Thursday, May 16, 2019

የብርሃኑ እና የብርቱካን መዲቅሳ አዲሱ ሴራ በልደቱ አያሌው ፓርቲ ላይ! ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)


አሁን የደረሰኝ ትኩስ ዜና

ትናንት ሓሙስ (5/16/2019) ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ከሌሊቱ 5 ሰዓት ያልታወቁ ሰዎች በየመንደሩ እየዞሩ በተለይ ቀበሌ 5 እና 6 የሰው መኖርያ  ቤቶችን  ማቃጠል እና ጥይት መተኮስ እንዲሁም የመንግስት ህንጻዎች እና የሆቴሎች መስተዋቶችን ሲሰባብሩ አድረዋል። የሚቆጣጠራቸው የመንግሥት ወታደር ወይንም አካል እንደሌለ ከስፍራው ያገኘሁት ቀጥተኛ መልእክት ያመለክታል። ትንሽ ቆይቶ ነገሩ ቢሰክንም ሕዝቡ ግን ሽብር ገብቶበት ማደሩን ካገኘሁት ቀጥተኛ መልእክት ለማወቅ ችያለሁ። ለዝርዝሩ ሰፊውን ዜና እስካቀርብላችሁ ድረስ ተከታተሉኝ። ሥርዓተ አልባው መንግሥት ተብየው የዜጎችን ህይወት ሽብር ውስጥ አንዳይገባ ሽብርተኞችን  ስርዓት ማስያዝ እንዳልቻለ ይህ ማስረጃ ነው። (ዜና ምንጭ Ethiopian semay)

የብርሃኑ እና የብርቱካን መዲቅሳ አዲሱ ሴራ በልደቱ አያሌው ፓርቲ ላይ!   
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)

ልደቱ አያሌው ሲናገራቸው እና ሲቀሰቅስባቸው በነበሩት አንዳንድ ፖለቲካዊ ሁኔታዎቹ እንደብዙዎቻችሁ ቅሬታ እንዳለኝ እና ስተቸው እንደነበረ ታውቃላችሁ ብየ እገምታለሁ። ልደቱ ስሕተቶቹን ተረድቶ እራሱን ‘ትንሽ’ ሞርዶ ለፖለቲካው እራሱን እንደገና ካዘጋጀ ማንኛቸውን ፖለቲከኛ ማስገንደስ የሚችል በርቱ ጭንቅላት ያለው ወጣት ነው የሚል እምነት አለኝ። በዚህ እንተማመን እና ያ እንዳለ ሆኖ የኢሳት ባለቤት የነበረው ግንቦት 7 የተባለ በሰብኣዊ ጥሰት ወንጀል ክስ ሊከሰስ የሚገባው ድርጅት እና ድርጅቱም በበላይነት ሲመራ የነበረው ሴረኛው ብርሃኑ ነጋ አሁን ባለው ‘የአናርኮ የፋሺሰቶቹ’ ስርዐት ምሕረት ተድርጎለት ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከገባ ጀምሮ ብዙ ክስተቶች አይተንበታል።

ለሥልጣን ከፍተኛ ጉጉት ያለው፤ በቂም እና በሴራ የተካነው ይህ ሰው የመጀመሪያ ሴራውን ማጠንጠን የጀመረው አዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርቶ ‘በተከታዮቹ በኩል’ በአደባባይ ኢትዮጵያ ሕዝብ እየተመለከተ እና እየሰማ በተቀናቃኙ በልደቱ  አያሌው ስብእና ላይ ነበር መዝመት የጀመረው። ‘ስሙን በማጉደፍ እና ፎቶግራፉም ተዘቅዝቆ’ ለሕዝብ እንዲታይ ከፍተኛ ዘመቻ ተደረገበት። ይህ ደግሞ ሊረጋ ነው ተብሎ ብዙ ተስፋ የተጣለበት የአናርኪሰቶቹ የፖለቲካ ጥሪ ‘ከውጭ ይዞት የመጣበትን መጥፎ የሴራ ባሕሪውን’ ገና እግሩ መሬት ሳይረግጥ በልደቱ ላይ የጊንጥ መርዙን በመርጨት ግጭት መፍጠር  ጀመረ።

ልደቱ አያሌውም በጨዋ ፖለቲካ ብርሃኑ ነጋን ጋብዞ በሚዲያ እንወያይ ብሎ ሲጋብዘው ግብሩን/ባሕሪው ስላወቀ “አልቀርብም ብሎ ተሸማቀቀ”። ልደቱ አያሌው ብርሃኑን ጋብዞ ለውይይት መጥራቱ ክብር አስሰጥቶታል። እኔ በበኩሌ ተገቢውን ክብር ሰጥቼዋለሁ። 
  
ይቀጥል እና ብርሃኑ ነጋ ከአስመራ ይቅርታ ተደርጎለት በምረት ወደ አዲስ አበባ እንዲገባ ስለተደረገለት ለደስታው ‘ፌስታ’ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ (?) ሰንጋ ጥሎ አሸሸ ገዳየ ሲረግጥ የገዛ ታጋዮቹ ብዙ እሮሮ አቅርበውበት የገዛ ጓዱ ንኣምን ዘለቀም በቅሬታ ከድርጅቱ ተሰናበተ። ይህ ሰው ሰሞኑን ደግሞ በተካነበት የማፍረስ ፖለቲካዊ ሴራ ተጠቅሞ ከፖለቲካ ወደ “ቄሳቄስነት” ባሕሪ የተለወጡ ብርቱ ሲባሉ የነበሩትን ፖለቲከኞች (ለምሳሌ እንደ እነ አንዷለም አራጌን የመሳሰሉትን) ባመሰባሰብ “በአናርኮ ፋሺስቱ ድርጅት” ‘በኦሆዴድ’ ሥልጣን በተመዘዘቺው በብርቱካን ሚዲቅሳ “ትብብር ይደረግላቸው ደብዳቤ ሸኚነት ድጋፍ” ኢዴፓ’ የተባለው የነ ልደቱ አያሌው ድርጅት ሳይከስም “ከኢደፓ ጋር” አዲስ ፓርቲ መስረተናል ብለው ብርሃኑ ነጋ መሪ ሆኖ ሴራ ጎንጉኖ ከልደቱ አያሌው ጋር የነበረው የፖለቲካ ቅራኔ ለመቀስቀስ ሆን ብሎ የቋጠረውን “ቁርሾ” እንደገና ስቀስ ልደቱ አያሌውም ‘ሂደቱ’ በሴራ የተቀናጀ እውነትነት ያልተከተለ “ሕገወጥ ነው” ሲል ተቃውሞውን ለዜና ዘጋቢዎች ቃለ መጠይቅ ሰጥቷል።

ይህ የውህደት አሰራር እውነትም ‘ሕገወጥ’ ብቻ ሳይሆን እንደገና ፖለቲካውን አታካራ ውስጥ ከትቶ ብርሃኑ ነጋ በለመደው ‘የማምታታት’ ፖለቲካዊ ባሕሪው ተጠቅሞ ቅንጅት ላይ በፈጠረው የማፍረስ እና የንትርክ ክስተት በመፍጠር ዛሬም በተመሳሳይ አየሩን እንደገና ለመበከል መዘጋጀቱን የሚያሳየን ምልክት ነው።

የሚገርም ነው! ወይ አዲስ አበባ! የአብይ ድርጅትና የለማ መገርሳ ‘ወንጀለኛው ኦሆዴድ’ እየጎነጎነው እና እየሰራው ባለው አዋኪ መንፈስ ምክንያት የተበከለው አየር እንዳይበቃት ብርሃኑ ነጋ መልሶ አየሩን ተጨማሪ አዲስ አበባበአታካራ ብጥብጥ ሊበክላት እንደገና እየሰራ መሆኑን ስንመለክት አሁንም ወይ አዲስ አባባ! ምኑ ጉደኛ ከተማ ነች? የሚያሰኝ ነው።

የተማረው ለሕዝባችን ጠንቅ ነው እያልኩኝ ስጮህ የነበረው ዛሬም ያው የተበከሉ “ኦልድ ስታብልሽመንት” ወጣት ፖለቲከኞችንም እየበከሉ ስለሆነ ከፖለቲካው ካልተወገዱ ያንን የተበከሉበትን ባሕሪ ይዘው የአገሩቷን ህይወት መልሰው መላልሰው ወደ ባሰው ብጥብጥ እንደሚወስዷት የተነበይኩይትን ትንበያ ያው ህየው እየሆነ የምታዩት ክስተት ነው። የብርሃኑ ነጋ ድረጅት እንደምታውቁት ‘የአንድነት ሃይሉን’ በተለይም አማራውን እጅግ አድርጎ የሚጠላ መሆኑን (ከድርጅቱ የተሰናበቱ አባላቶቹን ያቀረቡት ስሞታ እና ክስ ልብ ይለዋል) እና ካሁን በፊትም አማራ እና ትግሬ ለዘመናት ስለገዙን አሁን የመግዛት ጊዜአችን ወደ ደቡብ ሊሂቃን መዛወር አለበት ብሎ በግንቦት 7 ጋዜጣ አሳትሞ እንዳስነበበን የምታውቁት ታሪክ ነው። የግንቦት 7 አመራሮች (አበበ ቦጋለ የተባለ የፖለቲካ ዋሾም ጭምር) አመራሮቹ በዚህ ጉዳይ ሲጠየቁ ይህንን መጻፉን አናውቅም ፤ ወይንም አልተመለከትኩትም እንዲህ የሚል ካለ እንደገና እመለከታዋለሁ….ወዘተ እያሉ ሲያምታቱን እንደነበር የምታወስ ነው። ያንን ያላነበባችሁ ስለምትኖሩ ታሪክ ነውና እነሆ እንዲህ ይላል፦

የግንቦት 7 ድምጽ ቁጥር 25 ጥቅምት 27/2001 ዓ.ም ርዕሰ አንቀጽ

“ከትናንት በስቲያ ለባርነት ሲሸጡና ሲለወጡ የነበሩ ጥቁሮች ዛሬ ለአሜሪካ ፕረዚዳንት መመረጥ ከቻሉ በአገራችን ኢትዮጵያም ለአሰርት-መቶዎች አማታት እየተፈራረቁ ሱገዙን የነበሩትን የአማራና የትግሬ ሊሂቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት እስከሆነ ድረስ ቦታው ለደቡብም፤ ለኦሮሞውም፤ ለአኝዋኩም ለመልቀቅ ፈቀደኛ የማይሆንበት ምክንያት የለም” (የግንቦት 7 ድምጽ ቁጥር 25 ጥቅምት 27/2001 ዓ.ም ርዕሰ አንቀጽ)

በማለት መጪው የመንግሥት ዘመን የሚገዙን የደቡብ እና ኦሮሞ ሊሂቃን መሆን እንዳለባቸው ነው እንግዲህ ስላለፈው ምሬቱ እያወሳ ለመጪው ገዢዎቻችን እነማን መሆን እንደሚገባቸው ሲገልጽ የነበረው።

እንግዲህ ብርሃኑ ነጋ እና አንዳርጋቸው ጽጌ በጋዜጦቻቸው እየነገሩን የነበሩት መጪው ምርጫ በኢትዮጵያዊነት እውቀት የተላበሰና ቅን እና ሰብአዊነት የታጠቀ ማንኛውንም ዜጋ እንዲመራን ከመወትወት ይልቅ አገዎችን ሶማሌዎችን አማራዎችን ትግሬዎችን… እና የመሳሰሉ ዜጎች አግልሎ ከደቡብ እና ኦሮሞ ሊሂቃን ማስተዳዳር እንዳለባቸው ነበር በርዕሰ አንቀጹ ሲቀሰቅስ የነበረው። የርዕሰ አንቀጹ ብልት ስንሰነጥቀው በውስጡ ብዙ ምስጢር እንዳለው ግልጽ ነው። የመልእክቱ ፍሬ ነገርም ግንቦት 7 ከጸረ አማራው ከዋለልኝ መኮንን የቀዳውአማራ እና ትግሬ እየተፈራራቁ ….” የሚለውን ፍሬ ነገርን ነው እንደገና ከብዙ አመት የዋለልኝ ሕልፈት በላ የዋለልኝን ክርክር ከመቃብር አወጥቶ ግንቦት 7 ነብስ ዘርቶለት በዛው ትርክት እንድንዳክር የጣረው። ይህ ደግሞ የዘር ፖለቲካ የተንተራሰ ቁልጭ ያለ ዘረኝነትን ለማስፋፋት መስበክ ነው።

ተራ ዜጋው ‘ከማንም ይምጣ ከማንም ጎሳ ሰላም ካስመጣልን የምንፈልገው ያንን ነው” ሲል የግንበት 7 ፖለቲከኞች ግን እነሱ ባመላከቱን ክልሎች የተወለዱ ሊሂቃንን በፈረቃ እንዲገዙን መቀስቀስ ጎሰኛነታቸውን ሳይደበቁ ያሳዩበትን ጋዜጣዊ ርዕሰ አንቀጽ ነው። ለዚህ ነበር ‘ያ የዚያ ጎሳ ሊሂቅ ገዝቶናል አሁን ደግሞ ተራችን ነው’ እየታባለ የኢትዮጵያውያን ትላልቅ ዋርካዎች/ፋና ወጊዎችን/ በስልት እና በግልጽ እየገደሉ ካገር እንዲወጡ እያደረጉ አገሪቷ ያለ ከዋክብት አስቀርተው በትናንሽ ሰዎች እየተመራች መከራዋን በማየት ላይ ያለቺው።

አሁንም የአናርኮ ፋሺስቱ ድርጅት (ኦሕዴድ) መሪ (አብይ) እንደ እነ ብርሃኑ ነጋ የመሳሰሉ ‘የሥልጣን ጉጉተኞችን’ አየሩን እንዲያቃዉሰት ወደ ጎኑ በማስጠጋት በጣም ጥቂት አሉ የተባሉ እንደ እነ እስክንድር ነጋ የመሳሰሉ ከዋክብቶችን በማጨለም “Wiping out remaining icons of Ethiopianity” የተሰኘ ሃዳዊ ዘመቻው ሲቀጥል እያየን ነው። ቀስ ብሎም በታወቁ ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች እንደ እነ ቴድሮስ ጸጋየ፤ርዕት ዓለሙ ወዘተ…. የማሳሰሉ ውጭ በቀል ሳይሆን ‘አውተንቲክ ኢትዮጵያዊነትን’ (ኦረጋኒክ ኢትዮጵያዊነት) የሚያራምዱትን የማጠልሸት ሙከራ እየተደረገ ነው።

እንዲህ ያለ ሴረኛ ስልት በወያኔ ዘመን ነበር። አለቅላቂዎችም እንዲሁ። ዛሬም በአብይ አሕመድ መሪነትም ጎልቶ እየታየ ያለው እነ ብርሃኑ ነጋን በማስጠጋት የግንቦት 7 ጋዜጠኞች እነ ሲሳይ አገናን፤ አበበ ገላው፤ መሳይ መኮንን እና ተማሩ የሚባሉ አስቂኝ አይነቶቹ ምሁራን እንደ እነ ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ በዕድሉ ዋቅጅራ… የመሳሰሉ ምሁራኖችን ደጋፊ በማግኘት አብይን የሚተቹ ተቺዎች ላይ ‘እንደ ተርብ በመረባረብ’ አብይም ተቺዎቹን ሊዝት እና ሊወነጅላቸው ዕድል ተከፍቶለታል (ለእስክንድር የዛተበትም ለዚህ ነው)። ብርሀኑም ከባሕሪው የተነሳ ለዚህ ሴራ ተመራጭ ያደርገዋል። አስገራሚው የብርሃኑ ነጋ የስልጣን ጉጉተኛነቱ የአብይ አሕመድ ድጋፍ ለማግኘት ሲል አብይ አሕመድ “እስክንድር ነጋ የመሰለ ጀግና ጋዜጠኛ እና አዲስ አበቤ ተከታዮቹን” እንዲያ ሲንገላቱ እና በአብይ አሕመድ ሲዘለፍ (ጀግና እንዲባሉ መታሰርን የሚናፍቁ ብሎ ያለውን ልብ በሉ!) እና ሲወነጀሉ (ይህን የ አብይን ውንጀላ አትርሱ- “….በአዲስ አባባ በሚመለከት ጉዳይ ላይ እውነቱን ለመናገር እኔ ያልተመቸኝ “መፈንቅለ መንግሥት የሚመስል ጉዳይ ስለሆነ ነው” (አብይ አሕመድ)። በማለት በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እስክንድርን  ወንጅሎ “ወደ ግልጽ ጦርነት እንደሚገባ” የዛተበትን ዛቻ እንዳይበቃ ብርሃኑ ነጋ ያችን ዕድል ተጠቅሞ ለአብይ አሕመድ ድጋፉን በእንዲህ ገልጾለታል፡-

ብርሃኑ ነጋ አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ጸረ አማራ ከሆነው “አ ኤም ኤን” ከተባለው የተገንጣይ ኦሮሞ የፕሮፓጋንዳ ማሰራጪያ አውታር ላይ ቀርቦ ባደረገው ቃለ ምልልስ ስለ አብይ እና አዲስ አበባ (አስክንደር ነጋ ባለ አደራ) ጉዳይ ሲመልስ እንዲህ ይላል።

አኔ አብይን ሙሉ ለሙሉ አምነዋለሁ!!!” ካለ በሗላ፤ “ታከለ ኡማም ቢሆን (እንደ አብይ አሕመድ) አሸጋጋሪ ነው” “በሕግም ብምንም “የሌለ” ባላደራ “ምናምን” የሚባል ለኔ ብዙም እንትን አያደርገኝም……ታከለም ሆነ አብይ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት አሻጋጋሪዎቻችን ናቸው”። ለዚህ ነው ወደ እዚያ ስለሚያሻግሩን እንርዳቸው አብረን እንሂድ የምለው።”  ካለ በላ ብርሃኑ ነጋ በመቀጠል

‘ጋዜጠኛው የለውጡ እንቅፋቶች ምንድናቸው ይላሉ?” ለሚለው ሲመልስ በሦስት ክፍሎች ከፍሎ ሦስተኛው በእንዲህ ያስቀምጣቸዋል፡

”ለወጡ በፍጥነት እየሄደ አይደለም፤ እኛ የምንፈልገው እያገኘን አይደለም ብለው በቁጭት ለውጡ ተሎ ወደ እሚፈለገው ነገር መግፋት አለበት፤ ካልሆነ ሽግሩ ወደ ሌላ ነገር ያመራል ብለው የሚፈሩ ብችኩልነት በተወሰነ ደረጃ ይህንን ለውጥ እንቅፋት የሆኑ ሃይሎች አሉ።” በማለት ብርሃኑ ነጋ በጃዋር ሜዲያ ቀርቦ የሰጠውን ቃለመጠይቁን ያገባድዳል።

የሚገርመው ደግሞ “ሶሻል ሚዲያ” ለጥርጣሬው ተጨማሪ ነዳጅ እየሆነ ነው በማለት ልክ እንደ አብይ አሕመድ ችግሩ የውስጥ (የስርዓቱ) ሳይሆን ‘ውጪኣዊ ነዳጅ’ የፈጠረው ጥርጣሬ በሽግግሩ አራማጆች ላይ እምነት እንዲታጣ ተደርጓል’ በማለት ብርሃኑ ነጋ በፌስ ቡክ ላይ ቅሬታውን አንጸባርቋል።  

ይህ ሙሉ ለሙሉ አምነዋለሁ የሚለው ደንቆራአዊ የእምነት አባባል በብርሃኑ ብቻ አልተወሰነም፡ ፀሐይ አሳታሚ የሚባለው የመጻሕፍት ሕትመት ባለቤት የሆነው ኤልያስ ወንድሙም ስለ አብይ አስተዳዳር ከ ቪ ኦ ኤው -straight talk Africa የውይይት ክ/ጊዜ ዋና አዘጋጅ ከሆነው ሻካ May 1/2019 እንዲህ ሲል ኤልያስን ይጠይቀዋል “How do you grade the Prime Minster?” መልስ (ኤልያስ) (If you ask me the report card for one year, I will put A+ (A plus)” በማለት ከሚገባው በላይ የስራ አፈጻጸም ውጤት ሰጥቶታል። ኤ ብቻ ሳይሆን ከ ኤ በላይም ሰጥቸዋለሁ’ ሲል ሻካ እራሱ “እርግጠኛ ነህ እስከዚህ ድረስ የሚደርስ ነጥብ “ሪሊ?” በማለት አግራሞቱን ገልጿል (በነገራችን ላይ አብራ ለውይይት የተጋበዘቺው የግንቦት 7ትዋ ‘ሊሊት’ (በስም ሞክሼነት እንዳይሆን እርስዋ ትሁን አትሁን አላወቅኩም) “ምንም ግሬድ አልሰጠውም! “መቆጠብን መርጫለሁ!” በማለት አስተዋይ ድምዳሜዋን መልስ ሰጥታለች። መጀመሪያ አብይን በመደገፍ ደስታውን አላስችል ብሎት ሰማይ ሲጨብጥ የነበረው የኒውዮርኩ “ተድላ አስፋው” አድ ስለነበረ ጣቢያውን ደውሎ “አብይን “ሲ/C/” አልሰጠውም’ በማለት አብይን ክፉኛ ተቃውሞታል። 

እንግዲህ እነ ብርሃኑ ነጋ ሙሉ በሙሉ እናምነዋለን “ኤ ፕላስ” ሰጥተነዋል እያሉ  የአብይ ‘የወደቀ/የሰነፈ’ የስራ አፈጻጸም ስንመረምረው፤ አውነታው ተቃራኒ ነው።

አንዴት ነው ነገሩ?!!! “የመንግስት መዋቅሮች ለኦሮሞዎች” እየተሰጠ ፤ ’ሰላማዊ ጥያቄ ያቀረቡለትን ዜጎች “እያገደ እና እያስፈራራ”፤ በሚሊዮኖች የተፈናቀሉ ዜጎችን፤ ከ18 በላይ የባንክ ዘረፋዎችን “ዝም በሉዋቸው/ታገስዋቸው/ የፈለጉት ድርጉ የሚል ለወንጀል ድርጊት የሚታገስ መሪ፤  እህቶች፤ እናቶች፤ አረጋውያን እና መነኮሳት በጋጠወጥ ተገንጣዮች ሲደፈሩ፤ቤቶቻቸው በቡልዶዘር ሲፈርስባቸው፤ ህጽናት ትምህርት ሲታገዱ፤ ቤተፀለቶች ሲቃጠሉ፤ ዜጎች በወረበሎች ታፍነው ሲጠፉ፤ መላው የሐረር ከተማ ሕዝብ  በውሃ ጥም እንዲረግፍ ቧምቧ የቆረጡ ብዛት ያለቸው የተደራጁ የከተማ ወንበዴዎችን መታገስን፤ የመዝናኛ ስፍራዎች (ሪዞልት) ማገድ እና  ባለቤቶችና ሰራተኞችን አፍኖ “ገንዘብ መጠየቅን” የመሳሰሉ ከፍተኛ ወንጀሎች ሲከናወኑ እንታገሳቸው (‘ወንጀለኞች’ ታፍነው ስለነበሩ ዛሬ ነፃነት ስለተሰማቸው ነው ይህንን የሚያደርጉ የሚለንን አብይ) በሚያስፈራ ፍጥነት ወንጀልን ያሳደገ አናርኪስት መሪ ብርሃኑ ነጋ “አብይ ሙሉ በሙሉ አምነዋለሁ” ሲለን  እነ ኤልያስ ወንድሙ ደግሞ  ኤ ፕላስ” ሰጥተነዋል፤ እያሉ አስቂኝ ምሁራዊ “የስራ አፈጻጸም ሪፖርት” በመስጠት “አዲሱ መሪያቸው” አብይ አሕመድ በሕግ አንዳይጠየቅ የወደፊት መሪ እንዲሆን በተዘዋዋሪ ቅስቀሳ ማድረግ የለመድነውን የምሁራን ውድቀት ዛሬም ከስሕተታቸው አልተማሩም።

ብርሃኑ ነጋ ስለ እስክንድር ነጋ የሚመራው የሲቪክ ማሕበረሰብን የሕዝብ ጥያቄ አይደለም፤ ሕጋዊ አይደለምብሎ ያጣጣለበትን ‘ጸያፍ’ እና አድርባይ ንግግሩ የኢሳት ጋዜጠኞች እነ ኤርሚያስ ለገሰ እና ሃብታሙ አያሌው በብርሃኑ ነጋ አድርባይነት ተገርመው” ዶ/ር ብርሃኑ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው በማለት በይፋ ወርፈውታል።

ወደ ልደቱ ኢዴፓ እና ወደ ግንቦት 7ቱ ብርሃኑ ነጋ አዲስ ንትርክ ልውሰዳችሁ፡

የቅርቡ የልደቱ እና የብርሃኑ ነጋ ሁኔታ በሚመለከት ልደቱ አያሌው እያቀረበ ያለው ቅሬታ ‘ብርሃኑ ነጋ’ በሊቀመንበርነት እየመራው ያለው አዲስ የተመሰረተው ፓርቲ “ኢዴፓ” ጋር ውህደት ፈጽሜ አለሁ ብሎ ሌሎች ፓርቲዎችም ያሉበት ውሕደት በመሰረቱ እቃወመዋለሁ፤ ሕጋዊነትም የለውም! ሲል ልደቱ ይከራከራል። ለዚህም ብርቱካን መዲቅሳ በምርጫ አስፈጻሚ ተቋም ሃለፊነትዋ ተጠቅማ ውህደት ፈጽመናል ብለው በሚዲያ በዜና መልክ ሲያስነግሩ እርስዋም ሕጋዊ እንዳልሆነ እያወቀች መቃወም ሲኖርባት አዲስ ፓርቲ ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ በሄዱበት ቦታ ‘ድጋፍ ይደረግላቸው’ ብላ ፈርማ ደብዳቤ ሰጥታቸዋለች።
ልደቱ እንዲህ ይላል።

“የፈለጉት ኦደፓን ፓርቲ ለማክሰም ነው። በሕግ ከሆነ ይህ ሴራ አይሰራም፤ብሔራዊ ምክር ቤት ውሳኔ ባልሰጠበት ሁኔታ  ኢዴፓ ከሰመ/ተዋሃደ/ማለት አይቻልም። በዚህ መልክ በሄደበት ውህደት የሚባለው ውህደት ‘ሕግ ካለ’ አይችሉም፤ ሕግ ለከሌለ ግን ይቻላል። ኢዴፓ ላይ የተሰራ ይህ ደባ የሚቀጥል ከሆነ የ27 አመቱ ስርዓት አልተቀየረም ማለት ነው። ስርዓቱ መቀየሩ እርግጥ ከሆነ “ኢደፓ” ከማንኛውም የፖለቲካ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ገንቢ የሆነ ፖለቲካ እንዲተከል ዋጋ የከፈለ ነው። እንዲህ ያለ ደባ ሲፈጸም ማየት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባህላችን ውስጡ ምን ያህል አለመቀየሩ የሚያሳይ ነው። እንዲህ ከሆነ አሁን እየተካሄደ ያለው አዲስ ለውጥ ውጤታማ አይሆንም። ተመልሶ ይደናቀፋል። በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ፓርቲ የአመራር ዘመን ዕደሜ የወሰነ ብቸኛ ኢዴፓ ነው። ለ4ኛ ጊዜ 4 መሪዎችን ለውጧል (በሕገ ደምባችን ደምጽ ብልጫ እየተሰጠ)። እኛ በወጣትነታችን የሥልጣን ፍላጎት አድሮብን አያውቅም፤ አቅማችን አውቀን “እነ ዶ/ር ሃይሉ አርአያ፤ ደ/ር አድማሱ ገበየሁ እንዳወም ‘ቱ ዘ ኤክስተንት” (ርቀን በመሄድ) ብርሃኑነ ነጋ ኢዴፓ ሊቀመንብር አንዲሆን እና ኢዴፓ  ውስጥ እንዲገባ ከማንኛወም በላይ ጥረት (ሎቢ ካደረጉት አንዱ እኔ ነኝ) አድርጌአለሁ! መጥቶ እንዲመራን በሚል።” ሲል ልደቱ በሰፊው ስሞታውን አሰሰምቷል።

ልደቱ በቃለ መጠይቁ እንዳብራራው ኢዴፓ ፈርሷል ብለው እነ ዶር ከበደ ጫኔ ከብርሃኑ ጋር የውህደት ስምምነት ማድረጋቸው ሕግ የጣሰ ነው የሚለው የልደቱ አባባል ትክክል ነው። ልደቱ ሦስት ነጥቦችን አቅርቧል። 1ኛ  ጠቅላላ ጉባኤ እንድናካሂድ ተወስኖ እያለ ዶ/ር ከበደ ጫኔ ጉባኤው አንዳይካሄድ ሲሰሩ ነበር።  2ኛ አስቸኳይ አዋጅ በታወጀበት ወቅት ወያኔ ጋር ድርጅታችንን ወክለው እሳቸው እና ሁለት ሰዎች ሆነው ከወያኔ ጋር ድረድር ሲያደርጉ፤ የድረድሩ ዘገባ “የዕለት-ተለት የተደረገው ድረድር” እያመጡ የተነጋገሩበትን ሃሳብ ወደ ፓርቲው እያመጡ ኣቋም እና ውይይት እንድንሰጥበት ሲያደርጉ የነበረውን በጎ ሃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው አቆሙት። በዚህ ሁኔታ ፓርቲው እና ድርድሩ ተነጣጠለ። ስለዚህ እንደማንኛውም ዜጋ ሲደረግ የነበረውን ድድር በሚዲያ መስማት ጀመርን። እኛም  ሁኔታው ስላሳሰበን የድርጅቱን ሕግ የጣሰ ስለነበር የወሰኑት ውሳኔ/ድድር በድርጅቱ መወሰን ሲገባው እራሳችሁ መወሰናችሁ ሕግ የጣሰ ነው ስንላቸው ሊቀበሉ አልፈለጉም። ስለሆነም ከሃላፊነታቸው እንዲወርዱ ተደረገ። የምርጫ ቦርዱም የድርጅቱ ብሔራዊ ምክር ቤት የሰጠው ምክንያት እና ውሳኔ አልቀበልም አለ (ወገንተኛ ሆኖ ከነሱ ጋር አበረ)።.....ብሔራዊ ምክር ቤቱ የሚሰጠውን ውሳኔ ነው የሚያስፈጽመው እንጂ ስራ አስፈጻሚው ብሔራዊ ምክር ቤቱ ያልወሰነውን ምክር ቤቱን ሳያሳውቅ በፈቀዱ ሊወስን አይችልም (በመተዳደሪያ ደምቡ የተቀመጠ ነው)። ከዚያ ከኢዴፓ/ብሔራዊ ምክርቤት የሚቀርብ ማንኛውም አቤቱታ አንቀበልም ተብሎ “በር ተዘጋብን”። ምርጫ አስፈጻሚውም ብሔራዊ ምክርቤት እያለ “እነ ዶ/ር ከበደ ጫኔ ማለትም 4 ሰዎች እንደ ፓርቲ አውቅና ሰጥቶ ‘ምክር ቤቱን’ አላወቅህም አለው። 

ስለዚህ ስብሰባም መግለጫም እንዳንሰጥ ታገድን ማለት ነው። ምርጫ ቤቱም እውቅና ለነሱ ሰጠ። ስራ አስፈጻሚውም ከድርጅቱ ውጭ መሆናቸውን እና ሕገ ደምቡን በመጣሳቸው ሃሳባቸው እንዲቀይሩ ብናወያያቸውም ‘አሻፈረን” አሉ። ስለዚህ ስራ አስፈጻሚው ውሳኔ አሳለፈባቸው። እነሱም ወደ ፍርድ ቤት ሄደው ያለ አግባባብ የማሕበሩ ጸሐፊ ማሕተሙን ለእነ ዶ/ር ጫኔ እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ተላለፈ። ይሕ ውሳኔ ደግሞ “የወገንተኛው የብሔራዊ ምርጫ ምክር ቤት ውሳኔ በመመርኮስ ነው”። ድርጅቱ ባንክ ቤት ውስጥ አስቀምጦት የነበረው ወደ 400መቶ ሺሕ ብር በሦስት ሰዎች ፌርማ ተፈርሞ መውጣት እና መንቀሳቀስ የሚገባውን የድርጅቱ ገንዘብ ምርጫ ቤቱ በስልጣኑ በደብዳቤ ለባንኩ በመጻፍ ለነ ዶ/ር ከበደ ጫኔ እጅ ተፈርሞ አካውንቱ እንዲተላለፍ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ይህ ደግሞ የድርጅቱ ሕገ ደምብ ጥሶ በማያገባው ገብቶ ምርጫ ቦርዱ የድርጅቱን አካውነት ለነሱ አስተላለፈ። ፍረድ ቤቱም የመተዳደሪያ ደምባችንን ሳይፈትሽ የምርጫ ቦርድ የወሰነውን ወገንተኛ ውሳኔ ተቀብሎ ለግለሰቦች ውሳኔ ሰጠ (2010 ዓ.ም)

ከዚያም ይላል ልደቱ፤-

“የተቃውሞ መግለጫ አወጣን። ተቃውሞአችን የሚለው “ምርጫ ቦርዱ ከሕግ ውጭ ጣልቃ በመግባት ያለ አግባብ ፓርቲያችንን አፍርሶታል” የሚል ነው። (ሓምሌ 2010)። ስለዚህ ኢዴፓን የሚወክለው ብሔራዊ ምክር ቤት እንጂ 4 ሰዎች አይደሉም። ምክር ኢቤቱ 25 ሰዎች አሉት። ከሃያ አምስቱ ውስጥ 15ቱ ስራ ላይ ነን ያለነው። ምልኣተ ጉባኤው 13 ሰው ነው። ቀሪዎቹ 5 ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ውጭ አገር በመሄዳቸው በፓርቲው ጋራ አይደሉም ያሉት። ሌሎቹ 4 ሰዎች ግን አሁን ከነ ዶ/ር ጫኔ ያሉ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ 4 ሰው እና 15 ሰው እንዴት አድርጎ ነው የድርጅት ውክልና ሊኖራቸው የሚችለው?” ሲል ልደቱ ይጠይቃል። የኢዴፓ ውክልና ሕጋዊ ሊኖሮው የሚችለው ምልኣተ ጉባኤ ሲከናወን ብቻ ነው። ያ ደግሞ ይኼው ወረቀቱ ላይ ተፈርሞ እንደምታዩት 15 ሰው ነው። ለዚህ ኢሕአዴግ በነዚህ ሰዎች በኩል ውዝግብ እንዲፈጠር ሕጋዊ ልሆነ ጣልቃ በመግባት ኢዴፓን እንዲፈርስ አድርጓል። ምርጫ ቦርዱ ደግሞ “ድርጅታዊ ተልዕኮ” ስለነበረው በግልጽ አፍርሶናል።

ለውጡ ከመጣ በላም ይህንን አንስተን ከዶር አብይ ጋር ተነጋገርን፡ የተፈጸመብንን ግፍ ማመልከቻ አቀረብን።  ጠ/ሚኒሰቴሩ ይህንን ጉዳይ አላቀውም ፤ይህ ጉዳይ አሁን መግለጫ ስትሰጡ ነው ያወቅኩት ብለውናል።ሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ማመልከቻውም አልደረሰኝም አሉን። ማመለክቻውን ቀን እና የተሰጠበትን ማስረጃ አሳየናቸው። እሳቸውም ተመለከቱት እና ‘እሺ’ አንግዳውስ (እዛ ቁጭ ብየ እንዳለሁ) ለምርጫ ቦርዱ ስልክ ደውለው “ጉዳዩ ይጣራላቸው” ብለው ስልክ ደወሉለት። ለ5 እና 4 ወር በራቸወን ዘግተው ‘አናነጋግርም’ ብለውን የነበሩን የምርጫ ቦርድዋ ሰብሳቢው እሳቸው ስልክ ከደወሉላቸው በላ ‘በስልክ እንድናናጋግራቸው ጠሩን” (ሴትዮዋ ብርቱካን ከመሾምዋ በፊት የነበሩት ሰብሳቢ ናቸው)። እኛም ሄደን አነጋገርናቸው። ያለፍንበትን ሂደት አነጋገርናቸው፤ እሳቸውም ደነገጡ። ከዚያ በላ የማጣራት ሂደት እንዲጀመር እና እንደገና እንዲጣራ ተባለ። የማጣራቱን ሂደት ከማለቁ በፊት ሴትየዋ ከስልጣን ተነስተው በምትካቸው ወ/ት ብርቱካን ተሹመው መጡ።

አሁንም ከወ/ት ብርቱካን ጋር ተገናኝተን ተወያየን። የማጣራቱን ሂደት ተጠናቀቀ። ማጣራቱ ተጠናቅቋል፤ ወሰኔ ለመስጠት “ብሔራዊ ምርጫ መቋቋም አለበት” አሉን ወ/ት ብርቱካን። “እሺ ብለን” የሰጡትን ውሳኔ ተቀበልን። በነገራችን ላይ ስናስረዳቸው በመግባባት ነበር። እሳቸውም የቤት ስራቸውን ሰርተው አጣርተው ነው የጠበቁን። እንዳውም ከነ ደ/ር ጫኔ ጋር ቁጭ ብላችሁ እንድትወያዩ ብለው ሲያነጋግሩን እነ ዶ/ር ከበደ ጫኔ አንወያይም ብለው ነው ጥለው የሄዱት። ችግሩን ለመፍታት የተከረበትን መፍተሄ አንቀበልም ብለው ጥለውት ሄዱ።

ከዚያ በላ ምርጫ ቦርዱ ተቋቁሞ ውሰኔው ምንም ይሁን ምን ለመቀበል ተዘጋጅተን ምርጫ ቦርዱ እስኪቋቋም ድረስ እየተጠባበቅን ባለንበት ሰዓት ነው እነ ዶ/ር ጫኔ ኢዴፓ ከሌሎች ፓርቲ ውህደት ፈጽመናል በማለት መግለጫ ሰጡ። ይህ ደግሞ ሕገ ወጥ ነው አይቻልም። ሁለተኛ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት የማድረግ ፤ውህደት የመፍጠር ውሳኔ መስጠት የሚችለው ብሔራዊ ምክር ቤት ነው። አንቀጽ 9 13 ነጥብ 4 ላይ ይህንን በሚመለከት ከማንኛወም ፓርቲ የሚደረግ ግንኙነትም ሆነ ውህደት የሚወሰነው ኢዴፓ በብሔራዊ ምክር ቤት ነው ይላል። ብሔራዊ ምክር ቤቱ ከወሰነ በላ ውሳኔው ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ ያጸድቃል ይላል (2006 ዓ፣ም ተሻሽሎ በወጣው ደምባችን ውስጥ)። በዚህ መሰረት አይደለም ብሔራዊ ምክር ቤት መሰብሰብ  ጠቅላላ ጉባኤም አልተሰበሰበም አልወሰነበትም። ሊሰበሰብም ሊወስንም አይችልም፡ ምክንያቱም “ምርጫ ቦርድ እገዳ ጥሎበታል”።  መሰብሰብ ይቻል እንኳ ቢኖር አብዛኛው አባል (ማጆሪቲው) እኛ ጋር ስለሆነ ውሳኔ መስጠት ካለበት  እኛ ጋር ያለው አብዛኛው አባል ነው። የተወሰኑ ሰዎች ከመሰላቸው ፓርቲ ጋር ሄደው በኢደፓ ስም ውህደት ፈጽመናል ሊሉ አይችሉም። 

 ሚዲያዎች ሃላፊነት አላችሁ። ምርጫ ቦርድ እስኪቋቋም ጠብቁ ተብለን ውሳኔ እየተጠባበቅን እንዳለ ውህደት መፈጸም ሕገ ወጥ ነው። እናንተ ሚደያዎች ፓርቲዎች እንደተዋሃዱ አድርጋችሁ ዜና መሰራጨታችሁ ስሕተት ነው።

ሌላው የሚገርመው ነገር ደግሞ “እነዚህ ውህደት ፈጽመናል ብለው እያወሩት ያሉት የውህደት እንቅስቃሴ አይደለም። ምከንያቱም ለምርጫ ቦርድ ማመልከቻ ጽፈው “አዲስ አገር አቀፍ ፓርቲ ልናቋቁም ስለሆነ ፌርማ እንድናሰባስብ የትብብር ደብዳቤ ይሰጠን ብለው ማማለክቻ አቅርበዋል።” ምርጫ ቦርድ ደግሞ “ያንን ደብዳቤአቸው መሰረት አድርጎ እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ አዲስ አገር አቀፍ ፓርቲ ሊያቋቁሙ ስለሆነ በየክልሉ ፌርማ ለማሰባሰብ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትብብር ይደረግላቸው’ ተብሎ በወ’ት ብርቱካን ፌርማ የድጋፍ ደብዳቤ ሰጥቷቸዋል። ያ ሂደት ውህደት ሳይሆን አዲስ ፓርቲ የማቋቋም ሂደት ነው። 

.....ውህደት ልታደርግ ከሆነ ሕጋዊ መሰረት ኖሮህ “ፌርማ ማሰባሰብ” አያስፈልግም። እንዴት ውህደት መፍጠር ንዳለብህ፤ እንዴት ግምባር መፍጠር እንዳለብህ ሕግ አለ። ለምሳሌ ግንቦት 7 ብትወስድ ሕጋዊ እውቅና ስለሌለው የሌለውን አውቅና ተጠቅሞ “ውህደት” ሊፈጽም አይችልም። መጀመሪያ ፓርቲ መሆን አለበት፡አሁምመ ፓርቲ አይደለም! ከሌሎችጋር ሆኖ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ስራ እየሰራ ነው። ስለዚህ ውህደት ሳይሆን አዲስ ፓርቲ ማቋቋም ነው መባል የነበረበት። ስለዚህ ኢዴፓ ከስሞ ሌላ ፓርቲ መስረተናል ብለዋል። እኛ አልከሰምንም የራሱ የድርጅቱ መተዳዳሪያ አንቀጽ አለ ፤  እሱ አልተፈጸመም። ሴራው እኮ ትልቅ “ፕላንደር ነው”! የምርጫ ቦርድ ያለ ሥልጣኑ እጁን በማስገባት የባንክ አካውንት ገንዘብ ለ4 ሰዎች እንዲሰጥ ማድረጉ እጅግ “ወንጀል” ነው። እኛ እንደ ዜጎች መደራጀታችንን ተነፍገን መሰብሰብ መወሰን አልቻልንም። ባጠቃላይ ኢሕዴግ የወሰደው እርምጃም ሆነ ግንቦት 7ም የወሰደው ያለው እርምጃ ቅንነት የጎደለው ነው። ቅን አይደለም።

ከፖለቲካ እና ከድርድር ተገፍተን ከፖለቲካ ውጭ እንድንሆነ ተደርገናል። እነ ብርሃኑ ነጋ ሆን ብለው “ኢደፓን” በዚህ ስልት አክስመው ለማለፍ ስለሚፈልጉ ልክ የፓርቲዎች ውህደት ንደተፈጸመ አድርገው ቅስቀሳ እያደረጉ ነው። እናንተም ይህንን ተቀብላችሁ ነው እያስተጋባችሁ ያላችሁት። የሴራ ፖለቲካ ምርጫ 97 አክስሮናል፤ ዛሬም ከዚያ አልተላቀቅንም። አልተማርንም።  )” ይላል ልደቱ አያሌው። (ናሁ ቲ/ቪ ከሰጠው ቃለ መጠይቅ በከፊል ያገኘሁት

ለዚህ ነው ብርቱካን መዲቅሳ የብርሃኑን ባህሪ እያወቀች፤ የኢዴፓ ጉዳይ እንጥልጥል ላይ ያለ መሆኑን እና “የምርጫ ቦርድ እስኪመሰረት ቆዩ ብላ” ለሁለቱ የኢዴፓ ተከራካሪ ወገኖች ውሳኔ በመስጠት ያስተላለፈቺውን ውሳኔ እያለ ‘እንደገና’ ንደ አዲስ ለነ ደ/ር ከበደ ጫኔ፤ብርሃኑ ነጋ፤አንዷለም አራጌ… የሰጠችበትን የድጋፍ ደብዳቤ እንዳለ እያወቀች “ውህደት” ፈጽመናል ብለው በይፋ በሚዲያ መግለጫ ሲሰጥ የምርጫ በርዱ “ጆሮ ዳባ” ብሎ ማለፉን የሚያሳይ እውነትም ልደቱ እንዳለው “በልደቱ እና በጓዶቹ የሚመራው ኢዴፓ” በመጪው የፖለቲካ ሜዳ እንዳይገባ የተደረገ ሴራ ነው ተብሎ መውሰድ ይቻላል። ልደቱ ለአብይ ያለው ድጋፍ ምን እንደሆነ ባላውቅም እንደ እነ ብርሃኑ ነጋ እና አንዷለም አራጌ ሙሉጭ ያለ “ድጋፍ” ስላልሰጠው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለኝ። ለዚህም ይሆናል ‘ምርጫ ቦርድ’ ተብየዋ ብርቱካን መልስ እንድትሰጥ ስትጠየቅ “አጣርተን እንነግራችለን” ብላ መስርያቤቷ ለናሁ ቲ/ቪ መስ እንዲሰጥ የተደረገው። ያም ሆነ ይህ የድሮ ፓለቲከኞች በበሰበሱበት ጎዳና ዛሬም ወደ አታካራ አስገብተውናል።

 ስለዚህ  ባጠቃላይ ልደቱ የሚለው፦ ምርጫ ቦርዱ የመተዳደሪያ ሕጋችንን በመተላለፍ  በፍርድቤት እና በቦርዱ ፖለቲካዊ ተልእኮ እነ ደ/ር ከበደ ጫኔ ጥለውት የሄዱትን ጽ/ቤት ቁልፉን እና የድርጅቱን ማሕተም እንዲረከቡ ተደርጎ እኛ አቤቱታችንን የሚሰማን አጣን። ወደ ፍርዴ ቤት ሄዶ ይግባኝ መጠየቅ አንችልም ፤ ምክንያቱም የምርጫ ቦርዱ ፖለቲካዊ ተልዕኮ ስለነበረው ከንቱ ዙረት ይሆንብናል ብለን ትተነው ነበር። ዛሬም ይኼው ውሳኔ ሳይሰጠን ጠብቁ እየተባልን ከፖለቲካው እንድንገለል ተደረጓል። ይላል ልደቱ አያሌው።
ይኼ በጣም አስገራሚ ነው። የበሰበሰ የፖለቲከኞች ባሕሪ ዛሬም አንደ አዲስ ብርሃኑ ነጋ እና መሰሎቹ አየሩን ለመበከል ዝግጁነታቸውን ማየት ችለናል። ብርሃኑ በኢደፓ ብቻ ሳይሆን በእስክንድርም በአማራውም የጎነጎነው ሴራ የሚያሳየን ብርሃኑ መለወጥ የማይችል መሆኑነ ነው።   

እስኪ ወደ ላ ልመልሳችሁ እና ላገባድድ።

 “ግንቦት ሰባትን ያቋቋሙትና የሚመሩት ብርሃኑ ነጋና እራሱ የመረጣቸው ከራሱ ነገድ የመጡ ጉራጌዎች፣ብሎም ሌላው የደቡብ ሰው ታደሰ ብሩና ኢዮኤል እንዲሁም እንደ ነዓምን ዘለቀ የኢትዮጵያን አንድነት በጎሪጥ የሚያዩ ሥብስቦች ናቸው።” ይላሉ ከበደ በለው የተባለ ጸሐፊ። እውነትም ናቸው ለማለት የሚያስችል ንግግራቸውን ስናስታውስ የሚገርም ነው። ለምሳሌ የግንቦት ሰባቱ ነዓምን ዘለቀ ”ኢትዮጵያ የምትባል አገር እና የኢትዮጵያ አንድነት ብቻ ሲባል “ስፎኬት” (suffocate) ያደርገኛል” ሲል ተደምጧል። የአትዮጵያ አንድነት ሲባል እስትናፋቻውን የሚያፍን፤ ለመስማት የሚቀፋቸውና አስጠሊታ እንደሆነባቸው ነው እንግዲህ የዚህ ድርጅት አመራሮች በግልጽ እንዲህ ያለ አስገራሚ የመድረክ ንግግሮች ሲያደርጉ የነበሩት።

ብርሃኑም አማራ ብሎ የሚጠራቸው ሟቹ ኢንጂኔር ሃይሉ ሻውልም እንዲህ ሲል ሲተቻቻው ነብር “መለስ የሚባል ትግሬ አስወግደን ሃይሉ የሚባል አማራ ለማስመጣት ነው ትግላችን?” በማለት የሰውየው የፖለቲካ ባሕሪ ከመተቸት ይልቅ በነገዳቸው በኩል በመግባት ነገዳቸውን ዋና መከራከሪያ ነጥብ አድርጎ ሲከራከር ነበር።        

ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ብርሃኑን ይጠይቃል፡- ስለ ‘የብሔር ፖለቲካ’ እንደ ግንቦት 7 ያላችሁ ፖሊሲ ምንድነው?

 ብርሃኑ
ንቅናቄ ስለሆንን ስለ ብሔር ፖለቲካን በሚመለከት ፖሊሲ የለንም። የወስድነው ወይንም የምንተቸው አቋም የለንም።” (ብርሃኑ ነጋ)

ስለ ኦነግ በሚመለከት የሰጠው አስተያየት እንዲህ ይላል፦

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄ አላቸው የሚባሉ ድርጅቶች እንደ ኦነግ የመሳሰሉ ድርጅቶች እንኳን አሁን ባለፉት ሁለት አማታት በተደረጉት ውይይቶች በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እስካለ ድረስ መገንጠልን “የሞት የሽረት” አላማ አድርገው እንደማይታገሉለት በግልጽ እያሰቀመጡበት ያለበት ጊዜ ላይ ነን ያለነው አሁን።እዚህ ስብሰባ ከመምጣቴ በፊት ኢመይሌን ስመለከት ያገኘሁት አንድ ኢመይል የኦነግ ሃይሎች እንደምታውቁት ለሁለት ተከፋፍለው ላለፉት ሁለት አመታት “ሞር ኦር ሌስ - ፓራላይዝ” ሆነው የቆዩበት “ኢንቫይሮንሜንት” ነበር። ይህን በሚመለከት የዕርቅ ድርድር ስያደርጉ ነበር፡ትናትና የህንን ዕርቅ ድርድር ጨርሰው ተስማምተዋል (ይህንነ ካለ በሗላ ከአዳራሹ ‘ደናቁርት ካልቶች’ የቀለጠ ጭብጨባ ይደመጣል)። ይኼ በጣም ስግኒፊካንት የሆነ “ዴቬሎፕሜንት” ነው።አንዱም በጋራ እንዳንታገል ችግር ሆኖ የነበረው በዚህ የኦነግ ክፍፍል ነው። ይህንን ክፍፍል ካቆመ ለኢትዮጵያ የሚደረገው የነፃነት ትግል አብረን እንደምንቆም ቅንጣት ያክል ጥርጥር የለኝም! (ጭብጫባ ይደመጣል)። ይልና በመቀጠልም-…

ይህ ደግሞ ሕዝቡ እርስበርሱ ይባላል ስንባል የነበርንበትን ስሕተት መሆኑን መመለስ የሚችል እርምጃ ነው። እኔ አስከገባኝና እስከማውቀው ድረስ እንደ ግንቦት 7ትነቴ በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ያሉት መሰረታዊ ልዩነቶች “ከሞላ ጎደል” የተመለሱበት ደረጃ ላይ ነው (አየ ብርሃኑ!! ይህ ደግሞ ዛሬ ከምናየው ሃቅ የሚጣረስ ውሸት ነው!!!) -(ትንተናው የተጣሉ የተራራቁ ፤ያልተስማሙ ገንጣዮች/ኦነጎች/ አንድ መሆናቸው ላገራችን አንድነት መድህን ነው ከሚለው ቀጣፊ እምነቱ ተነስቶ ነው እንዲህ እየተቸ ያለው። ተባብረው የሚሰጡት መግለጫና ቻርተር ምን ንደሆነ የምታውቁት ነው::)

ብርሃኑ በመቀጠል፤-ወያኔ ከጣልን በላ፡ሚለውን ንግግሩም እንዲህ ይላል፡

“ወያኔን ለመጣል ብቻ ሳይሆን ወያኔ ከጣልን በላ ለምንመሰርተው “አንድነት” የኢትዮጵያን አንድነት ሊያስጠብቅ እንሚችል ከሞላ ጎደል ማረጋጋጥ የሚቻልበት ደረጃ መድረሳችንን ማረጋገጥ ይቻላል። ይህ “ ዚስ ኢዝ ‘ቬሪ ኢምፖርታንት’ ዴቬሎፕመንት ነው”። ይኼ ደግሞ ዝምብሎ የመጣ አይደለም፡ ለሁት አመት ለሦሰት አመት ብዙ ልፋት እና እንቅስቃሴ የተደረገበት ነው። ወደ ውጤቱ ለመድረስ ብዙ ሰዓታትና ክርክሮች ተካሂደውበታል። 
 
 (የኦነግ ኦሮሞዎች ልዩነታቸውን አቻችለው “አንድ ሆነዋል” እያለ እንደ ‘ብስራት/አስደሳች/ ዜና” ቆጥሮት ወደ ኢትዮጵያዊነት ተመልሰዋል እያለ ነው ብርሃኑ። አሁን ያለው ደግሞ “አረጋግጠናል ሲለን የነበረው ማረጋገጫ ኦነጎች አንድ ሆነው ‘ምን እያደረጉ” እንደሆነ እነ በቀለ ገርባ እነ ሌንጮ፤ እነ ጃዋር ምን እየሰሩ እንደሆነ የምታዩት ሃቅ ነው። ብርሃኑ እንዴት እንደሚዋሽና አድማጩን ለማስጨብጭብ ብልጠቱን ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ማረጋጋጫ ነው)።

እንደምታውቁት ይላል ብርሃኑ፤

 እንደምታውቁት ማሕበረሰባችን የነፃነት ችግር ሳይሆን “የመተማመን ችግር ነው ያለው”። ወያኔ ከወደቀ ምንም ነገር አይመጣም! እመኑኝ ነኝ የምላችሁ ምንም ነገር እየመጣም! የሚጣ መጥፎ ክስተት ቢኖር “እሱ/ወያኔ/ ላለመውደቅ የሚያደርገው ጉዳት ብቻ ነው። ኢትዮጵያ ካሁን በላ ትገነጣጠላለች የሚለው ራቢሽ ካሁን በላ አይኖርም። ሁሉም በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ነው ወደ ሥልጣን የሚወጣው። “ያ በማጭበርበር ሥልጣን መያዝ አክትሟል። “ዘመዶቼ የተበላ ዕቁብ የሚሉት ዓይነት ነው።  ዊዝ ኮንፊደንስ ነው የምነግራችሁ!  ብርሃኑ ኦነጎች ወደ ኢትዮጵያዊነት ወደ አንድነት ትግሉ ተቀላቅለዋል እያለ ነው “ኮነፊደንስ” የሚለው ቃል ሲጠቀምበት የነበረው።

እንዲያ እያለ ነበር ብርሃኑ ተከታዮቹን ሲያጃጅል እና በስሜት ስካር በየአዳራሹ እየሰበከ “የመተማመን ችግር ከሞላ ገደል ተቀርፏል ሲል የነበረው”። ኦነጎችን እንመናቸው ወያኔ ከወደቀ ምንም ነገር አያመጡም! እመኑኝ ነኝ የምላችሁ; ምንም ነገር እይመጣም! የሚመጣ መጥፎ ክስተት ቢኖር “እሱ/ወያኔ/ ላለመውደቅ የሚያደርገው መፍጨርጨር ብቻ ነው። እያለ ሲያጃጅለን ከርሞ ዛሬ ኦነግ ምንም ነገር አያመጣም ሲል የነበረው የብርሃኑ ነጋ ውሸት ተጋልጦ “እኛ እንደተነበይነው” ባስገራሚ ክስተት “ኦነጎች ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ከገቡ በላ አገር ውስጥ ከነበሩት ከሌሎች ‘ኦሮሞ ድርጅቶች’ ጋር ግምባር ፈጥረው የመጀመሪያ ጦርነት የከፈቱት ከግንቦት 7 ደጋፊዎች እና የግንቦት 7 ሚዲያ ከሆነው ኢሳት ቴ/ቪ ላይ ነበር”።  የሚገርም ነው! አይደለም እንዴ?
  •  በመጨረሻ ኦነጎችን እና የማሳሰሉትን ድጋፍ ሰጥቶ አንድነት ሃይሉን  ሲያንኳስስ ኢሳት የግንቦት 7 ድርጅት ስለነበረ” የብርሃኑን ትዕዛዝ ለመፈጸም  የኦነጎችን ባንዴራ ኢሳት ቴ/ቪዥን ውስጥ እየተውለበለበ ‘የኦነግ ወታደሮች’ እንዴት ወደ ድል ተራራ እንደወጡ ኢሳት ሲሰብክበት የነበረውን ጉደኛ ታሪኩን ለማንበብ ይህንን የዶ/ር ማንከልክሎት ሃይለስላሴን ሰነድ የጻፉትን አንብቡ “ 
  • (A deliberate and outright deception--part I Part II Part III by Dr.Mankelkilot Haileselassie )
ይህ ከታች ያለውን የብርሃኑ ንግግር ላስምርበት እና  በዚህ ልደምድም፡

“አንድ ሰው ባንድ ስብሰባ ሲናገር የሰማሁት ነገር አለ፤ ‘የኢትዮጵያ አንድነት ካልተቀበሉ በቀር ይላሃል!!! እንዴ!? እኔ የምለው መጀመሪያ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡ የመቀበል አለመቀበል ብሎ ነገር ምንድነው? የምንሰጣቸው እና የምንቀማቸው አይደለም “ዜይ ኣር ዋት ዘይ ኣር?” በደል ደርሶብናል ስላሉ “የሁላችን ስራ ነው”። እንዲህ ያለ ወሬ ከማናፈስ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን….” በማለት ለግንጣላ ተነስተው እኛ ኢትዮጵያውያን አይደለንም፤ ኢትዮጵያዊነት በላያችን ላይ የተጫነብን እንጂ እኛ “ኦሮሚያ’ ነን እያሉ በግሃድ እና በጽሑፍ በፕሮግራም ቀርጸው “ኢትዮጵያዉያን አይደለንም አገር እናፈርሳለን” እያሉ እየተከራከሩ እየታወቀ ‘ብርሃኑ ነጋ’ እነሱን በመከላከል አገር ወዳዶችን “ወሬኞች” እያለ ጥንቃቄ አድርጉ እያለ ኢትዮጵያውያኖችን ያስጠነቅቃል። 

ዛሬ  አብይ ኦነግን በአንቀልባ አዝሎ “በእሽሩሩ ኦነግ” መዘሙር እየተጓዘ፤ ዜጎች ከአዲስ አባባ ውጡ! አዲስ (ፍንፍኔ) የኦሮሞዎች ናት! እያሉ ባንክ ዘረፋ ገብተዋል። የብርሃኑ ነጋ ኦነግን አትጠራጠሩ ፕሮፓጋንዳ እና “እመኑኝ! እመኑኝ!” ዛሬ እውነታውን “ኮንፊዴንሱን” አየነው። ብርሃኑ ዛሬ በልደቱ አያሌው እና በእስክንድር ነጋ የሚያሴረው ሴራ የሚነግረን ነገር ካለ ብርሃኑ ለሥልጣን ሲጓጓ የነበረው የብዙ አማታት ጉጉቱ እውን ለማድረግ እየሮጠበት ያለውን ፖለቲካዊ ውስልትናው ተጠቅሞ ወደ ቄሳዊ የሰበካ ባሕሪ የተለወጠው “ጀግናው አንዱአለም አራጌን’ ምርኩዝ በማድረግ ወደ ሥልጣን የሚወጣበትን መወጣጫ መሰላሉ እያበጃጀ ግርግሩን እየተጠቀመበት መሆኑን ነው።
አመሰግናለሁ! ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ አዘጋጅ) 


  


No comments: