Wednesday, June 4, 2008

A Must Read Reporters' Editorial Paper




ማ ከማን ይደብቃል?
Wednesday, 04 June 2008
የአንድ ሀገር ሕዝብ ለሚኖርባትና ለተፈጠረባት ሀገር ጉዳይ ባለቤትና የእጣ ፈንታዋም ወሳኝ መሆን እንዳለበት በመርህ ደረጃ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በሕዝብ የተመረጡ መንግሥታት ይኸንን መሰረታዊ መርህ ጠብቀው የመረጣቸውን ሕዝብ ካላገለገሉ በተጠያቂነት ይቀርባሉ፡፡


ሕዝቡ ባለቤት በሆነበት ጉዳይ፣ መንግሥት እቅዱንና አቅጣጫውን እንደ አስፈላጊነቱ ቀድሞም ሆነ በሂደት ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ያ ካልሆነ የሕዝብና የመንግሥት ተሳትፎ እየላላ፣ የጋራ የሆነው የዕድገት ክንውን እየተደናቀፈ፣ ይሄዳል፡፡ በሃገራችን የኑሮ ውድነት ታይቶ በማይታወቅና በሚያስደንግጥ መልኩ እያሻቀበ ነው፡፡ መሰረታዊ የምግብ እህሎች ዋጋ በአስፈሪ ሁኔታ "ጣራ እየነካ" በመሆኑ የቤተሰብ የኑሮ ሥጋት የዚያኑ ያህል ከፍ ብሏል፡፡ የኩንታል ጤፍ ዋጋ በአራት ቀናት ልዩነት 140 ብር የጭማሪ ልዩነት ሲያሳይ መጭዎቹ ወራቶች በጭንቀት የሚጠበቁ ቢሆኑ አይገርምም፡፡ የጤፍና የሌሎች የምግብ እህሎች ከአቅም በላይ ሆነው በማያግተረትሩበት ወቅት ተዛማጅ የሸቀጥ ዕቃዎችም "የማይቀመሱ" እየሆኑ ሥጋት ፈጥረዋል፡፡ አማካይ ደመወዝ ተከፋይ የሚባለው እንኳ ሊቋቋም በማይችልበት የኑሮ ውድነት በመቀጥቀጡ ሥጋቱ የትየለሌ ሆኗል፡፡


አንዳንድ የሃገሪቷ ክፍሎች በድርቅ መመታታቸው ከምንጊዜውም በላይ አስግቷል፡፡ከዜና አቅራቢዎች ያለው መረጃ በአንዳንድ ቦታ ቀያቸውን ለቀው በመፍለስ ላይ ያሉ ዜጎች እየበረከቱ መሆናቸውን ነው፡፡ በርካታ ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ በማጣት በረሃብ እየተሸነቆጡና እየደከሙ መሆናቸውን የሚገልፁ መርዶዎች በውጭ ሚዲያዎች ይቀርባሉ፡፡ እንዲሀ ዓይነቱ ከፍተኛ ችግር በሕዝብ ላይ ተጋርጦበት ሳለ በመንግሥት በኩል ያለው ምላሽ የቀዘቀዘ ሆኖ ይታያል፡፡


ባለሥልጣኖቻችን አልፎ አልፎ የውድነቱን መንስኤ ሊነግሩን ብቅ ከሚሉ በስተቀር የችግሩን ተጋሪነት የሚያሳይና ለመፍትሔው ምን እያሰቡ መሆኑን እንድናውቅ እድል አልሰጡንም፡፡ በሃገራችን ድርቅ ገብቷል፤ የሚለው መረጃ ለማስተላለፍ ብዙ ጥንቃቄ እየተደረገ፣ ለሕዝቡ "ምስጢር" እንዲሆን መፈለግን በሚያሳይ ሁኔታ ብልጭ ድርግም የሚል እንቅስቃሴ ብቻ ይታያል፡፡


የሕጻናትን ችግር የተገለገፀውም፣ የውጭ ሚዲያ የሰጠውን ቁጥር ለማስተባበል ተብሎ የታሰበ ስለመሰለ ቅሬታ ይፈጥራል፡፡ ቀድሞ ሊገለፅለት ሲገባ አልተነገረውም፤ አሁንም መፍትሔውን አልተገለፀለትም፡፡ እንዲህ አይነት አስፈሪና አሸባሪ ሁኔታዎች በታዩበት ወቅት መንግሥት የቀየሰውን መፍትሔ አለማወቅ የባሰ ያጨናንቃል፡፡ መንግሥት ለዚህ ከፍተኛ ችግር፣ ያዘጋጀውን የመፍትሔ እቅድ ብቻ ሳይሆን የተግባራዊነቱ የጊዜ ገደብ መገለፅ አለበት፡፡


እነዚህን መሰል ከሕዝቡ ኑሮና ስሜት ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ጉዳዮች፣ ለሕዝቡ አለማሳወቅ ሕዝብን የሚያበሳጩ፣ በመንግሥትም ላይ ያለውን መተማመን የሚያመነምኑ ናቸው፡፡ በሕዝብ ሥልጣን ላይ የተቀመጠ መንግሥት የሕዝቡን ጭንቀት መካፈልና ማቃለል ግዴታው መሆኑን ከዘነጋ ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሱዳንና በኢትዮጵያ ወሰን በኩል የተሰማው የድንበር መተላለፍ ሥጋት የተፈጠረው እስከዛሬ የተደበቀ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን አሁንም የተሟላ መረጃ ያለማግኘት መንስኤ ነው፡፡ የሱዳንና የኢትዮጵያን ወሰን በተመለከተ እስካሁን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተደብቆ የኖረ እንደመሆኑ ድንገት እጁ ላይ "ሲዘረገፍበት" ጥያቄዎቹን ማንሳት የግድ ይለዋል፡፡ በምን ምክንት ምን እንደተፈፀመ፣ በባለሥልጣኖች የተሰጠው ማብራሪያ እንዲታመንበት ከተፈለገ የዘገየም ቢሆን ማብራሪያውን በማስረጃ ማስደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩን በአጠኑትና በባለስልጣናቶቻችን መካከል ያለው መረጃ ክፍተት የፈጠረ በመሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ብዥታ ፈጥሯል፡፡ ስለዚህ ባለቤቱ ለሆነው ሕዝብ ከመግለጫ ባለፈ በአስረጂ ሰነድ ተደግፎ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይኸ ካልሆነ በሃገሩ ወሰን ድንበር ጉዳይ ባይታወር እየሆነ፣ መንግሥት ለሚወስደው ርምጃ ሁሉ ጥርጣሬውን እያዳበረ ይሄዳል፡፡ ይኸም ሆድና ጀርባ ለመሆን የራሱን አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡


ለምን ተደብቆ ቆየ የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ መፍትሄውስ ህዝቡን ያሳተፈ ይሆናል ወይ? የሚለውን ሌላ የጥርጣሬ ጥያቄ ያቀርባል፡፡ በሱዳን ድንበራችን በኩል ታምቆ የቆየው ክርክርና የመንግሥታቱ ስምምነት፣ በሶማሊያና በጅቡቲ በኩልስ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ለመጠራጠር ይዳርጋሉ፡፡ ሌሎችም አብነቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡


መጠራጠር ለአንድ ሃገር ሕዝብና መንግሥት የሚበጁ አይደሉም፡፡ ይከፍላሉ፤ ያራርቃሉ፡፡ የመንግሥት "ሚስጥር ጠባቂነት" እየበዛ በሄደ ቁጥር በሥሩ የተደረደሩት የአገልግሎት መስጫ ተቋሞች በስህተት ላይ ስህተት ለመፍጠር ይዳርጋቸዋል፡፡ በቀጥታ ከሕዝቡ ጋር እንደመገናኘታቸው የሚቀርብላቸውን የሕዝብ ጥያቄ መመለስ ያዳግታቸዋል፡፡ አንድ የክልል መንግሥት ወይም የቀበሌ አመራር፣ ለምግብ ፍጆታዎች መናር መንግሥት ያዘጋጀው መፍትሔ ምን እንደሆነ ሊያስረዳ ካልቻለ፣ በሕዝቡ ዘንድ የተናቀና የተጠላ ይሆናል፡፡


በየአካባቢው በቤቱ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ወደ ከተማ ስለሚፈልሰው ዜጋ በድርቅ መጎዳቱ አለመነገሩና መንግሥት ምን እያደረገ መሆኑን አለመረዳቱ የጥላቻ መገለጫ ምልክት ተቀባይ መሆን አይቀርለትም፡፡በማስረጃ ተደግፎ እውነቱን እንዲደርሰው እስካልተደረገ ድረስ ምንም ያህል ችግር ቢያንገላታው ለድንበሩ ቀናዒ የሆነና ይኸንኑም በተደጋጋሚ ያስመሰከረ ሕዝብ በመንግሥት መናደዱና በቁጣ እንደሚሞላ አያከራክርም፡፡


ሕዝብ መጋፈጥ የሚገባውን ችግሮች መንግሥት ማወሳሰብና ባይታወር ማድረግ፣ መፍትሔዎችን በጊዜው ባለመግለፅ "በስጋት አረንቋ" ላይ እንዲቆዩ ማድረግ የለበትም፡፡ ባለጉዳይ ለሆነው ሕዝብ ያለውን ችግር ማካፈል፣ መፍትሄውን ማፈላለግና የተገኘውን መፍትሔ መተግበር አለበት፡፡ እንዲህ ካልሆነ ሕዝብና መንግሥትን የሚያስተሳስራቸው ቁርኝት የተበላሸ ሲሄድ፣ ከግለሰቦች ይልቅ በሃገር ላይ የሚደርሰው ጉዳት ያሳዝናል፡፡ ስለዚህ መንግሥት አሁን ላሉት ችግሮች ያሰበውን መፍትሄ ሳይደበቅ ይንገረን፤ ተግባራዊም ሲያደርጋቸው እንይ፡፡

No comments: