Sunday, August 18, 2024

እናውቃለን“ኖች” ሆይ! መልስ ለአለም አቀፍ የፋኖ አስተባባሪ ኮሚቴ ከጌታቸው ረዳ 8/18/24 ETHIOPIAN SEMAY

 

እናውቃለን“ኖች” ሆይ!

መልስ ለአለም አቀፍ የፋኖ አስተባባሪ ኮሚቴ

ከጌታቸው ረዳ

8/18/24

ETHIOPIAN SEMAY

ዶ/ር ጋሻው ካሴ ይባላል በውጭ አገር የዘመነ ካሴ ፋኖ ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አንዱ ነው።

እርሱና መሰሎቹ (ጌታቸው በየነ የተባለ ስም አጥፊም አብሮት አንዱ ነው) በሚያዘጋጁት ዩ ቱብ ላይ የእስክንድር ነጋን ታላቅ ተጋድሎ በማጠልሸት ስሙን በማኘክ የተጠመዱ ናቸው።

ስለ እስክንድር ታላቅነት ማጠልሸት በአገራችን

በአጼ ዘርአ ያዕቆብ ፤ በአጼ ምንሊከ ፤ በአጼ ኃይለስላሴ እና በመሳሰሉ ብዙ ነገሥታቶች እንዲሁም በአፍሪካ የነፃነት ታጋዮች በኔልሰን ማንዴላ፤ በንኩርማ በሉቡምባና በሙጋቤ በመሳስሉ መሪዎች ላይ እስካሁን ድረስ ስማቸውን በማጠልሸት የተጠመዱ ቡድኖችና ስዎች አሉ።

ስም ማጥፋት የተጀመረው የሰው ልጆች ባህሪ ቢሆንም እያደገ የመጣው ከ1928 ዓ.ም ንጉሱ በባለሞያዎቻቸው ግፊት ምክንያት ወደ ስደት ከሄዱ  ጀምሮ “የሸሸ ንጉሥ” እያሉ ስማቸውን ማጥፋት ነው። ከዚያ ጀምሮ ፈረንጆች “ታጊንግ” የሚሉት ኢትዮጵያዊያኖች “በንጹህ ሰው ላይ ስም መለጠፍ” “በአማራ ማሕበረሰብና በአማራ ነገሥታት” መልካም ስማቸው ላይ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥልጣን በወጡ ቡድኖችና በታዋቂ የፓርቲ መሪዎች የሚመራ ስም አጥፊ ክፍል ሕጋዊ መድረክ ተሰጥቶት የተለመደ ባህል ሆኖ ታሪክና አገር ሲጎድፍ ታዝበናል። አንድ ወዳጄ እንደነገረኝም “ብዙ ምሁራን ያንን ስም ማጠልሸትና ስድብ በመፍራት ወደ ትግሉ ላለመቀላቀል እንቅፋት ሆኖባቸው ዳር ተመልካች ሆነዋል” ሲል አጫውቶኛል። አሁን ደግሞ “ፋኖ” ከተመሰረተ በኋላ በባሰ መልኩ አድጓል።

ዶ/ር ጋሻው ካሴ ማስረጃ ሳያቀርብ እስክንድርን የአውሮጳ መንግሥታት እና የአሜሪካ መንግስት ቅጥረኛ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለወደፊቱ በሚመሰረተው አዲስ መንግስት የአሜሪካና አውሮጳ መንግስት ጥቅም ለማስጠበቅ የተላከ ፤ ለቅጥረኛነቱም ከአሜሪካ የስለላና መረጃ መ/ቤት በርከት ያለ ዶላር የተሰጠው ፣ መሆኑን “እናውቃለን” ይላል።

እዛው በዋሸበት ዩቱብ ላይ “እናውቃለን” ማስረጃ አይሆንም፤ አንተና ስም አጠልሺ ጓዶችሀ “እናውቃለን” የምትሉትን ሰነድ አምጣና አሳየን፤ ካልሆነ እንዲህ ያለ ስም ማጥፋት በዶከተሬት ማእርግ የምትጠራ ሰውየ በዚህ መንገድ መናገር ራስን ማስገመት ነውና ሰነዱን አሳየን ብየ ፃፍኩ። መልስ የለም።

የተባለው ማስረጃ ማቅረብ ሳይችል “እናውቃለን” በሚል የተለመደው የአበሻ “እናውቃለን” ስም ማጠልሸት ተምሮ ኢንዳልተማረ ማይምነትን ማሰራጨት ነውር ነው።

 ሰማሁት። እንዲህም ይላል።

<<እስከንድር ነጋ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ አሜሪካ መጥቶ የተገናኘው ሰው ከዚህ ከውጭ አገር የስለላ ስራ ግንኙነት ካለው ሰው (ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ማለቱ ነው) ጋር ነው። ከዚህ ሰውየ ጋር ሴራ ሲጎነጉኑ ቆይተው ቢቻል የምዕራባዉያኑን ዓለም ፍላጎት ሊያስፈጽም የሚችል አንድ ሌላ መንግስት ወደፊት እንዲመሰርት አስተዋፅኦ እንዲያደርግ በስተጀርባ  የተደረገ ስምምነት እንዳደረገ ፤ እርሱም በፋይናንስ በኩል ሊታገዝ እንደሚችል የተሰሩ ሴራዎች እንዳሉ እናውቃለን>> ይላል።

 “እናውቃለን!!!” እናንተ እናውቃለን’ኖች ሆይ ማስረጃ ላይ እንዴት ኮሰመናችሁ? እናውቃለን ማስረጃ ሳይሆን በማስረጃ ያልተደገፈ የመንደር ቡና ጠጪዎች ሐሜት ነው ብለን ማለፍ አይቻልም፡ ምክንያቱም ምሁራን ናችሁ ፤ ሆን ብላቸሁ የያን ሰው ስም ለማጠልሸት ሆን ብላችሁ ያደረጋችሁት ስም የማጥፋት ዘመቻ ነው። ካልሆነ ማስረጃውን ይፋ አድርጉት!

ጋሻው እንዲህም ይላል፤

እስክንድር አንድም ቀን “አማራ” የሚል ቃል ካንደበቱ ተናግሮ አያውቅም

ይህ ማይምነት አልገረማችሁም? አማራ የሚል ቃል? የመሁር ማይምነት ሲጎለብት እስከዚህ ድረስ ይወርዳል። የዶ/ር ጋሻው ካሴ ስም ሲነሳ የማውቀው ብዙ አመት ነው (በየትኛው ሚዲያ እንደሆነ በትክክል ባላውቅመ ምናልባት መላው አማራ ድርጅት (?) እስከዚህ ድረስ ይወርዳል ብየ አልገመትኩም።

የኔልሰን ማንዴላ ታሪክ የዚህ ይነት የውሸት ቡድን ደቡብ አፍሪካ በጥቁር ወጣት ክፍሎች ሲደመጥ አልፎ አልፎ ሲያናንቁት አድምጫለሁ። ፅንሰ ሀሳቡ ከብሩን የሚያጎድፍ አንድ ሰው እንኳን ቢነሳ እና በድህረ ገጽ ሲሰራጭ ብዙ ማይም ስላለ ገበያ አግኘቶ እያደገ ሲሄድ፣ ሌሎችም የውሸት ቡድኖች እየተበራክቱ የነበሩ የታጋዮቹ ታሪክና ትዝታዎች እጠፉና እየተበከሉ መጨረሻ ላይ የሚያስታውሳቸው አይኖርም።

የታጋዮችን ስም የሚያብጠለጥሉ ፋኖ ከተመሰረተ ወዲህ በርካታ የሃሳብ ድንክዎች መድረኩን ይዘውታል።

እስክንደርን ከአብይ አሕመድ የተላከ አድርገው ስሙን ከሚያጠፉትና “አማራ አይደለም ፤ጭምብል ያጠለቀ ባንዳ፡ እኔ ፓሊስ እስክንድር ሌባ እያለ በመፈረጅ ” ስሙን ከሚያጠለሸው በረቂቅ ዲፕሎማሲና ፖሊቲካ ያልበሰለ በጠመንጃና በጀሌ ብዛት ትዕግሥትና ጥበብ የሚጠይቅን የፓቲካው መድረክ የሚቆጣጠር የሚመስለው የመንደር ጎበዝ ሆኖ ለሱ የማይታዘዝ ፤ በራሱ አመራር ሥር ያልተስለፈ ሁሉ “አንጃ” የሚል ስም በመለጠፍ ታጣቂዎችን የሚያባርር ፤አፋኝና አስፈራሪው የጎጃሙ ዘመነ ካሴ ዋናውና አውራ ነው።

 ሰሞኑን ደግሞ “መረጃ ቲቪ” በሚባል ኢሳያስ አፈወርቂን ታላቁ የአመቱ ሰው እያለ ኢሳያስን ሲያሞካሽና ፎቶ አብሮት ሲነሳ የነበረው ኤልያስ ክፍሌ በሚራው ሳተላይት ቴ/ዥን በመድረክ ብቻውን ተዋናይ የሆነበት እንደ አስፈሪው "ኦይስተር (dragonfish)" አፉን ክፉኛ የሚቀድ እስክንድርን ስም ሲያጠፋ የሚውል አሁን አሁን በቅርቡ ስታዘበው ጤነኛ የማይመስለኝ በታጋይ እስከንደርንና በታጋይ መከታው ማሞ መልካም ስም ላይ ጥቅርሻ የሚቀባ ዘመድኩን በቀለ የተባለ ሰውየ የሚገለገልበት መረጃ ሳተላይትን እንዲደግፉ  ተክታዮቹን (ካልቶቹን) ጥሪ አስተላልፎ አድምጬው ዘመነ ገና ከዘመኑ ጋር የማይሄድ የሚጠላቸውን የሚሳደቡለት ሰዎች ሲሰማ የሚደሰት ጠብ ያልጠገበ የመንደር ጎረምሳ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።  

እርሱ ብቻ አይደለም። በውጭ አገር የሚኖሩ አጉራ ዘለል ባሕሪውን እንዲገፋበት “ግፋ በለው” እያሉ የሚያበረታቱት የዘመነ “አጨብጫቢዎችም” አሳምነው ጽጌን ያስገደለው እስከንድር ነው እስከማለትና ያለ ምንም ይሉኝታ ሚዲያ ላይ ሲወነጅሉት ከማየት ሌላ የዝቅተኛነትና የትንሽ ሰው መሆን ተምሳሌትነት ሌላ ምን ሊሆን ይችላል። 

ስም የማጥፋት ዘመቻቸው በእስክንድር ላይ ብቻ አልተወሰኑም። እዩኝ የማይል ድምጹ ምንም የማይሰማ በትግሉ ብቻ ያትኮረው የሸዋው ፋኖ ተዋጊዎች መሪና የእስክንድር የትግል ጓድ የሆነውን “መከታው” የሚባለውንም ሳይሳቀቁ ባንዳ” ይሉታል። የሚገርም ውንጀላ  ነው፡ አደለም እንዴ!!?

በሚገርም አነጋገር ከዘመነ ጀምሮ እስከ መሰሎቹ እስክንደርን “አስጠጋነው” ይላሉ። አንዳንዱም ከመከታው ጋር “ተጠለለ”፡ ሲሉ እሰማለሁ። እንዴት ነው ነገሩ? ማን ማንን ነው አስጠጊና ተጠጊ የሚሆነው? እንኳን እስከንድርን መሳይ ታላቁ አማራና ታላቁ ኢትዮጵያዊ ሰው አማራ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የአማራ ገጠሮችና ተራራዎች ሄዶ ሁለት ራሱም ቢሆን ጠመንጃ ይዞ ለኢትዮጵያም ይሁን ለአማራ በመረጠው የትግል መስመር መታገል መብቱ ነው። እንዴት ነው ነገሩ? ከመቸው ውዲህ ነው ካለ አማራ ሌላው ኢትዮጵያዊ አማራ መሬት ላይ መንቀሳቀስ አይችልም ወደ እሚል ወደ ወያኔነት መስመር ከመቼው ገባችሁ? እንዲህ የሚሉት ግን ወያኔ ያስተማራቸው ወጣቶች አማራ ለአማራ ብቻ የሚሉ ወጣትና ሽማግሌ የአማራ ትምክሕተኞች ምሁራን እንዲህ ያለ ናዚያዊ የባለቤትነት ቅዠት ውስጥ በመግባት አገራችንና አማራውን ተጨማሪ ችግር እያበራከታችሁበት እንደሆነ አይገባችሁም?

ስም ማጠሽት በነዚህ አላበቃም

መላውን ኢትዮጵያ አንቀሳቅሰው ወያኔን እርቃኑን ካስወለቁት አንዱ አርበኛው ኢትዮጵያዊው የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት ወይም “መአሕድ” ክዚያም “መኢአድ” ከዚያም የቅንጅት ሊቀመንበር የነብሩት ነብሳቸው ይማር “ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል” (1928 – 2009) “መአሕድ”ን ትተው (ለዚያም ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል) ከዚያም “መኢአድ” በመመስረታቸው ጸረ አማራ አድርገው እየሰደቡዋቸው ነው።

ኢንጂኔሩ በሚገርም ሁኔታ ዓለም የማይረሳው እንደ ትንታግ ተናጋሪው ልደቱ አያሌው እና እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የምሳሰሉት ታላላቅ ምሁራንን በመምራት ዓለም ያስገረመ፤ ወያኔን እንደ ደነገጠች በቅሎ ያስበረገገውን ትግል የመሩትን በማንኳሰስ “አማራ ያልሆነ ትግል” እያሉ ያንን መሳይ አስደናቂ ትግል ሲያጣጣሉት መስማት ያሳምማል።

የኚህን ታላቅ ሰው ስም እያጥፉት ያሉት የፋኖ ደጋፊዎችና ምሁራን “ተብየዎቹ” ናቸው።

በዚያ ሳይወሰኑ ሰዳቢዎቹ ሳያፍሩ ብዙ አሉባልታ ሲነዙባቸው እሰማለሁ። ደጋግሜ የምጠይቀው ጥያቄ ሊመልሱት ያልተቻላቸው ጥያቄየ ይህ ነው፡

 << እሺ “መአሕድ” ትተው “መኢአድ” በመመስረታቸው አማራው የሚታገልለት አጥቶ ለጥቃት ተጋለጠ ካላችሁ ‘እናንተ የማን ጎፈሬ ስታበጥሩ ጊዜ አጥታችሁ ነው አማራው ለጥቃት ሊጋለጥ የበቃው። በሳቸው ምትክ “መአሕድ” ን ማስቀጠል ያልቻላችሁበት ምከንያታችሁ ምንድ ነው? >>  መልስ የለም!!!

ጉረኛ ሁሉ ዛሬ በፋኖ ሙቀት ተጠልላችሁ ሲዋደቁና ታሪክ ሲሰሩ የነበሩትን አርበኞች ስማቸውን የምትወነጅሉ ሁላ ማን መሆናችሁ በመልክ በስም ባላውቃችሁም አድር ባይ ምቾት ፈላጊዎች ሚሊዮኖቻችሁ ይልቅ እኔው ትግሬ ወላጆቻችሁ ዘምዶቻችሁ እናቶቻችሁ በወያኔ ፤ በኦብነግና በኦነግ ሲታረዱና ሲበደሉ ብቻየን ስጮህላቸው ምድረ አጭበርባሪ  ጆሮህን ደፍነህ የነበርክ ሁላ ፤ አሁን በፋኖ ሙቀት ተጠልላችሁ ያልሆናችሁበትን ነን እያላችሁ የብርቅየ ኢትዮጵያ አርበኞችን ስም በማጥፋት ተጠምዳችሁ ሳይ ትገርሙኛላችሁ። 

ተጨማሪ ለአማራ ዘረኛ ብሔረተኞች ምክር

ፋኖ ከተመሰረተ ወዲህ ጎሰኛነት እያቆጠቆጠ መምጣቱን ባለፈው ሰሞን ጽሑፌ ጠቅሻለሁ። ወጣት አማራ ብሔረተኞች ሴቶችም ወንዶችም በማወቅ ወይንም ባለማወቅ አስጊ የሆነ ባሕሪ እያደመጥኩ ነው። በተለይ በአውሮጳ፤ ዓረብ አገሮችና አሜሪካ እንዲሁም ካናዳ ያሉ ወጣቶች!

በተለይ በየ “ቲክ ቶክ” ላይ በአማራ ትግል ክልሶችን አስወግዱ የምትሉ (የሸዋ ተወላጆች በተሰበሰቡበት “ልጅ ተድላ” በሚመራው መድረክ ላይ አጋጣሚ ተለጥፎ ዩ ቱብ ላይ ነው ያደመጥኩት፤እሱም ተናጋሪው እንዲታረም አላደረገም)፤ እንዲህ ያለ ነውር ተናጋሪዎችን መድረክ መንፈግ ይኖርባችኋል።

ዛሬ ደግሞ አዘጋጆቹ ማን እንደሆኑ ባላወቅም ዩ ቱብ ላይ ያደመጥኩት የብአዴን ወያኔ ታጋይ ከዚያም የብርሃኑ ነጋ ግንቦት 7 አባል የነበረ “ሳምሶን አበራ” (ሳሚ እያሉ ሲጠሩት ሰምቻለሁ “ብዙ ሳሚዎች አሉ ሳሙኤል፤ ሳምሶን ወዘተ….) የተባለ የዘመነ ካሴ ደጋፊ “አማራ ነህ ወይስ የትውልድ ሐረግሕ ከየት ነው ዘርዝር?” እያሉ ቃለ መጠይቅ ያደረገበት ቦታ ነው ፡ “እኔ ደርግ የገደለው የኢሕአፓ (?) የዶ/ር አበራ ልጅ በናቴ ደግሞ የደጃች ውቤ የልጅ ልጅ ነኝ” ይላቸዋል፡ በዚው አንድ ጽንፍ የረገጠ “አማራ” ነኝ የሚል ፋላሻዎችን፤ አገዎችን፤ ቅማንቶችን ወዘተ “ማሲንቆ መቺዎች” ከትግላችን መቀላቀል የለባቸውም የላል፡ አንዱዋም እንዲሁ ፋኖ “አማራነቱ የተረጋገጠ” ብቻ መታገል እንዳለበት “ከአማራ በቀር ሌሎች ኢትዮጵያዊያን” መፍቀድ እንደሌለባቸው በዘረኛ ሙቀት ትምበለበላለች። 

ፋኖ ከተከሰተ ወዲህ ወጣቱ ብቻ አይደለም ፡ ሽማግሌዎቹም አብደዋል። አንድ ትልቅ ስው ናቸው የት እንደሚኖሩ አላውቅም አይቻቸውም አላውቅም፡ ያንድ የ ዩ ቱብ ውይይት መድረክ አድሚን ናቸው። ታዲያ እኚሀ ሰው ምን ይላሉ “እስክንድር ባለበት ተፈልጎ መገደል አለበት፤ እኔ ራሴ ባገኘው እገድለዋለሁ፤ደግሞ አይቀርለትም” እያሉ ወጣቶቹን ይቀሰቅሳሉ፤ ወጣቶቹም “አብረው ንግግራቸውን  ያፀድቁላቸዋል”። ጽንፈኝነት በጥላቻ በበታችነት ስሜት በድንቁርናናቁጣ ማህጸን ውስጥ የሚያድግ መርዘኛ ባሕሪ ስለሆነ ሰውን በሰውነቱ ሳይሆን በብሔር መመዘንና መክነፍ ማረፊያው የት እንደሆነ ከናዚዎችና ከጣሊያኖች እንዲሁም ከወያኔና ክኦነጎች አረመኔ ክፋትና በአማራና በኢትዮጵያ ላይ ያደረሱብንን ታሪካዊ ፤ ሰብአዊ ፤ አካላዊ፤ መልክአ ምድራዊ ጥቃት ፤ የባሕልና የሞራል ብከላ እያዩ የአማራ ወጣቶች ከዚያ ብከላ መራቅ ካልቻሉ ምን እንደሚያስተምራቸው አላውቅም።

ጌታቸው ረዳ


No comments: