ወንጀለኛው ስየ አብርሃ እና የመራኛው አንበሳ ኮሎኔል ሰረቀብርሃን
ጌታቸው ረዳ
Ethiopian Semay 2/16/25
ፎቶ ከላይ ወታደራዊ
ደምብ ልብስ ለብሰው የሚታየው ፎቶ የሦስተኛ ክፈለጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል ሰረቀብርሃን ከታች ወንጀለኛው የህወሓት ስየ አብርሃ
ከታች አሁንም ረዳት ይምጣልኝ ብለው ሲጠይቁ ረዳት አጥተው ብቻቸውን ወያኔን ሲያስጨንቁትና መፈናፈኛ ካሳጡት በኋላ የመዋጊያ ስፍራ
ለመቀየር ኮሎኔል ሰረቀብርሃን በመራኛ ዳገት ቁልቁል መንገድ በእግር ሲወርዱ <<በአምሐራ ገበሬ ጠቋሚነት>> መንገድ
ላይ አድፍጠው ሲጠብቋቸው በነበሩት ህዋሕቶች ድንገት ተይዘው በወያኔ ገሃነማዊ እስር ቤት ሆነው ደብዛቸው ከመጥፋቱ በፊት ለድምጺ
ወያነ ጋዜጠኛ ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉ ነው።
ስለ ኮለኔሉ ያቀረብኩት መጣጥፍና በመጽሐፌ የታተመው የሦስተኛ ክፈለጦር ዋና አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል ሰረቀብርሃን ከወያኔው ቱልቱላ የድምጺ ወያኔ ራዲዮ እና ቴ/ቪዥን የሰጡት ቃለ መጠይቅ ከትግርኛ ወደ አማርኛ አንኳር ነጥቦቹን ለትውስታ እንዲሆን ለአንባቢ ያቀረብኩት ነበር። ቃለ መጠይቃቸው መጀመርያ በ1990 ዓ.ም (ኢትዮ ዘመን አቆጣጠር) ከዚያም በቅርቡ በ2021 (ፈረንጅ ዘመን) እሳቸውን ለማስታወስ ድጋሜ <የመራኛው አንበሳ>> በሚል ርዕስ ያቀረብኩት ፎቶግራፋቸው ነው።
ስለ ኮሎኔሉ ለማንበብ በድረገጼ ላይ ከትንተናው መጨረሻ ያከተትኩት “ሊንክ”
(መስፈንጠሪያ) በመጫን ማንበብ ትችላላችሁ።ዛሬ የማቀርበው ጉዳይ
ለእኚህ ጀግና ኢትዮጵያዊ የጦር መሪ ሕልፈተ ሕይወት ተጠያቂ ስለ ሆነው ስየ አብርሃ ጉዳይ በቅርቡ ካገኘሁት መረጃ እንመለከታለን።
ትግራይ መሬት ከተፈጠሩት
ወያኔ በመባል የሚጠሩ “ጥቋቁር ጣሊያኖች” ጋር በደርግ ዘመነ መንግሥት አገር በማዳን ፍልሚያ የተካፈሉና ህይወታቸው ያጡ ጀግኖች
የኢትዮጵያ ወታደሮችና አዋጊ መኮንኖች፤ ወያኔዎች ሳይቀሩ ስለ ውጊያ
አመራር ብቃታቸው ያደነቅዋቸው አንዱ ኮለኔሉ ሲሆኑ በድንገት ሳያስቡት ባንድ “ከሐዲ” ጠቋሚ ገበሬ ተይዘው ጠላት እጅ
ከገቡ በኋላ ፤ ወያኔዎች በተለይ “ወንጀለኛው ስየ አብርሃ” በኮሎኔሉ ሕልፈተ ሕይወት የተጫወተውን ሚና በቅርቡ፡ያገኘሁትን መረጃ
እንመልከት።
ከዚህ በታች ያለው
ምንጭ ያገኘሁት በወቅቱ ኮለኔሉን ከማረኩት “አሉላ ክ/ጦር” በመባል የሚጠራው የወያኔ ተዋጊ ክፍል ሲመራ ከነበረው በቅሩቡ “አዙሪት”
የሚል መጽሐፍ ደርሶ ለገበያ ካቀረበው ደራሲ የወያኔው ሌ/ጀነራል ዮሐንስ ገ/መስቀል ነው።
እንዲህ ይላል፡
….ወደ መሐል ሜዳ እና አካባቢው ለመድረስ ግን ወረኢሉ፤መራኛ አካባቢ እና
በአካባቢው የነበረው የደርግ ሠራዊት ጋር መዋጋትና አካባቢውን መቆጣጠር ነፃ ማድረግ ነበረብን።
በአካባቢው በኮሎኔል
ሰረቀብርሃን የሚመራው የደርግ 3ኛ ክ/ጦር ስልታዊ የበላይነት የተጠናቀቀው የመጀመሪያው ውጊየ ሲደረግ፤ እኔ የምምራው የአሉላ ክፍለ
ጦር ሠራዊት ወደ ደሴ አቅጣጫ ጉጉፍ በሚባል አካባቢ ግዳጅ ተሰጥቶን ግዳጃችንን በአግባቡ ተወጥተን ለሌላ ግዳጅ እንጠባበቅ ስለነበረ
አልተሳተፍንም። ሌሎች ክፍለጦሮች ይዘው ተዋግተው ሲያቅታቸውና ሲበላሽባቸው ግን ወዲያው የምመራውን ሃይል ይዤ መራኛ እንድደርስ
አዘዙኝ።
እኔም በፍጥነት ተጉዤ
መራኛ ደረስኩና ድጋሚ ዕቅድ ወጥቶ እንደገና የማጥቃት ውጊያ አደረግን። እንግዲህ ዝነኛው 3ኛ ክፍለጦር ከዚያ በኋላ ነበር ከጥቅም
ውጭ የሆነው።
ክፍለጦሩን እኛ ከሰሜን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ስናጠቃው ሌሎቹ ክ/ጦሮች ደግሞ
በግራና በቀኝ ነበሩ።
ከበባው 3ኛ ክ/ጦርን
ክፉኛ ጎድቶት ስለነበር፡ የቀረው ብቸኛ አማራጭ ወደ አህያ ፈጅ ቁልቁል ወርዶ ወደ መሐል ሜዳ ለመሸሽ ጥረት ማድረግ ነበር። ኮ/ል
ሰረቀ ብርሃን የቀረውን ሃይሉን ይዞ ፤ አህያ ፈጅን ማድረግ ነበር። ኮ/ል ሰረቀብርሃን የቀረውን ሃይሉን ይዞ አህያ ፈጅን አቋርጦ
ለመሻገር ጥረት ሲያደርግ ቁልቁለቱን ጨርሶ ወንዙ ላይ እንደደረሰ እየተከተሉ ያጠቁት የነበሩ የአሉላ ሁለት ሬጂመንት አዛዦች የሚመሯቸው
ታጋዮች ከነባልደረቦቹ ጋር ኮ/ል ሰረቀብርሃንን ማረኩት።
ሬጂመነቶቹ በታጋይ
ሙሉጌታ በርሄ እና በታጋይ ብርሃ በየነ የሚመሩ ነበሩ። (እዚህ ላይ ደራሲው ያልጠቀሰው ነገር “የመመራኩ ሁኔታ ታሪክ ሙሉ ለማድረግ” የኮለኔሉ አካሄድና አቅጣጫ ልክ ቢሆንም፤
ሊማረኩ የበቁት ግን የተጠቀሱት ማረኩት የተባለላቸው አንዱ ወንድ አንዷ ሴት (ሙሉጌታ በርሄ እና ሴት ታጋይ ብርሃ በየነ) ካሁን
በፊት የለጠፍኩት ቃለ መጠይቃቸው የሚገልጸውም ሆነ የወያኔ ታጋዮች የተናገሩትና ኮለኔሉና ጋዜጠኛው ያሉት ቀደም ብሎ ኮለኔሉ አስቀድሞ
ካካባቢው ገበሬዎች ከነበራቸው ግንኙነት ምክንያት አንዱ ከሐዲ ገበሬ ለወያኔዎቹ የኮለኔሉን እቅጣጫ ወዴት እየተጓዙ እንደሆነ ስለጠቆማቸው
አድፍጠው ድንገት እንደተያዙ ነው ታሪኩ የሚገልጸው_ የተጨመረ -ከኔው ከጌታቸው ረዳ)
ሁለቱ አዛዦች እነ ኮ/ል ሰረቀብርሃንን እንደማረኳቸው ሪፖርት አደረጉልኝ።
እኔ ወዳለሁበት እንዲልኳቸው በማዘዜ ኮ/ል ሰረቀብርሃንና ባልደረቦቹ እኔ ጋር ደረሱ። ከኔ ጋር እረፍት ወስደው ምግብና ውሃ ሻይ
ተብለው የተወሰነ ካረፉ በኋላ በተሽከርካሪ ባካባቢው ወደነበሩ አስተባባሪዎች ላኩኋቸው። ከ/ል ሰረቀ ብርሃን ረጅምና የሚገርም የከፍተኛ መኮንን
ቁመና ያለው በሙያም
ብዙ ርቀት የተጓዘ እንደሆነ ገና ሳይማረክ ከ3ኛ ክ/ጦር ጋር ባደረግናቸው
ፍልሚያዎች (ብቁ አዋጊነቱን ያየሁበት) በስተመጨረሻም እጁን ሰጥቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳገኘው ለመገንዘብ ችያለሁ።
ብሏል ሌ/ጀነራል ዮሐንስ ገ/መስቀል በመጽሐፉ ውስጥ (ዓረፍተነገሩ ለሟሟላት- በቅንፍ ከኔው የተጨመረ)
ይቀጥልና እንዲህ
ይላል፡-
የህወሓት መሪዎች
ኮ/ል ሰረቀ ብርሃንን ከተረከቡት በኋላ፤ ስየ አብርሃ ይመራው ወደነበረ የሥልጠና ማዕከል ወደ ‘አግበ’ (ተምቤን) ተወሰደ። በዚያም
ከነ ስዬና ሐለፎም ቸንቶ ጋር ሆኖ፤ ከ3ኛ ክፍለጦር ጋር ባሳለፈው የውትድርና አመራር ሕይወቱ ያካበተውን ዕውቀትና ልምድ ለሠልጣኞች
እና እዚያው ለነበሩት አሠልጣኞች ጭምር በማሠልጠን ሙያውንና ዕውቀቱን እንዳካፈለ በደንብ አውቃለሁ። (ተምቤን የሚለው በቅንፍ የተጨመረ)።
ሁኔታውና ዝግጅቱ
አዲስ አበባን ወደ መቆጣጥር ማምራት ሲጀመር ግን እነ ስየ ኮ/ል ሰረቀበርሃንን መቐለ ተወስዶ እንዲታሰር እንዳደረጉት ሰምቼ ነበር። (በወቅቱ) ለምን እንደሆነ ባላውቅም “ኮ/ል ሰረቀብርሃን የት ደረሰ?
ምን እያደረገ ነው? እያልኩ እከታተል ነበር፡ ለዚያም ነው መጀመሪያ ላይ እያሠለጠነ እንደነበረ፤ ቀጥሎ ደግሞ
እስር ቤት እንደከተቱት መረጃ ይደርሰኝ የነበረው። የት ደረሰ? ምን እያደረገ ነው? እያልኩ ልከታተል ያደረገኝ ምክንያት ፤ ምናልባትም
ሰዎቹ ማሰር መግደል አንዱ አስጸያፊ ሥራቸው
ስለነበር ይመስለኛል። (ደራሲው “ሰዎቹ” ሲል የወያኔ
መሪዎች ማለቱ ነው)
በመቀጠልም እንዲህ
ይላል፡
በወቅቱ የያኔውን ጠንካራ እና የጸና ዓለም አቀፍ የምርኮኛ አያያዝ ሕግ በጊዜው
ባላውቀውም አብሮኝ የኖረው “ሰውኛ” የመሆን ባሕሪ ግን ተዋሕዶኛልና
ምናልባትም እሱ ሊሆን ይችላል የኮሎኔሉን ጉዳይ እንድከታተል የገፋፋኝ። መታሰሩ ከሰማሁ በኋላም በሕይወት አለ ወይ?
እያልኩ እጠይቅ ነበር። አዲስ አበባን እስክንቆጣጠር (ድረስ) እስረኛ ሆኖ በሕይት እንዳለ እሰማ ነበር። በሂደት ግን
በሕይወት የለም ሲባል መስማት ጀመርኩ። ይህንን ስሰማ ደነገጥኩ። ጥርጣሬ ቢኖረኝም፤ በድል ላይ ሆነን አዲስ አባባን
ተቆጣጥረን ‘ጉሮ ወሸባዬ’ እያልን የድል ዘፈን እየዘፈንን፤ የፈለገ ወንጀል ቢኖርበትስ፤ ወደ ፍትሕ መላክ ሲገባው “በምን መመዘኛ በበረሃ ሕግ ሕይወቱን
እናጠፋለን?”
ካለ በኋላ ሌ/ዮሐንስ
ገ/መስቀል እንዲህ ይቀጥላል፡
…ስዬ አብርሃና አብረውት የነበሩት፤ ይህንን ኮሎኔል ወደ ሕግ ከማቅረብ ይልቅ በመቐለ 06 እንዲታሰር አድርገው ሕይወቱ እንዲጠፋ በማድረጋቸው ሐላፊነቱን መውሰድ አለባቸው። በተለይ ስየ አብርሃን አሰልጣኝ አድርጎ
ዕለት ተዕለት ባንድ ማዕድ አብረው እየበሉ በአግበ ማሠልጣኛ ጣቢያ የቆየበት ጊዜ ብዙ ነው። በተቃራኒው በሕወሓት ቁንጮ አመራሮች
ስለ ሙርኮኛ አያያዝ ሁኔታ ሲታሰብ “ህወሓትም በአመራሩ ሳይሆን በታጋይ
የሚተገበር የምርኮኛ አያያዝ ሥርዓት ነው የነበረው ለካ!” ያስብላል።
…>>
እያለ ዮሐንስ ገብረመስቀል አዙሪት በተባለው በዚህ ዓመት በ2017 ዓ.ም የታተመው አዲስ መጽሐፉ ስለ ስየ አብርሃ ወንጀለኛነትና ጨካኝነት በገጽ 65-66 … ገልጿል።
ስየ አብርሃ ማለት የህወሓት ማዕከላዊ አመራር አባል የነበረ ዘለባጅና አቋመ ቢስ፤ “ሌባ ብሎ ያሰረውን መለስ ዜናዊ
ሲሞት ደም ያነባ እርኩስ “አልትራ ናሺናሊሰት ትግሬና ጸረ ኢትዮጵያ” የሆነ ግለሰብ ነው። ስለ ስየ አብርሃ ለማንበብ በጓደኛው
በወቅቱ የወያኔ ውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር በስዩም መስፍን በ21/10/1993 ዓ.ም ከወያኔ ሬዲዮ ጋር ያደረገው 17 ገጽ የያዘ የትግርኛ
ቃለ መጠይቅ ተመልከት።
በመጨረሻም ስለ ኮለኔሉ አንድ ነገር ልብልና ልደምድም። የተወለዱት ሲዳሞ ክፍለሃገር ጀምጀም አዉራጃ ዉስጥ ክብረመንግሥት ከተማ ነዉ። ከድምጺ ወያነ ጋር ያደረጉት ከትግርኛ ወደ አማርኛ የተረጎምኩትን አንጀት የሚበላ አሳዛኝ ታሪካቸውን ለማንበብ ከፈለጉ ይህንን ሊንክ ይጫኑ
አመሰግናለሁ ጌታቸው
ረዳ
https://ethiopiansemay.blogspot.com/2021/01/ethiopian-semay-01012021.html
No comments:
Post a Comment