Sunday, January 15, 2023

በውሸት የመነዳት ወይስ ዲሞክራሲ የማጣት የችግራችን መበርታት ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay 1/15/2023

 

በውሸት የመነዳት ወይስ ዲሞክራሲ የማጣት የችግራችን መበርታት

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay

1/15/2023

ሰላምታ እንደምን አለችሁ? ቀውስ ከገባን ብዙ አመታት ሆኖናል። ብርቱ ቀውስ ያየንበት ወቅት ደግሞ በዘመነ ኦሮሙማው አብይ አህመድ በዚህ 5 አመት ውስጥ ነው።

በብልህ እና የማያቋርጥ ፕሮፓጋንዳ በመተግበር ሰዎች ገነትን እንደ ገሃነም እንዲመለከቱ ማድረግ እና በጣም መጥፎ የሆነውን ሕይወት እንደ ገነት እንዲመለከቱ ማድረግ ይቻላል ። (ሂትለር)”

“Through clever and constant application of propaganda, people can be made to see paradises as hell and also the other way around to consider the most wretches sort of life as paradise.” (Hitler

በዚህ ቀውስ ውስጥ እንዴት ልንገኝ ቻልን? ብዙዎቻችሁ የምትሰጡት መልስ “ዲሞክራሲ” በመታጣቱ ነው እንደምትሉ በእርግጠኛነት መናገር እችላለሁ። እንዲህ ያለ ድምዳሜ ልትይዙ የቻላችሁበት ምክንያት “የፖለቲካ መሪዎች” በዚህ እምነት ብዙ ጊዜ ደጋግመው ሲያስተምሩና ሲሞግቱ በመስማታችሁ፤ ያንን እንደ እውነታ ተይዞ “የዲሞክራሲ” እጦት ለዚህ ዳርጎናል፤ ወደ እሚለው ድምዳሜ ልትድርሱ አስችሏችሗል። ዲሞክራሲ በሌለባቸው አገሮች ሕዝቦች እኛ ካለንበት በተሻለ ህይወት የሚኖሩ በጣም በርካታ ሕዝቦች አሉ።  ለመሰደዳችን እና ለመበጣበጣችን ዓይነተኛ ምክንያት ዲሞክራሲ በመታጣቱ ሳይሆን፤የምንከተላቸው መሪዎችና ድርጅቶች/ወይንም መንግስት፤ “ስለሚዋሹን” ነው።

በዋሹ ቁጥር፤ ወንጀል ይሰራሉ፤ ሕብረተሱም አብሮ ተካፋይ ይሆናል፤ አስተጋቢ ዋሾ ሆኖ ይዋሻል፤ወይንም ሲዋሹ ይታገሳቸዋል፤ ግፉም አብሮ ይበረታል። ውሸት ሕብረተሰብን “የሚገድል እና የሚያጋድል” መሰረታዊ የሆነ ማሕበራዊ ነቀርሳ ነው።

ውሸት ምን ማለት ነው?

ውሸት ማለት የተነገረና የተደረገ ነገር መካድ ማለት ነው። እውነት ደግሞ ‘ሃቅ’ ማለት ነው።ሃቅ ማለት ደግሞ ነገሮች ሳያጠማዝዙ፤ሳይደብቁ፤ሳይሸሽጉ፤ሳያታልሉ የተደረገው፤ የሆነው፤ የተነገረውን ነገር ሁሉ መናገር ማለት ነው።ውሸት ብዙ ክፍሎች አሉት። መዋሸት ማታለል፤ መጠምዘዝ እና መደበቅ። ፈረንጆቹ deceiving lying, spinning, concealing የሚሏቸው ማለት ነው። በነዚህ ስር ደግሞ ብዙ ዘርፎች አሉዋቸው።“ በዚህ ርዕስ ከብዙ አማታት በፊትስለጻፍኩበት ያንን በድረገጼ መመለክት ነው።

‘ዋሾ’ መሪዎች፤በዋሹ  ቁጥር ምሁራን የውሸቱ ዋና አዝማቾች ሆነው ሕብረተሰቡም አብሮ እየዋሸ ‘እየታገሳቸው’ በሄደ ቁጥር “የሚፈለገው” ሰላማዊ የሆነ ፍትሕ የነገሰበትና ‘ተጠያቂነትን’ የሚያከብር ስርዓት እንዳይመጣ እንቅፋት ይሆናሉ ማለት ነው። “ውሸትና ዋሾ መሪዎች” በግሃድ ዓለም በግልጽ ባለመተቸታችን ለቀውስ እንዳረጋለን ተዳርገናል።

 ተጠያቂነት ያለው ስርዓት እንዳይሰፍን (ዲሞክራሲ፤ሪፑብሊክ፤ሶሻሊስት…..የፈለጋችሁ በሉት) ውሸት አጥቂ ሆና፤እውነት የመጀመሪያዋ ተጠቂ ረድፈኛ ሆናለች። ውሸት፤ መሪዎችን ብቻ ሳይሆን የሕብረተሰብን ጤነኛ ህሊና የመንጠቅ ሃይል ስላለው፤ በመሪዎች አማካይኝነት “ዕብድ ሕብረተሰብ” ይከሰታል። ኦሮሞዎች፤ ትግራይን፤ ኤርትራን እና ሶማሌን ብትወስዱ ማሕበረሰቡ በውሸት እራሱን አታልሎ በስሜታዊ እኔነት የተነሳ እራሱን ያጣ ማሕበረሰብ ወደ መሆን የተከሰተበት ምክንያትም ይኼው ነው።

ሕበረተሰቡ በታወሸ ቁጥር እውንት እየመሰለው በስሜት እየጋለበ እውነትን “ያጠቃታል” እውነት ስትጠቃ ሕብረተሰቡ ወደ ትርምስና ስደት ይገባል።

ውሸት እንዲሁ ከደመና የምትፈልቅ አየር ነገር አይደለችም። በማሕበረሰቡ ሕሊና መኖርያ ተሰጥቷት፤ በተለይም አገር በሚመሩና ከፍተኛ ሃብትን ያከማቹ ንግድ በሚያካሂዱ ቱጃር ሰዎች ተደላድላ የምትኖር፤ እድሜዋም የሚያስቀጥል ጠበቃዎችና ተከላካዮች አሏት። ውሸትን በመድረክ አደባባይ እንዳንተቻት የሚገድቡን “የሚዲያ” ክፍሎችንም እዚህ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አትርሱ።

ለምሳሌ በነ መሳይ መኮንን፤ሲሳይ አገና፤ ፋሲል የኔ አለም፤ ደረጀ ፤ግዛው ወዘተ… የመሳሰሉ ሰዎች ስርዓቱ የሚፈጽማቸው ግፎች እንዳይታዩ የተለያዩ የውሸት መከላከያ  ሽፋኖችን በመስጠት የግፍ ደጋፊዎች ሆነው ታይተዋል።

በተለያዩ ጽሑፎቼ ካሁን በፊት እንደገለጽኩት፤የግፍ መሪዎች ዕድሜ የሚቀጥለው ብዙውን ጊዜ ጋዜጠኞች ለግፍ ሰሪው ሲያድሩ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

 ይህ ሲሆን  ሁለት ክፍሎች ይከሰታሉ። ደላሎችና ነገሥታተቶች። እነዚያ አድርባይ ጋዜጠኞች ደላሎች ሆነው ሕብረተሰቡን ያምታቱታል፤ ግራ ያጋቡታል። ይህ ሲሆን ማሕበረሰቡ በሁለት ባሕሪ ማለትም በ “Dual” (ድርብ) እየተምታታ ለግፍ ይጋለጣል። እነኚህ ክፍሎች በጋዜጠኛነት ቢከሰቱም በጋሃዱ እንቅስቃሴአቸው “ደላሎች” ስለሆኑ አገርን ማበጣበጥ፤ጨቋኝ መሪና ግለሰብን ማንገስ የሚያስችል ሰላቢ የብዕር ችሎታ ስላላቸው፤ ማሕበረሰብን ማፋለስ ወይንም የማረጋጋት ችሎታም አላቸው። ውሸት በነዚህ ክፍሎች ትጎለብታለች ወይንም ትታገዳለች። ስለሆነም፤ ለቀውሳችን ምክንያት “ዲሞክራሲ” ስላጣን ሳይሆን፤ወደ ዲሞክራሲ የሚወስደን መንገድ “ዘጊ ሃይል” ሆነው እያስቸገሩን ያሉት ‘ሚዲያዎች እና መሪዎች” ናቸው (እዚህ ላይ ለስርዓቱ ያደሩ ምሁራን የዚህ ቡድን ሦስተኛው አካል ተዋናዮች መሆናቸውን አትርሱ!!)።

የኛ ነገር ስናጤነው አንጀት ይበላል። አይደል!? የገዛ ልጆቿ ደመኛዋ ሆነዋል። መነኮሳትን የሚያርዱ፤ ቤተ ክርስትያኖችና መስጊዶችን የሚያቃጥሉ ዜጎች በብዛት ተፈጥረዋል። የኦሮሚያ አገር ዜጎች ነን፤ ኤርትራ ነን፤ትግራይ ሪፑብሊክ ነን …..የሚሉ ራሳቸውን ያጡ ክፍሎች ተከስተው፤ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን፤ እንዲሁም ሌሎቻችንም ነካክተው ለስደት ዳርገው የቀውሳቸው ሰለባ አድርገውናል።

ሕብረተሰቡ ከሚዋሹት ዕብዶች ጋር አብሮ ውሸታቸውን እንዲያጅብ በማስገደድም ሆነ በማታለል፤ ሕብረተሰቡ ውዥምብር ውስጥ ጨምረውታል። ይህ ለምን ተከሰተ? መሪዎች ሲክዱ፤ሲዋሹ፤ነገሮችን ሲጠማዝዙ፤ሲያጭበረብሩ፤ ሕዝቡ የነዚህ ሰዎች ባሕሪ እየተከተለ ዋሾ እየሆነ እራሱን እያጣ፤ የሱዳን፤አውሮጳ፤ካናዳ፤አሜሪካ፤የአውስትራሊያ…. አገሮች ዜጋ እንዲሆን እየለመነ፤እንደዋዛ  ቀስ በቀስ እራሱንም አገሩን አጥቷል። ጭራሽኑ አንዳንዱም ኢትዮጵአዊ አልነበርኩም ጥቁር አይሁድ ነኝ ብሎ የጥቁር መፈጠሪያ ኢትዮጵያን ክዶ ጥቁር ባልተወለደበት ምድር ወደ ነጮቹ አገር ወደ እስራኤል እየጎረፈ ሲደብረው የአማርኛ እስክስታው እያቀለጠ የጽዮናዊያን ጠመንጃ አንጋች ሆኗል።

በየዓለማቱ እንድንሰደድ ያደረገን አንዱ ምክንያት የመሪዎቻችን “ሞገደኛ-ውሸት” ከመሃል መስመር ወደ ውጭ ተገፍትረን እንድንጣል ስለገፋን ነው። ሳናስበው እራሰችንን አጥተን የሰው አገር ዜጋ የመሆናችን ክስተት እጅግ አሳዛኝ ነው! አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ ለስደታችን መንስኤ የሆኑ የድርጅት መሪዎችና ምሁራን አገር እየጣሉ ከኛው ጋር ተቀላቅለው፤ እንደገና እነሱንም በማጀብ፤ ዛሬም የነዚህ ክፍሎች ሰለባ የመሆናችን ክስተት እየቀጠለ መሆኑን ስንመለከት ሕብረተሰቡ በክፉኛ የተቃወሰ ሕሊና መጠቃቱን አመላካች ምልክት ነው።ለዚህ ድግሞ ፓልቶክ መድረኮች፤ፌስቡኮች እና ዩትዩብ መድረኮች ጠቋሚ ሚዛን ሆነው እናገኛቸዋለን።

በነዚህ መድረኮች የሚሰነዘሩ ስብከቶች ስናደምጥ የሕብረሰተሰቡ ትክክለኛ የሕሊና ግራፊክ/ስዕል/ በቀላሉ መምዘን ያስችላችሗል። እንዲህ ያለ የተደናበረ ማሕበረሰብ የስነልቦና እና የስነ አእምሮ ሊቃውንት፤እውነተኛ ፓለቲከኞች ጋር ሆነው ተሎ ካልደረሱለት፤ ‘ጨርቁን ጥሎ’ ያበደ ማሕበረሰብ ተብሎ ባይጠራም፤ በውሸት የሚነዳ ‘ሕሊና ያጣ” ማሕበረሰብ የመሆኑ የማይቀር ሃቅ ነው።

ለዚህ ሁሉ ጠንቅ፤ ዛሬም ውሸተኞችና ወንጀለኛ መሪዎች በሕግ እስካልተቀጡ ድረስ ማሕበራዊ ቀውሱ ማቆሚያ የለውም።

አመሰግናለሁ፤

ጌታቸው ረዳ                                                                                             

 

No comments: