Sunday, January 16, 2022

የወያኔ ትግሬዎች ለምን ታሪክ ይሰርቃሉ? ጌታቸው ረዳ (ክፍል 1) ETHIO SEMAY (1/17/2022)

 

የወያኔ ትግሬዎች ለምን ታሪክ ይሰርቃሉ?

ጌታቸው ረዳ

(ክፍል 1)

ETHIO SEMAY (1/17/2022)


የሰሜኑ ክፍላችን ታሪክ ሲነሳ በዛው አካባቢ በመወለዳቸው ምክንያት በዛው አካባቢ ለመጡ ጠላቶች በቅርበት መርቶ በመጋፈጥ “የአጼ ዮሐንስ እና የራስ አሉላ አባ ነጋ” ስም የገነነ ስም እንዳላቸው ታሪክ ያወሳል።

አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘረኛ ዘመናዊ ሙዚቃ አቅራቢ አዝማሪዎች በሚያሰራጩት ቪዲዮ የታዘብኩት ነገር አለ። ሙዚቃዎቻቸው “አጼ ዮሐንስን እና ራስ አሉላን” በተለይ የዮሐንስን ምስል በመጥላት የነ ቴድሮስ፤ምኒሊክ፤ተፈሪ፤ መንግሥቱ… በስዕላዊ ሙገሳ  ሲያስተጋቡላቸው፤ ያልታደሉት ዮሐንስ በወያኔዎች የመወደዱ መስሎአቸው ምስላቸውን ቆርጠው ሲያስተጋቡ ቀላል የማይባሉ የሙዚቃዊ ቪዲዮ ቅንብሮች ሲታተሙ አይቻለሁ።

ለምሳሌ (ዮሐንስን ያገለለው የቪዲዮ ሙዚቃ “አሞናል በለው” የተባለው የአብይ አሕመድ ቱልቱላው የዘሐበሻው ሔኖክ ዓለማዮህ ያዘጋጀው ይህ እጅግ የደንቆሮዎች የስራ ውጤት በምሳሌ ማቅረብ ይቻላል”) ሆኖም ወያኔዎች ዮሐንስም አሉላም በሕዝብ ግፊት ተገድደው ካልሆነ ሁለቱንም መሪዎች በወያኔ አይከበሩም።

በዚህ ትችት መጀመሪያ ክፍል 1 እንደመግቢያ ብቻ አቀርባለሁ (ባክ ግራውንድ የሚሉት ፈረንጆች “የጀርባ ማሕደር”)። በክፍል ሁለት ሙሉውን ታሪክ በማቅረብ ወያኔዎች ሲዋሹ የነበረውን የዘመናት ውሸት በማስረጃ በሰሜን ኢትዮጵያ (ዶጋሊ፤ጉራዕ፤ጉንደት….ወዘተ) የተደረጉ ጦርነቶች ትግሬዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዴት ተካፍለው ድል እንዳደረጉ አቀርባለሁ። ለጊዜው ረዢም የሆነ የታሪክ ማሕደሮች የማንበብ ችሎታ የሌላችሁ የፌስቡክ “ጮርቃ አንባቢዎች” እንዳይረዝምባችሁ በማለት ይህንን የወያኔ ማሕደር ገላጭ እንደ መግቢያ ክፍል 1 ላቅርብ፡

የወያኔ መሪዎችና የወያኔ ታሪክ ምሁራን ስለ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲናገሩ ብዙ ጊዜ የሚናገሩትን አድምጣችኋቸው ወይንም የሚጽፉትን አንብባችከሆነ “አማራ  ታሪክ የለውም” የሚናገረው ታሪክ የትግሬዎችን ታሪክ ሰርቆ የራሱ አስመስሎ የመጻፍ ባሕል ነው ያለው፡ “የአሸናፊነት ታሪክ ሰሪ ያለው ትግሬ እንጂ ማንም የለም” እያሉ ሲዋሹ እስኪሰለቻችሁ ድረስ የውሸት ትርክታቸውን ሰምታችኋቸዋል ብየ አምናለሁ።

ሰሞኑን አቻምየለህ ታምሩ ለአንድ በኦነግ ትምህርት ቤት የተማረ የአብይ አሕመድ አዲስ ሹመኛ ካድሬ “ዓድዋ ጦርነትን ከተካፈሉት ኢትዮጵያውያን ውስጥ 50% ኦሮሞዎች ናቸው” በማለት የዘላበደውን ውሸት አጋልጦታል። እኔም አንዱ ተከየ “የትግራዩ አቻምየለህ ታምሩ” ብሎ በሰየመኝ ስም ልሂድና የወያኔ ካድሬዎች የሚዋሹትን ላጋልጥ።

የወያኔ ትግሬዎች እያልኩ ስጽፍ ትርጉሙ ያልገባችሁ ሰዎች ብዙ ሰዎች እኔን ለምን እንዲህ ትላለህ እያሉ ሲሰድቡኝ ነበር ትርጉሙ ያልግባችሁ ስለምትኖሩ ልግለጽ። ካሁን በፊት ደጋግሜ እንደገለጽኩት የወያኔ ትግሬዎች ማለት በወያኔ ስርዓትና ትርክት የሚያምኑ የወያኔ ተከታይ ትግሬዎች ማለት ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን ትግሬዎች ማለት ደግሞ እኔ እና መሰል የወያኔ ተቃዋሚ ክፍል ማለት ነው። ባጠቃላይ አነጋገር በነገድ ሳይሆን በአመለካከት ሁለት ትግሬዎች አለን ማለት ነው እንደየ አመቺ ርዕሱ “ትግሬዎች” ብየ የምጠቀምባቸው ስለ ብዙሃን የወያኔ ተከታዮችም ስላሉ እንደሁኔታው ግንዛቤ ውሰዱ።

የወያኔ ትግሬዎች “አማራ ታሪካችን የነጠቀን ነው” ብለው ለሚሉት አማራ ብቻ ሳይሆን ላንዳንድ የትግራይ አካባቢ ትግሬ ማሕበረሰብም እንዲህ እያሉ ሕዝቡን በጥላቻ  ለመከፋፈል ሲያስተምሩት የነበረውን ዘፈን እንደመግቢያ ላስቀምጥና ምን ያሕል ዕብደት እንደተጠናወታቸው ጠቁሜ ወደ ርዕሱ ልግባ።

ይህ በመጽሐፌ የተጠቀሰ መጽሔቶችም የኔን መጽሐፍ እየጠቀሱ ሲጠቅሱት የነበረውን ግጥም ታስታውሳላችሁ?

“ዓድዋ አኽሱም ሽረ ጹሩያት ተጋሩ

ራያ እንደርታ ተምቤን ጎረቤት አምሓሩ”

ትርጉም አማርኛ

“ዓድዋ አኽሱም እና ሽሬ የጠሩ ትግሬዎች

ራያ እንደርታ ተምቤን ያማራ ጎረቤቶች (ክልሶች)“ እያሉ ትግሬው ከትግሬ ሲያጋጩት የነበረው ማስረጃ ነው።

ሌላው አማራን የታሪክ ሌባ ነው እያሉ በውሸት ወጣቱን እንዴት ሲያወናብዱት እንደነበር ከዘፈኖቻቸውን አንዱ ልጥቀስ፤

 የወያኔው ዘፋኝ ኪዳነማርያም ረዳ

 በትግረኛ ዘፈኑ እንዲሕ ይላል፤-

“ንአብነት ማይ ጨዉ ዓድዋ እንተዘከርና፤

ተምቤን ዓቢይ ዓዲ ሽረ እንዳባጉና፤

ኩይናት ምስ ገበሩ እቶም ወለድና፤ ጸላኢ ደምሲሶም ታሪኽ ሓደጉልና።

ጨቆንትና አምሓሩ ምስ ታሪኽ ፀሓፍቶም ንዓና ዓብሊሎም ታሪኽና ጎቢጦም አለዉ ይምክሑ ብደም ወለድና፤

ንቃለስ ተጋሩ ክንመልስ ቅያና “

አማርኛ ትርጉም፦

“ ሓቀኛ ታሪክ ተደብቆ አይቀርም ለምሳሌ የማይጨዉን፤ የዓድዋን፤የሽረ የእንዳባጉናን ታሪክ ስንመረምር ወራሪዎችን ድባቅ በምመታት ትግሬ ወላጆቻችን አኩሪ ታሪክ ትተዉልን አልፈዋል። ይሁን እንጂ፤አባቶቻችን ብብዙ ዓዉደ ዉግያዎች ደማቸዉን አፍስሰዉ ያስመዘገቡትን የትግሬዎች አኩሪ የድል ታሪክ “(ጨቆንትና አምሓሩ ምስታሪኽ ፀሓፍቶም”) “ጨቋኞቻችን አማሮች እና ታሪክ ጸሃፊዎቻቸዉ” በአሁኑ ወቅት እየተኮፈሱበት ነዉ። ታሪካችንን ቀብረዉ በአባቶቻችን ደም/ታሪክ እየተመኩበት ናቸዉ እና የትግራይ ተወላጆች የሆንን በሙላ ታሪካችነን ለማሳደስ በፅናት መታገል አለብን!” 

ይል ነበር፤ ተደርሶ የተሰጠው በረሃ ላይ እያለ የወያኔ ሙዚቀኛ የነበረው (የወያኔ ዘፋኝ ኪዳነ ማርያም ረዳ። ምንጭ (ይድረስ ለጎጠኛው መምህር፤- ደራሲ ጌታቸው ረዳ።)

ሰሞኑን ትግሬዎች እያሰራጩት ያለው ቪዲዮ አይታችሁት ይሆናል ብየ እገምታለሁ። ይህ የድንቁርና እና የስርቆት እንዲሁም የትምክሕት የታሪከ ማጭበርበሪያ ቪዲዪ “ትግራይ ሚዲያ ሃውስ” የተባለ የወያኔ ዜና አቅራቢ ምስኪኑ “ስታሊን ገብረስላሴ” እውነተኛ ታሪክ መስሎት በደስታ ፈንጥዞ ቪዲዮው “ታሪክ ለማያውቁ እነ ባሕሩ ዘውዴ እና መሰሎች “ ታሪክ ዋን ኦ ዋን” እናስተምራቸው” እያለ ለምስኪን አድመጮቹ ሲያግታቸው አደምጫለሁ።

ይህ ቪዲዩ ምስኪኑ ስታሊን ብቻ ሳይሆን በስሜት የሚጋልቡ የወያና ጀሌዎችም እውነት መስሏቸው ሲጎረኑበት (ሲመኩበት) እና በየፌስቡካቸው ሲለጥፉት አይቼው ስስቅባቸውም ስገረምባቸውም ሰንብቻለሁ። ስለዚህም አንድ ልብል።

እነ ስታሊን ገብረስላሴ የፈነጠዙበት የቪዲየው የታሪክ ተንታኝ ማን ነው ብትሉኝ “ደደቢት በረሃ እነ አረጋዊ በርሄ ጽፈው የበተኑትን አንብቦ ያደገ ከንቱ የታሪክ ተማሪ ነው”።

ቪዲዮው ምን ይላል? በክፍል ሁለት ቪዲዮው የምታደምጡት ይሆናል። ባጭሩ እንዲህ ይላል፡

“የመጀመሪያ ጊዜ የነጭን ጦር ያሸነፈው የአሉላ ጦር ነው።የትግራይ ወታደር ነው ያሸነፈው።ይህንን ዜና እነ አፄ ምኒሊክ ሸዋ ሆነው ነው በወሬ የሰሙት። ሌላውም ኢትዮጵያዊ እንዲሁ በደብዳቤ እና በወሬ ነው የሰማው። ለአፄ ዮሐንስም “እንኳን ደስ ያለዎት” የሚል መልዕክት ነው የላኩት።ይህ ፈር ቀዳጅ የሆነ ታሪክ የሰራው በብሔር ከመጣን የመጀመሪያ ቀዳሚ ባለቤቱ የትግራይ ሕዝብ ነው። መጀመሪያ ከግብፅ ጋር አሉላ ከአፄ ዮሐንስ ጋር 9 ጊዜ ተዋግቶ ነው የመለሰው።ይህ ጦርነት ብቻውን የተዋጋውና ያሸነፈ የትግራይ ጦር፤ የትግራይ መኳንንት የመሩት ወታደር ብቻ ነው።  ስለዚህ ጠላቶችዋን አሳፍራ የመለሰች ተብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊጠቀስ የሚገባው የትግራይ ሕዝብ ነው።…….”

እያለ ታሪክ በሰሜን የተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ እነ አሉላ እና ዮሐንስ ባልተወለዱበት ዘመን የነበሩት የሸዋ አምደጽዮን እነ ዘርአያዕቆብ ያስከበሩትን የሰሜን የባሕር በራችንን ረስቶ፤ ትናንት የተወለዱትን በዮሐንስና በአሉላ በትግራይ ሕዝብ ብቻ እንደተከናወነ አድርጎ ሲዋሽ ከላይ እንደጠቀስኩት የትግራይ ምሁር ነኝ የሚለው ለወያኔ ጋዜጠኛ ሲተነትንለት ከቃለ መጠይቁ የቀነጨብኩት ነው።

ጥያቄው ትርክቱ እውነታ አለው ወይስ የለውም? የሚለው ጭብጡን በክፍል ሁለት አቀርባለሁ።

 የወያኔ ምሁራን የኢትዮጵያውያንን አኩሪ ገድል ለትግሬዎች እየሸለሙ፤ ታሪክ የሚሰርቅ ዋሾ ትውልድ በትግራይ በብዛት መወለዱ ስመለከት እኔ እራሴ ደጋግሜ እንዳልኩት ትግሬነቴን ካስጠሉኝ አንደኛዎቹ ምክንያቶች ውስጥ እነዚህ ዋሾች በሚዘላብዱት እንዲህ ባለ ዕብደት ምክንያት ነው። በነገድ መኩራት እንዳለ ሁሉ ነገድህ በሚከተለው ድርጊትም ታፍራለህ፤ ማፈር አለብህ፤ ያስጠላል!

አሁን ወደ እውነተኛው ታሪክ ልግባ።

ይህ ማስረጃ በሁለት መጻሕፍቶቼ ያቀርብኳቸው ሲሆኑ አንዳንዶቹ እንደገና በተጭማሪ ላቅርብ።

ኢትዮጵያውያን ከአክሱም ጀምሮ እስከ ቱርክ፤ ግብፅና ጣሊያኖች ባደረጉት የአገር መካለከል ጦርነትና ድል ወያኜዎች የኛ የትግሬዎች ብቻ ነው ብለው የሚዋሹት የታሪክ እውነታውን በጦርነቱ ላይ የማን ጦር እንደተሳተፈ ተዋጊው ጦረኞቹ ስማቸው ማን ይባል ነበር? የሚለው በማስረጃ ከማቅረቤ በፊት ወያኔዎች ራስ ዓሉላ እያሉ በውሸት ራስ ዓሉላ አባ ነጋን መጠቀሚያ ሲያደርጓቸው በተግባር ግን እንደማያከብሯቸው ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ።

መጀመሪያ የወያኔ ትግሬዎች አሉላ አባ ነጋን አይወዱም። ተምቤን አብይዓዲ ውስጥ አዲስ ዘመናዊ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ተሰርቶ በሕዝቡ ጥያቄ በራስ አሉላ ስም ተሰይሞ የነበረውን አዲስ ትምሕርት ቤት ተሰርዞ የመለስ ዜናዊ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ተብሎ በህዳር 21 ቀን 2004 ኢ.ዘ.አ ተቀየረ። ስያሜው ሲከናወን

በስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረገው የሕወሃት ሲሲ/ማአከላዊ አመራር አባል/ ኮማንደር የትባረክ አለነ” እንዲህ ሲል ተናገረ።

“ደስተኛ ያልሆነ ሕዝብ “ ተቃዋሚ ፓርቲ ነን የሚሉ ሁሉ “ራስ አሉላን” ማምለክ አለባቸው፡ ሲያከብሩትም አዲስ አበባ ወይም አስመራ…ወይም በዋሽንግተን ዲሲ፣ በሽሽት በሚኖሩበት ዓለም እንጂ እዚህ ትግራይ ውስጥ አይደለም:: “አዲሲትዋን ትግራይን” የፈጠርነው “በልጆቻችን ደም” እንጂ “በአሉላ ደም አይደለም።”

በማለት ንግግር ካደረገ በኋላ በሕዝቡ እና በታጠቁ የህወሓት የደህንነት አባላት መካከል ግጭት ተፈጥሮ መኖሩን በዜና እንደተሰራጨ ታስታውሳላችሁ።

አሉላን ብቻ ሳይሆን አጼ ዮሐንስንም እንደማያከብሯቸው አንድ ሌላ ማስረጃ ላቅርብ እና ስለ ወደ 15ኘው እና 19ኛው ክ/ዘመን የማን ጦር/ሕዝብ ተሳትፎ ነበር ወደ እሚለው እገበላሁ።

አሉላን ብቻ ሳይሆን አጼ ዮሐንስንም ባደረጉት የጦርነት ድሎች መጠቀሚያ እንጂ በግብር ግን ከልብ እንደማያከብሯቸው ልክ እንደ ራስ አሉላ ዮሐንስም መቀሌ ውስጥ በወያኔዎች ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሞአቸዋል።

የዶቸ በሌ ጋዜጠኛ ዘጋቢ ከመቀሌ በቀጥታ ያሰተላለፈው ዜና እነሆ እንዲህ ይላል፦

“ በመቐለ ከተማ በብቸኝነት የነበረው ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት፤ ባሁኑ አጣራር “መሰናድኦ ት/ቤት” እድሳትና ማስፋፋት ሥራ እስካሁን ስለ መቆየቱ ጉዳይ የመቀሌ  ኗሮዎች ቅሬታ ነበር። ለወትሮው  የፈየደው ነገር የለም፤ ይልቁንስ ከመሃል አገር ሕዝብ እያጠላን ነው። ሕድሳቱ ሕዝቡ የሚወቅሰውን እያስተጋባ ያለውን ቅሬታ  ለማስታገስ ይመስላል ይኼው የትግራይ መልሶ ማቋቋም  ድርጅት፤የፖለቲካ ትኩሳቱ ለማብረድ ጭማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ገንብቷል። ኗሪው ግንባታው በደሰታ ቢቀበለውም፤ በነባሩ ሕንጻ ላይ የአቶ መለስ ዜናዊ ‘ፎቶ’ በትልቁ መለጠፉ ቅሬታን ወልዷል።”

በማለት ዘጋቢው ሁኔታውን ካስረዳ በኋላ፤ የሚከተለው ኗሪ እንዲህ  ሲሉ ቅሬታቸው ሲያሰሙ ተደምጠዋል፦

<<ለምን? ስሙ አፄ ዮሐንስ ነው፤ ሌላ ፎቶግራፍ እና ስም መለጠፉ  ለምንድ ነው ያስፈለገው? ይህንን ነገር ስንናገር ደግሞ ፎቶው ወይ ያነሱታል፤ ወይ ይሸፍኑታል።>>

 ሲሉ ሌላ ሴት ተናጋሪ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፤

<<ስሜ ማራናታ ይባላል።የአፄ ዮሃንስ ተማሪ ነኝ። እኔ በበኩሌ ቅር ብሎኛል። ምክንያቱም ት/ቤቱ የሚታወቀው በአፄ ዮሐንስ ነው፡ አፄ የሃንስ ደግሞ ትልቅ ጀግና ናቸው። መሆን የነበረበት ፎቶግራፍ ደግሞ “የኤፄ ዮሐንስ” መሆን ነበረበት።  ነበሳቸው ይማረውና የጠቅላይ ሚኒስትራችን መሆን አልነበርበትም። ከፈለጉ የራሳቸው በስማቸው ሌላ ት/ቤት መሰየም ነበረባቸው እንጂ በዚህ  በጣም ቅር ተሰኝቻለሁ።>>

ስትል የታሚሪቷ ቅሬታ ምን እንደሚመስል ገልጻለች።

ቀጥሎም፤ የስጋቱ መሰረት በዛው በትምህርት ቤት ብቻ የተወሰነ አልነበረም ይላሉ አንድ አስተያየታቸው ለየት ባለ ቅሬታ የገለጹት።

እንዲህ ሰሉ፤-

“ይህ ክስተት በአጼ ዮሃንስ ብቻ የተወሰ አይደለም አንደዚህ የተደረገው። በተምቤን ዓብይ ዓዲ የራስ አሉላ ፕሪፓራቶሪ ት/ቤት ሲባል የነበረው፤ “መለስ ፕሪፓራቶሪ” ተብሏል። ከፍተኛ ተቃውሞ አለ። በዓዲ ነብሪኢድም ፤ ሕዝቡ “ሓየሎም አርአያ’ ፓርክ ብሎት የነበረው፤ ‘መለስ ዜናዊ ’ ፓርክ ተብሎ እንዲጠራ ተደረገ። ይህ ፖለቲካዊ እንደምታው ምንድ ነው? ብለን ብንመለክት “የመለስ ራዕይ” የሚባል እንደ ትልቅ አጀንዳ አድርጎ የሚያንቀሳቅሰው የወያኔ ቡድን አለ።  ይህም በሕብረተሰቡ ተቀባይነት አላገኘም።  እነሱ የፈለጉት “መለስ ዜናዊ” የመጀመሪያም  የመጨረሻም ሰው” እንደሆነ ተደርጎ ሊስሉት ይፈልጋሉ። ይህም ተቀባይነት እንዲኖሮው ለማድረግ እየተጣረ ነው። ሕብረተሰቡ ግን ሊቀበላቸው አልቻለም። በአጼ ዮሐንስም እየተደረገው ያለው ያ ነው።”>> 

ሲሉ በዚህ ጉዳይ የት/ቤቱ ርዕሰ መምሕር አቶ ተወልደ ገብረሚካል ተጠይቀው የሰጡት ምልስ እንዲህ ብለዋል፦

<< አጼ ዮሐንስ እንደ መሪ ለአገራቸው ሲሉ መተማ ሄደው መስዋዕት ከፍለዋል፤አቶ መለስም ለሕዝባቸው ሲሉ መስዋዕት ከፍለዋል ። ይህ የሚያሳየን፤’ታሪካዊ ትስስር’ እንዳለው እንጂ ‘የአቶ መለስ ታሪክ ብቻ ጎልብቶ የአፄ ዮሐንስን ታሪክ ለማንቋሸሽ የሚል  በትክክል ለሚያስብ ሰው አንድምታ የለውም””> 

ዘጋቢው በመጨረሻ እንዲህ ሲል ዘገባው ደምድሞታል።

<<በተለይ ተማሪዎቹ እንደሚሉት ‘ከአልበርት አነስታይን ጎን አቶ መለስ ወደ ህዳሴው ግድብ እጃቸውን እያመላከቱ የሚያሳይ ስዕል አልተቃወምንም፤ ስለገነቡልን ግን ታሪክ በሚያዛባ መልኩ የሳቸው ፎቶ በህንጻዎቹ መለጠፉ ግን ሰሚ የለም አንጂ እንቃወማለን።>> ለዶቸቬለ ራዲዮ የተጠናከረው ዘገባ ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር ነኝ።መቐለ።>> ሲል ዘገባውን ደምድሟል። እንግዲህ ወያኔዎች የታሪክ ባለቤትነታቸውን ለመጠቀም ሲፈልጉ ዮሐንስን እና የአሉላን የ ርነት ውሎች በማንሳት በስማቸው ሊጠቀሙ ይፈልጋሉ፤ ብግብር ግን እንደት እንደሚጠልዋቸው ከላይ አሳይቻለ።

በክፍል 2 ስለ ግብፅ እና ኢትዮጵያ ጦርነት ማን ተካፈለ እሚለው ክፍል ሁለት ይዤ እመለሳለሁ። እስከዛው ሰላም ሁኑ።

እኔ ሓለፊነቴን እየተወጣሁ ነው እናንተም ላላወቁ ለማሳወቅ ሰነዱን ተቀባበሉት (ሼር)፡

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ ETHIO SEMAY    

 

 

 

 


No comments: