Sunday, June 5, 2016

አበበ ተ/ሃይማኖት/ጆቢ ማን ነው? የሚቀጥለው ግፍ ከፈጸሙት ወያኔዎች አንዱ ነው! አቅራቢ ጌታቸው ረዳ (የኢትጵያን ድረገጽ አዘጋጅ/ Ethiopian Semay)June, 02/2016

አበበ ተ/ሃይማኖት/ጆቢ ማን ነው? የሚቀጥለው ግፍ  ከፈጸሙት ወያኔዎች አንዱ ነው!
አቅራቢ ጌታቸው ረዳ (የኢትጵያን ድረገጽ አዘጋጅ/ Ethiopian Semay)June, 02/2016
 

Photo-General-Abebe-Teklehaimanot
Photo-Getachew Reda (Editor Ethio Semay)
ኪዚህ በታች የቀርበው ማሕደር የተገኘው ሓይካማ ከተባለ የትግርኛ መጽሐፌ ወደ አማርኛ ተርጉሜ ለአማርኛ አንባቢዎች እንዲመች አቅርቤዋለሁ። ከዚህ በታች የቀረበው ማሕደር በቅርቡ ስለ ዓሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ ይገባታል ጉዳይ ከሪፖርትር ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል ተብሎ በዘ-ሐበሻ ድረገጽ ተለጥፎለት የነበረው ወያኔው ሜ/ጀኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት በተያያዘ ጉዳይ ነው።እንዲህ አምሮባቸው፤ አሸብርቀው፤ ሰው መስለው ፤ወታደራዊ ማዕረግ ለብሰው ሰለ አገርና ስለ ሰው ልጅ መብት ዘብ የቆሙ መስለው ቢታዩም፤ እነኚህ ወያኔዎች ከነመሶሎኒ እና ከጀርመን ናዚዎች ጋር የሚያመሳስላቸው ብዙ አውሬ የሆነ ባሕሪ አላቸው። ለማያውቀቸው “ሰው መስለው” ስለሚታዩት ፤ ብዙ የዋህና ግንዛቤ የጎደለውን ሰው ማሞኘት ችለዋል። ከለበሱት ልብስ በታች የተቀበረው ባሕሪያቸው ስትፈትሹ ግን የትግሬ “ሰው መሰል አራዊቶች” በአዛውንቶችና በህጻናት ላይ ሲወስዱት የነበረው የጭካኔ ዓይነትና የተላበሱት አረመኔአዊ ማንነት ማየት ትችላላችሁ።

ያ ሁሉ ግፍና ወንጀል ሰርተው፤ ተጠያቂነት ሳይኖራቸው፤ ዛሬም ለ25 አመት ጫካ ውስጥ ሲያካሂዱት የነበረው አረመኔነት ቀጥለውበታል። እነሱን የሚፈትሽ ‘ፍርድ-ቤት” ይቋቋም ብለው በረሃ የተሰቃዩና የተገደሉ ወገኖቻቸው ባደባባይ ለነ ገብሩ አስራትና ለመለስ ዜናዊ ለነ ስብሓት ነጋ ቢጠይቁም “በረሃ ላይ የሰራነው ወንጀል አንጠየቅበትም” በማለት ጥቅርታ ሳይጠይቁ በማን አለብኝ መልሰውላቸዋል። የትግሬና (ወያኔዎች) የኦሮሞ (ኦነግ) ሰው መሳይ አራዊቶች በኢትጵያ ዜጎች ላይ የፈጸሙት ግፍ ዘግናኝ ነው። ይኼውና ወያኔዎች የሚመጻደቁበት ከናዚዎች ጋር የሚያመሳስላቸው ተጠያቂነት የሌለው ባቸው እንድትፈትሹት ማሕደሩን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ። የወያኔዎች ጭካኔ የትግራይ አዛውንት አንደበት ንዲህ ይገልጹታል። መልካም ንባብ።
በእሳት እና በፈላ ዉሃ እያቃጠሉ መረመሩኝ

የህዝባዊ ሓርነት ትግራይ ሰለባ ከሆኑት ከፊታዉራሪ ገዛኢ ረዳ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ፤

(ጌታቸዉ ረዳ - ሳን ሆዘ - ካሊፎርኒያ -አሜሪካ)


“…በወቅቱ “ኢድዩ” ወደ አካባቢዉ በብዛት ሰራዊቱን ይዞ እየገሰገሰ በፍጥነት ስለመጣ በድንገት ስለደረሰባቸዉ ወያኔዎች ተደናገጡ። ኢዲዩ መጥቶብናል እና እንግደላቸዉ ብለዉ እኛን ለመግደል ወያኔዎቹ ሌሊትኑ ወደ ታሰርንበት ዳስ ክፍል ገቡ እና አስወጥተዉ በተራ አስሰለፉን።“አዛዉንቱ አቶ ገብረሊባኖስ መዝገቦም ሲመረምሩዋቸዉ ሰዉነታቸዉ በሞላ በእሳት እያቃጠሉ እየደበደቡ ስላደከሙዋቸዉ / መራመድ ስለማይችሉ ልንሸከማቸዉ አንችልም ብለዉ አቶ ገብረሊባኖስ መዝገቦን በእንቅልፋቸዉ ተኝተዉ እንዳሉ በሦስት ጥይት ገደሏቸዉ። የገዛ ታጋያቸዉም በሃይለኛ ወባ ተይዞ ተኝቶ ስለነበር አሱንም አንሸከመዉም ብለዉ በጥይት ገደሉት…።” ገዛኢ ረዳ። ከቃለ መጠይቁ የተወሰደ። ዝርዝሩ እነሆ።

አቶ ገብረሊባኖስ መዝገቦ ማን ነበሩ? የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ (ጌታቸዉ ረዳ) አማች የነበሩ ናቸዉ።

ቃለ መጠይቁን ያዘጋጀዉ ዶክተር ሃይለማርያም አበበ-(ከደጀን-ራዲዬ)፡ተርጉሞ ወደ ጽሁፍ መድረክ ያዘጋጀዉ ጌታቸዉ ረዳ።
 
ደጀን ራዲዮ፦

ጤና ይስጥልኝ በመጀመርያ ሰላምታየን አቀርባለሁ አቶ ገዛኢ ረዳ። የደጀን ራዲዮ እንግዳ ሆነዉ በተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ የደረሰበዎት ግፍ በመላዉ ዓለም ለሚያዳምጡን የትግርኛ ፕሮግራም አድማጮች ለመግለጽ ፈቃደኛ ሆነዉ በመቅረብዎ በራዲዮ ጣቢያችን እና በደጀን ራዲዮ አድማጮች ስም አመሰግናለሁ። አቶ ገዛኢ ረዳ የትግራይ ተወላጅ ነዎት፡ በትግራይ ክፍለ ሃገር ዉስጥ ወያኔዎች ሲይዙዎት የመጨረሻዉ ስራዎ በምን ስራ ላይ ተሰማርተዉ ይኖሩ ነበር?
 
አቶ ገዛኢ ረዳ፦

ትዉልዴ የትግራይ ተወላጅ ነኝ።በመንግስት ስራ ገና በወጣትነቴ ጀምሬ ለብዙ ዓመታት በአገር አስተዳደር ጽ/ቤት ዉስጥ በልዩ ልዩ ክፍሎች ተመድቤ ሰርቻለሁ።መጨረሻ ወያኔዎች ሲይዙኝም በትግራይ ክፍለሃገር በአገር አስተዳደር ሚኒስቴር ሥር በሽሬ አዉራጃ በምኖርበት በዋናዉ ከተማዋ በእንዳስላሴ ከተማ በአዉራጃዉ አስተዳደር ጽ/ቤት ዉስጥ ነበር ስራየ።

ጥያቄ፦
 ወያኔ ገና ወደ መንግስትነት ከመምጣቱ በፊት በረሃ ዉስጥ እንዳለ በጣም ክፉ ምርመራ እና የተለያዩ ስቃዮች በእርስዎ ላይ እንደፈጸሙበዎት ሰዎች ነግረዉኝ ነበር፡ ወያኔዎች ይሄነን በደል ለማድረስ ያነሳሳዉ ምክንያት ምንድነዉ? በደል ደረሰብኝ የሚሉትስ ምን ዓይነት ግፍ ነበር ተፈጽመዎበታል የሚባለዉ?

አቶ ገዛ ረዳ፦ 
በእርግጥ ወያኔ በእኔ ላይ መጥፎ ግፍ ፈጽሟል። ይህ በደል በእኔ ብቻ ሳይሆን በጣም ቁጥራቸዉ እጅግ ብዙ የሆኑ ታዳጊ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ከኔ በላይ እጅግ የከፋ ግፍ የተፈጸመባቸዉ የትግራይ ተወላጆች ስላሉ የደረሰብኝ በደል በግፍ ተሰቃይተዉ ከተገደሉት ሰዎች ሲነጻጸር የሰዉ ልጅ ከማይችለዉ በላየ ላይ ግፍ ቢፈጸምብኝም፤ ተሰቃይቼ በተጨማሪ የጠየቁኝን ገንዘብ ከፍየ ሳልሞት በሕይወት ተርፌ የእኔ ታሪክ እና አብረዉኝ በግፍ ሲሰቃዩ ያየሗቸዉ ሰዎች ስቃያቸዉን እና ታሪካቸዉ ከራሴ ታሪክ ጋር አብሬ ለዓለም ሕዝብ ለመግለጽ ለታሪክ ምስክርነት በመብቃቴ አምላክ ምስጋና ይድረሰዉ እላለሁ። የደረሰባቸዉ በደል ለሕዝብ ሳይገልጹ ያለፍርድ በግፍ የተገደሉት ሰዎች ዛሬ በሕይወት ከእኛዉ ጋር ባለመኖራቸዉ ግን በጣም ያሳዝናል።
ጥያቄ፦ የተያዙበት ምክንያት መነሻዉ ቢያብራሩልኝ እና የትስ ነዉ ወያኔዎች አርስዎን አግኝተዉ ሊይዝዎት የበቁት?
 
አቶ ገዛኢ፦
 መጀመሪያ ደርግ ወደ ስልጣን ሲወጣ፤ እኔ እና ስማቸዉ አሁን ልጠቅስ ያልፈለግኳቸዉ ጓደኞቼ ሆነን ደርግን ለመጣል በምስጢር ተነጋግረን ተደራጅተን ነበር።በከተማዉ ዉስጥ በወቅቱ የወያኔ አባላትም ይንቀሳቀሱ ነበር። እኛ የራሳችን እነሱ ደግሞ የራሳቸዉ እንቅስቀሴ በማድረግ የየግላችን በማካሄድ ጸረ ደርግ እንቅስቃሴ እናካሂድ ነበር። እኛ በወቅቱ ወያኔዎች ወደ በረሃ ከመዉጣታቸዉ በፊት አድያቦ በሚባል በረሃ ታጋዮቻችን አሰማርተን ትግል ጀምረናል። ኢድዩ ከመባላችን በፊት የድርጅታችን መጠሪያ “ጠራናፊት” ነበር የሚባለዉ።ጠራናፊት በሗላ ቆይቶ ወደ ኢዲዩ ተቀላቅሎ ‘አዲዩ’ ተባለ። ይህንን ትግል ወያኔዎች በረሃ ከወጡ በሗላ የጠራናፊት እንቅስቃሴ እንዳለ እና አባሎች መሆናችንን አዉቀዋል።እንግዲህ እየወነጀሉን ያሉት እናንተ ከከተማ ወጣቶችን እየመለመላችሁ ወደ ጠራናፊት ትልካላችሁ በሚል ነዉ እንዲይዙን መነሻ የሆናቸዉ። በእርግጥ በወቅቱ እኛ ደርግ አልነበርንም፡ጸረ ደርግ ሆነን ተደራጅተናል።በእርግጥ ተንቀሳቅሰናል “መብታችን” ነዉ። ይህ በመሆኑ በወያኔ መጠየቅ አልነበረብንም።በእነሱ
ዉንጀላ ጠራናፊትን ማደራጀት “ጸረ ወያኔነት” ስለሆነ ጸረ-ወያኔ ነህ ብለዉ ነዉ የያዙኝ። 

ጥያቄ፡- 
በጠራናፊትም ሆነ በማንኛዉም ድርጅት መደራጀት የናንተ የግለሰዎች የምርጫ መብት ነዉ፡ ለምን አስከዚህ ድረስ ሊገፉበት አነሳሳቸዉ?

አቶ ገዛኢ ረዳ፡-
እንቅስቀሴዉ በጣም አስግቷቸዉ ነበር።ተሓህቶች ሕዝቡን መቅጣት፤ ማስፈራራት፤ መግደል እና ማሰቃየት ስለጀመሩ በተናጠል ገበሬዉንም እያስገደዱ ማታገላቸዉን ስላየ፤ ኗሪዉ ሕዝብ ወደ ጠራናፊት እየሸሸ የመደራጀት ፍላጎቱ እየበረታ መሄዱን ስላስተዋሉ የጠራናፊት አባሎች መሆናችን ስላወቁ፤ እኛኑን ለመያዝ መነሻቸዉ ይሄ ነዉ እንጂ ሌላ ምንም ወንጀል በእነሱ የፈጸምኩት ነገር የለም። ኢድዩ ሃገራዊ ነዉ። ባሕሉን ሃይማኖቱን ጠብቆ ሕዝቡን መስሎ የሚጓዝ ድርጅት ስለነበር እነሱ አልወደዱትም። እና ሊይዙኝ የቻሉት በዚህ ነዉ።

ጥያቄ፡- 
የት ነዉ ሊይዝዎት የቻሉት?

አቶ ገዛኢ፦ 
ዕለት 20 በሕዳር 1969 ዓ.ም ከሰዓት በሗላ አብቶባስ ተሳፍረን በማግሰቱ 21 የዓመቱ የአክሱም “ሕዳር-ጽዮን” በዓል የሚከበርበት ዕለት ስለነበር ከሽሬ/እንዳስላሴ ከተማ እኔ እና ጓደኞቼ ሆነን ወደ አከሱም ከተማ ስንጓዝ “ላዕላይ ቆራሮ”- ዉስጥ “ማይ ጋሕጋሕ” በሚባል ቦታ በአዉራ ጎዳናዉ እመንገዱ ላይ አድፍጠዉ መሽገዉ ቆዩን። “ቁም!” በማለት ነጂዉን አዘዙት። እኔም ሾፌሩን “ዝምብለህ ቀጥል!! ቀጥል!!” እንዳልኩት ጉዞዉን ሊቀጥል ሲል “ቦምብ” ወርዉረዉ በጭስ አፍነዉ አስቆሙት። ታሳፋሪዉ በሙሉ እንዲወርድ አዘዙት።ወረድን።እኛን እመንገድ ዳር አስቀምጠዉ መንገዱን ዘጉት። 50 ከሚሆን ከታገተዉ ተሳፋሪ መሃል “እኔ” እንደዚሁም “ገብረጻድቅ ወልዱ” እና “ፍስሃ” የተባሉ ጓደኞቼን ሦስታችን ለይተዉ በማስቀረት ሌሎቹን ለቀቁዋቸዉ። ከቦታዉ ፈንተት አድርገዉ ትንሽ ወንዝ ያለበት ጣሻማ ወደ ሆነ ስፍራ በመከወል ለጊዜዉ እዛዉ ቁጭ በሉ አሉን። ጌዘዉ እየመሸ ሲሄድ “እባካችሁ አቡቶቡሷ ጥላን እንዳትሄድ ነገ በዓለማርያም “ሕዳር-ጽዮን” ነዉ እና ለመሳለም ነዉ አክሱም ስንሄድ ያስቆማችሁን እና ልቀቁን” ብልን ለመንናቸዉ። (እስከዚህ ጨካኞች መሆናቸዉን አላወቅንም። እባካችሁ አቡቶቡሱ ጥሎን እንዳይሄድ አልን እንጂ እኛ ይህ ሁሉ መካራ ይመጣብናል አላልንም ነበር)።ሲመሽ፤ አቡቶቡስዋም ጥላን ሄደች፡ እኛም ይዘዉን “ማይ ድማ” ወደ ሚባል ቦታ ወስደዉ ከብት እና ፍየል በሚኖርበት በረት “ነጭ-አመድ እና እበት” ያለበት በረት ዉስጥ አስገብተዉ “እዚህ ተኙ” ብለዉ እንደከብት በረቱን ዘጉብን እና አዳሩን እዛዉ አደርን።

ከእዛ በማግስቱ ጥዋት ሌሊት “ማይ ቡር” ወደ ሚባለዉ የማርያም ህዳር-ጽዮን በዓል ወደ ሚከበርበት ቤተክርስትያን ወሰዱን። ከዚያ ወደ ሰመማ ወሰዱን። ከሰመማ ወደ ዓዲ ዳዕሮ ወሰዱን። ከዓዲ ዳዕሮ ወደ ዓዲ ነብርኢድ ሄድን። ዓዲ ነብርኢድ ስንደርስ አቶ “ፍቕረ አርአያ” የተባለ ወጣት ገበሬ ቤት አዳር አደረግን (ፍቕረ አርአያ ደርግ የገደለዉ የሃየሎም አርአያ ወንድም ነበር)። እንግዲህ እንደዚያ እያልን ወደ “ባድመ” ደረስን።

በእነዚህ ገጠሮች ስናልፍ አዳራችን ቤት ባልታጣ “ሆን ብለዉ” በብርድ እንድንሰቃይ እና እንድንታመም ብለዉ እከብቶች እና ፍየሎች በረት ነበር አጉረዉ እንድተኛ የሚያዝዙን። በደረስንባቸዉ ቦታዎች ሁሉ ወጣት ዋጣቱን እየያዙ ነበር እየለቀሙ የሚጓዙት። አስረዉ ሲያመጡዋቸዉ፤-ሁለቱን እጆቻቸዉ አጥብቀዉ ስለሚያስሯቸዉ፤ “ዓይኔ ሊፈነዳ ተቃርቧል! እጄ! ልቤ ሊፈነዳ ነዉ! ጣቴ ሊቆረጥ ነዉ!” “እባካችሁ ፍቱልኝ! ወይም ላላ አድረጉልኝ! ፤ልሞት ነዉ! ስለ ፈጠራችሁ አምላክ!” በማለት ይለምኗቸዋል። ለመታሰራቸዉ ምክንያት ደግሞ “ኢዲዩን ለመቀለቀል አቅዳሃል፡ የኢዲዩ አዝማሚያ ታሳያለህ…” እያሉ ናቸዉ የሚዩዝዋቸዉ። መጀመሪያ ከአፍ ጋህጋሕ ስንያዝ ሦስታችን ብቻ ነበርን።ቀስ በቀስ ወደ 30 እስከ 40 የምንሆን እስረኞች ደረስን። እነኚህ ከየቦታዉ የለቀሙዋቸዉ አብዛኛዎቹ ገላቸዉ በግርፋት የተላላጠ የተጎሳቆሉ አስረኞች ናቸዉ። 

ከባድመ ወደ “ንበት” ወደ ተባለዉ ስፍራ ወስደዉ አሳረፉን። እዛ ስንደርስ በጣም የሚያስፈራ.የሬሳ.የመቃብር.ክምር.የሚመስል-ይታያል።ያስፈራል፤ይዘገንናል። ባድመ ስንደርስ መጀመሪያ ስንያዝ እንደነበረዉ ሁሉ አሁንም እንድንተኛበት ያዘዙን ስፍራ የነጭ አመድ ክምር ያለበት አስከ “የእግርህ-ባት” ድረስ የሚዉጥ አመድ ላይ “ተኙ” ብለዉን እዛዉ “እያስነጠሰን” “ሳል” እያሳለን አደርን። ጥዋቱን ከምኝታችን ስነሳ ሁላችንም ፊታችን “ነጭ-አመድ” ለብሶ አመድ መስለናል። በተንቀሳቀስን ቁጥር አመዱ ከልብሳችን “ቡን-ቡን” እያለ ይበንናል። ሲይዙኝ ከአዲስ አበባ የገዛሁት ጥቁር ሱፍ ልብስ ወደ አክሱም ስሄድ ለበዓሉ ብየ ለብሼዉ ስለነበር ሱፍ ልብሴ በአመድ ተበላሽቷል።

ከዚያ በሚቀጥለዉ ቀን ወደ አስርቤት ወስደዉ ከሌሎች ጋር ቀላቀሉን። ስንቀላቀል ወደ 40 አስከ 50 አስረኞች እዛዉ ቆዩን። ስትመለከታቸዉ በጣም የሚያስደነግጡ ፍጡራን፡ ገላቸዉ ያለቀ፤አጥንት ብቻ የቀሩ፤ ቆዳቸዉ ተጣብቋል።የደከመ ዓይናቸዉ ሲንከባለል እናያለን። ጸጉራቸዉ አልቋል።በንዴት በብስጭት እና በጸሃይ ብርሃን እጦት ተቃጥሏል።ቆዳቸዉ ወደ ቢጫነት ተለዉጧል።በምርመራ ግርፋት እና በእሳት ሰዉነታቸዉ ተቃጥሎ “ቁስለዉ” ተገሸላልጠዋል።ለማየት በጣም የሚያስፈራ እና የሚያስደነግጥ ተርዒት ነበር ያየነዉ። አነዚህ አስረኞች፤መነሳት መቆም አይችሉም። “እንደምናችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ”፡ ሲሉን መናገር አቅቷቸዉ “ድምፃቸዉ” በጣም እጅግ በጣም “ሎሆሳሳ” “ቀጭን ድምጽ” ብቻ እንደምን ብለዉ ለመናገር ይሞክራሉ።እኛ ደነገጥን። እኛም እንደነሱ የምንሆን አልመሰለንም “የምን ተአምር” ነዉ እያየነዉ ያለን ብለን የምንናገረዉ ነገር ጨንቆናል።በብረቱ ድንጋጤ ተዉጠናል።አነሱም በዛ ቀጭን ድምጻቸዉ “አቤት- አግዚኦ! እናንተም ወደ እዚህ ሲኦል መጣችሁ? ብለዉ ስለኛ አዘኑ”። ታጋዮቹ መጡ እና “አንድ ክንድ የም’ታክል” በክንዳቸዉ ለክተዉ/ “አንተ የምትተኛበት ቦታ እዚህ ነዉ፤ ያንተም እዚቹ ነች”፦ እያሉ የምንተኛባት ስፍራ አስታዉቀዉ ለክተዉ ሰጡን። መተኛት የምትችለዉ እነሱ ለክተዉ በሰጡህ የምኝታ ስፍራ ነዉ። እዛችዉ ሲኦል ያየሁባት የዳስ አስር ቤት 6 ወር ታስሬ አለሁ።

ጥያቄ፡- 
ሰዉነታቸዉ በግርፋት እና በጸሃይ እጦት የተሰቃዩት ሁኔታቸዉን ስታዩ በጣም ያስደነግጣል ያሉዋቸዉ እነኚህ እዛዉ አስር-ቤት ያገኛችሗቸዉ ሰዎች የዕድሜ ክልል ምን ያህል ነዉ?

አቶ ገዛኢ፡- 
 ህጻናትም አሉ! ህጻን፤ ሽማግሌ የሚባል ነገር አይለዩም። ሲያስሩ እና ሲገረፉ ማን ምን አይሉም። በጣም አረመኔዎች ናቸዉ። ከሚገረምህ ነገር ተይዘዉ ተደብድበዉ ብዙ ጊዜ ጸሃይ ስለማይሞቁ አእምሮአቸዉ ስተዉ “ያበዱ” የዓዲ ዳዕሮ፤የዓዲ አዉዓላ እና ከሌሎች ስፍራዎች የተያዙ አእምሮአቸዉ ስተዉ ያበዱ ወጣት ተማሪዎች ነበሩ።
 
ጥያቄ፡-
 በድብደባዉ ምክንያት ነዉ አእምሮአቸዉ የሳቱት?

አቶ ገዛኢ ረዳ፡-
 በድብደባ እና ምንም ባለሰሩበት ነገር እየተለጠፈባቸዉ ለብዙ ጌዜ አስረዉ መላወሻ ስላሳጧቸዉ በጭንቅ በሃሳብ በብስጭት ኣእምሮአቸዉ ሳቱ።ያለቅሳሉ! ራሳቸዉ ስተዉም የማይሆን ነገር ሲዘላብዱ፤ሲናገሩ ትሰማቸዋለህ።
 
ጥያቄ፡- 
ወደ አስር ቤቱ ከተወረወሩ በሗላ እርስዎንስ ምን አደረጉዎት።

አቶ ገዛኢ ረዳ፡- 
ጠራናፊት ነበርክ አሉኝ። አዎ እኔ ጠራናፊት ነበርኩ አልኩዋቸዉ። ይሄም በከተማ ዉስጥ ያሉት አባሎቻችሁ ያዉቁታል።አብረን እናወራለን እንዝናናለን ወዳጆች ነን። ነገር ግን በናንተ ድረጅት ላይ ያደረስኩት ጥፋት፤ ፤አበሳ ወይም በደል የለም። ከተማ ሆነህ ሰዎች ወደ በረሃ እንዲሄዱ ወደ ድርጅትህ ስንቅ ታቀበል ነበር፤መረጃም ታስተላልፍ ነበር፡ ብለዉ ወነጀሉኝ። ከዚያ በሗላ ማስፈራራቱን ቀጠሉበት።ከቃል ጥያቄ ምርመራ በሗላ በማግስቱ ጥዋት “ተነስ” ብለዉ ወስደዉ አጠገብ ካለዉ አንድ ዛፍ ሰር አስረዉ ከዛፉ ጋር አጣብቀዉ አሰሩኝ። በዙሪያየ የእንጨት ማገዶ ከመሩብኝ።…
 
ጥያቄ፡-
 እርስዎኑን እንዲያቃጥሉዎት ነዉ?

አቶ ገዛኢ፦
 አዎ! እኔን ለማቃጠል። ቀጭን እንጨት እና የሚቀጣጠል ሳር ዙርያየ ደርድረዉበታል። ሊያቃጥለኝ የቆመዉ መርማሪየ ሰዉየ እጁን ዘርግቶ በመለካት “አንድ ክንድ” ከለካ በሗላ እኔን ከዛፉ ጋር የፍጢኝ አስሮ ማገዶዉን በዙርያየ ከምሮ የፍጥኝ እንደታሰርኩ ከዛፉ ዙርያ “ኩምትር” ብየ እንድቀመጥ አዘዘኝ። በአንድ ክንድ ርቀት በዙርያየ የተከመረዉ ሳር እና ቀጫጭን እንጨት በሳር አቀጣጥሎ እሳት ለኰሰበት። እንጨቱ መጀመሪያ ጭስ ማዉጣት ጀመረ፤ ሳሩም መቀጣጠል ጀመረ ጭሱ አፈነኝ። ጭሱ ሲያፍነኝ ማስተንፈስ አልቻለኩም ጨነቀኝ። ጥልቅ ባሕር ዉሃ ዉስጥ ጠልቀህ ተዉጠህ መዉጫ እናዳጣ ሰዉ ነዉ ትንፋሽ አጥሮኝ የተሰማኝ። ጭሱ በዙርያየ እንደ ጉም እየተልመለመለ ሲነሳ መርማሪየ አሳቱ ይበልጥ እንዲቀጣጠል ቆሞ ይቆጣጠራል ፤እኔኑም ያየኛል። ጭሱ ወደ እኔ እየገፋ እየበራታብኝ “አፈነኝ”። ሲያፍነኝ መሳል፤ማስተንፈስ አልቻልኩም። በጣሙን ጨነቀኝ። ነፋሱ በርትቶ ጭሱን ካስወገደዉ በሗላ፡-እንጨቱ እየተቀጣጠለ ወደ አሳት ተቀይሮ መንደድ ጀመረ። 

ነፋሱ ነበልባሉን በሁሉም አቅጣጫ ወደ እኔ ዙርያየ ይገፋዉ ስለነበር ገላየን መለበለብ ጀመረዉ። እጄ የፍጥኝ ታሰሬአለሁ። አግሬ እጄም መላወስ ስለማልችል፤ ወላፈኑ አሰቃየኝ። ሙቀቱ የቃጠለዉ ወላፈን ነብሰ ስጋየን አሰቃያት። ከጎን እና ከሗላ እየለበለበኝ ካለዉ ወላፈን ለመሸሽ እግሬን ወደ ፊት ለመዘርጋት ብሞክር ወደ ባሰ እሳት ይጠጋል። የማደርገዉ ጨነቀኝ። እጄ የፍጥኝ በጥብቅ ስለታሰረ፤ ያለሁት “ቁጭ” ብየ አግሮቼን “ኩምትር” አድርጌ ነዉና ወደ ግራ ስል ወደ ቀኝ ወደ ሗሊት ማምለጫ የለኝም። ወደ ሗላየ እንዳላፈገፍግም ከዛፉ ጋር የፍጢኝ ተጣብቄ እንዳልንቀሳቀስ ታስሬአለሁ።ወዴትልግባ!ወዲያዉኑ ሰዉነቴ ቆዳየ በመላ አካላቴ “ቱት.. ቱት.. ቱት.. ብሎ ዉሃ ከረጢት ቋጥሮ አበጠ።
 
ጥያቄ፡- 
ገላዎ ዋሃ ቋጥሮ ነዉ?

አቶ ገዛኢ ረዳ፡
አዎ! መላ አካላቴ እሳቱ ስለለበለበኝ ሰዉነቴ ዉሃ ቋጠረ። ወዲያዉኑ እንደተሰበረ እንስራ “ቧ!!!!” ብሎ የቋጠረዉ ዉሃ ፈሰሰ!

ጥያቄ፡-
 “በስመ አብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ”! …ከዚያ በሗላስ?
አቶ ገዛኢ፡- ከዚያ በሗላ፤ “ዕረፍት!” አሉኝ። አምላክ ዕረፍት አይስጣቸዉና! ያሰሩኝን ፈቱልኝ። ሲፈቱኝ ወደ መሬት ተንጋለልሁ እና ተዘረጋሁ። ሰዉነቴ ወደ መዛል ሲል “ተነስ!” አሉኝ። አእምሮየ የት እንዳለሁ አይታወቀኝም -ነገር ግን ትንሽ ትንሽ ይታወቀኛል። ተነስ ብሎ እንደገና ሳሩን በእሳት አቀጣጥሎ መሬት ላይ ተዘርግቼ እንዳለሁ “የተቀጣጠለዉ የሳር እሳት” እንደ ቀጤማ በላየ ላይ ወርዉሮ በትኖ በመነስነስ እፊቴ ላይ ረጨብኝ።

ጥያቄ፡- 
ወይ ጉድ! ወይ ጉድ! በስመ አብ! በስመ አብ! ምን ተአምራት ነዉ!? እሺ ይቀጥሉ።

አቶ ገዛኢ ረዳ፡-
በሗላ -አሳቱን ገላየ ላይ ሲበትነዉ፡ “ከስቃይ ሰመመን” ባንኜ “እናንተ ሰዎች ከእኔ የምትፈልጉት ነገር ምንድ ነዉ? ለምን አትገድሉኝም ከዚህ ሁሉ? አልኳቸዉ።እኔ እናንተን በጠላትነት የተነሳሁበት ቀን የለም፡ እኔ ደርግን ነዉ የተቃወምኩት እንጂ ወያኔን አልተቃወምኩኝም።ወንጀል አለህ የምትሉት ካለ አምጡልኝ፤ በወንጀሌ ልቀጣ፡ ካልሆነ ግን አታሰቃዩኝ ብየ ብማጠናቸዉ ሊሰሙኝ አልፈለጉም።መጀመሪያ እሳቱን ለኩሰዉ ሲለበልቡኝ ነጭ ጭስ እየተምዘገዘገ ወደ እላይ “ቦለል” ማለት ሲጀምር ገና አይቸዉ “አቤት! አቤት! ቅዱስ ሚካኤል! ሳልሞት በምድር በሕይወቴ እያለሁ “ገሃነመ እሳት” አሳየኸኝ!? ማረኝ አምላኬ ብየ ጸሎት ሳደርስ” መርማሪዎቼ *ከት-ከት* ብለዉ *ሳቁብኝ*።“ምንድ ነዉ የምትለዉ?” ብለዉ ተሳለቁብኝ። *ቅዱስ ሚካኤል ፍርድህን ላክልኝ፤ምሕረቱን ላክልኝ* ነዉ ብየ ጸሎት እያደረስኩ ያለሁኝ ስላቸዉ፦ እንደ ገና “ከት-ከት” ብለዉ ተሳሳቁብኝ። “ቧልጪት መሳይ ሁለት የድንጋይ ኮረት ከመሬት ለቅመዉ” *ኮረቶቹን እርስ በእርስ እያጋጩ፤ቅዱስ ሚካኤልህን በዚህ የድንጋይ ብልጭታ ይታያሃል?” በማለት ተሳለቁብኝ።ከዚያ-የእሳት ስቃይ
ምርመራ-አስወጥተዉ-ወደ-ቦታየ-ወሰዱኝ።

በስቃይ እንደሰነበትኩ ቁስሌም አልዳነም፦ እንደገና በሁለት ታጋዮች ታጅቤ ወደ አንድ መርመራ አቀረቡኝ። መርማሪዉ “አሁንስ ተማርክ ወይ?” ብሎ ጠየቀኝ። ቁስልህ ዳነ? ብሎ ጠየቀኝ። እኔም ይሄዉ እንደምታየዉ ነዉ፡ ቁስሌ እንኳን ሊድን የቁስሉ ስቃዩ እየበረታብኝ ሄዷል አልኩት። አሁንሳ ተማርክ? አለኝ። “ጥሩ ትምርት ተምሬአለሁ አዎ!” አልኩት።ታዲያ ተምሬአለሁ ካልክ የምታምነዉን አምነህ ንገረን አለኝ? የሰራሁት ነገር ስለሌለኝ የማምነዉ ነገር የቱ እነደሆነ አልገባኝም። ምን ጥፋት በደልኩኝ? ወንድሞቼ ለምንድ ነዉ በደሌን የማትነግሩኝ? “ጠራናፊት” ነኝ ብያችሗለሁ። ከዚያ በላይ የምታዉቁት ካለ ንገርኝ እነጋገርበት ካልሆነ አታሰቃዩኝ። አልኩት።የለም የምታዉቀዉ ነገር አለ፡ታዉቃለህ!አለኝ።የምታዉቁት ነገር ካለ ለምን አትነግሩኝም? ስለዉ፦ የተማርክ መስሎን ነዉ እንጂ ገና አልተማርክም እና ትገባታለህ ብሎ “ታጋዮቹን ዉሰዱት!” ብሎ ወደ መግረፊያ ቦታ ወስደዉ አግሬን ወደ ላይ ጭንቅላቴን ወደ ታች ዝቅዝቅ ከጣራ ጋር አስረዉ-በማንጠልጠል.የቀኝ-“ሆድ-እግሬን” ከዉስጥ ገልብጠዉ ”በጎማ ጠበጠቡኝ!ጠበጠቡኝ!”

ሙልጭ አደርገዉ ነብሰ ስጋየ አስከ ምስት ገረፉኝ። ጎማዉ በጣም ያሳምማል። ጎማዉ ዉስጥ ጠጣራ በትር የሚመስል አለዉ። ሆድ እግሬን ጠብጥበዉ ጠብጥበዉ ደም አስኪፈስ ድረስ ገሸላለጡኝ። ሰዉነቴ ሃይለኛ ትኩሳት እና ላብ ተወብቄአለሁ። ከጉልበቴ በታች “ድምብል ብል” ብሎ ተነፍቶ አብጧል። አግሮቼ ለረዥም ጊዜ መዳን አልቻለም። አስከዚች ደቂቃ እና ቀን አስከዛሬ ድረስ ያመኛል። መሮጥ ቀርቶ ረዥም መንገድ መራመድ አልችልም።ስቃዩ ብርቱ ነዉ። ሆድ እግሬ በጎማ ለረዢም ሰዓት ስለገረፉኝ ወደ “ዉስጥ ጎርጉዶ” ስጋ መሙላት አቅቶት አ ጥንት እና ጅማት ስለቀረ፤ ፈጠን ብየ በመርገጥ ረዢም ጉዚ ለመራመድ ከሞከርኩኝ ያመኛል። ጣቶቼም በጎማ ስለጠበጠቡኝ በጣም ብዙ ስቃይ እያሳለፍኩ ነዉ ያለሁት።እና አንደዚህ ዓይነት ስቃይ በእኔ ብቻ ሳይሆን ቁጥር ስፍር የሌለዉ ያለ ምንም ጥፋት እና ፍትሃዊ ፍርድ/ቤት መአት ብዙ ሰዎች በእሳት እየተለበለቡ ብዙ ግርፋት እና ስቃይ ደርሶባቸል። አንዚህ ሰዎች “አዛዉንት አያከብሩም፤ አያዉቁ”፤”ቤተስብ የሚባል ነገር እያዉቁም” ከባህላችን ዉጭ የሆነ የጭካኔ ምርመራ አካሂደዋል። አረመኔዎች ናቸዉ። አነዚህ ህዝባቸዉን የካዱ ናቸዉ።ከትግራይ ሕዝብ አብራክ ወጥተዉ በሕዝቡ ላብ ተምረዉ፤እዉቀት ገብይተዉ፡በአካባቢዉ ልምድ እና ወግ አድገዉ፡ተመልሰዉያሳደጋቸዉን ያስተማራቸዉን ያጎረሳቸዉ እና የተንከባከባቸዉ ህብረተሰብን የሚያጠቁ “ክፉ ሰዎች” “አጋንንት” ናቸዉ።የሰዉ ልጅ ሕሊናም የላቸዉም። ብዙ ሰዉ ደብድበዉ ከጥቅም ዉጭ አደርገዋቸዉ አበላሽተዋቸዋል።

ጥያቄ፡- 
አቶ ገዛኢ ዕድሜዎ አባት አዛዉንት ነዎት። በእሳት ተቃጥሎ በሕይወት መትረፍ፤ በእዉነቱ የእግዚአብሔር ድርሳን የጸለዩለትን የለመኑትን ቅዱስ ሚካኤል በክንፉ አጥልሎዎታል። ይህ በሰዉ ልጆች ላይ የተፈጸመ ጭካኔ በትግራይ ተወላጆች ላይ የተፈጸመ ወንጀል፤ ላልሰማ ላላወቀዉ ሕዝብ እንዲነግሩ በማለት መርማሪዎቹ የተሳለቁበት አምላክ “ቅዱስ ሚካኤል” ከሞት በር በእግዚአብሔር አምላክ ታአምር ያዳነዎት መሆኑን ነዉ አንጂ የሰዉ ልጅ በእንደዚህ ዓይነት አረመኔነት ተደብድቦ በእሳት ወላፈን ተቃጥሎ መትረፍ በእዉነቱ የሚገርም ተአምር ነዉ፡ከመላት ምን ማለት ይቻላል!ከዛ ከድብደባዉ በሗላስ ምን አስከተለ?

አቶ ገዛኢ ረዳ፡- 
መቸም ይህ በእኔ ላይ የተፈጸመዉ ግፍ በእኔ አልተጀመረም በእኔም ላይም አልቆመም።ብዙ አስረኞች፤ያለ ጥፋት ተደብድበዉ በእሳት ተቃጥለዉ መላ ሰዉነታቸዉ “ደም” እና “መግል” ቋጥሮ “ለቁስል” እና “ለዘላቂ ስቃይ” “ለአእምሮ መታወክ” ከመዳረጋቸዉ በላይ በየቀኑ በእዉነቱ ከ3 አሰከ 4 አሰከ 7 ወይንም 8 ድረስ ከተለያዩ ቦታዎች የሰበሰብዋቸዉ አስረኞች ይገደላሉ። ሊገድልዋቸዉ-ሲፈልጉ፤ጥዋት-ጥዋት “ተሰናበትዋቸዉ” ይሉናል። እየጠሩ ሲወስድዋቸዉ የሚገደሉት ሰዎች “ለወንድሜ ንገሩልኝ፤ለእናቴ ለአጎቴ ንገሩልኝ”- “ደህና ሁኑ” ከእንግዲህ ወዲህ አንገናኝ ይሆናል! “እግዚአብሐር-ከእናንተ-ጋር-ይሁን”!እያሉ፤ይሄዳሉ።

በጣም ከሚያሳዝን ነገር፤ “አቶ ገብረሊባኖስ መዝገቦ” የተባሉ የተከበሩ ትልቅ ጨዋ ሰዉ በሽሬ አዉራጃ ዋና ከተማ በእንዳስላሴ ከተማ ኗሪ ፤ የሆኑት እኒህ ሰዉ ፤ያዉራጃዉ ግምጃ ቤት ሂሳብ ሹም ሆነዉ ሲሰሩ፤ በወቅቱ ደርግ ትላልቅ የአገሬዉ ታዋቂ ሰዎች የሚባሉ ሰብስቦ “በረሃ ድረስ ሄዳችሁ “ምንድነዉ ነገሩ? ብላችሁ” አስኪ ነገሩ በሰላም የሚፈታ ከሆነ በሰላም ለመፍታት እንዲቻል በረሃ ድረስ ያሉበት ቦታ ሄዳችሁ የወያኔ መሪዎችን አነጋግራቸሁ ለዕርቅ አነጋግሯቸዉ። በሽምግልና የሚታይ ከሆነ እንሞክረዉ እና አስኪ ሄዳችሁ ህዘቡን ወክላችሁ አነጋግሯቸዉ” ፤በማለት እሳቸዉ እና ሌሎችም እንደዚሁ “ባላምባራስ ተወለደ ገብረስላሴ” የተባሉ የእንዳስላሴ ከተማ ጭቃ ሹም፦ሌላም ገስጥ ኪዳነማርያም የተባለ የትልቅ ባላባት ልጅ ከሽማግሌዎቹ ጋር ለሽምግልና ተመርጦ አብሮ ሄዶ ነበር (ልጁ በወቅቱ አባትየዉ ከሚኖሩበት ከተማ ሄደዉ ወያኔዎች የገደሏቸዉ መሆኑንም ጭራሽ አልሰማም፤ኣላወቀም ነበር)። ሽምግልናዉ ስላልወደዱት “አይሆንም ብለዉ ወደ መጡበት ከመመለስ ፈንታ እነሱንም ያለ ምንም ወንጀል ይዘዉ አስቀርዋቸዉ”።የታሰሩት ቀደም ብለዉ እኛ ከተማ ዉስጥ እያለን ከመያዛችን በፊት ነዉ። አብረዋቸዉ የነበሩ ሌሎች አስረኞች ጭምር ታስረዉበት ከነበረዉ “ግህነም” ከተባለ “የጋሀነመ እሳት አስር ቤት” መጥተዉ እኛዉ ጋር አብረን ተቀላቅለናል። ልክ እኔን በእሳት አቃጥለዉ እንደለበለቡኝ አነሱም ሰዉነታቸዉ በሙሉ በእሳት ተቃጥሎ ለብልበዋቸዋል።ገላቸዉ ቁስል ደም እና መግል ብቻ-ሆኗዋል።

በተለይ አቶ ገብረሊባኖስ መዝገቦ እኔ በእሳት ከተጠበስኩት በላይ ተጠብሰዋል።ምክንያቱም በጀርባቸዉ ደምም መግልም ይንዠቀዠቃል። መተኛት አይችሉም- የቁስሉ መጠን ለዓይን ይዘገንናል።አቶ ገብረሊባኖስ መዝገቦም ሆኑ ባለምባራስ ተወልደ ገብረስላሴ በጣም ደግ የተከበሩ ባላባቶች ናቸዉ።ባላምባራስ ተወለደ ገብረስላሴም የአከባቢዉ፤የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ማዕረግ/አድባር ነበር ማለት ይቻላል።ባላምባራስ ገብረስላሴ ወደ ምርመራ ሲወስዱት “አይዞህ ቆመንም ያዉ ሞት ነዉ፡ ብንሞትም ያዉ ሞት ነዉ- በርታ” ያልዋልክበት አበሳ ንገረን ቢሉህ ያላደረግከዉ ነገር በጭንቅ “አዎ” ብለህ አትመንላቸዉ፡ብየዉ ወስደዉ ደጋግመዉ እንደገና በእሳት እየለበለቡ እየደበደቡ ሲያሰቃዩት፡መከራ ሲበዛበት“የሚሉት ሁሉ ኣዎ! አላቸዉ”። ቀጥለዉም ለወጣት “ገስጥ ኪዳነማርያም “እዚህ የመጣኸዉ አባትህን ስለገደልንልህ የደም ብድር ለመመለስ ነዉ ወደ እኛ አዚህ ድረስ ደፍረህ የመጣኸዉ?” አሉት። አሱ ደግሞ አባትየዉ በእነሱ እንደተገደሉም ጭራሽ-አላወቀም-ነበር።

ሌላዉ ደግሞ ከዓድዋ ሰለኽለኻ ወደ ተባለች ትንሽ ከተማ እህቱን ለመጎብኘት መጥቶ የነበረ አንድ ህፃን ልጅ (ታዳጊ-ወጣት) ይዘዉት አብሮን ነበር። “አንተ ደግሞ እዚህ የመጣኸዉ ከምንጠጣበት ወንዝ መርዝ ልትጨምር ነበር የመጣኸዉ? ብለዉ፤ እሱንም በእሳት ለብልበዉ ገርፈዉ አሰቃይተዉ እንድንምርህ ከፈለግህ “አዎ” ማለት አለበህ ብለዉት “አዎ” አምናለሁ ብሎ ባልዋለበት ነገር አሳምነዉ አክስቱን ለመጠየቅ ወደ ሰለኽለኻ አብሮት ከዓድዋ ወደ ሰለኽለኻ የመጣዉ “ብርሃነ መስቀል ጎሽም” እንደገና መሓመድ የተባለዉ ወጣት ልጅ በአንድነት በአንድ ቀን ሁሉንም ወስደዉ ረሸኗቸዉ።

ወስደዉ ከረሸንዋቸዉ በግምት ወደ 30 ወይም ወደ 35 የሚሆኑ ሰዎች መካከል ናቸዉ።ዝርዝር ስማቸዉ ቆይቼ ልገልጽልህ ነዉ። የጭካኔያቸዉ መጠን የሰዉ ፍጡረነትክን ያስጠላል። ትግሬነትክን ያስጠላል። በወቅቱ ያ ግፍ ስትመለከት “የትግራዋይነት ትርጉም ሃዘን መሆኑን ይሰማሃል”። ይህ ጭካኔ የሚያራምዱ ባዕዳን ሳይሆኑ ከምድሪቱ ከእኛዉ ትግራይ መሬት የተወለዱ የአምላክን ክብር የሚንቁ ከአብራካችን የወጡ የትግራይ ተወላጆች ያሳደግናቸዉ የምናዉቃቸዉ ልጆቻችን ናቸዉ” ይህ ሁሉ ግፍ በሕዝብ ላይ እየፈጸሙ፤ያሉት።

ለምሳሌ የአማራ ተወለጅ የሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች የተያዙ ነበሩ።ይለቁዋቸዋል። ትግሉ ለትግራይ ተወላጅ እንጂ እነዚህን አይመለከትም እያሉ። ትግሬዎች የመታገል ግዴታ አለባቸዉና ይሄነን ያልፈጸሙ ፤ለቅጣት እና ለሞት መዳረግ አለበት ይላሉ። የትግራይ ሰዉ በእሳት ተቃጥሏል፡ አልቋል።ሌላ ቀርቶ የፈላ ዉሃ እየደፉብህ ይመረምሩሃል። ሳንጃን እሳት ዉስጥ አሙቀዉ ገላህን ይጠብሱሃል። የጓንዴ ሳንጃ በጣም ትልቅ ነዉ። ሳንጃዉ በሃይለኛ የእሳት ፍም ያኑሩት እና እሳቱን እያፋሙ ሳንጃዉ በከፍተኛ ግለት ያግሉታል። የጓንዴ ሳንጃ ነዉ። ሳንጃዉ እንደጋለ ወደ እሳትነት ተለዉጦ ብረቱ ቀይ ሆኖ ሲፍም የጋለዉ ሳንጃ ያነሱ እና የእስረኛዉን ገላ በጋለዉ ሳንጃ ይጠብሱታል።እያቃጠሉ፡ደም በደም አስኪሆን ዉሃ አስኪቋጥር ድረስ “አግዚኦ!!” እያለ ቢማጸንም ሰሚ የለዉም-ያቃጥሉታል።ጭካኔዉ በጣም ብዙ ነዉ።

ጥያቄ፡-
አቶ ገብረሊባኖስ መዝገቦስ በእሳት ያሁሉ ስቃይ ካስቃዩዋቸዉ በሗላ ከእስር ተለቀቁ ወይንስ እንዴት ሆኑ?

አቶ ገዛ ረዳ፡- 
አልተፈቱም። ገደልዋቸዉ! ሰዉየዉ ሲገድሏቸዉ፤ አረመኔነት በተላበሰ እርኩስ አገዳደል ነዉ የገደሏቸዉ። እነሱ እንደነገሩን ከሆነ፡ በወቅቱ “ኢድዩ” (ኢድሕ) ወደ አካባቢዉ በብዛት ሰራዊቱን ይዞ እየገሰገሰ በፍጥነት ስለመጣ በድንገት ስለደረሰባቸዉ ያካባቢዉ ወያኔዎች ተደናገጡ። ኢዲዩ መጥቶብናል እና “እንግደላቸዉ” ብለዉ እኛን ለመግደል ወያኔዎቹ ሌሊቱኑ ወደ ታሰርንበት የዳስ እስር-ቤት ገቡ።ገቡ’እና አስወጥተዉ በታራ አስሰለፉን።

ጥያቄ፡- 
ምን ሊያደርጓችሁ?

አቶ ገዛ ረዳ፡-
 ሊፈጁን! ሊገድሉን አስበዉ የነበረዉን እንደገና ይቆዩ ብለዉ ሃሳባቸዉን ለወጡ። እንደ ገና ተነጋግረዉ ሃሳበቸዉን ለዉጠዉ ወደ አንድ ሸለቆ መሳይ አስገቡን።
 
ጥያቄ፡
ለምን?

አቶ ገዛኢ፦
ሊገድሉን። መልሰዉ ሃሳባቸዉን ለወጡ እና እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ አቆዩን። እኛን በሰልፍ መዳዳዉ እንድንቀመጥ ካደረጉ በሗላ አቶ ገብረሊሰባኖስ መዝገቦ በጠበሷቸዉ የእሳት እና የግርፋት ስቃይ ስለበዛባቸዉ “መቆምም መነሳትም መራመድም ስለማይችሉ አካላቸዉ ኩፉኛ ስለተጎዱ እንደ አንዳንዶቻችን ቆመዉ መራመድ ስላማይችሉ፡ አሳቸዉ እና ሃይለኛ የወባ በሽታ ይዞት ታምሞ በጠና ተኝቶ ሲሰቃይ የነበረ አንድ የእነርሱ ታጋይም (ትዉልድ ቦታዉ እንትጮ ወረዳ) ሁለቱን እዛዉ ገደሏቸዉ።
 
ጥያቄ፡-
 እንዴ! የገዛ ታጋየቸዉም ጭምር?

አቶ ገዛኢ፦
አዎ! የራሳቸዉ ታጋይ። እኛ ጋር አልታሰረም፡ ከአጠገባችን ካለዉ መጠለያ ዳስ ነበር ራቅ አድርገዉ አስተኝተዉት ሲታከም የነበረዉ።ታጋያቸዉ ነዉ።የገዛ ታጋያቸዉም ጭምር ገደሉት።ወባ ይዞት ተኝቶ እንጂ እስረኛ አይደለም።አቶ ገብረሊባኖስ መዝገቦም ተኝተዉ እንዳሉ በጥይት ገደሏቸዉ ። በሦስት ጥይት ተኩሰዉ እዛዉ እንዳተኙ ገደሏቸዉ።እጅግ ዘግናኝ ፤ጭካኔ ያለበት፤አስደንጋጭ አገዳደል ነዉ። የነሱ ታጋያቸዉም በመታመሙ ከእኛ ጋር መጓዝ ስለማይችል አሱንም ገደሉት። በጣም መልከ መልካም ረዥም ቁመና የነበረዉ ወጣት ነበር።በጣም አረመኔዎች ናቸዉ።
 
ጥያቄ፡-
 በጉዞ ላይ እንዳይሸከሙት በማለት ነዉ?

አቶ ገዛ ረዳ፡- 
አዎ! እንዳይሸከሙት።እነሱን በጭካኔ መንገድ ከገደሏቸዉ በሗላ፤መረብ ዉስጥ “ማይ ላም” ወደ ተባለዉ ቦታ ወሰዱን። ከባድ ችግር ገጠመን።ሕሊናችን ባየነዉ ጭካኔ ተጎድተናል፡በዚያ ላይ እዛ ድረስ ለመድረስ ትልቅ ችግር ነዉ የገጠመን። መንገዱ በጣም ሃሩር ነዉ፡አሸዋማ ነዉ።አሸዋዉ አያስኬድም፡ከባድ ነዉ።ብዙዎቹ ደከሙ። መራመድ አልቻሉም፤እሩቅ ጉዞ ነዉ።አንዳንዶቹ አእምሮአቸዉ ተዳክሞ ነበር፤በሃይለኛ የራስ ምታት የተሰቃዩም ነበሩ።በስንት መከራ አንዳንዶቻችንን እየጎተቱም እያስፈራሩም መንገዱን-እንድንገፋ-አደረጉ። እጀግ ከደከሙት መሃል “ሃለቃ ጥላሁን ረዳ” የተባሉ (የትዉልዳቸዉ “ዓዲ አዉዓላ”) ደክመዉ መላወስ ስላቃታቸዉ፡”እንግደለዉ- ከዚህ ሰዉ ጋር ስንንቀራፈፍ ጊዜ አናጠፋም” በማለት ሊገድሏቸዉ ሲዘጋጁ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ “የድርጅቱ ሃላፊዎች” በዛዉ ሲያልፉ ድንገት ስለተገናኙ፤ “የደከመ ሰዉ አለን እና ልንገድለዉ ወስነናል፤ምን-ይመስላችሗል?”ብለዉ ጠየቋቸዉ። “ጥፋታቸዉን አረጋግጣችሁ ለሞት የተፈርዶባቸዉ ናቸዉ?” ብለዉ ጠየቋቸዉ፡ “ገና አልተፈረደባቸዉም” ሲሏቸዉ- “ይቆዩ አትግደሏቸዉ ብለዋቸዉ ከተሰነባበቱ በሗላ፦ ሊገድሏቸዉ ተዘጋጅተዉ የነበሩት አቶ ጥላሁን ይግዛዉን “ እንደ ጀምቢል ዕቃ በአንዲት ቀጭን እንጨት በገመድ አስረዉ ዥወዙዌ አንጠልጥለዋቸዉ ወደ መረብ ቀጠልን።

እዛዉ አሰልቺዉ በረሃ የዉሃ ጥም ይዞን ለአመሉ ለራሳቸዉ ይዘዉት ከነበረዉ “ኮዳ/ብራሾ” ዉሃ ከንፈራችንን እና የደረቀዉ ምላሳችን እንድናረጥብ አቀመሱን። ሃለቃ ጥላሁንም በዛች እንጨት አንጠልጥለዋቸዉ ሲጓዙ በጣም፤ እጅግ በጣም ስለተዳከሙ፤ እንረፍ ብለዉ በአንድ ቦታ አዳር አደርግን እና አረፍን።ቦታዉ “የኤርትራ ቦታ ነዉ”፡ላዕለዋይ ባርካ ይባላል። እዛዉ እንደደረስን ማታዉኑ በሰልፍ “ለሁለት ምድብ” ከፈሉን።ከዚህ ወዲህ ያላችሁት ወደ “ቀይ ኮከብ” ትሄዳላችሁ፤ ይሄኛዉ ምድብ ደግሞ ከእኛ ጋር ጉዞ ትቀጥላላችሁ፡ ብለዉ ስም ዝርዝር ጠርተዉ ለያይተዉ ሌሊቱን አዳር አደረግን። ከእኛ ለይተዉ ያሳደሯቸዉን ሰዎች ሌሊቱን ከተኙበት ቀስቅሰዉ በማስወጣት “ፈጇቸዉ!!። ትንሳኤ ቀን ነበር፤ በዓዉደ አመት ዕለት በጥዋቱ ፈጇቸዉ! የፈጇቸዉም ቦታ ካረፍንበት ስፍራ ብዙም አይርቅም። ሁሉንም ረሸኗቸዉ።ሃያ አመስቱን (25) ሰዎች በጥይት ደብድበዉ ገደሏቸዉ። ሲረሽኗቸዉ፤የተኩሱ እሩምታ ይሰማናል።25ቱን ሰዎች በጥይት ደብድበዉ ከገደሏቸዉ በሗላ በላያቸዉ ላይ “ቅጠል አርከፍክፈዉባቸዉ እዛዉ ጥለዋቸዉ ሄዱ”።
 
ጥያቄ፦
 ሳይቀብሯቸዉ፤አመድ ሳያለብሷቸዉ?

አቶ ገዛኢ ረዳ፡-
አልቀበሯቸዉም! ገዳዮቹ ጋኔል ስለተጫናቸዉ ነገረ- ስራቸዉ ሁሉ የጋኔል ነዉ። “በተርታ ተሰለፉ!” እያሉ ነዉ ሲገድሉም ምን ሲሉም ሲሄዱም “በሰልፍ ነዉ፡ ሲገድሏቸዉም አስሰልፈዉ በመደዳ ጥይት እንደርከፈከፉባቸዉ ነዉ ወድቀዉ እንዳሉ ‘እርጥብ ቅጠል’ በላያቸዉ ላይ ጣል-ጣል አድርገዉባቸዉ ሄደዉ ነዉ ሳይቀበሩ የተገኙት።ሬሳቸዉም የተገኘበት መንገድ- ግጦሽ ሲግጡ የነበሩ ከብቶች ሬሳዎቹ ከወደቁበት አካባቢ ሲደርሱ “ምን መጣብን ብለዉ ደንግጠዉ” ወደ ሗሊት ሲሸሹ፦እረኞቹም “ምን አይተዉ ነዉ እነኚህ ከብቶች የተደናገጡት?” በማለት ከብቶቹ ከሸሹበት ስፍራ ተሰብስበዉ ሲሄዱ የተረሸኑትን የ25ቱን ሰዎች ሬሳ መደዳዉን በሰልፍ ወድቀዉ እርጥብ ቅጠል ተርከፍክፎባቸዉ ሲያዩ “እረኞቹም ደንግጠዉ” ዜናዉን ይዘዉ እየረጡ በመክነፍ “ለኤርትራ ጀብሃዎች” ስለ ሁኔታዉ ነገርዋቸዉ።ጀብሃዎቹ ምን እርምጃ እንደወሰዱ እና እንዳስከተሉ

ወደ ሗላ እመለስበታለሁ። ከተረሸኑት መሃል ለጊዜዉ ማስታወሻየ ስላልያዝኩ በሕሊናየ የማስታዉሳቸዉ ሰዎች “ተወልደ ገብረስላሴ” የሚባሉ ቅድም የነገርኩህ የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ጭቃ ሹም የነበሩ አዛዉንት ሰዉ፤ አበበ ገብረማርያም የተባሉ የዓዲ አዉዓላ ልዩ ስሙ “ዓዲ ብዕራይ” የተባለዉ ኗሪ የሆኑ በጣም ሃይማኖተኛ ጸሎት እና ቅዳሴ እንጂ ሌላ ባሕሪ ያልነበራቸዉ ቸር የእግዚአብሔር ሰዉ፤ የ16 ዓመት ዕድሜ ነበረዉ ታዳጊ ወጣት (የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ኗሪ) “ብርሃነ መስቀል ጎስም” የተባለ፡ እና የ12 ዓመት ዕድሜ የነበረዉ መሓመድ የተባለ ከዓድዋ አክስቱን ለመጎብኘት ወደ ሰለኽለኻ መጥቶ ይዘዉት ነበር ያልኩህ ልጅ እሱንም አብረዉ ገደሉት። ከሚገርመዉ ነገር “መሓመድ” ልጅ ስለነበር “እናቴ ናፍቃኛለች እና መሄዴ ነዉ እያለ እያለቀሰ፦ሲጎተጉታቸዉ የነበረ ህጻን ልጅ ነዉ። ለምንድ ነዉ እኔን እዚህ ያመጣችሁኝ እናቴ የምትኖረዉ እዚህ አይደለም እና ልቀቁኝ” እያለ ሲወተዉታቸዉ የነበረ፤ልብ ያልሰራ ገና ያልጠና ህጻን ነበር።

ወደ ሗላ ልመለስህ እና እረኞቹ ወደ ጀብሃ ሄደዉ ሲያመለክቱ፤ ጀብሃዎችም ሁኔታዉን ለማየት ወደ ስፍራዉ ሲሄዱ 25ቱም ሬሳዎች ወድቀዉ አይዋቸዉ። ጀብሃዎቹ የአካባቢዉን እረኞች አና ታጋዮቻቸዉን ሰብስበዉ እንደ ደምቡ “ድቤ-አመድ አለበሷቸዉ”። ይህን ካደረጉ በሗላ፤ ወደ ተሓህት ታጋዮች ዘንድ በመሄድ “ምን ጉድ ነዉ የሰራችሁት? በሽማግሌዎች እና ህጻናትን አንዴት እንደዚህ ዓይነት ነገር ትፈጽማላችሁ? ነዉር አይደለም ወይ-? ስትፈልጉ ለምን በገንዘብ እና በሌላ አትቀጥዋቸዉም ነበር? ህጸናቶቹስ ቢሆን አስተምራችሁ ከድርጅታችሁ ጋር ማሰለፍ አይሻልም ነበር ወይ? በማለት “ለትግራይ ሕዝብ ያልራራችሁ ለእኛም የምትረቡን አይመስለንም እና በአስቸኳይ ከቦታችን ለቅቃችሁ ዉጥልን”። በማለት በእዛዉ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የወያኔ ታጋዮች በሙሉ አካባቢዉን “እንዲለቁ አደረጉ”። ይህ መረጃ እኛን ሲጠብቁ ከነበሩ ሁኔታዉ ሊቀበሉት-ያልቻሉ፤በጣም እጅግ በጣም ከዉስጥ አንጀታቸዉ ያረረ፤ያዘኑ የተሓህት ታጋዮች ናቸዉ ምስጢሩን የነገሩን።

በዚህ ምክንያት እኛንም ከቦታዉ አብረናቸዉ እንድንለቅ ሆነ። ከዚያ በሗለ ይግዛዉ ደስታ የሚባል ወላጅ አባቱ ዓድዋ አዉራጃ ዉስጥ የታወቁ የባላባት ልጅ የቀኛዝማች ወይም የግራዝመች ደስታ ሃይሉ የተባሉ ልጅ ነዉ። ይግዛዉ በጣም ብርቱ የሚያምር ቁመና ያለዉ ጥቁር መልከመልካም ጉብል ወጣት ነበር። ይግዛዉ እነሱን (ተሓህትን) አይቀበልም። ይከራከራቸዉ፤ይቃወማቸዉ-ነበር። አይታዘዛቸዉም። እሱንም ገደሉት። ሊገድሉት ሲታገሉት፡ ታግሎአቸዉ፤ አሱም ኣንድ ገድሎ አንድ አቁስሎባቸዉ ነዉ የሞተዉ። እጁ ታስሮ ሊገድሉት ሲወስዱት “እጆቹን አንደታሰረ፤ ታግሎአቸዉ፤በገዛ ካራቸዉ ወግቶ ገድሎአቸዉ ሲያመልጥ እሱን ለመያዝ እንደ ጅግራ በጥይት ሲያባርሩት፤አምልጥዋቸዉ-ሲቶኩሱበት-በአጋጣሚ አንዲት ጥይት መትታዉ ስለነበር ከቦታዉ ካመለጠ በሗላ ወዴት እንደተሰወረ ስላጡት ከጊዜ በሗላ አሞራ በሰማይ ከብበዉ ሬሳዉን እያንዣበቡበት የተመለከቱ ታጋዮች ወደ ስፍራዉ ሲሄዴ “ይግዛዉ ደስታ” በተመታባት ጥይት ሬሳዉ ወድቆ አገኙት። ይግዛዉ ደስታ የታወቁት የዓድዋ ተወላጅ የደጀች ሃይሉ የልጅ ልጅ ነዉ።በጣም ዘግናኝ ሁኔታ ነዉ ያለፍነዉ። የተገደለዉ ሰዉ ብዙ በጣም ስፍር ቁጥር የለዉም። ብዙ፤እጅግ ብዙ ነዉ።
 
ጥያቄ፦
 የእረስዎ ነገር መጨረሻዉ እ ምን ላይ ደረሰ?

አቶ ገዛኢ፦
መጨረሻ እኔን ጠርተዉ $15,000 (አስራ አምስት ሺሕ ብር) የገንዘብ ቅጣት እንድትከፍል ተፈርዶብሃል እና ወደ ቤተሰቦችህ ደብዳቤ ልከህ ገንዘቡን እንዲከፍሉልህ ላክላቸዉ አሉኝ። እኔም እንዴ! 15 ሺሕ ብር የሚባል ገንዘብ ከየት ላምጣዉ? ብየ ብጠይቃቸዉ፦ “ትከፍላለህ- ትወጣለህ፦ አትከፍልም፦ አዚቹ ትቀራታለህ!!” አሉኝ። ዉሳኔዉ “የተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ ዉሳኔ ነዉ! የተጋድሎ ሓርነት ህዘቢ ትግራይ ዉሳኔ- የዉጣ ዉረድ ገበያ አያዉቅም””። አሉኝ . እንግዲህ ካላችሁ’ማ ወደ “ዓዲ ዳዕሮ” ዉሰዱኝ እና እዛ የሚያበድረኝ ሰዉ ባገኝ ልፈልግ” ብላቸዉ። እዛዉ እማ ጠላት ይዞታል አንወስድህም፡ አሉኝ።በሗላ ወደ ባለቤትህ ደብዳቤ ላክ አሉኝ። እኔም ደብዳቤ ጻፌ ላክኩላት። ስጽፍላት የሁኔታየ ጉዳይ፡የገንዘቡ መጠን-ጽፌ ላኩሁላት። ሦስት ልጆቻችንን የምትጠዉርባት አንዲት ንግድ ሆቴል ነበረችን፡እና ሆቴሉን ሽጣ፤አልበቃ ብሏት በላዩ ላይ ከሰዉ ከወዳጅ ተበድራ ጨምራ የጠየቁትን $15,000 (አስራ አምስት ሺህ ብር) ይዛ “ሰለኽለኻ” ወደ ተባለ ትንሽ ከተማ ድረስ መጥተሽ አስረክቢ ስላሉዋት፤ ሄዳ ከፈለቻቸዉ። የከፈለችበት የ$15,000 አስራ አምስት ሺሕ ብር ደረሰኝ ለታሪክ እንዲሆነኝ ብየ አስከ አሁን ድረስ ደረሰኙ በእጄ ይገኛል።ገንዘቡን እንደተከፈላቸዉ ላዕላይ ባርካ አጠገብ ከነበረዉ ከታሰርንበት ቦታ ፈትተዉ ለቀቁኝ።በማይ ምነ አድረጌ “ ማይ ደገላ” የሚባል በሰመማ አድርገን ወደ እንዳስላሴ ሽሬ አዉራጃ ዋና ከተማ ገባሁ።

ጥያቄ፦ 
በእዉነቱ አቶ ገዛኢ በጣም ለጀሮ እና ለሕሊና እጅግ የሚከብድ ፍዳ፤ “ዉጉዝ ከመአርዌ” የሆነ ጭካኔ በእርስዎም ሆነ በ ተቀሩት ሕዝባችን የደረሰዉ የጭካኔ ግፍ፡ የደረሰበዎት ለዓለም ለሰዉ ልጆች ለመንገር ታድለዉ አምላክ አብቅተዎታል።በሌሎቹ የትግራይ በረሃ አካባቢዎች “ጣት” ፈልፍለዉ እየመዘዙ በማዉጣት በሰዉ አንደበት ለመግለጽ ለህዋሳት የሚከብድ የጭካኔ ምርመራ ሲፈጸም ነበር ይባላል። ይህም አርስዎ ከነበሩበት የተለየ ሌላ ሰዋራ ቦታ ነዉ ይባላል፤፡ ይህ ድበቅ ቦታ ያዉቁታል ? ታስረዉበት ነበር?

አቶ ገዛኢ ረዳ፡-
 የግፉ እና የእስርቤቱ ዓይነት ብዙ ነዉ። ይህ አሁን ይካሄድ ነበር ወይ ብለህ የጠየቅከኝ ጭካኔ ዓይነት እማ ስንቱ ብየ ልዘርዝር ብየ ነዉ እንጂ በእኔም እኮ የደረሰብኝ ሌላ ጭካኔ ያልነገርኩህ ብዙ አለ። እኔን የፍጥኝ አስረዉ ቁጭ ብየ ሲቆፍሩት ያየሗቸዉ ለመቀበርያየ የቆፈሩት ጉድጓድ እንድቀበርበት ከሞት አፋፍ ገብቼበት እንዳየዉ አደርገዉኛል። ያዉም ጉልበቴ በድብደባ እና በምግብ እጦት ደክሞ ስለነበር ጉልበት ስላልነበረኝ ራሳቸዉ ቆፈሩልኝ እንጂ፤ ሌላ ጊዜ ግን ራሳቸዉ ሟቾቹ ናቸዉ መቃብራቸዉን እንዲቆፍሩት የሚያዝዋቸዉ። ጉድጋዱን እንደቆፈሩ፤ “እዛዉ ቆይ!” ብለዉ እዛዉ ረሽነዉ አፈር አልብሰዉ ይቀብሯቸዋል። መቸስ ያልደረሰበት ሰዉ- አሁን እየተነጋገርንበት ያለዉ ይህ ሁሉ አረመኔነት “እዉነት አይመስለዉ ይሆናል”” ምክንያቱም ከሰዉ ልጅ ጭካኔ እጅግ ያለፈ ግፍ ስለሆነ ‘መቀበል ያዳግተዋል። በተለይም ከራሱ አብራክ የወጡ የገዛ ልጆቹ በወላጆቻቸዉ እና በጎረቤቶቻቸዉ ይህ መሳይ ግፍ ሲፈጽሙ ያላየ ሰዉ ማመን ያዳግተዋል። ነገር ግን ግፉ በተግባር በእኔም በሺዎቹ የተፈጸመ ነዉ።ለምሳሌ እኔ በእሳት ብቻ ሳይሆን በፈላ ዉሃ ሳይቀር እየደፉብኝ ግፍ ተፈጽሞብኛል። እንደነገርኩህ ለእርድ እንሚቀርብ በግ እግሬን ከጣራ ጋር አስረዉ ጭንቅላቴን እና እጆቼ ዝቅዝቅ አንጠልጥለዉ እግሮቼ በጎማ ጠብጥበዉ ክፉኛ አሰቃይተዉኛል። ይህ ሁሉ ካደረጉ በሗላ መጨረሻ ነገ ስለምንገድልህ- (ነገ ስለምትሰዋ) ኑዛዜ ለቤተሰብህ ጻፍላቸዉ አሉኝ።እኔ የምጽፈዉ ኑዛዜ የለኝም፡ አለኩዋቸዉ።ለምን? አሉኝ። እኔ ያለችኝ ባለቤቴ ኣንዲት እቤት ያለችዉ እሷ ብቻ ነች፡ በለቤቴም የማታዉቀዉ ሌላ የምስጢር ኑዛዜ የለም፦ልጆቼም ያሉኝ እነሱ ብቻ ናቸዉ እና ከዚህ ዉጭ ልዩ ኑዛዜ የለኝም፤የምጽፍበት መክንያት የለኝም አለኩዋቸዉ።ንብረት በሚመለከትም ቢሆን ልጆቼ የምታስተዳድርባት ሆቴል አለችን፤ከዚህ ዉጭ ምንም የተደበቀ ለኑዛዜ የሚያደርስ ምስጢር የለኝም አለኩዋቸዉ።እንደገና ሊደበድቡኝ ማስፈራራት ቃጣቸዉ። ነገር ግን አልደበደቡኝም። የሆኖ ሆኖ ነገ መስዋዕት መሆንህ ስለማይቀርልህ ከመገደልህ በፊት ብትጽፍ ጥሩ ነዉ ካልሆነም መገደልህ አይቀርልህም ሲሉኝ፡_ እኔም ይህች አሁን ያልኩዋትን በወረቀት ጽፌ ሰጠሗቸዉ። ያኔ ሌሊቱን “ሳዝን” “ጸሎት- ሳደርስ” “ሳለቅስ” ነኝ ያደርኩት እና ጥዋት በማግስቱ አቶ ገዛኢ ረዳን “ይቀስቅሷቸዉ!” የሚል ትእዛዝ አስቀድሜ ተገደሉ ብየ ስማቸዉ ካነሳሑዋቸዉ ሰዎች ዉስጥ አንዱ የሆኑት አቶ አበበ ገብረማርያም የተባሉ እኔን እንዲቀሰቅሱኝ አድርገዉ ቀሰቀሱኝ። ያኔ ሌሊት ተአምር የተሞላበት ሕልም አይቼ ነበር። ህልሜን ብነግርህ ይቻላል?
 
ደጀን፦ 
አዎ! ይቀጥሉ፦

አቶ ገዛኢ ረዳ፦ 
እሺ። አንድ የካህን ጥምጣም ያደረገ ግርማ ያለዉ ቄስ፡ በጣም ነጭ የሆነ ጋቢ ነጠላ ደርቧል። ከታሰርንበት ቦታ ካጠገቧ ኣንድ ትንሽ ተራራ የምትመስል ዳገት ነገር አለች። በዛች ዳገት ቁልቁል ወደ እኛ ተጣድፎ በመዉረድ፡ አኛ ታስረንበት በነበረዉ አስር ቤት መስኮት አንገቱን ብቅ አርጎ በማስገባት “ዝም በል!ግድየለም ትወጣለህ! አለኝ። ያን ጊዜ ይሄንን ቃል ስሰማ “አይ ጊዜዉ አጭር ነዉ፤ጊዜም የለም፤ ሰዉ የለም፤ አሁን ታዲያ በመጨረሻዋ ሰዓት በምን ተአምር ከሞት አፋፍ ልድን እችላለሁ አምለኬ ሆይ? ብቻ ስልጣንህ እና ተአምራትህ ሰፊ ነዉ እና ሕይወቴ ባንተ ስር ነች፡ ከሞትኩም ነብሴን ተረከባት ከዳንኩም ተአምራትህ ብዙ ነዉ ላንተ የሚሳነዉ የለም “ተአምራትክን ለዓለም ሕዝብ እነግራለሁ“ብየ ትንሽ ስለደከመችኝ “ዓይኔን ገርበብ አድረጌ እንቅልፍ ሊወስደኝ ሲል “አበበ! አበበ! ቀሰቅሰዉ ቀስቅሰዉ!! አሉዋቸዉ አቶ አበበን። እኔም ስለሰማሗቸዉ፤ እሺ-ግዴላችሁም-እነሳለሁ-ብያቸዉ-ተነሳሁ። “ስትገድሉት ልብሱን ግፈፉት/አስቀሩት። ሱፍ ልበሱን ጓዶች ወደ ዉጭ አገር ለስራ ሲሄዱ / ከሰዉ ጋር መገናኛ እንዲሆናቸዉ ልብሱን አስቀሩት፡ ይጠቅመናል።” ብለዉ ልበሴን ከላየ ላይ ለመግፈፍ ወስነዉ እንደነበር አንዲት ታጋይ ነግራኛለች። ሊገድሉኝ ሲያስነሱኝ ልብሴን.ከሰቀልኩት.ቋት.ለማዉረድ.ስሞክር“ተወዉ!ተወዉ!”አሉኝ። 

እኔ ደግሞ “እቺን ልብሴን ከገላየ በደም ታጥባ ትወስዷት እንደሆነ እንጂ ከቶ በምንም ተአምር አልሰጣችሁም ብየ እልክ ያዘኝና “አይሆንም አልሰጥም!” አልኳቸዉ (ሞት ላይቀረኝ!)።ሞት አይቀረኝም እና ብየ አልተለማመጥኳቸዉም!! ልብሴም ቀደም ብየ እንደነገርኩህ ፤ከአዲስ አበባ አስሰፍቼ ያመጣሁት ለሕዳር ጽዮን ለብሼዉ እንድዉል ወደ አክሱም በዓሉን ለማክበር ቤተክርስቲያኒቱን ለመሳለም ስጓዝ ነበር የያዙኝ።

እምቢ ብያቸዉ ልብሴን ኮቴን ብቻ ያለ ከነቲራ ያለ ክራባት እና ሸሚዝ ለብሻት እንደለበስኩዋት ወደ አንድ ስምጥ ሸለቆ ወሰዱኝ። መቃብርህ ቆፍር አላሉኝም። አኔ በወቅቱ እንኳን ጉድጓድ ለመቆፈር ነብሴ አልቋል። ትንሽ ቀላል ዕቃ እንኳ ለማንሳት አቅም የለኝም።ግን መቃብሬን እራሳቸዉ ጉድጓዱን ቆፈሩት። በዛ ወቅት- እጆቼ የፍጥኝ በጣም በሃይል አጥብቀዉ ስላሰሩኝ “ጣቶቼ እና ጥፍሮቼ ደም ስለቋጠሩ፡ይነዝረኝ፡ይጠዘጥዘኝ ጀመር። ዓይኔ ሊወጣ፤ ልቤ ሊፈነዳ ትንሽ ስለቀረኝ ስቃዩ ስለበረታብኝ መግደላችሁ ላልቀረ ትንሽ ከስቃዩ እንዳርፍ “እጆቼን ትንሸ ላላ” አድርጉልኝ አሉኳቸዉ። ከታጋዮቹ አንዱን ስሙን ጠርቼ፤ ‘እባክህ “መሰለ” ገመዱን ከእጆቼ አላላልኝ’ ብየ ስለምነዉ። “መሰለ ወልዱ” ይባላል “የዓድዋ ልጅ ነዉ””። እባክህ በፈጣሪ ስለዉ “አንተ ሰዉ! አንጀትህ በካራ ብንጫወትበትም ከእንግዲህ ወዲህ ሕይወትህ ምን ይረባሃል?፤አሁን መሞትህ ነዉ! አሁን ታርፈዋለህ፤ትገላገላለህ መቀበሪያ ጉድጓድህ እየቆፈርነዉ ነዉ! -ጉድጓዱ ያዉም ጉልበት የለህም ብለን እንጂ አንተ ነበር መቃብርህን መቆፈር የነበረብህ፤ ግን ትልቅ ሰዉ ነዉ ብለን አክብረንህም ነዉ” አለኝ።

እኔ ደግሞ፤-ካከበርከኝ ጥይት ከማርከፈከፍህ በፊት እጄን ላላ አድርግልኝ አልኩት። ቆፍረዉ ሲጨርሱ- ጠሩኝ። ወደ ጉድጓዱ ወስደዉ “ግባ!” ብለዉ ከተቱኝ። እጆቼ የሗሊት በመታሰሩ ቁጭ ማለት ስለማልችል ጀርባየ የጉድጓዱን ግድግዳ አንዲደገፍ ወደ ጥግ እንድጠጋ አስተካክለዉ ራሳቸዉ አስጠጉኝ። ሃይማኖተ ቢሶች ስለሆኑ፤ ጸሎታቸዉ “ዝክረ ሰማዕታት” የሚሉት ነገር አላቸዉ፡ “ሰጥ በል/ተጠንቀቅ ብለዉ “ዝክረ ሰማዕታት” አድረገዉ “አንገታቸዉ ሰበር በማድረግ የፊት ግምባራቸዉ ሁሉም ወደ መሬት ደፋ ደፋ አደርገዉ ጸጥ ሲሉ-እኔም “አቡነ ዘበሰማያት ትቀደስ ስምከ ትምጻእ መንግስትከ ለይኩን ፈቃድከ” ብየ የግል ጸሎቴን ለማድረስ ስጸልይ “መሰለ ወልዱ” የተባለዉ ታጋይ “ምንድነዉ የሚለፈልፉት?” አለኝ። “አምላኬ ንጹህ ነኝ እና በንጽህናየ ተቀበለኝ” ብየ ነዉ ጸሎትየን ለፈጣሪየ እያደረስኩ ያለሁ”። አልኩት። እሱም “ ዞር በል! በማለት ቀለደብኝ እና ተመልሶ አንገቱን ወደ መሬት በመቀልበስ “የነሱን ሃይማኖት “ዝክረ ሰማዕታት” ጸሎቱን ለመጨረስ አንገቱን ሲደፋ “ አለምሰገድ” የተባለ ታጋይ እየሮጠ ከሩቅ “መሰለ! መሰለ! መሰለ! አትግደሉት ይቆይ! ይቆይ! ምርመራ ገና ይደረጋል እና አቆዩት አትግደሉት አቁሙ! ብሎ ከሩቅ በሩጫ እየተጣራ መጣ። ከጉድጓዱ አስወጡኝ።

በወቅቱ ሸሬ እንዳስላሴ ከተማ የጎረቤቴ ልጅ የሆነ “ወዲ ሊላይ የሚሉት “ንጉሰ ሊላይ” የሚባል ወጣት በደህና ጊዜ እሱ እና ጓደኞቹ ተማሪዎች ሆነዉ ለሕዝብ ትያትር ሲያሳዩ እኔም ፎቶግራፍ በማንሳትም ሆነ የወጣቶች ስፖርት ክላቦች ለማዳበርም ገንዘብ ሲፈልጉ እየረዳሁ ወጣቶቹን ሳበረታታ ስለነበር ፦በዚያ ጊዜ ልጁ ያከብረኝ እና እንደ ወላጁ ሲያየኝ ስለነበር ፡ከሚገርመዉ ነገር ሊረሽኑኝ “ኡዚ ጠመንጃ” ይዞ ከተመደቡት ዉስጥ አንደኛዉ “ንጉሰ ሲሳይ” ስለነበረ፡ ወዲያዉኑ አለምሰገድ የተባለዉ ታጋይ “አቁሙ! ቆዩ!” ሲላቸዉ ወዲያዉኑ ንጉሰ ወደ ጉድጓዱ በመግባት ገመዱን ከእጄ ሊፈታልኝ ሲሞክር፦ የተቀሩት ገመዱን በካራ ቁረጠዉ፤በጥሰዉ! ብለዉት ገመዱን በካራ በጥሶ ከፈታኝ በሗላ “ታጋዮቹ በሙሉ ፊታቸዉ እንደ ብርሃን ወጋገን ሲበራ አየሁዋቸዉ”።ግዴታ ስለታዙ አንጂ ከዉስጥ የኔን መረሸን እንዳልወደዱት ከሞት ስድን ያሳዩት እፎይታ ለመረዳት ችያለሁ።በሗላ ወደ ጣብያችን መልሰዉ ወሰዱኝ። ምነዉ ስላቸዉ “ሌላ ምርመራ እናደርገልሃለን እና ትቆያለህ፡ ሲሉኝ “ለምን ገድላችሁ አትገላግሉኝም እና ከዚህ መከራ ልገላገለዉ” አልኳቸዉ።

ታሪኩ በጣም ዘግናኝ እና ረዢም ነዉ። እና የጠየቅከኝ ጥያቄ ልክ ነዉ በእያንዳንዳችን የተለያዩ ፍዳዎች ተፈጽመዉብናል። ለእኔም እንደዚህ ዓይነት ስቃይ አድርሰዉብኛል፡ለማለት ነዉ።አነዚህ ሰዎች “የትግራይ ሕዝብ ጠላቶች ናቸዉ፡ ርሕራሄ የሚባል የማያወቁ የቤተሰብ የዘመድ ወዳጅ የባህል የሃይማኖት ጠላት አረመኔዎች ናቸዉ።

ጥያቄ፦ 
ክብር አቶ ገዛኢ፤ የትግራይ ሕዝብ ሃይማኖተኛ፤ ህግ አክባሪ በአርአያ ስላሴ የተፈጠረ ፍጡር በሰዉ እጅ መገደል ነዉር ነዉ የሚል ማህበረሰብ ነዉ። እኔም ሆንኩኝ አብረዉኝ ያደጉት ጓደኞቼም ጭምር የተማርነዉ ታላለቅ ሰዎች ወላጆቻችሁ አዛዉንትን ሃይማኖታችሁን አክብሩ ሲሉ ነዉ ያስተማሩን-ትምርት ቤትም ገብረገብነት ስንማር የተማርነዉ የምናዉቀወ ባህላችን ነዉ።እነዚህ አሁን በእንደዚህ ዓይነት አረመኔ ስራ የተሰማሩ ትላለቅ አዛዉንት አባቶች በእሳት የሚጠብሱ ደፋሮች ከየት እንደበቀሉ ለራሴ ይገርመኛል? ይሄ ጉድ ስሰማ “እነዚህ ሰዎች እዉን ከትግራይ የበቀሉ ናቸዉ? ብየ እጠይቅና፤ የኛ ናቸዉ ብየ አፌን ሞልቼ ለመናገር ዛሬ ያዳግተኛል። ሞሶሎኒ እንኳ እረስዎ ከደረሰበዎት አረመንያዊ ጥቃት በላይ አልፈጸመም። ይሄ አረመኔ ስራ ሲደርስበዎት “አነዚህ “ከትግራይ ሕዝብ አብራክ የወጡ ናቸዉ፤ የኛ ናቸዉ” የሚል በሕሊናዎ ያድርበዎት ነበር?
 
አቶ ገዛኢ ረዳ፡-

በእዉነቱ በወቅቱ ይህ ዓይነቱ ጭካኔ ሲደርስብን አንኳን ከትግራይ የተገኙ ወጣቶች ናቸዉ ለማለት ቀርቶ ሰዉ መሆናቸዉም ተጠራጥረን “ከጋኔል ከሲኦል ወደ መሬት የሰዉ ልጅ ለመከራ እንዲዳርጉ የወረዱ አጋንንት ናቸዉ ነበር ያልናቸዉ። እንኳን እና የኛ ናቸዉ፤የእነ እገሌ ልጆች ናቸዉ ለማለት ቀርቶ፤ በተአመር ወደ መሬት የወረዱ “ጽልመተ መናፍስት” ነበር የምናስባቸዉ። እነሱን ስናይ እያንዳንዱ እስረኛ የሚያሳየዉ ጭንቀት ፍርሃት (ነብሰከ ታአምር ቀታሊሃ) - ልክ አንደ ጋኔል ነበር የሚታዩን። የሰዉ ባሕሪ ርቋቸዉ ስለነበር ሰዉ ፍጡራን አልነበሩም። በቃላት ለመግለጽ በጣም ያዳግታል። የነሱን ጭካኔ ለመረዳት በጭንቁ ውስጥ ካላለፉበት በቃላት ለመግለጽ በእወነቱ ይከብዳል።

ጥያቄ፦ 
ይህ ሁሉ ግፍ ሲያሰልፉ፡ ጉድጓድ መቃብርዎ አይተዉ ገብተዉ ወጥተዉ አሁን ወደ ሗላ መለስ ብለዉ ሲመለከቱት ይህ ሁሉ የመንፈስ ብርታት ከየት አገኙት ጭካኔዉን ማስፈራራቱን አንዴት ሊቋቋሙት ቻሉ?

አቶ ገዛኢ፡-
መቸም አነሱም ብዙ ጊዜ ይነግሩኝ ነበር ፡ ምን ብርቱ ሰዉ ነህ ይሉኝ ነበር። ብዙ ተደራራቢ ጭካኔ ደርሶብኛል። በአምላክ ብርታት ብርታቱን ሰጥቶኝ ነዉ የተረፍኩት። ምግብ እንኳ የምንበላዉ ምግብ “ምግብ አይምሰልህ!”፦ እንጀራ እንዳይመስልህ- አነሱ ራሳቸዉ ጋግረዉ ነበር የሚያመጡልን። ደረቅ ነዉ። አፈር የነካዉ ነገር ነዉ፡ ከላዩ ላይ አፈሩን ምኑም በእጃችን እያነሳን እየለየን ነዉ የምንገምጠዉ (እንጀራ አይሉት! ቂጣ ነገር አይሉት!) እንደ ዋልካ/ዋለሃ “ድንኩል” ነገር ነዉ። እጅህ ላይ እያለ ይፈረካከሳል። ላምባ ስለሚጨምሩበት፤ ስትቀምሰዉ “ላምባ፤ላምባ ይላል””። ወጡ “ሽሮ” አይይደለም፦ የሟሽላ ዱቄት-ነዉ። ጨዉ እና በርበሬ ተጨምሮበታል።እሱን እንደ ወጥ ስለሚሰጡን “ተቅማጥ” ይለቅብሃል። ይሄ ዓይነት አመጋገቡም “ሆን ብለዉ” እኛን “ለመቅጣት” የሚያደርጉት ነዉ። ይህ ሁሉ ሲመግቡን፦ አብረዉን የነበሩ ወንድሞቻችን ሲገድሏቸዉ፤ በሚቀጥለዉ ማታ ወይንም ነገ የኔ “ተራ” ትሆን? እያልን በፍርሃት በጭንቀት ስለምንኖር “ስለምግቡ አስከፊነት” ብዙም የምናስብበት አልነበረም። ጭንቀታችን “መቸ ይሆን የኔ ዕጣ?” ነበር ቀዳሚዉ ጭንቀታችን። እኔ ከዚህ ሁሉ መዓት እወጣለሁ ብየ አልገመትኩትም። ከሞት ጉድጓድ ፈትተዉ ሲያስወጡኝም ታጋዮቹ “አንተ ምን ዓይነት ወፍራም ቆዳ ነዉ ያለህ? ከፊትህ ፍርሃት ለምን አታሳይም?ሌሎቹ ታጋዮቻችን ሳይቀሩ ለመገደል እየተገፉ ሲሄዱ “እያለቀሱ! እየተማጠኑ! ነዉ የሚሞቱት አንተ ግን ልዩ ነህ፤አእምሮህም እንደተቀሩት አልሳትክም” እያሉ እነሱ ራሳቸዉ ሳይቀር ይገረሙ ነበር።ሆኖም ነገሩ አልሞትኩም ብየ አልዋሽም! ሆኖብኝ ነዉ እንጂ “ሰዉነቴ ሁሉ አልቋል፡ተጎሳቁያለሁ፤በእሳት ነበልባል ተለብልቤአለሁ” እንድሞት ብቻ ነበር የምለምናቸዉ።

ጥያቄ፦ 
እንደገና ቀደም ብየ ልጠይቀዎት አስቤዉ የነበርኩት ሌላዉ ሊያስረዱን የፈለግኩት የወያኔ ዕስር ቤቶች ግፍን በተመለከተ፤ነፋስም ሆነ የጻሃይ ብርሃን የማይገባበት የጉድጓድ እስር ቤቶች እንደነበሩ የተለያዩ የራሳቸዉ ታጋዮች ይናገራሉ።በእነዚህ ጉድጓዶች ትላልቅ አዛዉንት ወጣቶች በቅማል እና በሌላ ለመሳሰሉት ጨካኝ ስቃይ ተዳርገዋል ይባላል። አርስዎ ስለዚህ የሚያዉቁት ነገር አለ?

አቶ ገዛኢ፦ 
አዎ አለ። የጉድጓድ እስርቤቶች በብዛት እኔ በነበርኩበት ምዕራባዊ ቆላ አካባቢ አልነበረም። ነገር ግን በጎንደር አካባቢ “ቃሌማ” ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ልዩ የጉድጓዱ መጠርያ “ግህንም” (ጋሃነብ) የሚባል በረሃ አለ። አዚያ ዉስጥ ለዉስጥ የተቆፈሩ ጉድጓድ እስር ቤቶች እንዳሉ እንሰማ ነበር። ሌላዉ በተከዜ አካባቢም እንደዚሁ ተፈጥሮ የቆፈራቸዉ ጭለማማ የሆኑ አለታማ ሰፋፊ ጉድጓዶች (ባዓቲ- ምሽጎች) ዉስጥ ሰዎች የታሰሩበት እንደነበሩ እንሰማለን። እንደምነሰማዉ፦በአካባቢዉ ስትደርስ ከእላይ ሆነህ በእግርህ የምትረግጠዉ መሬት ከስሩ የጉድጓድ አስር ቤት መኖሩን አታዉቅም፡ጭራሽ አያስታዉቅም ሲሉ እንሰማለን። የጉድጓድ አስርቤቶቹ በጥበብ እንደማይነቃባቸዉ ተደርገዉ ነበር የተሰሩት።በተምቤን.እና በዓዴት (ኣክሱም) ዉስጥም እንዳላቸዉ ይነገራል። አዎ- ግብረ ክፋት-ጭካኔ ሲፈጠር አብሮአቸዉ የተፈጠረ ነዉ የሚመስለዉ። ስራቸዉ ሁሉ አያስታዉቅም።ቅማልን በተመለከተ፦በቅማል መሰቃየታችን እኔ ብቻ ሳልሆን አስረኛ በሙሉ ተሰቃይቷል። መተኛት መቀመጥ ማረፍ አትችልም።ሌት ተቀን መፏከት ነዉ።ሰዉነታችን ልብሳችን በቅማል ተወ’ሯል። ሰዉነታችን ጸጉራችን ቅማል ተልቶ ወደ መሬት ይንጠባጠባሉ። እግዚኦ የሚያሰኝ ስቃይ ነዉ። የቅማል ነገር ሲነሳ በዛዉ ላይ ቁስላችን በእሳትም በፉል ዉሃም በግርፋት ድብደባም ያመረቀዘም ያላመረቀዘዉም ደም የሚተፋዉ ቁስላችን ላይ ቅማሎቹ ተልተዉ ተጨምረዉበት ሲበሉን፤ሲያሳክኩን ስቃዩ አይጣል ነዉ።

በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናት የምፈልጋት “ታጋይ ለምለም ገሰሰዉ” የተባለች የአቶ ገሰሰዉ አየለ (ስሑል) (ወላጅ አባትዋ ወያኔን ከመሰረቱት አንደኛዉ) የተባለች ልጃቸዉ ድሮ እንዳስላሴ ሽሬ ከተማ ዉስጥ ከቤተሰቦቿም ጋር ትዉዉቅ ስለነበረን በታጋዮቹ ዘንድም ተወዳጅ ስለነበረች ፤እሷ በነበራት የዋህ አዛኝ ልብ እና አስተዋይ ሕሊና ወደ እሰር ቤቱ እየመጣች በቅማል የተወረረዉ ከናቴራየ እና ጸጉር ራሴ ጸሀይ ላይ አዉጥታ በመቅመል እና በማስጣት እጅግ ሰብአዊ ርሕራሄ በማሳየቷ፤ በእዛ በጭለማ በክፉ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት አስገራሚ ሰብአዊ ዕርዳታ ስላደረገችልኝ ምስጋናየ በዓለም ሕዝብ ፊት ሳመሰግናት እወዳለሁ። በእዉነቱ ድሃ ሆኜ እጄ በማጠሩ እንጂ ብድሯን ለመመለስ ምን እንደማደርግላት አስካሁን ከባድ ሸክም ሆኖብኛል። ድንገት በዚህ ዓለም ካለች እና የምታዉቋት ሰዎች ካላችሁ- በዚህ አጋጣሚ “ምስጋናየን አድርሱልኝ” ።በጣም ፤በጣም ዉለታዋ እግዚአብሐር ይክፈላት።ወለታዋ አስካሁን አልረሳዉም! እና የቅማሉ ነገር ከልክ ያለፈ ስለነበር አይወራም ብሎ ማለፉ ይሻላል።
 
ጥያቄ፦ 
በወቅቱ ልጆች ነበሩዎት?

አቶ ገዛኢ ረዳ፡-
አዎ ትንንሽ ሦስት ልጆች ናቸዉ። ግፋ ቢል ዕድሚያቸዉ ከ7 ዓመት አይበልጡም ነበር።
 
ጥያቄ፦
ሕጻናት ያለ ጧሪ እንዲያድጉ፤ አባታቸዉ ከመንገድ ጠልፈዉ ወደ በረሃ ወስደዉ ፤ህጻናት ያለ አባት አስቀርተዉ፡ የልጆች አባት በእሳት መጥበስ፤መበደል፤ግፍ መፈጸም ነዉሩነቱ ወያኔዎች አልታያቸዉም። ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጽሙ እነዚህ ሰዎች ነጻ እናወጣለን የሚሉት ማንን ነዉ። ምንስ እያሉ ነበር በወቅቱ ስብከት የሚያሰሟችሁ?

አቶ ገዛኢ ረዳ፦
ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ የትግራይ ህዝባችንን ከጨቋኙ ከአማራ ነጻ ለማዉጣት ነዉ ።ትግላችን ጸረ-አማራ፤ጸረ መሳፍንት ስርዓት ነዉ። ሕዝባችን ነጻነት ለማዉጣት ነዉ። ይሉን ነበር።

ጥያቄ፦
የ7ዓመት ዕድሜ ከዚያም በታች የሆኑት የታዳጊ ህጻናት አሳዳጊ አባት ከመንገድ ጠልፈዉ ሲለዩዋቸዉ፤ እነሱ ከሚሉት ነጻነት ቅራኔ አልገባም ወይ?

አቶ ገዛኢ፦ 
አዎ! በእርግጥ ይጻረራል እንጂ። ለነጻነት የቆመ ሃይል “ልጅ ከወላጁ” “አባት ከህጻናት ልጆቹ ከሚሰቱ” ጠልፎ ወስዶ ለስቃይ መዳረግ እነሱ ከሚሉት የነጻነት ትርጉም የተለየ ነዉ። ሰብአዊ ፍጡር በእሳት መቀቀል፤ በፈላ ዉሃ ማሰቃየት የሰዉ ልጆች ነጻነት የሚጻረር ነዉ። የልጆች ጉዳይ ካነሳህ ላይቀር አንድ ታሪክ ልጨምርልህ። አስረኛዉን ለመግደል ሲፈልጉ፦በነጻ ተፈትተህ ወደ ቤትህ እንለቃሃለን፡ ትሄዳለህ ይሉዋቸዉ እና- ዉሃም ሻሂም ይሰጡዋቸዋል። ከእስር ቤቱ አስወጥተዉ ራቅ ያለ ከሰዉ ዕይታ ትንሽ ሰወር ካለዉ ጎድጓዳማ ስፍራ ይወሰዱ እና በራሳቸዉ በአንገታቸዉ ላይ የሚያጠልቁት ከአቡጀዲ የተሰራ ከረጢት የስገቡላቸዋል። ዓይናቸዉ ዓያዩም፡ በከረጢቱ ይሸፍኗቸዋል። ሁሉንም በራሳቸዉ የምትገባዉ ከረጢት አስገብተዉ አንገታቸዉ ላይ ይቋጠራል። ዓይናቸዉ፤አፋቸዉ፤ ፊታቸዉ እንዳለ በሙሉ ይሸፈናል ማለት ነዉ። ተር…እንዲሉ በመደዳ አሰልፈዉ ያስቀምጧቸዋል።ከዚያ-በሗላ ይረሽኗቸዋል።ከመገደላቸዉ በፊት ግን ለእስረኛዉ እና ለአካባቢዉ ኗሪ አስረኞቹ እገሌ እገሌ ነገ ጧት ወደ ቤቱ እንለቀዋለን በማለት ያስወራሉ። ከእሰር ሲወስዷቸዉ “ሻይ” “ዉሃ” ጠጣ ብለዉ መንገድ ስንቅ እንዲሆንህ ብለዉ ነዉ ከሰዉ ፊት የሚሰጡት። እንግዲህ አስረኛዉ ወደ ከተማ ድንገት ቢለቀቅ እነ እገሌ የት ደረሱ ተብለዉ ሲጠየቁ ፡እሱ እማ ከተፈታ ቆይቷል” በማለት ያልሆነ ወሬ ለሕዝቡ እንዲሰራጭ ለማድረግ እንዲያመች ነዉ።

ላንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ትግል ፈቅጄ መስዋዕት ለመሆን ስለወሰንኩ፤ከአገሬ ከሕዝቤ በላይ ምንም ነገር የለም እና ግማሹን ንብረቴን ላንቺ አስቀርተሽ ግማሹን ለምታገልለት ድርጅት ለህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ በምስጢር እንድታስረክቢአቸዉ በማለት ሟቹን በግድ አስገድደዉ ደብዳቤ እንዲጽፍ ያደርጉታል። ያችን ደብዳቤ ይዘዉ ሄደዉ ከተነጋገሯት በሗላ ቀጠሮ ይዘዉ ዕቃዋን አንዳለ ግማሹን ንብረት ይወስዱታል። ማንኪያ ሳይቀር ይወሰዳሉ።ብረት ድስት፤ምንም የሚቀራቸዉ ነገር የለም።ይሄ ለሚረሽኑት ሰዉ ሲሆን ነዉ። ወደ ኢዲዩ ወደ ደርግ ወደ ማንም ድርጅት ገብቷል ከተባለ ወደ ቤቱ ሄደዉ ያለዉን ንብረት በሙሉ ሙልጭ አደርገዉ ይወስዱታል። ከብቱ ፍየሉ ምኑ ምናምኑ እንዳለ ይወስዱታል። ህጻን ልጅ ሚሰት አለዉ አይሉም።ለባለቤቱ ድርሻዋ የሚባል ነገር የለም፤ እንዳለ ይወረሳል።

ለምሳሌ ዓዲ ሓገራይ በተባለ አካባቢ ገ/ጻድቕ ጽጌ የተባለ ወጣት ገበሬ (ሐኔታ ጽጌ ይባላሉ ወላጅ አባቱ የአዲያቦ ኗሪ ናቸዉ) ወንድሙ ሐኔታ አስመላሽ ጽጌ ወረዳ ገዥ የነበሩ ናቸዉ። ትዉልዳቸዉ“ኤርትራ” ናቸዉ ነገር ግን ዕድመያቸዉ በሙሉ አድያቦ ዉስጥ ነዉ የኖሩት፡ ሁሌም የተከበሩ ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ።ገብረጻድቕ የጭነት መኪና አለዉ፤በጣም ሃብታም ገበሬ ነዉ። ገብረጻድቕ ጽጌን ወስደዉ ረሸኑት። እሱን ገድለዉ፤ወደ ቤቱ ሄደዉ ንብረቱን ግማሽ ወሰዱት።ከግማሽ ንብረቱ መወረስ በላይ ባለቤቱን እቤቷ ድረስ ሄደዉ $12,000 (አስራ ሁለት ሺሕ ብር ክፈይ አልዋት። አሁን በእጄ $6,000 ብር ብቻ ነዉ ያለኝ እና ተበድሬ ልከፍል ጊዜ ስጡኝ ስትላቸዉ፤ አሁኑኑ ካልከፈልሽ አብረሺኝ ከእኛዉ ጋር ወደ በረሃ ትሄዳለሽ ብለዉ አስገድደዉ ወሰዷት። ሲወስዷት በሰዉ መልእክት ልካ ተበድራ የጠየቁትን $12,000 (አስራሁለት ሺሕ ብር) ከፈለቻቸዉ። ከዚህ በላይ ቆላ በራሃ ዉስጥ የነበሩት ወደ 500 የሚጠጉ ከብቶቹ፤ላሞቹ በሙሉ ሰብስበዉ ወሰዷቸዉ። ለወደፊቱ ታሪኬን ለማስቀመጥ ያግዘኛል ብየ የያዝኩትን በግል የመዘገብዩት ማስታወሻ አንድ ቦታ ተወሰደብኝ እንጂ አሁን በአእምሮየ ያልያዝከኳቸዉ በሰዉ ልጆች ላይ የፈጸሟቸዉ ግፎች ብዙ ነገሮች እነግርህ ነበር።

ጥያቄ፦ 
አርስዎ ክፈል የተባሉት $15,000 ብር ከፍለዉ ሲለቀቁ ከእነሱ ጋር በምን ተለያያችሁ?

አቶ ገዛኢ ረዳ፦
አንድ ማሃላ ነበረኝ። ከእንደዚያ ዓይነት ጭካኔ እና ግፍ በሗላ ከአንግዲህ ወዲህ የሰዉ ልጆችም ሆኑ እኔ ሰላም የተሞላበት ኑሮ እንኖራለን የሚል ሃሰብና ግምት በኣእሙሮየ ጭራሽ አልተቀረጻም። የኔ አላማ- ባለቤቴን እና ልጆቼን ዓይን አይቼ እነሱን ተሰናብቼ ፤ናፈቆቴን ገልጨ እነዚህ በትግራይ ሕዝብ ሕየወት የሚቀልዱ አረመኔዎች ለመፋለም .ቁርጥ አላማ ያዝኩ። ሕሊናየ በፍጸም ዕረፍት ሰላም አጣ። ከሲኦሉ እንደወጣሁ ወደ ልጆቼ እና ባለቤቴ ወደ ቤቴ በገባሁባት ቀን ፤መለቀቄን ለአዉራጃዉ አስተዳዳሪዉ ለማመልከት ስሄድ፤ በወቅቱ የትግራይ ክፍለ ሃገር ዋና አስተዳዳሪ የነበሩት ኮሎኔል ቃለ ክርስቶስ አባይ የተባሉ የትግራይ ሰዉ (በትዉልዳቸዉ ዓድዋ) ከአዉራጃዉ አስተዳዳሪ ጽ/ቤት አብረዉ አገኘሗቸዉ።ያኔ በወሬ መምጣቴን ሰምተዉ ስለነበር፡ እኔን ስያዩ “እንኳን ደህና መጡ ይግቡ” ብለዉኝ ቁጭ እንዳልኩኝ “እንዴት በትላለቅ አዛዉንቶች አዋቂዎች የህጻናት ልጆች አባት እንደዚህ መሳይ ጭካኔ ይፈጸማል? ለሕዝብ እንቆረቆራለን እያሉ ይህ ዓይነት አረመኔ ስራ በኗሪዉ ሕዝብ ላይ ሲፈጽሙ በጣም ለህሊና ይከብዳል!” ብለዉ ኮለኔሉ አዘኑ።የደረሰብኝ ስነግራቸዉ፤ በጣም ነበር ያዘኑት።ከዚያ በሗላ ኮሎኔሉ ያመጣቸዉን ጉዳይ ለማከናወን የከተማዉን ሕዝብ ስብሰባ ጠርተዉ በማግስቱ ሲያነጋግሩ፤- ኮሎኔሉ “ንግግራቸዉ እንደፈጸሙ የተወደዳችሁ ወንድሞች እህቶች ሆይ፦ የዚህ ከተማ ኗሪ የሆኑ አቶ ገዛ ረዳ የተባሉ ከናንተ መሃል አሁን ካሉ እባክዎትን ይነሱ” ብለዉ ሲጠዩቁኝ ያኔ እኔ አንድ ነገር በህሊናየ ታወሰኝ። ኮሎኔል ቃለክርስቶስ አባይ የደረሰብኝ ግፍ ለሕዝቡ ገልጸዉ በተጨማሪ እኔዉ ራሴ የደረሰብኝን እንዳበራራ ሲጠይቁኝ፦እንዳለሰማሁ ዝም አልኩ (ሲለቁኝ ከማንም ሰዉ፤ ደርጅት፤ ግለሰብ፤ ወይንም መንግስት ጋር የደረሰብህ ነገር ብታወራ እርምጃ እንወስድብሃለን ብለዉ ስላስጠነቀቁኝ)። ከ3 ቀን 4 ቀን በሗላ ወያኔዎቹ “የሰጠንህን ማስጠንቀቂያ ባለመጠበቅህ ፤ባንተ ላይ እርምጃ የምነወስድብህ መሆናቸንን እንድታዉቀዉ በማለት ደብዳቤ ላኩልኝ።

450 ብር የገዛሁት የእጅ ሰዓቴን 8ግራም የሚመዘን የአንገቴ ሃብል 23 ግራም የጣት ቀለቤት በሙሉ ከተማ ከገባህ በሗላ ይላክልሃል ብለዉኝ የነበረዉን ንብረቴን አስቀሩት።አልላኩልኝም። ከደብዳቤዉ ላይ የላኩልኝ መልእክት የሚለዉ 1-እርምጃ ይወሰድብሃል 2- የተያዘዉ ወርቅ አንልክልህም- ዉርስ ሆኗል።የሚል በባለቤቴ ዘመድ በሆኑ ሰዉ አስልከዉ እንዲደርሰኝ አደረጉ።ሕይወትህ ከእንግዲህ ወዲህ አትኖርም ስላሉኝ። እኔም ጊዜ እንደሌለኝ እና እነዚህ አረመኔዎች እንደሚገድሉኝ ስላወቅኩ፤ ቤተሰቦቼን ተሰናብቼ የነበረኝን ጠመንጃየን ይዤ ወደ በረሃ ወጥቼ ከኢዲዩ ጋር ተቀላቀልኩ። በወቅቱ የኢድዩ ድርጅት የኔን ሁኔታ ስላወቁ መልዕክት ልከዉ ታጋዮች አስልከዉ ከተማ ዉስጥ ገብተዉ ነዉ ያስወጡኝ።ለመጀመሪያ ጊዜ ዓዲ ዳዕሮ ወደ ሚባል ቦታ ሰቀቀን በሌለበት ሙሉ ነጻነት ተሰምቶኝ ያለፍርሃት ገባሁ። ከዚያ በሗላ ከኢዲዩ ጋር ስታገል ቆይቼ፤ ዓዲ ዳዕሮ ዉስጥ ሰልለዉ ነብሰገዳይ በመላክ በጥይት መትተዉ አቆሰሉኝ።ከእዚያ በሗላ ለሕክምና ወደ ሱዳን ተላክኩኝ።ሱዳን ስታከም፤ ቆይቼ ፤ራስ መንገሻ ሥዩም ከሱዳን ወደ ወልቃይት እንድመጣ አድርገዉ ከዚያም ታጋዩ ወደ ሉግዲ ወደ ሱዳን ጠረፍ እንድዞር ተደረገ። እንዲህ እንዲ ሲል ትግሉ እና ታጋዩ ጠንካራ ቢሆንም መቸስ የአመራር ድክመት ይመስለኛል ሳይሳካ ቀረ።እኛም በየ ዓለማቱ ተበትነን ለስደት ተዳረግን።

ጥያቄ፦ 
አቶ ገዛኢ፦እንደሚያወቁት የወያኔ ማንነት ከማንኛችንም በላይ አዉቀዉታል።ሕዝባችን እያሉ የሚነግዱበት ሕዝብ ክብር የተጋፉ አዛዉንቶች እና ታዳጊ ህጻናትን እየረሸኑ አገር ያዋረዱ ፡ወላጆቻችን አሉላ እና ዮሃንስ በደማቸዉ ቆስለዉ ሞተዉ ከጥንት ከዘመነ አክሱም ጀምሮ ተከብሮ የቆየዉን የባሕር በራችንን ያስረከቡንን ድምበር፤ ካለሕዝብ ፈቃድ አስገንጥለዉ አገራችን ወደብ አልባ አደረጓት።ዛሬ አገር እና መንግስት ማስተዳደር ተያይዙታል። እነኚህ ሃይማኖት የሚዳፈሩ ጸረ ባሕላችን የዘመቱ ሰዎች ወደ እዚህ ደረጃ ይደርሳሉ የሚል ግምት ነበረዎት?

አቶ ገዛኢ ረዳ፦
አስተዳደር የሚካሄደዉ ሰብአዊ ክብር እንዲጠበቅ ሲደረግ ነዉ። ባህል ሃይማኖት ሲከበር ነዉ። ሰዉን በ እሳትየሚጠብሱ አረመኔዎች ወደ አስተዳደር ችሎታ መገመት ሕሊና ላለዉ ማየቱ ቀላል ነዉ።ሃይማኖት ላልከዉ ታሪክ ላነሳኸዉ ግን አንድ ነገር ማለት እችላለሁ። በረሃ ላይ እያሉ የቤተ ክርስትያን ሰፊ ግቢ የፖለቲካ ስብከት የሚካሂዱበት መናኸርያ እና “መጨፈሪያ” አድርገዉት ነበር። ቤተክርስትያን ግቢ ዉስጥ ሺጃራ ያጨሱ ነበር። የገዳማት የቤተክርስትያን ቅዱስ መጋራጃ “እየቀደዱ የጨዉ እና የበርበሬ መቋጠርያ ያደርጉት ነበር” አስሰፍተዉ ልብስ ይለብሱት ነበር።ለምሳሌ ሸራሮ መድሃኒ አለም ቤተክርስትያን ዉስጥ ያለዉ ሰፊ ግቢ እንደዚህ ዓይነት ተግባር ፈጸመወበታል። ሌላ ቀርቶ ካህናት ቀሳዉስት በግድ ጠመንጃ ታጥቀዉ ወደ ጦርነት እንዲሳተፉ ተደርጓል። ዘፈን፤ጭፈራ ሲደረግ ቄሶቹን ወደ ፊት በማሰለፍ ጭፈራዉ እንዲመሩት ይደረጋል። የሕዝብ ስብሰባም ጭፈራም ቄስ እንዲከፍተዉ ይደረጋል። ካህናት መነኮሳት ክላሽን እንዲታጠቁ ተደርጎ የእግዚአብሄር መልክት ትተዉ በጦርነት ሕይወትን በመግደል ተሰልፈዉ “ቄሶቹ” በቤተክርስትያን ደምብ እና ማዕርግ “ቀሲስ ወይም አባታችን” እገሌ- ከመባል ይልቅ “ጀግኖች” እየተባሉ የሰማዩን ስራ ትተዉ የምድሩን ስራ እንዲሰሩ ተገድደዉ ቀሳዉስት እና መነኮሳት በጀግኖች ተታኳሾች ማዕረግ ሲሰየሙ “የዓለም መጨረሻ- ምጽአተ ዓለም መሆኑነ ነዉ”። የህ ግፍ የሰሩ አሁን አስተዳደር ዉስጥ መንግስት ዉስጥ ገባን ሲሉ በእወነቱ ለሕሊና ይጎረብጣል። ተጋሩ ወላጆቻችን ያገራቸዉን የኢትዮጵያ ዳር ድንበር አስከብረዉ በክብር የቆሙ ባለታሪኮች ነበሩ። እነዚህ ግን የአባቶቻችንን ክብር የረገጡ ጠላቶች ናቸዉ። 

አሳፋሪ ታሪክ ነዉ የገባንበት ዘመን። ለምን እንዲህ ሊሆን እንደቻለ ብዙ ሰዉ ግራ ገብቶታል። በዘመናዊ የታሪክ መጻህፍት እና በመጽሃፍ ቅዱስ የተነገረላቸዉ ያገራችን ባለታሪክ የትግራይ ጀግኖች፡ ዛሬ “ታሪክ አፍራሾች” “አገር ሻጮች” “የወላጆቻቸዉ ጀግንነት አራካሾች” እንድንባል አደረጉን። የኢትዮጵያ የትግራይ ድምበር ሕዝቡን ሳያማክሩ በገዛ ፈቃዳቸዉ ሸንሻኝ፤ሰጪ እና ከልካይ ሆነዉ በሕዝብ ታሪክ እና በትግራይ ተወላጆች ስም አስጸያፊ ተግባሮች በመፈጸማቸዉ በምድር ታሪክ እና ይህን ዓለም በፈጠረ አምላክ ፊት ተወቃሾች እና ተከሳሾች ናቸዉ የሚል እምነት አለኝ። ይህ ዕድል ሰጥተህ ጭሆቴን እና ብሶቴን ለዓለም ህዝቦች እንዳስሰማ በማድረግህ እግዚአብሔር ያክብርልኝ። አመሰግናሉ:://-//

በሚቀጥለው ክፍል ሁለት እኔው እራሴ አቶ ገዛኢ ረዳን ሳወያይ ያደረገኩላቸው ቃለ መጠይቅ ላይ የጭካኔ ምርመራ ሲካሄድባቸው ግምባር ቀደም ተጠያቂ ያደረጉትን የወያኔው ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት (ዑስማን/ጆቢ) ላይ ዝርዝር እንገባለን። አበበ ያ ሁሉ ግፍ ፈጽሞ እና አስፈጽሞ፤ ዛሬ ቀ/ሃ/ስ (አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሕግ ያስተምራል።
 
ዛሬም ሳያፍር
“ሕግ ደካማዉ በጉልበተኛው የሚመታበት መሳርያ ሆነ፤ ህግ ዝሆኖችን የማትነካ የስልጣን መከታ የሌላቸው የታችኛው አመራርና ሲቪል ሰርቫንቱ መምቻ ሆና እንደማየት ምን እሚያሳቅቅ ነገር አለ? በህግ መግዛት ነገስ፤ የመልካም አስተዳደር እንቅስቃሴ ከጅምሩ እየተኮላሸ ነው። ካልተስተካከለ የዉድቀት መንገድ ነው።,,……..ከፍተኛ አመራሮቹም በግልና በቡድን ተጠያቂ የሚሆኑበት እና ለህዝቦች በግልፅ የሚታወቅበት ሁኔታ መፍጠር በዚህም ስርዓቱን እንዲያስተካክሉ ማድረግ ለነገ የማይባል ስራ ነው።”እያለ የውሸት ብዕሩን እውነት የሕግ ተቆርቋሪ መስሎ ያሳስታል። ምንጭ “የተገኝዉን ሰላምና እድገት የሚንድ የአመራር ዘይቤ ባስቸዃይ ይታረም!(ሜ/ጄ አበበ ተ/ሃይማኖት)” Monday, April 4, 2016 (Horn Affairs)

እንያም ሆኖለ በደም የጨቀየው የራሱና የወያኔ ማሕደርን ሲያሞካሽ አሁንም ሳያፍር እንዲህ ይላል፤

“ተቋማት እዉነተኛ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲሆኑ በማድረግ ዴሞክራቲክ ብሄርተኝነት ያስፋፋ። ቁርጠኝነት እና ጥበብ በተሞላበት መንገድ ከተሰራ አሁንም እማይቻል ነገር የለም፤ ምክንያቱም ኢህአዴግ ከሞት አፋፍ ተነስቶ፣ አንሰራርቶ ለድል የመብቃት ባህል አለውና።” ይላል። “የተገኝዉን ሰላምና እድገት የሚንድ የአመራር ዘይቤ ባስቸዃይ ይታረም!(ሜ/ጄ አበበ ተ/ሃይማኖት)” Monday, April 4, 2016 (Horn Affairs) ይላል።

ያለ ምንም ወንጀልና የሕግ አካሄድ ሳይደረግባቸው በጫካ ሕግ መሰረት “በወያኔ ጥይት ተረሽነውና በእሳት ተለብልበው” የሞቱት እና ከሞት አፋፍ ተነስተው ዘላለማዊ የሕሊና እና  የአካል ጉዳት ያተረፉት” ወገኖቻችን ገራፊዎቻቸውና ገዳዮቻቸውን ሕግ ፊት አቁመው ሊጠይቁ አልተፈቀደላቸውም። ወያኔ በሰው ደም አንሰራርቶ “ለድል” ቢበቃም፤ ዛሬ እንዳያንሰራሩ ቃላቸው የታፈኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ግፉኣን ዘመዶቻችንና ዜጎቻችን አንድ ቀን እነ አበበ ተ/ሃይማኖትና በመቶ የሚቆጠሩ የወያኔ ወንጀለኞች ለፍርድ ይቀርባሉ። አለማፈሩ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሕግ ያስተምራል ሲሉኝ፤ ከመገረም አልፎ ብስጨዕትና ቁጭት ነው ያሳደረብኝ። የዚህ ሕዝብ ነብስ እንዴት መቀለጃ ሆኖ እስከዛሬ ድረስ ያለ አንዳቸውም ተጠያቂነት ሊዘልቁና ሊንደላቀቁ አንደቻሉ ሳስበው እጅግ፤እጅግ፤እጅግ ይገርመኛል።

ጥፋቱ ወንጀለኞቹ ሳይሆኑ፤ ተማርን ብለው የሕግ ዲግሪ ሰቅለው እነዚህ ወንጀለኞች በየዓለማቱና በየከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተዘዋወሩ ሲማሩና ሲንሸራሸሩ፤ የሕግ ምሁራኖቻችን በየሳምነቱ ስለ መብት መጣስ በየኢንተርኔቱ ከመለቅለቅ ባሻገር አንድም ፍሬ እስካሁን ሊያሳዩን አልቻሉም።…የሰውን ለጅ በእሳት እያቃጠሉ ሲመረምሩና ሲደበድቡ የነበሩ የኢትዮጵያ አውሬዎች; ስለ የሰው ልጅ መብትና ስለ ባሕር ወደባችን መከበር ሊያስተምሩን ሲፈቀድላቸው (ይግረም ደግሞ ያውም አንዳንድ ጸፋቸው በተቃዋሚ ድረገጽ ላይ ሲለጠፍላቸው) የሕግ ምሁራኖቻችን በፍርሃት ጀርባቸውን ሰጥተው አይተው እዳላይዋቸው እያለፏቸው ነው። ጠበቃ ያጣ ሕዝብ!
አመሰግናለሁ።

ጌታቸው ረዳ (የኢትጵያን ድረገጽ አዘጋጅ/ Google it at Ethiopian Semay) getachre@aol.com

No comments: