Friday, September 12, 2008

The record that speaks of Priests and Deacons abused in Tigray by the TPLF leaders






The Record That Speaks of Priests and Deacons Abused In Tigray by the TPLF Leaders
የትግራይ ድያቆናትንና የቀሳዉስት ዕምባ (ለማስታወሻዎ) የህወሐት ታጋዮች በሰባት ጥይት ድብድበዉ ጫካ ወስደዉ ጣሉኝ”
(ምንጭ፦ ኢትኦጵ መጽሄት- ቅጽ 2 ቁጥር 016 መስከረም 1993 ዓ.ም) ( ጌታቸዉ ረዳ) ( ሳን ሆዘ ካሊፎርኒያ )
ይህ ታሪክ ኣማርኛ ለማያነቡ የትግርኛ ተናጋሪዎች ተርጉሜ መሳ ለመሳ ሰሞኑን በዚህ የህዋ ሰሌዳ ቀርቧል። ሃቅን አድበስብሶ ለጊዜዉ በመሸፋፈን ዜጎችን ያስለቀሱ ወንጀለኞችን ባንዳንድ አድረባዮችና ጅላጅል ተቃዋሚዎች ሽፋን ሰጪነት፤የህወሐት አመራር ወንጀለኞች የህዝብ ኣሳቢዎች እንደነበሩና ዛሬም ነጻ ያወጡናል ብለዉ በየራድዮናቸዉና በህዋ-ሰሌዳቸዉ አጉል ቅስቀሳ ሲያደርጉላቸዉ ብንታዘብም ፡ እዉነት ተሸፋፍኖ አይቀርምና፤ ሰሚ አጥተዉ ፤ የሚጮህላቸዉ ዜጋ ፍለጋ ለዓመታት የደም ዕምባ ላፈሰሱት የወያኔ አመራር ሰለባዎች ደግሞ በኛ በኩል በዚህ ዓምድ ዕምባቸዉና እሮሮአቸዉ ለሕዝብ እናስተጋባለን። ፈራጁ ታሪክ እና በዓይን የሚታይ ጥቃት እንጂ “ዘመን የለገሳቸዉ ግራ ተጋብተዉ የዋሁን ማህበረ ሰብ ግራ የሚያጋቡ አፈጮሌ ባለ ራዲዮኖችና የህዋ -ሰሌዳ ባለቤቶች ” አይደሉም።
ስለዚህም የሕዝባችን ጥቃት ከማስተጋባት ወደ ሗላ ያላልንበትን ቃል ኪዳናችንን መሬት ተንተርሰን የመጨረሻዋ እስትንፋሻችንን እየተነፈስንም ቢሆን ትግላችን ይቀጥላል። አገር እና ሕዝብ ያስለቀሱ የባሕር በራችንን ያስሳጡንን <በረሃ እያለን ለፈጸምነዉ ወንጀል አንጠየቅበትም> ብሎ በስልጣን ማን ያህለኝነት የፏለለዉ ገብሩ አስራትን እንደ እስራኤሉ ሙሴ ነጻ አዉጪያቸዉ አድርገዉ በመቁጠር እሱን ለማስተዋወቅ የሚጥሩት የዋሽንግተን የሚድያ ኮበሌዎችና መሰሎቻቸዉ ፤በስመ ዲሞክራሲ ወንጀለኞችን የሚኳኩሉበትን ዕብደታቸዉና <”ይቻላል” እያሉ በራቸዉን ክፍት አድርገዉ ከሄያጁም ከመጪዉም በመተሸሸት የፖለቲካ ዉርዴ የሚሸምቱ “የፖለተካ -መበለቶችን” እግዚሃር እንዲምራቸዉ እየተማለልን “ታሪክ እኛኑን ወይንም እነሱን ከሁለት አንዳችን ይጥለናል>።የድሮ የወያኔዉ ትግራይ መንግሥት አስተዳዳሪ እና አዲሱ የወያኔዉ ድርጅት የዓረናዉ መሪ “ገብሩ አስራት እና የሱ አመራር አባል አረጋሽ አዳነ” ስልጣን ላይ እያሉ “ተበደልን ፍትሕ እንፈለጋለን” ብለዉ ለጠየቁ የትግራይ ህብረተስብ አባላት መልሳቸዉ ምን እንደነበር ከሚቀጥለዉ የወያኔዎች የገመና ማህደር እንመልከት። የኢትዮጵያ ሰማይ ለአዲሱ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ የሚለዉ በዳመናዉ ዉስጥ እየተንሳፈፈ የፍትሕ ያለህ በማለት እየጮኸ ያለዉ ‘ወያኔ” የደም ዕምባ ያስለቀሳቸዉን የዜጎችን እሮሮረን በማሰማት ነዉ። ጌታቸዉ ረዳ።
አሁን ወደ ታሪኩ ልዉሰዳችሁ፡ << እንግዳችን ብርሃኔ ገ/ሕይወት ይባላል። ወደ ሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህወሓት) ትግል ዉስጥ እንዲቀላቀል የቀረበለትን ጥሪ ባለመቀበሉና በመቃወሙ፤ በተደጋጋሚ መታሰሩንና በመጨረሻም በአሰቃቂ ሁኔታ በሰባት ጥይት መደብደቡን ይነግረናል። ይህ ወጣት ቤተክርስትያን በማገልገሉም ሳቢያ፤ከፍተኛ ተፅእኖ ተደርጎበት የድቁና መታወቂያዉንም የሕወሐት ታጋዮች ቀድደዉታል። የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ በሐገር ዉስጥ ህክምና የማይድን መሆኑንም የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሰኔ 20 ቀን 1986 አረጋግጧል። ይህንንም ማረጋገጫ የሰጡት ከፍተኛ ህክምና አንደሚያስፈልገዉ ያረጋገጡት ደ/ር ተመስገን ፍጡር (ቀዳጅ ሐኪም)፤ ዶ/ር ዘሩ ገ/ማርያም (ሜዲካል ዳይሬክተር) ፕሮፌሰር W.Mcquillan (የቀዶ ሕክምና አማካሪ) ናቸዉ።
ይህ የ35 ዓመት ወጣት ከዚህ በሗላ ከደረሰበት ጉዳት ለመዳን ዕርዳታ ያደርጉለት ዘንድ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶችን አነጋግሯል። “ዳዉተር ኦፍ ቻሪቲ” ከተሰኘ ግበረ-ሰናይ ድርጅት ጥሩ ምላሽ በማግኘት ከዉጭ ሃገር ገንዘብ ቢሰበሰብለትም ገንዘቡ በድርጅት ሓላፊዎች መበላቱንና በሗላም እሱ ሜዳ ላይ መጣሉን ይናገራል። ወጣቱ በዚህ ጉዳይ ኬንያ ድረስ ሄዷል፤ ወደ ትግራይ ብቅ ብሎም የትግራይ ክልል ዋና ፀሐፊ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነን አነጋግሯል። እዚያም አንደር-ግራዉንድ (ከመሬት በታች) ዉስጥ እንዲገባ በማድረግ ለረዢም ሰዓት በጥያቄ እንዳፋጠጡት ይናገራል ።ይህ ወጣት ሰዉነቱ ላይ ያለዉ ቁስል እያመረቀዘ እንዳስቸገረዉ ለማየት ችለናል።…ይህን ቁስሉን ለማዳንና ከበሽታዉ ለመፈወስ 6 ሚሊዮን 200 ሺህ የኬኒያ ሽልንግ (103 ሺህ ዶላር) እንደሚያስፈልግም ደ/ር ጆን.ኢ.ኤ የተባሉ በኬኒያ የሚገኙ ሃኪም ያረጋገጡበትንና እ/ኤ/አ ዲሴምበር 21/98 የተፃፈ ወረቀትም ይዟል። ሁሉንም ከእርሱ እንከታተል።>> ኢትኦጵ -ቅፅ 2 ቁጥር 016 መስከረም 1993 ዓ.ም }/- ስምህ ማን ይባላል? ብርሃነ፦ ብርሃነ ገ/ሕይወት። ትዉልድና ዕድገትህ ብርሃነ፦ ትዉልዴ አድዋ አዉራጃ ሲሆን፤ቀበሌዉ ጣቢያ ኮረም መንደሩ እንዳ መትከል ስብሃቱ ይባላል። አድዋ አዉራጃ እያለህ የደረሰብህ በደል ምነድ ነዉ?-
ብርሃነ፦ ቤተክህነት ተማሪ እያለሁ በ1975 ዓ.ም ከአክሱም ጽዮን ድቁና ተቀብ ስሄድ በወድቅት ሌሊት የማላዉቃቸዉ ሰዎች ኢሳ ወደ ሚባል ወረዳ አስረዉ ወሰዱኝ። በአሁኑ ወቅት ያለዉ ጳጳስ ከደርግ ጋር ሰዉ እንዲገደል ያወጀ ስለሆነ ቅስናንም ሆነ ድቁናን ሊባርክ አይችልም።” የሚል ምክንያትም ስጡኝ። ጳጳሱ ማን ነበሩ? ብረሃነ፦ ስማቸዉን ዘንግቼዋለሁ በዚያ ሰዓት ስማቸዉ መታወቂያየ ላይ ነበረ። የትግራይ ተወላጅ ናቹዉ? ብርሀነ፡- እኔ እንጃ…አማርኛ ነበር የሚናገሩት።
በተያዝክበት ወቅት ማለትም በ1975 ዓ.ም አካባቢዉን የሚያስተዳድረዉ ደርግ አልነበረም እንዴ? ብረሃነ፦ ከተማዉ ደርግ ነዉ፡በገጠር ወረዳዎችን የሚያስተዳድሩት ወያኔዎች ነበሩ። ከገጠር ነበር ያያዙህ? ብርሃነ፦ አዎ! ከገጠር ነዉ የያዙኝ። እኔ ስለ እናንተ ዓላማ አላዉቅም፡ ከዚህ በፊትም አላዉቃችሁም። እኚህ ጳጳስ ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መሪ መሆናቸዉን ብቻ ነዉ የማዉቀዉ እንጂ፤ ጦርነት ያዉጁ አያዉጁ እኔ የማዉቀዉ ነገር የለኝም ፡ስላቸዉ በቅጣት 10 ቀን አስረዉ መታወቂያየን ቀዳደዱት። በሗላም ደርግ ካለበት አካባቢ እንዳልደርስ አስጠንቅቀዉ በዋስ ለቀቁኝ። ሌሎችም ቅስና እና ድቁና የተቀበሉ ከ50 በላይ የሆኑ ሰዎች ታስረዉ ነበር። እነሱም ከእስራትና ከቅጣት በሗላ መታወቂያቸዉ ተቀምተዋል።
የተቀሙት የድቁና መታወቂያቸዉን ነዉ? ብርሃነ፦ የድቁና እና የቅስና መታወቂያቸዉ ነበር የተቀሙት።ከዚያ እዚያዉ ቆይተን በ1981 ዓ/ም በግድ ወደ ግንባር ዝመቱ አሉን። በ1975 ዓ.ም እንደተያዛችሁ እንድትዘምቱ አልጠየቅዋችሁም? ብርሃነ፦ ይጠይቁን ነበር፤ ነገር ግን ግዴታ አልነበረብንም። በዘፈን ይቀስቅሱን ነበር። በስብሰባ ያስቸግሩናል። ይቆጡናል እንጂ የጠነከረ ግዴታ አልነበረም። በ1981 ዓ.ም ግን ዉጥረቱ ሲበረታባቸዉ ነዉ መሰል ግዴታ ታገሉ አሉን። እኛ “አንታገልም፤እናንተ ታገሉ፡ እኛ ድሆች ነን፡ ገና ዳቦ አንኳን አልጠገብንም” ስንላቸዉ፡”ማን አጥንቱን ከስክሶ ሊያኖርህ ፈለግክ?” በማለት በተለይም “ቢሄን” የተባለ ታጋይ አፈር በእጁ ከመሬት ቆንጥሮ በማፈስ ወዳፍንጫችን አስጠግቶ እንድናሸት አስፈራራን። በአገራችን መኖር ካልቻልን ተሰድደን እንሄዳለን፡ ይለፍ ብቻ ስጡን ስንል ስትፈልጉ በሰማይ ሂዱ እንጂ አይሰጣችሁም፡ እያሉ ያፌዙብን ነበር።
“ታዲያ የት እንድረስ?” ስንላቸዉ “የራሳችሁ ጉዳይ!ከፈለጋችሁ አገራችሁን ነፃ አዉጡ። ነፃ አናወጣም የምትሉ ከሆነ ግን የዚህችን ምድር በረት አትረግጡም። አሉን። “ከማን ነዉ ነፃ የምናወጣት?” ደርግም ኢትዮጵያዊ ነዉ እናንተም ኢትዮጵያዊያን ናችሁ።” ስንል <ከበስተጀርባችሁ የሆነ ነገር አላችሁ!> በማለት ማሰር እና መቅጣት ጀመሩን።
ስንት ትሆናላችሁ? ብርሃነ;- 1500 እንሆናለን። ከዚያ ምን ተከተለ? ብርሃነ;- ፦ወላጆቻችን ታሰሩ። የእርሻ ማስታዎሻችንም ተወረሰ። ቀንደኛ ዓድመኞች ናችሁ በተባልን በተወሰንን ሰዎች ላይ ከባድ ቅጣት ተፈጸመብን። ከ6 ወር አስከ ዓመት በእስራትና በግርፋት ተቀጥተናል። ክንዶቹ ለረዥም ጊዜ በቀጭን ጅማት ነገር በመታሰራቸዉ ምክንያት ጣቶቹ ደም አስከ ማንጠባጠብ የደረሰ ጓደኛችንም ነበረ። በጅማት ታስሮ እጁ ደም ያንጠባጠበዉን ጓደኛህን ስም ታስታዉሰዋለህ? ብረሃነ፦ የአንዱ ስም አላስታዉሰዉም። ሰለዳም የሚባል ቀበሌ ነዋሪ ነዉ። ሌላዉ በግርፋት አንድ እጁ እና አንድ እግሩ ሽባ የሆነ ጓደኛየ ሃለቃ ሓዲሽ የባላል። ቢዚያን ወቅት <ሙሹሮችና ካህናት> ሳይቀሩ <በህማማት ጊዜ ከቤተክርስትያን> ተወስደዉ ከሽማግሌዎች በቀር ሁሉም ታፈሶ ተወሰደ። ለመሸሽ የሞከረዉን እንደጅግራ እያሯሯጡ በጥይት ያሳድዱት ነበር።
ይህ ሁሉ የተፈጸመዉ መቸ ነዉ? ብርሃነ፦ የካቲት ወር 1981 ዓ.ም ጀምሮ ማለት ነዉ። ትግራይ ነጻ ከወጣች በሗላ ማለት ነዉ? ብረሃነ፦ አዎ:: ከዚያ… ሰዉ እንደ አዉሬ በአካባቢዉ እየተበተነ በአካባቢዉ በቀን ሰዉ የሚባል አይታይም ነበር። እነሱም እንደ ጅግራ እያደኑ ይዉላሉ፤መሬታችንም ለታጋይ ቤተስብ ታድሎ የምንቀምሰዉ የምንልሰዉ አልነበረም።ከቀበሌ ወደ ቀበሌ የሚያስተላልፉ የነሱ ካድሬዎች ካዩን ጥይት ይተኩሱብናል፤ የተኮሱብን ጥይት አልመታንም እንጂ ቁጥር የለዉም።ከዚያ በሗላ እየተንከራተትንና እየተራብን ቆይተን ህዳር 21/1983 ዓ.ም ገረዳ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ለአቶ በርሄ እህል ስንሸከምላቸዉ ዉለን፤ቤት ገብተን ገበታዉ ቀርቦ እህል ልንበላ ስንል ቤቱ ተከበበ። የማይታወቁ ታጣቂዎች ናቸዉ። ከተሰበሰበዉ ሰዉ እኔን ጠሩኝና ዉጣ አሉኝ። መጀመሪያ እህል ይብላ እና ዉሰዱት ብለዉ የቤቱ ባለቤት ቢጠይቁም <<አስቸኳይ መልዕክት ስላለን ነዉ፤አሁን ይመለሳል>> ብለዉ ወሰዱኝ።ሌሎችም ከያቅጣቻዉ ተሰበሰቡ።ወደ 5 እንሆናለን። ሁላችንም በስብሰባ ላይ የምንከራከራቸዉ ነበርን። <<እነዚህ ካልጠፉ ወጣቱ አይታገልም፤በታኞች ናቸዉ፤ከደርግ ለይተን አናያቸዉም>> በማለት ከዚያ በፊት እንዳጠፏቸዉ ወጣቶች እኛንም ለማጥፋት ተዘጋችተዉ እየወሰዱን ሳለ፤ እርስ በርሳችን እንነጋገር ነበር። ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ይሆናል።
የት ነበር የሚወስዷችሁ? ብርሃነ፦ ጫካ ነዉ፤ እኛ አናዉቀዉም። ኢሳ የሚባል በረሃ ነዉ። ምን ይሻላል? ለመሞት ለመሞት እዚሁ እንሙት እየተባባልን እንደገና ጉዞ ጀመርን። አልፎ አልፎ ነዉ እንጂ እኛን ባንድ ላይ አይወስዱንም ነበር። አንድ እዚህ፤ አንድ ደግሞ ራቅ አድርገዉ ሊወስዱን ከፊት ያለዉን ገፍቼ ሸሸሁ። ቁጥር የሌለዉ ጥይት እላየ ላይ ዘነበ። ፀጉሬ ላይ ትንሽ ነካኝ እንጂ አልመታኝም። አምልጬ ሕግ ያለ መስሎኝ ወደ ዋናዉ አለቃ ሄጀ <የማይታወቁ ታጣቂዎች ሌሊት መጥተዉ በደል አደረሱብኝ፤ በነዚህ ሰዎች ላይ ክትትል ይደረግልኝ፤ከየት እንደመጡ ማን እንደላካቸዉ ይጣራልኝ> ብየ አቤቱታ ሳቀርብ፡ <<እኛ እናጣራዋለን፤ እንከታተላቸዋለን>> ሚል መልስ ሰጡኝ። በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ ጥር 23 ቀን 1981 ዓ.ም ሥራ አድሬ ከንጋቱ 12 ሰዓት አካባቢ ወደቤቴ ስሄድ……..
ምንድነዉ ስራህ? ብርሃነ፦ የቤት ስራ፤ቤት በደቦ ስንሰራ ደክሞኝ እዚያ አድሬ ነበር። አባቴ ሞቷል..እናቴ አለች፤ የእናቴ ትንሽ መሬት ነበረችን፡ ቤቴ እንደደረስኩ በረቱን ከፍቼ ለበሬዎቹ ድርቆሽ ልሰጣቸዉ ስል….የ.ማላዉቃቸዉ ሰወች ብትንትን ብለዉ ተኝተዉ አገኘሗቸዉ። ቤቱ ተከቦ ነዉ ያደረዉ። እናንተ እነማን ናችሁ? ስላቸዉ አንዱ እያናገረኝ ሌላኛዉ በሰባት ጥይት መታኝ። በሆዴ እና በአንጀቴ ላይ ደሙ እየተንዠቀዠቀ ሲፈስ እናቴ እንዳታይና እንዳትጮህ ውስጥ ግቢ አሏት። ከዚያ በሗላ <እግሬና እጄን አንጠልጥለዉ ጎትተዉ ጫካ ዉስጥ ጣሉኝ>። አንጀቴ ተበጥሷል። እንጀቴ ይታያል፡ቅጠላቅጠል አልብሰዉኝ ተሰወሩ።ይህ ሁሉ ሲሆን ከሩቅ ይከታተሉ የነበሩ የአካባቢዉ ሰዎች እነማን እነደሆኑ አይተዋል።
ስንት ነበሩ? ብርሃነ፦ ወደ 10 ይሆናሉ። ሕዝቡ ተከትሏቸዉ፤ << እነማን ናችሁ? ቁሙ! ነፍስ አጥፍታችሁ አትሄዱም>> ሲላቸዉ “እየሳቁ” ሄዱ ። በመጨረሻ ከወደቅኩበት አንስተዉ በሰልፍ ተሸክመዉኝ ዓድዋ አዉራጃ አሰተዳደር ወሰዱኝ።<<የዛሬ ብርሃነ ዕድል ነገ ለኛ ነዉ። ይሄ ልጅ ምን አጠፍቶ ነዉ በወጣትነቱ የተቀጠፈዉ?>> ብሎ ህዝቡ አቤቱታ አቀረበ። በዚህ ወቅት ሕዝቡ መቷል ብሎ ስላመነ ጉድጓዴ ሳይቀር ተቆፍሮ ነበር። ጫካ ወስደዉ እንደጣሉኝ የተነገረኝም በሗላ ነዉ። ሕዝቡ አሰከረኔን ተሸክሞ <<ደርግን ግፈኛ ትላላችሁ እንጂ ይሄዉና የናንተም ግፍ!>> ሲሏቸዉ 15 ወጣቶች በሲሚንቶ የተሰራ የጣሊያን ጉድጓድ ዉስጥ አስገብተዉ አሰሯቸዉ። በአጠቃላይ ሕዝቡ 500 (አምስት መቶ) ይሆን ነበር። ወጣቶቹን ካሰሩ በሗላ ህዝቡን በዱላ በታተኑት። እኔንም የሚያዉቁኝ ሰዎች ወደ አክሱም አመጡኝ በአጋጣሚ ነጮች ነበሩ ኦፕራሲዮን አደረጉልኝ።
የት ነዉ ኦፕራሲዮን ያደረጉልህ? ብርሃነ፦ አክሱም ሆስፒታል። ሁለት ሰዎች ደም ሰጡኝ። ደም ጨርሼ ነበር። ይሄን ሲነግሩኝ እንጂ እኔ አላዉቅም። ለ3 ወር ያህል ሕይወቴን አላዉቅም ነበር። የተኛሁበት የጀርባየ ጠባሳ አሁንም አለ። ሕይወቴ መቆጣጠር ስላልቻልኩ መቀሌ ታከምኩ። እዚያም ስላልቻሉ አዲስ አበባ ጥቁር አምበሳ መጣሁ። ጥቁር አምበሳ የመጣኸዉ መቸ ነዉ? ብርሃ፦ በ1984 ዓ.ም ሚያዚያ 4 ቀን አዲስ አበባ መጣሁኝ። ጥቁር አምበሳ ሆስፒታልም አስከ መጨረሻ ጥረት አደረጉልኝ። ሕይወቴን ለማዳን በህክምና ብቻ ሳይሆን በተለያየ መልኩ ሲረዱኝ ቆይቶ መጨረሻ ሲያቅተዉ በ1986 ሰኔ 16 ዉጪ ድረስ ሄጄ እንድታከም ወስኖ አሰናበተኝ። ከዚያ በሗላ አማራጭ አጣሁኝ። ቀኑ ጨለመብኝ።
ከጥቁር አምበሳ ስትወጣ ወዴት ሄድክ? አዲስ አበባ ቤተሰብ አለህ? ብረሃነ፦ የለኝም። ታዲያ የት አረፍክ? ብርሃነ፦ እዚሁ ሆስፒታል ኮሪደር ላይ ነበር የምተኛዉ ። ከተሰናበትክ በሗላ? ብርሃነ፦ አዎ። ከዚያ ወደ ትግራይ ሄድኩ ። የማላዉቃቸዉ ሰዎች አዋጥተዉ ቲኬት ቆረጡልኝ ። ትግራይ ከሄድኩ በሗላ ከብዙ ደጅ ጥናት በሗላ የክልሉ መንግሥት ጸሃፊት ወ/ሮ አረጋሽ አዳነን አነጋገርኳት። <ምን ሆንክ> አለችኝ። <በጥይት ተመትቼ> <ማን መታህ?> <የህወሃት አባላት><እንዴ! ምን ብለዉ ይመትሗል? ክሰሳቸዉ።>
<ምን ብየ እከሳቸዋለሁ? ታዉቁት የለም እንዴ ራሳችሁ። እንደ ብርሃነ አንዳትሆኑ እያላችሁ መድረክ ላይ ስበሰባ ላይ ትናገሩ አልነበረም አንዴ? ከ500 ህዝብ በላይ አቤቱታ ለማቅረብ ሲቀርብ በዱላ አላባበረራችሁትም? ወንጀለኛ ከሆንኩኝ ግደሉኝ፤ካልሆንኩ ግን አሳክሙኝ። አናዉቅም የምትሉኝ ከሆነ ደግሞ ስንብት ወረቀት ስጡኝና የትም ሃገር አቤት ልበል>> ስላት፡<የለም ምንግሥት አይመታህም> አለችኝ።<መንግሥቱ ሃይለማርያም አሰቃይቶ የገደለዉ ሰዉ የለም። የእርሱ ወታደሮች ግን ሰዉ ገድለዋል።የህወሐት ወታደሮችም እንደቅጠል ነዉ የቀጠፉን፤የገረፉን።ዕድሜ ልካችንን ሲያሰቃዩን ነዉ የከረሙት። ስለዚህ ለዉጥ የለዉም።ፍረድ ቤት በደርግ ጊዜ ነበረ አሁንም አለ። ያለዉ ፍርድ ቤት ነዉ እንጂ ማሕበራ ፍርድ ቤት አይደለም።የመሰላችሁ ፍትህ ስጡኝ> ስላት፡ <ግብረሰናይ ድርጅቶች ጠይቅ አለችኝ።> <ከ300 በላይ ግብረሰናይ ድርጅቶችን አነጋግሬ “መንግሥት ማንንም ሰዉ በግለሰብ ደረጃ እንዳትረዱ የሚል ማስጠንቀቅያ ሰጥቶናል” ብሉኛል፡ አኔ ከ60 ሚልዮን ሕዝብ በላይ ስለማልበልጥ ብጠይቃቸዉም መልስ አጥቻለሁ።> ስላት <ይህንን ነገር እንዴት ልታወቅ ቻልክ?> <ይሄማ ግልጽ የሆነ እኮ ነዉ>ስላት <ይሄማ የፓለቲካ አዝማሚያ ነዉ> ብላ ወዲ ሻምበል የሚባለዉን የፖሊስ አዛዥ ጠራች ።አሱም መጣ።ሌሎችም ተከተሉ።ድምፅ እንኳ ወደማይሰማበት “አንደር-ግራዉንድ” አስገቡኝ።
አንደርግራዉንዱ አዚያዉ ምክር ቤት ዉስጥ አካባቢ ነዉ ያለዉ? ብርሃነ፦ አዎ። ከ8፡00-1130 ድረስ ጎሮሮየ ደርቆ መናገር አስኪያቅተኝ ድረሰ በጥያቄ አፋጠጡቡኝ። የሚጠይቁህ ምን ነበረ? ብርሃነ፦
የደረሰብህ ነገር ተንትነህ በሙሉ ንገረን፤ያየሀዉ ነገር ሁሉ ተናገር፤ሙሉ መብት ሰጥተንሃል አሉኝ። እኔ በመጀመሪያ የቤተክህነት ተማሪ ነበርኩ።ወላጆቼ ቤተክርስትያንን እንድታገለግል ለቤተክርስትያን ሰጥተንሃል አሉኝ። እኔ በመጀመሪያ ደረጃ የቤተ ክህነት ተማሪ ነበርኩ።ድቁናየ ስቀበል ደግሞ ታጋይ ሐጎስ የሚባል የወረዳ አስተዳዳር “የድቁና የምስክር ወረቀቴን ቀደደዉ”።ቀጥለዉ ታገል ተባልኩ። እኔ አልታገልም ሰርቼ ነዉ የምበላዉ ስላቸዉ፡ “የለም መታገል አለብህ ” አሉኝ። መጨረሻ ወጣቱን በታኝ ነህ! አሳዳሚ ነህ!> አሉኝ።የበተንኩት ሰዉ የለም።ብርሃነ እንዳትታገል ብሎኛል የሚል ሰዉ ካለ አምጡት አልኳቸዉ።
መጨረሻም ወጣቱን ማፈን ጀመሩ። መፈን መባረር ሲጀምሩ እኛም የምንገባበት ቦታ አጣን።ተረበሽን፤ የት እንሂድ? ገሚሶቹ ወጣቶች ወላጆቼ በእኔ ሰበብ ከሚሰቃዩ አኔ ልሙት እያለ ወደ ትግል ግምበር ሄዶ ሞቷል።እላዩ ላይ ሳር በቅሎበታል።የተቀረንም ሰዉነታችን በጥይት ተበሳስቷል።እሳት ጨብጦ፤ፈንጅ ረግጦ ለስልጣን ያደረሳችሁ ወጣት በየፌርማታዉ ወድቋል፡ግማሶቻችንም ጠፍተናል።
ለምሳሌ ያህል ይግዛዉ ጣሰዉ - ከማይጓጓ ፍቱሕ ገ/ሕይወት - ከማይዳዕሮ አለቃ ሐጎስ- ከማይደዕሮ ገ/እግዚአብሔር= ከደዕሮ ሸዊቶ ዓለምሰገድ ይግዛዉ -ከዳዕሮሸዊቶ አረፋይኔ ከገረዓ፤ አበበ ገብረአብ - ከገረዓ ሲጠቀሱ ከነዚሁ አንዱ አኔ ነኝ
እነዚህ የተገደሉ ናቸዉ? ብርሃነ፦ ታፈነዉ ተወስደዉ የጠፉ፤አድራሻቸዉ የጠፋ ናቸዉ። አሁንም የት አንዳሉ አይታወቅም? ብርሃነ፦
የሉም! በቃ!....ለአብነት ያህል ከነዚህ ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ። ጊዜ ከሰጣችሁኝ በመቶ ሚቆጠሩ ሰዎች አዉቃለሁ አልኳቸዉ። በመጨረሻ <መሬት ተወስዶብኛል ብለሃል ማን ነዉ የወሰደዉ?> አሉኝ። አኔ እዚህ ሆኜ መሬቴ ተወስዷል፡መሬት የለኝም።የሚል መለስ ሰጠሗቸዉ። <በምን ትደዳራለህ> አሉኝ፤ <ለምኜ ዕድሜ ለሕዝቤ> የሚል መልስ ሰጠሗቸዉ። <በል አሁን የምትፈልገዉ ምንድነዉ? ደረሰብኝ የምትለዉ በደልስ ምንድነዉ?> አሉኝ <<እኛ የትግራይ ተወላጆች በሦስት ፓርቲ ብዙ ችግር ደርሶብናል።ከኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ ሁኔታ የትግራይ ህዝብ በደረግ በሻዕቢያ በህወሐት ተበድሏል። እንደዚህ ሆኖ እያለ የደርግ ባለስልጣኖች ለፈጸሙት ግፍ በፍረድ ቤት ሲጠየቁ እኛስ ለምን መፍትሔ ለምን አይሰጡንም?ለምሳሌ ለደርግ ባለስልጣናት በጀት መድባችሁ ጠበቃ አቁማችሁ ፍ/ቤት እንዲቀርቡ አድርጋችሗል።በህወሐት እና ፡በሻዕቢያ በኩል በደል የደረሰብን ሰዎችስ ምን እንሁን?እኛም እኮ ሰዎች ነን።ቅጠል አይደለንም።መፍትሔ ለምን አይሰጠንም?>>
ብየ መልስ ሰጠሗቸዉ።አንዲያዉም የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገብሩ አስራት <<በትግላችን ወቅት ያጋጠሙን አንዳንድ ችግሮች በአሁኑ ሰዓት ሊያስጠይቁን አይችሉም።>> የሚል መለስ በመድረክ ላይ ተናገረ።
በስብሰባ ላይ ነዉ? ብርሃነ፦ በስብሰባ ላይ የተናገረዉና በቴሌቪዥን የቀረበ ነዉ ፤መልስ የሰጠዉ። እኔ የተናገርኩት እና ሌሎችም ቤተሰቦቻችን አምጡልን፡ሞተዉም አንደሆነ ንገሩን ብለዉ አቤቱታ በማቅረባቸዉ ነዉ። ከእነ ወዲ ሻምበል ጋር በእንዴት ተለያያችሁ?
ብረሃነ፦ መጨረሻ ላይ አሁን የት ነዉ ምትኖረዉ አሉኝ? እኔም አቅጣጫ ቀይሬ አዚህ ቦታ ነዉ የምኖረዉ አልኳቸዉ። ተከትለዉ ሊይዙኝ ነዉ የፈለጉት። እዚያዉ ትግራይ ዉስጥ ነዉ ያልከዉ? ብረሃነ፦ አዎ።መቀሌ ዉስጥ የሀሰት አድራሻ ነግርያቸዉ፤ ከከተማ ወጥቼ ቲኬት አስቆርጨ አ/አበባ መጣሁ። አ/አበባ እንደመጣሁ ድርጅቶች ዉጭ ልከዉ አንዲያሳክሙኝ ጠየቅኩ።
የዉጭ ድርጅቶችን ነዉ? ብረሃነ፤_ አዎ “ዳዉተር ኦፍ ቻሪቲ” ወደ ሚባለዉ ድርጅት ሄጀ “ሲሰተር ካትሲል ካሲን” የምትባል አነጋግሬያት አልቀበልም ብላኝ ነበር።ዶክሜነቴን ካየች በሗላ ግን ተቀብላ ፈቃደኛ ከሆንክ ዉጭ ገንዘብ አሰባስቤ ለንደን ወስጄ ላሳክምህ አለችኝ። እኔም ፈቃደኛ ሆኜ ያለኝን ዶክሜንት እና ፎቶግራፌን ጭምር ሰጠሗት። እርግጠኛ አይደለሁም ገነዘቡ ሲገኝ እነግርሃለሁ አለችኝ።እሺ ብየ ስጠብቅ በ1988 ዓ.ም ነሐሴ አካባቢ “ሲስተር እዉነቱ” የምትባል የሷ “ጸሃፊ” እና አሷ ሆነዉ <ገንዘቡ ተገኝቶልሃል ዉጭ ትሄዳለህ፤አሁን አሁን ፎርሙን ትሞላለህ > አሉኝ። እሺ ብየ ፎረሙን ሞላሁ።የምታዘጋጀዉ ነገር ካለ አዘገጅ አለችኝ። ተዘጋጀሁ። በዝግጅት ላይ እያለሁ ነሐሴ መጨረሻ ታመመምኩ። ምኒሊክ ሆስፒታል ተኛሁ።
ከምኒሊክ ሆስፒታል ተኝተህ ከወጣህ በሗላ ከሲሰር ካትሲል አልተገናኘህም? ብርሃነ፦ ለምሳሌ ያህል ሲሰተር ጤናየ በአካል ጉዳዩን ታዉቀዋለች። ዶ/ር ሙሉጌታ እና ዶ/ር ሥዩም የሚባሉ ባሉበት “ሲሰተር ካትሲል” <እኔ ከሁለት ሳምንት በሗላ ወደ ዉጭ አልከዋለሁ።ጊዜያዊ ዕርዳታ አድረጉለት ገንዘብ አሰባስቤለታለሁ> ትላቸዋለች። እነሱም የዉጭ ዜጋ ሆነሽ እንደዚህ ካደረግሽ እኛ የኛ ወገናችን ሆኖ ዕርዳታ የማናደርግለት ምንም ምክንያት የለም። አሏት። ከዛ አስወጥታ ቤቷ ድረስ ወሰደችኝ። ቤቷ ከወሰደችኝ በሗላ…
እራሷ ቤት? ብርሃነ፦ አዎ። መኖሪያ ቤቷ ከወሰደችኝ በሗላ፤”ሲሰትር ጆኣን” የምትባል ሃኪም ነበረች። እገሬም መንቀሳቀስ አይችልም ነበር፡ በጣም ደክሜአለሁ። ከሆስፒታል የታዘዘልኝ መርፌ ነበርና <ልዉጋህ መሬት ዉረድ ከአልጋ > አለችኝ።አሁን “ሴንት ሜሪ” ነዉ የምትሰራዉ። አስክትነግሪኝ ድረስ አልቆይም ወርጄ እወጋ ነበር፤ነገር ግን አቅም የለኝም ሁሌም አልጋ ላይ ነዉ ተኝቼ የምወጋዉ> ስላት፤እግሬን ጎትታ መሬት ላይ ወረወረችኝ።ደም ፈሰሰኝ።አለቀስኩ። በሗላ የትግራይ ኢሮብ አካባቢ ተወላጅ የሆነች “ሲሰተር ሳባ” የምትባል የሰጠችኝ መልስ << ብርሃነ! ይህ እኮ የካቶሊክ ድርጅት ነዉ፡ ለምን ቅድስት ማርያም ሄደህ አትለምንም?>> አለችኝ። ከዚያም ለሲስተር ካትሲል <<የካቶሊክ እማኞች እያሉ ይሄ እንዴት ይሄዳል? የተሰበሰበለት ገንዘብ በካቶሊክ ድርጅት እንጂ በኦርቶዶክስ ድርጅት አይደለም፤ሊሄድ አይችልም>> ብላ ተቃዉሞ አቀረበች። በወቅቱ ለእኔ ይነገረኝ የነበረዉ ግን ገንዘቡ እንደመጣ ከሁለት ሳምንት በሗላ አንደምሄድ ነበር የተነገረኝ።>>
ሲስተር ሳባ የተቃወመችህ ኦርቶዶክስ ስለሆንክ ነዉ ወይስ ከህወሐት ጋር ግንኙነት ኖሯት ኖሯል ይሆን? ብርሃነ፦ ያን ጊዜ በህወሐት እንደተመታሁ አያዉቁም ነበር። እንዲያዉም ግልፅ አድርጌ አልናገርም ነበር። ከዚያስ ምን ተከተለ? ብረሃነ፦ በሰኔ ወር 1990 ዓ.ም ፈረንጇ አዲስ ወረቀት አምጣልኝ እና እሞክራለሁ ስላለችኝ ሆስፒታል ከጤና ጥበቃም ጭምር አስፅፌ ሰጠሗት። ማስረጃዉን ስሰጣት ክረምቱን ዉጭ ነዉ የምቆየው ገንዘብ አሰባስቤ እመጣለሁ አዚሁ እየሰራህ ቆየኝ>> አለችኝ። ተመልሳ ስትመጣ <<ትንሽ ገንዘብ አግኝቼአለሁ እና እንዳልከዉ ኬኒያ ብትሄድ ምን ያህል ያድኑኛል ብለህ ታምናለህ? >> አለችኝ። እኔም <<እርግጠኛ አይደለሁም፤ ነገር ግን ወደዚያዉ የሚመላለሱ ነጋዴ ዎች ስላሉ ከነሱ ጋር ልመካከር።>> አልኳት። እንግዲያዉስ ተነጋገርና በአጭሩ ቀን መልሱን ስጠኝ>> አለችኝ። ነጋዴዎቹ የሕክምና ማስረጃየን ኬንያ ከወሰዱ በሗላ <ኬኒያ ደርሰን ለዶክተሮች አሳየነዉ፡ የሕክምናዉን ወጪ ግምቱን እንጂ ከወዲህ ይህን ያህል ይፈጃል ማለት አንችልም፡የራጁ ዉጤት ስለሌለም ለመገመት ያዳግተናል፤አንደሚታየዉ ጉዳቱ ከባድ በመሆኑ ከ15ሺህ ዶላር በታች አይበቃዉም>> መባላቸዉን ገለጹልኝ። ይህንኑ አምጥቼ፤ በአማርኛ ተጽፎ የነበረ፤ በእንግሊዝኛ አስተርጉሜ ሰጠሗት።ስላት፡<<በል ተዘጋጅ፤ አሁን ትሄዳለህ፡ፓስፖርት አዉጣ>> አለችኝ።ፓስፖርት ካወጣሁ በሗላ ወደ ናይሮቢ ከመሄዴ በፊት ገንዘቡ ይሰጠኝ ችግር ሊያጋጥመኝ ይችላል እና ትለልቅ ሰዎች ስላሉ ገንዘቡን ለነሱ ስጪሊኝ>> ስላት <<የለም እዚህ አልሰጥም ከኢንግላንድ ቀጥታ ከአባ ሚካኤል 15 ሺህ ዶላር ተቀብለህ ታክመህ ትመጣለህ።ካነሰህ ከዚያ ደዉለህ ንገረኝ>> ብላ አድረሻ ሰጠችኝ።
ኣባ ሚካኤል ደግሞ መናቸዉ? ብረሃነ፦ የአባታቸዉን ስም አላቅም፡ ፈረንጅ ናቸዉ።ካቶሊክ።አድራሻቸዉ ጽፋ ሰጠችኝ።ያለ ተቀባይ ቀጥ ብየ ሄድኩ። ከዚያ ስደርስ ችግር መጉላላት ደርሶብኛል።እግዚአብሔር ጥሎ አልጣለኝም ከዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ትብብርና ዕርዳታ አድርገዉልናል። በገንዘብም በሌላም።ከእኝህ ሰዉ ጋር ያገናኙኝም አነሱ ናቸዉ።በሗላ ግን የተጠቀሰዉገንዘብ አላገኘሁም።
ሰዉየዉን ስታገኛቸዉ የለም አልሁ? ብርሃነ፦ ትንሽ ገንዘብ ነዉ ያለዉ አሉኝ።<ምን ያህል አለ?> ስላቸዉ <2ሺህ> አሉኝ። 2ሺህ ዶላር በናይሮቢ ደረጃ ለቀለብ እንኳን አይበቃም ብየ ለሲስተር ክርስቲና አዲስ አበባ ደወልኩላት። በኬንያ የታወቀ ሆስፒታል ስንት ዶላር እንደሚያስከፍሉ ተመርምረህ ወይም ግምቱን ላክልኝ ወይም ይዘህ ና አለችኝ፤፡ አኔም ኬንያ ዉስጥ አጋርካን በሚባል ሆስፒታል ደ/ር ጆን የሚባል ሃኪም ለ1 ሳመንት መርምሮኝ ዋጋዉን አሳወቅኳት።ሁሉን ነገር ካየ በሗላ 4 ወር ትተኛለህ፤ሦስት ዓይነት ኦፐራሲዮን ታደርጋለህ እግርህም ይድናል። እንደነበረዉ ይሆናል። ለአጠቃላዩ ወጪ 6ሚሊዮን 200 ሺህ የኬንያ ሽልንግ ወይም 103 ሺህ ዶላር ትከፍላለህ አለኝ።ይህንኑ መልስ ለሲሰተር ካሰቲል ሰጠሗት። ሲስተር የሄን ጊዜ ፈነጠዘች። <3ጊዜ>። <አንዳለ ፈረንጅ በሙሉ የግምቱን ወረቀት ሲያይ አጨበጨበ>።
ለምን? ብርሃነ፦ በዚህ ሰነድ ከብዙ ሃገሮች ገንዘብ ስለሚሰበስቡ።..በካናዳ፤ በአሜሪካ፤ በእንግሊዝና በሌሎችም አገሮች ለሚገኙ በጎ አድራጊዎች ወረቀቱን እበትነለሁ። በዚህ ሰነድ ገንዘብ ሲመጣ ተመልሰህ ትሄዳለህ ትለኛለች። እሺ ብየ በመጠባበቅ ላይ እያለሁም ለ”ጋሽም” የጉዞ ወኪል ልካ ገንዘብ ጨምረን ስለምንልከዉ ተመልሶ ለሕክምና ስለሚሄድ ከቲኬቱ ከሚመለሰዉ ገንዘብ እንኳ መልሱት ብላ እዚያዉ አስቀሩት። ከታህሳስ አስከ ሚያዚያ ሲያመላልሱ አቆይተዉኝ አለርት ሆስፒታል እንሂድ አሉኝ።
<< አለርት ሆስፒታል ስጋ ደዌ ህክምና ነዉ ያለዉ፤የኔን በሽታ አይመለከትም፡ ባለሞያወቹ ጥቁር አምበሳ ሆ/ል ነዉ ያሉት ስለዚህ አልሄድም> ብል፡ <እገሌ ከሚባልደ/ር ጋር ተስማምተናል።> አሉኝ።ምነድነዉ ምትስማሙት 5 ዓመት ሙሉ መለመኛ ሆኜ ተቀምጫለሁ። ከዚህ በሗላ መለመኛ ሆኜ መቀጠል አልፈልግም። ያገኘሁት ፋይዳ የለም። ስለዚህ ባላችሁት መሰረት ላኩኝ፡ አንልክም የምትሉ ከሆነ ግን በስሜ የተዋጣዉን ገንዘብ ስጡኝ፡ የትም አገር ሄጄ ታክሜ እድናለሁ> ስላቸዉ ሲስተሯ ተደበቀች።
በሗላ ባሕር ዳር ሄዳ መሸሸግዋን አወቅኩ። ባሕር ዳር ሄጀ ለፓሊስ ኮሚሽኑ እንዲህ ያለች ሴትዮ አለች ተባበሩኝ አልኳቸዉ። ያለችበትን ንገረን እንተባበርሃለን አሉኝ። እኔን ስታይ ትደበቃለች ብየ በሌላ ሰዉ ሳስጠይቅ እንዲህ የምትባል እዚህ የለችም አሉኝ። ከባህር-ዛፍ ዉስጥ ተደብቄ ቆየሁና መኪና ይዛ ስትወጣ ያዝኳት። ሕግ ቦታ አንሂድ ገንዘቤን ስጪኝ። ስላት፡
<<ተዉ አታጋልጠኝ፡ እኔ ሲሰትር ሜሪ ለምትባል አዉስትራሊያዊትና ለሲስተር ትብለጽ አስረክቤ ነዉ የመጣሁት፡ 1 (አንድ) ቀን ብቻ ስጠኝና አስጨርስልሃለሁ።>> አለች ።ችግር የለም፡ አልኳት።በሗላ ግን ተመልሳ ወደ አዲስ አበባ ጠፍታ ሄደች። አግኝቻት ነበር፡ ጠፋች አልኩ።ለፖሊሶች።ፖሊሶች ለአየር መንገድ ስልክ ደወሉ። በየጠዋቱ በረራ እንደመጣች አረጋገጡ። ከባሕር ዳር መጥቼ “ሴንት ሜሪ ” አዲስ አበባ ከተማ አገኘሗት። ሳገኛት <<በይ አሁን ኡ! ኡ! እላለሁ! መፍተሄ ስጪኝ፡>> ስላት፡
<<አዲስ አበባ የመጣሁት እኮ ስላንተ ጉዳይ ለመነጋገር ነዉ። የባንክ ደብተር ከፍተህ እኔ ጋር ና>> አለችኝ። እዉነት መስሎኝ ይህንን ሰኔ 20ቀን 1991 ዓ.ም ከተነጋገርን በሓላ ሰኔ 22 ደብተር ከፍቼ ወደ ሴንትሜሪ ስሄድ ጽሁፍ አዘጋጅታ ድርጅቱን ሰራተኞችና ሌሎችም የማይታወቁ ሰዎች ይዛ “አንደር-ግራዉንድ” ዉስጥ አስገብታ፤መስኮትና በር ተቆልፎ በቀኝና በግራ እጄን ይዘዉ በማላምንበት ወረቀት አልፈርምም አሉኝ። በማላዉቀዉ ጉዳይ አልፈርምም አልኩ።
ምንድነዉ የምትፈርመዉ? ብርሃነ፦ ሕክምና አልፈልግም፤… ምናምን የሚል ይዘት ነበረዉ። አላነበብከዉም? ብርሃነ፦ ትንሽ ነዉ ያየሁት አላነበብኩትም።3ገጽ ነዉ የተጻፈዉ።በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ። አምቢ ስላቸዉ ጊዜ ሰራተኞቹ ለመኑኝ። <<የሰዉ እንጀራ አትዝጋ፡ ለምን አትፈርምም? የሰጠችህ ገንዘብ አለ።አሉኝ። ልወጣ ስል ከለከሉኝ።በየት ልዉጣ?! በሩ ተቆልፏል። ከዉስጥ ሌላ ክፍል አለ፦ ፊታቸዉ እንዳይታይ ኦፐሬሽን እንደሚያከናዉን ዶ/ር ዓይናቸዉ ብቻ የሚታይ ሰዎች ጩቤ እና መሳሪያ ይዘዉ ደረቴ ላይ ደገኑብኝ። ካሁን በሗላ ወይ ለጋዜጠኛ አልያም ለፖሊስ ከተናገርክ ወዮልህ! ትፈርማለህ …አትፈርምም? የማን ገንዘብ ልትበላ ነዉ?ካንገራገርክ እዚሁ እንደፋሃለን!>> አሉኝ። የነሱን ዘዴ ስላወቅኩ ገድለዉ በቆሻሻ መኪና ሊጥሉኝ እንደፈለጉ ግምት ስላደረብኝ ችግራችሁ ይሄ ከሆነማ አምጡ፡ እፈርምላችሗለሁ።>> ብየ ፈርሜ 5 ሳንቲም ሳልይዝ ወጣሁ። ሁሉንም ለፖሊስ ጣቢያ፤ለጠቅላይ ሚ/ሩ ቢሮ ለፍትሕ ሚ/ርና ለዉጭ ጉዳይ መ/ር በአስቸኳይ አሳወቅኩ።
ማመልከቻ ነዉ? ብረሃነ፦ ማመልከቻ ባስቸኳይ በፖስታና በተለያዩ መንገዶች ከ70 ብር በላይ አዉጥቼ ላክሁ። የተሰጠኝ መልስ ግን የለም። የዉጭ ጉዳይ ሚ/ር ከስንት ጊዜ በሗላ እንዲጣራ ብሎ ለፌደራል ፓሊስ አስታወቀ። መጨረሻ የማይረባ ገንዘብ ሰጥተዉ አሰናበቱኝ። ማን? ብርሃነ፦ እነሱ። እነሱ እነ ማን? ብርሃነ፦ እነ ሲሰተር ክርሰቲኒ፡ ምን ያህል ላኩልህ? ብርሃነ፦ ወደ አስር ሺህ ገደማ ላኩልኝ።በዛችዉ ስታከም ቆየሁ። መንግሥትም ዞር ብሎ አላየኝም። አስካሁን ድረስ በዛች ገንዘብ ነበር ቆየሁት። አሁን ግን የምቀምሰዉ እንኳ ቸግሮኛል። ጠ/ሚ/ሩ ቢሮ አመልክተህስ ምንም ምላሽ አልመጣም? ብርሃነ፦ ከሦስት ወር በሗላ ከፍትሕ ሚ/ር እና ከአደጋ መከላከል ጠይቅ የሚል መልስ ነዉ የተሰጠኝ።
በፖሊስ በኩልስ? ብርሃነ፦ ፖሊስ እና ፍትሕ ብንጠይቃቸዉ አቃቤ ሕግ የዉጭ ዜጋ ለመያዝ ማን ፈቀደላችሁ? ብሎ የከ’ሰናል! ስለዚህ ዓቃቤ ህግ የጻፈልን እናጠራለን ብለዉኝ ነበር። ፌደራል ፖሊስ በተደጋጋሚ አቤቱታ አቅርቤ ለፍትሕ ሚ/ር ደብዳቤ ጻፈልኝ። ይሄ ድርጅት በመንግሥት ተመዝግቧል ወይስ አልተመዘገበም? ባስቸኳይ መልስ ስጡን ብሎ ጻፈ። ደብዳቤዉን አላየሁትም፡እንደዚያ የሚል ደብዳቤ ተጽፏል አሉኝ። ፍትሕ ሚ/ር አቶ መስፍን ጋር ሂድ አሉኝ።
መስፍን ግርማ የፍትሕ ሚ/ር የነበሩት? ብረሃነ፦ አሳቸዉ ጋር ስቀርብ አቶ መስፍን <<ይሄ ድርጅት የዉጭ ዜጎች ስለሆኑ በዉጭ ስለሚያስጠይቀን ልንጠይቃቸዉ አንችልም ።>> ሲሉ መለስሉኝ።
ከዚያ በሗላ አልጠየቅክም? ብርሃነ፦ ከዚያ በሗላ ተስፋ ቆረጥኩ። ልጠይቅም አልችልም።ብጠይቅም ተሰፋ አልነበረኝም። ሁሉንም ቦታ አቤት ብያለሁ።ከዚያ ወዲያ የት አቤት ልበል? አሁን አንተን የሚረዳህ ማን ነዉ? ብርሃነ፦ እንዲሁ የአዉቁኝ አንዳንድ በሁኔታየ ያዘኑልኝ፤የሆዴን የሚያዉቁ ሰዎች በይበልጥ የአዲስ አበባ ዶክተሮች ይረዱኝ ነበር። በ አብዛኛዉ ደግሞ አንድ ዶክተር የተባበሩኝ ነበር። ለቤት ክራይም ይከፍሉልኝ ነበር። እሳቸዉ ከዚህ ከተቀየሩ በሗላ ግን በሕክምናዉም፤በመድሃኒቱም በጣም ጨልሞብኛል።
ተከራይተህ ነዉ የምትኖረዉ? ብርሃነ፦ ተከራይቼ ነዉ።ከፈረምኩ በሗላ ከነበርኩበት አካባቢ እየመጡ አላስቀምጥ አሉኝ። እየደወሉ እቤት እየመጡ ብርሃነ አለ ወይ እያሉ ሲያሰቸግሩኝ የግድ ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ። አሁን የት ነዉ ያለኸዉ? ብርሃነ፦ እየከፈልኩ ወይንም ከማቃቸዉ ሰዎች ካገኘሁ ከነሱ ዘንድ አድራለሁ።
እንጂ ቋሚ ቤት የለህማ? ብረሃነ፦ ቃሚ ቦታ የለኝም። አሁን ወላጅ እናትህ ዓድዋ ናቸዉ? ብርሃነ፦ ጥቁር አምበሳ ሆስፒታል እያለሁ ነች ከዚህ ዓለም ተለየችኝ። እህት እና ወንድሞችህስ? ብርሃነ፦ በዚህ የተነሳ የት እንዳለ እንኳ አላዉቅም። ሸራሮ አሉ ይባላል፡ ማን ወደ እዛ እንደወሰዳቸዉ አላቅም።
እንደምትነግረን ሥር የሰደደ በደል ደርሶብሃል። በደሉም ማብቂያ አጥቷል። እንደምናየዉ በሰዉነትህ ላይ ያለዉ ቁስል እጅግ እጅግ ያሰቅቃል። ሽታዉም አንዲሁ። አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወይም መንግሥት ምን እንዲያደርግልህ ነዉ ምትፈልገዉ? ብረሃነ፦ እካሁን የቆየሁት በኢትዮጵያ ህዝብ እና በኢትዮጵያ ዶክተሮች ድጋፍ ነዉ። ለ9 (ዘጠኝ) ዓመት ላቆየኝ ለሰፊዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ምስጋና አቀርባለሁ። አሁንም ቢሆን ሰፊዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግሥት እና በዉጭ ድርጅቶች የደረሰብኝን ግፍ ግምት ዉስጥ አስገብቶ ችግሬን እንዲከታተልልኝ እፈልጋለሁ።
በሁለተኛ ደረጃም፤ በዘህ እሸት የወጣትነት ዘመኔ ካለሁበት አሠቃቂ ስቃይ እና አስከፊ በሽታ እንድላቀቅ ይረዳኝ ዘንድ በተቻለ መጠን እዲተባበረኝ በትህትና እጠይቃለሁ። ዋናዉ በሽታህ ያለዉ እግርህ ላይ የሚታየዉ ነዉ? ወይስ ሌላ ነዉ? ብርሃነ፡_ ከ አንጀቴ ደም እና መግል ያለማቋረጥ ሆዴ ዉስጥ እየፈሰሰ ነዉ። (ቁስሉን እያሳየ) ይሄ በገሃድ ሚታይ እና በባለሞተኞችም የተረጋገጠ ነዉ። ካሉት በታች፤ከሞቱት በላይ ሆኜ ሕይወቴ በቋፍ ላይ ነች። 24 ሰዓት በስቃይ በችግር እተጠበስኩ (በምሬት እያለቀሰ) ነዉ ያለሁት።//-/ አመሰግናለሁ አቶ ብረሃነ። ማሳሰቢያ ከላይ የቀረበዉ ቃለ መጠይቅ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን በመጽሄታቸዉ አትመዉ ለታሪክ ማሕደር የተዉልንን የኢትኦጵ መጽሄት አዘጋጆች ከፍተኛ ምስጋናየን አቀርባለሁ። “የትግራይ ነፃ አዉጪ ድርጅት መሪዎች” በትግራይ ዲያቆናት እና ካህናት እንዲሁም ወጣቶች ላይ በስብእናቸዉ ያደረሷቸዉ የመብት ረገጣ ወንጀሎች ሳይጠየቁበት ዓይናቸዉን በጨዉ አጥበዉ ዛሬም በዉሸት ዓለም “ኑ!” እናሞኛችሁ ሲሉን፤ የትግራይ ህዝብ ዕምባ ከጉዳይ ሳይቆጥሩ ከነኚህ እርኩሶች ጋር እንተሻሽ የሚሉንን ዉጭ አገር የሚኖሩ በተቃዋሚነት ስም የሚፎልሉትን “የፖለቲካ ነጋዴዎች እና ግብዞችን” በድፈረት “የፖለቲካ ሽርሙጥናቸዉን” እንዲያቆሙ መጠቆም የዜጎች ሃለፊነት መሆኑን ከወዲሁ አደራ እላለሁ። የዜጎች ደም፤ እምባ፤ኡ ኡ ታ ዛሬም ከምድር በታች እና ከምድር በላይ ይጮሃል።ፍትህ ማግኘት ይኖርበታል። ፍትሕ ጠየቃችሁ ብለዉ የሚጠሉን ካሉ፤እኛን ሳይሆን የጠሉት ፍትሕን ነዉ። ጌታቸዉ ረዳ ሳንሆዘ ካሊፎርኒያ www.Ethiopiansemay.blogspot.com

No comments: