የባላምባራስ ሻህእርገጥ ስለ አድዋ
ጦርነት
የዓይን ምስክርነት
(አቅራቢ፥ ጌታቸው ኃይሌ)
ከኢትዮ ሰማይ ማሳሰቢያ ለአንባቢዎች
ማሳሰቢያ
ሰነዱ የቀረበው ነብስ ይማር ፕሮፌሰር
ጌታቸው ኃይሌ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ያቀረቡት የዓድዋ ታሪክ በድረገጼ ተለጥፎ የነበረ ሰነድ ነው።
March 1/2025
አሁን ወደ ታሪኩ
በ፲፰፻፸፱
ዓ ም ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ጃንሆይ አጼ ምኒልክ ሐረር ጨለንቆ አሚር አብዱላሂን ድል አድርገው ወዲያው ባላምባራስ መኰንን ነበሩና
ደጃዝማች ብለው ሐረርን ሾሟቸው።
ባ፲፰፻፹፩
ዓ ም አጼ ዮሐንስ ጐጃም ነበሩና ጐጃምንና ሸዋን ለመውጋት ስላሰቡ ደጃዝማች መኰንን ከሐረር ታዘው አዲሳበባ ወጥተው ግንደበረት
ተቀምጠው በዚያ በኩል አጼ ዮሐንስ ወደሸዋ እንዳይመጡ ይጠባበቁ ነበር። አጼ ዮሐንስም መምጣቱን ትተው ወደመተማ ደርቡሽን ሊወጉ
ሄዱ። ከዚያው ከጦርነት መጋቢት ፩ቀን ባ፲፰፻፹፩ ዓ ም ሞቱ።
በዚሁ
ቀን ደጃዝማች መኰንን ካጼ ምኒልክ ጋራ ወደሐይቅ ሄደው ሲመለሱ በግንቦት ወር እኔ ሻህ እርገጥ አሽከር ሆኜ ከደጃዝማች መኰንን
ጋራ ወደሐረር መጣሁ። ባ፲፰፻፹፩ ዓ ም ሰኔ ፲፪ ቀን ቡርቃ አደርን። ሰኔ ፲፫ ቀን በሮዳ ገባን። ታቦቱ ጊዮርጊስ ነበረና ሰኔ
፲፯ ቀን እኛው መገበርያውን ፈጭተን ተቀደሰ። መተከሉም በዚሁ ቀን ነው። . . . .
ወዲያው
ሐምሌ ፭ቀን ወደኢጣልያ አገር ሮማ ሔዱ። ባ፲፰፻፹፪ ዓ ም በግንቦት ከኢጣልያ አገር በምጽዋ ተመልሰው ጃንሆይ አጼ ምኒልክ ቦሩ
ሜዳ ድረስ ሄደው ከዚያ ተገናኝተው ጨርጨርን የራስ ዳርጌንና የደጃዝማች ወልደ ገብርኤልን አገር በሐረር ላይ ጨምረው ራስ
መኰንን ብለው ሾሟቸው። ከዚህ በኋላ ደጃዝማች ሥዩምን ይዘህ ወደሐረር ሂድ ብለዋቸው ይዘው ወደሐረር ሲመጡ ጨርጨር ሐርዲም
ሲደርሱ አሩሲ ከድቶ የራስ ዳርጌን አሺከሮች ፈጃቸው ቢሏቸው ደጃዝማች ሥዩምን ባ፲፰፻፹፪ ዓ ም በሐምሌ ወር ለቀኛዝማች ወንድ
ይራድ እሰር ብለው ሰጥተዋቸው ራስ መኰንን ወደአሩሲ ዘመቱ። ባ፲፰፻፹፫ ዓ ም ለመስቀል ሐረር ገቡ።
ከዚህ
በኋላ ባ፲፰፻፹፰ ዓ ም መስቀልን ውለው ጣሊያንን ለመውጋት አጼ ምኒልክ ራስ መኰንን ግምባር አድርገው ተነሱ። እኛም
አሽከሮቻቸው ከጌታችን ከራስ መኰንን ጋር ዘመትን። የኅዳር ሚካኤል የጁ አላ እጅረት አደርን። ከዚያ ተነስተን ጐሊማ አደርን።
ከዚያ ተነስተው መቃ ወሀ አደሩ። ከመቃ ወሀ ተነስተው አላማጣ እሚባል ዳገት ጐራው አላስኬድ ብሎ ግማሹ አሸንጌ ባሕር ሰፈር
ሆነ፤ ግማሹ በየገደሉ አደረ።
ኅዳር
፲፰ቀን ረቡዕ በ፮ ሰዓት ራስ መንገሻ ጣሊያኖች እየተከተሉ ራስ መንገሻ ወደኛ ሲመጡ ራስ መኰንን ሰፈር ደረሱ። ከራስ መኰንን
በተገናኙ ጊዜ እንዲህ ብለው አሸለሉ፤
ለየጁ
ለጐንደር ለወሎ ለጐጃም ብነግረው ጩኸቴን ዝም አለኝ።
ከባሕር
ዳር መጥቶ መኰንን አዳነኝ።
፪ኛ
እንዲህ አሉ፤
እሪ
በሉ ትግሮች እሪ በሉ፤ ለየጁ ንገሩ።
የጆች
እሪ በሉ፤ ለጐንደር ንገሩ።
ጐንደሮችም
ጩሁ፤ ለወሎ ንገሩ።
ወሎች
እሪ በሉ፤ ለጐጃም ንገሩ።
ጐጃም
እሪ በሉ፤ ከክስክሱ ብረት ሐረር ለቃኘው ንገሩ።
እሪ
በሉ ሐረጌዎች፤ እሪ በሉ፤ ለንጉሠ ነገሥት ለዳኛው ንገሩ።
ይቆጣ
የለሞይ ሲሰማ ላመሉ።
ከዚህ
ወዲያ ያባ ቃኘው (የራስ መኰንን) አሽከሮች እየታጠቁ ከሰፈር ተነስተው ወደጣሊያኑ ሲሄዱ ሰፈር አድርጐ ፍየልና በጉን አርዶ
ቆዳውን ሳይገፍ የራስ መኰንን አሽከሮች ቢደርሱበት ትቶ ሸሸ። ከዚያ በኋላ ተከታትለው አባረው ወደሰፈር ተመለሱ። ፲ ቀን ያህል
ቆይተው ራስ መኰንን የጦር አበጋዝነቱ የሳቸው ነበረና በውስጣቸው እነራስ ሚካኤልና እነራስ ወሌ፥ እነራስ ወልዴ፥ እነፊታውራሪ
ገበየሁ፥ እነፊታውራሪ ተክሌ፥ እነአድነው ጐሹ ነበሩ። ኅዳር ፳፰ ቀን አምባ አላጌ ከማጆር ቶዞሊ (= Toselli) ጋር ጦርነት ሆነ።
የሰፈረበት
ቦታ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነበረና እኔም ከጌታዬ ከራስ መኰንን ከጦርነቱ ነበርሁና ከቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ዱቄት ማስቀመጫ
በግና ፍየል ማሰሪያ አድርጎት ጽላቱን ከዱቄቱ ማስቀመጫ ስር እኔ ሻህ እርገጥ አግኝቼ ጽላቱም ጊዮርጊስ ነበረ ድል ከሆነ በኋላ
አንስቼ ላቶ ውበቴ ብነግራቸው ለምዳቸውን አውልቀው ሰጥተውኝ በዚያ ሸፍኜ ይዤ አቶ ውበቴ ለራስ መኰንን ነገሩ። ራስ መኰንንም
እኔን አስቀርበው እንደምን አገኘኸው ብለው ጠየቁኝ። ጣሊያን ዱቄት እሚያስቀምጥበት ስር ነው አልኳቸው። የክርስቲያን ምልክቱ
ይህ ነው ብለውኝ፥ ይኸው ያነሳኸው ታቦት ቅዱስ ጊዮርጊስ ይጠብቅህ ብለውኝ፥ ቀኛዝማች ኃይለ ማርያም የእሚባል ትግሬ ራስ
መኰንን ሳይደርሱ ጣሊያኖች ማርከውት የነፍስ አባቱ ከራስ መኰንን ጋር ሰይፋቸውን አንግተው ተሰልፈው ቆመው ነበርና፥ ይኸው የኔ
አሽከር ጣሊያን እንዳለወገን አድርጐ ያረመኔ ሥራ ሠርቶ ታቦቱን ጥሎ የፍየልና የበግ ማሰሪያ የዱቄት ማስቀመጫ አድርጐት አንስቶ
አምጥቶታልና ወደፊታችን ወዳለው ቤተ ክርስቲያን እንዲያገቡት ይቀበሉት ብለዋቸው ተቀብለውኝ እንጣሎ ሚካኤል ወስደው አስገቡት።
ማጆር
ቶዞሊ ሲሸሽ ፊታውራሪ አባ ውርጂ የተባሉት ደርሰውበት ተናንቀው ሁለቱም ገደል ገብተው ሞቱ። አንድ ወታደር ሁለቱንም ገፏቸው
ለራስ መኰንን ግዳይ ሊጥል እየፎከረ ሲመጣ በሕይወቱ የተማረከ ጣሊያን ከራስ መኰንን አጠገብ ነበረና ይህ ባርኔጣ የማጆር ቶዞሊ
ነው ብሎ ቢነግራቸው ያንን ቦታውን ታውቀዋለህ ቢሉት አወን አውቀዋለሁ ቢል ሂድና አሳይ ብለውት ሰው ታዞ የሁለቱ ሬሳ መጥቶ
መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተቀበረ። ኅዳር ፳፱ ቀን ነው።
ታኅሣሥ
፩ቀን ካላጌ ተነስተው እንጣሎ ሰፈሩ። ከዚያ ተነስተው እንደርታ ሰፈሩ። ፳፮ ቀን እንደተቀመጡ ጃንሆይ አጼ ምኒልክ ጨለቆት
ሰፈሩ። ታኅሣሥ ፳፰ቀን ገና ሆነ። ፳፱ ቀን ራስ መኰንን ወደጃንሆይ ሲሄዱ እኔ አብሬ ሄጄ ነበረ። ከተገናኙ በኋላ የጣሊያን
ዘበኞች (ወታደሮች) ከምሽግ ውጪ ተቀምጠው ነበርና ጃንሆይ አጼ ምኒልክ ራስ መኰንንን ሰው ላክ ብለዋቸው ቀኛዝማች ዋቄ
ገድልን፥ አቶ ጋባዥን፥ አቶ ተገኔን፥ አቶ ስለሺን፥ አቶ ወዳጆን አዘዋቸው ሲሄዱ እኔም ካለቃዬ ጋር ሄጀ አቶ አይተንፍሱ፥ አቶ
መሸሻ አሽከሩ አፈሳን ልከው ዘበኛውን ( ወታደሩን) ካስነሱ በኋላ ከምሽጉ ገብቶ ከውጭ አንድ የዘበኛ መጠበቂያ ቤት ነበረና
ከዚያ ውስጥ ድማሚት ቀብሮ ኖሮ እዚያውም ውስጥ እቃ ኖሮ ያንን ሲሻሙ ከምሽጉ ሆኖ ቢተኩስ ድማሚቱ ተነስቶ ባሻ ወልደ መስቀል
አሽከሩ አፈሳን ሁለት ወታደሮች አራቱ ሞቱ፤ ፯ወታደሮች ቆሰሉ። ከዚህ በኋላ ፊታውራሪ ኮላሴንና ፊታውራሪ ደስታ ሣህሉን ልከው
ለነሱ አስረክበን ወደሰፈር መልስ ሆነ።
ከዚህ
በኋላ በተራ ሲጠበቅ ሰንብቶ ጥር ፫ቀን መቀሌ ራስ መኰንን አሽከሮቻቸውን ይዘው ሌሊት ምሽጉን ሊሰብሩ የሄዱ እለት እኔም አብሬ
ሔጄ ምሽጉን መስበር አቃተ። ሰዋችንም አለቀ። ብዙ መኳንንቶች ብዙ ወታደሮች አለቁ። እነቀኛዝማት በሻህ፥ እናቶ መሸሻ ሞቱ።
ሬሳ ማንሳት ከልክሎ በ፰ኛው ቀን ተቀበሩ። እኔም ደገፉ የእሚባል ባልንጀራዬ በጥይት ሞቶ እሱን አነሳለሁ ብዬ ቆሰልሁ።
ጣሊያኖቹ
ወሀ ተይዞባቸው የሚጠጡት አጥተው ሊያልቁ ቢሆን እግዚኦ ብለው በዘበኛ በፊታውራሪ ደሳለኝ እየተጠበቁ ጉዞ ሆነ። ወደአውዜን
አብርሃ ወአጽብሐ ወደእሚባለው ስንደርስ ወደዋናው ወደጀኔራል ባኅርይ (Baratieri) ተቀላቀል ብለውት ሄዶ ተቀላቀለ።
ጃንሆይ
አጼ ምኒልክ ከነሠራዊታቸው ወርን ተሻግረው አደሩ። ከዚያ ተነሥተው ፈረስ ሜዳ ሰፈሩ። ከፈረስ ሜዳ ተነስተው ገንደብታ ሰፈሩ። ከዚያ ተነስተው ራስ ሀጐስና ራስ ስብሐት ከጣሊያን
ከድተው ወደራስ መኰንን ሰፈር ገቡ። ራስ መኰንን ታመው አጼ ምኒልክ ሰፈር ውለው ነበረና የራስ መኰንን ዘበኞች
ወደአጼ ምኒልክ ወሰዷቸው።
፰ቀን
ያህል እንደተቀመጡ የካቲት ፲፬ ቀን ወደአድዋ ጉዞ ሆነ። ፲፭ ቀን አድዋ ሰፈር አደረጉ። የካቲት ፲፮ ቀን እሁድ ራስ መኰንን
ወደአስመራ ሊሄዱ ወደመረብ ጉዞ ሆነ። ወዲያው ወደጃንሆይ ጣሊያኖች መጥተውባቸው ኖሮ መንገዱ ጐራ ነበረና ግማሹ ሰፍሮ ግማሹ
ሲጓዝ የአጼ ምኒልክ መላእክተኛ መጥቶ የካቲት ፲፯ቀን መልስ ሆነ። አዷ ተመልሰው ሰፈሩ።
የካቲት
፲፰ቀን ሠራዊቱን ሽሬ ወደእሚባል አገር ዘረፋ ሰደዱት። የካቲት ፳፫ቀን እሁድ ግማሹ ገብቶ ግማሹ ሳይገባ መኳንንቱም አክሱም
ጽዮን ሄዶ ነበርና ይኸንኑ አሰልሎ ጣሊያን ለጦርነት ተሰልፎ መጣ።
ያጼ
ምኒልክ እድልና የኢትዮጵያ አርበኛ በእግዚአብሔር ኃይል ቅጽበት አልቆየም፤ ወዲያው ድል ሆነ።ንጉሠ ነገሥቱም አርበኞቹም በደስታ
ተመለስን።
ከዚህ
በኋላ እስከ ፲፭ ቀን ቆይተን ወደሸዋ መልስ ሆነ። የጸሎተ ሐሙስ እንጣሎ ሰፈርን። የስቅለት እለትም አላጌን አልፈን ሰፈርን።
የቅዳሜ ስዑር እለት ወፍላ አሸንጌ ስር ሰፍረን ትንሣኤን እዚያ ዋልንና ከዚያ ተነስተን መርሳ በእሚባል አገር ሰፈርን። እዚያ
ታምሜ ቀረሁ። ባ፲፭ ቀን በጐ ሆኘ ፩ግንቦት ልደታ ደሴ ዋልሁ። አጼ ምኒልክና ራስ መኰንን በጨፋ ከንቦልሻ ወደሸዋ ገቡ።
እኔ የማውቀው እስከዚህ ድረስ ነው።
ሻህርገጥ እረኛው።
Ethiopian Semay
No comments:
Post a Comment