። “ዘ እምነገደ-እስማኢል” የሚለውን ጽሁፍ ሳይ ዐይኖቼን አላመንኩም ነበር። የገዛ ዐይኖቼን ተጠራጠርኳቸው። ሌሎች ሰዎች እንዲያነቡልኝ እስከመጠየቅም ደረስኩ። ሁሉም “ነገደ እስማኤል” እያሉ አነበቡልኝ። እስካሁን አልተዋጠልኝም። ዐይኖቸ ቢሳሳቱ እመርጣለሁ። አጼ ዮሐንስን የአረብ ዝርያ ያላቸው ይመስል በማህተማቸው ላይ ለምን  “ነገደ እስማኤል” የሚል ጽሁፍ አስቀረጹ?”

ይህን ጥቅስ  የፕሮፌሰር ፍቅሬ መጽሐፍ እንደወጣ አይቼ ንቄ ትቸው ነበር። እንደ እውነተኛ ታሪክ እየተጠቀሰ ሲታይ ግን፥ ዝም ማለት ተገቢ አልመሰለኝም።

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ከላይ የተቀስኩን ከጻፈ በኋላ፥ አንድ የማይነበብ የአጼ ዮሐንስ ማኅተም ፎቶግራፍ አንሥቶ ከመጸሐፉ ውስጥ አስገብቷል። ፎቶግራፉ ከወሰደበትና ከሌሎች ቦታዎች ስናየው የማኅተማቸው ጽሑፍ የሚለው እንዲህ ነው፤

“ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን፤ መስቀል ሞአ ነገደ እስማኤል።

(የጽዮን ንጉሥ ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ፤ መስቀል  እስላሞችን ድል ነሣ።)” ማለት ነው።

ነገሥታቱ ሁሉ በማኅተማቸው ላይ የሚጽፉት የየራሳቸው ቃላት ነበሯቸው። የአፄ ቴዎድሮስ፥ “ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ይል ነበር፤ ተጨማሪ አርማ አልነበራቸውም። ከአፄ ቴዎድሮስ በፊት የነገሡት ነገሥታት አርማቸው ምን እንደነበረ የሁሉም አይታወቅም።

የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን ነገሥታት አርማ፥ “ነግሡ፡ በጽድቅ፡ አብርሃ፡ ወአጽብሐ፡ ነገሥተ፡ ጽዮን” (የጽዮን ንጉሦች አብርሃና አጽብሐ  በትክክል ነገሡ) የሚል ነበረ።

“ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ” (የይሁዳ ነገድ አንበሳ ድል ነሣ) የሚል አርማ የጀመሩት አፄ ምኒልክ ናቸው።

አፄ ዮሐንስ ራሳቸውን “ንጉሠ ጽዮን” ማለታቸውም አዲስ ነገር ወይም “አዲስ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት” የሚባልም አይደለም። ከነገሡበት ዕለት ጀምሮ የሚጠሩበት የሹመት ስማቸው ነው

ከዚያ ቀጥሎ፥ አርማቸው፥ ከላይ እንደጠቀስኩት፥ “መስቀል ሞአ ነገደ እስማኤል” (መስቀል  እስላሞችን ድል ነሣ) ይላል። ከእስላሞች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሻካራ እንደነበረ የታወቀ ነው። ይህ አርማ ያንን ግንኙነት ያንጸባርቃል።

ራሳቸውን “ዘእምነገደ እስማኤል” ብለው ግን አያውቁም አንበሳው የሚያመለክተው የነገደ ይሁዳ  ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሆነ፣ ራሳቸውን ከቀደሟቸው ነገሥታት በምንም ረገድ አልለዩም።

የአፄ ቴዎድሮስና የአፄ ዮሐንስ ማኅተም በተጨማሪ በዐረቢኛ “መሊክ አል-ሙሉክ አል-ሐበሻ” የሚል አለበት፤ “ንጉሠ ነገሥ ዘኢትዮጵያ” ማለት ነው። በማለት አጼ ዮሐንስንና ኢትዮጵያን እንዲሁም ምንሊክን እንዲሁም አምሐራን ለማሳነስ ሲውተረተር የነበረው “ቢሸፍቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ያደገው ሟቹ ባንዳው ኤርትራዊው ተስፋዬ ገብረአብ” የተሰጠው መልስ ነበር።

ስለዚህ በነገሥታትና ባህላችን ላይ ከፍተኛ ቅስቀሳ እየተደረገ እነሱ የዚህ ነገድ፤ የዚህ ጎጥ፤ የዚህ ጎሳ ነኝ እያሉ ባልተናገሩት፤ባልጻፉት፤ ባልሰሩትና ባልተሳተፉበት የዘመናችን ምሁራን እና ያልተመራመሩ ታዳጊ ወጣቶች ነገሥታቶችን በዘርና በነገድ መቧደን እያስገቡ የዛሬ ወጣቶች እየሄዱበት ያለው ድክመታቸው እንዲያርሙና  ሰፊ ሃገርና ባሕል የሰጡንን ለነገሥታቶቻችን ምስጋና በመስጠት ሁሉም ባለውለታዎች ናቸውና በዕኩል ዓይን እንዲታዩ ለምሁራን እና ላልተማሩ ወጣቶች ይህንን መልዕክት አስተላልፋለሁ።

በመጨረሻም ድረጌን ከጠበቅኩት በላይ አንባቢ በቀን ከ3ሺሕ እስከ 7ሺሕ አንባቢ እያደገ በማየቴ ደስ እያለኝ ሃገራችንን እንድትቆይ ጠላቶችዋን እየተጋፈጥን እንደየችሎታችን የበኩላችንን እናበርክት።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ

 

 

 

 

No comments: