Tuesday, May 14, 2019

የሔራዊ እርቅና መግባባት ኮሚሽን ትኩረት ቢያደርግባቸው!

From the Editor;-
Here is another important paper a must read!


5/14/19
የሔራዊ እርቅና መግባባት ኮሚሽን ትኩረት ቢያደርግባቸው!

“አባቶቻችን ሲታረቁ ካንጄት ሲታጠቡ እስከ ክንድ” ይላሉ:: እርቁ የሰመረ የሚሆነው የጠቡ መነሻ የሆኑ ጉዳዮች ተጢነው በዳይ ክሶ ተበዳይ ሲካስ ነው:: እርቁ ካንጄት የሚሆነውም የበዳይና ተበዳይ ጉዳይ ሚዛን ላይ ተቀምጦ ሚዛኑ ትክክለኛ መሆኑን ሁለቱም አካሎች አምነው ሲቀበሉት ነው:: መተማመኛ ማሳመኛውም አስታራቂዎቹ በተሸምጋዮቹና በማኅበረሰቡ ውስጥ ለሐቅና ለእውነት የቆሙ መሆናቸው ጥያቄ ውስጥ የማይገቡ መሆኑ እንዱና ዋናው ነው:: የእጥበቱ እስከ ክንድ መዝለቅም የእርቁን ዘላቂነትና ወደ ሁዋላ የማይመለስ የፀና እንደሚሆን የሚያረጋግጥ እንዲሆን ነው::

ይህ ኮሚሽንም በአባቶቻችን የእርቅና መግባባት መርሕ በመመራት ብሔራዊ እርቁና መግባባቱ የሰመረና ወደ ሁዋላ የማይመለስ እንዲሆን በመንግሥት ስም በበዳይነት የቆሙ ቡድኖችን እና ተበዳዩን ሕዝብ ግራና ቀኝ አቁመው  የበደሉን ዓይነትና መጠን የተበዳዩን ማንነትና የበደሎች ዓይነት ለመለየትና በዳዮች ክሰው ወይም ይቅርታ ጠይቀው ተበዳዮች ተክሰው ወይም ይቅርታ ተጠይቀው ብሔራዊ እርቁ የፀና እንዲሆን በዳዮች በደል ፈጸሙ የተባሉባቸው የበደል ዓይነቶች ወይም ወንጀሎች በግልጽ ሕዝብ በሚያውቀውና በሚረዳው መልኩ መቅረብ ሲችል ነው::

የኮሚሽኑ ዓላማም አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ክፉ የመጠፋፋት ዘመኖች ከገባችበት አዙዋሪት ሕዝባችን ወጥቶ በሕግ የበላይነትና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንድትመራ የሚያስችል የፍትሕ መንገድ ማደላደል እንደሚሆን ስለሚታመን የብሔራዊ እርቁና መግባባቱ የሚጉዋዝበት መንገድ የተጣመመውን የማቃናት  የጎበጠውን የማረቅ የሻከረውን የማለስለስ የመረረውን የማጣፈጥ  የተቁዋረጠውን የማገናኘት ጠንካራ ባህላዊ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ድሮችን ወደ ነበረ መልካም የአብሮነት ዕሴቶች መመለስን የሚያረጋግጥ እንዲሆን ይጠበቃል::

ለዚህ ጉዞ ይበጅ ዘንድም ባለፉት ዘመናት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የተሠሩ ወንጀሎች በሰብአዊ ፍጡር ላይ የተፈጸሙ ኢሰብአዊ ድርጊቶች  መዋቅራዊ በሆነ መንገድ የተፈጸሙ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ዓለም አቀፋዊ ወንጀሎች የመሬት ነጠቃና የመብት ጥሰቶች በቦታ በጊዜና በድርጊት ተዘርዝረው መቅረብ ለሚፈለገው እርቅና መግባባት ምቹ የመስማማት መደላድል እንደሚፈጥር ይታመናል:: ይህንም ለማድረግ የወንጀል ዓይነቶችን በመለየት ጊዜ ቦታና ወንጀሉ ማን እንደፈጸመው በማን ላይ እንደተፈጸመ እንዴት እንደተፈጸመ የሚያሳይ መረጃ ሕዝቡ እንዲሰጥ ዕድል የሚያገኝበት ሁኔታ ቢመቻች ወንጀሎች ሳይድበሰበሱ በሥፋት ወጥተው ወጥና የተጠቃለለ የእርቅ እርምጃ ለመከተል እንደሚያስችል አመላካች ይሆናል::

ይህ መንገድ የዲሞክራሲ ዋና መርሕ የሆነውን አሳታፊነትን ከማሳየቱም በላይ የኮሚሽኑን ጉዞ ግልጽና ታማኒነት ያለው ያደርገዋል:: ከዚህ አንፃር እንደ ዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ምልከታ ባለፉት ዘመኖች በኢትዮጵያ አገራዊ አንድነት ብሔራዊ ጥቅም በሕዝቡ አብሮነት ኢኮኖሚ ሰብአዊነትና ዲሞክራሲ መብት ላይ የሚከተሉት ወንጀሎች ተፈጽመዋል ብሎ ያምናል::

እነዚህም:-
1.     አገራዊ ክህደት:- ያለሕግ አግባብና ያለኢትዮጵያ ሕዝፍ ፍላጎት የኤርትራ መገንጠል እና ኢትዮጵያን ያለወደብ መቅረት:
2.    የዘር ማጥፋት:- ዐማራን በገዥነት በጨቁዋኝነት በበዝባዥነት በጡት ቆራጭነት በትምክህተኝነት በነፍጠኝነት በመፈረጅ ከሥነልቦና እስከ አካላዊ ጥቃት መፈጸሙ ከፕሮፓጋንዳ እስከ እስራት ማሸማቀቅ የቡድንና የተናጠል ግድያ መፈጸሙ:
3.    የዘር ማጽዳት:- ዐማራው በማንነቱ ተለይቶ ለዘመናት ከኖረባቸው ያባቶቹ ግዛቶች ቤት ንብረቱን ተነጥቆ እንዲፈናቀል መደረጉ:
4.    መሬት ነጠቃ:- መሬትን የመንግሥት በማድረግ ስበብ አራሹ ገበሬ የመንግሥት ጭሰኛ እንዲሆን በማድረግ ገበሬው ለችግርና ለድህነት መዳረጉ:
5.    ዜጎች ያለሕግ አግባብ ለዘመናት መታሰራቸው: መገደላቸው መሰቃየታቸው:
6.   የሕግ የበላይነት ሳይሕግን የፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ መሣሪያ በማድረግ በዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግፎችና ወንጀሎች:
7.    ዘረኝነትን መመሪያቸው በማድረግ የነሱ ዘር ባልሆነው ላይ የተፈጸመ የዘር ጥቃትና በኢትዮጵያ አብሮነት ላይ ያስከተለው መከፋፈል እና መጠፋፋት
8.    ወዘተ-----/
እነዚህና መሰል የወንጀል ዓይነቶች በሙያተኞች ትርጉምና ማብራሪያ ተሰጥቶአቸው ዜጎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጎ የወንጀሎች ዓይነትና የወንጀለኞች ማንነት ተበጥሮ እንዲታወቅ ቢደረግ የኮሚሽኑን ሥራ ቀልጣፋ ውጤታማና ታማኒነት እንዲኖረው ያደርጋል:: ሕዝባችን ለፍትሕ ያለው እምነት ከፍተኛ ነውና ባለፉት አገዛዞች የጠፋውን ፍትሕ ይህ ኮሚሽን መልሶ እንዲገነባ እንዲያደርግ ጥርአችን እናቀርባለን!

በውል ከሄደች በቁሎየ ካለውል የሄደች ዶሮየ ትቆጨኛለች!
(Posted at Ethio Semay)



No comments: