Thursday, November 23, 2017


ወንድ ቅምጦች እና የተጧጧፈው የፌስቡክ ገንዘብ ልመና!




ወንድ ቅምጦች እና የተጧጧፈው የፌስቡክ ገንዘብ ልመና!
(
ሁሉም አንባቢዎቸ ልታነቡትና ልትጠነቀቁበት የሚገባ ጉዳይ)
(
አሌክስ አብርሃም)

አንዲት አውሮፓ የምትኖር ሴት ከአንድ አገራችን ላይ ሙጥቅላ እውቅና ካለው ሰው(የወንድ ሞዴል እና አንድ ሁለት አማርኛ ፊልሞች ላይ የሰራ ተዋናይ) ጋር በፌስቡክ ትተዋወቃለችቀስ በቀስም የልጁ አቀራረብና ሁሉ ነገሩ ይማርካታል ….ሲጀመር ቀለል ባለ ስጦታ ሲቀጥል ጠቀም ያለ ገንዘብ በመላክ ፍቅሯን መግለፅ ጀመረች …. የላከችበት ምክንያት ደግሞ ልጁ ጋር በፌስቡክ ትውውቅ የጦፈ ፍቅር ውስጥ በመግባቷና ስትመጣም እንደሚጋቡ በየቀኑ ቃል ስለሚገባላት ነበር! ቀን ከሌት ቫይበር ላይ ያወራሉየሚያበሳጨው ነገር የማይሆን የማይሆን የራሷን ፎቶ ሁሉ ልካለታለች (ላኪልኝ ብሏት)

በመጨረሻ እዚህ መጥታ ተጋብተው ሊኖሩ ይወስናሉ …. ልጁ አማላይ የሚባል አይነት ነው ….በቃ ይች ሚስኪን አፍቃሪ ወደኢትዮጲያ መጣች አጅሬው አገኛታ …. ጥብርር ያለ ዘናጭ ነው …. ሴቶች ሰፍ የሚሉለት ለግላጋ አቋምእናም ‹‹አፈስኩት›› አለች ላቧን ጠብ አድርጋ ባጠራቀመቻት ብር ኢትዮጲያን ከሰሜን እስከደቡብ ይሄን ልጅ እያዞረች አስጎበኘች ተዝናኑ ብሯን ራሷን ሁሉን ነገሯን ሰጠችውቤተሰቦቿ ጋር እንኳን ያሳለፈችው ሙሉ ቀን አልነበረምልጁ የተለያየ ምክንያት አቅርቦ ከአንድ አመት በኋላ ሊጋቡ ቃል ተገባብተው ተመልሳ ሄደች . . . አይታው ከሄደች በኋላ ፍቅሯ ባሰባት ….

ብቸኝነቱ አለ በዛ ላይ ውጭ አገር ሲኖር የኔ የምንለው ሰው እንደሰው መከበር መፈቀር ይናፍቃልና ….በዚህ ልጅ ፍቅር አበደችችግሩ እሱ እንደበፊቱ አልሆን አለስልክ አያነሳምፌስቡክ ላይ ይገባል ብትፅፍለት አይመልስም …..አበደች ….‹‹ምን ሆንክ ምን አጠፋሁ ›› ስትለው ‹‹ባክሽ ለስራየ ፈቃድ ላወጣ አምሳ ብር ጠይቀውኝ ደብሮኛል ››…ሚስኪን አፍቃሪ ‹‹ታዲያ እኔ እያለሁልህ›› አለችና ቁጥር ቁጥር አድርጋ ላከችለሳምንታት ፍቅሩ መለስ አለለትፕሮፋይሉን ሁሉ ስታተሱን ቀየረው ‹‹ኢን ሪሌሽን ሽፕ›› ብሎ ደስ አላት ! የሚያስቀው ብር ስትልክኢን ሪሌሽን ሽፕካላከች ደግሞ ሲንግል ይሆናል ስታተሱ !!

ይሄ ልጅ ቀስ በቀስ የጋራ ጓደኞቻች ከሆኑ አንዳንድ ልጆች እንዳጣራሁት መልኩን እና ይችን እውቅና እያስያዘ ፌስቡክ ላይ ከሚያጠምዳቸው ሴቶች ብር መቀበልና ኑሮውን መግፋት ስራው ያደረገ ሰው ነበር !! ቆይቶ ይችኑ ልጅ ‹‹ቤቴ ሌባ ገብቶ መርፌ አልቀረም ሙጥጥ አድርጎ ዘረፈኝ ›› የሚል መልእክት ላከላትደነገጠች እናም ከልብ አዝና እጇ ላይ የነበረውን ብር ላከችለትእንደውም ብር ያንሰኛል ብሏት ተበድራ ሁሉ ጨምራለች ….ነገሩ በዚሁ ቀጠለ በአጥንቷ እስክትቀር ከሁለት አመት በላይ አራግፏት በመጨረሻ አንድ አስገራሚ ነገር ተከሰተ . . .

ልማደኛው ለአንዲት ሴት ተመሳሳይ መልእክት ላከየሚገርመው ለዚችኛይቱ ደግሞ የቤተክርስቲያን ልጅ ሁኖ ነው የቀረባት ….የዛን ሰሞን ኬት እንዳገኛቸው ባይታወቅም አራት የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ጋር ተነሳውን ፎቶ ላከላትፌስቡክ ግድግዳው ላይም ለጥፎ ልጆቸ ናቸው የሚል ትሁት ማስታወቂያ ቢጤ ጨመረበት ….‹‹ዋው›› ምናምን ተባለለት …‹‹በጎ ደግ ››ብለው አንዳንዶች አሞካሹት እንደዛ ሽክ ብሎ ድሪቶ የለበሱ ልጆች ማቀፉም እንደፅድቅ ተቆጠረ !

እና ምን ቢል ጥሩ ነው …‹‹ቤተሰብ የሌላቸው ከጎዳና አንስቸ የማሳድጋቸው የማስተምራቸው ብዙ ልጆች አሉ አሁን ግን ከአቅሜ በላይ ሆነ ትምህርት ምግብ ወጭያቸውን በግሌ መሸፈን ከበደኝ ›› ልጅት አዘነችእንደውም ጓደኞቿ ጋር ደውላ ሁሉ ጉዳዩን በመንገር ብር ለማሰባሰብ ሞከረችእንግዲህ አንዷ የቅርብ ጓደኛዋ የዚህ አጭበርባሪ የመጀመሪያ ሰለባ የሆነችው ልጅ ናትእንደውም ያጠመዳት ከመጀመሪዋ ልጅ ጓደኛ ዝርዝር ውስጥ ነው !

ይሁንና ይህን በጎነቱን መደበቁ አላስከፋትም እንደውም አደነቀችውምናልባትም ብር የማይበቃው ለዚህ ይሆናል ብላ ሳታስብ አልቀረችም ….ቆይቶ ግን አጅሬው ለሁለተኛዋ ሴት አንድ መልእክት ላከ … ‹‹ ቤቴ ሌባ ገብቶ ስልኬን የስራ ካሜራየን አዲስ ሊወጣ ቀረፃው ያለቀ ፊልም ….ልብሴን እና ለልጆቹ ያሰባሰብኩትን አስራአምስት ሺህ ብርጥርግርግ አድረጎ ወሰደብኝ …››

በቃ ተባነነግን ምን ዋጋ አለው ለመጭው መጠንቀቅ እንጅ ያለፈው አለፈብላ ተወችው ልጁ ግን ዛሬም በአማላይ ፎቶዎቹ ፌስቡክ ላይ እየተንጎራደደ ይገኛል !
ኧረ አንድ ማስታወቂያም ላይ ዘወትር በቲቪ ብቅ እያለ ራሱንም ሸቀጡንም ይሸጣል ያሻሽጣል! ልጅቱ ይህን ታሪክ ከነልጁ የፅሁፍ ሜሴጅ ስክሪን ሹት ልካልኛለች … !!

*** *** ***

ዋናው መልእክቴ በጣም ብዙ ሴቶች ፌስቡክ ላይ ለተዋወቋቸው ወንዶች ተታለውም ይሁን በፈቃደንነት የገንዘብ የቁሳቁስ ስጦታ በመላክ (በተለይ ከአረብ አገራት) መጨረሻ ላይ ራሳቸውን ለማይሆን ኪሳራና ሃዘን እየዳረጉ ይገኛሉ
በእርግጥ ሰው ከወደደ ማንም የሚወደው ሰው እንዲቸገርበት አይፈልግምና መደጋገፍ ተገቢ ሊሆን ይችላል ….ግን እዚህ ስራ ፈቶ እየተሸቀረቀረ ቦሌ ክለብ ለክለብ ሲልከሰከስ የሚውል ቅምጥ ወንድ በፍቅር ስምም ይሁን እንዲሁ በትውውቅ ከአቅማችሁ በላይ የምታደርጉ ሴቶች እባካችሁ ከእንቅልፋችሁ ንቁ !!

እንደውም ብታፈቅሩ እንኳን ስጦታና ገንዘባችሁ የሩቅ ፍቅራችሁን በቁሙ ከመግደል የዘለለ ፋይዳ የለውምና እንስፍስፍ አትበሉ !! እድሚያችሁን ቤተሰባችሁን የመማሪያ ጊዚያችሁን እየሰዋችሁ ያላችሁት ገንዘብ አግኝቶ ራስን ለመቀየር ከሆነእባካችሁ ገንዘባችሁን በተገቢው እና ርግጠኛ በሆናችሁበት ጉዳይ ላይ አውሉት !! የእናተ ገንዘብ ፍቅር አይገዛም!”
ሌላው እዚህ ፌስ ቡክ ላይ ያላችሁ አንዳንድ የምትፅፉም ሁኑ ምንም የምትሰሩላይክ ላደረጓችሁ ውጭ የሚኖሩ ሴቶች ሁሉ ስኒከር ላኪልኝመነፅር ላኪልኝ እያላችሁ አስቀያሚ ጥገኝነታችሁ የሁሉም ኢትዮጲያዊ ባህሪ አታስመስሉመስራት ከቻላችሁ ተመስገን ብላችሁ ኑሩ !

ቢያንስ ስጋ ዝምድና ካልሆነም ‹‹ላኩልን›› ለማለት የሚያበቃ ጓደኝነት ሳይኖር እንዴት ከመሬት ተነስቶ ሰው ላገኘው ሁሉ ብር ላኩ እቃ ላኩ እያለ ይሟዘዛልደግሞ የበለጠ የሚገርመው የሴቶቹ ነውእውነቴን ነውእዚህ ‹‹እናት ለምን ትሙት ትቀመጥ በሙዳይ …›› የሚል ግጥም በፃፋችሁ ቁጥር ለነሱ የልባቸው የተነገረ በመሰላቸው ቁጥር እንደዘፋኝ ዶላር ወላ ዩሮ ቱቱ ብለው ግንባራችሁ ላይ መለጠፍ ያምራቸዋል! እውነቴን ነውእነሱ የሚመለከቱት መውደዳቸውን እንጅ የሚፈጥሩት የጠባቂነት ስነልቦና አይገባቸውም !!

እዩትላችሁ እናተ ላኪዎቹ የኪነጥበብ ሰዎችን መርዳት የለባችሁም ከልብ ካደነቃችኋቸው ስራቸውን በተገቢው ዋጋ ገበያ ላይ ሲወጡ ግዟቸውይሄ የመረዳት ስሜትን ሳይሆን ሰርቶ የማግኘት ስሜትን ከፍ ያደርጋል!! አቅማችሁ ከፍ ያለም ከሆነ አሳታሚዎች ከሚወስዱት ፐርሰንት ዝቅ ባለ ፐርሰንት ስራዎቻቸውን በህጋዊ ውልና ስምምነት ተፈራርማችሁ በማሳተም በጋራ እናንተም አትርፋችሁ እነሱም ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ትችላላችሁ !
በተረፈ የተቸገሩ የሚቀምሱ የሚልሱት ያጡ ሚስኪኖች ብዙ ስለሆኑ እነሱን እርዱ ! ማንኛውም የፍቅር ስጦታ ጥሩ ነውግን ከስጦታና ከገንዘቡ ፍቅሩ የተፈቀረው ሰው ራሱ ሲቀድም ነው ጥሩ የሚሆነው …!! በኋላ እኔ እንዲህ አድርጌለት እንደዛ ሰጥቸው ፈለጠኝ ቆረጠኝ እያሉ ማለቃቀስ ምንም ዋጋ የለውም !!

ባጭሩ ውጭ አገር ያሉ ሴቶችን ፌስቡክ ላይ እያጠመዱ በሚልኩላቸው ብር ዘና ብለው መኖር የሚፈልጉ ሽቅርቅር ወንድ ቅምጦች ስለተበራከቱ (( !!)) እንዚህ ወንዶች በእርዳታ ስምበሃይማኖት ተቋማት ስም በሌላም ዘወርዋራ መንገድ ሊመጡባችሁ ይችላሉ !! እናቴ ታማብኝ ማሳከሚያ ቸግሮኝ ሊሏችሁ ይችላሉ!! የማስላክ ሱሳቸው ጣራ ከመንካቱ ብዛት መንገድ ተሻግረው መግዛት የሚችሉትን ኮንዲሽነር እንኳን እንደከባድ ነገር በዚህ ሳምንት ካልደረሰኝ ሟች ነኝ ሊሏችሁ ይችላሉ!!

አሳማኝ ምክንያት ….እንዲሁም የእውነት በማድረጋችሁ የሚሰማ የመንፈስ እርካታ ከሌለ ሰባራ ሳንቲም ለማንም አትስጡ !! የለፋችሁበት ነዋ!! ሰው እድሜውን እድሜውን ለሚያሳጥር ነገር ይሰጣል ?? በዛ ላይ እናተ በምትረዱት ገንዘብ እዚህ ላቡን ጠብ አድርጎ የሚኖረው ሚስኪን ላይ ነው የሚጨማለቁት !!

ቅምጦች ደግሞ . . . ከምር በጣም ታስጠላላችሁ !!
ጨረስኩ !!

Posted at Ethiopian Sema –source Mereja

No comments: