አዎ የዓድዋን በአል ለማክበር እንመጥናለን
መልስ ለጋዜጠኛ ቴድርስ ጸጋዬ ርዕዮት
ሚዲያ
ጌታቸው
ረዳ
(ኢትዮ
ሰማይ)
3/5/22
ሰላም ለሁላችሁ ይሁን እያልኩ የርዕዮት የውይይት እና የዜና ማሰራጫ ማዕከል ባለቤት የሆነው “ጋዜጠኛና የሕግ ምሁር የሆነው ቴድሮስ ጸጋዬ” ዘንድሮ የ 126 ኛው የዓድዋው የድል በዓል አከባበርን አስመልክቶ በመላ ኢትዮጵያ የተከበረው በዓል ‘አክባሪዎቹን’ “አድዋን ሊያከብር የማይመጥነው ትውልድ..” በሚል ርዕስ የተቸበትን አብዛኛዎቹን ትችቶቹ ለምን እንደማልስማማባቸው አሳያለሁ።
አንዳንድ ትችቶቹ ተቀባይነት ያላቸው ቢሆኑም ማጠንጠኛው ላይ ግን ቴድሮስ በጠባብ ትግሬነትን የተተበተበትን ገመድ ጠልፎ ሲያደናቅፈው እየተሰማውም ቢሆን ያንን ‘ትብ-ትብ’ ለመበጠስ ሲያስቸግረው ታዝብያለሁ።
ትችቱን ከመግባቴ በፊት ስለ ቴድሮስ አሁናዊ መስመሩን እንመለከታለን።
በአጼ ምኒሊክ የተመራው ጦርነትና ድል ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፈው ያምናል።እዚህ ላይ ችግር የለም።ለብዙ አመት ያከበረው እና ያደመቀውም መሆኑን ለብዙ አመታት የምናውቀውን ቴድሮስን በዚህ የሚታማ አይደለም። ዛሬም በዓሉን እንደ መታወቂያው አድርጎ እንደሚቆጥረው ተናግሯል። ስለ በዓሉ ይዘት ችግር የለውም።
ችግሩ የመጣው የወያነ ትግሬዎች ሥልጣናችን በአብይ አሕመድ ሳይሆን በአማራ “በነፍጠኛ” ለምን ተነጠቅን በሚል የውሸት ምክንያታቸው ኢትዮጵያ ላይ በከፈቱት ጦርነት ያስከተለው “ጦስ” (ኮንሲኮንስ) በትግራይ ሕዝብ ላይ እና በራሱም “ሳይክ” ያሳደረበት ጫና “ከዚህ በዓል አከባበር ጋር” በማያያዝ በብዙ ኢትዮጵያ ክፍሎች ያከበሩትን አካባሪዎች “መንጋ” በሚል ሰይሞ በዓሉን ለማክበር አይመጥኑም ሲል ይኮንናቸዋል።
እየለየ ስም እየጠራ ቢተችም በጠቅላላ “ይህ ትውልድ” በማለት በዚህ ትውልድ ዘመን በሕይወት ያለነውንም
ጭምር የዓድዋን ድል ለማክበር “የማትመጥኑ መንጋዎች” ሲል ኮንኖናል።
እኔ እንዴት እንደምመጥን በሗላ እምለስበታለሁ።
ቴድሮስ ለዚህ ሁሉ ድምዳሜው ከመለስ ዜናዊ የማይሻል “የኢትጵያን መሬት ለሱዳን ፈቅዶ ያስረከበ” (የሱዳን ጦር እንዲገቡ ፈቅዶ እንደሰጣቸው የሱዳሰን መሪዎች ነግረውናል) ባንዳው የኦሮሙማው አብይ አሕመድ የሚመራው ሥርዓት በትግራይ ላይ የዘር ማጥፋት አዋጅ ሲታወጅ “መንጋ” ብሎ የጠራውን አገር ውስጥም ውጭ አገርም በዓሉን ያከበረው አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ አዋጁን ባለመቃወሙ ኮንኗቸዋል።
ወያኔዎች ብለው ራሳቸውን የሚጠሩ ትግራይ ውስጥ የበቀሉ በመንፈስ “የሙሶሎኒ
ልጆች” የሆኑ ወያኔዎች ያቀዱበት የተዘጋጁበት እና የፈለጉትና የከፈቱት ጦርነት (ቴድሮስ ጀማሪዎቹ ወያኔዎች አይደሉም ቢልም) በተከተለው
የዘር ማጥፋት ወንጀል ትግራይ ሕዝብ በኢኮኖሚ ማዕቀብ ገብቶ በከበባ ሲጨነቅ “ከበባውን ለምን አልተቃወማችሁም” የሚል ነው የቴድሮስ
መነሻ። ስለሆነም ዓድዋን ድል ለማክበር አይመጥናችሁም ነው ክርክሩ።ነገሩ በግማሽ ቢያስኬድም መንጋውን በኮነነበት ልክ ወያኔዎች
የዓድዋን በዓል “በወያኔ መዝሙር” በትግራይ ፖሊስ ኦርኬስትራ እየታጀበ ዓድዋ የትግሬዎች እንጂ የነ ምኒሊኮች አማራዎች አይደለም
እያሉ በአደባባይ ሲያከብሩ “ቴድሮስ ጸጋዬ” እሳት የለበሰው የተዋጣለት ምላሱ እዛ ጎራ ሲደርስ ምነው ተተበተበት? የሚል ጥያቄ
ላቀርብለት እፈልጋለሁ።
ቴድሮስ “የወያኔ መሪዎችና ጀሌዎቹን በሚመለከ ዓድዋን የማክበር ሞራል የላችሁም፤ አትመጥኑም ብሎ አንድ ሰዓት የፈጀ ፕሮግራም በራዲዮኑ ሲናገር ሰምታችሗል? ከሰማችሁ ንገሩኝ? ለምን ዝም አላቸው? ወገናዊነት ወይስ አልሰማም? አላወቀም ሆኖ? ያውቃል እንጂ። እነሱን ለማውገዝ የሚያስችለው ቅናቱ ተፈትቷል። ሰዋስውኛው “ትግራዋይነት” ስለሆነበት ነው። ሌላ ቋንቁኛ የለውም።
እኛ ኢትዮጵያዊያን በዓሉን ለማክብር እንዴት እንደምንመጥን እና እርሱ ለወገነለት የትግራይ መከላከያ ጦር ተብሎ ለሚያሞካሸው ለወያኔ ድርጅትና ወራሪ ጦር ግን ዓድዋን ለማክበር ሞራሉ እንደሌለው እገልጻለሁ።
በተጨማሪም ስለ ማዕቀቡና ከበባው አስመልክቶ ኢትዮጵያዊያንን ሲኮንን የትግራይ ሕዝብ ለ47 አመትና ዛሬም ለዚህ ጦስ መነሻ ለሆነው “ወያኔ” የተባለው አክራሪ የፋሺስት ድርጅት እራሱን ለማላቀቅ ምን ስራ እየሰራ ነው? የሚለውን ጥያቄ ለቴድሮስም ይሁን ለአምሳያዎቹ ይህ ጥያቄ አቀርባለሁ።
ከበባውን እና ማዕቀቡን ለመበጠስ እስከ ደብረብርሃን ድምበር (?) ድረስ ሄዶ ሱሪውን አሳይቷል የሚል መልስ በቂ ሊሆን አይችልም። እዛ ድረስ ለመድረስ የተከተለው የወንጀል ተግባር ግን ማዕቀቡን የባሰ እንዲጠብቅ አጠናክሮታል።
ይህ ሳይረዳቸው ቀርቶ ሳይሆን አንድ ሕዝብ እራሱን ለፃ ለማውጣት ካልሞከረ ከማዶ ያለውን ሕዝብ ነጻ እንዲያወጣው ለምን ይጠብቃል? ይግረም ብሎ “ወያኔ በአንቀልባ አዝሎ በሺዎቹ የሚቆጠሩ ልጆች በወያኔ ሥር እየተመሩ እንዲሞቱና የአማራንና የዓፋርን ሕዝብ ሴቶች እንዲደፍርና እንዲገድል” ሂድ እያለ የሚያስማራ ሕዝብ እራሱን ከመፈተሽ ይልቅ “ማዕቀብ” ስለተጣለብኝ ሌላውን ሕዝብ ሂድና ታጥቀህ ውረራቸው፤ ሴት መነኮሳትና የ12 ዕድሜ ያላቸው ልጃገረዶችን ድፍር የሚል ሕዝብ “ከምጣኔው ማዕቀብ” ሊወጣ እንደማይፈልግ ማሳያ ነው። ከጎረቤቶችህ ጋር እየተገዳደልክ ምጣኔ ሃብት እንደልብ ይፈስሳል ብሎ “ኤከስፔክት” ማድርግ የትግራይ feeble minded” ሊሂቃን የማሰብ ስፋት ብቃት እንደሌላቸው ያሳያል።
የትግራይ ሕዝብ መጀመሪያ ማድረግ ያለበት እራሱን ለ47 አመት የተጓዘበት መንገድ መፈተሽ ነበረበት። መንግሥቴ “ወያኔ ብቻ እና ብቻ ነው” በማለት አረጋጧል። ስለዚህ መፈተሽ ሳይሆን በዛው አጥፊ ፋሺስታዊ መንገድ ለመቀጠል ከፍላጎት በላይ አሳይቷል።
እየሄደበት ያለው መንገድ ከጥዱ ወደ ማጡ እየሆነ የሚያዩትና የሚገፋፉት እነ ቴድሮስ ጸጋዬ ደግሞ “ሕዝቡ እገነጠላለሁ ካለ ወያኔ መሪዬ ነው ካለ ውሳኔውን አከብራለሁ” በማለት ሕዝብ ፋሺሰትነት እመርጣለሁ ካለ እደግፋለሁ ማለት ያን downtrodden (የተረገጠው ማሕበረሰብ) ይብልጥኑ ለፋሺሰቶቹ አገልጋይ (“submissive) እንዲሆን መፍቀድ ነው።
የወያኔ መጋረጃ ያዢዎች ማወቅ ያለባቸው ወረበላው አብይ አሕመድ በሚመራው ኦሮሙማው ስርዓት ምክንያት የራሴ ቤተሰቦች ተሰቃይተዋል; (ትግራይ ውስጥም ኢትዮጵያ ውስጥም) አሁንም ስቃይ ላይ ናቸው። ሆኖም ኦሮሙማው መንግሥት ቤተሰቦቼን ስላሰቃየብኝ “ኢትዮጵያዊነቴን” በማውገዝ በደም የተጨማለቁትና የትግራይን ሕዝብ እንኳ ሳይቀር ገርፈው ጸጥ ለጥ ያደረጉት ወንጀለኞ በሚመሩት መንጋ ውስጥ መቀላቀል አይጠበቅብኝም።
እኔም ሆንኩኝ ቴድሮስ የሚጠበቅብን አብይን ማውገዝ፤ ወያኔንም ማውገዝና ከሁለቱም ወረበላዎች ነጻ የሆነ ትችት በመተቸት ሕዝቡን ማንቃት እንጂ ‘ዘልሎ” ካንድ ፋሺሰት ወደ ሌላ ፋሺሰት መወሸቅ መፍትሔ አይለም።
ለዘር ማጥፋትና የጅምላ እስር “አብይ አሕመድና ጀሌዎቹ” መሆናቸው እኔም ብዙ ብያለሁ። ለዚህም ቅጣታቸው ማግኘት ይኖርባቸዋል።
ሆኖም ቴድሮስ በአብይ አሕመድ አነሳሽነት በትግሬዎች ላይ የተካሄደው የዘር ማጥፋት አዋጅ ሲያወግዝ በሌላ በኩል ፡ ትግሬዎች ያደራጁትና ያስታጠቁት “ወራሪ፤ ሴት ደፋሪ፤ ቤተ እምነት አፍራሽ፤ ተቋማት ዘራፊና ‘ጸረ አማራ” ዘር አጥፊ በሆነው በወረባላው የትግራይ ጦር ላይ ተመጣጣኝ ክስ ያስተጋባው 1% ነው።
ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያስደመጠን “ክስ” 99% ትግሬዎች መበደላቸው ብቻ ነው። ይህ በሽታ የሚያሳየን በአክራሪ ነገዳዊነት ክር መተብተቡን ያሳያል። ቴድሮስ ከሌሎቹ የትግራይ አክራሪዎች የሚለየው ነገር ቢኖር ቀጥተኛ ከመሆን እየሸሸ በተሰጠው የተፈጥሮ ብልጥ የቋንቋ ስልት አጣቃቀም እየተጠቀመ ከመታየት ለማምለጥ ይሞክራል።
ከመጨረሻ ጽሑፌ በምሰጣችሁ የቪዲዮው መስኮት በመጠቀም የሚከተሉትን ሲናገር ታደምጣላችሁ።
“ይህ ትውልድ በአሉን ለማክበር ይመጥናል ወይ? እኛ ኢትዮጵያ ተወልደን፤አፈርዋን ቅመን ውሃዋን ጠጥተን ተጫውትን ስላድግን በአሉን ለማክበር እንመጥናለን ወይ? ይልና
ዓድዋን ለማክበር “ከበሮ እየደለቁ እያንቋረሩ በመሰባሰብ ሳይሆን የዚያ ጦርነት ትርጉም እና ጣታ ሻራን በተግባር ስንተረጉም ነው እንጂ የዚያን ወራሪ ባሕሪ (የጣሊያን ማለቱ ነው) በገዛ ሕዝቡ ላይ (በትግራይ ሕዝብ ህይወት ማለቱ ነው) የሚፈጽም ሆነ የሚያንጸባርቅ ከወራሪው ያልተሻለ “መንጋ” ትውልድ በዓሉን ለማክበር አይመጥንም! ሲል ሃሳቡን ሰንዝሯል።
ሃሳቡ ልክ ቢሆንም ከላይ እንደገልጽዩትና ከታች እንደምገልጸው የጣሊያን ወራሪ ባሕሪ የተሸከመው የትግራይ ሕዝብ እየቀለበውና እያስታጠቀው ያለው ትውልድስ ዓድዋን ለማክበር ይመጥናል ወይ? ብሎ ቢጠይቅ የተሟላ ያደርገው ነበር፤ ሆኖም ወገናዊነቱን አጠቃውና ያንን ሊነካ አይፈልግም፤፡
ወደ ሌሎች ሃሳቦቹን ከመግባቱ በፊት እኔ በግገኝበት በዛሬው ትውልድ ስለ እራሴ መልስ ልስጥ። አዎ እኔ በዚህ ትውልድ የምገኝ በህይወት ያለሁ ትግራዋይ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በዓሉን ለማክበር በብዙ መንገድ እመጥናለሁ።
መጀመሪያ በአያቶቼ ልጀምር። እናቴ ብርሃናዊት ትባላለች የፊታውራሪ ሓጎስ የልጅ ልጅ ነች። ሓጎስ ጣሊያንን ለመውጋት ከተሰለፉት የትግራይ አርበኞች አንዱ ናቸው። ጣሊያን ድል ሆኖ ከጦርነቱ መልስ ብዙዎች ወደ ገጠራቸው ሲመለሱ እርሳቸውና አንጋቾቻቸው (እኔ በማላውቀው ምክንያ) በወቅቱ አልተመለሱም። ባለመመለሳቸው፤ እንደሞቱ ተወስዶ “በተወለዱበት “ዓዲ ግባ” እንዳጀወርጊስ” አምባ ላይ የሓዘን ጥሪ ተደርጎ “ዳስ ተጥሎ” መላ ገጠር ተሰባስቦ ሲለቀስ ድንገት ደረሱ።
“አረ መጡ ሲባል፤ ሕዝቡና ቤተሰብ ተደናግጦ ዕልልታውን አቅልጦ፡ አንዲት
አልቃሽ “ስለሞመታቸው አስመልክታ በዳሱ ላይ የገጠመቺውን ግጥም”
“አታልቅሱ፤ አታልቅሱ” ሲባል፤ እሳቸውም፤ ባልሞትም ያያሁት ነገር ከሞት አይተናነስም የሚል “አልሞትኩም ብየ አልዋሽም” ዓይነቱ
የትግርኛ ግጥም መልሰው ገጠሙ።
ከስንኞቹ ጥቂቶቹ ዘለላዎች የእናቴ እናት እምበይተይ ንግሥቲ ለእናቴና
ለወንድሞቿ የነገረቻትን ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላልፎ ከጥቂት አመታት በፊት የታላቅዋ እህቴ
ልጅ ወደ ገጠር ትውልድ መንደራችን ሄዳ ያስጻፈቻትን፤ እንዲህ ይላል፡
ጠስሚ ዓመት ብኣባዕኸ ዝመኸኸ
ኣይትበሉባ ኣይበኸ ፤
ዝረኸብኩዎ አገብኸ?!”…በማለት የጦርነቱን አስከፊነት ለተሰብሳቢው ከነገርዋቸው በሗላ የሰሩት ጀብዱ እንደገለጹ የወላጆቼን የዓድዋ ጦርነት ሱታፌ በዚህ መልክ እንደተነገረኝ አውቃለሁ።
በሚገርም ሁኔታ ከጥቂት ወራት በፊት ባንድ ስሙን ያለስታወስኩት ከመቀሌ የሚተላለፍ የወያኔ ራዲዩ/ቲቪ “ይህን ግጥም” የትግራይ ሕዝብ መሬት ልሶ እንደሚነሳ በአድናቆት ገጥሙን ተጠቅመው ሲያስተላልፈው ስምቼ (ክሊፕ ብቻ ነው ያደመጥኩት) እራሴ ደነገጥኩና ስለ አያቶቼ ከወያኔ ጋር እንዴት አያያዙት ብየ ገርሞኛል።
ስለሆነም ለወንድሜ ቴድሮስ ልነግረው የምፈልገው የዓድዋን በዓል የማክበር ሙሉ መብትና ሞራል አለኝ ማለት ነው።
ሌላው የማከብርበት እኔነቴን የመመጠን የሞራል ልዕልናየ ደግሞ፤ የሚከተለው ነው።
አያቶቻችን ጣሊያን ይዞት የመጣውን ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነ፤ ተዋህዶ ቤተክርስትናን፤ አማራን እና አማርኛ ቋንቋ በማጥፋት ኢትዮጵያን በነገድና በቋንቋ የማስተዳርን መርሃ ግብር በግብር ያዋሉትን ከትግራይ የበቀሉ “ወያኔዎች” ተብለው የሚጠሩ “ጥቋቁር ጣሊያኖችን” በጽሑፍ እና በንግግር ብቻ ሳይሆን በጠመንጃ በክላንሽንኮቭ በመራራው የትግራይ አስቸጋሪ ተራራና ሜዳ ከትግራይ ገበሬ ጎን ቆሜ በሚገባ በአኩሪ ድፍረት የተዋጋሁዋቸው ኢትኦጵያዊ ነኝ።
በሚገርም ሁኔታ ወንድሞቼና ዘመዶቼ ከወያኔ ጋር ወግነው እኔ በነሱ ላይ ስተኩስ እነሱ በኔ ላይ ይተኩሱ ነበር ማለት ነው (የናት ሆድ ዥንጉርጉር!)። ይህ የሞራል ልዕልናየ የድዋን ድል ማክበር እመጥናለሁ ማለት ነው።
እነ ቴድሮስ ጸጋየ እና አብርሃ በላይ የጣሊያንን መርሃ ግብር በተግባር ያዋለ እና ዛሬም ያንኑ ትምክሕቱና ዓላማው በትግባር ለማዋል እየሰራ ካለው የወያኔ ጦር አፈቀላጤ ሆነው በሚዲያቸው “የኢትዮጵያ ሠራዊት” “የአብይ ጦር ነው” ብለው “እምሽክ ብሎ ለዘላለም መጥፋት አለበት” ሲሉ ባንደበታቸው ሲናገሩ ዳግመን ሰምተናቸዋል።
“የጣሊያን መርሃ ግብር” በተግባር ያዋለ፤ አማራ እና አፋር አካባቢ ገብቶ ሴቶችን የደፈረና የወረረ “ወራሪ የወያኔ ሠራዊት” ግን “እምሽክ ይበል ቀርቶ “ትጥቁ መፍታት አለበት” ማለት ተውትና “ግፋ በለው! አይዞህ!” እያሉ ሲያሞካሹት ሌት ተቀን እየሰማናቸው ነው” (የገንዘብ ዕርዳታም ሳይለግሱለት አይቀሩም)።
ስለዚህ የዓድዋን ድል ማክብር የሞራልም የሕግም የመንፈስም ልዕልና የሌለው “የዓድዋ ድል የትግሬዎች ነው” የሚል ምኒሊከን የሚዘልፍ ጭራቁ የወያኔ ጀሌና የወያኔ መሪዎች ናቸው የዓድዋን ድል “አይመጥናችሁም” ማለት የሚገባው።
የሉዓላዊነት ትርጉም በተግባር የካደ ባንዳው ወያኔ ኢትዮጵያን (ትግራይንም ጭምር) ያለ ወደብ አስቀርቶ የሶማሌና የጅቡቲ ጥገኛ እንድትሆን ያደረገ ፤ ለሻዕቢያ ወግኖ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንን ኤርትራ በረሃ ገብቶ ደም ያፈሰሰ “ማፈርያ” ዓድዋን በምንም መመዘኛ ማንሳትም ሆነ ማክበር አይገባውም ተብሎ በነ ቴድሮሰ ጸጋዬ መነገር የነበረበት ለወያኔ መንጋ ነበር እንጂ ለኛ በህይወት ላለነው ትግራይ ውስጥ 47 አመት ትግራይ እና ኢትዮጵያ ደም ያቃቡ “ጥቁር ጣሊያኖችን” የተዋጋን “አገራዊያንን” በቴድሮስ አንደበት መዘለፍ አይገባንም።
በሚቀጥለው ክፍል ሁለት
የውጭ ጋር ወራሪ ሃይል አስገብቶ ትግራይን ማስደፈር ስለሚለው እውነትነት ቢኖሮውም ወያኔ የውጭ ወራሪ የሚባለው ድሮም ሻዕቢያ ዛሬም ሻዕቢያ “ከበረሃ ጀምሮ እስከ 1998 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያ እንዲደፍር እንዲዘርፍ ተባብሮ እንዲወርር ያደረገ ወያኔ” ዛሬ ደርሶ ቴድሮስ ለምን አገር ካስደፈረው ወያኔ ጋር ወግኖ ወራሪውን ሻዕቢያና አብይን ብቻ ለመኮነን ፈለገ?
ለመሆኑ ከውጭ ወራሪ (ሻዕቢያ ማለቱ ነው) ተባብሮ ትግራይን ደፍሯል የሚለው ክርክሩ እውነትነት ቢኖሮውም ቴድሮስ በርታ ግፋ እያለ የሚያሞካሸው በወያኔ የሚመራው የትግራይ ወራሪ ጦር የአማራን ሕዝብ ገድሎ ስጋው በልቶ ደሙን የሚጠጣ አስፈሪ የዘመናችን “ኦነግ” ከተባለው ጭራቅ የጋራ ውል አድርገው አማራን ሲፈጁ ምነው ቴድሮስ በሻዕቢያ ብቻ እያተኮረ ከሻዕቢያ የማይተናነሱትን ወያኔና ጭራቁ “ኦነግ” ምነው ተለሳለሰላቸው?
ቴድሮስን የምጠይቀው የትግራይን ሕዝብ እኩል ሲያሰቃዩት የነበሩት (ዛሬም
እንዲሁ) በደም የጨቀዩት የትግራይን ተዋጊ የሚመሩት የጦር መሪዎች ጋር እንዴት ሊወግን ቻለ?
የውስጥም ይሁን የውጭ ወራሪ- ሁለቱም ግፋቸው ተመሳሳይ አይደለም ወይ? የትግራይ ተወላጅ ሙዚቀኛው ኢንጅኔር እምብዛ ገድለው ሬሳውን በቢላዋ ቆራርጠው የጣሉለትን አከላቱ ተለቃቅሞ ከተቀበረ በሗላ “ሬሳውን አንደገና ከመቃብር ቆፍረው የበሰበሰውን አከላቱን እንደገና ቆራርጠው ለጅብ የሰጡት የወያኔ አረመኔዎች” እንዴት ከወራሪው ሻዕቢያ ጋር እኩል አላነጻጸርካቸውም? ሃሎ!! ሃሎ!!!
ስለዚህ የድዋን ድል ሊያከብር የሚመጥን ትውልድ አይደለም ሲል ቴድሮስ ሌላ የሚመጥን ትውልድ እስኪፈጠር ድረስ “በኣሉ ሳይከበር ለዘመናት ዝም ተብሎ ይታለፍ?” እናንተስ በዚህ ትስማማለችሁ?
ሌላው አስገራሚ ክርክሩን “መንጋ ብሎ ለሚጠራው የዓድዋ በዓል ሌላውን
አክባሪ በብልጣብልጥ የቃላት አጠቃቀም ችሎታው (ስድቡን መሸፈኛ እያደረገ) እንዲህ ሲያሳንሰው የሚሰማውን በክፍል ሁለት እመለስበታለሁ፤
እንዲህ ይላል-
<< “ኢትዮጵያ ቀዳሚም ዳግማዊም ልደትዋ ትግራይ ሆኖበት ነው፡በቃ! መከራውን ያያል! ወደ ሗላ የኢትዮጵያን ታሪክ ሄዶ የኢትዮጵያ ቀዳሚ ልደት የት ነው? ሲባል “አክሱም” ያደርሰዋል። ወደ እዚህኛው ዘመን መጥቶ ኢትዮጵያን የተበየነበት እንደገና በመስዋእትነት የተባጀችበትሥፍራ የት ነው ቢባል “ዓድዋ” ይወስደዋል፡ “ምን ያድርገው! በጣም እኮ ነው የተቸገረው?” ኢትዮጵያን ሲያስብ ቀዳሚም ዳግማዊም መነሻዋ ኢትዮጵያ ሆነበት፤ አሉላ ሆነበት! ባሻይ አውዓሎም ሆኑበት! ዮሐንስ ሆነበት። ያ ችግር ሆነባቸው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ “በኮር ስቴትነት” (በአገር ስኳልነት) ትግራይ ነች……….>> እያለ
ወያኔዎች ኢትዮጵያን የፈጠርን እኛ ነን የሚለው ብቸኛ ባለቤት የመሆን፤
አክሱም የትግሬዎች ስሪት ብቻ ነው የሚለው (Extreme greed for ownership) የሚያስገርም ነው። ይህ የታሪክ ነጠቃ
ስስት ኦሮሞዎች ሳይቀሩ አክሱም “የኦሮሞዎች ስሪት ናት” ማለት ጀምረዋል። ቴድሮሰ የተለመደው “የኬኛ” ፖለቲካውን ተደጋግሞ ለብዙ
ጊዜ አስደምጦናል። ይህንና ሌሎቹን ትችቶቹን
በክፍል ሁለት እመለሰላሁ…….ይቀጥላል……. እስከዚያው ድረስ ቴድሮስን
ለማድመጥ እነሆ፤
Reyot - ርዕዮት፦ አድዋን ሊያከብር የማይመጥነው ትውልድ
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)
No comments:
Post a Comment