በጀግኖቻችን አንገት ላይ የሚገባ ገመድ ሲፈትሉ ዝምታን
የመረጥን ህዘቦች መሰደድና ሞት ሲያንሰን ነዉ!
ጌታቸዉ ረዳ
የቁም ሞት ሞታችንን የማየት እና የማሳየት እሽቀድምድሙ እየበዛ በሄደ ቁጥር ገዳዮቻችንን አፍ’ጠን የምንከላከልባቸዉ ዓይኖቻችን በሰሜኖቹ ባንዳዎች ላይ የማትኮሩን ስራ ቀርቶ፤ አብረዉን እየተጓዙ የቁም ሞታቸዉን እየሞቱ እኛን መስለዉ እኛኑንና ጀግኖቻችንን የሚገድሉብን እነየቶቹ መሆናቸዉን ስናቅ አንጀት ያቀጥላል። አክ እንትፍ ብለዉ አያጠፉት ነገር፡ እጅግ የጨነቀ ነገር!
ታላቅ ሕዝብ እና ታላቅ አገር ተብሎ ስነቴና ስነቴ ተነገረ። ያዉም ለሺዎቹ ዘመናት። ታላቅነቱ ያስመሰከረ፤ ማንነቱን ያልስረከበ ያ ታላቅ ህዝብ አስከ ትናንት ነበር። ታለቅነቱን ለዉሾች አስረክበን ታላቅ አገር፤ ታላቅ ሕዝብ ሊያስ’ሰኙን ያስቻሉ ነባር አሴቶቻችን እንደ ዛፍ ቆርጠን፤ቆርጠን ግንድ ቅጠሎቻቸዉና ስሮቻቸዉ ሳይቀሩ በጥስን፤ነቅለን ከጣልናቸዉ ይኸዉ የሰዉ ዕደሜ አስቆጠርን።
የኢትዮጵያ ህጻናት በአዲስ መጤ የሃይማኖት ሰባኪዎች የአዲስ ዙር የቅኝ አገዛዝ የፈረንጅ ሰለባዎች ሆነዉ ህጻናቶቻችን ለእርዳታ ሲጮሁ ያዉና ዉርደታችን በቀኝ በኩል በዚህ የህዋ ሰሌዳ ተለጥፎ የምታዩት ቪድዮ ሕያዉ ምስክር ነዉ። ማነህ አንተ ድምበር ጥሰህ መጣህ!? ብሎ የሚል የግዙፋኑ ድምጽ ከየት ይምጣ? ልቅሶዉን ሁሉ ለህጻናቶቹ አስረክበን ይሄዉ አረፍነዉ።ሁኔታችን ሁሉ ልቅሶ ብቻ። አልቅሶ ላይመልሱት ነገር።
ሰማይን የሚያክል ከባዱ ሸክም ሲሸከሙልን የነበሩት አሴቶቻችን ለመሆኑ አንዴትና በእነማንሰ ተባበሪነት አንደተወገዱ እናዉቃለን? በነባር አሴቶቻችን እግር አዳዲስ እሴቶች ብቅ ባሉ ቁጥር በመርዘኛዉ ቅናታችን እየኮረኮምን እንደተቃጠለ ኮከብ ቦግ እያሉ እንዲሰወሩብን አደረግን። የትላልቁን ድምጽ ባፈንን ቁጥር ታላቅነታችን ወርዶ በማንም አላፊ እና አግዳሚ የሚደፈር አንገቱ የደፋ ጊላ/ባርያ ሆነናል። በማንም የሚደፈር ዜጋ ደግሞ ያገር ትረጉም ስለሚያጣ ፤ አገሩን ለደፋሮች አስረክቦ፤ እንጀራ ፍለጋ ሩቅ ተጉዞ የሰዉ ጥራጊ የመሆኑን ኑሩ በመሻት እሱም በፋንታዉ ብቅ ያሉትን የመኮርኮሙን ባህል ይዞ እየቀጠለ ይታያል።
ከላይ ጎልተዉ የሚታዩት ፎቶግራፎች ኢትዮጵያ በስንት ምጥ አምጣ ከወለደቻቸዉ ጥቂት ከታላላቆቹ የኢትዮጵያ ድምጸች አንዱ ብሁራዊ ጀግናችን የ120.000 የምመህራን መሪዉ ፤ ሊቁና የፍትሕ ተማጓቹ ደ/ር ታየ ወልደሰማእት ነዉ።
ታየ ብሔራዊ መዘክራችን ነዉ።ታየ የኢትዮጵያ ገድል ታሪክ ነዉ። ታየነቱን የኢትዮጵያዊነት ታሪክ ለመሆን በጨለማዉ ጉዞ በድፍረት ለማንም ሳያጎነብስ በክብርና በኩራት እንደ ጧፍ በርቶ አብረቶልን የተጓዘ ጀግና ነዉ። ታዩ፡ወያኔን ያለ ጠመንጃ በተማጓች ድምጹ ብቻ ያስጎነበሰ፤ያስደነበረና ያስጨነቀ ከትላልቆቹ ዛፎቻችን በህይወት የሚወዛወዝ ረዥሙ ዛፈችን ነዉ። ዛፍ! ያዉም ስጋ የለበሰ ትልቁ ዛፍ!
ይሄን ዘፍ ለመቁረጥ፤ ብዙ ተመኮረ። ያዉም ከመሃላችን እዚሁ በዉጭ በስደቱ ዓለም። እኛኑን መስለዉ፤ እኛነታችን የመገዙን! ዛሬ ታየ በሕይወት እንደሌለ ለማስመሰል ሚዲያዎቻቸዉ በመጋዦች ተርመስምሷል። ታየ በግምባር ቀደም ሰልፉን መርቶ በሺዎቹ እንዳላታገለ፤ የከፈለዉ መስዋዕት የእያንዳንዳችን የጉራ ቁምጣ ሱሪዎቻችን እንዳላስነቀ ሁሉ፤ መስዋዕትነቱን ሁሉ ዉሃ በጠማዉ ምድረበዳ መሬት ላይ በከንቱ ተረጭቶ እንዲደርቅ በዚህ ሁለት እና አንድ ዓመት ዉስጥ እንደተሞከረ የምታዉቁት ጉዳይ ነዉ።
ያልታደለዉ ህዝብ ታየን ያክል ትልቁን ሰዉ ለማሳጣት ስንሯሯጥ የሞራል ድጥ ሰርተን ስንንከባለል ጀግናዉን ስናሳዝን ፤ስናስቆጣ ታይተናል። የትግራይ ባንዳዎች ባዘጋጁለት የጨለማ እሰር ብቻዉን ዘግተዉበት መከራዉን አይቶ ፤ ዓለም እሪ ብሎ ባእዳን ሁሉ ያደነቁትና የጮሁለት ጀግና፤ከእስር ሲለቀቀቅ ዓለም በተጠንቀቅ ቆሞ፤ መላ ያበሻ ህዝብ ምድሪቱ ሰንደቃለማዋን እያዉለበለበች የተቀበለችዉን በሕይወት ያለ ጀግናዋን፡ ትንሽ ሰዉ ለማድረግ የሞከሩትን ትከሻ ለትክሻ ገጥመዉ ከባንዳዎች ጋር እየተሻሹና እየተሳሳቁ ዉስኪ ሲራጩና ሲጨልጡ አስራ ምናምኑ ዓመታት ወያኔን በንግድ በዲፕሎማቲክ ኮሩና በሕጉ ዘርፍ፤ የጎሳ የደም፤ የቋንቋ በናዚ ፍልስፍና ህዝበን የሚሰብኩ ትምርቶቻቸዉን ሲጽፉና ሲያሰራጩ፤ በከንቲባነት እና ባማካሪነት ለባንዳዎቹ ለነ መለስ እና ለነ ገብሩ አስራት መንግሥት ደፋ ቃና ሲሉለት የዘመኑትና የከረሙት እነ ብርሃኑ ነጋ፤እነ አንዳርጋቸዉ ጽጌ፤ብርሃኑ መዋ፤ወርቅየ ብርየ፤ጋዜጠኞቻቸዉ እነ ዳዊት ከበደ እና ክንፉ አሰፋ የመሳሰሉት በመምህራኑ መሪ በታየ ላይ ብዙ ዘለፋዎችና አስጸያፊ ዉረፋዎች በመከመር ጀግናዉን ለማሳነስ እና ከመድረክ ለማሰወገድ ያልጣሩት ያልቆፈሩት ድንጋይ አልነበረም። ከናንተዉ ጋር ነን ብለዉ እንደ ጆፊ አኮብክበዉ አለ ሃፍረትና ርህራሄ ሲቦጭቁትና ሲከቡት አብዛኛዎቻችን ተመልካቾች ነበርን። አሳዛኙ ገበናችን ጀግናን ስናስቆጣ እና ስናሳዝን አስከመቸ አንዲህ ሊቀጥል እንደሚችል ሁላችን መፈተሽ የሚገባን ጉዳይ ይመስለኛል?
አሜሪካኖች…..ይላሉ የጦቢያዉ ጸሃፊ ጸጋየ ገብረ መድህን አርአያ “አሮጌ እሴቶች እና አዳዲስ ሃሳቦችን” ሲያወሱ ከብሄራዊ አክብሮት ጋር ነዉ። “አባቶቻችን” ይላሉ፡ “ጀግኖች ወላጆቻችን ይላሉ”። ከትንሿ ዘመን- ለአጭርዋ የህልዉና ታሪካቸዉ ዘመን ከፍተኛ አስተያየት አላቸዉ። በዚሁ በአጭርዋ ዘመን ታሪካቸዉ እንዲህ ሲኮሩና ሲያጌጡባት፤አንደ እሳት ሲሞቁባት፤እንደ ሻማ ሲቀልጡባት ባሕላዊ እሴቶችን ሲፈጥሩ በአዳዲስ እና ገንቢ እሳቤ ሲያበለጽጉት ሰባት ሺህና ከዚያም በላይ ዕድሜ ያለዉ ታሪክና አገር ያለን ወገኖች ስናፍርበት ስንረግጠዉና በዉሻ ፊት ስንወረዉረዉ እንገኛለን።
በፋሺስቶች ዘመን የነበረዉን የኢትየጵያዊንን ተጋድሎ ከመስማት እና አልፎ አልፎም ከማንበብ በቀር ሁኔታዉን በዓይኔ ለማየት አልታደልሁም። ነፍስ ማወቅ እንደጀመርሁ ግን ( ---------ነዉ- የተወለድሁት) አጎቶቼና ያክስቶቼ ልጆች፤ ጎረቤቶቻችንና አንዳንድ የመንደራችን ሰዎች ጠመንጃቸዉን ከጎናቸዉ፤ ጥይት የሞላበት ዝናራቸዉን ከወገባቸዉ ሳይለዩ በየቀኑ በኩራት በመሃላችን ሲንጎራደዱ ከእነሱ የበለጠ ሰዉ አለ ብየ ገምቼ አላዉቅም። አንድ ቀን እንደነሱ ጠመንጃ ተሸክሜ፤ዝናር ሙሉ ጥይት ኖሮኝ ለወዳጅ ኩራት፤ለጠላት ሥጋት ሆኜ መኖር እመኝ ነበር።” ይላሉ ጸሃፊዉ።
ጸሃፊዉ እንዳሉት እወነትም በዚች አገር ጎልያዶች ነበሩ። በዳዊት ጠጠር የሚሸነፉ ዓይነት ጎልያዶች ሳይሆኑ በእርግጥ ሰማዩን ሁሉ የሚሸከሙልን የሚመስሉ የታለቅነት መለያዎች ነበሩን። “ብዙዎቹ አይቻቸዋለሁ” ይላሉ አቶ ጸጋየ ገብረመድህን ይህንኑን ሲያረጋግጡ፡ “ብዙዎቹ አይቻቸዋለሁ። እምብዛም ሳልቆይ እና ይልቁንም ወደዚህ አዲስ አበባ ወደ ሚሉት ባቢሎን ስመጣ ድንክየዎች (pigmies) አያለሁ ብየ አላስብኩም፤አልሜም አላዉቅም ነበር። ይሄ አስቆዝሞኛል።
ርዕሱን ረሳሁት እንጂ በማስተወቂያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ክፍል ባለዉ መጻሕፈት ቤት የሚገኝ መጽሐፍ ስለ ቴዎድሮስ ያወሳል። የመጻሕፍት ቤቱ ሠራተኛ ወደዚያ ብቅ ስል መጽሓፉን ከፍቶ ይጠብቀኛል። “አጤ ቴዎድሮስ አገሬ ገነት ናት። የሚኖሩባት አህዮች ሆኑ እንጂ አሉኝ” ይላል ደራሲዉ። ለንዴት የጣፏቸዉ መይሳዉ ካሳን አይወቅሱም። በሕዝብ ድፍረት አይከሰሱም። ባይሆን እህያ ወይም ሰዉ መሆናችንን ማጣራት ያለብን እያንዳንዳችን ነን። እንደትናቱ ዛሬም ታዲያ በየዘመኑ ከመሃከላችን ለሚነሱ አድባር አዉራዎች ደንቃራ አይደለንም ያሰኛል?። እንዴት ብሄራዊ ህልም እንጣ?” ሲሉ ጭነቀታቸዉን በጥያቄ የወረወሩልነን ዓመታቱ ልብ በሉት። በጣም ረዥም ጊዞ ሆኗል።ዛሬም ያዉ ነን። አልተለወጥንም።
እንዲህ ያለ ረቂቅ ድምጽ መስጠት ስለማንችል፤ ጀግኖቻችን በሌቦች በዋሾችና በዉሾች ሲነከሱ አልተከላከልንላቸዉም። ጋዜጦች፤ራዲዮኖችና ቴሌቪዥኖች ታየ አንዳያስተምርበት እና እንዳይቀሰቅስበት መድረኮቻቸዉን ለታየ አግደዉ፤ ለግብር ይዉጣ ብለዉ የ120 ሺህ ምመህራን መሪዉን በጨለማ ላሰረዉ ለስርአቱ መስራች ገብሩ አስራትን አስከ ትግራይ ድረስ በስልክ እያፈላለጉና አስካለንበት ዓለም ድረስ እያስመጡ እየረገጠን ንቆን እንዲሄድ አዲስ ጀግና ሊፈጥሩብን የሚሞክሩትን ዲስኩረኞቹ ያዲስ ድምጽ ራዲዮ አዘጋጆቹ እነ አበበ በለዉንና ምንትስ ምንትሴዎቹ ሁሉ ጠዉልገዉ የነበሩትን ኮትኩተዉ ዉሃ እያጠጡ እያበቀሉብን ያሉት እሾህ ችግኞቻቸዉን እንዳይወጋን ካሁኑ በንቃት ተከታተሉት።
ከትናነት በስትያ ጸጋየ ደብተራዉና ጓደቹ አንቀዉ ሲወስዱብን፤ ዝም አልን።ቀጥሎ አሰፋንና በህታዊዉ ፈቀደ ስላሴን በጠራራ ብርሃን በጥይት ሲነጥቁብን ዝም አልን። ትናንት የደቡቡ ጀግና ህዝብ የመረጠዉ ፊታዉራሪ መኮንን ዶሪንና የባህረ ነጋሹ ኢትዮጵያዊዉ ጀግና አበራ የማነ አብን ሲነጠቁብን ዝም አልን። ኢንጂኔሩ አረጋዊዉ የእልፋ እላፍ ሕዝበ መሪዉ ሃይሉ ሻዉል ተምሞብን ሲታከም “አልታመም- አምሮበት ነዉ” ሲሉን፤ ዝም አልን። ዛሬም በተቀሩት ጀግኖቻችን አንገት ላይ የሚገባ ገመድ ሲፈትሉባቸዉ እያየን ስንቶቹን ጀግኖቻችን በዝምታ አናስነጥቅ?
ጌታቸዉ ረዳ
መስከረም 2001
No comments:
Post a Comment