Thursday, December 21, 2017

የትግራይ ትግርኚ ዓላማ መሠረተ ድንጋይ እየተጣለ ነው እንበል?

የትግራይ ትግርኚ ዓላማ መሠረተ ድንጋይ እየተጣለ ነው እንበል? ጌታቸው ረዳ www.ethiopiansemay.blogspot.com ስድራ ቤታት ትግርኛ ወይንም (የትግርኛ ተናጋሪ ቤተሰቦች) መተዳደርያ ሕገ ደምብ በሚል ቀን እና ዓመተምሕረት የማይጠቅስ “ለሰላም ፈላጊዎች ሁሉ” በሚል ርዕስ ስምና አድራሻ የሌለው ነገር ግን የኢመይል አድራሻ ተደርጎበት selamin_hiwinetn@yahoo.com የሰላምና የወንድማማችነት ምስረታ (የትግርኛ ተናጋሪ ቤተሰቦች) ተግባራዊ እንዲሆን ከጥቅምት መጨረሻ እስከ ሕዳር ወር አጋማሽ ድረስ (ብግሮጎርያን - ኤውሮጳ ኣቆጻጽራ) መስራች ጉባኤ ለመጥራት ቀነ ቀጠሮ ( ዓላማ) ስላለው ለዚህ ዓላማ መሳካት ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ ለማግኘት በደስታ እንጠባበቃለን። በማለት- የትግርኛ ተናጋሪ ቤተሰቦች የሰላምና የወንድማማቾች ማሕበር የሚባል አዲስ ድርጅት ለመመስረት እንደታሰበና ድርጅቱም ከትግርኛ ተናጋሪ “ቤተሰቦች” (የትግራይና የኤርትራ ትግርኛ ተናጋሪዎች) ብቻ ሳይሆን ከትግርኛ ተናጋሪው ብሄር ጋር አጎራባች የሆኑት (የኩናማ/ዓፋር…) ጋርም ወንድማዊ የሰላምና የአብሮ መኖር ትብብር እንደሚያደርግ ይህ “ማሕበር ሰላምን ሕውነትን ትግርኛ ስድራቤታትን ተዳወብቲ ብሄራትን” በሚል ራሱን የሰየመ አዲስ ድርጅት ሲደራጅ ዋና ጽ’ቤቶቹ ሽሬና እና መቀሌ እንደሚሆን ይገልጻል። የዚህ ድርጅት መስራች ማን እንደሆነ በግልጽ ባይታወቅም ግምታዊ ቢመስልም በእርግጠኝነት ማን እና እነማን ይህ አዲስ “ቤተሰባዊ የትግርኛ ተናጋሪዎች ሕብረት” ለመመስረት እንዳቀዱ ለማወቅ አያስቸግርም ። ወደ ዝርዝር ከመግባቴ በፊት የድርጅቱ ፖለቲካዊ እምነት “የቤተሰብ መብት” (ክላን) እና “የብሔር መብት” (አካባቢ) አንደሚከተል ግልጽ ሲያደርግ ከብሔር (ጎሳ?) ይልቅ ቅድሚያ “ለቤተሰባዊ ማሕበር” ቅድሚያ እንደሚሰጥ እና ለዚህም ምክንያት ሲገልጽ ቤተሰባዊ ማሕበር ሲከበር የብሔሮች መከበር ማለት ስለሆነ የብሔሮች መብት ሲከበር ደግሞ “የሕዝቦች” መብት መከበር ማለት ስለሆነ የዚህ ማሕበር መመስረት “ስድራቤታት ቅሳነት” (የስጋ ዝምድና፤የጋብቻ ትስስር) ያለው የቤተሰብ ሕይወት መብትና ግንኙነት በዘላቂነት የሚረጋገጥበት ምክንያትም ቀበሌ፤ወረዳ፤አውራጃ የሚባሉ ቤተሰብ የሰፈረባቸው አካባቢዎች የቤተሰብ (ፋሚሊ/ክላን) መሰረት ስለሆኑ ይህ የቤተሰብ ክፍል (ክላን) ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአያቶቹ ያስረዳደር ደምብ ስላሉት፤ ሕገ ደምቡ ሲጥስም ሆነ ፍትህ ሲፈልግ በአባቶቹ ስርአት እንዲተዳደር ስለሚገደድ ራሱ አስተዳዳሪና ፍትህ ሰጪ ስለሆነ ከውጭ አስዳዳሪና አቀነባባሪ ስለማይኖረው ማንነቱ የሚያረጋግጥበት ፍጹም ዘላቂ ሰላማዊ ሕይወት የሚረጋገጥበት ስለሆነ ቤተሰባዊ ማሕበር የብሄሮች ሁሉ መሰረቶች ናቸው። ይላል። ባጭሩ የብሔር ፖለቲካ አንድ ብሔር የውስጥም የውጭው ፍላጎቱ በመሰለው መንገድ ገደብ የለሽ የመሰለው መወሰን መተክያ የለውም ይላል፡(ይህ በራሪ ወረቀት የወደፊት “ግልጽ” አቋሙ ግልጽ ላለመድረግ በድብብቆሽ ሲገልጸው)። መልዕክቱ ደጋግሞ የሚያነሳው የብሔሮች መብት (ግልጽ ባያደርገውም እሰከ መገንጠል ድረስ ሊሄድ ይችላል) መከበር የሕዝቦች መብት መከበር ማለት ነውና ይላል። የዚህ ማሕበር ዓይነተኛ መመስረት በሚከተለው ዓረፍተነገር ግልጽ ያደርገዋል። “ማሕበር ሰላምን ሕውነትን ንዘረጋግጾ ሸቶ ሕውነትን ሰላምን ናይ ብሄረ ትግርኛ ኤርትራን ኢትዮጵያን ኣረኣያ ኾይኑ ናብ ኩለን ተዳወብቲ ብሄራት ክሰፍን ኽከባበር ዕቱብ ቅዱስ ጻዕርታቱ የከናውን፡፡””(የሰላምና የወንድማማቾች ማሕበር ዋናው ትኩረት የኤርትራና የትግራይ ትግርኛ ተናጋሪ ማሕበረሰብ ወንድማማችነትና ሰላማዊ ግንኙነት በአርአያነት መመስረት ሲሆን ሊያረጋግጠው ያቀደው ዕቅድም ወደ እነኚህ ተጎራባች ብሄሮችም እንዲሰፍንና እንዲከባበርያልተቆጠበ ቅዱስ ጥረት ያከናውናል። ይላል። የሚከተሉት ጥያቅዎች ጭሮብኛል።የኢትዮጵያና የኤርትራ ወንድማማችነት ለምን ወደ ጎን ተውት? የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ሰላማዊና ወንድማዊ ግንኙነት ለመመስረት አቀበት ነው ብለው ነው የተውት ወይንስ ወደ ታች ቆይቼ በምገልጸው የትግራይ ትግርኚ ምስረታ መሰረተ ድንግያ እንዲጥሉ ስለተፈለገ”? ግንኙነቱ እንመሰርተዋለን ዋናው መቀመጫ ቢሮዎቹም (ሁኔታው ሲመቻች ለወደፊቱ አስመራ፤ዓሰብ ባረንቱ እንዲሆን እንመኛለን) ሽሬ እና መቀሌ ይሆናሉ ሲል አስመራ ዓሰብ…ሲል የሻዕቢያው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ከወያኔዎች ጋር ሲታረቅ ማለት ነው ወይስ በዚህ ጉዳይ በጉዳዩ በምስጢር እጁ አስገብቶበታል? ኢሳያስ ከተወገደ ማለት ከሆነ ለምን በሁለቱ ብቻ ዕርቅ እንዲደረግ ተፈለገ? ሁለቱም ትግርኛ ተናጋሪዎች በተለያዩ አገሮች ማለትም (በኤርትራና በኢትዮጵያ) ተብሎ በሚታወቀው በዛሬው አነጋጋር በጠላትነት በሚተያዩበት እና ደም በተፋሰሱበት ሁኔታ አሁንም በደም በሚፈላለጉበት ሁኔታ ላይ የሚኖሩ መሆናቸውን እየታወቀ “ሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪዎች” ለማቀራረብ ቀላል የሆነበትና ከመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለማገናኘት የከበደበት ምክንያት ምን ይሆን? የደም መፋሰሱ ከተነሳ ጠቡ እና ደም መፋሰሱ በሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆን ጠቡና ጦርነቱ ከመላው የኤርትራ ሕዝብ ጋር እና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንደሆነ ዓለም የሚያውቀው ነው። ታዲያ እነኚህ መቀሌ ውስጥ መሠረታቸው የጣሉ አንዳንዶቹም እዛው የሚኖሩና አንዳንዶቹም ውጭ አገር የሚኖሩ የወያኔ አፍቃሪ ኤርትራዊያን ምሁራን እና በጠባብ ጎጠኛ ሕሊና የሰከሩ የወያነ ትግራይ ምሁራን ቡቹላዎች “ጠቡ/ጦርነቱ” በሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪ ማሕበረሰቦች የተወሰነ ጦርነትና ጥላቻ ነው ብለው መወሰናቸው መሠረቱ ምን ይሆን? ሁሉም ያካተተው ጦርነት ወያኔዎች ገና ሳይፈጠሩ እየተካሄደ እንደነበር እየታወቀ በትግርኛ ተነጋሪው ማሕበረሰብ ብቻ ሰላምና ወንድማማችነት ሲመሰረት ዋናው ቢሮው አስመራ፤ሽሬ አና መቀሌ እንዲሆን በማሕበሩ ሕገ ደምብ መቀየስ “ጣሊያንና እንግሊዞች የጣሉት” ፖለቲካ ትግርኛ ውልድ (ኦፍስፕሪንግ) መጣል ወየስ ………….? ማሕበሩ ሰላምና ወንድማማችነት በሁለቱም ትግርኛ ተነጋሪዎች ከተረጋገጠ በመላይቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ኤርትራዊ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር ሰላም ያውርድ አያውርድ የመኖር ዋስትናው በሸሬ፤ በአስመራና በመቀሌ በሚመሰረተው ቢሮ በኩል የመኖር ዋስትናውና ግንኙነቱ ይረጋገጥለታል ማለት ኢትዮጵያን ለዝንተ ዓለም የማስተዳደሩ ሕልም የተመደበ ክፍል አለ ማለት ነው? ከተቀረው ጋር ሰላም እንዲፈጠርለት ካልተመቻቸ ትግራይ ትግርኚ ሲመሰረትስ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ኤርትራዊ ዕጣ ፈንታው ምን ይሆን? ወይስ ትግርኛ ተናጋሪዎቹ ብቻ ከታረቁ የተቀረው በትግርኛ ተነጋሪ ክፍሎች የሚወሰንለት ዕቅርቀ ሰላም ዕድል መቸም ቢሆን በሊሂቅ ማሕበረሰብነቱ/ ኤሊትነቱ ወሳኝ ስለሆነ ወሳኝነቱ ለትግርኛ ተናጋሪው ክፍል ነው ማለት ነው? ይህ ንቀት ብቻ ሳይሆን፤ለትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነትም ኤርትራ ውስጥና ትግራይ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ጎሳዎች አደገኛ ፤ጠንቀኛ እና ከፋፋይ የፖለቲካ ተልዕኮ እንዳለው በምንም ሁኔታ አልጠራጠርም። ባለፈው ወር ትግራይ ውስጥ እና በሌሎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች የተደረጉ ስብሰባዎች የጎሳ ፖለቲካ ኤርትራ ውስጥ በነበረውና አሁንም በቆላ እና በከበሳ በአውራጃዊነትና እና በሃይማኖት ልዩነት እየሰፋ ያለው ቁስል እንደገና ለማስፋት ኤርትራ ውስጥ እስከ መገንጠል የሚል የጎሳ ፖለቲካ ታቅፎ ብቅ ማለቱ በተጨባጭ የዚህ በር ከፋችነትና ወያኔዎች ሆን ብለው እየቀየሱት ያለው የጎሰ ፖለቲካ አደገኛ ምልክት ይዞ ብቅ እንዳለ ከስበሰባዎቹ የተሰጡ የድርጅቶቹ መግለጫዎች መረዳት ይቻላል። ይህ አዲስ ድርጅት ደግሞ “በቤተሰብነት/በቋንቋ/በስጋ ዝምድና እና ባምቻ ጋብቻ”ሰላማዊ እና ውንድማዊ ግንኙነት ለመመስረት እስከ ተባበሩት መንግሥታት የሚሄድ ዕቅድ ምን ማለት እንደሆነ ለወደፊቱ የምናየው ክስተት ሲሆን፤ ድርጅቱ ከዚህ ሂስ ተምሮ ራሱን ካላስተካከለ የጎሳ ፖለቲካዊ ተልዕኮው ወደ 1940ዎቹ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ሕዝብን በጎሳ የሚሸነሽን ፖለቲካ በስፋት እድሜው እንዲራዘም የተደረገ የጎሰኞች/የፋሺስቶች አዲስ ሴራ ነው የሚል አምነት አለኝ። ባለፉት የጦርነት ታሪኮች ትግርኛ ተናጋሪው ብቻ ተዋግቶ ደም የተቃባ እና የመበዳደሉ ሁኔታ ጥላቸው ቅሬታው በሁለቱ ወንድማማቾች ብቻ ነው ብሎ የተወሰነ ቋንቋ ተናጋሪ ለማገናኘት መጣር ከፖለቲካዊ ተልዕኮ ሌላ መልዕክት የለውም። እኔኑ በጣም ያስገረመኝ “የማሕበሩ አባላት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ትግርኛ ተናጋሪ ትግሬዎችና ኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ትግርኛ ተናጋሪ ኤርትራዊያኖች ናቸው። ምክንያቱም ይልና “በሁለት የተለያዩ ሉአላዊ አገሮች ተለያይተው ይኑሩ እንጂ ከጥንት ጀምሮ አያቶቹ ያቆዩለትን ቤተሰባዊ ሕግ እና ግንኙነት በጋብቻ ቃል ኪዳን በአጥንት ሰጋ ዝምድና እና በባሕል አንድ ስለሆኑ ናቸው። ከእንግዲህ ወዲህ ጥላቻ ጠፍቶ ሰላምና ፍቕር በመሃላቸው የሚሰፍንበት፤ይቅር፤ይቅር ለእግዚአብሔር ተባብለው የሚሳሳሙበት፤ካሁን ወዲህ እንዳለፈው ሳይፈልጉት ያለፈቃዳቸው እንዳይጎዳዱ ፤ወንዳማዊ ዝምድናቸው እንዳይራከስ መሰረት የሚጥሉበት ማሕበር ነው። የትግርኛ ተናጋሪው ብሔር ነባራዊ እንዲሆንና የፍቅር አርአያ እንዲሆን በሁለቱ ማሕበረሰቦች ሰላም እንዲሰፍን ፍቅሩም ከትውልድ ትውልድ ነባራዊ ሆኖ እንዲተላለፍ መሰረት መጣል ዋነኛው የማሕበሩ ዓላማ ነው።” ይልና - ቀጥሎም በአንቀጽ 9 ላይ ስለ ማሕበሩ ጽ/ቤት ምቹ ከተማ/ቦታ እስኪያገኝ ድረስ ዋና ጊዜያዊ መንቀሳቀሻ ጽሕፈት ኣዲስ ኣበባ፤ ሽረ እና መቐለ/መቀሌ ይሆናል፡፡እኒህ ቦታዎች የተመረጡበት ምክንያት ሲገልጽ “ሽረ/ሽሬና መቐለ/መቀሌ ለትግርኛ ተናጋሪዎቹ ሁኔታዎችን በቅርብ ለመከታተል ቅርብና አመች ስለሆኑ፤በተጨማሪም በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ንብረቶች ለመጠገን የተፈናቀሉ ቤተሰቦች ተከታትሎ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲያገኝ ለማድረግ እንዲመቸው የተመረጡ ናቸው። ኣዲስ ኣበባ ጽሕፈት እንዲኖረው የሆነበት ምክንያትም ከውጭው ዓለም ጋር ግንኙነት ለማድረግ እንዲያመችና ግንኙነትና ደገፍ በር የሚያገኝበት መሰረት ለመፍጠር ሲሆን ሁኔታው ሲፈቅድም ኤርትራ ውስጥም አስመራ፤በረንቱ፤ዓሰብ ውስጥ ጽ/ቡቶች ለመክፈት ምኞት አለው።ይላል። ከላይ ባጭሩ የተረጎምኩላችሁ አንዳንድ የማሕበሩ አባባሎች በክፍል ሁለት በሰፊው “ስለ ትግራይ ትግርኚ መሰረተ ድንጋይ የመጣል አዝማሚያ” መሆኑ በሰፊው ስለማብራራው ማሕበሩ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ ጎጠኛ ማሕበር መሆኑ የሚያመለክተው ትግርኛው ተናጋሪው ክፍል በተለያዩ ወቅቶች እርስ በርሱ የሚናናቅና የሚጋደል የተጋደለና የተዋሃደ አብሮ የኖረ አንዴ ሲዋጋ አንዴ ሲዋደድ የኖረ መሆኑ ቢታወቅም፤ ያገሪቱ ርዕሰ ከተማ አዲስ አባባ በወያኔ ቁጥጥር ስለሆነች አስፈላጊው ለማሕበሩ የሚያስፈልገው የውጭ ዲፕሎማሲያዊና ቁሳዊ ድጋፍ ለማግኘት ያመቸው ዘንድ ያለ ምንም ቀረጥና በውጭ ዕርዳታ ስም ሌላ የመበዝበዣና የመዝረፍያ ቦይ እንዲሆነው ዕቅድ ማውጣቱ ሲሆን፤ እጅግ የሚያሳዘነው ግን ባድሜ፤ዓሰብ፤ዛላምበሳ እና በደርግ ሰርም ሆነው በወታደራዊ ግዳጅ ተሰልፈው ሕይወታቸው ያጡ፤ጧሪ ያጡ፤ዜጎች ግን አስታዋሽ የሌላቸው መቅረታቸው ያሳዝናል። ይህ ማሕበር በዚህ ጠባብ ጎጠኛ ባሕሪው ሳይወሰን ይግረማችሁ ብሎ ለሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪዎች አመቺ በሆነ ቦታ ከዓለም ግብረ ሰናይ ማሕበራት፤ከተባበሩት መንግሥታት፤ከደጋፊ አባላት…የሚገኝ ገንዘብ ሃወልትና ሆስፒታል እንዲቋቋም ዕቅድ ውስጥ አስገብቶታተል። በዚህ አላቆመም፦ የማሕበሩ ሕገደምብና ዝርዝር ሁኔታ ሕጋዊነት በቅጂ ለተባበሩት መንግሥታት ያሳውቃል ይላል። የማሕበሩ ሕገደምብና ዝርዝር ሁኔታ ሕጋዊነት በቅጂ ለተባበሩት መንግሥታት ያሳውቃል ሲል ራስ ተሰማ በ1947 ዓ.ም አካባቢ የመሰረቱት በእንግሊዝ ቅየሳ የተደራጀ የሊበራል ፓርቲ መርሃ ግብር ለተባበሩት መንግሥታት ኮሚሽን ልኡካን ያሰሙት የትግራይ ትግርኞ መንግሥት ማመልከቻ ተግባራዊ ለማድረግ ይሆን? ማሕበሩስ የራሱ ወይንም የትግራይ ትግርኚ ዕቅድ ባንዴራስ ይኖረው ይሆን? ራስ ተሰማ አስበሮም በተባበሩት መንግሥታት ኮሚሽን ምን ብለው ነበር? “……..በአፄ ዮሐንስ ዘመን የባዕድ መንግሥት ከውጪ መጥቶ ከኢትዮጵያ ላይ ቆርሶ የወሰደው አገር የለም። ጣልያን ኤርትራን ቅኝ ግዛቱ ያደረገው፤ አጼ ዮሐንስ ከሞቱ በሗላ የኢትዮጵያን ሥልጣን የተረከቡት ንጉሥ ሚኒልክ በገንዘብ ስለሸጡት ነው።…እንደሚታወቀው የተሸጠ ዕቃ በማናቸውም መንገድ እንደማይመለስ ሁሉ፤ዛሬም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሃምሳ ዓመት በፊት የሸጥኩት አገር ይመለስልኝ ማለት አይችልም፡… የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን በግዴታ ካልወሰድኩ ብሎ የሚታገል መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።ይህ መንግሥት በትግራይ ወንድሞቻችን ላይ የመሰረተው የግፍ አስተዳደር በጣም የሚያሳዝን ስለሆነ፤ይህ አስከፊ ዕድል በኛም በኤርትራውያኖች ላይ እንዲደርስብን አንፈልግም።….የትግራይ ሕዝቦች አንድ ዓኢነት ዘርና አንድ ዓይነት ባሕል ያላቸው፤አንድ ዓይነት ቋንቋ የሚናገሩ ስለሆኑ፤ በአንድነት ተዋህደው ነፃ መንግሥት ለማቋቋም እንዲወስንላቸው አጥብቀን እንፈልጋለን። " የህ በዘመነ ወያነ ትግራይ ተንከባካቢነትና በአንዳንድ አድርባይ ጎጠኛ ኤርትራኖች “የሰላምና የወንድሞች የትግርኛ ተናጋሪ የቤተሰብ ማሕበር” በማለት የተመሰረተ አዲስ ቅኝት በእንግሊዝ ቅየሳ እና በራስ ተሰማ ግምባር ቀደም ጥረት ተወጥኖ የነበረው ውጥን ለመቀጠል ይሆን? ታላቋ ትግራይ የተባለው የፖለቲካ ስታረተጂ በመቅረጽ የትግራይ ኢትዮጵያዊነት ለሁለተኛ (ለሦስተኛ) ጊዜ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ያደርግ ይሆን? ታሪኩን በዝርዝር እንመልከት። ይቀጥላል….. ጌታቸው ረዳ ኢትዮጵያን ሰማይ ብሎግ አዘጋጅ www.ethiopiansemay.blogspot.com

No comments: