ስልጣንና ህገ-መንግስት በኢትዩጵያ….
መንግስታት በየጊዜው በተለወጡ ቁጥር ህገ-መንግስትን በህግ አርቃቂ አካላት በማርቀቅና በማሻሻል ለሚመሩትና ለሚያስተዳድሩት ማህበረሰብ ጠቃሚ ከለላና ጠባቂ ሆኖ ህገ-መንግስት የአንድ ሀገር የበላይ ህግ ሆኖ ይረቀቃል። የህግ አውጪውም ክፍል በህገ-መንግስቱ መሰረት ህግ ያወጣል።ስራ አስፈጻሚው ክፍልም በህግ መሰረት ይሰራል የሚለው የህገ-መንግስቱ ጽንሰ ሃሳብ የህገ-መንግስትን የበላይነት ያረጋግጣል።
ህገ-መንግስት በመሰረቱ በዜጎች መብት፣ዲሞክራሲ፣የነፃ እንቅስቃሴና ስልጣን የህዝብ አካል በሚሉ ሃሳቦች የተመረኮዘ ቢሆንም እንኳን ከንጉሰ ነገስታቱ የህገ-መንግስት ረቂቅ ጀምሮ ያሉት ህገ- መንግስታዊ ረቂቆች ባገሪቱ ያለውን የሃይል ሚዛን ባልተዛባ ሁኔታ የዜጎችን መብት የሚያረጋግጡ ረቂቆች ሆነው አያውቁም።
የኢህአዴግ ህገ-መንግስት ስልጣን ለተለያዩ አካላት የማከፋፈልና ስልጣንን ለህገ-መንግስቱ ተገዢ ላልሆኑ በፓርቲው ጀሌዎች ታጥሮ ያለና የዳኝነቱን ክፍል ነፃነት የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡በህግ ሰፍረው የሚገኙ የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጡ አንቀጾች በፓርቲው ፈላጭ ቆራጭ አመራሮች ያለ ምንም ገደብ በቀላሉ ሊጣሱና ሊረገጡ የሚችሉ ናቸው፡፡የገዢው ፓርቲ አባሎች በህዝብ ላይ ለሚያደርሱት አፈና ግድያና የሰብሃዊ መብት ረገጣዎች የስልጣንን የበላይነት የሚቃወምም ሆነ የሚከላከል ብሎም የህገ-መንግስቱን መከበር የሚያረጋግጥ ነጻ የሆነ የህግ አካል የለም።
ነፃ የሆነ የዳኝነት አካል መኖር የዲሞክራሲ አንዱ ገጽታ ነው።የኢህአዲግ ህገ-መንግስታዊ አንቀጽ 79/3 “ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነፃነት ያከናውናሉ።ከህግ በስተቀር በሌላ ሁኔታ አይመሩም።”ይላል ግን በየጊዜው በየፍርድ ቤቶች ከገዢው ፓርቲ ያፈነገጡና የኢህአዴግ ኢሰብሃዊ የዜጎች አፈናና ጭፍጨፋ አሜን ብለው ሳይቀበሉ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ንፁህ ዜጎች ገዥው ፓርቲ ባሴረላቸው የሃሰት ውንጀላና በሃሴትነት ባስቀመጣቸው ዳኞች ሐሴተኛ ውሳኔ ለእስራት፣ለግርፋት፣ ብሎም ለግድያ የተዳረጉትን ንፁህና ሰላማዊ ዜጎቻችን እሮሮ የየእለቱ ዜና ነው።የኢህአዴግ ህገ-መንግስታዊ ረቂቅ በህዝብ ሃሳብና ፍላጎት የተመረኮዘ ሳይሆን ጥቂት ለዚህ ህዝብ እኛ እናውቅልሃለን በሚሉ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣኖች በር ተዘግቶ ለጭቆናዊ አመራራቸው አመቺ በሆነ መልኩ የስልጣን ጥም እድሜ ማራዘሚያነት ያረቀቁት ነው።
በጥር 12 ቀን 2001 አ.ም በእነ አቶ መለስ ዜናዊ እና በጀሌዎቻቸው አቅራቢነት ለይስሙላ ለህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ቀርቦ የፀደቀውና አወዛጋቢው የ27 ፌዴራል ዳኞች ሹመት ከተለያዩ ታላላቅ አገር በቀል ምሁራን ተቃውሞ የገጠመውና ከህገ-መንግስቱ አዋጅ ቁጥር 24/88 አንቀፅ 8’’2 ጋር የሚጋጭ ነው።በዚህ አንቀፅ “ማንኛውም ሠው በመንግስት ህግ አውጪ ወይም አስፈፃሚ ውስጥ በአባልነት በሚያገለግልበት ጊዜ አጣምሮ የዳኝነት ሥራ ሊሰራ እንደማይችል ይደነግጋል።” ነገር ግን በዚህ የዳኞች ፌዴራል ምርጫ በርካቶቹ በራሱ በ ኢህአዴግ ፓርቲ ውስጥ በአባልነት የሚያገለግሉ ናቸው።ምነው ኢህአዴግ ራሱ ያረቀቀውን ህገ-መንግስታዊ ረቂቅ ዘንግቶት ነው ? ወይስ ሻሪም ሿሚም እኛው ነን ነው ? የዳኝነት አካላት ነፃና ከማንኛውም የፖለቲካ ወገን ገለልተኛ ካልሆኑ በዜጎች ላይ የህግ የበላይነትን ማስፈን ያዳግታል። ይህን የነ አቶ መለስ ዜናዊን ሴራ የህግ የበላይነትን ሳይሆን የስልጣንና የጭቆናዊ ወታደራዊ አገዛዝን የበላይነት ፍንትው አድርጎ የሚያንፀባርቅ ነው።
ከጀሚላ አብዱልቃድር
ጥር 26/2001 አ.ም
Monday, February 9, 2009
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment