Sunday, October 30, 2022

ኤርትራ ወደ ትግራይ ጦርነት ጣልቃ መግባትዋን በሚመለከት ያለኝ አስተያየት ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay 10/30/22

 

ኤርትራ ወደ ትግራይ ጦርነት ጣልቃ መግባትዋን በሚመለከት ያለኝ አስተያየት

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay

10/30/22

ስለ መስከረም አበራ እና ስለ ልደቱ አያሌው ክርክር አንስቼ ትናንት በለጠፍኩት ጽሑፍ ላይ ተሞርኩዛችሁ  ስለ ኤርትራ በትግራይ ጦርነት መሳተፉ “ኤርትራ የፈለገው ስጋት ይኑራት ጸረ ሉኣላዊነት አይደለም ወይ?” ብላችሁ በውስጥ መስመር ለጠየቃችሁኝ ሰዎች እዚህ ላይ አንባቢዎቼንም እንዲያውቁት በይፋ ልመልስ።

ስለ ኤርትራ ጦር ወደ ትግራይ መግባቱ መልሴ እንዲህ ነው፡

 አውሮጳ ውስጥ በታወቀ አለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ዓለም አቀፍ የሕግ ትምህርት ፕሮፌሰር (መምህር) ነው፡ ባጋጣሚ ሰሞኑን በስልክ ስናወራ ይህ ጉዳይ አንስተን ስንወያይ የነገረኝን ላካፍላችሁ፡

እንዲህ ይላል፡

“እንደምታውቀው እኔ የማስተምረው የሕግ ትምህርት ነው፤ የማስተምራቸው ተማሪዎች ለፒ ኤች ዲ ዲግሪ ደረጃ ነው። አንዲት አገር የውስጥ ወታደሮቿ ተናግተውባት ሉአላዊነትዋ ሲነጋ እና የተከፈተባት የውስጥም ሆነ የውጭ ሃይል መቋቋም ካልቻለች፤ ወዳጄ ብላ የምታምነው ጎረቤት አገርም ሆነ ማንም ወዳጅ የምትለው  አገር ጋብዛ እገዛ እንዲደረግላት ጣልቃ የማስገባት  አለም አቀፍ ሕግ መብት አላት።ይህም “Intervention by invitation ( የጣልቃ ገብነት ግብዣ)” ይባላል። በዚህ በኩል አንድ ሕጋዊ ሰነድ እልክልሃለሁ” >> ሲል ነግሮኛል።

የራሴን ለመጠቀስ ደግሞ ከስምምነታቸው አንዱ እዚህ ላይ ኤርትራና ኢትዮጵያ ይፋ እና ይፋ ያልተደረጉ ምጣኔ ሃብታዊ እና ወታደራዊ ስምምነቶች (ፓክት) አድርገው ስለሚችሉ (መብትም ስላላቸው) ባእድ ጦር ገባ ተብሎ የኤርትራን ወደ ትግራይ ጣልቃ መግባት መጥቀስ አይቻልም። እዚህ ላይ እኔ አብይ አሕመድ ብሆን ይህን ከመጥቀስ የሚቸግረኝ አይሆንም ነበር። ችግሩ አብይ አሕመድ ሲቀላምድ ወዲያ ወዲህ እያለ ሲቅለሰለስ መስመሩን ግልጽ ባለማድረጉ ወያኔና አለም ኢምፔሪያሊስቶች ሲንጫጩበትን ሲያስፈራሩት እየሰማን ነው።

አሜሪካ የትኛው ሕግ ፈቅዶላት ነው ወደ ኢራቅ ገብታ ኢራቅን ዶጋ አመድ ያደረገቺው? ያውም የተባበሩት መንግሥታት አንፈቅድልህም እያሉት አደለም “ቡሽ” ወደ ኢራቅ ሄዶ “መሪዋን አንቆ፤ገድሎ” አገሪቷን ወደ ድንጋይ ዘመን የቀየራት? ይህ አጉራዘለልነት እንደ ህግ ከተቆጠረ፤ 70 ከመቶ የሚባለው ጦርዋን በውስጥ ጠላት ዶጋ አመድ ሲሆን፤አገሪቷ መከላከያዋ ሲዳከም፤ ጎረቤት የምትለውን አገር ጠርታ የጋራ “ኦፔረሽን” ማድረግ የሚያግዳትስ የትኛው ሕግ ነው? ወታደራዊም ሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ወይንም ኣካባቢያዊ ስምምነቶች የመስማማት ወይም፣ የማቋረጥ የግድ  < የተባበሩት መንግሥታት የተባለው  የኢምፔሪያሊሰት አሜሪካና እንግሊዝ ፈረንሳይና ጀርመን አገሮች>  መፈንጫ የሆነው ይህ የጉልበተኞች ተቋም አገሮች የጋራ ስምምነታቸውን ለመስማማት ወይንም ስለማቋረጣቸው ለማሳወቅ አይገደዱም። የኢሳያስ ንግግር ካደመጣችሁት አስመራ ውስጥ አብይን ጋብዞ ሲያነጋገር ማንኛወንም ችግር ሲገጥምህ ከጎንህ ሆነን እንረዳሃለን አብረን እንወጣዋለን ሲል ስምምነቱን ይፋ አድርጎ መናገሩን ታስታውሳላችሁ፡ አደለም እንዴ?

የኤርትራ ጦር ትግራይ ገብቶ ወንጀል ሰርቷል ከተባለ ደግሞ ልክ እንደ ኢትዮጵያ ወታደሮች አለም አቀፍ የጦር ሕግ ከጣሱ ይከሰ

ሳሉ። ከዚህ ሌላ “ሉአላዊ ተጣሰ” የሚለው መንጫጫት የአብይ አሕመድ መቅለስለስ ወዲያ ወዲህ ማለት ካልሆነ እንደ ትልቅ መከራከሪያ ተደርጎ ጎልቶ የሚነገርበት ክርክር ከላይ በጠቀስኩት ምክንያቶች አያስኬድም።

አመሰግናለሁ።

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

Thursday, October 27, 2022

የመስከረምና የልደቱ ውይይት የሞገስ አብሻቂ ጣልቃ ገብነት ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 10/27/22


የመስከረምና የልደቱ ውይይት የሞገስ አብሻቂ ጣልቃ ገብነት

ጌታቸው ረዳ

(Ethiopian Semay)

10/27/22

በልደቱ ላይ እንደምታውቁት ብዙም ትችት አላበዛም ነበር። የተቸሁት ጊዜ ከብዙ አማታት በፊት ወያኔ የደርግ ባለሥልጣናትን ስያስር እኩል ፍትሕ ለመስጠት ኢህአፓንም ማሰር ነበረበት ሲል በመናገሩ፤ ወቅሼዋለሁ። ለመውቀሴ መነሻ ለምን ኢሕአፓ አይታሰርም አለ በሚል ሳይሆን፤ ወያኔ ታሰሪ መሆን የነበረበት እንጂ ፍትሓዊ የሆነ ፍትሕ አስፋኝ አድርጎ በማየቱ እጅግ ተገርሜ ተችቼዋለሁ። ወያኔ ደርግ ብሎ ያለ ሃጥያታቸው አስሮ ብዙ አመት ካሰቃያቸው በኋ ላ በነፃ የለቀቃቸው ስላሉ ፍትሕ የተመረኮዘ አልነበረምና ልደቱን ወያኔን አሳሪና ፍትሕ አንጋሽ አስመሰሎ በማቅረቡ ወያኔነት ነው ብየ ተችቼዋለሁ። 

በተረፈ በድጋፍም እንዲሁ እንግሊዝ አገር ለስብሳባ ሄዶ ተቃዋሚዎቹ አላናገር ብለው ሲንጫጩበት ክፉኛ ወቅሼአቸዋለሁ ። ምክንያቱም ልደቱ “ሃሳብ ካላችሁ በሃሳብ እንወያይ እና አናግሩኝ እያለ በጨዋ መልክ ሲለምናቸው ጨርቃቸው ጥለው አብደው አላናገር ስላሉት የመናገር እና መልስ የመስጠት መብቱን መጣስ የራሳቸው ድንቁርና ማንጸባረቃቸው አልወደድኩተምና ልደቱን ደግፌ ተችቼአቸዋለሁ።

በሌላ ትችቴም ልደቱ እንግሊዝ አገር ለትምህርት ይሁን ለፖለቲካ “ኦሬንተሽን/ኮርስ (?)” ተጋብዞ ሄዶ እያለ፤ ድንገት መለስ ዜናዊ በሞት ሲለይ፤ ልደቱ ኩፉኛ አዝኖ ባደረገው የቃለ መጠይቅ ይሁን ያስተላለፈው የሃዘን መግለጫ  ልክ ያሬድ ጥበቡ እንዳለው አይነት “ኢትዮጵያ/አገሪቷ ታላቅ ሰው አጣች” ሲል ሰምቼው ክፉኛ ተችቼዋለሁ። ኢትዮጵያን ለዘላለሙ የባሕር በር ያሳጣት፤ በዚህ ምክንያት በእስላማዊ አገር ጎረቤቶች ቢሊዮኖች ብር እየከፈለች “ወደብ ክራይ  ልመና” በጠላቶችዋ እጅ እንድትወድቅ ያደረገ ሰውና “የባንቱስታ’ አፓርታይድ አስተዳደር የመሰረተልን አደገኛ “የሙሶሎኒ ተግባር አስፈጻሚው ትንሹ ሰው መለስ ዜናዊ” እንደ ታላቅ ሰው ፈርጆ ለሕዝብ ማስተማሩ ክፉኛ ተችቼዋለሁ።

በቅርቡም እሱን በመደገፍ ደግሞ በዘመነ ኦሮሙማው መሪ በአብይ አሕመድ በግፍ ሲታሰር እዚህ ፌስቡክ እና በድረገጼ ላይ፤

<< በኢሳያስ አፈወርቂ  ትዕዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ተወካይ በሆነው በአብይ አሕመድ ዓሊ ተባባሪነት ኢትዮጵያዊ ትንታጉን ልደቱ አያሌውን አስሮ እያሰቃየው ነው! ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) Saturday, July 25, 2020>>

በሚል ርዕስ መታሰሩን ተቃውሜአለሁ።

ይህ ካልኩኝ ዘንድ በቅርቡ ስለ ትግራይ አስመልክቶ እየሰጠው ያለው ትንታኔ አልወደድከለትም። ትናንት የመስከረም እና የልደቱን ውይይት አደምጥኩ። ልደቱ የሰጣቸው ክርክሮች ከተቻለ ሌላ ቀን እመለሳለሁ። በዛው ላይ ጊዜ አልፈጅም። ምክንያቱም መስከረም በሚያስደንቅ በቂ መልስ ሰለሰጠችበት። ልደቱ ያልጠበቀው ትንታግ ተከራካሪ ስለገጠመው “ፍራስትሬትድ መሆኑን” በቁጣውና በገጽታው ያስታወቅበታል።

የመስከረም አበራ እና የልደቱ አያሌው ክርክር የተካሄደበት የውይይታቸው ቦታ “የሃሳብ ገበታ” በሚባል (Buffet of ideas) የሕግ ምሁር በሆነው የኢሳቱ ሞገስ ዘውዱ ተሾመ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው።

አንድ ቀን ሲያመች ይህንን አስመልክቶ ስለ ልደቱ የምመለስበት ብሆንም፤ እጅግ የገረመኝ የልደቱ አብሻቂ ንግግሩን እና የመስከረም አበራ መልስ አንዲት ነጥብ ላስታውሳችሁ እና ወደ ሞገስ እገባለሁ።

ልደቱ ስለ ኤርትራ ተዋጊ ሃይሎች ወደ ትግራይ ስለመግባት ካነሳቸው ነጥቦች አንዱ እንዲህ  ይላል።

“ከውዝ የለውም” “ንብረት ለመዝረፍ የትግራይ ሴቶችን ለመድፈር ብሎ ነው የገባው” ሲል ይከራከራትና መስከረም ደግሞ “ሻዕቢያ ወደ ጦርነቱ የገባው “የራሱ ስጋት/ከውዝ/ ስለነበረው እንጂ የትግራይን ሕዝብ እጎዳለሁ የትግራይ ሴት እደፍራለሁ ብሎ ከመነሻው እንደ አላማ አልመጣም ብየ እገምታለሁ።” ስትል በማከልም፤ “አለመታደል ሆኖ ስለ ሴቶች መደፈር ደግሞ በጦርነት ላይ የሚከሰት ክስተት ነው” ብላ በማለትዋም  ልደቱ ደግሞ “የትግራይ ሴቶች የተደፈሩት የትግራይን ሕዝብ ላለመጉዳት ስለተፈለገ ነው?” እያለ “የጀነሳይድ ደጋፊ እንደሆነችና የሴቶችን መደፈር ግድ አንደማይላት ለማሳየት አጉል ሲባትል “እንድትሸማቀቅ” ሲዳክር  መስማቴ ገርሞኛል።

ወደ መጎስ ከመሄዴ በፊት ላንባቢዎች ይህንን ላጥራላችሁ።

ጦርነት ሲካሄድ እንደ ናዚ እና እንደ ወያኔ መሪዎች ዓላማ ተይዞ በጽሑፍ በሰነድ የተደገፈ የዘር ማጥፋት ውግያ ሲካሄድ “ሆን ተብሎ ነው” የሚል ክርክር ማካሄድ ይቻላል። ወያኔ በአማራ ላይ ያደረሰው የሴቶችና የንብረት ዝርፊያ በሰነድ አስደግፎ አገሪቷን አፈርሳለሁ ብሎ አማራን ሰላም እነሳዋለሁ ብሎ በተደጋጋሚ የቆዩ ያልተሰረዙ ዛሬም ህያው የሆኑ ሰነዶቹ ይመሰክራሉ።

በቅርቡም "የአማራ አገር እና ስሪት" የሚላትን "ኢትዮጵያ" በከርሰ መቃብር

 ላይ ብርሃን የሞላባት ያደገች ሃገረ ትግራይ እመሰርታለሁ ብሎ  በመስከረም 30 በ2013 ዓ.ም ወያኔ ከመቀሌ ጽ/ቤቱ የዘረጋው ባለ 86 ገጽ ሰነድ ባለፈው ሰሞን የለጠፍኩላችሁን የጦርነት ሰነድና አላማው አንብቡት። 

በተጨማሪም ተዋጊዎቹ በመመሪያ የተሰጣቸው የድርጅታቸው አማራን እያሳደድክ አጥፋው የሚለውን ይፋ የሆነው በለጠፍኩት “እባቦቹ የሚተፉት ምራቅ! ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 10/13/22 የሚለውን አስታውሱ።

እንዲህ ይላል፤

ትግርኛው ግጥም

 <<“ጎበዝ ተዓወት ተጋዳለይ ትግራይ

 አርኪብካ በሎ ነዚ ዓሻ አምሓራይ “>>

አማርኛው ትርጉም፡

<<ጎበዙ የትግራይ ታጋይ ሆይ

ድሉ ያንተው ይሁን እያንበረርክ በለው ያንን ሞኝ አማሃራ (ይ)>>

የሚለው ተዋጊዎቹ እየጨፈሩ የሚያሳየው ቪዲዮና እንዲሁም ፤

<<አማራውን “በእናታችሁ በቃኝ” አሰኘነው! ይላል የትግሬው ሩዋንዳ ሁታዊው  ኢንተርሃሙዌው የሙዚቃ ቡድን! ጌታቸው ረዳ ( Ethiopian Semay) 9/19/22 >>

የሚለውን የለጠፍኩትን በዚህ በጦርነቱ መሃል እየጨፈሩ በፖሊሲ ደረጃ አማራን ለማጥፋትና ለመጉዳት እንደተነሱ በርዕሱ የጠቀስኳቸውን ቪዲዮ የሁለት ሳምንት ማስረጃዎችን መልሳችሁ ጎብኝዋቸው።

የወያኔ ሙርከኞች የሚናገሩት ዘራፊዎች፤ሴት ደፋሪዎች፤ ቤት አቃጣዮች፤ ረሻኞች በየምድብ በመሪዎች ትዕዛዝ እንደተመደቡ ተናግረዋል። አንዱ ደፋሪም እኔ አንዱ ደፋሪ ነበርኩ ሲል ኑዛዜውን ይናገራል። ባይናገሩም ቪዲዮዎቻቸውን ማየት ነው።

ከዚህ አያይዤ ብዙ ሰዎች ልደቱ አያሌውን ጨምሮ ስለ ተረሸኑት የትግራይ ወጣቶች እያለ የሚከራከረው ክርክር (“በእርግጠኛነት እንደተደረገ ያምንና ፤ እንደገና በገለልተኛ እስኪጣራ እያለ ጥርጣሬ እንዳለው ደግሞ ያማላክታል) እንመልከት።

የልደቱ እና የቴድሮስ ጸጋዬ ክርክር ኢሳያስ ወደ ትግራይ የገባው “ፖለቲካዊ አጠባ ለማካሄድ ወደ ትግራይ እዘምታለሁ” ባለው መሰረት ነው የገባው ሲሉ ያልተባለውን ትርጉም ተርጉመው እንደተከራከሩበት ባለፈው ለቴድሮስ ጸጋዬ (ርዕዮት) በሰጠሁት ትችት የኢሳያስ ትክከለኛ ቅጂ ትርጉም የለጠፍኩትን ሰነድ በዚህ ፌስቡክ ፈልጋችሁ ተመለክቱ (በቅርብ ነው የተለጠፍኩት) እንዲህ ይላል  << ቴድሮስ ፀጋዬ መስከረም አበራን ለመሞገት የኢሳያስ አፈወርቂን የትግርኛ ንግግር ለምን ማጣመም አስፈለገው?

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 10/9/2022። የሚል አንብቡት

ልደቱ ትግርኛ አያውቅም፤ ቴድሮስ ጸጋየም እንዲሁ ይናገራል እንጂ ጥልቅ የትግረኛ ትርጉም አቅም የለውም። በስማ በለው የሰሙትን ተርጉመው ሲከራከሩ መስማት ልደቱ ምን ያህል እንደታጠበ አመላካች ነው። ያንን ልተውና፡

ለምሳሌ ወያኔ የኢትዮጵያ ወታደሮች ትግራይ ውስጥ ገብተው “ማህበረ ዴጎይ” (የአክሱም ገጠር ወረዳ) ውስጥ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ወጣቶች እየተረሸኑ ወደ ገደል ሲጣሉ በቪዲዮ ሲያሳይ፤ ግድያወን የፈጸሙ ወታደሮች የተባሉት በወያኔ እጅ ሲወድቁ ከመቀሌ  እስር ቤት ያደረጉት ቃለ መጠይቅ እዚህ ፌስቡኬ ላይ ለጥፌዋለሁ <<፡አክሱም ማሕበረ ዴጎይ የተፈጸመውምንድነው? ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay 9/30/2022>>፡የሚለውን እሱንም በዚህ ፌስቡክ ላይ ደግማችሁ ተመልከቱት 

ወታደሮቹ ሲረሽኑ ከመንግሥት የተሰጣቸው ትእዛዝ ሳይሆን ይልቁኑ አንድ ሰው እንዳታንገላቱ እንዳትረሽኑ” ተብለው ከመአከላዊ መንግሥት ጦር ማዘዣ ስምሪት ለያንዳንዱ ሰራዊት የተላላፈውን የደብዳቤ መልእክት ወደ ጎን በመተው የበታች አዛዦች ያደረጉት ወንጀል እንደሆነ እራሳቸው ወያኔዎች ባስተላለፉት የቃለ መጠይቅ የቪዲዮ ያሳያል።

አምሳለቃ (ሳርጀንት) ኢብሳ ተረፋ ይባላል፡ በመግደል የተሳተፈና አዛዥና ታዛዥም የነበረ ነው። እንዲህ ይላል፡_

<< ንፁሃን ዜጎችን እንዳትገድሉ። ሰላማዊ ንጹህ ዜጎችን መግደል የለባችሁም፡ እንዳትገድሉ” የሚል መመሪያ ከበላይ በራሪ በደብዳቤዎች በየክፍለ ጦሩ ተላልፏል። ሆኖም በቅርብ አዛዦቻችን ምክንያት ተግባራዊ አልሆነም። እኔ ሦስት ሰዎች እንዲገደሉ አዝዣለሁ፤ እኔ እራሴም ሁለት ሰዎች ገድያለሁ።”

 በማለት ሰው በመግደልና ቤቶችን በማቃጠል የተሳተፉት እነዚህ ወታደሮች ከላይ የተላለፈውን የደብዳቤ ትዕዛዝና መመሪያ በመጣስ በሕዝብ ላይ ወንጀል ፈጽመዋል። ስለዚህ በፍርድ ስንመለከተው በመንግሥት የተላለፈ ትዕዛዝ ሳይሆን ከታች ያሉት ወንጀል ሰሪዎች ሃላፊነትን ይወስዳሉ።

ስለዚህ መስከረም የተከራከረቺበት መንገድ “አንድ አገር ወደ ጦርነት ሲገባ ኮውዝ (ስጋት) ይዞ እንጂ በመመሪያ ሴቶችን ልደፍር ነው ብሎ አይገባም” “ሴቶች ሲደፈሩ ደግሞ አለመታደል ሆኖ ጦርነት ውስጥ የሚከሰት የጦርነት አንዱ ባህሪ ነው” የምትለው የጦርነት ምንነት ከገባው ተመራማሪ ሰው የሚነገር ትክክለኛ ክርክር ነው። ልደቱ ግን “በመስከረም ላይ ጠባሳ ለመጣል ጎል ሊያስቆጥርና  በመጥፎ እንድትታይ መሞከሩ ብልህ ብየ ስቆጥረው ከነበረ ፖለቲከኛ ወደ ታች ወርዶ ሳየው ያልጠበቅኩት ነበር።

አሁን ወደ ሞገስ ልግባ።

አወያዩ ወደ ኋላ ተሻለው እንጂ መጀመሪያ አካባቢ በመስከረም አበራ ላይ ያሳየው ጣልቃ ገብነት/አደናቃፊነት/ ጭራሽ ነበር ያበሳጨኝ። ስለዚህም በማግስቱ ትችት ለመጻፍ ፈለግኩና እስኪ ለዛሬ ልልፈው ብየ ተውኩት። ግን ደግሜ ሳደምጠው በዚህ ቪዲዮ የምትመለከቱት አጭር የመስከረም አበራ “ደጋግማ የምሬት ብስጭት” ያሳየቺው የሁለቱ ልደቱና የሞገስ አላናግር ብለዋት ሊረባረቡባት ሲሞክሩ “የምታሰማው ቅሬታ” ሳደምጥ አላስችል አለኝና በሁለቱም ላይ “ብልጭ የሚል የንዴት ስሜት ተሰማኝ። እነሆ ቀርብኩ።

በኦነግና በወያኔ የተደረገው የስምምነት ውል አማራን ለመጨፍጨፍ እንደሆነ እየታወቀ የሕግ አዋቂውና ተንታኝ አቶ ሞገስ ጣልቃ ገብቶ፤ ሃሳብዋን ሲያደናቅፍ መልሶ በሌላው ወቅት “ፋክችዋል ኤረር” በሚል ሰበብ  ሃሳቦችዋን ሁሉ እንዲሰናከል አድርጓል። መስከረም ደግሞ “አረ እባካችሁ ይህ አሁን ፋክችዋል ኤረር ነው? እሺ በናንተው መንገድ ለመሄድ “እሺ” ፋክችዋል ኤረር ነው ልበልና “እሺ” ካልኩ በኋላ ለምን አታቆሙም/ ስትል ማን ትዝ አለቺኝ “አስቴር በዳኔ” ። ኑ ገበያ በተባለው ሰለሞን ሹምየ በሚያወያው መድረክ ላይ አንድ ሴት አስቴር ብቻ ነበረችና እማሃል ወንዶች ሆና  "ብሄርሽ ምንድነው?" የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡላት እስዋም ጥያቄውን ለማብራራት ስትሞክር ከግራም ከቀኝም እያዋከቡ አላናግር ሲልዋት “እንዴ እናንተ ወንዶች ስትባሉ ሴትን አላናግር የሚለው አመላችሁ ምነው አታቆሙም አናግሩኝ እንጂ..?” እያለች ምርር ብላ ስትናገር ዛሬ ደግሞ የመሲ ምሬት አስቴር በዳኔን አስታወሰኝ።

አወያይው ማድረግ የነበረበት፤ ጠያቂዎች ለመጠየቅ በሰሌዳው ላይ ከሚጽፍዋቸው ጥያቄች መርጦ አጭር የድምጽ ጥያቄ አቅርቡ ብሎ ዕድል ከመስጠት ይልቅ  ሞገስ ጣልቃ እየገባ ለማደናቀፉ የሰጠው ምክንያት ደግሞ ሰዎች ሲናገሩ ያልሰማነው << ሰዎች የጠየቁት ነው>> እያለ ማምለጫ መፈለጉ አትኩራ ሃሳብዋን እንዳትሰጥ ማደናቀፍ አልነበረበትም (የጠያቂዎች መሆኑን በምን እናረጋግጥ?)።  “ኦነግና የወያኔ የስምመንት ውል” አማራን ለማጥፋት እንደሆነ እየታወቀ ነገር ግን “ወጣት ሞገስ በጸጉር ስንጠቃ ሊሞግታት” መሞከሩ አልወደድኩትም።

መስከረም “እሺ” ስላችሁ ለምን አታናግሩኝም እያለች ሁለቱንም ስትማጸናቸው በሚገርም ሁኔታ እንደገና አዋያዩ አቶ ሞጎስ ዘውዱ  ተመልሶ ይመጣና፤ ስለ ኦነግ ሰራዊትና ስለ ወያኔ ስምምነት ጥልቅ ትንታኔ ለመስጠት ስትሄድ ጣልቃ ገብቶ የሕግ ባለሞያነት ነገር ሆኖበት መሰለኝ፤ ስለ ኦነግና ወያኔ ሰምምነት “ጸጉር ስንጠቃ” ገብቶ ሲያደናግራት ይደመጣል።

<< እኔም ጣልቃ ልግባና..” ሲል መስከረም ድግሞ “ሁለታችሁም ጣልቃ እየገባችሁ እየረበሻሁኝ ነው” እያለች ምሬትዋን ስትገልጽ “መጎስ ወደ መጨረሻ አካባቢ ከሕዝብ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን አቀርባለሁ ያለውን ረስቶ  የራሱን ሕግ በመጣስ እመሃል ንግግረዋ ላይ እንዲህ ይላል፤-

“የእኔ ሃሳብ እኮ መስኪ! ፤ መስኪ! የሕዝብ ጥያቄ ነው እየጠየቅኩሽ ያለሁት ፤የሕዝብ ጥያቄ ነው እያቀረብኩ ያለሁት፤ “ኢምፓክቱ……እያለ” ትንተና ውስጥ በመግባት ወደ መጨረሻ የሕዝብ ጥያቄዎችን አቀርባለሁ ያለውን ንግግሩን ዘንግቶ (ባለመዋቅ ነው እላለሁ) ሲያበሳጫት የልደቱን እንዳይበቃት የመጎስ አደናጋሪነት ተጨምሮበት “ጉንፋን በያዛት የሰውነት ድካም” ላይ ሲጨመርበት ለመቋቋም ያሳየቺው ጥንካሬዋን አደነቅኩ።

ፅሑፉን ሌላውን ለማሳወቅ መቀባበል “ሼር” ማድረግ ትችላላችሁ

ጨርሻለሁ

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ  Ethiopian semay

Tuesday, October 25, 2022

የወያኔ ጦር ጫሪነትና የኤርትራ ስጋት እውነታነት ከጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 10/25/22

 

የወያኔ ጦር ጫሪነትና የኤርትራ ስጋት እውነታነት 

ከጌታቸው ረዳ

(Ethiopian Semay) 10/25/22

 “አሁን ደግሞ ምነው የኢሳያስ ፕሮፓጋንዲሰት ሆንክ” እንደማትሉኝ ተስፋ አለኝ። በዚህ ሰነድ የማቀርበው እውነታው እንጂ ለማንም የሚወግን አይደለም።

ታስታውሱ ከሆነ ባለፈው ጽሑፌ ‘ቴድሮስ ጸጋዬ (ርዕዮት ሚዲያ) ኢሳያስ ጦሩን ወደ ትግራይ ያስገባበት ምክንያት ኢሳያስ “ፖቲካዊ ሕጽቦ” (የፖለቲካ አጣባ) መካሄድ አለብኝ ባለው መሰረት ጦሩን አስገብቶ የትግራይን ሕዝብ ለመጨፍጨፍ ፍላጎት ስለነበረው ነው በማለት ኢሳያስ  በትግራይ ላይ ጦርነት ከፍቷል፡ በማለት የተከራከረውን የትርጉም ስሕተቶች እኔ ወሸት እንደሆነ ለቴድሮስ መልስ ሰጥቼ እንደነበር ታስታውሳላችሁ። በዚህ መሰረት ይህ ክፍል ሁለት ነው።

ይህ ክፍል ሁለት የምንነጋገረው መምህርት መስከረም አበራ “ኤርትራ የራስዋ ስጋት ሳይኖራት አልቀረም” ብላ በመናገርዋ እነ ቴድሮስ ጸጋዬ ሲንጫጩባት ከርመዋል። መስከረም  ግን እውነት ነበራት።

ከጦርደነቱ በፊት ኤርትራ ከወያኔ የተሰነዘረባት ዛቻ እውነታ እንደነበረው በማስረጃ አቀርባለሁ።

ዛሬ የማቀርበው ሰነድ ከወያኔ ሰነድ ነው። ሰነዱ ጦርነቱ ከመነሳቱ በፊት በመስከረም 30/2013 መቀሌ ጥብቅ ምስጢር ብሎ ባሰራጨው 86 ገጽ ያለው ሰነድ ነው። የሰነዱ ርዕስ በአማርኛ በጻፈው መሰረት እንዲህ ይላል። (የትግል ልዩ ምዕራፍ እድገቶች እና የምከታችን ቀጣይ ስትራቴጂዎች፣ ስልቶች እና አቅጣጫዎች (ቁጥር - ሁለት) ሰነዱ ወደ ትግርኛም ተርጉሜዋለሁና ትግረኛውንም ይለጠፋል።

 ኤርትራን በሚመለከት እንዲህ ይላል።

2.3.7. ከኋላችንን የሚወጋንንም እንጠንቀቅ (ገጽ 64-66)

I.             በአጠቃላይ የኤርትራ ጉዳይ በተለይ ደግሞ የኢሳያስ ቡድን በቀጥታ ከምከታችን ጋር እና ከፍላጎታችን ባሻገር የሚዛመድ ነው፡፡ የዚህ ቡድን ፖለቲካዊ፣ ጸጥታዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ወዘተእንቅስቃሴዎቹ እኛ ላይ በተዘዋዋሪ ሳይሆን ቀጥተኛ እና ከባድ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡ እጅግ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ የኢሳያስ ቡድን እና የአብይ ቡድን ተቀናጅተው በትግራይ ህዝብ ... ጉዳይ ስር የሰደደ ጥላቻ ይዞ ዳግም እንዳናንሰራራ ሊያጠፉን የሚያልሙ እና እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ መሆን ነው፡፡ ይህም የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁለቱም ስልጣናቸውን ማስቀጠል እና ብዛታቸውን ማስፋት ካለባቸው ይህ ድርጅት እና ህዝብ መጥፋት አለባቸው ብለው አቅደው እና ተመካክረው የጋራ እቅድ አውጥተው ነው በእኛ ተቃራኒ ቆመው እየገጠሙን የሚገኙት፡፡ ስለሆነም ይህ ስለታም የጥፋት ጫፍ ከአሀዳዊው እና ፍፁም ፀረ-ዲሞክራሲ ቡድን ብቻ ሳይሆን ከኢሳያስ ቡድንም ጭምር እንጂ፡፡ አንድ አንድ ጊዜ ለብቻው አንድ አንዴ ደግሞ ከደመኞቻችን / ጠላቶቻችን ጋር ተሻርኮ ፍላጎቱን እና አመለካከቱን የሚተገብርበት ክህሎት/ ችሎታ አጥቶ እንጂ እኛን ከዛሬ ነገ ለማጥፋት እንደተመኘ - እንደፎከረ ነው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም ሀይሎች በተጨባጭ ህልውናችንን የሚፈታተኑ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ በመሆን ነው እየሰሩ የሚገኙት፡፡ የአብይ ቡድን ወድቆ የኢሳያስ ቡድን መዝለቅ/መቀጠል ድላችንን ከንቱ የሚያደርግ በተለመደው አዙሪት ከመዳከርም አንወጣም፡፡

 ስለሆነም የኢሳያስ ቡድን እድል እና እጣ እንዲሁ ከአብይ ቡድን እጣ ጋር አብሮ እንዲጓዝ የኢሳያስን ቡድን የሚያዳክም፣ የሚያፈራርስ ፈጣን፣ ተጨባጭ እና መጠነ ሰፊ እቅድ ይዘን እንስራ፡፡ አካሄዳችንን እንቀይር፡፡

(እዚህ ላይ ሰነዱ የሚያሳየው አንዱን ደምስሰህ አንዱን መተው ለኛ ስጋት ሰለሆነ አብይ እና ኢሳያስ አብረው መደምሰስ አለባቸው እያለ ነው)

II. የኢሳያስን ቡድን ከሞላ ጎደል ለማዳከም እና ለማፈራረስ የሚያስችል አሁንም ልክ እንደ ሀገራችን በሳል ነባራዊ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይህ ቡድን ሙሉ በሙሉ ከኤርትራ ህዝብ ተነጥሏል ሊባል ይችላል፡፡ ውለህ በሰላም ግባ የሚለው ህዝብ የለም፤ ተስፋ ቆርጠውበታል፡፡ በዚሁ ገዢ መደብ ውስጥም ግዙፍ ስንጥቃት ነው ያለው፡፡ በሰራዊት ውስጥም ከባታሊዮን አመራር በታች የሚገኙ የሰራዊቱ መኮንኖች እና ተራው አጋር/ እግረኛ እና ሰፊው ህዝብ በፀረ-ስርዓቱ አንድ አይነት አቋም አላቸው፡፡ ከብርጌድ አመራር በላይ የሚገኙትን በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች፣ እጥረቶች/ ድክመቶች እና በስለላ ጭምር እያስታመመ ለመያዝ እየሞከረ እንደሆነ ነው የሚገለፀው፡፡ የኤርትራ ህዝብ ወታደር ሆኖ መኖር አንገፍግፎት አሀዱዎቹን ከጠቅላላ መጠናቸው ሲሶ በማይበልጥ የሰው ሃይል ነው እየተጓዙ የሚገኙት፡፡ ይህንን ትልቅ ጉድለቱን ቋሚ/ነባር ሰራዊትን በማደራጀት ነው ለመሸፈን እየሞከረ የሚገኘው፡፡

እንደ አቅሙ 65 ዓመት በታች እድሜ ያላቸውን የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ የቋሚ/የነባር ሰራዊት አባል በማድረግ ነው ህልውናውን ለማሳየት እየሞከረ የሚገኘው፡፡ የኢሳያስ ቡድን የማቆያ ክር ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው የሰራዊቱ ከፍተኛ አዛዦች፣ ሀገራዊ ደህንነት እና ስለላ እንዲሁም የሚከተለው አሰራር እና አደረጃጀት ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለፀው ሁሉም 65 አመት እና ከዚያ በታች እድሜ ያላቸው ቋሚ/ነባር ሰራዊት ብሎ በመስመር እና ጋንታ ውስጥ አስገብቶ - በሰራዊት ስም በንቁ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ/ ንቅናቄ እንዳይገባ አፍኖ ይዞታል፡፡ ከፍተኛ ጀነራሎችን እና የሀገር ደህንነት ስለላ አካላት ደግሞ በሙስና እና ጎጠኝነት እርስ በእርሳቸው እንዲጠባበቁ እና ኢሳያስን እንደ አዳኛቸው እንዲመለከቱት አድርጎ በፈጠረው ወጥመድ ነው እኩል በእኩል እያራመደው የሚገኘው፡፡ በዋናነት ደግሞ በሀገራችን የባሰውን የአመራር ክፍተት (ሁሉንም በራሴ የሚያስከትለውን ችግር/ሁኔታ) እንደ እድል ተጠቅሞ የኤርትራን ህዝብ በባርነት ቀንበር ስር አስገብቶ እኛን ለማጥፋት ሌት ተቀን እየባዘነ ይገኛል፡፡

III. ይህንን አጭር ጠቋሚ/ አመላካች ሁኔታን/ እውነታን መሰረት በማድረግ የኢሳያስን ቡድን ለማፈራረስ የሚያስችል እድል ሰፊ ነው፡፡ ስለሆነም ሁለት በጥብቅ የተያያዙ/ የተሳሰሩ የስራ እቅድ አቅጣጫዎችን ይዘን እንሰራበታለን፡፡

አንዱ፦ በኤርትራ የውስጥ አቅሞች ላይ ተመርኩዘን ኢሳያስን <<የሚገረስስ>> ተጨባጭ እና የተደራጀ እገዛ ማድረግ፡

 ሁለተኛው፦  የኢሳያስ ቡድን የዚሁ ይፋዊ ወረራ አካል ሆኖ በእኛ ላይ ጦርነት ካካሄደ ደግሞ በጦርነት የሚደመስስ ወታደራዊ ዝግጁነት እና ስትራቴጂን ይዘን ለመመከት መዘጋጀት፡፡

በኤርትራ የውስጥ አቅሞች ላይ ተመርኩዘን ማድረግ የሚገባን ተጨባጭ ድጋፍ በአንድ በኩል የጠላትን ድክመቶች ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያሸጋግር እና በሌላ በኩል ደግሞ የለውጥ ሀይሎች ተደራጅተው እንዳይነቃነቁ፣ እንዳይመክቱ ከባድ ክፍተት/ ጉድጓድ ሆኖ የሚገኘው የአመራር ችግር እንዲሁ ለመፍታት የሚያግዝ ወጥመዶችን የሚበጣጥስ እንዲሆን ማድረግ፡፡

ወጣም ወረደ ግን <<የኢሳያስን ቡድን ማፈራረስ ማዕከል ያደረገ ውሳኔን ይዘን ራሱን የቻለ ስትራቴጂ እና አቅም እንዲዘጋጅለት፣ ይህንን የሚመራ እና የሚያስተዳድር አደረጃጀት እንዲፈጠር፣ አካባቢውን እና ስራውን የሚያውቅ በቂ የሰው ሃይል እንዲመደብ፣ አቅማችን የፈቀደውን ያህል የፋይናንስ እና ማቴሪያል ከፍ ለማድረግ>>

ለመጨመር በሁሉም ረገድ በህዝብ፣ በድርጅቶች፣ በሰራዊት፣ ሚዲያ እና አክቲቪስቶች እንዲሁም በውስጥም ሆነ በውጪ (የይብቃ/ ይአክል/ ህዝባዊ ንቅናቄ) ወዘተአስተባብረን የኢሳያስን ቡድንንም እንገረስሳለን”፡፡

ከፊት ከፊታችንም ከኋላችንም (ጀርባችንን) “ነፃ እናወጣለን”፣ ምከታችንን መጪው / የወደፊት ጊዜ ጉዞ ዋስትናው የተረጋገጠ እንዲሆን ሁኔታዎችን ማስተካከል፡፡ እንችላለን ጎበዝ ደል ንሳ መሪ ድርጅታችን ... ምን ይሳነዋል !! 

ምንጭ - (የትግል ልዩ ምዕራፍ እድገቶች እና የምከታችን ቀጣይ ስትራቴጂዎች፣ ስልቶች እና አቅጣጫዎች (ቁጥር - ሁለት) በጥብቅ የሚያዝ ... /ቤት

መስከረም 30/2013.  መቐለ 2 )

አመሰግናለሁ!

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 10/25/22