Sunday, May 13, 2018

ለዮሐንስ ሐውልት ከተነፈገው፤ ለቴዎድሮስም ለምኒሊክም ለሃይለስላሴም አይገባቸውም! ለጸረ ትግሬዋ ለቬሮኒካ የተሰጠ መልስ ከጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)


ለዮሐንስ ሐውልት ከተነፈገው፤ ለቴዎድሮስም ለምኒሊክም ለሃይለስላሴም አይገባቸውም!
ለጸረ ትግሬዋ ለቬሮኒካ የተሰጠ መልስ
ከጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

የአማራ ፋሺዝም በሚል ርዕስ የጻፉት ፕሮፌሰር መስፍን ዛሬ ተስማምቶኛል። እያቆጠቆጠ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል። እሳቸው በጻፉት ትከክለኛ ማስረጃ ጠቅሰው ባሉት ጉዳይ በሌላ ርዕስ እምለስበታለሁ። ዛሬ ቢህህ ጉዳይ እንነጋገር። ቬሮኒካ የሴት ስም ነው። ይህ ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት የውቅሮ (ረስቼወለሁ ወይንም የመቀሌ) እግር ኳስ ተጫዋች በነበርኩበት ጊዜ ከታወቁት የአዲግራት የእግር ኳስ ተጫዋቾች (ከነ መኮነን ከሚባል የታወቀ የአዲግራት እግር ኳስ ተጫዋች ለመግጠም)  ወደ አዲግራት ከተማ ሄጄ በነበርኩበት ወቅት የተዋወቅኳት ቬሮኒካ የምትባል አንዲት ወጣት ከጨዋታው በላ ወደ እኔ በመምጣት እቤትዋ ድረስ እንደጋበዘቺኝ ትዝ ይለኛል  (ተጫዋቾች የታወቀው የከተማው ጠጅ ለመጠጣት በየአቅጣጫችን ተበታትነዋል)። አዲግራት ለመጎብኘት የመጀመሪያየ ነበር፡ በውቅቱ የከታማዋ ወጣት ሴቶች ልክ እንደ የዓድዋ ወጣት ተማሪዎች ዘመናዊ ናቸው፡አያፍሩም፤(ቆንጆዎችም ናቸው) ስሟ እንግዳ ሆኖብኝ ስጠይቃት የአጋሜ አውራጃ ክፍል ከሆነው የኢሮብ ተወላጅ እንደሆነች ነገረቺኝ። ዛሬ ይህ ስም በመጠቀም “ቬሮኒካ” በሚል ስም በየድረገጹ ስለ አማራ ቆሚየለሁ እያለች እኛን የትግራይ ማሕበረሰቦችን ለማጥላላትለማሳነስለመስደብምናልባትም ከመድረገጽ እንድንጠፋም ፍላጎት ሳይራት አይቀርም። ካሁን በፊት ስለ እኛ ብዙ ነገሮችን ሳታፍር ጽፋለችና!

ቬሮኒካ መላኩ እያለች የምትጽፍ ጸሐፊ ‘እውነተኛ ስም ይሁን ወንድ ይሁን ሴት የምናውቀው ነገር የለም”። ለዚህ ነው ድረገጾችን ብዙ ጊዜ በውሸት ስም የሚጽፉ ፎቶግራፋቸው እና ስማቸው እንዲለጥፉ ካልሆነ ግን ማስተናገድ እንደማይቻል ሕግ እንድታወጡ እያልኩ የምወተውታቸው። ሆኖም አንድን ማሕበረስብ ከአንዱ ማሕበረስብ እንዲባላ በግሃድ ሲጽፉ ስማቸው እና ማንንታቸው ግን እንዲደበቅ እየተደረገ ድረገጾች ተበባባሪዎች እየሆኑ ነው። በዚህ ረገድ አንድ በድፍረቱ የማከብረው ጸረ ትግሬ ቢሆንም ማንንቱን ሳይደብቅ ፎቶግራፉን የሚለጥፍ ሠዓሊ ገ/ኪዳን ከነዚህ እየተደበቁ የሚያናክሱ ፈሪዎች ጋር ሳነጻጽረው ገ/ኪዳን አራጋው ለበድፍረቱ አደንቀዋለሁ። ይህንን ድፈረቱ በማየት በግሌ ስለጻፈው ሁሉ ይቅርታ አድርጌለታለሁ።

ቬሮኒካ ካሁን በፊት አንዳንዶቹ “ተስፋየ ግበረአብ ነው’ ይላሉ። አንዳንዶቻችን ግን “ኣክራሪ አማራ” ነች እንላለን። ያም ሆነ ይህ በአማራ ዙርያ እና እንዲሁም ‘ሞረሽ’ በተባለው ራዲዮ ጽሑፈፖጫ የሚነበብላት ስለሆነ አነሰም በዛም በውስጥ አዋቂዎች ማንንት እስክንደርስበት ድረስ “አክራሪ አማራ” ነች በሚል ልደምድም እና ወደ ነገሬ ልግባ።

የህች ሴት/ወንድ/ ለትግራይ ማሕበረሰብ ካላት ጥላቻ የተነሳ በርካታ የጥላቻ ጽሑፎችን አስነብባናለች። ለዚች “አክራሪ አማራ” መልስ ስሰጥ ዛሬ ሁለተኛ ጊዜ ነው። ካሁን በፊት ስለ ኤርትራ ትግሬዎች እና  ስለ ትግራይ ትግሬዎች በጻፈቺው ላይ የጻፍኩትን መልስ ስላጣች ‘አፍራ’ ተወሽቃ ቀርታለች። ዛሬ ደግሞ ወደ አፄ ዮሐንስ ዞራለች። በጣም ረዢም አመታት ለሆነ ጊዜ እስካሁን ድረስ “ወያኔዎችም ሆኑ በተቃዋሚ የቆሙ ፖለቲከኞች እና ጸሐፊዎች ደራሲያንሙዚቀኞች…” ያለፉት ነገሥታት በማንሳት “ነገሥታቱ የተወለዱበት አካባቢ” ተወካይ በማድረግ “እገሌ ንጉሥ የኛ እገሌ ደግሞ የነዚያ” በሚል ጠቦች እና የዘረኞች ጨዋታ በመግባት የአገሪትዋ አንድነት ማፍረሻ ሰበብ እየሆናችሁ ስለሆነ ስለ ነገሥታቱ ስታነሱ እናንተን ወይንም የተወለዳችሁበትን ነገድ እንደሚወክሉ እያደረጋችሁ በስማቸው አትነግዱ ። ሕዝብን ከሕዝብ ግጭት አትፍጠሩ ስል ‘የሚሰማኝ አልነበረም’ እና ይኼው ዛሬ በዚህ ንትርክ አስገብተውናል። ስለሆነም ሳንወድ ስናመሰግናቸው የነበሩትን ነገሥታት ዛሬም በነዚህ ዘረኞች ተገድደን ፡የኛ” የሚልዋቸው ነገሥታት ምን ስራ ይሰሩ ነበር? ብለን ለመነጋገር ተገድደናል እና እንነጋገር።

ቬሮኒካ Ethiopanorama.com (በሌሎቹም ተለጥፎ ሊሆን ይችላል) “አፄ ዮሀንስ ሀውልት ሊሰራላቸው አይገባም ስንል….” ቬሮኒካ መላኩ በ5/12/2018 (አውሮጳ ዘመን) በማለት የጻፈቺውን ተመለክቼዋለሁ። አጼ ዮሐንስን በምትፈልገው የስሜት ፈረስ እየጋለበች ንጉሡን እንደ አልባሌ ሰው በመቁጠር መተማ (ጎንደር) ሓውልት ሊሰራለት ነውና ተብሎ ሊሰራለት አይገባም ስትል ተቃውሞዋን አቅርባለች። ይህ ስለ ንጉሡ ሃውልት ስለ ማቆም ዕቅድ ዜና የሰማሁት አሁን ከቬሮኒካ ጽሑፍ ነው። ለተቃውሞዋም የሚከተሉትን ዘርዝራለች።
2 ~ አፄ ዮሀንስ የወሎ ሙስሊሞችን በአሰቃቂ ሁኔታ የጨፈጨፈ መ ነው ይሄ ጉዳይ መቼም አለም የሚያውቀው ብዙም የተፃፈበት ስለሆነ ለማስረዳት ብዙ መድከም የለብኝም። በኢትዮጵያ ታሪክ በመንግስት አዋጅ እስልምናንና እስላምን ለማጥፋት አዋጅ ያስነገረ መሪ ዮሀንስ ብቻ ነው (ስለ ቦሩ ሜዳ ኮንፈረንስ ማንበብ የፈለገ እስኪሰለቸው አሰቃቂውን የዮሀንስ ወንጀል ማንበብ ይችላል)
3 ~ << በላይኛው ጌታ በባልንጀራዎ
በቅዱስ ሚካኤል በጋሻ ጃግሬዎ
ጎጃምን ይማሩት ፈሪም አንልዎ። >>
ተብሎ ግጥም እስኪገጠም ድረስ የጎጃምን ህዝብ በደም ያጨቀየ ነው።
4~ የራያ ህዝብ ላይ የዘር ፍጅት  ፈፅሟል
5 ~ ከእሱ በፊት ንጉስ የነበረውን ዋግሹም  ጎበዜን ወይም አፄ ተክለጊዮርጊስን በጦርነት ተሸንፎ ሲማርከው በክብር ይዞ በህጉ እንደመዳኘት በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ ሁኔታ አፄ ተክለጊዮርጊስን  ሁለት አይኑን በብረት ጉጠት  ፈንቅሎ አውጥቶ የገደለ Sadist ነው።
ዮሀንስ እንደሚወራለት ለኦርቶዶክስ ክርስትናም ደንታ ያለው መሪ አልነበረም ጎጃም ውስጥ ያሉ ታቦታትንም እያወጣ ያቃጠለ ፀረ ኦርቶዶስም እንደነበር መታወቅ አለበት።  ቅዱስ ታቦታትን ከመንበሩ እያወጣ  እያስፈለጠ  ያነደደና ያጋዬ መሪ  ዮሀንስ ብቻ ነው።
ሌላው የዮሀንስ የግል ህይወትም  የሚያስገርም፣ የሚቀፍና ለትውልድ ሞዴል የማይሆን  ነበር። ዮሀንስ በንግስና ዘመኑ  ህጋዊ ሚስት የሚባል አልነበረውም።  የዮሀንስ ቤተ መንግስት ውስጥ የነበረችውንእቴጌየሚነግረኝ ሰው  ካለ በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ አስመዘግበዋለሁኝ

እውነት አንባቢዎች እነዚህ ነጥቦች ቬሮኒካ ትንሽዋን ጭንቅላትዋ በየጥሻው አሰማርታተጉዛ ንጉሡን የሚያጥላላ ገመና አገኘሁባቸው ብላ ስትል እውነት ሌሎቹ ነገሥታት እነዚህን እና መሰል ገመናዎች አልፈጸሙም ልትለን ነው?  እስኪ የነቬሮኒካ እና መሰል አክራሪ ሃይላት ጭኸት እና ሴራ እውነቱን ለማወቅ ክርክራችንን እንቀጥል።

ቬሮኒካ ትናንት ተወልደሽ ዮሐንስ ባስረከበሽ መሬትንፍጥሽን ጠርገሺበት፤ ተንደላቅቀሽ፤ ቦርቀሽ፤ተምረሽ ያደግሽበትን መሬት ዮሐንስ ያቀናው መሆኑን ትክጅየለሽ? ዮሐንስ ንጉሥ ምኒሊክን ወክየሃለሁ እና ገር አቅና ብሎ አሉላን ወደ ምኒሊክ ልኮለት ወደ ደቢብ እና ምስራቅ አገር ዘምቶ ላንቺ ያስረከበውን ሰፊው አገር ማን ባቀናው ነው ብለሽ ትገምቺያለሽ? ስለ ኢትዮጵያ ትርጉም ምንነት ለኢትዮጵያውያን ያስተማረ የመጀመሪያው ንጉሥ መማን ሆኖና ነው? ዮሐንስ!!  ለመሆኑ ጎንደሬዎች እስላም ልያደርገን የመጣ ቤተክርስትያን ያቃጠለ ሴቶቻችን እየዘረፈ የመጣ ድረቡሽ የሚባል መጥቷል እና አድነን ብለው ደብዳቤ ሲጽፉለት የጎንደርን ሕዝብ ለማዳን መታማ ላይ አንገቱን ለእስላም ሰይፍ የሰጠውን ዮሐንስ መተማ ሃውልት ይቁም ቢባል ለማን ነበር ልትሰጪው የፈለግሺው? ለድርቡሽ? ዮሐንስ ከሃዲ ነው መሬት ባሕር ለጠላት አሳልፎ የሰጠ..ትያለሽ፦-- ለመሆኑ ወያኔ እያሯረጠ መላውን አገሪቷ ለ27 አመት ገዝቶ አንቺኑን ወደ ውጭ አገር ስያባርር ምነዋ አንቺ አገር ማስመለስ አቅቶሽ እስካሁን ድረስ ስለዮሐንስ ታወሪያለሽ? እንደ ዮሐንስ አነገትሽ ለሰይፍ መስጠት ፈርተሽ ወደ ውጭ በርርሽ እራስሺን ስለ ከማመጻደቅ ስለ ዮሐንስ ማውራትሽ ትትሽ እራስሺን ብትፈትሺ ምናለ? ትንሽ እፈሩ እባካችሁ!  

ለመሆኑ ጎንደር/መተማ የማን አገር ነው? ያንቺው? ወይንም ያንቺው ብቻ? ዮሀንስ የጎንደር ተወላጅም ነው ሲባል በታሪክ አልሰማሽም”? ከነ ፋሲል ይወለዳል ሲባል አልሰማሽም? ዮሐንስ ትግሬ ብቻ መስሎሽ ከሆነ አማርኛ ከማሳመር ባሻገር ብዙ እውቀት ይቀርሻል። ለዮሐንስ ሐውልት ከተነፈገው፤ ለቴዎድሮስም ለምኒልክም ለሃይለስላሴም እንደው ለጠቅላላ የኢትዮጵያ ነገሥታት ሃውልትም ሙገሳም መቅረት አለበት!! ምክንያቴን ባጭሩ ልግለጽ። ቬሮኒካ እና መሰል አክራሪ ሃይሎች ዮሐንስን ለማጥላላት የሚጠቀሙበት ካነበቡት እየጠቀሱ ነው። እኔም ካነበብኩት ልጥቀስ። ማለቂያ አለው የለውም ለታሪክ እንተወው።

1)    ከቴዎድሮስ ልጀምር።- ቴዎድሮስ ደምበኛ ስመ ክርስትናው ገብረኪዳን፤ ደምበኛ (ዓለማዊ) ስሙ ደግሞ ካሳ፤ ስመ መንግሥቱ “ቴዎድሮስ”።ቴዎድሮስ አክሱም መንገሡን ያነበብኩት ነገር የለም። ወደ ትግሬ መምጣቱ ግን አውቃለሁ። በ1847 ደጃች ሃይለማርያም ውቤን ተዋግቶ በማሸነፍ ‘ደረስጌ ማርያም’ በሚባል ዳግማዊ ቴዎድሮስ ተብሎ እንደነገሠ እንጂ እንደ ሕጋዊዎቹ ሌሎች ነገሥታት አክሱም ድረስ መጥቶ መንገሡን አላነበብኩም።  እንግዲህ ሁሉም በክርስትና የሚያምኑ ነገሥታት አክሱም ሄደው ነግሠዋል።ነግሦ ከነበረም ልታረም።

2)   ቴዎድሮስ አገሪቷን አንድ ለማድረግ የሚያስችል ስልት የጎደለው ሰው ነበር፡ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ስልት ለመምራት ሲከተለው የነበረው ተቃራኒ ስልቶችና እርምጃዎች ከነበረው ዓላማ ሊደናቀፍ ችሏል። (ባሕሩ ዘውዴ ገጽ 31)

3)   ኢትዮጵያውያን ዛሬም ጭካኔን እንደ ጀግንነት ስለወሰድነው ቴዎድሮስ እንደ ልዩ ጀግና አድርግን የመሳል ልምዳችን ከወላጆቻችን የወረስነው ልምድ ስለሆነ አሁንም አብሮን አለ።  ቴዎድሮስ እጅግ በጣም ጨካኝ ስለነበር፤ በህዝብ፤በያንዳንዱ ዜጋ የፍርሃት ቆፈን ያነገሠ መሪ ነበር።ቀሳውስት፤ተራ ዜጋ፤ገበሬ፤ ኦሮሞ ሁሉንም በየፊና ሲጨፈጭፍ የነበረ በጣም አደገኛ ንጉሥ ነበር። 

4)   ሕሩይ ወልደስላሴ የተባሉ የጥንት ጸሐፊ የነገሩን ነገር አለ። ንጉሥ ሃይለመለኮት ሞተዋል የሚል ወሬ ሲሰማ ፤ ቴዎድሮስ ወደ ሽዋ በመሄድ የሃይለመለኮት መሞት ማመን ስላቃተው ፤የሃይለመለኮትን የመቃብር ቦታ በማስቆፈር ሬሳውን ካየ በላ ወደ አንኮበር ከተማ አመራ፡ እዛው እንደደረሰ፤ ወደ 500 የሚሆኑ መኳንንት፤ሊቃውንት እና መሰል ሰዎችን ሰብስቦ እጅ እና እግራቸው እንዲቆረጡ አድርገዋል።

5)   አንኮበር የሚገኝ የጥንት ንዋየ ቅዱሳት/መጻሕፍት ሙጥጥ አድርጎ ዘርፎ በመውሰድ ወደ ጎንደር ይዞት ሄዷል።

6)  በዚህ የተነሳ አጼ ቴዎድሮስ ምነው ተዋረዱ ፤ የሸዋን ሰው ሁሉ እጅ ነስተው ሄዱ” ሲሉ ጽፈዋል።
7)   ወጣቱ ምኒልክ በወሎይትዋ ወ/ሮ ወርቂት አማካይነት ሰው አስልካ ከቴዎድሮስ ግዞት አስመልጣ ወደ ሸዋ እንዲያመልጥ በመርዳትዋ የተነሳ ፤ ቴዎድሮስ ወሎ የካደው መስሎት፤በቁጥጥሩ ስር መቅደላ ውስጥ ታስረው የነበሩትን የወሎ /የወረሂመኑ ይማሞች እና መኳንንት እጅ እና እግራቸውን ቆርጠው ከነ ነብሳቸውወደ ገደል እንዲጣሉ አድርገዋል።  (ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረስላሴ 1969-55-56)

8)    በዚህ የተነሳ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለራቀው ቤተክርስትያን ማቃጠል ሴት፤ወንድ ሳይል ሁሉን እቤት ውስጥ ሰብስቦ በማገባት በእሳት አጋያቸው። በሬዎችና ላሞች እየተዘረፉ በጎራዴ ተጨፈጨፉ፤ ሕዝቡ ይህን ግፍ ሲያይ በፍርሃት ቆፈን ተንቀጥቅጦ ወደ እየ አገሩ መበተን ጀመረ። በሞላ አገሪቷም የሽፍቶች እና የወረበሎች አገር ሆነች።( (ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረስላሴ 1969-55-56)
9)  በጳጉሜን 1847 ዓ.ም ወደ ወሎ ሄዶ በነበረበት ጊዜ “ጊምባ” በሚበል ቦታ እንደደረሰ 47 ሰዎች ሁለቱን ግራ እና ቀኝ እጆቻቸው አስቆርጦ፤ ይህንን አረመኔነት እንደ ጀብድ ቆጥሮት ‘የተቆረጡትን እጆቻቸው’” በገመድ አስሮ አንገታቸው ላይ አንጠልጥለውት እንዲሄዱ ሸኛቸው። (ፕሮፌሰር ፋዜላ የቴዎድሮስ ታሪክ ከሚል መጽሐፍ ገጽ 92-94) 

10) በመስከረም 1851 ቴዎድሮስ ከአመዴ በሽር ጋር ተዋግቶ 787 የወሎ ሰዎች ሁለቱንም እጆቻቸው እያስቆረጠ አሰናበታቸው። እስከ ነሓሴ ወር 1851 በወሎ ምደር ውስጥ አጅግ እግራቸው የተቆረጡ ሰዎች ወደ ሺህ እንደሚጠጋ ይነገራል።

11)   ቴዎድሮስ መጋቢት 1848 ዓ.ም ወደ ደምበጫ ዘምቶ 7 ሰዎች ማርኮ እመሃል ገበያ ሕዝብ ተሰብስቦ እያየ እዛው እንዲታነቁ አደረገ። ጠመንጃ ነጥቆ ለመሸ የሞከረ አንድ ሰውየ ካስያዘው በላ፤ ሰውየው ወደ መድፍ አፈሙዝ ተጠግቶ እንዲቆም ካዘዘው በላ በመድፍ ጥይት ደብድቦ የሰው ገላ እንደ ተበጣጠሰ ጨርቅ ብትንትኑ ወጣ።(ምንጭ-እንደላይኛው)

12) በግንቦት ወር በ1850 ዓ.ም አጼ ቴዎድሮስ ዋግ ሹም ገብረመድህን እና ቢትወደድ ብሩ የሚገኙበት ሰባት ሰዎች አጅግ እግራቸው ቆርጦ በገመድ እያነቀ ተንጠልጥለው እንዲሞቱ እንዳደረገ “አለቃ ዘነበ” ስለ አጼ ቴዎድሮስ በጻፉት መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅስዋል። 

13) ቴዎድሮስ ከደጃች ጓሉ ጋር ውግያ ለመግጠም በ1858 ወደ ጎጃም አቀና። ቀጥሎም የተማረከው ሕዝብ እንዳለ በጠቅላላ ወደ እንጂባራ ወስዶ አንገት አንገታቸው እንዲቆረጡ አዘዘ። የተቆራጩ ሕዝብ ብዛት ብዙ ስለነበር፤ ጭለማ ስለመጣ ፤የቀሩትንም መሬት እስኪነጋ እንዲቆዩ ተደረገና ሊነጋጋ ሲል ቴዎድሮስ ያልተቆረጡትን ወደ እኔ አምጡዋቸው ብሎ በማዘዝ፤ ቆረጣውን አስቁሞ እፊቱ ዘንድ እያየ “እየተቀጠቀጡ” እንዲሞቱ አደረገ። ሌሊት የተቆረጡትን ለማየት እየዞረ ሲጎበኝ አንድ ሰው ሲያጣጥር አይቶ’ ቆራጮቹን’ ጠርቶ ለካ ሳትገድሉዋቸው ነው የተውዋችቸው! ብሎ ሁሉን እራሱ እየዞረ ካረጋገጠ በላ ፤ሲፈራገጥ ሲያጣጥር የነበረው ሰውየ እራሱ ቴዎድሮስ ገደለው። (ሃለቃ ወልደማርያም- የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ገጽ 31)

14) አምቢታ ኣንፅር ወርርቲ በሚል የመምህር ገብረኪዳን ደስታ የትግርኛ መጽሐፍ እንደገጸው ይቀጥል እና ስለ አንጅባራ- እንዲህ ይላል፡

“አጼ ቴዎድሮስ በ1858 ዓ.ም አንጅባራ ከደጃዝማች ተድላ ጓሉ ተዋግተው ድል ካደረገ በላ በወቅቱ የተማረኩ ወታደሮችና እና የአካባቢው ኗሪ ወደ 20,000 እንደነበር ይገመታል፡ ቴዎድሮስም የተማረከው ሕዝብ እና ተዋጊ ሠራዊት በሰልፍ አስሰልፎ በጥይት እና በጎራዴ እየተደበደበ እንዲደገደል አደረገ።ጭፍጨፋው ከተጠናቀቀ በላም “ ጌታ ሆይ ጠላቶቼን እፊቴ ላይ እንዲወድቁ ስላደረግክልኝ ምስጋና ይድረስህ” ሲል መሬት ተሳለመ፡ ከዚያም አንዲት የጎጃም ሴት
     አንጠረኛው በዙ ከንጉሡ ቤት
     ባል አልቦ አደረጉት ይህን ሁሉ ሴት
           
 ሰትል ስትገጥምላቸው፡

ሌላ የጎጃም ሴት ደግሞ ፤-

ልቤንም ገረፈው ለበሰው እረኛ
በሬየንም ነዳው አረደው ነፍጠኛ
እህሌን ዘረፈው በላው ቀለብተኛ
ንጉሥ የቀረዎ ጥቂት አማርኛ
ምነው ሆድ አይዘርፍ አረፈ እንደተኛ
አገሬን ዘረፈው እያለው ደስ ደስ
ሞኙ ቤጌምድሬ ፈንታው እስኪደርስ (ምንጭ ሃለቃ ተክለየሱስ----- (እምቢታ አንጻር ወረርቲ- መምህር ገብረኪዳን ደስታ)

ክቡራን አንባቢዎች ‘አክራሪ አማራዎች እና መሰል አክራሪዎች” የኢትዮጵያን አንድነት ለማናጋት ሲሉ አማራ እና ትግሬን ለማናከስ ሲሉ አንዱ ካንዱ ንጉሥ እያበላለጡ ለዘመናችን የጎሳ ፖለቲካ ማዳበሪያ እያደረጉ “ዮሐንስ’ እንዲህ አደረገ እያሉ ሲያወሩ የኛ ብለው የሚጠሩት ቴዎድረስን ግን በጀግንንት ብቻ እየጠሩ ዮሐንስ አገር ከጂ እና ጨካኝ እያሉ ሚዘናዊ ባልሆነ ብዕር ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ጎሰኛ እና ኣናካሽ ውግዘት በመግባት እኛም ሳንወድ የምናከብራቸው ነገሥታት ገመና ለመተቸት ተገድደናል። በዮሐንስ ላይ እየተካሄደ ያለው ሆን ተብሎ የጎሳ ፖለቲካ ለማዳበር የሚደረገው ሴራ ካልቆመ ተጠቃሚዎቹ “ኢትየጵያን” ለመበተን የተሰለፉ የውስጥ ጣለቶች እንደሚሆኑ ላስገነዝባችሁ እፈልጋለሁ።

ከሊቀሊቃውንቱ ፕሮፌሰር ይሌ ያነበብኩት የሰሞኑ አዲስ ጠቃሚ መረጃ ስለ አጼ ዮሐንስ ማህትም አስደግፌ ልደምድም፡

ባለፈው ሰሞን ክቡር ፕሮፌሰር ጌታቸው ይሌ በ Ethiopanorama. Com  የአፄ ዮሐንስ ማኅተም (ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ)10/05/2018በሚል ያስነበቡን ነገር ላስታውሳችሁ።

ኢትዮጵያውያን እያስመሰሉ ስለሚጽፉ ጸረ ኢትዮጵያ ሃይላት እና የመሳሰሉ ግዴለሽ ኢትዮዮጵያውያን ጸሐፍትን በሚመለከት እንዲህ ይላሉ።

ንቄ ያለፍኩትን ርእስ እንድመለስበት ኅሊናየ አስገደደኝ። ጉዳዩ የአፄ ዮሐንስን ማኅተም ይመለከታል። የምጽፈው ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚጥረው ኤርትራዊው ተስፋየ ገብረአብ በአማርኛ በጻፈው መጽሐፉ ያደረገውን የታሪክ ማዛነፍ ለማቃናት፣ነው።በአሁኑ መጽሐፉ ውስጥ ካሰፈራቸው  እኩይ ትችቶች አንዱን ጠቅሼ ላስተባብል። እንዲህ ይላል፤
         “”አዲስ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አጤ ዮሃንስ ራሳቸውንየጽዮን ንጉስብለው ይጠሩ ነበር። በማህተማቸው መካከልም ዘውድ የደፋ አንበሳ ነበረ። የሸዋ መሳፍንት እንደሚያደርጉት ራሳቸውን ከሰሎሞናዊ ዘር ጋር የማቆራኘት ዝንባሌ ግን አልነበራቸውም። የአጤ ዮሃንስ የዘር ግንድ በቀጥታ ከአጤ ፋሲል ጋር የተያያዘ ነው። የፋሲል (የልጅ ልጅአምስተኛ ትውልድ የሆነችው) መና እስራኤል አያታቸው ናት። የአጤ ዮሃንስ ማህተም ላይ በአረብኛ የሰፈረው ጽሁፍ፣ንጉሰነገስት ዮሃንስ፣ ንጉሰ ጽዮን ዘኢትዮጵያ፣ ዘምነገደ እስማኤልይላል።እስማኤል ማነው?” የሚል ጥያቄ ሲነሳ የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ላይ አብርሃም አጋር ከተባለች ገረዱ ወለደው የተባለው ልጅ ስሙ እስማኤል ነበር።

የአቡነ ተክለሃይማኖት (ተክልዬ) የስጋ ዘመድ ይኩኖ አምላክ ዘሩን ቆጥሮና ተርትሮ ንጉስ ሰሎሞን ላይ ሲያደርስ፤ አጤ ዮሃንስ ደግሞ ተሸዋ ተረት ጋር ለመፎካከር በሚመስል መልኩ ከዚያም በላይ ርቀው የዘር ግንዳቸውን እስማኤል አብርሃም ላይ አደረሱት። አጤ ዮሃንስ ህጋዊ ሚስት ሃሊማ ሙስሊም ነበረች። አጤ ዮሃንስ ራሳቸውን ከአምላክ ጋር ለማገናኘት የእስማኤልን ሃረግ የተከተሉበት፣ ህጋዊ ሚስታቸውን ከሙስሊም ቤተሰብ የመረጡበት ስነ ልቦናዊ ምክንያት ምን እንደሆነ አይታወቅም። ዘእምነገደ እስማኤል የሚል ጽሁፍ የያዘውን የአጤ ዮሃንስን ማህተም ምስል ለመጀመሪያ ጊዜ አስተውሎ ትርጓሜ የሰጠው ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ነበር። ፍቅሬ ቶሎሳ እውነተኛ ታሪክ ውስጥ ልቦለድ የሚቀላቅል ግዴለሽ ታሪክ ጸሃፊ ቢሆንም የማህተሙን ፎቶግራፍ ስላተመልን መረጃውን እንቀበለዋለን።””አሁን ደግሞ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ስለ አፄ ዮሐንስ ማኅተም ምን እንዳለ እንይ፤
“”አጼ ዮሐንስ 4ተኛ ለአግአዚ-ሰሎሞናዊ ሐረጉ የሚጨነቅ አልነበረም። በዚህም ምክንያት እንደሌሎቹ አግአዚ-ሰሎሞናዊ ነገሥታት በማህተሙ ላይድል አድራጊው የይሁዳ አንበሳየሚል ጽሁፍ አላስቀረፀም። ሆኖም ራሱን የጽዮን ንጉስ ብሎ ይጠራ ነበር፤ በማሕተሙ መካከልም ዘውድ የደፋ አንበሳ ነበረው።

የአጼ ዮሐንስን ማሕተም ይመለከቷል፡ ማህተሙ የአረብኛ ጽሑፍ ነበረው። ጽሑፉንጉሠ ነገሥታት ዮሐንስ ንጉሠ ፅዮን ኢትዮጵያ፥ አምነገደ እስማኢልየሚል ነበር። እምነገደ-እስማኢልየሚለውን ጽሁፍ ሳይ ዐይኖቼን አላመንኩም ነበር። የገዛ ዐይኖቼን ተጠራጠርኳቸው። ሌሎች ሰዎች እንዲያነቡልኝ እስከመጠየቅም ደረስኩ። ሁሉምነገደ እስማኤልእያሉ አነበቡልኝ። እስካሁን አልተዋጠልኝም። ዐይኖቸ ቢሳሳቱ እመርጣለሁ። አጼ ዮሐንስን የአረብ ዝርያ ያላቸው ይመስል በማህተማቸው ላይ ለምን  “ነገደ እስማኤልየሚል ጽሁፍ አስቀረጹ?””

ይህን ጥቅስ  የፕሮፌሰር ፍቅሬ መጽሐፍ እንደወጣ አይቼ ንቄ ትቸው ነበር። እንደ እውነተኛ ታሪክ እየተጠቀሰ ሲታይ ግን፥ ዝም ማለት ተገቢ አልመሰለኝም።

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ከላይ የተቀስኩን ከጻፈ በኋላ፥ አንድ የማይነበብ የአጼ ዮሐንስ ማኅተም ፎቶግራፍ አንሥቶ ከመጸሐፉ ውስጥ አስገብቷል። ፎቶግራፉ ከወሰደበትና ከሌሎች ቦታዎች ስናየው የማኅተማቸው ጽሑፍ የሚለው እንዲህ ነው፤

ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ንጉሠ ጽዮን፤ መስቀል ሞአ ነገደ እስማኤል። (የጽዮን ንጉሥ ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ፤ መስቀል  እስላሞችን ድል ነሣ።)”

ነገሥታቱ ሁሉ በማኅተማቸው ላይ የሚጽፉት የየራሳቸው ቃላት ነበሯቸው። የአፄ ቴዎድሮስ፥ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያይል ነበር፤ ተጨማሪ አርማ አልነበራቸውም። ከአፄ ቴዎድሮስ በፊት የነገሡት ነገሥታት አርማቸው ምን እንደነበረ የሁሉም አይታወቅም። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን ነገሥታት አርማ፥ነግሡ፡ በጽድቅ፡ አብርሃ፡ ወአጽብሐ፡ ነገሥተ፡ ጽዮን” (የጽዮን ንጉሦች አብርሃና አጽብሐ  በትክክል ነገሡ) የሚል ነበረ።

ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ”  (የይሁዳ ነገድ አንበሳ ድል ነሣ) የሚል አርማ የጀመሩት አፄ ምኒልክ ናቸው።

አፄ ዮሐንስ ራሳቸውንንጉሠ ጽዮንማለታቸውም አዲስ ነገር ወይምአዲስ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙትየሚባልም አይደለም። ከነገሡበት ዕለት ጀምሮ የሚጠሩበት የሹመት ስማቸው ነው። ከዚያ ቀጥሎ፥ አርማቸው፥ ከላይ እንደጠቀስኩት፥ መስቀል ሞአ ነገደ እስማኤል” (መስቀል  እስላሞችን ድል ነሣ) ይላል። ከእስላሞች ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሻካራ እንደነበረ የታወቀ ነው ይህ አርማ ያንን ግንኙነት ያንጸባርቃል።

ራሳቸውን ዘእምነገደ እስማኤልብለው ግን አያውቁም። አንበሳው የሚያመለክተው የነገደ ይሁዳ  ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሆነ፣ ራሳቸውን ከቀደሟቸው ነገሥታት በምንም ረገድ አልለዩም።
የአፄ ቴዎድሮስና የአፄ ዮሐንስ ማኅተም በተጨማሪ በዐረቢኛ መሊክ አል-ሙሉክ አል-ሐበሻ የሚል አለበት፤ ንጉሠ ነገሥ ዘኢትዮጵያ ማለት ነው።” ጌታቸው ኃይሌ (የአፄ ዮሐንስ ማኅተም (ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ)10/05/2018 (Ethiopanorama. Com) 

አሁን አሁን ስመለከተው በጣም አክራሪ የሆኑ ከወያኔ ያልተናነሱ “የአማራ ፋሺስቶች” ቀስ በቀስ እየተባዙ መምጣታቸው አሳሳቢ አድርጎኛል። በተለይ ወጣቶች ስላሉበት አሳሳቢ ነው። ውጭ አገር ቢኖሩም የፋሺስት ትምክህታቸው አገር ላሉ ወጣቶች ሊበክል ይችላል። አንዳንዶቹም በሚገርም ሁኔታ የታወቁ አማራ ወጣት ምሁራን በዚህ ጨዋታ ውስጥ እየገቡ ይመስላሉ። አንድነታችን ለማራራቅ የጎሳ ቤንዚን በማርከፍከፍ ክርቢት ከሚጭሩት ስሜታቸው ልቅ የሚያደርጉ አማራ ወገኖች እየተራቡ መጥተዋል። በዚህ መልክ በዮሐንስ ብቻ የሚዘምቱ ጎሰኞች ስላሉ እና ዮሐንስ አማራን ይጠላል እያሉ ያልተደረገ ያልነበረ ፈጠራ እየሰሩ የንጉሡን ስም ጥላሸት መቀባት ስለተጀመረ፤ ይህ ካልቆመ ሁሉም ነገሥታት ገመና ስላላቸው “ለዮሐንስ ሐውልት ይነፈገው ከተባለ፤ ለቴዎድሮስም ለምኒሊክም ለሃይለስላሴም አይገባቸውም” ወደ እሚል ክርክር ስለምንገባ፡ ይህ አክራሪነትና ጎሰኛነት ካሁኑኑ ይቁም!
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) getachre@aol.com

      



No comments: