ወያኔዎች ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ለነጮች መነጠፍ የወረሱት ባሕልና በአብይ አሕመድ ተባባሪነት በትግራይ መልከዓ ምድር
ላይ የሚንጎባለለው ‘አጭበርባሪው ዝሆን’
ጌታቸው ረዳ
Ethiopian Semay
8/28/24
ፕሮፌሰር ሌማርቻንድ (Professor Lemarchand) የተባሉ ምሁር ሲአይኤንን (CIA) “ስድ ዝሆን”
(‘rogue elephant’) ይሉታል። ይህ ቀጪ የሌለው ሁሉንም ሕጎችና ፍጡራንን የሚረጋግጥ “ስድ ዝሆን” በአገር ገንጣዩ አብይ
አሕመድ ተባባሪነት ዛሬ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በክብር ተንሳፎ መቀሌ ከተማ በመገኘት የትግራይ ወያኔ መሪዎች ራሳቸው እንደቻሉ
እንደ አገር መሪዎች ቆጥሮ የወያኔ ባንዴራ ጠረጴዛው ውይይት ላይ በክብር ተቀምጦላቸው ከሲ አይ ኤው ወኪሎችና አምባሳደር ተብየው
ሲጨባበጡና ሲሳሳቁ አይተናል። “እርይ በይ አገሬ CRY MY BELOVED COUNTRY!!!!
የዚህ “ስድ
ዝሆን” ከጅምሩ የኤርትራ ሽምቅ ተዋጊው የሻዕቢያው ቡድን በሙስሊሙ ኤልኤፍ/ጀብሃ/ ላይ እንዲዘምት ሪቻርድ ኮፕላንድ የተባለው የ ሲ አይ
ኤ ወኪል በ1969 የዛሬው ኢሳያስ አፈወርቅን በአካል በማነጋገር ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል በመሳሪያ ትጥቅና ምክር በመስጠት
ሲ አይ ኤ ከፍተኛ በደል ፈጽመውብናል።
ያ አልበቃ
ብሎት ሲ አይ ኤ ከባሕር መነጠቃችን ሴራ ጀምሮ እስከ አፓርታይዳዊ
የወያኔ የጎሳ አስተዳደር መመስረት እጁ ረዢም ነበር።በዚም አልተወሰነም የዩሁዲ ሃይማኖት ተከታዮችን የእስራል ዜጎች
እንጂ ኢትዮጵያዊያን አፍሪካዊያን አይደሉም በማለት ዜግነታቸውና ማንነታቸውን በሴራ በመለወጥና በማሳመን በሺዎቹ የሚቆጠሩ ወጣቶች
፤ሕጻናት (ማንነታቸው ለመናገርና ለመከራከር መብት የሌላቸው ሕጻናት) እና በምርኩዝና በሰው ተደግፈው የሚሄዱ አረጋውያን የኢትዮጵያ
ዜጎች ከመንግሥቱ ሃይለማርያም ጋር ተመሳጥረው ወደ እስራል በገንዘብ ልውውጥ (ሂውማን ትራፊኪንግ ብየ የምጠራው) ወደ እስራኤል በማስገባት እዛው የተወልዱ አዲስ ትውልዶች ከፍልስጢኤማዊያን
በሚደረገው ጦርነት እንዲያግዙት እየመለመለ ለጦርነት እሳት እየማገዳቸውና የዘርና የቀለም ልዩነት ተጠቂ እንዲሆኑ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።
THE
SLAVE TRADE IN FALASHA OF ETHIOPIA” የሚለው የወዳጄና አስተማሪየ ዶ/ር ዓለሜ እሸቴ ጽሑፍ ያንብቡ።በተጨማሪም
Operation Solomon- the darling rescue of the Ethiopian Jews) By Stephen
Spector) የተፈፀመው ኢ ሕጋዊና የዜግንት ነጠቃ በዝርዝር በሚደንቅ አጻጻፍ የተደረገው ሴራ ሳይሸሽግ ይነግረናል (አንብቡት፤
ታዝናላችሁ)።
በአብይ አሕመድ ተባባሪነት ትግራይን ለማስገንጠል ከሰንደቃላማችን ማጥፋት ጀምሮ የትግራይ ሪፑብሊክ ግንጣላ በይፋ የሚሰብኩ ትግራይ ወስጥ በግሃድ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ ብቻ ሳይሆን፤ ይህንን የግንጠላ አጀንዳ ለማካሄድ የግንጠላ አጀንዳቸውን ሕጋዊ ለማድረግ ሳልሳይ ወያኔ የመሳሰሉ ወያኔን የተኩ አዳዲስ ባንዳዎች ፕሮግራማቸውና አላማቸው የትግራይ ሪፑብሊክ ለመመስረት እንደሆነና የሸዋ አማራዎች ስሪትና የትግራይ ሕዝብ ቀበኛ የሚልዋት ኢትዮጵያን ለመፋለም በውድድር ምርጫ ተመዝግበው እውቅና እንዲሰጣቸው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ “ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት” ተብየው ሳይቀር ማኒፌስቶአቸው በማቅረብ እንዲመዘገቡ ከተዘረዘሩት ስምንቱ የድርጅቱ ዓላማዎች ውስጥ በመጀመሪያ ረድፍ የሚነበበው “ሃገረ ትግራይ” ለመመስረትየሚለው ተቀባይነት አግኝቶ እንደተመዘገበ የሳልሳይ ወያኔ አቶ ሃይሉ ከበደ የተባለው በተደረገለት ቃለ መጠይቅ ነግሮናል።(ሰነዱ ለቦርዱ የቀረበው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተደረገ በኋላ ነው።)
ዛሬ ደግሞ
መለስ ዜናዊን የተካው የአሜሪካኖቹ አዲሱ “ቹዋዋ” (ፑፐት) አብይ አሕመድ ለሀገር መበታተን መነሳሳት የማይታለፍ ዓለም አቀፋዊ
ክስተት ነው ብለው ለሚያምኑት አሜሪካኖች ትግራይ ቀዳሚ አጀንዳቸው እንድትሆን እየተባበራቸው ነው።
እንደምታውቁት
ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ (ሶቪየት ከፈረሰች ወዲህ) አሜሪካ የሚመራው
ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጎሳ
ንቃተ ህሊና በማተኮር ለማስገንጠል
አዳዲስ አገሮች ለመሆን አሰፍስፈው ባገጠጡ “የክልሎችና የመንደር ልሂቃን” ፍለጋ ላይ ተጠምዶ ይገኛል። ይህ የማፍረስ አጀንዳ “ፕሮፊለቲክ ፓናሲያ” ብሎ ይጠራዋል፡ (ካልተሳሳትኩ ፈውስ ያልተገኘለት የመከላከያ ፈውስ/መፍትሔ’ እንደማለት ይመስለኛል (የሚገርም ነው!!!)
ኢትዮጵያ ፤ሱዳን
እና ሶማሊያ ለዚህ ምሳሌ ናቸው። በተለይም የ ሲ አይ ኤ የአፍሪካ መናሃሪያ የመጫወጫወቻቸው ሜዳ የሆነቺው ኢትዮጵያ “በጎሳ”
(ኤትኒክ ፌደራሊዝም) መጋዝ እተገዘገዘች ማየታቸው በጠመንጃና በመድፍ ባይሮፕላን ድብደባ ለማፍረስ ከባድ የሆነቺውን ጥንታዊትዋ
አገር፤ በጎሳ ፖለቲካ ታምሳ ስትንገዳገድ ማየታቸው ሌሎች አገሮችን ለማፍረስ ቀላል እንደሚሆንላቸው ደስታቸው ወደር የለውም።
የብሔር ድንበሮች፣ የሀይማኖት ድንበሮች እና የጎሳ ድንበሮች ያልነበራት ሶማሊያ በዓረቦችና በ ሲ አይ ኤ መጋዝ ተገዝግዛ ትገኛለች። ዛሬም ትግራይ ወስጥ ተመሳሳይ መጋዝ በፍጥነት እየሰራ ነው። ጣሊያኖችን ማማ ሚያ (እናቴ ድረሺ!) ያስባለቻቸው ኢትዮጵያዊትዋ ሰንደቃላማችን ካሸነፈቻቸው ምድር “በትግራይና በዶጋሊ” ፤ እንዲሁም “ሱዳኖችን በሰሐቲ” ፤ በተጨማሪም “አሜሪካኖችን፤ ግብጾችንና ቱርኮችን በጉንደትና (1867) በጉራዕ (1868 በራሳችን ዘመን አቆጣጠር) ተውለብልባ ያሸነፈቻቸው ሰንደቃላማችን በነኚህ ተራሮች ላይ እንዳትውለበለብ በወኪሎቻቸው በወያኔና ሻዕቢ በኩል ስለታገደች ቱርኮች፤ ዱርቡሾች፤ ግብጾች፤ አሜሪካኖችና ጣሊያኖች ዓላማቸው ተሳክቶላቸዋል።
የማፍረሱ ሂደት
ጋብ ያዝ ለቀቅ እያደረገ ሲጓዝ የነበረው የማፍረስ ጉዞው ድንበሮች ቢኖሩም ባይኖሩም፣ በአሜሪካ መንግሥትና በሲ አይ ኤ ወኪሎችዋ
በእነ “ፓል ሄንዝ”
እና “ሄርማን ኮኸን”
የተቀናጀው የቆየው ኢትዮጵያን የማፍረስ ሥራ ዛሬም እንደ አዲስ አገርሽቶበት
ይገኛል።
በሲ አይ ኤ
ጣልቃ ገብነትና ዕቅድ የሚከተሉት አገሮች ፈርሰዋል ወይንም በመፍረስ ላይ ናቸው፡
1. ሶማሊያ
2. ኢትዮጵያ
3.ሊቢያ
4.ዒራቅ
5. አፍጋኒስታን
(ባትፈርሰም ለዜጎችዋ የምድር ሲኦል አንደሆነች ይነገራል) አሜሪካኖች የተጫወቱት ሴራ ነው።
6. የኮንጎ
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ
7. የመን
8. ሶርያ
9. ሱዳን
10. ሄይቲ
11. ኤርትራ፤-
ኤርትራ፤ ባትፈርስም በተደረገው ጥናት በዓለም በፍልሰት ብዛት የያዛች
አገር ኤርትራ ነች። ሕዝቡ “ፈልሶ” ለስደትና ለተመጽዋችነት ተዳርጎ አገሪቱ ባጀት ስለሌላት ጥቁር ገባያ ለገቢ ማስገኚያ በመጠቀም
መንግሥት ተብየው ወኪሎቹን በየአገራቱ በመሰማራት በረሃ እያለ ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ ጥቁር ገበያ እንደ ኢምፖርት ኤክስፖርት
የገቢ ምንጭ ቆጥሮ ለራሱ ሥራ ማስኬጃው ይጠቀምበታል። ሕዝቡ ግን የገቢ ምንጭ ስለሌለው ውጭ በሚኖሩ ኤርትራኖች ለቤተሰቦቻቸው በሚልኩት
ገንዘብ እየቆነጠረ ይኖራል።
ዜጎችዋ የኢንተርኔት
አቅርቦት እቤታቸው ውስጥ አያገኙም። ሌላ ቀርቶ የእጅ ስልኮቻቸው ባትሪ ሲደክምባቸው (ቻርጅ ለማድረግ) ባትሪውን ለማሞቅ መሃል
ከተማ ሄደው ገንዘብ በመክፈል ስልኮቻቸው እስኪሞሉ እዛው ትተውላቸው ሄደው በማግስቱ ይወስዱታል። ያልፈረሰ የሚመስል ግን ከፈረሱት
አገሮች የሚቆጠር።
ኢትዮጵያ በአሜሪካኖች ዕቅድ ከሚፈርሱት (ያው ያልፈረሰች ግን የፈረሰች “ፈይልድ ስቴት ነች) አገር አንዷ ስለሆነች፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ በጎሳ ፌደራሊዝም የጀመረው የመለስ ዜናዊ ሴራና ተባባሪነት እውን ለማድረግ የመጀመሪያ ታርጌታቸው (ዒላማቸውን) ለማሳካት “ትግራይ” ተመራጭ አካባቢ ሆና አግኝተዋታል።
ይኸየውም ሟቹ መለስ ዜናዊ የአሜሪካኖችና የአውሮጳዊያኖች በተለይም የእንግሊዝ አይርሾች አሽከር ስለነበር፤ በመለስ አማካይነት ብዙዎቹ የወያኔ መሪዎች በነሱ ሥር የተመለመሉ ስለሆኑ (ስብሓትም በቃሉ መስክሯል) የአሜሪካን አምባሳደር የሚያክል ወደ መቀሌ በመሄድ ልክ “ትግራይ” እንደ አንድ አገር ተቆጥራ የተገንጣይ መሪዎችን እነ ጌታቸው ረዳን ብዙ ሰው አላወቀዉም እንጂ: “የእኔ ፍላጎቴ እንደ እናንተው ትግራይ አገር እንድትሆን ነው ፍላጎቴ በማለትባሳለፍነው ሓምሌ ውስጥ (ከአንድ ወር በፊት)የተናገረበት ቪዲዮው አለኝ): CIA እነኚህን ወንጀለኞችና ገንጣዮች እንደ ሕጋዊና ራሳቸው የቻሉ የአገር መሪዎች አድርጎ እስከ መቀሌ ድረስ ተጉዞ ሲያነጋግር ማየት ለብዙዎቻችን አዲስ ዜና ባይሆንም አሜሪካኖችን ትግራይ ድረስ ሄደው ሥራቸው እንዲሰሩ የፈቀደላቸው ምከንያት “አብይ አሕመድን ልክ እንደ የሱዳኑ አልበሽር (ዳርፉርን ጠቅሰው ደቡብ ሱዳንን ገንጥል የጀነሳይድ ክስም እንሰርዝልሃለን ብለው እንዳስፈራሩትና እንደፈጸመላቸው) አብይንም በጀነሳይድ እንከስሃለን እያሉ ስለሚያስፈራሩት አድርግ የሚሉትን እያደረገላቸው፤ ዛሬ የቄሳርዋ አገር አምባሳደርና የሲ አይ ኤ ወኪሎች መቀሌ ድረስ ሄደው የድርጅት ባንዴራ ጠረጴዛው ፊት ለፊት አንደ የአገር ባንዴራ ተቆጥሮ ተቀምጦላቸው ንግግር ሊያደርጉ በቅተዋል። ይህ የአገራችን ሞት አበሳሪና የ ሲ አይ ኤና የጎሳ ፖለቲካ ያስተዋወቀው የጣሊያን ፋሺሰቶች ድል ነው።
ዛሬ ትግራይ
ውስጥ እየተደረገ ያለው ለፈረንጅ መነጠፍ አዲስ አይደለም። ወያኔዎች ለፈረንጅ መነጠፍ ያገኙት ትምሕርት ከራስ መንገሻና ከራስ አሉላ
ያገኙት ነው። (ስለ ራስ አሉላ ሌላ ቀን አቀርባለሁ) ለምሳሌ ስለ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ለዛሬ ይህንን እንመለክትና ልደምድም።
ታሪኩ የተዘገበው
የትግሬ ጠባብ ብሔረተኞች ብዙ ጌዜ ለሙግታቸው ድጋፍ የሚጠቀሙበት በዓድዋ ጦርነት የተገኘው ብቸኛ የእንግሊዝ ቴሌግራፍ ጋዜጠኛ የነበረው
“አጉስተስ ዋይልደ Augustus Wylde” የዓይንና የጀሮ ምስክርንቱን እንዲህ ሲል ዘግቦት ይገኛል። ወደ አማርኛ ትርጉም የራሴ
(ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay አዘጋጅ)፡
እንዲህ ይላል፡
“ከፍርድ ቤት ውሎአቸው በኋላ መቀሌ ውስጥ ወደ ራስ መንገሻ መኖሪያ ቤት እንድመጣ ተጠየቅኩኝና፤ አትክልት ሥፍራ ሆነው ከልጅ ምርጫ ጋር ብቻቸውን አገኘሁዋቸው (ልጅ ምርጫ ማለት የአፄ የሐንስ የእንግሊዝኛ አስተርጓሚ የነበረ ወጣት ነው)። የተጠራሁበት ምክንያት ሲገልጹልኝ ንጉስ ምኒልክ እኔን ማየት እንደሚፈልጉ እና እኔን ማግኘት እንደሚፈልጉ የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ተነገረኝ ። በተቻለ ፍጥነት ወደ አዲስ አበባ መሄድ እንዳለብኝ ነበር የደብዳቤው
መልእክት።
ሆኖም ራስ
ከዚያ ይልቅ
ወደ ኤርትራ በማቅናት ከዚያም ወደ ለንደን ሄጄ የእንግሊዝ መንግሥት የጠየቁኝን ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ እንደሆንኩ እንዲያውቁልኝ እንድትነግርልኝ ነው የምፈልገው ብለው ጠየቁኝ። ከጣሊያኖች ጋርም መጣላቴ መቼም ቢሆን እጅግ ማዘኔንና ከጣሊያኖች ጋርም ምን ያህል ከእነሱ ጋር ወዳጃቸው ለመሆን እንደምፈልግ ንገርልኝ። አሉኝ።
እኔም ስመልስ እንዲህ
አልኩ፡ ‘አንድ መልስ ልስጥ፣ የጠየቁኝን ነገር ላደርገው የማይቻል ነው፡ የኔ ተልዕኮ ፖለቲካ አይደለም፣ የኔ ሥራ በእንግሊዝ ውስጥ ካሉት ታዋቂ የዜና ማሰራጫ ጋዜጦች
አንዱ የሆነው
ቴሌገራፍ ጋዜጣ የላከኝ በአቢሲኒያ ውስጥ ስላሉ ሁኔታዎች ለማጣራት እና ሙሉ ዘገባ ለመዘገብ የተላክሁኝ ዘጋቢ ነኝ እንጂ
የፖለቲካ ሥራ አይመለከተኝም። አለኩዋቸው።
አሁንም ወደ ሰሜን (ኤርትራ ማለቱ ነው) እንድመለስና የተላኩልኝን ዕቃዎችና ቴሌግራም ስለደረሰኝ ወደ ሰሜን እንድሄድ እንዲፈቀድልኝ ጠየኩኝ።
ሆኖም ለሁለተኛ ጊዜ በማግስቱ መኳንንት ባሉበት
ስብሰባ ተጠራ። ራስ አሉላ፣ የተምቤኑ ራስ ሐጎስ፣ ሹም አጋሜ፣ እና ሐጎስ ተፈሪ፣ የንጉስ ምንሊክ ወኪል የሆኑት ነብሩድ ወልደጊዮርጊስ እና እጀግ ወዳጄ የሆኑት የሟቹ የንጉስ ዮሃንስ ነብስ አባት የነበሩት ሊቀ ካህናት ወልደ ማርያም በራስ መንግሻ ሰብሳቢነት አብረው
ተቀምጠው አገኘሁዋቸው። የተጠራሁበትም ምክንያት ወደ አዲስ አበባ
መሄድ እንዳለብኝ ወስነው እንደነበር ገባኝ። አስተርጓሚው ልጅ ምርጫም አብሮአቸው አለ።
ምን የመሰለ ቁርስ ከጠጅ ጋር ቀርቦልን ቁርሳችንን በደስታ ከተመገብን በሗላ፤ ሰራተኛው መስርያውን (ምግቡን) አንስቶ ወደ ውጭ ከሄደ በኋላ የንጉሥ ምኒልክ ደብዳቤ እንድመለከተው ተደረገና ይዘቱ ተነገረኝ። የደብዳቤው ይዘት ወደ አዲስ አበባ ሄጄ የእስረኞች አያያዝ እንዴት እንደተያዙ ለማየት ወደ አዲስ አበባ እንድመጣ የሚል ነው። እኔም የቴሌግራም መልእክቶቼን ለማግኘት ወደ ማሳዋ መሄድ አለብኝ ብዬ አጥብቄ ገለጽኩ። ሆኖም ውሳኔ ስለተወሰነ አልሆነም።
በማግስቱ ጠዋት እጀግ ወዳጄ ወደ ሆነው ራስ አሉላን ልሰናበት ሄድኩ። ወዲያው ወደ ደቡብ (አዲስ አበባ ማለቱ ነው) ከመሄዴ በፊት ዓድዋ ከተማ የተውኩትን ዕቃዬን ወደ ዓድዋ ሄጄ እንድወስድ የፈቀደሉኝ እሳቸው ብቻ መሆናቸውን ነግረውኝ እንደገና እንድጎበኛቸው አደራ አሉኝ፣ እኔም እድል ካገኘሁ ላደርገው ቃል ገባሁ። ለመለያየት እጄን ስጨብጣቸው ፣ እሳቸውን የማየት የመጨረሻ ጊዜ እንደሆነ እና የብዙ የጦር ሜዳ ጀግና ህይወታቸው በማይረባ የመሬት ባለቤትነት ንትርክ እንደሚያጡ ፍጹም አላሰብኩም ነበር። የሚገርመው፣ ቀጥሎ የተሰናበተኩዋቸው ሰው ከራስ አሉላ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡት ሌላው የተምቤን ራስ ሐጎስ ሲሆኑ፣ በተመሳሳይ እሳቸውም ሕወታቸው ተቀጨ።
ከዚያም ራስ መንገሻን ለመሰናበት ሄድኩኝ። እሳቸውም እንግሊዛውያንን ምን ያህል እንደሚወዷቸው እንዳሳውቅላቸው ሲጠይቁኝ እውነቱን መናገር እንዳለብኝ ነገርኩዋቸው። እኝህ ራስ ምንም “የጀርባ አጥንት” የሌላቸው “ከጄሊ-ዓሣ” ተራ ጋር የሚሰለፉ በዚህ ልፍስፍስነታቸው አውሮጳውያኑ ወደ ማንኛውም ነገር “ሊቀረጽዋቸው” እንደሚችሉ አልጠራጠርም። ራስ መንግሻ በአውሮፓ ኃይል ከተደገፉ ያዘዝዋቸውን ሁሉ እንደሚፈጽሙ፡ ጠንካራ መሪ መሆን የማይችሉ ለአውሮጳዎቹ “የተሻለ አሻንጉሊት” ታዛዥ ቹዋዋ (ውሻ) ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው። .. (When he asked me to let the English know how fond he was of them, I told him, I should tell the truth. This Ras belongs to the jelly-fish order, with no backbones. I have no doubt he could be molded into anything, and if backed up by a European power, would do everything he was told, and perhaps, therefore, might be a better puppet to run than a stronger-minded man; ..,)" (አውግስጦስ ዋይልዴ (Modern Abyssinia –Augustus Wylde)
ዛሬ የኛ ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ/ም ጀምሮ የተከሰቱ መሪዎችዋ
ሕሊናቸው ለቅኝ ገዥዎች የማሰሪያ ሰንሰለት በመስጠት ይህ ቅጣትና
ቀጪ የሌለው ሁሉንም ሕጎችና ፍጡራንን ደፍጥጦ የሚረጋግጥ CIA የተባለ “ስድ ዝሆን” (‘rogue elephant’) በታሪክዋ ለመጀመሪያ
ጊዜ የፍጢኝ እንዲያስራት ተባብረዋል።
እዚህ ላይ ፋኖን ለመምከር የምፈልገው የኢትዮጵያ ፖለቲካ
ወዴት እያመራ እንደሆነ እያዩት ናቸው ብየ እገምታለሁ። የአማራ ፋኖዎች አጀንዳቸው ኢትዮጵያን ለማዳን ከሆነ በቂ ትምሕርትና ጥንቃቄ ወስደው ብቁ የሆኑ
ልምድ ያላቸው በሳላ የፖለቲካ መሪዎችን እንጂ በደመነብስ የሚነዱ የጠመንጃ አርበኞች ድርጅቱን እንዲመሩት መፍቀድ የለበትም። የዘመኑ
ፖለቲካ ከጠመንጃው የተለየ ረቂቅ ብስለተን ይጠይቃልና።
ያም ሆኖ አገራችን ዓለምንና የአለምን ፍርድ እጅቻው ወስጥ ባስገቡ ኃያላን በኩል ብዙ ግፍ ስለተፈጸመባት የምንጠብቀው የዓለም ፍርድ ሳይሆን የአምላክን ፍርድ ነው!
ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay አዘጋጅ
No comments:
Post a Comment