Sunday, November 21, 2021

የጅምላ ሳይኮሲስ ጌታቸው ረዳ (ETHIOPIAN SEMY) 11/22/2021

 

ጅምላ ሳይኮሲስ

ጌታቸው ረዳ

(ETHIOPIAN SEMY)

11/22/2021

የውስጥ አካላት ሓኪም እና ‘በሳይኪያትሪ’ ልዩ ሙያ ያለው የአምስተርዳሙ የዘወትር ወዳጄ ዶ/ር አሰፋ ነጋሽን ት/ምህርት ቤት የማላገኘውን የዘወትር ልዩ ዕውቁትን ለመቅሰም ሰሞኑን ደውየ ሳነጋግረው፤ “አሁን እየተካሄደው ያለው የአገራችን ጦርነት ለ “27+3” አመት የዘለቀ “የጅምላ ሳይኮሲስ” ( “የጅምላ እብደት) ውጤት ነው አለኝ።

እንዴት ብየ ስለው፡ በግርድፉ እኔ እንደገባኝ አባባል እንዲህ አለኝ

“የብሔረተኛነት ፖለቲካ ሰዎችን ከሰብአዊ ስነ ምግባር ውጭ አድርጎ ‘እንሰሳዊ ዕብደት’ ውስጥ ይከታቸዋል፤ ብዙሃኑ በዚህ ክስተት የተጠለፉ ናቸው ይላል። “የጅምላ እብደት በህብረተሰባችን   ውስጥ የተለመደ ክስተት ሆኗል። ለምሳሌ ትግራይ ውስጥ በጦርነቱ የተሳተፉ የ17 አመት ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ሕብረተሰቡ ‘ሬሳ፤ ግድያ እና ጭካኔ’ በዓይኑ እያየ ያደገ ማሕበረሰብ ሁሉ ሰለባ በመሆን “የጅምላ ሳይኮሲስ” ውስጥ እንደገባ የሚያጠራጥር አይደለም። መንጋ የምንለው  አማርኛችን በመጠኑ የሚገልጸው ቢሆንም “መንጋው” ያቀፈው ሕሊና ነው በጣም አስፈሪው። ስለሆነም በዚህ የጅምላ ሳይኮሲስ ውጤት “በጠላትነት የፈረጁት” ወገን ባገኙበት ቦታ ሁሉ “መግደል’ ብቻ ሳይሆን “ከብቶቹንም ጭምር” በበቀል ይጨፈጨፋሉ። ይህ የጅምላ  ዕበደት ውጤት ነው”፡ ይላል (ሓኪም  አሰፋ ነጋሽ)።

እውነት  ነው ይህ  የጅምላ ዕብደት በትግሬዎች ብቻ ሳይወሰን በኦሮሞዎችም  ጭምር አይተናል። የህ የጅምላ በሽታ የሚያስቀጥሉ ተዋናዮች ተቀባይ አላጡም። ምክንያቱም አታላዮቹ ሕብረተሰብ እውነቱን ከውሸት ለመለየት ባሕላዊ፤ ተፈጥሮኣዊ ወይንም ትምህርታዊ ግንዛቤ እንደሌለው ስለሚያውቁ በቀላሉ ያሳብዱታል “ጉስታቭ ሊ ቦን” የተባለ የስነ ሕሊና ተመራማሪ እንዲህ ይላል።  

“The masses have never thirsted after truth. They turn aside from evidence that is not to their taste, preferring to deify error, if error seduces them. Whoever can supply them with illusions is easily their master; whoever attempts to destroy their illusions is always their victim.”

Gustav Le Bon, The Crowd: A Study of the Popular Mind

ለኛ አማርኛ እንደሚጥም ስተረጉመው፤  እንዲህ ይላል

ብዙሃኑ እውነት ጠምቶት አያውቅም። እንዲጣፍጠው ተብሎ ተቆነጃጅቶ ያልቀረበ እውነታ ከሆነ ዘወር ይላል። ከጣፋጭነቱ እንጂ ከደረቅ እውነታው አይስማማም። ብዙሃኑ ስሕተት ቢያታልላቸውም ስህተትን መውደድ ይመርጣሉ። እያታለለ የሚሰብካቸው ሁሉ በቀላሉ ይገዛቸዋል ።የተታለሉበትን ሃሳብ ለማስወገድ የሚሞክር ቀና ሰው የነሱ ሰለባ  ይሆናል ።

(ጉስታቭ ለቦን፣መንጋ፡ ይፋዊው የአእምሮ ጥናት)

 ይህ እውነታ ብዙዎቻችሁ አንባቢዎቼ የምትረዱት ይመስለኛል። በጣት የሚቆጠሩ የመጠቁ ምሁራን ብዙሃኑን ለማስተካከል ሲሞከሩ የሚደርስባቸው “ዘለፋ” ለ30 አመት ያየነው እውነታ ነው። እነዚህ ፈልገህ የማታገኛቸው ምጡቃን ሰዎች በዜና ማሰራጫ፤በዩቱብ፤ በፌስቡክ፤ በመጽሔት፤በጋዜጣ ቀርበው ያላቸውን እውቀት እንዳያካፍሉ እንዲገለሉ ተደርጓል። ከተጋበዙም የተናገሩትን እየተቆራረጠ ዋናውን መልዕክት በስጋት ወይንም በሚዲያው አዘጋጆች ግላዊ ምክንያት ተቆርጦ ሳይተላለፍ ይቀራል።

ሚዲያዎቹ ለጥቂት ምጡቃን (ምሁራን) ለመገለል ከፍተኛ  አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ምክንያት፤ ብዙሃኑ አታላዮችን ለረዢም ወቅት ሲከተል አይተናል። አሁንም ከዚያ ባሕሪ አልተላቀቀም።  

የስነ ሕሊና ጠበብቶቹ እንዲህ ይላሉ፡

“የሰውነት በሽታ በሕዝብ ውስጥ ሊሰራጭ እና የወረርሽኝ መጠን ሊደርስ ይችላልየአእምሮ በሽታዎችም እንዲሁከእነዚህ የኋለኛው ዓይነት ወረርሽኞች የጅምላ ሳይኮሲስ” በጣም አደገኛ ነው። በጅምላ ሳይኮሲስ ምርምር “እብደት” በህብረተሰብ ውስጥ የተለመደ  ሲሄድ  አሳሳች እምነቶች እንደ ወረርሺን እንደ ኢንፌክሽን” ይሰራጫሉ።

 ሕብረተሰብን ለማታለል ብዙ መልክ ያለው ስለሆነ’ እብደቶቹ ዓይነቶች ስፍር ቁጥር በሌላቸው መንገዶች ይከሰታሉ። የጅምላ የስነ ልቦና በሽታ የሚፈጠርበት ልዩ መንገድበበሽታው በተያዘው ማህበረሰብ” *ታሪካዊ እና ባህላዊ*  አውድ ላይ በመመስረት ይለያያል። ከዚህ ባለፈ የጅምላ ስነ ልቦና ወደ ጠንቋዮች አደን እና እስከ የዘር ማጥፋት እና አልፎ ተርፎም የዘር ጭፍጨፋ ሲካሄድ በዳንኪራ ይታጀባል። ስለሆነም በዘመናችን ትልቁ ስጋት የሆነው  የማህበረስብ ዕብደት ስነ ልቦና ነው።” ይላሉ በዚህ  ሙያ የተመራመሩ ሊቃውንት።

እውነት ነው አገራችን ውስጥ በወላጆቻችን ዘመን ‘ተደርጎ ያልታየ” የጅምላ የዘር ጥላቻ እና ውድመት ደርሷል። ተወናዮቹ ከላይ ያሉ “የሴራው  ጠንጣኞች” ይሁኑ እንጂ ትዕይንቱን ወደ ተግባር  ለውጦ ተካፋዩ የሆነው ብዙሃኑ ነው።

በቅርቡ የንጹሃን ትግሬዎች በጅምላ እያፈሱ ወደ ማጎርያ ጣቢያ  ማሰር ብዙ ጉዳት አስከትሏል። ይህንን  ድርጊት ፈጻሚው “መንግሥት” ተብየው “የታሰሩ ንጹሃን ሰዎች የሉም” የሚለው “ውሸት” ወደ  ኋላ የሚያስጠይቀው ወንጀል መሆኑን ቢታወቅም (ምናልባት  አገሪቷ ካልፈረሰች እና ፍትሕ ከተፈጠረ) አስገራሚ ያደረገው ግን ‘ለዚህ ዘረኛ የጅምላ እርምጃ” በድጋፍ የቆሙ ብዙሃን ናቸው።

ያልጠረጠርኳቸው ይጥንት ወዳጆቼ ስላቸው የነበሩ “ደራሲያን” ሳይቀሩ የዚህ “ቀፍድደው ቁረጠው ገፋትረው” የሚለው “የጅምላ እሰር” ደጋፊዎች ሆነው ሳይ “የጅምላ ሳይኮሲስ” የተባለው በሽታ ሕብረተሰቡ እንደ ወረርሺኝ እንዳዳረሰው ተረዳሁ። አብይ አሕመድ  በሥልጣን ጉጉቱ የተነሳ ‘አምና’ እነ እስክንድር እነ አስቴር “በውሸት ውንጀላ” ተከስሰው  ወደ እስር ሲወረወሩ አንዱ ወዳጄ “እነ ልደቱም ጠበሉ  ይድረሳቸው እንጂ”  ሲል “ፌስቡኩ’ ላይ ለጥፎ ባየሁ ወቅት ሰዎች የጅምላ ዕብደት ውስጥ ሲገቡ የማሰብ “ፋካልቲያቸው” እንዴት እንደሚለወጥ ባየሁ ወቅት በድንጋጤ ነበር  ያነበብኩት።

ሰሞኑን ያስደነገጠጭ ያየሁት “የጅምላ ዕብደት” ካናዳ ውስጥም ይሁን አውሮጳ ወይንም እዚህ ዋሺንግተን ይመስለኛል “የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም” በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ልብስ የለበሰች  ሰልፈኛ ሴት  “የአብይ አሕመድ  ፎቶ በትልቁ  ከፍ ብሎ በሚታየው  “ታፔላ” አጠገብ  አብሮ “የሻዕቢያ ባንዴራ” ሲወለበለብ በነበረበት ቦታ ሩጣ በመሄድ “የሻዕቢያን ባንዴራ ስባ ስትስም” ስመለከት ሕብረተሰቡ ምን ያህል ዕብደት ውስጥ እንዳለ የታዘብኩበት  አመላካች ክስተት  ነበር።

ሰዎች ባንድ ወይንም በሌላ መልኩ ልንሳሳት እንችላለን። ሆኖም በዚያ ስሕተት ውስጥ ያለ ማቋረጥ በዚያ ‘ቦይ’ መፍሰስ የሚያስከትለው ጠንቅ  አገሪቱ ከምትሸከመው በላይ አድርጓታል።

 ከፈረንጆቹ ይልቅ ወያኔ፤ አብይ እና ሻዕቢያ ያመጡብን ጉዳት እጅግ፤እጅግ የከፋ ሆኖ ሳለ “የውስጥ አፓርታይድ” የመሰረቱትን ቡድኖች ላይ ማትኮር ትተው  ወደ “ውጭ” ትኩረት ማድረግ አንድም “ተዋናዮቹ” አላወቅናቸውም ወይንም ወዳጄ ዶ/ር አሰፋ እንዳለው ‘የጅምላ ሳይኮሲስ’ ውስጥ የገባን ማሕበረሰቦች ሆነናል ማለት ነው።

በአገር አንድነት ስም በጭፍን የምናደርጋቸው ድጋፎች “ፋሸስት” ገዥዎችን መላእክት ወደ ማድረግ  መለወጥ ብቻ ሳይሆን ሃገራዊያን “ሳይሆኑ” ሃገራዊያን “ናቸው” ብሎ ፋሺስቶችን የሚያቅፍ ማህበረሰብ በስነ ልቦና የተጎሳቆለ ህዝብ በመሆኑ አገሪቱ የገዛ እራሱ “ለጅምላ ስቃይና ህብረተሰባዊ ውድመት” ይዳርጋታል።

 በመሆኑም ሕዝባችን ማንም በማይክደው ‘የጅምላ ዕብደት’ ውስጥ ገብቷል።

ሌላው ትዝብቴን እንዲሁ አገር ለማዳን በሚል ስም ባንዳንድ ወገኖች በኩል ዝግጅት እተደረገ “ሦስተኛው የጥፋት ዙር” እየተመሰረተ መሆኑን  አንዳንድ ምልክቶች እያየሁ ነው። ይህኛው ደግሞ አስገራሚ ስብስብ ነው።

የ1983 ዓ.ም ተወናዮች የነበሩ፤ እንዲሁም 27 አመት በተቃዋሚነት ቆመው “ዘንዶዎቹ” ይብልጥ እንዲጎለብቱ ‘የፖለቲካ ምግብ’ ሲመግቡዋቸው የነበሩ “ገራገር ፖለቲከኞች” ዛሬም  ከነባር ወንጀለኞች ጋር በማበር የአብይ “አሕመድ ዓይነቱና ወያኔ ዓይነት”  ‘ቅጂ’  እንዲመጣ  እየተደራጁ እንደሆነ እያየን ነው። እንዲህ ያለ ስብስብ አደገኛ የሚያደርገው በሰሩት ዘር ማጥፋት ወንጀል “ቅጣታቸውን  ያላገኙ” ወንጀለኞች ጋር  የጋራ ትብብር  ማድረግ  የአገራችን ዓይነተኛው “ችግር” ፈጣሪ  ስለሆነ ከወንጀለኞች ጋር ትብብር ማድረግ መቆም አለበት ብየ ባስረዳ፤ባስረዳ፤ ሰሚ  የለም።፡

የድሮ ኢትዮጵያዊያን እና ኢትዮጵያዊያት ከመሬት ተቆፍረው እንደገና ካልተፈጠሩ “ኢትዮጵያ”  በምንም ልትድን  አትችልም።

ወይንም “የሐርረ  ወርቅ ጋሻው” እንዳለቺው  ‘የተማረው ሁሉ ሰብስበህ  እንደገና “ሀ ሁ ሂ ሃ” ቆጠራ  እንዲጀምር ወደ  ት/ቤት እንዲገባ  ገብቶ  “አገርን መከላከል” የሚለው የመጀመሪያው “አገርን የማዳን ሀ ሁ ፖለቲካ” እንዲማር ካልተደረገ አገሪቱ የሚጥል  ደጋግሞ እየጣላት ካለው “ከአዙሪት በሽታ”   መውጣት  አትችለም” (የሐርረ  ወርቅ ጋሻው)

አመሰግናለሁ

ጌታቸው  ረዳ (ETHIOPIAN SEMAY)

 

   

No comments: