ከመርሳት ማዳን ያለብን ታላላቅ ትውስታዎቻችንና ማንነታችን
ጌታቸው ረዳ
Ethiopian Semay 1/23/23
Please do not forget to watch the video attached at the end after you read.
ባለፈው ጊዜ ስለ ልደቱ አያሌው ተከታታይ ጽሑፍ ማቅረቤ ታስታውሳላችሁ። ትችቴ በልደቱ ይሁን እንጂ እንደ ልደቱ የመሰሉ በሺዎቹ ከሃዲ (ባንዳ) ፖለቲከኞችና (ደካማ) ምሁራኖችን ነው የተቸሁት።
በፖቲካው አለም ብዙም ልምድ የሌላችሁ አንባቢዎች ትችቴ እንደ ቀላል ትችት መስሎ ሊታያችሁ ይችላል። ለ30 አመት የዘለቅነው እልህ አስጨራሽ ትግል ባንዳዎችን በመታገል ነበር።። ባንዳ የነበሩ ዛሬ በሚሊዮኖች ግምባር ቀደም ታጋዮች ሆነው ተቀላቅለውናል። ብዙዎቹ አመርቂ አስተዋጽኦም እያደረጉ ነው። ወደ እኛው ጎራ ለመቀላቀል በቀላሉ ዘው ብለው አልነበረም የተቀላቀሉን። ዕንቅልፍ አጥተን በምንጽፋቸው በምንከራከራቸውና በምናነቃቸው የብዕር ትግላችን ነው። ወያኔ በጠምንጃ እንዳልተወገደ ታውቃላችሁ። እኛ በምንጽፋቸው የብዕር ትግሎች ወጣቱን ስላስነሳነው ነው።
የኔ የፌስ ቡክ ወዳጆች የሆናችሁ አዳዲስ ወጣቶች በፌስቡክ ላይ ስንቶቻችሁ እንደተከታተሉኝ መረጃ ባይኖረኝም (ጽሑፉን አንብበው ምልክት ሳይሰጡ የሚያልፉ አንባቢዎች ስላሉ) በድረገጼ ላይ ግን የቆዩ ደምበኞች ስላሉኝ ስለሚከታተሉኝ በርካታ ሰዎች እንዳነበቡት አውቄኣለሁ። አዲሱ ትውልድ ለ30 አመት ባሳዛኝ ደረጃ የማንበብ ችሎታና ፍላጎቱ “በሴራ” እንዲዳከም በመደረጉ ብዙዉን ጊዜ ሰፋፊ ሰነዶችን ከማንበብ ይልቅ ፎቶግራፎችን አጅግ “ጥልቀት” የሌላቸው አጫጭር ጽሑፎችን እና የመሳሰሉ ጊዜያዊ እርካታ በሚሰጡ የማሰብ ችሎታን በማይፈታተኑ ላይ ትኩረት በማድረግ ሕሊናው ሳያውቀው እየላሸቀ አሁን ላሉ ገዢዎቻችን ብቻ ሳይሆን ለሚመጡ ገዢዎችም ተመቺ “ተንቀሳቃሽ ዕቃ” ሆኖ እያየነው ነው።
እባካችሁ “ሼር” አድርገት ወይንም “እባካችሁ አንብቡኝ እማ!?” በማለት የሚማጸኑዋችሁ ጸሐፍያን ገጥሞዋችሁ ያውቃሉ? ከነሱ አንዱ እኔው ነኝ። የሚያስለምናቸው በጣም ግልጽ ነው። ትውልዱ ግብዝ በመሆኑ እባካችሁ እያሉ የሚለምኑበት ምክንያት ከላይ በገለጽኩት ምክንያት የተሰለበ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ካነበቡኝ ውስጥ አገራዊ ቁጭት በማሳደር ጥቂት የሚቆጫቸው ሰዎች ካገኘሁ በእነዚህ ጥቂቶች ሕሊና ውስጥ ካደረ ሌላውን እያስተላላፉ በጠላቶችና በባንዳዎች የተዳከሙትና የተፋቁትን የወላጆቻችን ቅርስም ሆኑ የተነጥቅናቸው የወደብ ባሕሮቻችንና በመጠቃት ላይ ያለው ሰንደቃላማችን ከመርሳት ማዳን ያለብንን ትላልቅ ማንንታችንን ሊያሳድሱት ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ብዙ ሰዎች አላወቁትም እንጂ የትግሉ ዋናው መርሕ ይኼው ነው።
እኔ የምተቻቸው ፖለቲከኞች ስለ መጻኢዋ አገር እጅግ አደገኛ ተምበርካኪዎች የሆኑትን ነው ። ከልምድ ምን እንደሚከሰት አውቃለሁ። ለምሳሌ ይህ አደገኛ የኦሮሙማ የአብይ አሕመድ ሥርዓት ከመምጣቱ በፊት ከአመታት በፊት “በተቃዋሚ ስም” ሲታገሉ የነበሩት እነ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ብርሃኑ ነጋም ሆኑ መሰሎቻቸው ላይ የጻፍኩትና በቃለ መጠየይቅም የተናገርኩት ነገር አንድ ሃቅ ነበር ።
ላስታውሳችሁ፤-
“ወያኔ ሲወገድ በሚከሰተው መጪው አዲስ ሥርዓት ትግላችን የሚሆነው ከነዚህ የአሁኑ ተቃዋሚዎች ጋር ነው” ብየ ነበር። ያለኩትም ሆነ። ኢሳት የነበሩ ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ፤ ታማኝ በየነ፤ አቡበከር አሕመድ፤ አሕመዲን ጀበል፤እነ ንአምን ዘለቀ፤ የሕግ መምህርና ጠበቃ አለማዩየሁ ገብረማርያም (አልማርያም) ፤ ጠበቃ ደረጀ ደምሴ ቡልቲ፤ ብርሃኑ ነጋ፤ቅጣው ያየህይራድ (ኔዘርላንድ)፤ የሺዋስ አሰፋ ፤ ብርትኳን መዲቅሳ ወዘተ..ወዘተ…በደፈናው ወያኔን እንቃወማለን ሲሉ የነበሩት ብዙዎቹ ዛሬ የማን ደጋፊዎች እንደሆኑ የምታዩት እውነታ ነው።
በኢሳትና በብርሃኑ ነጋ በኩል ወደ ኢትዮጵያዊነታቸው ተመልሰዋል እያሉ ሲሰበክላቸውና ሲያደነቁሩን የነበሩት መላው የኦሮሞ ነጻ አውጪዎችና እነ ታማኝ በየነ ሲጮሁላቸው የነበሩት እነ አሕመዲን ጀበልና አቡበከር አሕመድ ..ወዘተ..ወዘተ… ዛሬ የማን አገልጋዮች ሆነው ፤ ብዕራችን ዛሬም በነሱ ላይ እያነጣጠረ እረፍት እንዳሳጡን ህያው ምስክሮች ናችሁ። ያኔ ትግላችን የሚሆነው ከነዚህ ሰዎች ጋር ነው ብየ እንዲያ ስናገር ያመነኝ ይኑር አይኑር አላውቅም። ያምናሉ ብየም አልገመትኩም ነበር። ያኔ ሕዝቡ ተሰልቦ ስለነበር።
ነገን በዛሬ ይመሰረታል የሚባለው ልክ ነው። የዛሬ ባንዳዎች የነገ ክፉ ውጤት አመንጪዎች ናቸው። ዛሬ ፖለቲከኞቹ ሲንበረከኩ ነገ አገርም አብራ ተምበርካኪ ትሆናለች። በተምበርካኪዎች ምክንያት የተነጠቅነውን ሁለቱ የባሕር ወደቦቻችን ምን ዕዳ እያስከፈለን እንዳለ ዓለም ያውቀዋል።
ባለፈው ወቅት የጠቀስኳቸው ምጽዋ ላይ የተሰውት ጀኔራል ተሾመ እንዳሉት “መስኮት የሌለው ቤትና ባሕር የሌለው አገር አንድ ነው” እንዳሉት ኢትዮጵያም ዓለም ተዘግቶባት የሶማሊያ፤ የጅቡቲ የዓረቦች የኤርትራኖች የአሜሪካኖች ወዘተ…. ግብር ከፋይ ሆና “የቀይ ባሕር ባርያ” ሆና መቀጠልዋ ስትመለከቱ ስንቶቻችሁ እንደሚቆጫችሁ አላውቅም። በዚህ ባሕር ዕጦትና በውስጥ ጦርነቶች ብዛት ምክንያት ከጊዜ ብዛት ጭራሽኑም አገሪቱ ለባህር ወደብ የምትከፍለው ዕዳ ሳትከፍል ብትቀር እንደማትፈርስ ወይንም ምዕራባዊያንም ሆነ አረቦች ወይንም ግብጾች እንደማይወርሩን እርግጣኛ ሆኖ ዋስትና የሚሰጥ የለም። እንደምታዩት አገሪቱ እየኖረች ያለቺው በልመና በሚገኘው ስንዴ ነው።
ትናንት ወደቦቻችንን አስረክበናል፤ ዛሬ ደግሞ የቆዩ ቅርሶችን እየፈረሱ ሃውልቶች እየተደረመሱ ናቸው። ይቀጥልና ኦረሙማ የተባለ አረመኔ ቡድን “ኦርቶዶክስ ሃይማኖትን” ለማፍረስ መፈንቅለ ፓትርያሪክ አድርጓል። ለዚህም ተዋናዮቹ ኦረመኔዎቹ ብቻ ሳይሆን “የባንዳዎች እጅ” ድጋፍ ስላለበት ነው።
ስለሆነም ነው ለተምበርካኪ ፖለቲከኞችና ባንዳዎች ጀሮ አትስጡዋቸው እያልኩ ለ30 አመት የዘለቅኩበት ምክንያት ለዚህ ነው።
ሰሞኑን እኔን የመሰለ አንድ የሶቭየት ጻሐፊ ከታተመ ከ100 ዓመታት በኋላ የሆነው Pressenza የተባለው መጽሔት “ለህልም ፍላጎት” የሚል ርዕስ አውሮጳ ውስጥ በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ ብቅ ብሎ ሕትምት ሲጀምር: በነ ጎርባቾቭ የመሳሰሉ ሶቭየት ሕብርት ያፈራረሱ ባንዳዎች አንገታቸው ደፍተው የነበሩ “አገራዊያን” ምጽሔቱን ሲያነቡት “የትንሳኤ ጨረር” በሚል መልዕክት አጨናንቀውታል። እነ ጎረባቾቭና እነ የልሰን ወደ ሥልጣን ሲመጡ የቆየው “ዓለም አቀፍ ድሆችና ሰራተኞች ተባባሩ” የሚለው ታግዶ የነበረው የጥንቱ የሶቭየት ሕብረት ብሔራዊ መዝሙር ፑቲን ወደ ሥልጣን ሲመጣ ታዋቂ ኳየር (ኦርኬስትራ) ሊቃውንት ሰብስቦ እንደገና እንዲዘጋጅ አድርጎ ብሔራዊ መዝሙር ሆኗል።
የሶቭየት ሕብረት ከተመሠረተ ከ 100 ዓመታት በኋላ Pressenza መጽሔት በጃንዋሪ 10፣ 2023 ብቅ ብሎ ለሕትመት
ሲበቃ የቀረበው ሰፊ ሐተታ ቢሆንም ከመርሳት ማዳን ያለብን ትልቅ ትውስታ ለሙዚየሞች ብቻ አይደለም: ነገር ግን ለሚመጣው አዲስ ቅኝትና ትውልድ እንደ ቁሳቁስ ገና ያልተሰራ ትልቅ ተግባር መስራት ላይ ማትኮር አለብን ይላል።
ፀሐፊው በመቀጠልም እንዲህ ይላል፤
<< ከጥቂት ወራት በፊት ከዚህ አለም በሞት ከተለዩት ታላቅ ሰው ልጅ የቼ የበኩር ልጅ “ካሚሎ ጉቬራ” ጋር በሃቫና እየተነጋገርን የሶቭየት ህብረትን በአለም ታሪክ ውስጥ ያለውን ሚና ለመተንተን ስንሞክር እንዲህ አለኝ፡-
(…) እያወራን ያለነው በሁሉም ጥርጣሬዎች ላይ ራሱን የቻለ እና አስደናቂ አብዮት ስላዳበረ ታላቅ ህዝብ ነው። የናዚ-ፋሺስት ጭፍሮችን በህዝቧ መስዋዕትነት አሸንፎ የሰው ልጅን በዋጋ የማይተመን ውለታ የሰራ ሕዝብ ነው። ሶቪየቶች የተለያዩ አይነት እና ስፍር ቁጥር በሌላቸው መስኮች ድንቅ ስራዎችን ሰርተዋል። ኢምፔሪያሊስቶች የውስጥ ተምበርካኪዎችን ይዘው ያን ታላቅ አገር ማፍረሳቸው እንዳይበቃ ሶቭየትን የመሰለ ታላቅ አገር የመሰረቱና የናዚ ጦርን ያሸነፉ ታላላቅ መሪዎች ሃውልት እንዲፈርስና ስማቸው ከታሪክ እንዲፋቅ ያደረጉ ባንዳዎች ስመለከት እጅግ ይከነክነኛል።….” አለኝ ይልና
የውስጥ ተምበርካኪዎች በቆዩ ቅርሶች እና ታላላቅ መሪዎች ላይ የማጠልሸት ስራ ሲሰሩ “ኢምፔሪያሊሰቶች” አላመኑም ነበር። እኔም እንደዚህ አይነት ነገር ይደረግ ይሆናል ብየ ካላመኑት አንዱ ነኝ። ያም ሆኖ ቢደርግም እንዲህ ያለውን ግዙፍ ሥራ ለማጥፋት የሚያስችል ኃይል እንደሌለ ሁልጊዜ እርግጠኛ ነበርኩ። ከስሜታዊነት ወይም ከርዕዮተ ዓለም ዝምድና ያልተያያዘ አገራዊ ዙፋን ማደፉን የሚቆጨው እንደ በአንድ እርሻ ላይ ጥሩ ቡቃያ በድንገት እንደሚበቅል ሁሉ እንዲያ የሆነ አዲስ ትውልድ እንደሚከሰትም አልጠራጠርም” ብሎኝ ነበር ይላል ጻሐፊው።
ካለ በኋላ ጸሀፊው፤
ያገራችን ታላቅነት ለማደስ ተነስተናል፤ እኛን ለመጨፍለቅ የሚገዳደሩም አይጠፉም፡ እየተያየን ነው። ዓለም ያለ ተገዳዳሪ አልተፈጠረችም ወይንም አትኖርምና አገራችንም የጥንት ታላቅነትዋን ለማስነሳት አንድ ጉዞዋን ጀምራለች። ከኢምፔሪያሊስቶች ተደናግጠዋል፤ ፑቲንም የወላጆቹን አርማ አንስቷል! ሲል ደምድሟል።
የተለያየ ስም ቢሰጠውም ጦርነት አወዳሚ ቢሆንም ላገር ክብር ሲባል እንደ አዲስ ቡቃያ አጋጣሚ ብቅ ብሎ ወደ ስልጣን የበቀለው ፑቲን ሩሲያኖች የቀድሞ ሉኣለዊነታቸውን እንዲያስታውሱ አድርጎ ምዕራባዊያኑን እያስጨነቀ ነው።
ይህ ልዩ እውነታ እኛ ኢትዮጵያዊያንም እንደ ፍጡራን ሰዎች ታሪካዊ ትውስታችን ይዘን እንድንቆይ ትልቅ ፍላጎት እንደሚሰማን ይነግረናል ። ያ ጥንታዊ የኢትዮጵያዊነት ፕሮጀክት ከብርሃን እና ጥላ ጋር ወደፊት የሚለው የቃል ተስፋ ሰንቀን መሄድ አለብን። በነዚህ የ30
አመት የውስጥ ቅኝ ግዛት አሳዛኝ ገጠመኞች ማንነታችን ቅርሶቻችን፤ ወደቦቻችን ፤ ሃይማኖታችን እና ታላላቅ አርበኞቻችን ለውርደት ተጋልጠው ማየት፤ መራራ ቢሆኑም በማይምበረከኩ ልጆችዋ በማያቋርጥ ተከታታይ ንቃት “የተከናነብነው ውርደታችን”
ዘላለማዊ ሆኖ እንደማይቆይ በጊዜ ሂደት ሊቀለበስ እንደሚችል ተምረናል።
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay
Haile Selassie Accepts Eritrea (1952)
No comments:
Post a Comment