ወንጀልን ቸል ማለት ገዳዮችን ተቀበሎ ማክበር!
ኢትዮጵያዊያኖች እና አማራዎች በአዲሱ ፋኖ ውስጥ እንዴት ሊጣጣሙ ነው?
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)
1/24/26
ሰላም እና አንደነት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይከሰት ከ50 አመት በላይ ዕንቅፋት እየሆነ ያለው ምክንያት እሰኪሰለቸኝ ድረስ ደጋግሜ የገለጽኩት ጉዳይ ሕዝቡ የተፈጸመበትን ወንጀል «ቸል የማለትና የመርሳት» ፥ «ወንጀል የፈጸሙበትንም የታጣቂ አማጺያን መሪዎች እና በመንግሥትነት የተቀመጡ ወረበላ መሪዎች መሪ አድርጎ መቀበል» ትኩረት ያልተደረገባቸው ዋና የመከራችን ምንጮች-ናቸው።
ይህንን ለማስቆም- ጫካ ውስጥ ያሉ ታጣቂዎችም ሆኑ በመንግሥት ሥልጣን የተቀመጡ ቡደኖችን የሚፈጽሙዋቸው ሰብአዊ ጥሰት በቀጣይነት ማጋለጥና መቃወም ፤ ያንን አከታትሎ «በምትካቸው የዜጎችን ክብር አክባሪዎች እንዲተኩ በአመጽም ይሁን በተገኘው ሕዝባዊ ጎርፍ ማስገደድ መልመድ አለብን።
አለዚያማ እንዲህ ካላደረግን ወንጀል ፈጻሚዎቹ እኛን ለመግዛት ሽኩቻ ውስጥ ገብተው ሲታኮሱ ሃገራችን የመኖር ዕድለዋ ገደል ውስጥ ትገባና ምድሪቱ የወንጀለኞች መታኮሻ ሜዳ ሆና እሰከዘላለሙ መቀጠልዋ ነው።
በሉአላዊነታችን እና በሕይወታችን ሕልውና ላይ የተፈጸሙብን ወንጀሎችን ቸል በማለት ወንጀለኞችን የሕልውናችን መድሕኖች አድረገን የማቆለጳጰስ ባሕሪ በኤርትራ፥በትግራይ (ወያኔዎችን ሙጥኝ ብሎ ማምለክ) ፥በኦሮሞ (ኦነጎችን) በመንግስት ደረጃ የተቀምመጠውን አፓርታይዳዊው የአብይ አሕመድ ሥርዓት (በተለያዩ ኢትዮጵያዊያን ማሕበርሰብ አባላት የማቆለጳጳስ ባሕሪ ፥ አሁን ደግሞ በዲያስፖራ የአማራ ማሕበረሰብ ፋኖ ነፃ ያወጣናል ብለው ከነ ወንጅላቸው ጭምር ‘’የፋኖ መሪዎችን የማቆለጳጰስ’ ቀጣይነት ባሕሪ እያየን ነው። ይህ ባሕሪ ከአዙሪቱ መወጣት እንዳልቻልን መአመላካች ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ ትኩረቴ በፋኖዎቹ ላይ ነው።ሰለዚህም እንሂድበት። እነዚህ በወንጀል ድርጊት የተነከሩ የራሳቸውን ታጣቂ ወገን የሚገድሉና የሚገዳደሉ፤ ደም የጠማቸው ፥ ሞራል የጎደላቸው የፋኖ መሪዎችን የማጀገንና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመሪነት እንዲቀጥሉ በተባባሪነት እና በቁሞ ተመልካችነት ዋናዎቹ ተጠያቂዎች «ዲያስፖራ ያሉ ደጋፊ ምሁራን እና በሚዲያ የተሰለፉ ክፍሎች» ናቸው።
በሚገርም ሁኔታ ብዙዎቻችን ተስፋ ጥለንበት የነበረው ይህ ፋኖ የተባለው ታጣቂ ቡድን ያልጠበቅነው ወንጀል በመፈጸም ፥ አልፎም የአክራሪ ብሔረተኛ ባሕሪ በመከተልና ይፋ የሆነ የሻዕቢያ እና የወያኔ ጠበቃነታቸውን ሳይደብቁ ፥ ሳይሸማቀቁ በዜና ማሰራጫ ጣቢያዎች ለሕዝብ በማሳወቃቸው ትኩረታችን በአፓርታይድ ገዢው መንግሥት ላይ እናንዳናደርግ ተጨማሪ መስሕብ ሆነውብናል።
በሚገርም ሁኔታ አማራ እራሱን ለመከላከል ታጣቂ ሃይል መመስረት እንዳለበት ስወተውት እንደነበር አንዳንዶቻችሁ ታውቃላችሁ። ከተመሰረተ በኋላም ተስፋ ጥለንበት ወር ሳይቆይ «በጨካኝነቱ የሚኮራና ጨካኝነቱንም በራሱ የነገረን ዘመነ ካሴ እና «ጀምረናቸዋል እንጨርሳቸዋለን» እያለ የገዛ ወገኖቹን ለመጨፈጨፍ የሚዝት የብዙ መመሕራን እና ተማሪዎች ግድያ ተጠያቂ የሆነው፤ አስረስ ማረ የተባለው ምክትሉ ፤ ካለ የራሳቸው ታጣቂ ፋኖ ጎጃም ውስጥ ሌላ ታጣቂ መኖር የለበትም ብለው «ኮሎኔል መኳንንት» የተባለውን ወታደራዊ ማዕረጉንና ምቾቱን ጥሎ ለአማራ ሕዝብ ሕልውና ጫካ የገባ የጎጃም ወጣትና ተከታዮቹን እያዋከቡ አስከብበው በአብይ አሕመድ ጅቦች ተይዞ እንዲበላ አደርጉ።
በትግራዋይነቴ ትግራይ ውሰጥ መላው ዕድሜየን ያየሁትንና የተቃወምኩትን የፋሺስቶች ውልደት የሆነው የወያኔ ድርጊት እዚህ በፋኖ አመራሮችም አዲስ የፋሺስት ዕርግዝና እንደተጸነሰ ምልክት ሰጠኝ።
ከዚያ ቀን ጀምሮ የቀጠለባቸው እጅግ አስደንጋጭ እርምጃዎች እና ንግግሮች ስታዘብ ፋኖ የአማራ መዳኛ ሳይሆን የሥልጣን ጥም ያሳበዳቸው ራስን የመቆለል በሽታ ("Bizarre egocentricity) የተጠናወታቸው የወንጀለኞች ጥርቅም
criminal-insurgents እነደሆኑ በይፋ ማየት ቻልኩ። እየሆነ ያለው እና የወጡበት አጀንዳ አብሮ ስላልሄደ በመደናገጥ እና በመገረም የብዙ ሰዎች ትኩረት ከአፓርታይዱ መንግሥት ወደ እዚሁ አዲሱ የፋሺስት ጽንስ ሆነ።
የሆነ ያለው የጎረቤቶቹ ቅጅ ነው። ከ60ዎቹ መግቢያ ጀምሮ በኤርትራ ፣ በትግራይ፣ በኦሮሞ እና ሶማሊ ነፃ አውጪ አሁን ደግሞ የፋኖ ታጣቂዎች፤የመኖር የሕልውና ትግል እንካሂዳለን እያሉ የፖለቲካ አማጽያን ካባ በመልበስ ፓለቲካ እና ወንጀል በመንታነት በማዋሃድ የወንጀለኛ-አማፂነት
criminal-insurgents ባሕሪ ተላብሰው ብዙ ወንጀሎችን ፈጽመዋል። ፋኖውቹ እየተከተሉት ያለው መንገድም ከነዚያዎቹ ከ60ዎቹ ነጻ አወጪ አማጽያን የተቀዳ ባሕሪ ነው።
ሠለጠንን ባልንበት ዘመን ፣ አማራን ከግድያና ከመሰደድ ነጻ እናወጣለን ብለው መሃላ ገብተው ሲያበቁ በቅጽበት ወደ አራዊት ባሕሪ ተለውጠው «አማራ አማራውንን» በመግደል የተጀመረው ወንጀላቸው ተሻግሮ ሬሳ እንዳይቀበር፤የ5ኛ ከፍል ያለጨረሱ ተማሪዎች ያውም ጆሮዋ የማይሰማ ታዳጊ ወጣትና አብረዋት ለስለላ ተልከዋል የተባሉ ልጃገረዶች (በገልለተኛ አጣሪ እና ገለልተኛ ጋዜጠኛ ሳይጣራው በገፍ ረሸነው ጨፈጨፏቸው!!!!
ማንነቱ እንዳይታይ እራሱን ከካሜራ ደብቆ ሲመረምራቸው የነበርው የፋኖ መርማሪ ሰላዮች ተብለው የተረሸኑት የልጆቹ የዕድሜ ጨቅላነት (ቲን ኤጅ ብለን እዚህ እንደምንጠራቸው ናቸው) ።አንደኛዋ በምን ጆሮዋ ሰምታ በሰላየነት እንደተሰማራች ግራ የሚገባ የክስ ታሪክ ነው። የሆኖ ሆኖ ይህ ጭካኔ << Master of Death>> የሚል የናዚዎች የወንጀል መጽሐፍ ካነበብኩት ጋር የነዚህ የፋኖ ሰዎች ጆሮዋን መስማተ የማትችልን ታዳጊ ለጃገረድ የመረሸናቸውን ጨካኝነት ባንድመጽሐፍ ያነበብኩት የናዚዎች ጭካኔ አስታወሰኝ፦
እንዲህ ይላል መጽሐፉ፡ ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የተረጎምኩት ትርጉም
ሰባት የሲኦል መመሪያዎች
<<እንኳን አዋቂ ቀርቶ አንቀልባ ታዝሎ እንቅልፍ
ውስጥ ያለው ህጻን እንደ “መርዛማ እንቁራሪት” መረገጥ አለበት… እየኖርን ያለነው በብረት መጥረጊያ መጥረግ አስፈላጊ በሆነበት
በብረት ዘመን ውስጥ ነው።>> (ሄንሪክ ሂምለር፣ ሴፕቴምበር 1941) ይላል፤ ከአዶልፍ ሂትለር ቀጥሎ ሁለተኛ ሰው የነበረ
አይሁዶችን ያስፈጅ እጅግ ጨካኝ ሰው።
ህጻናትን የመረሸን የፋኖ ጨካኝነት አንዱ «የወያኔ ገበና
ማሕደር በሚል በራሴው መጽሐፍ ውስጥ የታተመው ተመሳሳይ ታሪክ ላሳያችሁ፦
ዕለት 20 በሕዳር 1969 በወያኔ ታጣቂዎች ከአቶቡስ ታፍነው ወደ ጫካ ከተወሰዱት
መካከል (አቶ ገዛኢ ረዳ) እንዲሁም ለሽምግልና ወደ ወያነ ከተላኩ ታዋቂ የሃገር ሽማግሌዎች ውስጥ በእሳት እየተቃጠሉ ከተመረመሩት
እና ከተረሸኑት መካከል ውስጥ የራሴ ቤተሰቦቼን) ያካተተ: - አቶ ገዛኢን ሳር እና እንጨት አቀጣጥሎ ሰውነታቸውን እየለበለበ የመረመራቸው
የወያኔው አመራር አባልና በትግሬዎች መንግሥት የወያኔ የአየር ሃይል ዋና አዛዠ የነበረው እዚህ እኛ ጋር ያለው አበበ ተ/ሃይማኖት
(ጆቢ) እዚሁ ባለሁበት ሳናግራቸው የነገሩኝ ሰለ ያንድ 10 አመቱ ሕጻን ልጅ ታሪክ እንዲህ ይላሉ.
«........ ከዓድዋ ሰለኽለኻ ወደ ተባለች ትንሽ ከተማ እህቱን ለመጎብኘት መጥቶ የነበረ
አንድ “እገረ-ተክል” (ታዳጊ ልጅ) ይዘውት አብሮን ነበር።
“አንተ ደግሞ እዚህ የመጣኸው ከምንጠጣበት ወንዝ መርዝ
ልትጨምር ነበር የመጣኸው? ሰላይ ነህ! ብለው፤ እሱንም በእሳት ለብልበው ገርፈው አሰቃይተው እንድንምርህ ከፈለግህ “አዎ” ማለት
አለብህ ብለውት “አዎ” አምናለሁ ብሎ ባልዋለበትና ምን እያሉት እንደነበር ባለገባው ነገር ፤ አሳምነው እንዲሁም አክስቱን ለመጠየቅ
ወደ ሰለኽለኻ አብሮት ከዓድዋ ወደ ሰለኽለኻ የመጣው “ብርሃነ መስቀል ጎሽም” እንዲሁም “መሓመድ” የተባለው ወጣት ልጅ በአንድነት
በአንድ ቀን ሁሉንም ወስደው ረሸኗቸው። እግዚኦ መሐረነ ክርሰቶስ! ነው ያልነው።
“ራበኝ ወደ አብሻይ (ወደ እናቴ) ውሰዱኝ እያሉ የሚያለቅሱ
ህጻናት ምንም፣ የማውቁ ህጻናት ወስደው ሲረሽንዋቸው የክርስቶስ የመምጫው ሰዓት መቃረቡን ነው የተረዳነው» አሉ።
ታዳጊ ህጻናትን በሰላይነት መረሸን በወያኔ የተጀመረው አሁን
ደግሞ በጎጃም ብዘመነ የጎጃም ፋኖ አመራር የጭካኔ ጥግ ስንመለከት ‘’የመስማት ችግር ያለባት ታዳጊ ልጅ እግር” እና 3 አብሯት
በሰላይነት የተያዙት ለጃገረዶችን መረሸን ፋኖ በመመራት ላይ ያሉት የዚህ ቡድን አምራሮች ለአማራ ብቻ ሳይሆን ለሃገራችን አደጋ
ናቸው። ይህንን እንዴይ ቸል ተብሎ የአማራ ሕልውና ጠባቂዎች ናቸው ብላችሁ በምን ሂሳብ ነው የምታቆለጳጵስዋችው? የሚል ጥያቄ አለኝ።
ከዚያም አልፈው “በሥራችን ካልተገዙ እንዳይኖሩ ሁሉንም
እንጨርሳቸዋለን” እያሉ ያለ ምንም ሰቀቀን በሚዲያ ለሕዝብ ወጥተው “የጭፍጨፋ-ወንጀል” እንደሚፈጽሙ በኩራት ድምጽ በመደንፋት መገዳደል
መጀመራቸው የምታውቁት ነው። የሞቱት ማን ይካሳቸው? ገዳዮቹስ ማን የጠይቃቸው? የሰው ልጅ ደም፤ ደመ-ክልብ ለምን ይሁን?
ያንን ላስታውሳችሁ እነሆ- አብርሃ ማንጁስ ይባላል፡ መቀሌ ከተማ በሓምሌ 2010 (ኦገስት መጀመሪያ በፈረንጆች 2017) በተካሄደው የወያኔ ተቃዋሚም ደጋፊም የሆኑ በመላ ዓለም የሚገኙ ትግሬዎች የተገኙበት ስብሰባ ከዴንማርክ ወደ ትግራይ ሄዶ እነ አረጋዊ በርሔ እና ቱባ የወያኔ መሪዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ የተናገረው በዚህ ትችት እንደ ርዕስ ለመነሻ የተጠቀምኩበት የአብርሃ ማንጁስ ንግግር ልጥቀስ እና ወደ ትንታኔ እንገባለን፦
“አብርሃ ማንጁስ እባላለሁ። የመጣሁት ከዴንማርክ ነው። ህወሓት ማለት አንዳንድ ሰዎች ትርጉም ላይ ይሳሳታሉ። ህወሓት ማለት የትግራይ ሕዝብ ድምር ማለት ነው።የትግራይ ሕዝብ ሠራዊት ማለት ነው። አረጋዊ በርሔ በህወሓት ውስጥ ጀግንነት “ኢንስቲቱሽናላይዝ” እንዲሆን ያደረገ ጀግና ታጋይ ነው። አረጋዊ በርሔ በግሌ የሰራው ስራ አለወይ? ከትግራይ መሳፍንት ተብለው በፊውዳልነት ተወንጅለው የታሰሩት የቆሰሉት እና የተገደሉት ውስጥ አንዱ የኔ ወላጅ አባት ነው። ይህ ወንጀል የፈጸመው ደግሞ አረገዊ በርሔ ሲመራው የነበረው ወታደራዊ ክንፍ የተፈጸመ ነው። ሆኖም እንደ አንድ “ፌየር-ትግሬ/ አንደ አንድ fair Tigrayan” አረጋዊ ማለት ለኔ በትግራይ ተጋይ ፤በትግራይ ሕዝብ ሠራዊት ውስጥ ጀግንነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ “ማተርያላይዝ” ያደረገ ጀግና ሰው ነው።ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ንብረት እና ኢንስትቱሽን ነው…..” በማለት አባቱን የገደለለትን ድርጅት እና ወንጀል ፈጽሟል ብሎ በወነጀለው ሠራዊት መሪ ላይ የጀግንነት ሙገሳ ለግሶለታል። ምንጭ (Ethiopian Semay)
ለሙገሳው ምክንያት ሲሰጥ ደግሞ ሁለት ልጆቹን ያጣ የፋኖ ደረጀ አነጋገር የሚቀራረብ ነው። ያስገረመኝ የአብርሃ ማንጁስና የፋኖ ደረጀ መመሳሰል አባባል” የሚከተለው ነው፡
“እንደ አንድ “ፌየር-ትግሬ/ እንደ አንድ fair Tigrayan” እንደ አንድ ሚዛናዊ ሰው ሆኜ ነው” የሚለው ነው አባቱን የገደለለት ሠራዊት የመራውን አረጋዊን ጀግና ነው ለማለት የበቃው። እንዴት አንድ ሰው ‘እኔ ሚዛናዊ ሰው ነኝ” ብሎ አባቱን የገደለለትን ሠራዊትን የመራ ወይንም ድርጅትን ሊያሞግስ በቃ? የተገደሉት ወላጅ አባቱ ሲገደሉ ወያኔ የሰጠው ምክንያት እራሱ አብርሃ አንደሚለው ደግሞ “ከትግራይ መሳፍንት ተብለው በፊውዳልነት ተወንጅለው የታሰሩት የቆሰሉት እና የተገደሉት ውስጥ አንዱ የኔ ወላጅ አባት ነው።” በሚል ነው። መስፍን ስለሆኑ/ከበርቴ/ሃብታም ስለሆኑ ብቻ ነው ህወሓት የገደላቸው። አይደለም እንዴ? ታዲያ ሓብታም/መስፍን በመሆናቸው ብቻ ሲገደሉ “እኔ እንደ አንድ ሚዛናዊ “ፈየር” የሆንኩኝ ትግሬ ሲል አባቱ ያለፍትሕ ሲገደሉ በአባቱ የተፈጸመውን ወንጀል ፍትሓዊ ነው ብሎ ወያኔን ሊያሞግስ የሚያስችለው የሚዛን መለኪያው ከየት አገኘው? የሚለው ጥያቄ አስከትሎብኛል።
በጎንደር አማራ ፋኖ አዋጊ የሆነው ፋኖ ደረጀ፤ አንዱ ወይንም ሁለቱ ልጆቹ ከዘመነ ቡደ እና “ናርሲስት “ እና በደም የተጨማለቀው “ወታደር ሳሙኤል ባለ ድሉ” የተባለ ጠላቶች በነበሩበት ከጥቂት ወራቶች በፊት ፤ ጎንደር ውስይ በዘመነ አጋር ፋኖዎች 2 ልጆቹ (በተለይ አንደኛው ልጁ) መገደላቸውን እውነት ከሆነ ፤ አሁን ለተመሰረተው ዘመነ ለሚመራው ቡድን ሲባል “ልጆቹ መገደላቸውን” እንደመስዋዕት ቆጥሮት ቸል እንዳለው የሰማሁ መሰለኝ (ካልተሳሳትኩ) ፤ ታዲያ ይህ ወንጀልን ቸል ማለት ገዳዮችን ተቀብሎ ማክበር. አሁን እየረበሸን ያለው ውንጀለኞችን እንደገና ሥልጣን ላይ እንዲቀጥሉ ማድረግ አደለም ወይ?
ይህ የአባት
ገዳይ፤ የልጅ ገዳይ በነዚህ ብቻ አልተወሰነም። ከላይ የተጠቀሱት የአቶ ገዛኢ ረዳ ልጅ የሆነች እዚህ የምትኖር ልጃቸው የወያኔዎች አምላኪ ተከታይ እና አሸጨብጫቢ ሆና ማየትም አስገራሚ እና መመርመር ያለበት በሽታ ነው።
አንድ
ወዳጄ ባንድ ጽሑፉ ላይ እንዳስቀመጠው ወደ እንደዚህ ዓይነት
ራሱ የሰይጣናዊ ምግባር መገለጫ ሆኖ እኔን ከሌላው ሰይጣን ከአቢይ ነፃ አወጣሃለሁ ቢለኝ ምፀት ነው።ካለ በኋላ ለዚህ ነው ፋኖ
እንደግመል ሽንት የኋሊት እየተጎተተ የመከራችን መራዘም፣ የትንሣኤያችንም መዘግየት ምክንያት ሆኖ እንደምናስተውለው የወቀሳና ስሞታ
ሰለባ ሊሆን የቻለው፡፡ እንጂ እንደትግሉ አጀማመር ቢሆንማ ኖሮ ነፃ ከወጣን ሁለተኛ ዓመታችንን ልናከብር ወደ ፈንዲሻ መሸጫ ሱቅ
ሄደን ወረፋ በያዝን ነበር።» ይላል ወዳጄ።
ዛሬ ፋኖዎቹ አንድ ሆኑ አልሆኑ፤ሃቁ የአማራ ስብእናቸውን አሽቀንጥረው የጣሉ ወያኔ እና ኦነግን የሚመስሉ
“የጫካ ነብሰገዳይ ወረበላዎች” አፍጠው መጥተዋል። የፋኖ መሪዎች በሕዝቡ ላየ የፈጸሙት ድርጊት እየጠቀሱ ሕዝብን ይፋዊ ይቅርታ አድርገው እስካልተጸጸቱ (ለወድፊቱም
ወቅቱ ሲፈቅድ እንዲቀጡ) ለኛ ለሚጠሉን «ኢትዮጲያኒስቶችም»
አደጋ ሰለሚሆኑብን ኢትዮጰያዊ ባሕሪያቸውን ጥለው ወደ አረመኔያዊ ባሕሪ ገብተዋልና ፋኖዎችንም ከወንጅለ ውስጣቸው ካላጸዱ ልከ
እንደ ወያኔዎችና እንደ ኦነጎች እንቃወማቸዋለን።
እስኪ አስቡት? ድሃ እናቶች አረቄ እንዳትሸጡ ተብለው ወደ ጫካ ተወስደው ተድብድበው ልጆቻቸው የሚመግቡበት የድህነት ሥራ እንዳይሰሩ በዋስ ተለቀው ሲሸጡ ከተገኙ ግን ለሞት ቅጣት እንደሚዳረጉ፤ በረንዳ አደር እንዲሆኑ ልጆቻቸውም ለማኞች እንዲሆኑ በድሆች ላይ የዘመቱ የፋኖ መሪዎች፡ (gang of thugs and robbers) የአማራን ሕዝብ ሕልውና ከድጡ ወደ ማጡ አላሻገሩትም ብሎ አፉን ሞልቶ መናገር ይቻላል?
የጎጃሞቹ ቡድን አያችሁልኝ? ይህ ፖለቲካ እና ወንጀል አጣምሮ በመንታነት
በHybrid nature የሚንቀሳቀስ ቡድን ካለ የራሱ ታጣቂ
በቀር በአማራ “ክልል” ውስጥ እንዳይኖር የተደራጁትንም በሁለት
ስልት «በጥይት እና በደባ» በማፍረስ ይህ ዘመነ ካሴ የተባለ እጅግ ማፈሪያ የሆነ የጫካ ወረበላ «መሪ የመሆን ሕልሙ «እስክንድር ነጋ ሕልሜን ነጠቀው»
እያለ ለሥለጣን ሲቃዥ የነበረበትን ሕልሙ ተሳከቶለት የበላይ ሆኖ
ወጥቷል።
አንድነት ፈጥረናል እያሉ
ያሉት እነማን ናቸው?
ጫካ ውስጥ ያሉት ገመና
ሰርተው ማን ይይዘናል የሚሉት ፋኖዎችም ሆኑ አዲስ አበባ ውስጥ ተቀምጦ
የመንግሥት ሥልጣን ተጠቅሞ ማን ይይዘናል የሚሉ «ዘመናይ ሽፈቶች» በሚሰጡን የመሸፈኛ አስካሪ ትዕይንት ገመናቸውን
እንዲቀጥሉበት ድጋፍ መስጠትና ዝምታን ከመረጥን ባሕል ሆኖ ይቀጥላል። እየሆነ ያለውም ይህ ነው፡
ፋኖዎች አንድ ሆነዋልና ዝም
በሉ፤ ማለት ምን ማለት ነው?
አሁን የምሰጋው ከፈተኛ አክበሮትና
ክብር ያለኝ ለምስኪኑ ሃቀኛ ታጋይ ለታላቁ እስክንድር ሕይወት ነው። አሁን
በፋሺቶች ጠመንጃ ሥር ወድቆ በገርነቱ እራሱን ለአደጋ ሰጥቷል። ግንቦት 7 ውስጥ የተማረው የወረበላነት ባሕሪ በፋኖ ውስጥም እየቀጠለ ያለው ወጣት ፋሺስቱ
ዘመነ ካሴ እና ደም የጠማው “አስረስ ማረ» እንደ ተቀሩት ፋሺት
ታጣቂዊች የደም ሱስ ስለሚያቃዣቸው እስክንድርን እንዳያስገድሉት እሰጋለሁ። ብዙዎቹ ትግሉን እየጣሉት እየህዱ ያሉት ዋነኛው ምክንያት በዚህ ደም የጠማው ቡድን ምክንያት
ነው።
ለመሆኑ ፋኖዎች ተዋሃዱ ተብሎ ዘመነ የሚመራው ይህ አንደነት በዘመነ (በምሬ) እና በአብዱላ
ገመዳ መካከለ የተደረገ ውህደት አያደለም ማለት እንችላለን?
እሰኪማሕደራችወን እንመልከት?
ምሬ ወዳጆ <<የሸዋ ፋኖን እየመራ ያለው “አባ ዱላ ገመዳ” ነው>> ሲል በይፋ ለአማራ
ሕዝብ ተናግሯል። ታዲያ <<የሸዋ ፋኖን ወከሎ የአዲሱ ፋኖ ምክትል ሊቀ መንበር የሆነው መከታው ማሞ ፣ “አባ ዱላ ገመዳን” ወክሎ
ሰለሆነ>> የአማራ ሕዝብ ይህንን አንድነት የራሴ ነው ብሎ ከተቀበለው ፋኖ ለሚያደርስበት ኪሳራና መከራ ወዶ የምቀበል
ግዴታ አለበት።
«እኔ የበረሃ ፖሊስ ነኝ እስክንድር ሌባ ነው (እያያችሁት ያለው መፈላለግ በበፖሊሰ
እና በሌባ መካከለ ነው፤ ይህንን ልንገራችሁ ብይ ነው ፡ ይላል ዘመነ እራሱ ሲናገር”” ለዚህም፣ ነበረ ታጣቂዎቹን አስማርቶ
የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያለበትን የእስክንድር ፎቶ ያለበት ከናቲራ «እስክንድር ሌባ» እያሉ በእሳት ሲያቃጥሉት ያየነው)። ፥ እኔ ድመት እስክንድር አይጥ ፥ እኔ
አማራ፥ እስክንድር አማራ ያልሆነ ጭምብል የለበሰ ፣ አማራን ለማጥፋት ከአብይ የተላክ ሰላይ፥ እያለ ራሱን እየቆለለ እስክንድረን ለመግደል የሚመኝ የጫካ ፖሊስ
እንዴት አንድ ሆነው ነው የሚጓዙት?
“እስክንድር ኢትዮጵያዊ እንጂ አማራ አይደለም” ብሎ ካለው ተፈራ ማሞ እና ኢትዮጰያዊው እስክንድር እና የአማራ ዜግነቱን ያውጀ ተፍራ ማሞ ጋር ውሃ እና ዘይት ሆነው በውሕደቱ ላይ ኢትዮጵያዊያኖች እና አማራዎች እንዴት ሊጣጣሙ ነው?
ደም የጠማው “ኢትዮጰያዊነትንና እስክንድርን በማጥላላት” አፉን የሚቀድ የወያን አሽከር አስረሰ ማረ የተባለው “ነብሰ ገዳይ” በሚያሾረው ቡድን ወስጥ አማራ ነኝ በሚለን የሻዕቢያው ሰላይ አማራው ተፈራ ማሞ ኢትዮጰያዊው እስክንድርን እንደማይገድሉት ምን ዋስትና አለ? አማራ አማራን ከገደለ፤ «ኢትዮጰያዊው እስክንድር በአማራዎቹ» ቢገደል የሚጠበቅና አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም የሚገርመን አይሆንም።
እቀጥላለሁ ካለም «ካልረሸኑት» መከታ የሚሆነው አፈንግጦ የሚወጣ ፋኖ እስኪከሰት ድረስ “የሚያውቅበትን ትዕግሥት” ይዞ መጠበቅ ነው።
ማጠቃለያ
ባለማወቅ አንዳንድ
ንግግሮቹን ስውቀሰው የነበረው እጅግ ምጡቅ የሕግ ምሁር የነበረው “ትንቢት ተናጋሪው” ማቹ ዶ/ር ደረጀ ከመሞቱ ጥቂት ወራት ሲቀረው ያሁኑ የፋኖ ምንነት
በትንቢት የተናገረው እውነታ የገእጸበትን አስታወሰኝ። ልጥቀስና ልደምድም። እንዲህ ብሎ ነበር፡
<<የአማራ ብሔረተኛነት ድግሞ ጭራሽ ወደ ዕብደት የደረሰ ነው -Almost ወደ near madness የደረሰ ነው» አሁን የአማራ ናሺናሊዝም የሚባል የለም ነው የምለው >> << ከኖረ
ግን እግዚአብሔር አይቅናው ቀንቶት ሥልጣን ከያዘ የአማራ ናሺናሊዝም የሂትለርን የሚመስለው ፋሺዝም ነው እዚች ሃገር
የሚያሰፍነው!>> ብሎ ነበር፡ ነብስ ይማር እውነተኛው ኢትዮጰያዊው ዶ/ር ደረጀ ዘለቀ።
ደህና እንሰንብት
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

No comments:
Post a Comment