Sunday, March 30, 2025

ከዓለም አካባቢ በጥራጊ መልክ የወጣው አፓርታይድና ፋሺዝም መጠለያው ኢትዮጵያ ውስጥ ካደረገ 33 ዓመት ሆኖታል! ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay 3/30/25

 

ከዓለም አካባቢ በጥራጊ መልክ የወጣው አፓርታይድና ፋሺዝም መጠለያው ኢትዮጵያ ውስጥ ካደረገ 34 ዓመት ሆኖታል!

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay 3/30/25

የሰቆቃ ድምጽ መስማት አይሰልቻችሁ። ቢያበሳጭም ካለማድመጥ ይልቅ ‘’ማድመጡ’’ ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋው አፓርታይዳዊ መንግሥት ለመገርሰስ የመፍትሔ ማፈላለጊያ መንገድ የሚረዳ የሰቆቃ ድምፅ ነውና ላለማድመጥ አትሽሹ። የእናቶች አምባ ላለማድመጥ መሸሽ “እናቶችን መካድ” ነው። ቪዲዮው ከሥር በመጨረሻ ትችቴ ላይ ተለጥፏል።

የምታደምጡት የኢትዮጵያዊያን አምሐራ ሰቆቃና እምባ የሚደመጠው ቪዲዮ ሐገር ለማፍሰረስ 27 አመት በወያኔ ትግሬዎች (“በትግራዋይነት ማኒፌስቶ”) ፤ 7 ዓመት ደግሞ እስካሁንዋ (2017 ዓ.ም)  “በኦሮሙማዊ ማኒፌስቶ” በጠቅላላ 33  ዓመት ለአምሐራ እና ለጋሞ ሕዝብ መሰቃየትና መጨፍጨፍ (ሌሎችም የጥቃት ሰለባዎች እንዳሉ አልዘነጋሁም) ምክንያት የሆነው ከዓለም አካባቢ በጥራጊ መልክ የወጣው “አፓርታይድና ፋሺዝም ሥርዓተ መንግሥት” በኦሮሞና በትግራይ ምሁራን ቀያሺነትና ስምምነት ተባብረው ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የመንግሥት ሥርዓት እንዲሆን በሕገመንግሥት በመደንገጉ ምክንያት ነው የምታደምጡት የምስኪን አምሐራ ሴቶች እምባና ልቅሶ።

ብዙ ሰዎች እንዳውም የማስታውሳቸው የአምሐራ ምሁራን እና ትግሬዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባው ሥነ መንግሥት ኢትዮጵያን የሚጠሉ፤ሃገር ለማፍረስ ተፈራርመው የመጡ፤ “ከጣሊያን የባሰ ‘ጣሊያን ቀመስ’ የሆነ ‘አገር በቀል የቅኝ አገዛዝ’ ሥርዓት ነው” እያልኩ ስጽፍ ከላይ የጠቅስኳቸው ምሁራን ለጽሑፌ መልስ ሲመልሱልኝ የነበረው መልሳቸው “በድንጋጤና በመገረም ተውጠው እንዴት ያንድ ሃገር ሰዎች በዚህ ዓይነት አገላለጽ ታስቀመጣቸዋለህ? አሁን ያለው ሥርዓት <<የአምባገነኖች ሥርዓት እንጂ አፓርታይዳዊ አይደለም፤ አባባልህ ሕዝብ ለሕዝብ ያቃቅራር…>> እያሉ ብዙ ስድብ ሲሰድቡኝ ነበር።

የጊዜ ጉዳይ ሆነና የሚሰማኝ ሳጣ ከመስመሬ ሳልወጣ በዚያው መከራከር ቀጠልኩበት። እንዳልኩትም የጊዜ ጉዳይ ሆነና ጊዜ ፈጅቶ ከባድ ጉዳት ደርሶ “ብዙ ሕዝብ በልቶ” ከጨረሰ በሗ እነዚህ ምሁራን እኔ ስለው ወደ ነበረው መስመር ገቡና ከኔ ብሰው መጮህ ጀመሩ ማለት ነው። ለዚያ አምላክ (ምናልባት) ሐላፊነት ወስዶ ዓይናቸው ስላበራላቸው አመሰግነዋለሁ።

እንደውም ለክርክሬ ማገር አድርጌ ሳነሳው የነበረው ነጥብ፤ ደቡብ አፍሪካ እና ሮዴሺያ (ዚምባቡዌ) የነበሩት ፓርታይዶች 33 ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋው “አፓርታይድ” ሲነፃፀር “የኢትዮጵያው አፓርታይድ የከፋ በዓይነቱም የተለየ ነው ስል ነበር። ካሁን በፊት ክርክሬን ላልተከታተላችሁ አዳዲስ አንባቢዎቼ ስለምትኖሩ በአባባሌ እናንተም ልትገረሙ ትችሉ ይሆናልና ላይላዩን ብቻ ባጭሩ ምክንያቴን ላስቀምጥ፡

  ቦር ወይንም “አፍሪካና” በመባል የሚጠሩት የሳውዝ አፍሪካ የነጭ ዝርያዎች የሚገዝዋት <<አፓርታይዳዊዋ ደቡብ አፍሪካ>> እና በእያን እስሚዝ የምትመራዋ <<ሮዴሺያ (የዛሬዋ ዚምባቡዌ)>> ይኖሩ የነበሩ ሁሉም ዘሮች ዕኩል የምጣኔ ሐብት ባለድርሻዎች ሳይሆኑ ተጠቃሚዎቹና የበላይ ገዢዎቹ “ነጮች” ብቻ (ሕንዶችም አሉበት) የሚቆጣጠሩት ሥርዓት ነበር።

ስለሆነም ይህንን አድሎአዊ ዘረኛ አስተዳዳር ለመቃወም የተነሱት የነዚህ ሁለት ሐገሮች ታጋዮች ዋናው ትኩረት “ምጣኔ ሐብትና  የሥራ አቀጣጠር ለሁሉም ዜጋ በዕኩልነት እንዲዳረስ ነበር ትግላቸው።

“በጥቁሮች ላይ ጭፍጨፋ ግድያ ዕስራት መሰወርና ግርፋትም እኮ ነበር?!” ልትሉኝ ትችላላችሁ፡ ቢኖርም ሆን ተብሎ ሥርዓቱን ለመቃወም በወጡት ሰላማዊ ሰልፈኞችና የተቃዋሚ ቡድን አባሎች ንክኪ አላቸው በሚል በየመንደሩ ገብቶ የጭካኔ ብትር ሲያሳርፍ ነበር እንጂ አርፈው የተቀመጡ ጥቁሮች ግን ልክ እንደ ኢትዮጵያው አፓርታይድ በየመንደሩ እየሄዱ ማረድና ዘራቸውን ለማጥፋት ቤቶቻቻውን፤ ፤ንብረቶቻቻውና ሰብላቸውን፤ እያቃጠሉ ከደቡብ አፍሪካ  “እንዲባረሩ” ብዙም ትኩረት አላደረገም። ብዙዎቹ የታዩት ጭፍጨፋዎች በሰላማዊ አድማ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ “አፓርታይድ ብሔር ብሔረሰብ አስተዳደር” ስመንለከት ግን ሕክምናው፤ የትምሕርትና የኩባኒያ ተቋማት፤ ሰፋፊ እርሻ መሬቶች፤ ለትግሬዎችና ለኦሮሞዎች እንዲዳረስ በማድረግ ሌሎቹ እንዲቆረቁዙ (ጋምቤላና ጉሙዝ አካባቢ እርሻ መሬቶችን አስታውሱ) በማድረግ የምጣኔ ሐብቱ ለገዢዎቹ ነገዶችና አለቅላቂዎቻቸው የተሻለ ኑሮና “የገዢነት መንፈስ” ልዩ ኩራት ትግሬዎችና ኦሮሞዎች እንዲሰማቸው በማድረግ ሌሎች ተሸማቅቀው በፍርሐትና በስጋት እየኖሩ እነሱ ግን “የኛ” የሚሉት መንግሥት መስርተው እንዳሻቸው ሲሆኑ አይተናል።

የሮዴሺያና የደቡብ አፍሪካ አፓርታይዶች እንዲሁም የጣሊያን ፋሺዝምና የናዚ ሥርዓቶችን ስንመለከት ግን ፡ ሐገራቸው ለማበልጸግና ለማጠናከር ከነበራቸው ይዞታ እንዲሰፋ ሲያደርጉ ፡ 33 አመት የተመሰረተው የኢትዮጵያ አፓርታይድ ግን በተጻራሪ መልኩ የሃገሪቱ የዘመናት የነፃነት አርማ የተባለቺው ሰንደቅአላማ መልክዋን በመቀየር 44 ጨርቆችን በማሰፋት “አፓርታይዳዊ ክልሎች” ልክ እንደ ራስ ገዝ ሃገሮች ባንዴራ እንዲኖራቸው በማድረግ <<ብሔር/ሃገር ብሎ በመሰየም የሐገሪቱ ሰንቃዎችን በማፍረስ ፤ ይዞታዋ የነበሩ የሃገሪቱ መርከቦች በሽልማት ለጠላት ሃገሮች በመሸለም፤ የባሕር በር ለጠላት በመሥጠትና ወደብ አልባ በማድረግ፤ ሠፋፊ ለም መሬቶች ለሱዳንና ኤርትራ ለምትባለዋ በመስጠት አፍራሽ ዒላማ የተገበረ ከተጠቀሱት አፓርታይዶችና ፋሺሰት ሥርዓቶች የተለየ አፓርታይድ ነው።” ፤

ልዩ የሚያደርገው ደግሞ “ለዘመናት ድርና-ማግ ሆነው ያቆዩዋት ሐገራዊ ባሕሎችዋና ሓይማኖቶችዋ” እንዲበረዙ በማድረግ’’ ‘ብሔራዊ ቋንቋ የሆነው የመረዳጃ ልሳን አማርኛ’ እንዲዳከምና እንዲጠፋ በግሃድ መንግሥታዊ ጥቃት ደርሶበት አልሞት ብሏቸው እየታገላቸው እነሆ በሰፊው ሕዝብ ምላስ አልጠፋ ብሏቸው ሲታገላቸው ማየት የመቸገራቸው ክስተት ደግሞ ሌለው አስገራሚው ከስተት ሆኖ እያየን ነው

ንግድቤቶች ትምሕርተቤቶች ሆስፒታሎች የሃይማኖት ተቋማት መንገዶች ሁሉ ስማቸው እንግሎዝኛ፤ ዓረብኛ ሆነው  ወጣቶቹ “ክ” ፊደልን በ “ህ” (እንዴት ነህ? አይዞህ! ለማለት “እንዴነክ? አይዞክ!” ይላሉ) ፊደል እየለወጡ ሲቸገሩ እንሰማቸዋለን። በሚገርም ሁኔታ ያነጋገር ስልታቸው ዓረብኛና እንግሊዝኛ ሆኗል። ይህ ሁሉ ሐገር በቀል አፓርታይዱ ሆን ብሎ 33 አመት የሰራበት ትውልድና ባሕል ለመግደል የሰራበት ዘመቻ  ሲሆን ፤ የመንግሥት ወታደሮች ተብለው መሎየና ጠብመንጃ የያዙ የሃገሪቱ የደሕንነት፤ የመከላከያና የፖሊስ ሃይል <<የፔንጤ   ሃይማኖት መሪ ወስላታ መሪዎች (እንደ እዩ ጩፋ የመሳሰሉትን)በወታደራዊ ሞተር ሳይክል፤ በወታደራዊ መኪኖች፤ በወታደራዊ ሰልፍ እና አጀባ እያደረጉ ፤ ወታደራዊ የክብር መሎዮአቸው ወደ ሰማይ እየወረወሩ አብረው ሲጨፍሩና ሲዘሉ የሚደረግበት ምክንያትም የሃገሪቱ አፓርታይድ ሥርዓት <<የሃገር መፍረስ>> አበሳሪነቱ እየነገረን መሆኑ ምልክት ነው።

ይህ ሁሉ ብልሽት ኢትዮጵያ የምትባል ሐገር እንዳትኖር የሁለቱ ነገድ ተወካዮች (መለስ ዜናዊና ሌንጮ ለታ) ተፈራርመው የመጡበት ዓላማ ለማከናወንም ‘’ነገዶች (ብሔር ብሔረሰብ በሚል ስያሜ) በሚናገሩት ቋንቋ በሚኖሩበት አካባቢ “ተከልለው” የማንም ኢትዮጵያዊ ሳይሆን የሃብትና የመሬት በባለቤትነቱ ለቋንቋ ተናጋሪዎቹ ብቻ እንዲሰጥና እንዲቆጣጠሩት በማድረግ፤ ሁለቱ ገዢዎች ያልነበራቸው የመሬት ስፋት በመያዝ፤ ሌሎች ነገዶች ጥገኛ ሆነው ባለቤቱ በሚፈቅድላቸው አሰራር ብቻ የሚኖሩ “በገዛ ሃገራቸው ጥገኛ ወይንም ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን”  እንዲሆኑ ያደረገ ነው።

ነገድንና ሃይማኖትን በጥቃት ቀለበት አስገብቶ “አምሐራ (ክርስትያንና-ዕስላም አምሐራ) <<በምድሪቱ እንዳይኖር በመጨፍጨፍ የሕልውና አደጋ እንዲደርሰው አምሐራውና ጋሞው በሚናገሩት ቋንቋ ብቻ ተለይተው <<በጥቃት ቀለበት>> ለይቶ ያስገባ ከሌሎቹ አፓርታይዶችና ፋሺስት ሥርዓቶች የተለየ ነው የምልበት ምክንያት፤ <<ኢትዮጵያዊ ሆኖ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተደራጅቶ የሚሰራ እስካሁን ድረስ መጠሪያ ስም ያጣሁለት ሐገር በቀል አፓርታይድ ሥርዓት ነው>> የምለው በቀላል አላለጽ ነው።

ከላይ የተጠቀሱ አፓርታይድ ሐገሮች ከሐገራችን አፓርታይድ የሚለያቸው መንገድ <<ኢትዮጵያ አንደ ሐገር የሕልውና አደጋ አንዲጋረጣት በጥናት በገዛ ልጆችዋ ዘመቻ ሲታወጅባት>> <<የዚምባበዌው ሙጋቤና የደቡብ አፍሪካው ኔልሰን ማንዴላ በአፓርታይድ ያቀረቡት ክስ ግን <<ነጮቹ ሐገራቸው በማፍረስ ዘመቻና መሬት ለባዕድ በመሸንሸን ሳይሆን አፓርታይዱን የከሰሱበት ፡የትግላቸው ዋናው ትኩረትጥቁሩ ሕዝብ በገዛ ሃገሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ባለመኖሩ ዕኩል እንደ ነጮቹ ተጠቃሚ የሚንበትን መንገድ መቀየስ ነበር ዋናው ትኩረታቸው>>

ይህ ነበር ዋናው የትግላቸው ትኩረት እንጂ እንደ ኢትዮጵያውን 33 አመት ሐገር በማፍረስ የተጠመደው የኛው አፓርታይድ <<የዚምባበዌና የደቡብ አፍሪአካዊያን ጸረ አፓርታይድ ታጋዮች “ሐገር እንዳያፈርስባቸው ስጋታቸው አልነበረም”። ያ ነው የነሱና የኛው አፓርታይድ የሚለየው።

ለማጠቃለል፡

 ጥቁሩ ዛሬ እንደ እኛው ሐገራዊ ሕልውናው አደጋ ላይ አይደለም ሆኖም ዋናው ፓርታይድ ያካበተው የሃገሪቱ ሃብት ግን “አፓርታይድ ተወገደ” ከተባለ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የጥቁሮች ድሕነት ባሰበት እንጂ አልተሻለውም። ምክንያቱም ፤ሕልውናው ለአደጋ የተጋለጠው እንደ ኢትዮጵያ የጀነሳይድ ጥቃት  ስለደረሰበት ሳይሆን ዋናው የጭቆናው መሳሪያው “ሥልጣንና ምጣኔሐብቱ” በተለይ ምጣኔ ሃብቱ (ዕርሻው ማዕድኑ እና ኢንዳስትሪው) ዛሬም ከነጮቹ እጅ ስላለወጣ ጥቁሩ ሕዝብ ዛሬም የፍትሕ ያለህ እያለ ነው።

እኛ ግን ከነሱ የሚለየን “ነብስ አድን የሕልውና እና የሐገር ያለሕ! እያልን ነው። በዕምባ እየታጀበ የምትሰሙት የአምሐራ እሕቶቻችን ኡኡታ ከዓለም አካባቢ በጥራጊ መልክ የወጣው አፓርታይድና ፋሺዝም መጠለያው ኢትዮጵያ ውስጥ በማድረጉ ያመጣው ጠንቅ ነው።

ሰላም እንሰንብት!

ጌታቸው ረዳ

 

 

No comments: