Tuesday, October 25, 2022

የወያኔ ጦር ጫሪነትና የኤርትራ ስጋት እውነታነት ከጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 10/25/22

 

የወያኔ ጦር ጫሪነትና የኤርትራ ስጋት እውነታነት 

ከጌታቸው ረዳ

(Ethiopian Semay) 10/25/22

 “አሁን ደግሞ ምነው የኢሳያስ ፕሮፓጋንዲሰት ሆንክ” እንደማትሉኝ ተስፋ አለኝ። በዚህ ሰነድ የማቀርበው እውነታው እንጂ ለማንም የሚወግን አይደለም።

ታስታውሱ ከሆነ ባለፈው ጽሑፌ ‘ቴድሮስ ጸጋዬ (ርዕዮት ሚዲያ) ኢሳያስ ጦሩን ወደ ትግራይ ያስገባበት ምክንያት ኢሳያስ “ፖቲካዊ ሕጽቦ” (የፖለቲካ አጣባ) መካሄድ አለብኝ ባለው መሰረት ጦሩን አስገብቶ የትግራይን ሕዝብ ለመጨፍጨፍ ፍላጎት ስለነበረው ነው በማለት ኢሳያስ  በትግራይ ላይ ጦርነት ከፍቷል፡ በማለት የተከራከረውን የትርጉም ስሕተቶች እኔ ወሸት እንደሆነ ለቴድሮስ መልስ ሰጥቼ እንደነበር ታስታውሳላችሁ። በዚህ መሰረት ይህ ክፍል ሁለት ነው።

ይህ ክፍል ሁለት የምንነጋገረው መምህርት መስከረም አበራ “ኤርትራ የራስዋ ስጋት ሳይኖራት አልቀረም” ብላ በመናገርዋ እነ ቴድሮስ ጸጋዬ ሲንጫጩባት ከርመዋል። መስከረም  ግን እውነት ነበራት።

ከጦርደነቱ በፊት ኤርትራ ከወያኔ የተሰነዘረባት ዛቻ እውነታ እንደነበረው በማስረጃ አቀርባለሁ።

ዛሬ የማቀርበው ሰነድ ከወያኔ ሰነድ ነው። ሰነዱ ጦርነቱ ከመነሳቱ በፊት በመስከረም 30/2013 መቀሌ ጥብቅ ምስጢር ብሎ ባሰራጨው 86 ገጽ ያለው ሰነድ ነው። የሰነዱ ርዕስ በአማርኛ በጻፈው መሰረት እንዲህ ይላል። (የትግል ልዩ ምዕራፍ እድገቶች እና የምከታችን ቀጣይ ስትራቴጂዎች፣ ስልቶች እና አቅጣጫዎች (ቁጥር - ሁለት) ሰነዱ ወደ ትግርኛም ተርጉሜዋለሁና ትግረኛውንም ይለጠፋል።

 ኤርትራን በሚመለከት እንዲህ ይላል።

2.3.7. ከኋላችንን የሚወጋንንም እንጠንቀቅ (ገጽ 64-66)

I.             በአጠቃላይ የኤርትራ ጉዳይ በተለይ ደግሞ የኢሳያስ ቡድን በቀጥታ ከምከታችን ጋር እና ከፍላጎታችን ባሻገር የሚዛመድ ነው፡፡ የዚህ ቡድን ፖለቲካዊ፣ ጸጥታዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ወዘተእንቅስቃሴዎቹ እኛ ላይ በተዘዋዋሪ ሳይሆን ቀጥተኛ እና ከባድ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ እጅግ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ የኢሳያስ ቡድን እና የአብይ ቡድን ተቀናጅተው በትግራይ ህዝብ ... ጉዳይ ስር የሰደደ ጥላቻ ይዞ ዳግም እንዳናንሰራራ ሊያጠፉን የሚያልሙ እና እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ መሆን ነው፡፡ ይህም የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁለቱም ስልጣናቸውን ማስቀጠል እና ብዛታቸውን ማስፋት ካለባቸው ይህ ድርጅት እና ህዝብ መጥፋት አለባቸው ብለው አቅደው እና ተመካክረው የጋራ እቅድ አውጥተው ነው በእኛ ተቃራኒ ቆመው እየገጠሙን የሚገኙት፡፡ ስለሆነም ይህ ስለታም የጥፋት ጫፍ ከአሀዳዊው እና ፍፁም ፀረ-ዲሞክራሲ ቡድን ብቻ ሳይሆን ከኢሳያስ ቡድንም ጭምር እንጂ፡፡ አንድ አንድ ጊዜ ለብቻው አንድ አንዴ ደግሞ ከደመኞቻችን / ጠላቶቻችን ጋር ተሻርኮ ፍላጎቱን እና አመለካከቱን የሚተገብርበት ክህሎት/ ችሎታ አጥቶ እንጂ እኛን ከዛሬ ነገ ለማጥፋት እንደተመኘ - እንደፎከረ ነው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ሀይሎች በተጨባጭ ህልውናችንን የሚፈታተኑ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ በመሆን ነው እየሰሩ የሚገኙት፡፡ የአብይ ቡድን ወድቆ የኢሳያስ ቡድን መዝለቅ/መቀጠል ድላችንን ከንቱ የሚያደርግ በተለመደው አዙሪት ከመዳከርም አንወጣም፡፡

 ስለሆነም የኢሳያስ ቡድን እድል እና እጣ እንዲሁ ከአብይ ቡድን እጣ ጋር አብሮ እንዲጓዝ የኢሳያስን ቡድን የሚያዳክም፣ የሚያፈራርስ ፈጣን፣ ተጨባጭ እና መጠነ ሰፊ እቅድ ይዘን እንስራ፡፡ አካሄዳችንን እንቀይር፡፡

(እዚህ ላይ ሰነዱ የሚያሳየው አንዱን ደምስሰህ አንዱን መተው ለኛ ስጋት ሰለሆነ አብይ እና ኢሳያስ አብረው መደምሰስ አለባቸው እያለ ነው)

II. የኢሳያስን ቡድን ከሞላ ጎደል ለማዳከም እና ለማፈራረስ የሚያስችል አሁንም ልክ እንደ ሀገራችን በሳል ነባራዊ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይህ ቡድን ሙሉ በሙሉ ከኤርትራ ህዝብ ተነጥሏል ሊባል ይችላል፡፡ ውለህ በሰላም ግባ የሚለው ህዝብ የለም፤ ተስፋ ቆርጠውበታል፡፡ በዚሁ ገዢ መደብ ውስጥም ግዙፍ ስንጥቃት ነው ያለው፡፡ በሰራዊት ውስጥም ከባታሊዮን አመራር በታች የሚገኙ የሰራዊቱ መኮንኖች እና ተራው አጋር/ እግረኛ እና ሰፊው ህዝብ በፀረ-ስርዓቱ አንድ አይነት አቋም አላቸው፡፡ ከብርጌድ አመራር በላይ የሚገኙትን በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች፣ እጥረቶች/ ድክመቶች እና በስለላ ጭምር እያስታመመ ለመያዝ እየሞከረ እንደሆነ ነው የሚገለፀው፡፡ የኤርትራ ህዝብ ወታደር ሆኖ መኖር አንገፍግፎት አሀዱዎቹን ከጠቅላላ መጠናቸው ሲሶ በማይበልጥ የሰው ሃይል ነው እየተጓዙ የሚገኙት፡፡ ይህንን ትልቅ ጉድለቱን ቋሚ/ነባር ሰራዊትን በማደራጀት ነው ለመሸፈን እየሞከረ የሚገኘው፡፡

እንደ አቅሙ 65 ዓመት በታች እድሜ ያላቸውን የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ የቋሚ/የነባር ሰራዊት አባል በማድረግ ነው ህልውናውን ለማሳየት እየሞከረ የሚገኘው፡፡ የኢሳያስ ቡድን የማቆያ ክር ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው የሰራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች፣ ሀገራዊ ደህንነት እና ስለላ እንዲሁም የሚከተለው አሰራር እና አደረጃጀት ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለፀው ሁሉም 65 አመት እና ከዚያ በታች እድሜ ያላቸው ቋሚ/ነባር ሰራዊት ብሎ በመስመር እና ጋንታ ውስጥ አስገብቶ - በሰራዊት ስም በንቁ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ/ ንቅናቄ እንዳይገባ አፍኖ ይዞታል፡፡ ከፍተኛ ጀነራሎችን እና የሀገር ደህንነት ስለላ አካላት ደግሞ በሙስና እና ጎጠኝነት እርስ በእርሳቸው እንዲጠባበቁ እና ኢሳያስን እንደ አዳኛቸው እንዲመለከቱት አድርጎ በፈጠረው ወጥመድ ነው እኩል በእኩል እያራመደው የሚገኘው፡፡ በዋናነት ደግሞ በሀገራችን የባሰውን የአመራር ክፍተት (ሁሉንም በራሴ የሚያስከትለውን ችግር/ሁኔታ) እንደ እድል ተጠቅሞ የኤርትራን ህዝብ በባርነት ቀንበር ስር አስገብቶ እኛን ለማጥፋት ሌት ተቀን እየባዘነ ይገኛል፡፡

III. ይህንን አጭር ጠቋሚ/ አመላካች ሁኔታን/ እውነታን መሰረት በማድረግ የኢሳያስን ቡድን ለማፈራረስ የሚያስችል እድል ሰፊ ነው፡፡ ስለሆነም ሁለት በጥብቅ የተያያዙ/ የተሳሰሩ የስራ እቅድ አቅጣጫዎችን ይዘን እንሰራበታለን፡፡

አንዱ፦ በኤርትራ የውስጥ አቅሞች ላይ ተመርኩዘን ኢሳያስን <<የሚገረስስ>> ተጨባጭ እና የተደራጀ እገዛ ማድረግ፡

 ሁለተኛው፦  የኢሳያስ ቡድን የዚሁ ይፋዊ ወረራ አካል ሆኖ በእኛ ላይ ጦርነት ካካሄደ ደግሞ በጦርነት የሚደመስስ ወታደራዊ ዝግጁነት እና ስትራቴጂን ይዘን ለመመከት መዘጋጀት፡፡

በኤርትራ የውስጥ አቅሞች ላይ ተመርኩዘን ማድረግ የሚገባን ተጨባጭ ድጋፍ በአንድ በኩል የጠላትን ድክመቶች ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያሸጋግር እና በሌላ በኩል ደግሞ የለውጥ ሀይሎች ተደራጅተው እንዳይነቃነቁ፣ እንዳይመክቱ ከባድ ክፍተት/ ጉድጓድ ሆኖ የሚገኘው የአመራር ችግር እንዲሁ ለመፍታት የሚያግዝ ወጥመዶችን የሚበጣጥስ እንዲሆን ማድረግ፡፡

ወጣም ወረደ ግን <<የኢሳያስን ቡድን ማፈራረስ ማዕከል ያደረገ ውሳኔን ይዘን ራሱን የቻለ ስትራቴጂ እና አቅም እንዲዘጋጅለት፣ ይህንን የሚመራ እና የሚያስተዳድር አደረጃጀት እንዲፈጠር፣ አካባቢውን እና ስራውን የሚያውቅ በቂ የሰው ሃይል እንዲመደብ፣ አቅማችን የፈቀደውን ያህል የፋይናንስ እና ማቴሪያል ከፍ ለማድረግ>>

ለመጨመር በሁሉም ረገድ በህዝብ፣ በድርጅቶች፣ በሰራዊት፣ ሚዲያ እና አክቲቪስቶች እንዲሁም በውስጥም ሆነ በውጪ (የይብቃ/ ይአክል/ ህዝባዊ ንቅናቄ) ወዘተአስተባብረን የኢሳያስን ቡድንንም እንገረስሳለን”፡፡

ከፊት ከፊታችንም ከኋላችንም (ጀርባችንን) “ነፃ እናወጣለን”፣ ምከታችንን መጪው / የወደፊት ጊዜ ጉዞ ዋስትናው የተረጋገጠ እንዲሆን ሁኔታዎችን ማስተካከል፡፡ እንችላለን ጎበዝ ደል ንሳ መሪ ድርጅታችን ... ምን ይሳነዋል !! 

ምንጭ - (የትግል ልዩ ምዕራፍ እድገቶች እና የምከታችን ቀጣይ ስትራቴጂዎች፣ ስልቶች እና አቅጣጫዎች (ቁጥር - ሁለት) በጥብቅ የሚያዝ ... /ቤት

መስከረም 30/2013.  መቐለ 2 )

አመሰግናለሁ!

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 10/25/22

 

No comments: