Wednesday, December 6, 2017

ፕሮፌሰርን ምን ክፉ ነካብን? ሰመረ አለሙ



ፕሮፌሰርን ምን ክፉ ነካብን?
ሰመረ አለሙ

በቅርቡ ሳተናዉ በተባለዉ የድረ ጥንጥን ስተላላፍ ፐሮፌሰር መስፍን ባልተለመደ መልኩ ዘረኝነትና ጎሰኝነት በሚል ርእስ ቱግ ግንፍል እያሉ ዲያሰፖራዉን ተመጣጣኝ ባልሆነ ስድበ ሲያስተናግዱት እኝሀ ፕሮፌሰር በስማቸዉ ጠላት ልኮ ካልሆነ በስተቀር የሳቸዉ ሊሆን አይችልም ብዬ ከራሴ ጋር ስሟገት ከቆየሁ በሗላ በእርግጠኝነት የሳቸዉ መሆኑን በወገን እርዳታ ደርሼበት ምን ነክቷቸዉ ይሆን በማለት እንዲህ ቱግ ግንፍል ያደረጋቸዉን ነገር ሳፈላልግ ከረምኩ።

እንደ እዉነቱ ከሆነ እንደ እሳቸዉ አይነት እድሜና ስም ጠገብ አንቱ የተባለ ዜጋ ላይ ብእር መምዘዝ በእጂጉ ከመክበዱም በላይ ከባህልም ጋር የሚያጋጭና ተፈታታኝም ጭምር ነዉ። በእርግጥ ወጣትና ጀማሪ ቢሆኑ ደግሞ ከዚህ ትምህርት አግኝተዉ ተጸጸትዉ ሊሰተካከሉ ይችላሉ ተብሎም በግል አድራሻቸዉም መጻፍ ይቻል ነበር። ነገር ግን ክሳቸዉና መልእክታቸዉ ሊሸፈንም ሊደበቅም ባለመቻሉ ለህዝብ እይታ መብቃቱ ግድ ስለሚል ወደ አደባባይ ይህን ጽሁፍ መላክ የግድ ብሏል።
የፕሮፌሰር መስፍን

የፕሮፌሰር መስፍን ዘመን ሲመረመር ቅድመና ድህረ ደርግ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል። ይህን ወደሗላ አቆይተነዉ ፐሮፌሰር መስፍን ከአቶ አለማየሁ ሞገስ (የቀድሞ የዩኒቨርስቲ መምህር) ከተቀያየሙ በሗላ አማራ የተባለዉን ማህበረ ሰብ ጥርስ እንደነከሱበት እሰከዛሬ ዘልቀዋል።

ክቡር አቶ አለማየሁ ሞገስም ኑዛዜዬ በሚለዉ ጽሁፋቸዉ ስለፕሮፌሰር መስፍን ዜጋ እንዲያዉቀዉ መልእክታቸዉን አስተላልፈዉ ነበር የፈሩት አልቀረም ፕሮፌሰር መስፍን አማራዉን ጥርስ እንደነከሱበት ዛሬም ድረስ አሉ። ዛሬ አቶ አለማየሁ ሞገስ የሉም ፕሮፌሰር መስፍን ግን በተለያየ ስብእና አሁንም አሉ።

አጼ ሐይለ ስላሴ የፕሮፌሰር መስፍንን ጎሳ ሳይጠይቁ ለዚህ ማእረግ አብቅተዋቸዋል ዛሬ አጼ ሐይለ ስላሴ እራሳቸዉን መከላከል በማይችሉበት ሁኔታ ፕሮፌሰር መስፍን እያነሱ ያፈርጡዋቸዋል ከሳቸዉም የደርገንና የወያኔን ዘመን በአሉታዊነት ያነሳሉ። ፕሮፌሰር መስፍን በነገርማሜ ነዋይ ሀገር መዉደድ ስሜት ተነሳስተዉ በጣም ለዉጥ ፈላጊና አብዮታዊ መስለዉ ሲቀርቡ እስቲ ያሰበዉን ይስራ ተብለዉ በንጉሱ ዘመን አዉራጃ ገዢነት ተሰጥቷቸዉ ነበር እሳቸዉ ግን ቅበሩኝ ብለዉ ባማላጂ አዲስ አበባ አራት ኪሉ ማኪያቷቸዊን እያጣጣሙ ቀርተዋል። አንባቢ በንጽጽር ሊያየዉ የሚገባዉ ግን ገርማሜ ነዋይ የአሜሪካ ትምህረቱን ጨርሶ ወደ ገጠር ሲመደብ ምደባዉን በደስታ ተቀብሎ ከገበሬዉ ጋር በመኖር ገበሬው የሚፈልገዉን አደረገለት እሱም በኢትዮጵያዉያን ዘንድ መልካም ሰመና ዝናን አተረፈ ተወዳጂም ሆነ በመጨረሻም ምንም ሳይጎደለዉ ለኢትዮጵያ ይጠቅማል ብሎ ባሰበዉ መንገድ ተጉዞ ዉድ ህይወቱን ለሀገሩ ሰጠ። ፕሮፌሰሩ የገርማሜ ንዋይን ያህል ለቤተ መንግስት ቅርበት ቢኖራቸዉ ያንን ጥቅማቸዉን ትተዉ እንደሱ መስዋእት ይሆናሉ ብሎ መገመት እጂግ ይከብዳል።

ከገነት ዘዉዴ መጽሀፍ እና ሌላም አጣቃሺ ማስረጃዎች ስንመለከት ፕሮፌሰር መስፍን ከወዳጃቸዉ ከኤርትራዉ በረከት /ስላሴ ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ከጠላት ተናንቀዉ ያቆዩ ዜጎችን አስደመሰሱ የኢትዮጵያ ምሰሶዎች በኢትዮጵያ ጠላቶች እንዲጠፉ ምሁራዊ ምክራቸዉን ለገሱ ከዚያ በሗላም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያን ሳትሆን እስከ አሁን እየተናጠች ትገኛለች ፕሮፌሰር መስፍንም ክወምበራቸው ዝቅ ሳይሉ በገዥዎች ተወዳጂ ሁነው ይኖራሉ ገዥዎችን ቀን ሲክዳችዉም ቀድመው አርበኛ ሁነዉ ለሚቀጥለዉ ተመቻችተዉ ብቅ ይላሉ በዚህ አሰራርም እጂግ ተክነዋል። ምናልባትም ፕሮፌሰሩ ከሀገሩ ተገንጥሎ ስለ መገንጠል ያወራል ያሉት የነበረከትን ምቾት ላለመንካት ዲያስፖራዉነ ለማጨናገፍ አስበዉም ይመስላል ዲያስፖራዉ ግን የተቀማዉ አገሩና ወደቡን እንዲህ በቀላሉ አይረሳዉም እሱ ባይደርስበትም ለተከታይ ትዉልድ አዉርሶ ያልፋል።

ፕሮፌሰር መስፍን ደርግ ቤት ወጣ ገባ እንደሚሉ የአደባባይ ምስጢር ከመሆኑም ባሻገር ብዙ የጽሁፍና የቪዲዮ ማስረጃዎች ተመልከተናል ኮለኔል መንግስቱም ይህንን አልደበቁም። ታዲያ የደርግ መንግስት መዉደቁ አይቀሬ መሆኑን የተገነዘቡት ፕሮፌሰር መስፍን ወዲያዉ ማሊያ ቀይረዉ ወደ ህዋአት አቀኑ። ሻቢያ እና ህወአት በለስ ቀንቷቸዉ ኢትየጵያን በተቆጣጠሩበት ጊዜ የአሜሪካዉ ሴናተር መፍትሄ ፍለጋ በተጠሩ ጊዜ https://www.youtube.com/watch?v=me5_siVG-ys ጀግናዉ ጎሹ ወልዴ ሊረዱኝ ይችላሉ ብሎ በማሰብ አጠገቡ አስቀምጧቸዉ ነበር ሰልፋቸዉን በቅጡ ያልተረዳዉ መኮንን። ይህ አገር ወደድ ዜጋ በእለቱ በተካሄደዉ ስብበሳ ታሪክን አጣቅሶ ከገንጣዮችና ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ብቻዉን ጉሮሮ ለጉሮሮ ሲተናነቅ ፕሮፌሰር መሰፍን ግን ተሳትፌያለሁ በሚል ቋንቋ መላ ቅጡ የጠፋ ንግግር አድርገዉ አዲሶቹን ገዥዎች ሳያስቀይሙ ተሰናብተዋል ከንግግራቸዉ በሁዋላም ከተገንጣዮቹ የፈገግታ ድጋፍ ተቺሯቸዋል ተመችተኸናል በሚል መልኩ። ከዚያም በሗላ በሳቸዉ በኩል ብዙ ቪዲዮዎችና ኦዲዎች በሳቸዉ በኩል ቢለቀቁም አንዳቸዉም ለትዉልዱ የሃገር ፍቅርን ሰሜትና የአንድነትን አሰተምሮት ያጣቀሰ መልእክት አልተገኘበትም ይልቁንም ኢትዮጵያን የሚያሳንስ የሚያንኳስስ ትዉልዱ ባለፉት አባቶቹ ጀግንነት እንዲያፍር ሁኖ የቀረበ ነበር፡ የሚገርመው ነገር ፕሮፌሰር መስፍን የሚከሰሱትን ስርአት ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆናቸዉ ስርአቱ ሲወገዝ እሳቸዉም አብረው መወገዛቸዉን መርሳታቸዉ ነዉ።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገሪቱን ሲቆጣጠሩ ፕሮፌሰር መስፍን ጊዜ ሳያባክኑ ከነመለስ ዘራዊ ጎን በመቀመጥ ተዉዋቸዉ የኛዉ ናቸዉ ብለዉ ሲያዘናጉ እነሱም ተረጋግተዉ የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በሀይማኖት መሸንሸን ጀመሩ እሳቸዉም ከነ ክንፈ አብረሀ ጋር በመሆን የጎደለውን እያሙዋሉላቸው ወዳጅነታቸዉን አጠናክረዉ የተረጋጋ ህይወትን ኖሩ። እኚህ ፕሮፌሰር የሰብአዊ መብት ጠባቂ ልሁን ብለዉ በመሰረቱት ድርጂት ሰፍር ቁጥር የሌለዉ አማራ ሲጋዝ፤ ሲገደል፤ በፖለቲካ ምልከታቸዉና በዘራቸዉ ዜጎች ሲጨፈጨፉ፤ ሲሰቃዩ፤ ለመንፈስና ለስጋ ስቃይ ሲዳረጉ የፕሮፌሰር ሰብአዊነት ግን እነሱ ዘንድ ሳይደርስ ቀር።

ፕሮፌሰር መስፍን በመርህ ደረጃ የያዙት አማራ የሚባል ነገድ የለም የሚል ነዉ። ህወአት የተባለዉ አማራን አጠፋለሁ ብሎ በመርህ ደረጃ የተነሳዉን ድረጅት ለማስደሰት ይመስላል።እዚህ ላይ አንድ ነገር የለም ከተባለ ባለቤት ስለሌለዉ ያገኘዉ ሊወስደዉ ሊያጠፋዉ ይችላል በህግም ዘንድ ተጠያዊነት አይኖርም የሌለን ነገር ማጥፋት። ፕሮፌሰር መስፍን በዚህ ምልከታቸዉ አማራዉን የገደለ ያባረረ ያሰቃየ (ፐርሶና ኖና ግራንታ ሰጥተዉታል) ለወያኔ አማራን መፍጀትም ህጋዊ መሰረት አስጨብጠዉታል ማለት ነው። የሚገረመዉ ጠላቱ ህወአት አማራ የሚባል ጎሳ አለ እጨርሰዋለሁ ሲል አማራዉ በተራው አለሁ ሲል ፕሮፌሰር መስፍን ግን የለህም በማለት ለጥፋት ዳርገዉታል።

ፕሮፌሰር መስፍን ሳይደበቁ የሚናገሩት የአማራ ጥላቻቸዉን ነዉ። ከህወአት መንግስትና መንግሰቱን ካቆሙት ጋር ወዳጅነትን ለመፍጠር ይመስላል ዘወትር የሚስነብቡን የትግራይን በደል ነዉ። ከእሳቸዉ በተጻራሪ መልኩ ግን ስብሀት ነጋ ከጥቂት አመት በፊት የሚቀጥለዉ 10 አመት የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን የትግራይን ህዝብ ወደ መካከለኛ የእድገት ደረጃ ማድረስ ነዉ ብሎ ነበር። ፖሊሲ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ፐሮፌሰሩ የሚያጡት አይመሰለኝም። አዲስ አበባ ያለዉ በትግርኛ የሚለምነዉ ለማኝ አገሩን የተቀማዉ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ መሆኑንም ፕሮፌሰረዉ አጥተዉትም አይደለም። የዘወትር መዝሙራቸዉ ግን ትግሬ ጭራሮ መሸከም ነዉ የተረፈዉ እያሉ ግን ሊያዘናጉን ይሞክራሉ። ፕሮፌሰር መስፍን በኢትዮጵያ ስም ብድር ተወስዶ ትግራይ ዉስጥ ኢንቨስት እንደሚደረግ ያዉቃሉ ትግራይ ተመጣጣኝ ባልሆነ መልኩ የአገሪቱን ሀብት መዉሰዷን ያዉቃሉ ለፌደራሎች ከተመደበዉ በጀት ፈሰሱ ወደ ትግራይ እንደሚሄድም ያዉቃሉ ኢፈርት የሀገሪቱን ኢኮኖሚም በሞኖፖል እንደያዘ ያዉቃሉ። ታዲያ ለፕሮፌሰር መስፍን ይህ ሁሉ ምንም አይደለም ማየት የሚፈልጉት በህይወት እያሉ ትግራይ እንደ ኤርትራ ነጻ ስትወጣ ማየትን ነዉ።

ፕሮፌሰርን እንዲህ ገንፍለዉ ዲያስፖራዉን የሰደቡበት ምክንያቱ ምን ይሆን ብሎ መጠየቅ አግባብነት ያለው ይመስላል። በቅርቡ አጼ ሐይለ ስላሴ የተሻሻለዉ ህገ መንግስት በስራ እንዳይዉል ጫና አድርገዋል ብለዉ የፃፉትን ጽሁፍ መልስ ለመስጠት እንደእኔዉ ሲያንገራግር የከረመዉ አቻምየለህ ታምሩ በታላቅ ጨዋነት ግማሺ ገጽ አክብሮቱን ከገለጸ በሗላ ወደ ዋና ጉዳዩ ገብቶ ፕሮፌሰሩ ያነሱት ክስ መሰረተ ቢስ መሆኑን ማስረጃ አስጨብጦ ታሪክ አሰረግጦ ተራዉ ህዝብ በሚገባዉ ቋንቋ አስነበበን በማህደራችንም ገባ። ታዲያ እንዲህ ያለዉን ነገር የልለመዱት ፕሮፌሰር መስፍን ይህን በማንሰላሰል ላይ እያሉ አስማማዉ /ጊዮርጊስ (http://www.mereja.com/amharic/556524) የተባለ ጸሀፊ መጻፋቸዉን ለማስተዋወቅ ከሚገባዉ በላይ አግዝፎ ወደ ኢትዮጵያ ሪቪዉ ለቀቀዉ። መልእክቱ ከተነበበ በሗላ አስተያየት ከሰጡት 36 ሰዎች መሀል ፕሮፌሰርን የሚደገፍ አንድም ነገር ጠፋ እንደዉም አንዳንዱ አስተዋዋቂዉን ጨምሮ ድባቅ መታ። እዚህ ላይ ፕሮፌሰር መስፍን አልቻሉም ነገር ተረባረበባቸዉ ቱግ አሉ ዲያስፖራዉን በጠላትነት ፈርጀዉ የግል ጉዳያቸዉን ከኢትዮጵያ ጋር አገናኝተዉ ሸለቱት። አይ የቀን ጎደሎ አለ በእዉቀቱ ስዩም። በፈረንጂ ብሰኩትና በምጽዋት የሚኖር፤ካገሩ ተገንጥሎ ስለ መገንጠል የሚያወራ፤ ፍርፋሪ ለቃሚ ዋጋ የሌለዉ እዛ ቁጭ ብሎ ልግዛችሁ የሚል ሀሜታና ህዝብ ለህዝብ በሚያጋጨ ሴራ ዲያስፖራዉን ባልተወለደ አንጀታቸዉ ደረማመሱት ለወያኔም በድፍረት አፍ ሆኑለት።

ሰዉ ተበሳጭቶ ጽሁፍ ባይጽፍ መልካም ነበር መጻፋቸዉን ያስተዋወቁት የኦክሰፎርድ/የል/ካምብሪጅ ምሁራንም የዲያስፖራዉ አካል በመሆናቸዉ በፕሮፌሰሩ ምላሺ አብረው ተብጠለጠሉ። ፕሮፌሰር እንደው ሌላዉን ቢረሱ እንዴት ጀግናዉ ጎሹ ወልዴን፤ጀግናዉ ፐሮፌሰር ጌታቸዉ ሐይሌን፤ዶክተር አሰፋ ነጋሸ፤ አቶ ጌታቸዉ ረዳ (ኢትዮ ሰማይ ብሎግ አዘጋጂ)፤ዶር አበባ ፈቃደን፤ፕሮፌሰር ሐይሌ ላሬቦ፤ ኢንጂነር (ዶር) ቅጣዉ እጂጉን በህይወት ባይኖርም፤ ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማን፤ / አክሎግ ቢራራን፤ፕሮፈሰር አልማርያምና ስፍር ቁጥር የሌላቸዉን ኢትዮጵያንን በአንድ ቅርጫት አድርገዉ ደፈጠጧቸዉ? እነሱም ለማኞች በፈረንጂ ምጽዋት የሚኖሩ ስለ ሀገራቸዉ የማያስቡ ዜጎች ናቸዉ ማለት ነዉ? ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሐይሌ ከዛዉ ካጠገቦ ጭቆናና በደልን በመጠየፍ የጨበጣ ዉጊያ ገጥመዉ የደረሰባቸዉን እንዴት በዚህ ባጭር ጊዜ ረሱት? በእርግጥ እነዚህ በትንሹ የተጠቀሱት ክብር ያላቸዉ እርሶ የተባሉ ዜጎች ለፍርፋሪ ብለዉ ነዉ ከስራቸዉ ተቆርጠዉ የቀሩት? አገር ያለ አግባብ መገንጠሉን ያለ ወደብ መቅረቱን በቁጭት ማንሳቱስ ጥፋቱ ምንድነዉ? ፕሮፌሰር ከእርሶ ምን እንማር? ያንን አይነት ስድብ በኢንተርኔት ሲለቁ ተመጣጣኝ መልስ አይጠብቁም? ዲያስፖራው በተሻለ ስብእና ላይ በመሆኑ አዝኖ ብቻ አልፎታል መልስ ግን ቸግሮት አይደለም።

ከላይ የተጠቀሱት ምሁራንና አገር ወዳድ ዜጎች የእርሶ አይነት ስብእና ቢኖራቸዉ 3 መንግስት ጋር ተመችቷቸዉ ይኖሩ ነበር ያንን በመጠየፋቸዉ ነዉ ከስራቸዉ ተባረሩት ለስደትም የበቁት ነገር ግን ከሀገራቸዉ ከወጡ ጀምሮ ይህ እኔና አብዛኛዉን የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ያጠቃልላል አንዴ ፋሺስቱን ደርግ አንዴ ደግሞ የትግሬ ፋሺስትን ቡድን እየተቃወምን ሃገራችን ወደ ቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ በጽሁፍ፤ በተቃዉሞ ሰልፍ፤ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በማድረግ፤ የማቴሪያልና የገንዘብ እገዛ በማድረግ ሌት ተቀን ስለሀገራችን እያሰብን እንኖራለን እርሶንም በተለያዩ ስብሰባዎች በመጋበዝ ሃሳቦን እንዲያካፍሉን አድርገናል ከንግግሮ ብዙም ፍሬ ባናገኝበትም።

እንደአዉነቱ ከሆነ እንደእርሶ ተስማምቶት ከተቀመጠዉና ብትር ካቃበለዉ ምሁር ይልቅ ዲያስፖራዉ ለሀገሩ ከምንም በላይ መስራቱን በኩራት ሊነገሮት ይገባል ይህ ዲያሰፖራዉን ከወገኑ ለማለያየት የጠነሰሱት ተንኮል ከህወአት የተሰጦት ተልእኮ ሊሆንም ይችላል የሚያጣጥሉት ዲያስፖራ ቤተሰቡ ያለዉ ኢትዮጵያ ነዉ እርሶ ባስቀመጡን መልኩ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በሚያዉቀን መልኩ ያዉቀናል። እዚህ ላይ በግል ሳልጠቅሰዉ የማላልፈዉ አቶ ጌታቸዉ ረዳ (ኢትዮ ሰማይ) ይህ ግለሰብ በትዉልዱ የትግራይ ተወላጅ መሆኑን ያዉቀታል ይህ ዜጋ ከማቴራሊያዊ ጥቅም ይልቅ፤ የህወአት አባል ሁኖ ሊያገኘው ከሚችለው ጥቅም በላይ የሀገር ፍቅር ሰሜቱ ስለበለጠ ያንን ጥቅሙን ትቶ ከወያኔ ጋር ተናንቆ ሊያገኝ የሚገባዉን የወንጀል ጥቅም ወዲያ ብሎ በኩራት ይኖራል ክብር ለጌታቸዉ ረዳ። እሱ ኩራት ራት ቢል ያምርበታለ ከእርሶ ይልቅ።

ፕሮፌሰር በእርሶ ዘመን ጥቂት ፕሮፌሰሮች ስለነበሩ ዘመኑ ቢያልፍም የክብሩ ትዝታዉ አእምሮዉ ዉስጥ ስለቀረ የቀደመ ክብሮን ሊያቆዩ ግብ ግብ የያዙ ይመስላል። ፐሮፍ ዛሬ 23 አመት ጀምሮ ወጣቶች ፕሮፌሰር እየሆኑ ነዉ ዛሬ ለዜጋ የምንሰጠዉ ክብር በትምህርቱ ታላቅነት ሳይሆን ለሀገሩ በሚከፍለዉ መስዋእትነት ነዉ። አጼ ተዎድሮስ፤ አጼ ምንሊክ፤ አብዲሳ አጋ፤ በላይ ዘለቀ፤ አብቹ ነጋ ነጋ፤ ገበየሁ ባልቻ፤ ደጃዝማች አፈወርቅ፤ የጥቁር አንበሳ ጀግኖችን ድምበር ሳይገድበን ከመቃብር በላይ የምንዘክራቸዉ ለሀገራቸዉ ባደረጉት መስዋእትነት እንጂ በትምህርታቸዉ ብዛት አይደለም ምሁር ይፈለፈላል ጀግና ግን ተመጥኖ ነዉ የሚሰጠዉ። ፕሮፌሰር አስራትም እዛዉ እርሶ ሰፈር ሀገር አይገነጠልም ኢትዮጵያ ያለወደብ አትቀርም ብለዉ ለሀገራቸዉ በህይወት መስዋእትነት ሲከፍሉ ገድላቸዉ ግን የእርሶን ቀልብ አልሳበም። እንደእርሶ ተገላብጦ ኑሮ ዛሬ አገርና ወገን ላይ ሲቀልድ ማየት በእጅጉ ይከብዳል እባክዎን ቃላቶን ይመዝኑ በቅርቡ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለኢሳይያስ አፈወርቅ የሰጡትን ክብር ኢትዮጵያዉያንን አይንፈጉዋችው። / መራራ ጉዲና / ብርሀኑ አጠገብ ተቀመጥክ ተብሎ መከራውን ሲያይ እርሶ አፈወርቂን ከአዋቂ በላይ አዋቂ ክመሪ በላይ መሪ አድርገው ወድ አዲስ አበባ ሲመለሱ በእቅፍ አበባ ነው የተቀበሎት። ይተውን የተጎዳን ህዝቦች ነን ማቴሪያላዊ ጥቅም ሳናጣ የሀገራችን ጉዳይ እየቦረቦረን ነው ያለነው።

ማጠቃለያ
ፕሮፌሰር ለእርሶ ስለ ሀገር መገንጠል ብዙም አያሳስብም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር መሸንሸኑም ችግሮም አይደለም፤ ትግራይ ሰፍቶ ሰፍቶ ሸዋ መድረሱም ችግር አይደለም፤ 100 ሚሊዮን ህዝብ ያለ ወደብ መቅረቱም አያሳስቦትም ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደርም ችግር የለዉም። ለእርሶ ትልቁ ችግሮ አማራ የተባለ ማህበረ ሰብ ነዉ አገሩን ተቀማ ተባረረ ለማኝ ሆነ ባመክን መድሀኒት ማህጸኑ ደረቀ፤ እግሩ መቆሚያ አጣ ከዚህ በባሰ መልኩ ምን ምን እንዲሆንሎት ይፈልጋሉ። አረ ፐሮፍ ከርሶ የምንጠብቀዉ ምሁራዊ ምልከታዎን ነዉ እንጂ ብሺሺቅ አይደለም የአንድነት ሐይሉን እያሳደዱ አይተናኮሉትየመዉጊያዉን ብረት ብትቋቋም ላንተዉ ይብሰብሀልየሚል የመጽሀፍ ጥቅስ ስላለ ያብላሉት ሁል ጊዜ አርበኛ መሆን የለም መስከንም እድገት ነዉ።

በዉነቱ ከዚህ በላይ ብዙ ብዙ ማለት ይቻል ነበር እርሶ እንዳሉን ከባህላችን አፈንግጠን የወጣን በአየር ላይ የተንሳፈፍን ዜጎች ሳንሆን ኢትዮጵያን ተሸክመን የምንዞር ኢትዮጵያ ኢትዮጵያን ሁና እንድትኖር ሳንታክት የምንሰራ ዜጎች መሆናችንን በድፍረት ልገልጽሎት እወዳለሁ። በዉጭ የተሰጠን ስም ኢትዮጵያዉያን አገራቸዉን ይወዳሉ የሚል ነዉ የእርሶ ስም በክፉም በደጉም ይነሳል በተሳሳተና ማስተዋል በጎደለዉ የሰጡት አስተያየት ነዉር ስለሆነ ምናልባትም ከዚህ ጽሁፍ በጠነከር መልኩ ወደፊት እርሶ ላይ ያነጣጠረ ጽሁፍ ሊወጣ ስለሚችል ይቅርታ ቢጠይቁበት ኩራትና አዋቂነት ስለሆነ በይቅርታ ታላቅነቶን ያሳዩን እላለሁ በእኔ በኩል በታላቅ አክብሮተ እሰናበቶታለሁ። ለማንኛዉም መልካም እድሜና ጤንነት።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
semere.alemu@yahoo.com

No comments: