Thursday, April 1, 2021

አብይ አሕመድ አማራዉን እያስገደለ ነው የሚለው ስሞታ “ፖለቲካዊ መፈክር አይደለም” መልስ ለተድላ አስፋው ጌታቸው ረዳ Ethio Semay

 

አብይ አሕመድ አማራዉን እያስገደለ ነው የሚለው ስሞታ “ፖለቲካዊ መፈክር አይደለም”

መልስ

ለተድላ አስፋው

ጌታቸው ረዳ

Ethio Semay

ተድላ አስፋው ኗሪነቱ ኒውዮርክ ነው። ወያኔን በመቃወም ታወቂ ሲሆን፤ አፍሪካንም “ሺት-ሆል” (የሰገራ ጉድጓድ) በማለት አፍሪካን የሰደበ የአሜሪካ ፕረዚዳንት የነበረው የዶናልድ ትራምፕም ጠንካራ ደጋፊ ነው። ተድላ አስፋው “አበበ በለው” በተባለ ድረገጽ ላይ እንዲህ ሲል የጻፈውን መጓች ጽህፉን ላስነብባችሁ፡

 

“በአማራው ላይ የቀጠለውን ግድያ መቃወም ተገቢ ነው። ለዚህ ዋናው ተጠያቂ የኦሮሞ ክልል አስተዳዳሪዎች ናቸው። ጠቅላይ ምኒስትሩ አማራዉን እያስገደሉ ነው የሚለው ፖለቲካዊ መፈክር የወያኔ ደጋፊዎች ዐቢይ አህመድ የሚመራው መንግስት ይፍረስ እና ወያኔና የነጃዋር መንግስት ይምጡልን ማለት ነው። ብልፅግና ኦሮሞ ዉስጥ የ ኦነግ ጃዋር አንጃ ለአማራው ግድያ በወለጋ ተጠያቂ መሆን ይኖርባቸዋል።” ይላል።

 

አብይ እንደ ሕጋዊ መሪ አድርጌ ባልወስደውም። ሕጋዊ መሪ ስላለሆነም በገዛ ፈቃዱ በመቀመጡ ሦስት አመት ሥልጣን መቀመጡ ይህች እራስዋ ተጠያቂ ታደርገዋለች። ሕጋዊ አድርገን እንውሰደው እና አንድ ሕጋዊ መሪም ሆነ ሕገወጥ መሪ ለይስሙላም ይሁን በእውነተኛ መሃላ በከፍተኛው የአገር መሪነት እርከን የተቀመጠ ሰው መጀመሪያ እራሱ ለማንኘውም ውድቀት ተጠያቂ እንደሚያደርግ መሃላ ይፈጽማል። ለዚህም ነው ሥልጣኑን ሲረከብ “ሥራየ ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት በብቃት እፈጽማለሁ፤ ሓለፊነትም እወስዳለሁ፡ ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳኝ!!” ብሎ መሃላ ምሎ በሕዝብ ፊት ኮንትራቱን በመጽሐፍ ቅዱስ/በቁርኣን ወይንም እንደኛዎቹ ኮሚኒስቶች በራሳቸው የኑዛዜ ደምብና መሃላ ፈጽመው ቀኝ እጃቸውን በማንሳት ተጠያነታቸውን ያረጋግጣሉ።

 

በዚህ ከተማመንን ፤ በተከታታይ በከፍተኛ ልዩነት ማከናወን ያልቻለ ማንንም - በተለይም ማንኛውንም የክ/ሃገር (የ ወያኔ ኦሆዴድ አፓርታይድ ክልል) ፕረዚዳንት/ አውራጃ/ ወረዳ/ ፖሊስ ኮሞሽነር፤ የመንግሥት ተቋም ሥራ አስኪያጅ ሓላፊነቱን በብቃት ካልተወጣ ፤ የተመደበበት ቦታ ስለማይመጥን “ያለ ርህራሄ የማስወገድ የሥራ አስፈፃሚው ዋና መሪ ሓላፊነትና ግዴታ ነው” ፡፡ እንደዚህ ያለ ሰው እንዲቆይ መፍቀድ ሌሎችን በአርአያነት ያበላሻል ፡፡

 

ይህ የሚሆነው አስተዳደርንና የሥራ ብቃት (ፐርፎርማንስ) ክንዋኔን በሚመለከት ነው። አሁን ስለ አብይ እየተነጋገርን ከሆነ ስለ ግድያ የዘር ማጽዳት የሆነ ከፍተኛ ወንጀልን ነው።

 

አብይ ከመጣ በ3 አመት ውስጥ ወያኔ ከነበረበት 27 አመት የጭለማ ጊዜ ለአማራው ነገድ እጅግ የከፋ የዘር ጭፍጫፋ የተፈጸመበት ወቅት ነው። አብይን ከዚህ ነጻ ለማውጣት መሟገት በጣም ኢ-ፍትሃዊ ነው ብቻ ሳይሆን፤ የመሪው ተከታታይ ንግግሮችና ሰብኣዊ ባሕሪ እንዲሁም መሪው አስከብረዋለሁ ብሎ በጥርሱም በጥፍሩም እየታገለለት ላለው “አፓርታይድ ፌደራሊዝም” እውቅና መስጠትና የሥርዓቱን ተልእኮ ትርጉም በቅጡ አለመረዳት ነው ፡፡

 

ሥርዓቱ የተዋቀረው አማራን ያገለለ ነበር። አማራን በጠላትነት የፈረጀ ነው። ስለሆነም አማራ ስርዓቱና የሥርዓቱ መሪዎች ሥልጣን ላይ እስካሉ አማራ እስካሁንዋ ሰከንድ ድረስ ለ30 አመት በዘሩ እልቂትን መፈናቀል እየተደረገበት ነው። አማራን በማፈናቀልና በመፍጀት የተዋቀረውን ሥርዓት “በስንት ደምና በትግላችን የመጣ ስለሆነ በደማችን እናስቀጥለዋለን፡ይህንን ሕገመንግሥት የማይቀበል ከምርጫ ውጭ መሆን አለበት” ብሎ አብይ አሕመድ በማያወላዳ ግልጽ ንግግር ተናግሯል።

 

አቶ ተድላ አስፋውም ሆኑ መሰሎቹ ይህንን አልሰሙም ብየ አልገምትም። አማራው ማህበረሰብ ምሬቱን እየገለጸ ያለው “ይህ ሥርዓት ማንነታችን እየለየ እየገደለን ነው እና ሥርዓቱ ይወገድልን” ሲሉ አብይ ደግሞ “በ14 አመቴ ወደ ጫካ ሄጄ በደሜና በላቤ ታግየ የገነባሁት ሥርዓት ስለሆነ አስቀጥለዋለሁ ፤ እናንተም መጨፍጨፋችሁ ይቀጥላል ነው” የመልእክቱ ቀጥተኛ አቋሙ። ያ ትክክለኛ ንግግሩ ደግሞ ከሥር ቃል በቃል አቀርባለሁ።

 

ስለዚህ አማራን እያስገደለ ያለው ሥርዓት በመሪነት የተኮፈሰው አብይ አሕመድ ተጠያቂ ነው። በደምብ ይጠየቃል እንጂ! ተጠያቂነቱ ከዚህ ይጀምራል።

 

አማራ በየቀኑ እየተባረረ፤ መጨፍጨፉ አቶ ተድላም አምኗል። ጨፍጫፊዎችም እነማን እንደሆኑ ለአቶ ተድላ ግልጽ ነው። አማራን በመጥላትና አማራን በማስጨፍጨፍም ይሁን አማርኛ ቋንቋን ለማጥፋት ስኬታማ ናቸው ብሎ የሹመት እውቅና ሰጥቶ፤ ግድያና ጥላቻ የሚያስፈጽሙበት ዕድሎች መርቆ የከፈተላቸው ነብሰ ገዳዮች እና ወንጀለኞች አብይ አሕመድ ነው። 3000 አመት እንገዛችሗለን ብሎ አዲስ አባባ ውስጥ በቴ/ቪዥን ቀርቦ የተናገረው “ሌንጮ ባቲ” የአብይ አማካሪ ነው። አደለም እንዴ?

 

እነ ታየ ደንዳኣ “አማራው ቡራዩ ላይ ምን ይሰራል በጭነት መኪና ተጭኖ ወደ ጎጃም ይሂድ” ብሎ የተናገረው የኦሮሞ ቄሮ ኢንተርሃሙዌው ካድሬ እና “ነፍጠኛን በቀበረን ቀብረነዋል፤አማራን ሸውደንም ሆነ አሳምነን በቁጥጥራችን አድርገን መቸም ቢሆን እንደማይነሳ አድርገን ቋንቋውን አጥፍተነዋል፡ ላሚትዋንም ወተትዋንም እጃችን ውስጥ ገብታለች…..” እያለ ኢንተርሃሙዌው ቡድን በግልጽ አዋጁን ለተከታዮቹ ያበሰሩት ኢንተርሃሜዎች ማን ነው የሾማቸው? ይህ ሁሉ ስያደርጉና  ይህ የዘር ማጽዳት አዋጅ ማወጅ ነው፤ ተብሎ እንደ  አቤቱታ ሲቀርብለትም አብይ አሕመድ ለምን አልተከፋም? ምክንያቱም ፍላጎቱ እየፈጸሙለት ስለሆነ ነው።

 

የሻሸመኔ ከንቲባ ሕዝብ በነገዱ እየታረደ ነው ንግድ ቤቶች እየነደዱ ነው ብሎ ከንቲባው ለሺመልስ አብዲሳ “ሥልክ ደውሎ” አስቸኳይ እርደታ ላክልኝ ሲለው፤ ሺመልስ አብዲሳ ከንቲባውን ምን ነበር ያለው “አያገባህም! ቤትህ ገብተህ አርፈህ ተኛ ብሎ ተቆጣኝ!” ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡ ብሎ ከንቲባው በአደባባይ ተናገረ። አብይ ምን አደረገ? ምንም!!!  

 ታዲያ ኢንተርሃሙዌው ቡድን ምን እየተናገረ እንዳለ እና ምን እየፈጸመ እንዳለ አብይ አሕመድ አያውቅም? የውቃል እንጂ!!!

 

አብይ አሕመድ የኢንተርሃሙዌው ቡድን መሪ ነው። ኦሆዴድ ደግሞ ለ30 አመት ከወያኔ የተቀናጀ “ኢንተርሃሙዌ” ነበር አሁንም ነው። ሲጀመር “አሁንም ለ30 አመት አማራን በመግደል ወንጀል የተጠመደ አደገኛ የወንጀለኞች ስብስብ ድርጅት ነው” ብየ ስል እውነት ነው። ተድላ ይህንን አይስተውም።

 

ኦሆዴድ የተባለ ድርጅት መሪው ማን ነው? አብይ አሕመድ! አዲስ አበባ ፍንፍኔ እያለ የሚጠራ ማን ነው? አብይ አሕመድ! አዲስ አባባ የነ አቢቹ የነ ገላን ጥንታዊ መሬት ነውና ፍንፍኔ የኦሮሞ ነች እንጂ የማንም አይደለችም ብሎ ያለው ማን ነው?  አብይ!!!

 

አማራውን ብቻ አይደለም እኮ ‘ውጡ’ እየተባሉ በአብይ መንግሥት እየተደገፈ የነገድ እልቂት የተፈጸመበት። ሲአዳማ ተወላጆችም ተጠቅተዋል። ለምሳሌ “ከኦሮሚያ ክልል ባሌ ጎባ ዞን ከ 5 ሺ በላይ የሚገመቱ የሲዳማ ተወላጆች ተፈናቅለዉ “በደቡብ ጭሪ ወረዳ” ፈስሰዉ እንደሚገኙና በሺዎች የሚቆጠሩ በየጫካዉ በመንገድ ላይ መሆናቸዉን እና  በእቅዱ መሰረት  ከቀሩት ሶስት ቀበሌዎች ዉስጥ የሚኖሩት የሲዳማ ተወላጆች እንዲፈናቀሉ ከተደረገ ባማካኝ ወደ ሰላሳ ሺ የሚጠጉ ዜጎች ለስደት እና ለረሀብ አደጋ እንደሚጋለጡ ከስደተኞቹ መሀከል ከአነጋገርነው ግለሰብ መረዳት ችለናል ። የሚል (September 11, 2017) ‘በኢትዮ ኤክስፕሎረር’ እና የዜናው ምንጭ ‘አባይ ሚዲያ’ የዘገበው ዘግናኝ የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ‘ቅጂ’ በአብይ ንግሥና ተፈጽሟል።

 

አብይ ወደ ባሌ ሄዶ የተናገረውን ሌላ ቀን አቀርባለሁ።

 

 በባሌ ክ/ሃገር (ክልል) በሮቤ ከተማ ደግሞ የከተማው ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ በመሃል ሜዳ ቆሞ በብዙ ሺሕ ሰው ፊት

 

“ከባሌ አባ ገዳዎች፤ከሃይማኖት አባቶች፤ከአገር ሽማግሌዎች እና ከቄሮዎች የአቋም መግለጫ ከተንጣለለው የገበያ አደባባይ በቪዲዮና በድምጽ የተቀረጻ አዋጅ ከድምጽ ወደ ጽሑፍ የገለበጥኩትን ላስነብባችሁ እና አብይ አሕመድ ሓለፊነቱን በብቃት መወጣቱን አለመወጣቱን እናንተው ፍረዱ፡ ይኼው

እንዲህ ይላል፦

 

“ዶርዜና ነፍጠኛ ከሚባል ማንም ሰው ግንኙነት አድርጎ የተገኘ ሰው ፈጣሪ መአት እንዲያወርበት በሼኮች የተረገመ ሲሆን ይህንን ትዕዛዝ ተላልፎ የተገኘ ከነፍጠኛ እና ከጠላት ለይተን አናየውም። ይህን በተመለከተ

1) ከዛሬ ቀን ከዚች ሰዓት ጀምሮ ከነፍጠኛ እና ከዶርዜ ንግድ አንገዛም አንሸጥም።

2) ከዛሬ ጀምሮ መግብ መጠጥ ልብስ ሲገበያይ የተገኘ ሰው የተረገመ ይሁን።

3) ከነፍጠኛ እና ከዶርዜ በልተህ ብትገኝ ፈጣሪ በሽታ ያድርግብህ፤

4) ይህ ድርጊት ፈጽሞ በሃይማኖት በሸኮች የተወገዘ ነው።

5) የኪራይ ቤት ወይንም ሱቅ በረንዳ ይህንን የመሳሰሉትን ከዛሬ ጀምራችሁ ካሁንኑ ሰዓት አከራይታችሗቸው ከሆነ እንድትነጥቁዋቸው።ያላከራያችሗቸው ከሆነም እንዳታከራይዋቸው። እንጠይቃችሗለን፡

6) መሬት እና ቤት እንዳትሸጡላቸው። አሁንም ለመውጣት ተዘጋጅተው ለመሸጥ ከፈለጉም እንዳትገዝዋቸው። መሬቱ የናንተ ነው፤ቤቱም የናንተ ነው።

7) የእህል ወፍጮ ቤት የንግድ ተቋማትም እንዲሁ የመኪና አገልግሎት የመሳሰሉትን አገልግሎቶች ለነዚህ ሰዎች አትፍቀዱ፤ እናንተም እንዳትጠቀሙ። ይህንን አድርጎ የተገኘ ነፍጠኛ ነው ማለት ነው።

8) ዛሬ ሰልፍ የወጣነው ጀግናችን የቄሮ አባት የሆነው “ኦቦ ጃዋር መሓመድ” ላይ ጠላት ለመግደል ሙከራ ስላደረገበት ድምጽ ሆነንለት ነው። ጃዋርን የሚቃወም መቼም ቢሆን የባሌ ሕዝብ ጠላት ነው።

9) የልጆቻችን ህይወት ያጠፉ የመንግሥት አካል የሆኑ፤ ደሞዝ የሚከፈላቸው መስተዳደሮች፤ ትናንት ልጆቻችንን የገደሉ፤ለፍረድ ይቅረቡልን።

 ይላል።

 

እንግዲህ ይህንን የዘር ማጥፋት ጥሪ ከተላለፈ በኋላ የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ድርጅት ጽ/ቤት የዘር ማጥፋት አዋጁ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት አደጋውን ለማስቆም ለአብይ አሕመድ ያስተላለፈው አስቸኳይ ጥሪ “አስቀድሞ ማስጠንቀቅ የዜጎችን ህይወት መታደግ” የሚል የባሌ ሮቤ አክራሪዎቹ እና አባ ገዳዎቹ እንዲሁም ሼኮች እና ቄሮዎች ከሰኞ ጀምሮ ሊወስዱት የተዘጋጀው “የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አዋጅ/ጀነሳይድ” መግለጫ በጽሑፍ አስታውቆታል።

 

 የተፈራው እልቂትም ደረሰ። በዛው ዓርብ ዕለት አዋጅ ታውጆ ለሰኞ እንመለሳለን ያሉ ታጣቂዎች ዓርብ ጥቂት ቀናት በፊት በአማራ ብቻ ሳይሆን በጋሞ ነገዶች ላይም ጥቃት ፈጽመው ነበር። መንግሥት ይህንን ያውቃል። የጋሞ ነገዶችም አርባ ምንጭ ውስጥ ለዜጎቻቸው ስጋትና ደህንነት ሲሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ። ሰሚ አልነበረም። 

 

ይሁንና እነዚህ በሃይማኖታቸው እና በነገዳቸው ተነጥለው ለግድያ የታጩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዶርዜዎች እና አማራዎች እንዲሁም ክርስትያኖች በቤተክርስትያን ተጠልለው በፍርሃት ቆፈን እየተንቀጠቀጡ፤ የአብይ አሕመድ መንግሥት እንዲያድናቸው የመንግሥት ያለህ/የአብይ ያለህ/ ሲማጸኑ ነበር። ይህ ደግሞ አበይ በደምብ መረጃውም ጥሪውም ደርሶታል።

 

 ጋሞዎች ምን የሚል መልእክት ለአብይ አስተላለፈው ነበር? እንዲህ ይላል ፤

 

“መንግሥት ሕግን ማስከበር የሚችል ከሆነ ያስከብር የማይችል ከሆነም እራስችንን ለመከላከል የምንጠብቅበት መንገድ ሁሉ ለመጠበቅ እንገደዳለን” ብለው ነበር። ሆኖም አብይ ይህንን አቤቱታ እና ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም “ግድያው ይቀጥላል፤ ከዚያ ይሰክናል” እያለ ነበር። በዚያው አዋጅ መአት ጋሞዎችና አማራዎች በሚያሳዝን አገዳደል ተጨፈጨፉ። ይህ የሆነው ጥቅምት በፈረንጅ ኦክተበር መጨረሻ ገደማ 2019 ነው።

 

አቶ ተድላ ግን አብይን በሃላፊነት የሚጠይቅን ፍትሃዊ ጥያቄ “የፖለቲካ መፈክር” ሲል አጣጥሎታል። ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊውን አርዶ በላው ሲባል “እርዱ ይቀጥላል፤ እስኪሰክን ግን ዝም በሉ፤ እኛ ከሠልጣን ከወረድን በመቶ ሺዎቹ ይታረዳሉ” ስለዚም እርዳን አትበሉ ይልቅኑስ አመስግኑኝ! ሲል እርዱ ሕጋዊ አድርጎታል።

 

አማራ እየተገደልን ነን ብለው አቤቱታ ሲያመለክቱም አብይ ለሚታረዱ እና ለተፈናቀሉ አማራዎች እና /ክርስትያናትም/ “አልቃሾች” ሲል ሰድቧቸዋል።

 

ቃል በቃሉ ልጥቀስላችሁ፡_

 

 እንዲህ ሲል፤

 

“አንድም ሰው እሚያመሰግን የለም። ከእስላም አፍ “አልሓምዱላህን” ተነጥቋል። ክርስትያናትም ማመስገን የለም “ማልቀስ ብቻ” ነው። አልቃሽ ሕዝብ ደግሞ አይሻገርም። ችግር ብቻ ነው የምሰማው። “እናንተን እያረጋጋሁ ስራየን ልሰራ አልቻልኩም”። ሕዝቡ ሰላሙን ካልጠበቀ ይህ አሁን የሰማችሁት ልቅሶ ትናንትናም ብዙ ልቅሶ ነበር፤ አሁንም እናንተንም ሸኝቼ አዲስ አልቃሽ ይመጣል፤ የኔ ሥራ እምባ መጥረጊያ “ሶፍት’ ይዞ መቅረብ ብቻ ሆኖ ቀረ። ሁላችንም እየተጋፋፋን እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል? አደራችሁን በሚቀጥለው አመትም እንደዚሁ “መሃረም” ይዛችሁ ኑ፤ እንዳትረሱ። ወንድሙን ወንድሙን መንገድ የሚዘጋ ከሆነ ‘እኔ ምን አድርጌ እፈታዋለሁ?’ ሃይማኖታችሁ እንኳ የማይገዛችሁ ከሆነ? ምን አደርጋችሗለሁ እኔ! በልቅሶ ብዛት አገር አይገነባም እና ትንሽ እንኳን ብትሆን እያመሰገንን እንኑር።”

 

ሲል አንገቷን በካራ የታረደባት ባል፤ ህጻናት በካራ የታረደበት እናት፤ ሰውን ሰው በልቷል ብሎ ‘አቤቱ ሆይ! አድነን ፤ወታደር ላክልን፤ በክልልህ የሾምካቸው መሪዎች እየገደሉን ነው፤ እነሱን አስወግደህ ጤነኛ መሪዎችን አምጣልን ፤ አብያተ ጸሎታችን ተቃጠለብን፤ ብለው አቤት ለሚሉ የሃይማኖት መሪዎች እና ምእመናን “እኔ ምን አድርጌ እፈታዋለሁ?’ለምን አታመሰግኑኝም ማልቀስ ብቻ “አልቃሾች” እያለ ጉልበት የሌላቸው እናቶች እና ደከማ ተጠቂውን የሚሳደብ፤ ለሚቀጥለው ዙርም 'መሃረም አትርሱ' የኔ ስራ ‘ሶፍት ይዞ አልቃሹን እንምባ ማበስ ሆኖ ቀረ’ እያለ እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ነብሰጡሮች እና አረጋዊያን እና እናቶች ከመኖርያ ቤቶቻቸው እየተጎተቱ ወደ በረንዳና ጫካ ሲጣሉ፤ አብይ ደግሞ አቤት ስላሉ “አልቃሾች እና ምስጋና ቢሶች” እያለ ያሾፍባቸዋል።

 

አቶ ተድላ ደግሞ ‘ስለ አብይ ሓሊፊነት መውሰድ ጥያቄ ‘የፖለቲካ መፈክር’ ሲል ያሾፋል። ያውም እኮ አብይ እራሱ ስለ ሓለፊነት ምንነት ለተድላ አስፋውም ጭምር እንዲህ ሲል ነግሮታል፦

 

“ሓላፊነት የምንወስድ ሕዝቦች፤ ሰዎች መሆን አለበን። ሓለፊነት ችግር መፍታት ነው። መወሰንን ይጠይቃል። ከወሰናችሁ ደግሞ ተጠያቂነት ይመጣል። ለዚያ የተዘጋጀ አመራር ፤ለዚያ የተዘጋጀ ሕዝብ መሆን አለብን።” ይላል (አብይ አሕመድ)።

 

እንዴት ሲሆን ነው ታዲያ አቶ ተድላ አስፋው “ጠቅላይ ምኒስትሩ አማራዉን እያስገደሉ ነው፤ የሚለው ፖለቲካዊ መፈክር የወያኔ ደጋፊዎች ዐቢይ አህመድ የሚመራው መንግስት ይፍረስ ና ወያኔና የነጃዋር መንግስት ይምጡልን ማለት ነው።” ሲል አብይ አሕመድን ለአማራ ግድያና ሰቆቃ “ተጠያቂ አይደለም” ተጠያቂ ማድረግ “ወያኔና የነጃዋር መንግስት ይምጡልን ማለት ነው።” በማለት አማራ ገዳዮቹን እነ ጃዋር እና ወያኔዎች ይግዙን እያሉ ነው” ብሎ በሚሰቀጥጥ ድፍረት ሊሞግት ፈለገ?

 

ከዚህ ወዲያ ማስገደል፤ ምን ሌላ መልክ አለው? የግድ እራሱ ቆጨራ ይዞ ስላልተገኘ ነው? የገረመኝ ደግሞ “ብልፅግና ኦሮሞ ዉስጥ የ ኦነግ ጃዋር አንጃ ለአማራው ግድያ በወለጋ ተጠያቂ መሆን ይኖርባቸዋል።” ይላል። ብልጽግና መሪው ማን ነው? አብይ አደለም እንዴ? የብልጽግና አንጃ ማለት ማን ነው? ብልጽግና አንጃ አለው ብሎ አብይ አሕመድ ሲናገር ሰምተን አናውቅም። ባጭሩ “ሓለፊነት ችግር መፍታት ነው። መወሰንን ይጠይቃል፤ ከወሰናችሁ ደግሞ ተጠያቂነት ይመጣል። ለዚያ የተዘጋጀ አመራር ፤ለዚያ የተዘጋጀ ሕዝብ መሆን አለብን።” (አብይ አሕመድ) ብሎ ከተናገረ ታዲያ አብይ ችግሩን መፍታት አልቻለም፡ ምክንያቱም መወሰን አልቻለም። በቃ!!

 

 ይህ ደግሞ በተግባርም በምላሱም ደጋግመን ሰምተነዋል አይተነዋል። የአብይ ስራ ሚስቶቻቸው የተገደሉባቸው እርጉዞች እና ሽሎች ከማህጸናቸው ተቀድደው ወጥተው የታረዱባቸው እናቶች “አልተከላከልክልንም” ብለው እምባ ለሚያፈስሱ ዜጎች እና የቤተክረስትያን አባቶችም እናቶችም “አልቃሽ ሁላ፤ አታለቃቅሱ በናንተ ምክንያት ስራየን ልሰራ አልቻልኩም፤ ሥራየ እምባ መጥረጊያ “ሶፍት’ ይዞ መቅረብ ብቻ ሆኖ ቀረ። እያለ የሚያሾፍ መሪ ተድላ አስፋው አብይ አሕመድ የተደበቁም ያልተደበቁም ወንጀሎች ከተጠያቂነት ነፃ ነው ቢልም ሚሊዮን አማራ ከመቃብር ተነስቶ ድምፁን በማስሰማት ተጠያቂ ያደርገዋል! የጊዜ ጉዳይ ነው።

 

ሕዝቡ እንዲማርበት ፤በተለይ ወጣቱ ፌስ ቡክ ላይ “ሼር” አድርጉት። እኔ ጨርሻለሁ፤ ሌሎች እንዲመለከቱት ሼር አድርጋችሁ ሓላፊነታችሁ ተወጡ !

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ

No comments: