Monday, June 9, 2008

The Lion of MeraNna





የመራኛዉ አንበሳ
(ጌታቸዉ ረዳ)
(ሳን ሆዘ ካሊፎርኒያ)
ካለይ ሚታዩት ፎቶግራፎች የመራኛዉ አንበሳ ኰሎኔል ሰረቀብርሃን ናቸዉ።ኰሎኔል ሰረቀብርሃን ሦስተኛ ክፈለጦር ዋና አዛዥ የነበሩ ናቸዉ።ኮሎኔሉ በመራኛ ጦር ሜዳ በዉግያዉ ወቀት በመጨረሻዉ ሰዓትድንገት ሳያስቡትበጠቋሚ ተደርሶባቸዉ በጸረ ኢትዮጵያዉ ቡድን በወያኔ ከተማረኩት የኢትዮጵያ ወታደሮች አንዱ ናቸዉ።ኮሎኔል ሰረቀብርሃን የተወለዱት ሲዳሞ ክፍለሃገር ጀምጀም አዉራጃ ዉስጥ ክብረመንግሥት ከተማ ነዉ።የሁለተኛ ደረጃ ትምርታቸዉን (ባዲስ አበባ ኮቶቤ) በማጠናቀቅ ላይ እያሉ፤ አገራቸዉን በወታደርነት ለማገልገል በጦር አካደሚ ትምርት ቤት በመግባት ለ 5 ዓመት ሰልጥነዉ በመቶ አለቅነት መዓረግ ተመርቀዉ በሁለተኛ ክፍለጦር ተመድበዉ በተለያዩ ወታደራዊ ሃላፊነት ሲሰሩ ቆይተዉ በ1974 ዓ.ም ዝነኛዉ የአምበሳ ሦስተኛዉ ክፈለጦር ከምስራቅ ወደ ኤርትራ ሲዘዋወር በክፍለጦሩ ብርጌድ አዛዥ ከዛም ምክትል አዛዥ በመጨረሻም የክፍለጦሩ ዋና አዛዥ ሆነዉ መራኛ ጦር ሜዳ ላይ ተዋግተዉ በወያኔ ቡድን አስከተማረኩበት ጊዜ አገራቸዉን አገልግለዋል።
ኰሎኔሉ በወያኔ እስር እያሉ ከወያኔዉ ጋዜጣ ቃለ ምልልስ ካደረጉበት ከ1990 ዓ/ም ጀምሮ በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ ሚታወቅ ነገር የለም።ለዚህ ጹሁፉ መነሻ የሆነዉ፤ ሶሞኑን በጥቂት የወያኔ መሪዎች ቁጥጥር ሥር የሚተዳደደር የፕሮፖንጋነዳቸዉ መገልገያ የሆነዉ ”ራድዮ ድምጺ ወያነ ትግራይ” የተለመደዉን ጉራዉን በመንግሥቱና በተካታዮቹ የተተበተበ ቢሮክራሲያዊና ብልሹ የጦር አመራር ምክንያት፤ ሞራሉ ላሽቆ የተወጠረ የኢትዮጵያ ወታደርን በጦር ሜዳ በመግጠሙ፤ የጣልያንን ወራሪ ጦር የገጠመ ይመስል ፤ የጦር ሜዳ ጉራዉን ለመንዛትእንደተለመደዉ ዛሬም በመራኛ ጦር ሜዳ ዉስጥ የነበረች “ሽሻይ ሕንጣሎ” የተባለች አንዲት የወያኔ ታጋይ ኮሎኔሉን እንዴት እንደማረከቻቸዉ ለግንቦቱ በዓል ማድመቂያ ይሆን ዘንድ ስለጦር ሜዳ ገጠመቻቸዉን ለአድማጮች እንድያብራሩ ከታደሙት የወያኔ ታጋይ በእንግዳነት አቅርቧት ነበር። ቃለ መጠይቁ ከጦርሜዳ ትግል አኳያ የቀረበ የወንድማሞች የጠብ ዉግያ ታሪክ ሳይሆን ሆን ተብሎ ትግሉ በወራሪና ተወራሪ፤ በባእድና በወገን ጦርነት መሃል የተደረገ ጦርነት አስምስለዉ የማቅረብ ልማዳቸዉ ዛሬም እየገፉበት ስለሆነ፤ኰለኔሉ ካሁን በፊትበ1990 ዓ.ም ወይን በተባለዉ ጋዜጣ ለቃለመ-ጠይቅ ሲቀርቡ ጋዜጣዉ የተቻቸባቸዉ አገላለጾችና ከቃለመጠይቁ ጋርም ተያይዞ የቀረበዉ “አንበሳ” በሚል ርዕስ የቀረበዉ ግጥም የተጠቀሙበት ቃላት (ሬሳዉ፤ከወገኖቹ ከነዚያ ከወራሪዎች፤ ከኖጮቹ ጋር ጋር አፈር አብልተን፤ አደባይተን እንዲቀበር ቀላቀልነዉ ……ወዘተ ሲል ግጥሙን ይደረድራል…) በወራሪና በተወራሪ መሃል የተደረገ የጣልያን ጦርነት አድርጎ ከማቅረቡ ባሻገር፤ ራሱን (ወያኔን) አንደ “አንበሳ” ፡የኢትዮጵያ ወታደር ግን አንደ “ፈሪ ዉሻ” እያስመሰለ የሚገጥማቸዉና የሚተቻቸዉ ፕሮፖጋነንዳዎቹ የተምታታ ሚዛኑ ያልጠበቀ ጉራና መርዘኛ አቀራረቡ መቆም አንዳለበትና፤ ወታደሩ ወያኔ እንደሚዋሸዉ ሳይሆን፡ ወታደሩ የተሸነፈዉ ሁላችንም እንደምናዉቃዉ አስሰርገዉ በመለመሏቸዉ ከፍተኛ ያገሪቱ ባለስልጠኖች ዉስጣዊ ቡርቦራና እንደዚሁም፤ መንግሥቱም በወታደሩ የተወደደዱ ዝነኛ አዋጊ ወታደሮችና ባለማረጎች በተከታታታይ በብዛት በሞት ስለቀጣቸዉ፤ ወታደሩ ሞራሉ አንደወደቀና በአብዛኛዉ ሳይዋጋ እጁን ይሰጥ እንደነበረ የምናቀዉ ታሪክ ነዉ።

የትዮጵያ ወታደሮች የጦር ሜዳ ዉሎች ለሕዝቡ የሚያቀርብ የመገናኛ ብዙሃን ቢኖር ኖሮ 'ታሪኩ ወያኔ እንደሚያወራዉ ባልሆነ ነበር። ባለመታደል ተቃዋሚዉና ሙሁር ተብየዉ የራሱን ዝና ለማስጻፍ እንደ ድኩላ ባዶ ሜዳ ላይ ባስቂኝ ሁኔታ ሲዘል ለባሕር ጠረፍ ክብርና ላገሪቱ አንድነት ሲል የወደቀዉና የትም የተበተነዉ ኢትዮጵያዊ ወታደርን እንደ ጠላት (ልክ ወያኔ እንደሚያዉ አይነት) ክብር ሳይሰጠዉ በመቅረቱ ፤ወያኔ ታሪክ እየደለዘ በራሱ ብእር እያሳመረ “ኰሎኔልን በድንጋይ ማራኪ!” እያለ ጦርነቱ በጣልያንና በአበሻ መሃከል፤ ወይንም በአማራና በትግሬ አንደተደረገ እያሰመሰለ (በሸዋዉያንና በትግሬ) ሚያቀርበዉ የጦርነት ታሪክ መርዘኛና የተምታታ በመሆኑ፤ ወታደሩ ለምን እነደተሸነፈ በ1990 ዓ.ም ኮሎኔል ሰረቀብርሃን የሰጡት ቃ ለመጠይቅ ከትግርና ወደ አማርኛ አንኳር ነጥቦቹን ለአንባቢ ለማስጨበጥ እወዳለሁ።

ሰሞኑ የኰሎኔሉን ስም የተነሳበትን “ሳይጠሩት አብየት ሳይልኩት ወዴት” የሆነዉ የመለስ ዜናዊ ልሳን እልፍኝ አስከልካይ፤ (አገልጋይ) “አይጋ-ፎረም” “ከድምጺ ወያነ” ያገኘዉ ኮፒ ለጥፎት እንደነበር ከላይ ጠቅሼ ነበር። ካሁን በፊትም ኮሎኔሉ “ወይን” በተባለ ጋዜጣ የሰጡት ቃለ መጠይቅ በ1990 ዓ.ም ትግራይ ዉስጥ ለአንባቢ ተሰራጭቶ ነበር።በሺ 1990 ዓ.ም ኰሎኔሉ ባደረጉት ቃለመጠይቅ ወታደሩ ለምን አንደተሸነፈና ምን ችግር ገጥሞት እነደነበረ ባጭሩ አብራርተዉት ነበር።ጋዜጣዉ በ1990 ዓ.ም ኮሎኔሉ የሰጡትን ማብራርያና ለሰራዊቱ የመሸነፍ ምክንያቶች ሲያብራሩ በማንኳሰስ ቢተቻቸዉም፤ዘሬም ያንኑ ትችት ከማድመቅ አልቦዘነም። ለማንኛዉም ሰራዊቱ የመዋጋት አቅም አንሶት ወያኔ በግጥሞቹ እንደሚለዉ”የጦርነት ችሎታ የሌለዉ” “ፈሪ ዉሻ” ሆኖ ለባንዳዉና ለፋሽስቱ ወያኔ ‘የተንበረከከ” ጦር ሳይሆን፡ ከገጠሙት አስቸጋሪ የዉስጥ አመራር አኳያ መሆኑን ቃለመጠይቁ ያስረዳል። ወየኔ ተገፍቶ እየተመታ ሰራዊቱ እየተከተለ ሲያባርረዉ ከላይ ከአዲስ አበባ የተቀመጠዉ አመራር ትንንቁ/ክትትሉ እንዲያቆምና ከአጥቂነት እርምጃ ወደ ሗሊት ወደ መከላከል ቀጠና፤ አንዲመለስና ብሎም የተለማመደበትንና የተቆጣጠረዉን ገዥ ነጥቦቹን ነቅሎ ወደ ሌላ ነጥብ አንዲሄድ ይነገረዉ እንደነበር ቃለመይቁ ያብራረራል። ታድያ ወያኔ በለስ ቀንቶት፤ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ተወጥሮ የነበረዉን ሠራዊትን ነዉ “አንበረከኩት” እያለ ነጋ ጠባ እያምቧረቀ የዋሃኑንና መረጃ ያለገኘዉን ክፍል በዉሸት የሚያታተልለዉ።

ወደ ቃለ መጠይቁ እንገባለን።ቃለ መጠይቁ ረዘም ይላል፤ሆኖም ጤናማ ምግብና የፀሃይ ብርሃን አየተመገቡ ግማሽ ሰዓት “ከአሸሸ ገዳየ” የቴሌቪዥን ዳንኪራ ሰዓታችንን ሰዉተን፤ሕይወታቸዉ በወያኔ የጉድጓድ እስር ቤት በስቃይ እየጮኸ ለሚጣራን የኰሎኔሉ ድምፅ ለግሰን ቃለ መጠይቁን እናንብብ።አነሆ።


ወይን ፦ ስለ አንበሳ ክፈለጦር አመሰራረት ብትገልጸልን?

ኰሎኔል- ሠረቀ ብርሃን፦ ክፍለጦሩ በኢትዮጵያ ዉስጥ ከተመሰረቱት ክ/ጦሮች የመጀመሪያዉ ነዉ።የክፍለጦሩ የመጀመሪያ መሪዎቹም እነግሊዞች ናቸዉ። አንበሳ የሚል ስም የተሰጠዉ ግን ኦጋዴን ዉስጥ ከሶማሊያ ጋር ባደረገዉ ዉግያ ነዉ። (አንባቢያን አዚህ ጋር ለመግለጽ የምፈልገዉ ፤ወያኔ “የአንበሳነት ታሪክ ሳይኖረዉ፤ አንበሳ ነኝ የሚል….” በማለት በየግጥሞቹና በዝርዝር ሀተታዉ ላይ የጦሩን ማንነት ለማንኳሰስ ቢጥርም፡ አንበሳ የሚለዉ ስም ክፍለ-ጦሩ ከባዶ ሜዳ የተሰጠዉ ስም እየመሰለዉ ወያኔ አሉ የተባሉ ዝቃጭና አንኳሳሽ የትግርኛ ሀረጎችን እየተጠቀመ ከትግርኛ አንባቢ ዓይን ፊት ለማነቋቋሸሸ ሞክሯል።አዲሱ ትዉልድ ስለ ሶማሊ ጦርነት የሚያዉቀዉ የለዉምና የወያኔ ፕሮፖጋንዳ ለጊዜዉም ቢሆን ተቀባይ አላጣም።)


ወይን፦ ስለ ጦርነቱና ጦሩ ወደ መራኛ እንዴት መጣ?

ኰሎኔል፤-ክፍለጦራችን ኤርትራ ዉስጥ ነበር።ሆኖም፤ የኢሕዴግ ሠራዊት ደሴን ሊቆጣጠር ነዉ የሚል የበላይ አካላት ስጋት ስለነበር በዚህ መሠረት በአካባቢዉ ሠራዊት ወልድያን ለቆ በመዉጣቱ እንደዛሬ ተነግሮን በማግስቱ ደሴ ባየር ጉዞ ገባን።ደሴ እንደገባንም እዛዉ አካባቢ በተከታታይ ዉግያ አድርገን ከተወሰነ ጊዜ በሗላ ደግሞ ወደ መራኛ ተመልሰን እዛዉ እንድንዋጋ ተነገረን።
<<መራኛ ላይ ዉግያ ለማድረግ ሲታሰብ በወገኔ ከመጀመርያዎቹ አልደገፍኩትም። እቅዱ የበሰለ አልነበረም። ከደሴ ወደ መራኛ መመለስ ወደ አዲስ አበባ እንደመሄድ ነዉ። ወደ መራኛ መመለሱ ቀርቶ ወደ ሰሜን ወሎ ተዋግተን መንገዶችን መዝጋት የበለጠ ነበር።ወደ ዉስጥ ከመግባት ይልቅ። ሌላዉ ደግሞ ብስለት ያላቸዉ ሰዎች አንድ የመጀመርያ ምክር ሰጥተዉን ነበር።”ሦስተኛ ክፍለጦር ጠላት እየተከታተለዉ መሆኑንና ወደ መራኛ ሲገባም ጠላት ከቦ ላንዴና ለመጨረሻ እንድያጠፈዉ ዝግጅት እንዳደረገ ጠቁመዉን ነበር። አሁንም ይህ መረጃ ለበላዮቻችን (አዛዦቻችን) አስታወቅን። ትዛዙ የፕረዚዳንቱ/ መንግሥቱ/ መሆኑንና ግዴታ መፈጸም እንዳለበት የበላዮቻችን ነገሩን።አማራጭ ስላልነበረን ቀጠልን።

እኔ አስከ ወረኢሉ ድረስ አንድይዝ ተደረገ።ወረኢሉ ልይዝ እንዳጋጣሚ ዉግያ ገጠምንና ከዛ አንተ ቀጥልና ስምንተኛ ከ/ጦር ያንተን ቦታ ይይዛል ተባለ። የተቆጣጠርነዉ ቦታ ለስምንተኛ ክ/ጦር ትተን ወደ ካራ ምሽግ ጉዞ አቀናን። ከዛ “ካራ-ምሽግ” ስንገባ ዉግያ አደረግን።ቀን በፀሃይ።

<<ያ ዉግያ የሚናቅ አልነበረም።እዛ አካባቢ የጠላት (ኢሕአደግ) ሠራዊት እንዳለ ስለምናቅ ጊዜ ስንለዉጥ አዩን። ለማጥቃት ያሰብነዉ ጊዜም ከሌሊቱ 6፡00ሰዓት ለማድረግ ወሰንን።በርግጥ የደርግ ሠራዊት የሌሊት የማጥቃት ዉግያ አድርጎ አያዉቅም። ያን ጊዜ ያልጠበቅኩትን ሙሉ በሙሉ ካራ ምሽግን ያዝነዉ።ካራ-ምሽግ እንደያዝን በማግሥቱ ጥቃት ተሰነዘረብን። ግን እኛም የጠበቅነዉ ስነዘራ ስለነበር፤ከቦታችን አልለቀቅንም። በዛ ጊዜ በኔ አስተያየት የጠላት ሠራዊት ጠንክሮ ይዋጋል ብየ ግምት አልነበረኝም። በመጨረሻም ቢሆን የኢሕአዲግ ሠራዊት ማፈግፈጉን ያወቅኩት ራድዮ ጠልፌ እከታተል ስለነበር ነዉ። በዛ ጊዜ ሓየሎም በራድዮ ሲናገር ሰማሁት። ለዛ በቅርብ ሲከተለዉ ለነበረዉ አመራር “ሃይልህን ይዘህ ወደኔዉ አምራ” ሲል መልክት አስተላለፈለት።የጠላት ሠራዊትም ወደ ሗላዉ ሸሸ።ማፈግፈጉን በሚመለከት ስለት ለመለወጥ ነዉ ወየስ ስለተሸነፉ ነበር? ለሚለዉ ጥያቁ አሁን ይሄ ነዉ ለማለት ያስቸግረኛል። በወቅቱ ግን በግሌ እምነት፤ ድል አንደተመቱ አድሬ ነዉ የማምነዉ።የሆኖ ሆኖ፤ ከካራ-ምሽግ ወደ ፊት ቀጠልን።ለመራኛም ያለ ዉግያ ያዝናት።

<<መራኛ እንደያዝንም፤ የነበረዉ ሁኔታ ለበላዮች አስታወቅኩ።የኔ ግዴታ አስከመራኛ መሆኑን፤ ቀጥሎም አንዴት ማምራት እንዳለብን ጠየቅኩኝ። ከበላይም መልስ አገኘሁ። አዲስ መመርያ አስኪተላለፍ ካለሁበት ከያዝኩት እመራኛ ላይ እንድቆይ ተነገረኝ።


ወይን፦ ከዛስ?

ኰሎኔል፦እኛ መራኛ እያለን፤የኢሀዴግ ሠራዊት ከሗላችን በነበረዉ የአየር ወለድ ጦር ላይ ጥቃት አወረደ። ይህ ፈጽሞ ያልገመትነዉ ጥቃት ነበር።በተሰነዘረዉ የማጥቃት ሂደት ዉስጥ የአየር ወለድ ሠራዊት እንዳለ ፈራረሰ። ይህ መረጃ ከጦርነቱ ሸሽተዉ ከመጡ ያየር ወለድ መኮንኖችና ወታደሮች ነበር ያገኘነዉ። ያየር ወለዱ መበታተን በቀጣይ የኛ ህልዉና እንዴት እንደሚቀጥል ማስብ ነበረብን።ምክንያቱም ሁሉም እዛዉ አካባቢ የነበረ የጠላት ሃይል ተሰባስቦ ወደኛዉ ሊመጣ እንደሚችል ስለገመትንና፤ግን ያ አማራጭ ወደ ፊት ከመገስገስ እዛዉ መከላከል እንደሚሻል ገመትን።

<<መራኛ ላይ እንዳለን ተከታታይ ዉግያዎች አካሄድን። ሆኖም በቂ ሰዉ ሃይልና ትጥቅ ስላልነበረን፤ለአመስት ቀናት ቆየን። በሗላ ዉግያዉ እየበረታ ሄደ። ይዘነዉ የነበረዉ የሰዉ ሃይል እየሳሳ ፤እየቀነሰ ሄደ።ይዘነዉ ነበረዉ ስንቅና ትጥቅም እያለቀ መጣ። ይታወሰኛል አምስት ጊዜ በሥስት አቅጣጫ ከባድ ጥቃት ተሰነዘረብን። ግን መራኛ ከማጥቃት ይልቅ ለመከላከል የተመቸ ቁልፍ ወታደራዊ መሬት ስለነበረ፤የጠላት ሠራዊትን ለተወሰነ ጊዜ መክቶ መከላከል ችሏል።ማለትም በሰሜን ሸዋ ያለዉ አቀማመጥ መራኛ ገደላማ ነዉ።በበኩላችን በገደላማ አቅጣጫ በኩል ይመጡብናል የሚል ሀሳብ አለነበረንም።ሆኖም በዛዉ በመሳላሉ ተቆናጥጠዉ ወጥተዉ ሊያጠቁን ሞከሩ። የማጥቃት ሙከራዉ ያደረገብንም የአዉሮራ ከ/ሠራዊት ይመስለኛል።በዚህ ጊዜ ሁሉም ገደላማዉን ሥፍራ ከመዉጣታቸዉ በፊት የተወሰኑ አባሎቻቸዉ ቢ.ኤም ሲያቃጥሉብን ሰላየናቸዉ በዛዉ የነበረ ጥቃት ከሸፈ።

<<በሌላ ወገን ደግሞ አሁን የየትኛዉ ከ/ጦር መሆኑን የዘነጋሁት አንድ ከ/ጦር፤ ዘግይቶ በመድረሱ ምክንያት ዉግያዉ ተበላሸ አንጂ የዉግያዉ አያያዙና ወታደራዊ ስልቱ አመርቂ ስነለበር ከመጀመሪያዉ ቢደረስ ኖሮ ድል የሚያስገኝ ነበር።ስለሆነም ፤ካሰብነዉ ጥቃት ድነናል።ምክንያቱ ዉግያ ለመከላከል አንደ መራኛ የሚመች ቦታ ኤርትራ ዉስጥም አይገኝም። <<መራኛ ሆነን ከመጀመሪያዉ የጠላት ጥቃት ስንዘራ ለመከላከል ብንችለም እንድያ አንደማይቀጥል ታየኝ።በሁሉም አቅጣጫ እየተዳከምን መጣን። ይህ ሃሳብ ለኤታ ማጆር ሹም ለዘመቻ መምርያ ሓለፊዉ ለጀኔራል ክንፈ ገብሪኤል ድንቁ ነገርናቸዉ።በበኩሌ ያለነን ሃሳብ ከነ መፍትሄዉ አቀረብኩላቸዉ።የነበረዉ ንብረት አቃጥየ ባንድ በኩል ሠራዊቱን ይዤ ልዉጣ አሉኳቸዉ። አነሱ ግን ከፕረዚዳንቱ ጋር ተገናኝተዉ መልስ አንደሚሰጡኝ ገለጹልኝ። አስቸኳይ መልስ አልተገኘም። እኛ ግን መልስ ለመስማት በጊዜዉ ተቻኮልን። አሁንም ከኔ ጋር ከነበሩ ተነጋግረን ዳግም በቴሌግራም እንድንገናኛቸዉ ወሰንን። በ24ሰዓት ዉስጥ አንድ መልስ ካልደረሰን ሠራዊቱ አንዳለ አንደሚደመሰስ ነገርናቸዉ።ግን፤ ሃሳቡ ወደ ፕረዚዳንቱ እንደቀረበና ለምላሹም መጠባበቅ እንዳለብን መመርያ ሰጡን።


ወይን፦ ሦስተኛ አምበሳ ክፍለጦር አመራሩን በቀጥታ ከመንግሥቱ አንደሚገናኝና አዛዡም (ኮሎኔሉ) ከመንግሥቱ ጋር ትዉውቅ እንዳለዉ እየታወቀ በቀጥታ ከምንግሥቱ ጋር አንደመገናኘት ለምን ከበላይ አዛዦች በተዘዋዋሪ ለመገናኘት ፈለገ?

ኰሎኔል፦<<ኤርትራ በነበርንበት ጊዜ መንግሥቱን አንደማንኛዉም ሰዉ በፎቶ ብቻ ከማወቄ በስተቀር በሌላ አላቀዉም።በቀይ ኮከብ ዘመቻ ወደ ኤርትራ መጥተዉ እንደነበር አቃለሁ። ሆኖም እኔ ጥበቃ ላይ ስለነበርኩ አላየሁዋቸዉም፤አላገኘሁዋቸዉም።በርግጥ በተዘዋዋሪ ክ/ጦሩ ራሳቸዉ መንግሥቱ አንደሚመሩት አቃለሁ። ጠቅላላ ወታደራዊ አመራር ወደ ቤተ መንግሥት ተዘዋዉሮ እነደነበር ይረዳኛል። መንግሥቱም የሦስተኛ ክፍለጦር አባል ሠራዊት መኖራቸዉንም አዉቃለሁ።ጠቅላላ ወታደራዊዉ አመራር ወደ ቤተመንግሥቱ ተዘዋዉሮ አንደነበርም የረዳኛል።ግን ለሦስተኛ ከ/ጦር ያኔ በስም አንጂ ከሌሎቹ በተለይ ዓይን ይንከባከቡት ነበር የሚል ነገር በተባራሪ የሚነገር ካልሆነ መንግሥቱ ከ/ጦሩን በግልጽ ያደረጉለት ነገር የለም።

<<ወደ ደሴ ከመጣን በሗላ ምናልባትም የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ሁሉ መንግሥቱ ሳያዉቁት አይደረግም ነበር። በሚወጡት ስልቶች አስተያየት አንሰጥም። ሐላፊነታችን መመሪያዉን መፈጸም ብቻ ነዉ። ለምን ቢባል ርዕሰ ብሔሩ አጽድቀው በፈረሙት ስልት መከራከር ስለማይቻል።

<<ከኔ ጋር በሬድዮ ግንኙነት ነበረዉ የተባለዉም ስህተት ነዉ።ሌላ ቀርቶ ከኔ ጋር በአካል ተዋወቅነዉ አንድ ጊዜ ወደ ደሴ በድብቅ መጥተዉ በነበሩበት ወቅት ነዉ። ደሴ እያለን ምፅዋ በሻዕብያ ቁጥጥር በመዉደቁ አንድ ከ/ጦር ሊወስዱ መጡ። የክፍለጦሮች አዛዦች ተሰበሰቡ ተባለ። እኔ በስም እንጂ በአካል ከመላዉቃቸዉና ከማያዉቁኝ መንግሰሥቱ ጋር ተዋወቅን። በተረፈ ከ1982 ዓ.ም በፊት ከመንግሰሥቱ ጋር በ አካል ይሁን በሬድዮ ግንኙነት አድርገን አናቅም።


ወይን፦ ከመራኛ የመሬቱ አቀማመጥና ባጠቃላይ መደረግ ነበረበት ብለህ በዉግያዉ ላይ የነበረህ አስተያየት?

ኰሎኔል፦ << መደረግ አለበት ያልኩት ካላደረግነዉ ሠራዊቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚደመሰስ መጨረሻ ሰዓት ላይ ገለፅኩ። ከዚህ በሗላ ጠላት በሚያስገርም ስልት ከሗላችን የነበረዉ 26ኛ ከ/ጦርን መታ። ቀጥሎ ጠላት ደሴ አንደሚይዝ ተገመተ። እኛ እመሀል ቀረን። እንዲህ እያልን አዲስ ትእዛዝ ደረሰኝ። ትዛዙም ጀኔራል ረጋሳ በሬድዮ ራሳቸዉ ቀርበዉ ነበር የነገሩኝ። አስረኛ ብርጌድ ወደ ደሴ እንድልክ ታዘዝኩኝ። በሙሉ ተስፋ ቆረጥኩ። ምክንያቱም የሰዉ ሃይል ስንቅና ትጥቅ የለንም እያልን ከሗላችን ቀነሱብን።ሄዶም ምንም ለዉጥ እንደማያመጣ እያወቅኩኝ ትእዛዙን ግን ተቀበልኩኝ።

<<ይህ ሲሆን የጠላት ሠራዊት እኛንም በዙርያ ቀለበት ዉስጥ አስገባን። ከከበባዉ በሗላ ሊደረግ የሚቻለዉ፤በታቸለ መጠን እየተዋጋህ ዕድል ከተገኘ መዉጣት ካልሆነም እዛዉ መሞት መሆኑን ታየኝ። ይህም እኔ ጋር ከነበሩ መሪዎች ጋር ተነጋገርንና የበላይ መሪዎችን መልክቱ እንዲደርሳቸዉ አደረግኩ።


<<ቀጠለና፤ በስምንት አቅጣጫ ድንገተኛ የጥቃት ስንዘራ ወረደብን። በሚቻለን መጠን የመከላከል ስልታችን እያጠበበን መጣን።በዛዉ ከጠልንም ድል መመታታችን እንደማይቀር ታየኝ። በዛዉ ጊዜም ከመሪዎች በሬድዮ መልክት ደረሰን። መለክቱ የሚቃጠል ንብረትና ደክዮመንት አቃጠላችሁ ወደ ደብረብርሃን አፈግፍጉ። አሉን። ይህነን ስናስብ ጠላት ጊዜ አልሰጠንም”” በቅርብ ርቀት ሆኖ ጥቃቱን አከታተለብን። ሁላችንም በመረጥነዉ አቅጣጫ ወደ ጎርጓዳማ ሥፍራ ወረድን። እኔና በቅርብ አብረዉኝ የነበሩ የሥራ ባልደረቦቼ ወደ ታች እንደወረድን ስለመሸብን ወደ አንድ ቋጥ ገባን።


ወይን፦ እንዴት ለመማረክ በቃህ?


ኰሎኔል-<እቋጡ ዉስጥ አድረን ወደ ቋጡ በሄድንበት ምሽት አንድ ስህተት ፈጸምን። መንገድ እንዲመራን ብለን አንድ የዛዉ አካባቢ ገበሬ ይዘን ነበር የሄድነዉ። አርሶ አደሩ በማግስቱ ወደ ነበርንበት ወደ መራኛ ይመለሳል። ሲመለስ ለኢሕአዲግ ታጋዮች ከነ ልዩ ምልክታችንና ት ቦታ እንደመሸግን ይጠቁማቸዋል። ማለትም በቡድን ሆነን እንደሄድንና የመገናኛ ሬድዮ እንዳለን። ታጋዮቹ ያገኙትን መረጃ አልናቁትም። መንገዱ አነዲመራቸዉም ጠየቁት፤እያዘገመ ወደ ነበርንበት ቋጥ አመጣቸዉ። ያልጠበቅነዉና ያልገመትነዉ ነበር”። ቋጥኙ ዉስጥ እጅ ከእጅ ተያያዝን። በርግጥ ሰረቀብርሃን እጁ ይሰጣል የሚልም አልነበረም፤ ብሎም የገመተ አልነበረም። ለኢሕአዲጎቹ ሠራዊቶችም፤ ሰረቀብርሃን እኔ ነኝ ስላቸዉ መጀመሪያ አላመኑም ነበር። ግን ሰረቀ መሆኔን ሳረጋግጥላቸዉ ወደ መራኛ ይዘዉኝ ተመለሱ። ከሐየሎም ጋርም አገናኙኝ። አስካሁን ድረስ እዚህ እሥር ቤት ዉስጥ በሕይወት አለሁ።

ወይን፦ሦስተኛ ከ/ጦር ዉስጥ እያለህ መጥፎ ነገር አደረግሁኝ ብለህ የሚቆጨህ ነገር አለ?


ኰሎኔል፦እኔ ኤርትራ ዉስጥ በነበርኩበት አብዛኛዉ ሕይወቴ በየተራራዉ ነኝ ያሳለፍኩት:: ኡሁን ስለ “ቀይ ሽብር ሲወራ” ለኔ እንደ አዲስ ሰዉ ነዉ የማዳምጠዉ።ወደ ደሴ እንደመጣን ነዉ ከሕዝብ ጋር ግንኙነት የጀመርነዉ። ሕዝብም በመንግሥት ላይ ያለዉ እምነት ጥሩ አንዳልሆነ እየተረዳን መጣን።
እየታዘብን ስንሄድ፤ለያዝነዉ ዓላማ መጠራጠር ጀመርን። እንዲያ ሆኖም ያ ሕዝብ ሲሰጠዉ የቆየ አመለካከት በሙሉነት ስላልያዝነዉ አስከ መጨረሻ ተዋጋን።

<<ከዉግያ በሗላም የተቆጨሁት ነገርም ነበር የራሴን ሕይወት ሳላጠፋ ሙርኮኛ መሆኔን ይቆጨኝ ነበር። በሗላ ግን የኔ የበላዮቼ አዲስ አበባ ዉስጥ በመኪኖቻቸዉ እየተመላለሱ እጃቸዉን አስረክቡ ሲባል፤ እኔ ሞኝ ነበርኩ ልበል? የሚል ጥያቄ ጠየቅኩኝ።ቁጭቴ ልክ እንዳልነበረ ተረዳሁ።>>

በተረፈ ግን የበታች አመራር በመኖሬ ፈጽም የተባልኩትን ፈፅሜ አለሁ። ሕይወቴን ለማዳን። ለምን ቢባል፤ የተሰጣቸዉ ትዛዝ ያልፈጸሙ መሪዎች ሲረሸኑ አይ ስለነበር።አሁንም ህዝብ በድያለሁ ብየ እምሮየ ዉስጥ የቀረጽሁት ቅር የሚለኝ ተግባር የለም።”” ምናልባት በአንድ ነገር የምቆጨዉ ነገር ቢኖር፡ ይሄዉም የኢሕአዴግ ዓላማ በበለጠ ለማወቅ ጥረት እንዳላደረግኩኝ መሆኔን አንጂ ሌላ ከዚህ ዉጭ የሚቆጨኝ የለም።


ወይን፦ በብኤም የመርሳን ሕዝብ መደብደቡንስ እንዴት ሰረቀብርሃንን አላስቆጨዉም?

ኰሎኔል፦ በኢሕአዴግም ሆነ በሕዝብ አንድ የተቋጠረ ስህተት አለ። ሦስተኛ ከ/ጦር ደሴ አካባቢ የነበረ ቢሆንም እንኳ ለሁሉም ተግባሮች፤እሱ ብቻ ይፈጽም ነበር ማለት አይደለም። በዛ ጊዜ ድብደባ ተፈጸሟል ተብሎ አቃለሁ። ግን ሦስተኛ ከ/ጦር ፈጽሞታል የሚል እምነት ግን የለኝም። በሆነ አጋጣሚ የኔ ምክትል አዛዥ የነበረ የሰጠዉ ቃለ መጠይቅ ተከታትያለሁ። ድብደባዉ በኛ ክፍለ -ሠራዊት እንደተፈጸመ አምኗል።እኔ ግን ተፈጽሟል የተባለዉ ድብደባ ሲካሄድ በዕለቱ ደሴ ለስብሰባ ሄጀ ስለነበር አላዉቅም።


ወይን፦ ብትኖር ኖሮ ከተፈጸመዉ ተግበር የተለየ ሥራ ምን ትፈጽም ኖሯል?

ኰሎኔል፦በርግጥ የተሰጠኝን መመርያ ከመፈጸም ወደ ሓላ አልልም ነበር። በተሰጠኝ መመርያ ቦታዉን በደበደብኩ። ግን በኔዉ ምክትል አዛዥ የተሰጠ ቃለ መጠይቅ ወዲያዉኑ የተደረጋና አንዲያም አንዲል የተደረገ እንጂ።

ወይን፦ እንዲል የተደረገ እንጂ ስትል በግፊትና በተጽኖ እንዲል ተደርጓል ማለትህ ነዉ?


ኰሎኔል፦አይደለም፡፤ ሙሉ ግፊትና ተጽኖ ላይኖረዉ ይችል ይሆናል።በጊዜዉ መዉጫ ለመፍጠር ተብሎ የተባሉ አባባሎች ናቸዉ አንጂ ሐቅ አይደለም።ይሄዉም ጊዜዉን ለመምሰል፤ለማዳመቅ ካልሆነ በስተቀር፤ እንደ ሓቅ አልወስደዉም።ሥስተኛ ክፍለጦር ፈጽሞታል የሚል ግን አላምንበትም።

ወይን፦ የተከሰስክበት ገመናስ ታወቀዋለህ?


ኰሎኔል፦ ቀርቦ ይሄ ነዉ የተከሰስክበት ገመና ብሎ የጠየቀኝ ሰዉ ወይም አካል ወይም ክፍል የለም። ቀደም ሲል ማለትም ስማረክ አስተምር ተብየ አስተምሬአለሁ።ምናልበት ድሉ ቢዘገይ እኛም እንደነዛ ሌሎች በ”ኢሕ.ዴ.ን” ዉስጥ ገብተን ማገልገል እንችል ነበር ይመስለኛል። ብቻ ደርግም ብዙ አልቆም አዲስ አበባም ተያዘ። እኛም እሥር ቤት ገባን። ከዚያ በሗላ አንድ ጊዜ ብቻ የሕይወት ታሪክህን ተናገር ተባልኩኝ እንጂ በዚህ ጉዳይ ተከሥሰሃል ያለኝ የለም።ከአንዳንድ አስረኞች እንደምንስማዉ የተማረኩ ታጋዮች፤ተገድለዋል፤የሚል ነዉ። በቪድዮም ይሄንን ደግሜ ሲናገሩ ሰምቸዋለሁ።የተማረኩ ታጋዮች ግፍ በሆነ አገዳደል እንደተገደሉ ተገልፆ ነበር። በመሠረቱ ሠራዊቱ ሲበታተንብን ሲፈራርስብን ምርኰኞችን ስናይ እንዲረሸኑ ከማድረግ ወደ ሗላ አንልም ነበር። አጋጣሚ ግን እኔ ወደ “ቢ ኤም” እና ወደ ሌላ ንብረት ማቃጠል ነኝ የገባሁት። ለምን እኝያ እዛ ተማርከዉ ነበር ተባሉት ታጋዮችም ቢሆኑ እንድንለቃቸዉ ነበር የምንጠባበቀዉ። እዛ መቆየታቸዉ በወታደራዊ ዓይን ከነሱ ሊገኝ ሚችል ጠቃሚ መረጃ ስላልነበረ ።ስለዚህ እነኛ ታጋዮች ተገድለዋል የሚል ለወደፊቱ በሚቀርብ ማስረጃ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሊቀርብልን ካልሆነ በስተቀር፤ ይህ አድረገሃል ተባልኩት የለኝም። ይህ አድረጌአለሁ የምለዉ የለኝም። ሕሊናየ የጠራ ነዉ።

እርግጥ ወታደሮች ነን። ያን የሚያክል ጦር ስንመራ ቆይተናል። ስሕተት አልተፈጸመም አልልም።……መቶ በመቶ ንፁሃን ነን ለማለት አልችልም።ተገድለዉም ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ አሁን ምትጠይቁኝን ጥያቄ ነገ ፍረድ-ቤት የምናገረዉ ይሆናል ብየ እገምታለሁ።


ወይን፦ የቀረህ የምትጨምረዉ አስተያየት ካለ?

ኰሎኔል፦ለድል መመታታችን የአመራር ድክመት ነዉ። ኢሕአዲግ በድል ሊወጣ የቻለዉ፤ ምክንአትም ያ ነዉ። ከተማረክሁኝ በሗላም አንድ ጥያቄ ቀርቦልኝ ነበር፡ “ካሁን በሗላ ለሕአዴግ ግሥጋሴ ምን የሚያስቆመዉ ሐይል ይኖራል ትላለህ?” አሉኝ። እኔም፡ አንጃ አንግዲህ ካሁን በሗላ ራሳችሁ አዉቃችሁ ካልቆማችሁ የሚያስቆማችሁ ሐይል የለም። ነዉ ያልኳቸዉ። እንዳልኩትም በእግር ሲኬድ፡የነበረዉ፡የኢሕአዴግ ጉዞ በመኪና ሆነ። የሄሊኰፕተር እጥረት ስላልነበረ ጉዞዉም እንዲሁ ሊፈጥን ቻለ።” በማለት “ወይን” ከተባለዉ የወያኔ የትግርኛ ጋዜጣ የሦስተኛ አንበሳ ክ/ጦር ዋና አዛዥ ከነበሩት ከመራኛዉ አንበሳ ከጀግናዉ ኰሎኔል ሰረቀብርሃን ቃለ መጠይቅ አዚህ አበቃ። ያነበባችሁትን ቃለ መጠይቅ፤ ኰሎኔሉ ለ7 (ሰባት) ዓመት ለፍርድ ሳይቀርቡ ወይም፤ ስለገመናቸዉ ሳይጠየቁ ፤ እሥር ቤት እንዳሉ ይህ የተደረገ ቃለ መጠይቅ ነዉ። ቃለ መጠይቁ ከተደረገበት ከ1990 ዓ.ም ወዲህ ወያኔ የት ኰሎኔሉ የት እንዳደረሳቸዉ አይታወቅም።ፍትህ ይዘገያል አንጂ አይቀርም።


እዚህ ላይ አንባቢ ልብ ማለት ያለበት፤ ወያነ ጦሩነቱ ራሱን ባንበሳ ሌላዉ፡በጥንቸልነት እየመደበ የሚደፍቀዉ አረፋ፤ከሚገባዉ በላይ በየሚድያዉ የሰማችሁት ጉዳይ ነዉ። ሀቁ ግን ወያኔ እንደሚደፍቀዉ ሳይሆን ከላይ ከኰሎኔሉ እንደሰማችሁት ለወታደሩ ሽንፈት ምክንያት አመራሩ ተብትቦ አላሰራም እንዳለዉ ያነበባችሁት ነዉ።ለዚህም ነበር ሠራዊቱ በግኖቦት 18 አና19 ምሽጉን እየጣለ መሳርያዉን ይዞ ወደ አዲስ አበባ በመግባት ዉድቀቱን ወዶ ሳይሆን

ሳይወድ ከአመራር ጉድለት ሽንፈቱን የተቀበለዉ።


ፍትሕን በሚያላግጡና ጊዜ በጣላቸዉ ኢትዮጵያዊያን ላይ በሚያሾፉ ትቢተኞችን አንድ ቀን ኢትዮጵያ ትፋረዳቸዋለች!
ጌታቸዉ ረዳ

(ሳን ሆዘ፤ ካሊፎርኒያ)

No comments: