Saturday, May 5, 2018

መልስ ለሰማያዊው ፓርቲ መሪ ይልቃል ጌትነት ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)



መልስ ለሰማያዊው ፓርቲ መሪ ይልቃል ጌትነት
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)
የአንዳርጋቸው ዓረዓያነት ናፈቀኝ!!! በሚል ርዕስ በየድረገጾች የተለጠፈው ጽሑፍህ በአግራሞት ተመለክቼዋለሁ። ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ የኢሳያስ አፈወርቅ  ይነት ‘እጆቹ በሰው ደም የታጠበው’ በጦርነት ሙርኮ ጊዜ አማራዎችን ለብቻቸው ለይቶ ልዩ ፋይል አዘጋጅቶ ለሲኦል ስቃይ የዳረገ ኢሳያስ አፈወርቅን (የ ‘ዋ ምጽዋ’ ፣ጽሐፍ  ደራሲ የመቶ አለቃ ታደሰ ቴሌ ‘ከ ሲ ቢ ኤስ ራዲዮ አውስትራሊያ’ ጋር እምባ የታጀበ ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ አድምጡ) ጸረ አማራው ሰውየ መሪያችን እንዲሆን የተመኘልንን ‘አንዳርጋቸው ጽጌን’ በአካል አላውቀውም ብትልም በጽሑፉና ባደረጋቸው ንግግሮቹ ተገንዝበህ እንደናፈቀህ እና እንደ እሱ የመሆን ፍላጎት እንዳደረብህ ሰው ምን ይለኝ ይሆን ሳትል በድፍርት በመጻፍህ ‘ድፍረቱን’ ባደንቅልህም ብስለትህ ግን የጫጨ መሆኑን አሁን ሳይሆን ባለፈው ወቅት አውጭ አገር ስላሉ “አክራሪ አማራዎች” ስለምትላቸው ዜጎች ከተናገርክ ጀምሮ መዝኘሃለሁ። 

“በህይወቱ የተጉዋዘውን ጠመዝማዛና ውጣ ውረድ የበዛበት መንገድ አስታውሰህ በጣም ከመደቀነቅህ አልፈህ የሱን ዓይነት ሰው እንደናፈቀህ” ገልጸሃል። የሱን ዓይነት ሰው ከምትናፍቅ እራስህ የሱን ቦታ ተክተህ ወደ ኤርትራ ምድር ሄደህ “አማራዎችን እና ጠንካራ ያድርጅቱ ታጋዮችን በስየል (ቶርች) መሰቃየት እና ከነ ኮለኔል ፍጹም ጋር ሆነህ ዜጎች እንዲሰወሩ ማድረግ፡ ከዚያም አልፎም የአርበኞች ግምባር መሪ የነበረው የአየር ሃይል አብራሪው ኮ/ል ታደሰ ሙሉነህ ……የታሰረበትን ምክንያትሌላ ሳይሆን “ኢሳያስ አፈወርቂን ከሥልጣን ለማስወገድ በተሞከረው ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር በተያያዘ መሆንን በውሸት መስበክ ካማረህ፤ ወደ አስመራ ተጉዞ የአንዳርጋቸውን ቦታ መያዝ ናፍቆትህ ባጭሩ ሊያስታግስልህ  ይችላል የሚል ምክር አለኝ። አንተ እንደ አንድ የታወቀ ወጣት የፖለቲካ ድርጅት መሪ ለእሱ እንዳዘንክለት ሁሉ በእርሱ እጅና በእርሱ የበረሃ የሥልጣን ዘመን የተሰቃዩ መኖራቸውንም ጭምር ማስታወስ በተገባህ።

አስገራሚው ደግሞ “ለእኔና ከእኔ በታች ላሉ ትውልዶች ዓርዓያነቱ በጣም ከፍተኛ ነው።” ብለሃል። አለፍ ብልህም፤ “….እስካሁን ድረስ ከፃፋቸውና ከተናገራቸው መገንዘብ ይቻላል።” ብለሃል። እስኪ  ምን እንደጻፈ እና እንደተናገረ ለአንባቢዎችህ ላስታውስልህ።

*.....በዚህ የሸዋ መኳንንት የግዛት መስፋፋትና ሕዝቦችን የማስገበር ዘመቻ ነበር የውጭ ሀይሎች የተለያዩ ብሄረሰቦች ድርሻ የየራሳቸው የታሪክ ዝርዝር የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ሳንረሳ በዋናው ቁምነገር ላይ ሰናትኩር የሀገሪቷ ምስረታ በአንድ ብሄር መሳፍንት በዋነኛነት ያውም በአንድ ክልል በሚገኝ የሸዋ አማራ መሳፍንት የሀይል እርምጃ የተከናወነ ነበር ማለት ይቻላል:(ገጽ9) 


*.....ሁላችንም እንድምናውቀው አሁን በአገሪቷ የሚገኙ ሕዝቦች በአንድ ማዕከላዊ መንግስት አስተዳደር ሲገቡ ሕዝቦች ፈቃዳቸው እየተጠየቀ በቅርቡ የአውሮፓ የጋራ ማኅበረሰብ ሕዝቦች እንድሚያደርጉት ሬፍረንደም እየተካሄደ በጋራ በተስማሙባቸው ወሎች አማካኝነት አልነበረም::(ገጽ-9)አንዳርጋቸው-ጽጌ-የአማራው-ሕዝብ-ከየት-ወዴት?
1985
.


*
በታሪካችን ውስጥ ሁሉንም ብሄሮች በጋራ ሰሜት የሚያስተባብሩ ታሪካዊ ክስተቶች አልነበሩንም ማለት ባይቻልም : ለምሳሌ የአድዋ ጦርነትና የአምስት ዓመት ጸረ ጣሊያን ተጋድሎ በዋነኛነት የመቶ ዓመት ታሪካችንን የሚገልጸው የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በእሳትና በብረት ገብረው : በእሳትና በብረት ሲጠበሱ በመኖራቸው የሚሰማቸው ቁጭትምሬትሐዘንናጸጸት-ነው::(ገጽ11-12) 

*
አንዳንዶቻቸን ብሄራችሁ ተብለን ስንጠየቅ ያለምንም ማመንታት አማራ ኦሮሞ አፋር ትግሬ ወዘተ ብለን ያለምንም ጭንቀት እንመልሳለን :: አንዳንዶቻቸን ተመሳሳይ ጥያቄ ሲቀርብልን ለምን ብሄር የሚባል ነገር ይነሳል ? ለምን ይህ ጥያቄ ያስፈልጋል ? ብለን የምንቆጣ አለን :: ለምን እንዲህ አይነት ጥያቄ ተጠይቅን በማለት ተናደን የሄድንበትን ጉዳይ ሳናሳካ የምንመለስም አለን :: ብሄር ሲባል ኢትዮጵያዊ ብለን የምንመልስም ሞልተናል :: (ገጽ 13) 


*
ግር የሚያሰኘው ብሄሩን ሲጠየቅ ኢትዮጵያዊ የሚለው ወይም ለምን ተጠየኩኝ ብሎ የሚቆጣው ነው። (ገጽ 14)

* ብሔርየ ኢትዮጵያዊ  ነው የሚለው ብሔሩን ሲጠየቅ ኦሮሞ ትግሬ አማራ ወዘተ ነው ብሎ የሚመልሰውን ሌላውን ኢትዮጵያዊ እንዴት ሊያየው ነው? ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ሀገር መሆኗን መካድ የማይቻል እውነታ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያዊነትን ለምን የብሔር መግለጫ አድርገን ለመውሰድ እንሞክራለን ? በኢትዮጵያ የተለያዩ ብሄርና ብሄረሰቦች እንዳሉ በእነዚህም ሕልውናቸው ገሀድ በሆኑ ብሔረሰቦች ዙሪያ የነበረና ያለ ብሔርተኘነት ዋነኛው የኢትዮጵያ ሕዝቦች መገለጫ ሆኖ ሳለ ብሔርህ ወይም ብሄርሽ ምንድን ነው ስንባል የምቆጣውለምን እንጠየቃለን የምንለው ለምንድን ነው? ችግሩ ከጠያቂው ነው ወይንስ ለምን እጠየቃለሁ ከሚለው ? (ገጽ 14)


*የተጋቡ የተዋለዱ ሰዎች እንዳሉ በናስቀምጥም በኢትዮጵያ የሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ እነዚህ ተዋልደናል ተጋብተናል የሚሉት ግለሰቦች እንድሚሉት ጋብቻና መዋለድ መላ አገሪቱን የቆላለፈ ጉዳይ አይደለም በአዲስ አበባና በአንዳንድ የደቡብ የአገሪቱ ከተሞች በመሳፍንቱና በባላባቱ በተለያዩ ብሔሮች መሀከል የሚታየውን ጋብቻ ብቻ ወስደን የሀገሪቱ ዋነኛ መግለጫ ማድረግ ሰህተት ነው :: (ገጽ 16 )


*.......ኢትዮጵያ ዳርድንበሯ ዓለምአቀፍ እውቀና አግኝቶ አሁን በውስጧ የተካተቱ የተለያዩ ብሄር ብሔረሰብ ሕዝቦች የያዘች በተማከለ መንግስት የምትተዳደር አገር ከሆነች አንድ ምዕተ ዓመት-አልፏል።(ገጽ9)  
 
አንዳርጋቸው-ጽጌ-የአማራ-ሕዝብ-ከየት-ወዴት?
1985
.

*በዚሁ አኳያ የብሔር ጥያቄ ሲነሳ ከላይ ባስቀመጥናቸው ምክንያቶች ጭንቀት ወስጥ እየገቡ ለምን ጥያቄው ይነሳብናል: ወይም የሌለ ብሄር ብሔረሰብ የሚል ጣጣ አምጥታችሁ በማለት በምኞት ሊቀየር ከማይችል እውነታ ጋር የሚጋጩ ወገኖቻችን ጉዳዩ የደም የአጥንት አለመሆኑን ሊያውቁት ይገባል። የየግል ወይንም የቤተሰብ ወሳኔያቸውን ያለምንም መሸማቀቅ ሊወስኑ እንደሚችሉ መረዳት አለባቸው  በእንዲህ ዓይነቱ ነጻ ወሳኔ ለሚደረግበት የአማራነት ምርጫ የአማራው ህዝብ ታላቅ ከበሬታን እንድሚሰጠው አንጠራጠርም :: (ገጽ 31)  ከአንዳርጋቸው ጽጌ -የአማራው ሕዝብ ከየት ወዴት? ከሚለው መጽሀፉ የተወሰደ።


አስገራሚ የሚሆነው ደግሞ ታማኝ በየነ ኢሳት ከመባሉ በፊት ‘ኢ ቲ ኤን’  ሲባል የነበረው ሚዲያ አንዳርጋቸውን ጋብዞ በመጀመሪያዎቹ ወያኔ ወደ ስልጣን በመጣባቸው ሁለት ዓመታት ከወያኔ ጋር አብሮ “የወያኔ/ኢሕአዴግ/ የፖለቲካ ርዕዮተ አለም የፕሮፓጋንዳ ዋና ሓላፊ ሆኖ ሕዝባችን ሲያተራምስ፤ታሪክ ሲየጣምም በነበረባቸው ጊዚያት ለጌቶቹ ለወያኔዎቹ እጅ መንሻ እንዲሆነው ከላይ ያነባበችሁት የአማራ ሕዝብ ከየት ወዴት (የመለስ ዜናዊ ‘የኤርትራ ሕዝብ ከየት ወዴት’ ትክክለኛ የርዕስ ቅጅ - (አባዱላ ገመዳ ደግሞ “የኦሮሞ ሕዝብ ከየት ወዴት- የመለስ ትክክልኛ የርዕስ ቅጅ) መፅሀፍ ፅፎአማራን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀገሩን በአደባባይ በይፋ ይቅርታ ትጥቃለህ ወይ? የሚል ጥያቄ ሲቀርብለት “አሁንም ይህ መጽሐፍ በመጻፌ ኩራት ይሰማኛል፤ይቅርታ አልጠይቅም” ሲል ነግሮናል። ያ ሁሉ እያወቀም ቢሆን ‘ታማኝ በየነ’ ለራሱ የተሸለመው የአንበሳነት ሽልማት ከአንገቱ አውልቆ የገዛ ሽልማቱን ለአንዳርጋቸው ጽጌ “የኔ አንበሳ” ብሎ ሸልሞታል።

 “ብሩህ አዕምሮ ያለው ሰው” ሰትል ያደነቅከው ሰውየ፤ ሀገራችንን የወረረውን አደግዳጊነትን የመጀመሪያው ሰው እንደነበረ እና አሙዋሙዋቂነትን እባ የወያኔና የዋለልኝ ጥራዝ ነጠቅነት ባህሪ የተላበሰ አድር ባይ ፖለቲከኛ መኖሩ እና ኢትዮጵያውያን እንጂ ብሔር የለንም ላሉ ሰዎች ከፍተኛ የሕሊና ስብራት ያደረሰ ሰው ከመሆኑ አልፎ “ኢትዮጵያ የ100 አመት ዕድሜ ያላት የሀገሪቷ ምስረታም የተከናወነው  በአንድ ብሔር መሳፍንት በዋነኛነት ያውም በአንድ ክልል በሚገኝ የሸዋ አማራ መሳፍንት የሀይል እርምጃ የተከናወነ ምስረታ መሆኑን እንዳንተው ላለው ዓድናቂ ለሆነው የዋህ አዲስ ትውልድ  ያስተማረ ፦   አገሪቱም በአማራዎቹ ነፍጥ እንጂ  በሬፈረንደም በዲሞክራሲ ባለመገንባትዋ እንዳንተው ዓይነቱ የአንዳርጋቸው ፕሮፓጋንዳ ናፋቂ ትኩስ ሃይል እንዲህ ሲል አስረምሯል 

 *.....ሁላችንም እንድምናውቀው አሁን በአገሪቷ የሚገኙ ሕዝቦች በአንድ ማዕከላዊ መንግስት አስተዳደር ሲገቡ ሕዝቦች ፈቃዳቸው እየተጠየቀ በቅርቡ የአውሮፓ የጋራ ማኅበረሰብ ሕዝቦች እንድሚያደርጉት ሬፍረንደም እየተካሄደ በጋራ በተስማሙባቸው ወሎች አማካኝነት አልነበረም “ (ገጽ 9 )

   ወረድ እያልኩ የይልቃል ጽሑፍ ሳነብ እያደር አስገርሞኛል። አንዲህም ይላል፡
በአጠቃላይ አንዳርጋቸው በስብዕና ጉድፍ በዝርክርክነትና አማካኝነት ለሚዋዥቀው ለእኔ ትውልድ አስተማሪነቱና ዓርዓያነቱ በጣም ከፍተኛ ነው።እንደ አንዳርጋቸው አይነት በብዙ መልኩ የጠራ ስብዕና ያለውና ለትውልድ ምሳሌ የሆነ ሰው በመከራ ቤት ሆኖ ተገቢውን ትኩረት አለማግኘቱ የምንገኝበትን የሞራል ዝቅጠት የሚያሳይብን የተግባር ምሳሌ ነው።” ብለሃል።

መታሰሩን እና ይፋ የሆነ ፍርድ ቤት ቀርቦ ውሳኔ ባለማግኘቱ ወያኔ የሚያስጠይቀው ክፉ የፍትሕ ብልሽነቱን ያሳያል። ከወያኔ ጋር ሆነው ሲሞዳሞዱ የነበሩ ስርዓቱን እንዲያ ጨካኝ እንዲሆን ያዋቀሩትን እንደ እነ ታምራት ላይኔ፤ ስየ አበርሃ አሁን ደግሞ አንዳርጋቸው የገዛ ያዋቀሩት ስርዓታቸው ሰለባ ሲሆኑ ያሳዝናል። ግን የኔ ወንድም ያንን እንዳለ ካንተ ጋር ብስማማመም። በእርሱ ላይ ሲደርስ ነው እንዴ ሰዎች በመራል ዝቅጠት መወቀስ ያለባቸው ወይስ በእራሱም ጭምር በተሰቃዩ ሰለባዎቹንም ያለማስታወስ ጭምር? ወያኔ አዲስ አበባ ገብቶ ወደ ሚሊዮን የሚሆኑ ወታደሮችና (የወታደሮች በተሶባቸውብ ተደምሮ) በረንዳ ላይ መለዮአቸው እና ማእረጋቸው በረንዳ አፍ ላይ አንጥፈው ቁራሽ አንጀራ ሲለምኑ በወቅቱ አንደርጋቸው ከእንግሊዝ አገር ተንደርድሮ ወደ ወያኔ ሲገባ ምን የሚሉት የሞራል ብቃት ነበረው? የሚለው ጥያቄ ማቅረቡ አንተ የሞራል ዝቅት አለብን ለምትለው ጥያቄ አብሮ የወቅቱ የእንዳርጋቸው የሞራል ዝቅጠት አብሮ ለመፈተሽ ያመቻል። 

እነዚህን ወታደሮችና ቤተሰቦቻቸው ከሥራቸው እተመነቀሩ ለልመና ብቻ የተዳረጉ አንዳይመስልህ፤ በየጎዳናው እንደ ‘የበረሃ ሚዳቋ’ በጥይት ሲታደኑ ነበር።ከታደኑት ሁሉ አንደኛው ልጥቀስ።  ኢትዮፕያን ረጅስተር’ በመባል እኔ በምኖርበት አካባቢ እዚህ ሲታተም በነበረው መጽሄት ያወጣው አንዳርጋቸው በወቅቱ የወያኔ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪ ሆኖ የዜጎች ሰብአዊ መብት ሲረግ ወይንም ሲአስረግጥ በነበረበት ወቅት በመጽሔቱ የተዘገበ ዘገባ የወቅቱ የአንዳርጋቸው ሞራል ልትነግረኝ ትችል እንደሆነ ልጥቀስ፦

 “ሠላም እና ዲሞክራሲ ሰፍኖባታል በተባለላት ሃገር ይህን የመሰለ ከሕግ ፥ ከሞራል እና ከሰብአዊነት ልጓም ያፈነገጠ፥ፍፁም አረመኔ ድርጊት ይፈፀምብኛል የሚል እምነትም ይሁን ግምት አልነበረብኝም። ለ14 ቀናት ሙሉ ሳይቋረጥ ሌሊት ከተኛሁበት ክፍል እያስወጡ የሽጉጥ አፈሙዝ ላንቃየ ድረስ እየሸነቀሩ፥እግሮቼን በኤሌክትሪክ “ኮረንቲ” እያስነኩ አግሮቼ ሁሉ ለመግለጽ በሚያስቸግር ስሜት እንደመብረቅ እሳት ሲያቃጥለኝ፤ ‘የመንግሥት ያለህ! ስለ እግዚአብሔር እባካችሁ!” ብልም እየሳቁ መልሰው ያንኑ ይደጋግቡኝ ነበር።

ቀን ሲሆንም ከስቃየ ለማጋገም እንቅልፍ እንዳልተኛ ከታሰርኩበት ክፍል እያስወጡ ወደ አንድ የተሰወሰነች ቦታ ጎትተው ሙሉ ቀን ዙርያውን እንድዞር አድርገውኛል። አከላቴ ሁሉ ደክሞ ተዝለፍልፌ ባለሁበት ሁኔታ ‘እንዳርፍ” ብለምናቸውም መልሰው በዱላ ይቀጠቅጡኛል። በዚህ ምክንያት እግሮቼ ላይ ባሉት ጅማቶች የመሸማቀቅ ጉዳት ደርሰውብኛል:: 


(ታለጌታ ልዑል ዳኜ ሃይለማርያም- ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳቱን ለትግሬ ዳኞች ሲያስረዳ ጋዜጠኞች ከዘገቡት ቃል በኢትፕያን ረጅስተር “ውሻ ነከሰኝ ተብሎ ለጅብ አይነግሩም’ በሚል ርዕስ የተዘገበ፤ በሓይካማ መጽሐፌ ላይ በገጽ 2 በትግርኛ የተጠቀሰ ምንጭ) 
  

“ውሻ ነከሰኝ ተብሎ ለጅብ አይነግሩም’ የሚል ርዕስ የተዘገበበት ምክንያት የዛሬ ወጣቶች ግራ አንዳይገባችሁ ታሪኩ እዚህ ላክልበት። ታሪኩ የተገገኘው ከላይ ያነበብነው አቤቱታ አቅራቢ ስሞታ በተሰማበት የፍርድ ችሎት ቀርቦ በነበረበት ዕለት ነው ሌላ ተከሳሽ ደግሞ አቤቱታ ሲያቀርብ ከተናገረው ታሪክ የተገኘው ነው። ነገሩ እንዲህ ነው። 

“* የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የወንጀል ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ትግሬ ናቸው። አቶ ሓጎስ ይባላሉ። እሳቸው የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕረሲዳንት ናቸው። ተከሳሹ በግድያ ወንጀል ዳኛ ተከስሶ ከእሳቸው ችሎት የቀረበው ይህ ተከሳሽ እንዲህ ሲል ለፍርድ ቤቱ መልስ ይሰጣል፦

“ገደልከው የተባልኩት ሰው ባለቤቴን በውሽምነት ይዞ ሲያማግጥ የነበረ ባለጊዜ ትግሬ ነው። የገደልኩትም እጅ ከፍንጅ ይዤው ነው። ለምን ገደልከው እያሉ ትግሬ ፖሊሶች ሲያበሻቅጡኝ ቆይተዋል። መዝገቡን ከፖሊሶች ተረክበው ሲያሰቃዩኝ የነበሩት መርማሪዎች ትግሬዎች ናቸው።መዝገቡንም ከፖሊሶች ተቀብሎ የከሰሰኝ ትግሬ ዐቃቤ ሕግ ነው። ወህኒ ቤት የሚጠብቁኝም ትግሬ ፖሊሶች ናቸው።…….እያለ ስሞታውን እያስሰማ እያለ ክሱን ሊያዩ የተሰየሙት ሰብሳቢ ዳኛ ጣልቃ ገብተው ሊያስቆሙት ይሞክራሉ።
 ተከሳሹም “*እኔ የምናገረው በግራና ቀኝ ለተቀመጡት ዳኞችን ነው፡ ላንተ እማ “ውሻ ነከሰኝ ተብሎ ለጅብ አይነግሩም የሚባለው አይነት ነው።” አላቸው። (ምንጭ እንደላይኛው (ይድረስ ለጎጠኛው መምህር መጽሐፌ ዝርዝሩ ተገልጿል። ገጽ 153) 

ይህ ሁሉ ታሪክ ወንድማችን ኢንጅኔር ይልቃልም ሆነ ለመሰል ሰዎች ላስታውሳችሁ የምፈልገው ይህ ሁሉ ጉድ ሲደረግ አንዳርጋቸው ከወያኔ ጋር ሆኖ ዜጎች ሲጮኹ ምንም ያልተሰማው ያውም መጽሐፍ እየጻፈ ከነሱ ጋር ሆኖ ሲንደፋደፍ የነበረ ሰው መሆኑንን ለማስታወስ እና አሁን “የሞራል ዝቅጠት” አለብን ለምትለው መልስ ለመጠየቅ ነው። አንዳርጋቸው በመጽሐፉ ውስጥ “ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ” ሲል የጻፈው መጽሐፉን ስታደንቅ “ሰብአዊነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ” ተብሎ አንዳርጋቸው ቢተች ቅር ይልሃል? ያውም ስለ አማራ እና ስለ ኢትዮጵያ የጻፈው “አሁንም እኮራበታለሁ” ብሎ ለተመጻደቀብን ሰው! 

ወንጀል የሰሩም ፤በግርፋትም፤ በሞራል ስብራትም ከወያኔ ጋር የተባበሩ ሁሉ ወደ “አምበሳነት” እና ነፃ አውጪነት እየተሾሙ ቅባቱን እየተቀቡ በቀጠሉ ቁጥር ሰብአዊ መብት ረገጣ የተፈጸመባቸው “ሰሚ እንዳያገኙ” የሚደረገው ሴራ እና ለበደሉት ሴራ “ይቅርታ ሳያደርጉ ያውም ለሰሩት ስራ ለሚኩራሩበት” ሁሉ አጥብቀን እንቃወማለን። በሆሆታ ዝም ማሰኘት ይቻላል። ታዋቂ ምላሰኞች መድረክ ላይ እየወጡ፤ እነዚህን ሰዎች ‘አንበሶችም ፥ ነፃ አውጪዎችም ፥ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎችም” ማድረግ መብታቸው ሊሆን ይችላል; የኛ መብት ደግሞ የተቃራኒው ቆመን የተበደሉትን ሰዎች አምባ አማስተጋባት እና ጩሖታቸው እንዳይረሱ ማድረግም መብታችን የተከበረ ነው። 


ሌላው ማሕደር ልጨምርልህ እና በሚከተለው ሰነድ ጽሑፌን ላሳርገው።
አንዳርጋቸው ጽጌ ኤርትራ በነበረበት ወቅት እርሱ ያሰቃያቸው ታጋዮች ሸሽተው መጥተው ምን እንዳደረጋቸው እና ከማንስ ጋር ይውል እንደነበረ በአውድዮ እና በጽሑፍ የተላለፉ ዘገባዎች አድምጠሃል? አንብበሃል? ሌላ ቀርቶ እነዚህ ሰዎች ከበረሃ ሸሽተው ከመጡ በኋላ ኢሳት ለተባለው የግንቦት 7 አፈቀላጤ ሚዲያ በአካል ቀርበው ከአንዳርጋቸው እና ከብርሃኑ ነጋ ጋር የደረሰባቸውን በደል እንዲጋፈጡዋቸው ሁሉንም ወገኖች እንዲጋብዙዋቸው ደብዳቤ ጽፈው ሲጠይቁዋቸው ፤ ኢሳት ሆየ! ጓዶቻቸውን አነ ብርሃኑ እና አንዳርጋቸው አንዳይጋለጡ በመስጋት ‘መድረክ’ እንደከለከሉዋቸው አንብበሃል? አድመጠህ ታውቃለህ? እስኪ የኔን ካላመንከው የሰብአዊ መብት ጠበቃ የሆነው “ያሬድ ሃይለማርያም” ለኢሳት የጻፈውን አንብብ፡

የግንቦት 7 የግፍ ተግባር እና የመገናኛ ብዙሃን ዝምታያሬድ ኃይለማርያም   (ጥር 29 ቀን 2006 ..ከብራስል) Human Rights in Ethiopia)


ወይንም Ethio media Forum (EMF) የግንቦት 7 የግፍ ተግባር እና የመገናኛ ብዙሃን ዝምታያሬድ ኃይለማርያም ጉል ብታደርግ ታሪኩን ታገኘዋለህ።

ኢንጅኔር ይልቃል ጌትነት የአንዳርጋቸው አርአያነት ከናፈቀህ ኤርትራ መሄድ እና ሲሰራቸው የነበሩትን ሥራዎችን ተክትህ መስራት ትችላለህ። ወደ ሥልጣን ግን እንድትመጣ አልጸልይም። ይህች አገር እንዲህ ዓይነቱ ናፋቂ ወጣቶች ሲበቅሉባት ዕጣ ፈንታዋ ምን እንደሆነ ለኔ እጅግ እየጠበበኝ መጥቷል።
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

No comments: