Sunday, June 10, 2018

ባሕር ዳር የተመሰረተው አዲስ የአማራ ንቅናቄ ታጥቦ ጭቃ ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)


ባሕር ዳር የተመሰረተው አዲስ የአማራ ንቅናቄ ታጥቦ ጭቃ
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)
በቅርቡ የተንጨበጨበለት አዲስ የአማራ ንቅናቄ ባሕርዳር ከተማ ተስብስቦ ዶ/ር ደስአለኝ ጫኔ በተባለው የንቅናቄው መስራች አባል ያደረገው ንግግር አድምጬ ገርሞኛል።

ይህንን ስለተቸሁ የምትንጫጩ አማራዎች እንዳላችሁ ዘንግቼው ሳይሆን፤ ለበርካታ አመታት አማራ ይደራጅ ብየ ስቆም በአማራዎች ስሰደብ የለመድኩት ጩኸታችሁ ስለሆነ አሁን በምተቸው ትችት የምትንጫቹ ካላችሁ ካሁን በፊት በኦነግ/ ህወሓት/ በአማራዎች/ በኢሕአፓዎች/ በግንቦት 7ቶች/ በሻዕቢያዎች ጩኸት እና ዘለፋ ያልተምበረከክኩኝ ብቸኛ ድምፅ መሆኔን ያልነቃ ሰው ብቻ መሆን አለበት በምተቸው ላይ ለመንጫጫት የሚዘጋጅ።

ችካጎ ውስጥ የሚኖሮው ግሩም የፖለቲካ ተንታኝ (ይህ ስል የምሬ ነው) ግርማ ካሳ (እኔም ካሁን በፊት ወያኔ ሲለኝ የነበረው እንዳለ ሀኖ ማለት ነው) የተባለ ጸሐፊ ሰሞኑን ስለንቅናቄው መመስረት የጻፈው ተመችቶኛል። ግርማ የሚለው፤ አማራን ከጥቃት ለመከላከል መደራጀታችሁ የምደግፍው ነው፤ ግን ከሌላው ሰፊ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ጋር  ቀልባችሁ እና ትኩረታችሁም ጭምር ካልጨመረ በአማራ ትኩረትና ግንኙነት ብቻ ተወስኖ ከቀረ ያው ከልላዊ እንጂ አገራዊ ትብብር ሊያገኝ አይችልም ባይ ነው። ይህ ልክ ነው የኔም ስጋት ነው።

ዛሬ ቀን በሚዲያ የተለጠፈው ከባሕር ዳር ከተማ የተላለፈው  በዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ የተላለፈው የመድረክ ንግግር ሳዳምጥ እራሱ እዛው አዳራሽ ያለውንም ሆነ መስራች ግብረሃይሉ አማራ በግራም በቀኝም ሲዋከብ 27-25 አመት (ሁለት አመት ከተኙበት ተንስተዋል እንበል) ጀሮ ዳባ ብሎ ተከናንቦ ሞቆት ሲያንኮራፋ ዘምኖ “እኛ ጥቂቶች” እባካችሁ የአማራ ምሁራን የት አላችሁ? ተነሱ ምን ነካችሁ?! ሕዝባችሁ አማራ በጸረ አማራ ሃይላት እየተጠቃ፤እየተገደለ ፤ እየተዋረደ ነውና እባካችሁ “በፈጠራችሁ” እኛ ጋር ኣብራችሁ ጩኹ፤ አስተምሩ አንቁት አነሳሱት እያልን ስንጮህ (ይህንን በማለታችን በአማራ ተወላጆች ሁሉ ሳይቀር ስንሰደብ) የነበርነውን ኢትዮጵያውያን ዜጎች ያደረግነውን እልህ አስጨራሽ ትግል ሳይታወስ፤ ስለ አማራ መጠቃት እና መነሻው እንዲሁም መነሳት እንዳለበት ያደረግናቸው  የጻፍናቸው በርካታ መጽሐፍቶች የጻፍን ከአማራ ውጭ ያለነው ጥቂቶች አንዳችንም አንኳ ለናሙና በታሪክ ፊት ሳያስታውሱን እዛው አማራ ለአማራ እርስ በርሳቸው እየተጠራሩ፤ የጻፉዋቸው መጻሕፈትም ሳይቀር እያሞገሱ ለሕዝብና ለታሪክ እያስተዋወቁ “አሁን ከእንቅልፋቸው ባንነው” አማራ ለአማራው በሚል መርሕ ሲመጋገሱ አድመጬ በጣም ነው የገረመኝ።

እኔስ ያው ትግሬ ነኝ “ትግሬ ትግሬ ነው፤ በአማራ ላይ ምን አገባህ ብለውኛል ‘አማራዎቹ ነን ባዮች” ግን ቅር ያለኝ ገናናውና ታላቁ ታጋይ፤ታላቁ ምሁር፤ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ስለ አማራ ሽንጡን ገትሮ ከማንኛችን በፊት ብቸኛ ድምፅ ሆኖ በግራም በቀኝም እየተሰደበ ወያኔ ከገባ ጀምሮ ስለ አማራ መጠቃት ለሕዝብ እና ለዓለም ከአስራት ወልደየስ ባልተናነሰ የታገለና ለአማራ የተሟገተ ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ እና ምሁራን ያልተነሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ወያኔ “የፋሺስት ስርዓት” መሆኑን ያስተማረ ብቸኛ ድምፅ የሆነው የ“አምሰትራዳም” ኗሪ ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ ስሙን ማንሳት ተጠይፈውት እርስ በርሳቸው ሲሞጋገሱ መስማት እጅግ ነው የገረመኝ።

ወዳጄ ሓኪም አሰፋ ነጋሽ ስለ አማራ በመድረክ መሟገት፤ ቃለ መጠይቅ ማድረግ፤ወያኔዎች በጻፉዋቸው የትግርኛ እና የአማርርኛ መጻሕፈቶቻው “ዘረኛ አማራ” እየተባለ እየተዘለፈ የታገለው ብቻኛው ብርቅየው ደ/ር አሰፋ ነጋሽ “እስር ቤት ካሉት አማራዎች የደረሰባቸው ሰቆቃ” እየዘገበ ፤ በሙያውም ጥናት በማድረግ ‘እናቶች አምካኝ መርፌ እየተወጉ እንዲመክኑ የመደረጉን ምስጢር’ ፤ አማራ በትራኮማ፤ በወባ እና በድህነት መማቀቁን ፤ የአማራ ህጻናት ለጥቃት መጋለጣቸው ፤ ያገሪቱን ሃብት ወደ ትግራይ እየተዛቀ የመሄዱን ወያኔ ከገቡ ጀምሮ እየታገለ በርካታ ሰነዶች እና መጽሐፍ የጻፈ ብርቅየው ሓኪም አሰፋ፤ አላስታወሱትም። አሰፋ የተቃዋሚ ሚዲያዎች ስለ አማራ እንዳይናገር ኢሳት/ ቪኦኤ/ ዶቸ ቨሌ,,,,፣ ሁሉም አግደውት ብዙ ትግል ያካሄደ “የአማራ ብቸኛው ድምጽ” አሰፋ ነጋሽስን ስም አንስቶ ባሕር ዳር ከተማ ውሰጥ በአማራዎች ምደር በታሪክ ፊት ማመስገንስ ይቅርባቸው ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ከጠቀሳቸው በአማራ ፀሐፍት የተጻፉ መጻህፍቶች እንኳ የዶ/ር አሰፋ ነጋሽ መጽሐፍት እና ሰነዶች መጥቀስ እልፈለገም።ለምን? እንደገና አሰፋ በተቃዋሚው ወገንተኛ ሚዲያ ድምፁ እንዲታፈን ተደርጎ እንዳያንስ እንደገና እነሱ ሲያንኮራፉ እሱ ባነቃቸው የዛሬ ጥዋት ምሁራን ተብየዎችም ጭምር ይረሳ? !!  ይኼ ይቅር የማይባል ነው።

ይህ ድርጅት ይግረምህ ብሎ “አማራ የኢትዮጵያ ኮለኒ ነች እና አማራን አስገንጥለን ሌላ አገር እንመስርታለን” ብሎ በማኒፌስቶ ይፍ ያወጠው “የአማራ ኦነግ” ብለን የምንጠራውን “ቤተ አማራ” የተባለው የቀኝ አክራሪ ድርጅት እና ሚዲያው ተደጋግሞ በዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ሲሞገስና ጭብጫባ ሲለገስለት መስማት ከመገረምም ገርሞኝ ይህ እንቅስቃሴ “ጤነኛ” እንደማይሆን ከተነገረው የመድረኩ ንግግር መገመት ችያለሁ። ለማንኛውም አገር ለሚያስገነጥሉትን እያሞገሳችሁ እርስ በርስ ከመሞጋገስ ይልቅ “ከዛ ከተከለላችሁበት አካባቢያዊ አጥር” ወጣ ብላችሁ ራቅ ከወዳለው ከወደ ሓረር የበቀሉ ትንታግ አማራዎችንም ዓይናችሁን ጎላ አደርጉ እና ሌለውም ዜጋ ከናንተ በበለጠ የታገለውን ሁሉ በታሪክ አስታውሱዋቸው። ግዮን ሚዲያ እያላችሁ “ቤተ አማራ” የሚፎልልበትን ሚዲያ ስታሞግሱ ለበርካታ አመታት ስለ አማራ እየተከታተሉ ሲዘግቡና ሲያስተምሩ የመበሩ የድረገጽ አገልጋይ ድረገጾች “ወልቃይት.ካም” “ኢትዮ-ፓትርዮሰትሰ” ድረገጽ አድራ (ሞረሽ” ራዲዮ ፤የኢትዮጵያን ራዲዮ (ስዊድን (ስቶክሆልም) የመሳሰሉ ራዲዮኖችና ድረገጾች ረሳችቸው።  ረጋ በሉ፡ አመድ አፋሽ እንዳትባሉ። ትናንት የመጣ ዓይን ዓወጣ! እንዳትባሉ። ‘ቤተ አማራ’ ምንማን ስትሉ “ኦነግ ኦነግ” የምትሉ ስለመሰለኝ ደንግጫለሁና ለማንኛውም መጨረሻችሁን በትዕግስት ወዴት እንደምታመሩ እንከታተላችለን። መልካም ዕድል እላለሁ ከወደ አሜሪካ።
የዘወትር ደምበኛችሁ
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay ድረገጽ አዘጋጅ)
            

No comments: