ቤተክርስትያን የታቦት ማዕከል ሆኖ እንዳገለገለ ሁሉ ፤አምሐራም በአገር ምስረታ ሰንተር / ማዕከል/ ሆኖ እዚህ ድረስ አምጥቷቷል!
ጌታቸው ረዳ
Ethiopian Semay
8/13/23
ይህ ትችት በሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ንግግር ላይ አቧራ በማስነሳት እየተንጫጫ ስላለው “ጋንታ ዋጭዋጭ” ሁለተኛ ክፍል ትችቴ ነው።
የሻለቃው ንግግር እስከዚህ በየሚያስጮህ እንዳልሆነ ሻለቃውን ለመከላከል በክፍል 1 ያቀረብኩዋቸው ነጥቦች እንዳሉ ሆነው፤ “ወደ ትፋቱ የተመለሰው ኤርሚያስ ለገሰም አደንቋሪው ጉጅሌን በመቀላቀል” የሻለቃውን ንግግር የተጣመመ ትርጉም በመስጠት “ይቅርታ ይጠይቁ” የሚል ተመጻዳቂ ጅራፋቸው በማስጮህ ቀጥለውበታል። ኤርሚያስ ለገሰም ይቅርታ አስጠያቂ?? ኤረረ ረ!!
የዋጭዋጭ ጉጅሌዎ መነሻ እንደየ ጉጅሌዎቻቸው የተለያየ ምክንያት ቢኖራቸውም፤ ምክንያታቸው የየራሳቸው ሆኖ እየመዘዙ እየተረባረቡባቸው ያሉት የሻለቃው ሁለት ንግግሮችን በድጋሜ እንመልከት። ለታሪኩ/ለሬከርድ ግን ሁሉንም ንግግራቸው እንድታስታውስዋቸው ካለፈው ሙሉውን ንግግራቸው እንደገና ልጥቀስና ወደ ሁለቱ ነጥቦች እገባለሁ።
ሻለቃ ዳዊት ንግግር፡
ጉጅሌው ሁለት ነጥቦችን በመቁረጥ መሬት እየጫረ አቧራ ሲያስነሳ እያየንባቸው ያሉት ሁለቱ ነጥቦች እንምልከታቸው።
1ኛ- <<በኛ ኮንዲሽን ፤ በኛ ተርም ፤ እኛ በምንፈልገው መንገድ አዲስ ሥርዓት እንመሰርታለን።>>
2ኛ- <<እኛ ነን እዚህ ያደረስናት ታሪካችን ባህላችን “ሰንተር” ማዕከል ሆነን እዚህ ድረስ ያመጣናት ኢትዮጵያ እኛ ነን።>>
እነዚህ ሁለት ነጥቦች ባለፈው ትችቴ በጥቂቱ ነክቻለሁ። ቢሆንም ዛሬም እየደጋገሙ ብዙዎቹ በነዚህ ሁለቱ ነጥቦች ናቸው እየጮሁት ያሉት።
<<በኛ ኮንዲሽን ፤ በኛ ተርም ፤ እኛ በምንፈልገው መንገድ አዲስ ሥርዓት እንመሰርታለን።>> በሚለው ንግግራቸው እንደገና እንሂድበት፡
እስኪ የሁለቱም እንግሊዝኛ ትርጉማቸው እንፈትሻቸው፡ ሻጩና ገዢውስ በነዚህ ትርም እና ኮንዲሽን እንዴት ሊግባቡ ይችላሉ የሚለው እንመለከታለን።
“ተርም” የሚለው ብዙ ትርጉም ያዘለ ቢሆንም ሳይፈጭ በጥሬ ትርጉሙ “ውል” ማለት ነው። “ኮንዲሽን” የሚለው ደግሞ “ሁኔታ” ሲሆን ይህ ቃልም በብዙ መንገድ የሚተነተን ትርጓሜ ሲኖሮው “አንድ ነገር አሁናዊውን ያለበት ሁኔታ እና በመጪው ጊዜ ሊገጥሙኝ ይችሉ ይሆናል የሚላቸው ስጋቶች “ሁኔታዎች” ይባላሉ ። ሁኔታው ምንድነው? ብሎ አንድ ዳኛ ሲጠይቅ “የገጠመህ ምክንያትና መነሻው ምንድነው?’ ማለቱ ነው።
አማራው በራሴ ሁኔታ ነው እንዲመሰረት የምታገለው ሲል ለሁኔታው መንስኤ ምድርና ሰማይ የሚመሰክሩለት ምክንያቶች አሉት ። ኮንዲሽን አለው። ያለ ውል (ያለ ተርም) ሲገፋ 35 ድፍን አመት አልፎታል። ስለዚህ በራሳችን ምክንያቶች ውሉን “ተርሙ” እንዲደነገግ እናደርጋለን ነው የሻለቃው አጽንኦት። ጫጫታ አያስፈልግም።
ተርሙ (ውሉ) አማራ የገጠመው “አስቸጋሪ ሁኔታ” እንዲያስቆመው ያደርጋል። በቃ! ሰው እንዴት ይህንን መረዳት ያቅተዋል።
እንዲህ ከሆነ ውሎች እና ሁኔታዎች የተዋዋይ ወገኖች የውል መብቶችን እና ግዴታዎችን ያመለክታሉ። ተዋዋይ ወገኖች በስምምነት ውስጥ ሊከተሏቸው የሚገቡትን ሰፊ የመመሪያ ጽንሰ-ሀሳብ ያመለክታሉ። ፖለቲካ ሸቀጥ ነው። የሚገዛም የማይገዛም አለ። አቅራቢው የራሱን “ተርም” (የጊዜ ገደብ ሊሆን ይችላል፤ “ኮንትራት/ውል/” ሊሆን ይችላል…ወዘተ) ። የሁኔታዎቹ አንገብጋቢነት በዝርዝር ሲቀርቡ “ውሎች/ተርሞች” እንዲሁ ይቀርባሉ።
ፖለቲከኞች በማንኛውም አገር የሚወዳደሩበት ምክንያት የራሳቸው “ተርምና ሁኔታዎችን” ለማስፈጸም ነው። በራሳቸው ተርምና ሁኔታ ቤተሰቦቻቸውና የሀገሪቱ አንድነት እና አስተዳደር በራሳቸው ትርምና ኮንዲሽን ለማስተዳደር ነው የሚወዳደሩት። ለፖሌካውም ይሁን ለማንኛውም መደበኛ የንግድ ስምምነት በዚህ ሕግጋት ይካሄዳሉ። ገዢ ሊኖር ላይኖር “ሁኔታዎችና” “ወቅቶች” ይወስኑዋቸዋል። ሁኔታዎች “ውል/ተርም” እንዲፈጠር ያስገድዳሉ “ውል/ኮንትራት/ተርም ያለ ሁኔታ አይፈጠሩም”
በዲሞክራሲ ሥም ‘ግብረሰዶማዊውም ሆነ ፤ የሰው ሥጋ የሚበላው ጭራቅ’’ በመንግሥትነት ተዋህዶ እየሰራ ያለው ግልጽና ህቡእ ጭራቅም” ለፖለቲካ ውይይት፤ ለአገር ሰላም ሲባል “የራሱ ትርምና ኮንዲሽን” ይዞ አንዲመጣ ይፈቀድለት የሚለው <<የዋጭዋጭ ጉጅሌው>> በኛ ውል እና ሁኔታ አዲስ ሥርዓት እንመሰርታለን የሚል ከአንድ የአማራ ምሁር ሰው ንግግር ሲሰማ “መንጫጫት” የለበትም።
አማራ አሁን ያለበት የ35 አመት “ሁኔታ” ካልቆመ በሃይልም በውይትም ሁኔታው ያበቃል! ኢትዮጵያ እንዳትፈርስና እንዳትናጋ እራሱ እየተናጋ እስካሁን አቆይቷታል። ለዚህ ነው አማራ ማዕከል ነው፤ እምቢ ባለ ጊዜ ግን አገሪቷ ማዕከልነትዋ ታጣና አስኳላ ይፈርስና አገሪቷም አብራ ትፈርሳለች የምንለው ለዚህ ነው። አማራውን ማዕከል አስገብተው የከበቡት ጠላቶቹ አሁን ያለው ኮንዲሽንና ተርም “አልቀበለውም” ብሏል።ይህ ነው የሻለቃው “ተርማና ኮንዲሽን” እየገለጹት ያሉት። ለምን ማጣማም ተፈለገ?
ከአእላፍ ሁኔታዎች (ኮንዲሽኖች) አማራዎች የተጋረጡዋቸው አንዲትዋን ችግራቸው ቢገባችሁ በምሳሌ ልጥቀስና ወደ ሁለተኛው እገባለሁ።
ሁኔታው በኛ ተርም እንመሰርታለን እንዲሉ ያስገደደ ንግግር ምንድ ነው? ትልቁ ጥያቄ ይህ ነው።
በዘመናዊ ምርምርና ጥናት ያልታነጹ “ያልተማሩ” ተብለው በሚጠሩ የጥንት ዘመን ነገሥታት ሳይሆን “በዘመናዊ ዲሞክራሲ ታንጸን “የተመራመርን ነን” በሚሉ ምሁራን “ተርምና ኮንዲሽን” የጸደቀ ሕገ መንግሥት የመብትና የታሪክ ጥሰቶችን በአማራው ላይ እየፈጸመ ነው።
<< ማተብ፤ የሰንደቃላማ፤ የሃውልቶችና ቅርሶችን ሁኔታን (ትርምና ኮንዲሽን) እንመልከት>>፡ (የደረሰበት የዘር ጭፍጨፋውን ወደ ጎን ትተን ፤ ጥቂተዋን እንደምሳሌ እንመለክት)
አማራው ክርስትያን ነው፤ ነገዱ አማራ ነው። አማራው በሃይማኖቱና በማንነቱ ተጨፍጭፏል። ይህንን ሰማዩንም ምድሩንም የሚመሰክረው ነው።
የአምሐራዊ ነገሥታቶችና የመኳንንት አርበኞች መታሰቢያ ሓውልቶችና ጥንታዊ ህንጻዎች፤ እየፈረሱ፤ በምትካቸው “የአዝማሪዎችኛ የፐኮክ እዋፋት ሃውልቶች አደባባይ ላይ እየተተከሉ” ፡ አገሪቱ የመሰረቱባትና ኣሕዛብ አሰባስበው ከጠላት የተከላከሉላት በሚሊዮን ኣእላፍ ሕዝብ እያውለበለቡ የወደቁላት “የሰማዕት ምልክትና የአደራ ቃል ኪዳን” የሆነቺወን አርማ “ሰንደቅአላማየን” ከገላየ፤ካንገቴ ከትምሕርት ቤቴና ከንግድ ቤቴ ፤ ከመኖሪያ ከመኝታ ቤቴ እና ከመኪናየ ፤ እንዳልለብሳትና እንዳላውለበልባት “ከገላየ እየተነጠቅኩ፤ማተቤ ካንገቴ እየተበጠሰ፤ ከመኪናየ በምላጭ እየተፋቀች” ትውስታዎችና ቅርሶቼ 35 ሙሉ በጠላቶቼ እጅ እንዳልሆኑ ሆነዋል። ከዚህ በሗላ “በቃ” በራሴ <<ተርምና ሁኔታ>> የማይገድለኝና የማይነጥቀኝ “ትረምና ኮንዲሽን” እንዲመሰረት በውድም በግድም አዲስ ሥርዓት ለመመስረት እየታገልኩ ነኝ። ማለት ምን የሚያንጫጫ ነገር ተገኘ?
ወደ ሁለተኛው ነጥብ ከመሄዴና ከመደምደሜ በፊት ስለ ትርማ ኮንዲሽን አንድ
ነገር ልበል።
የሻለቃው ተርምና ኮንዲሽን በአሜሪካው የሀገርቤት (የባለ ሃገር ቤት )
ዘፈን ዘፋኙ Jonny cash ተርማና ኮንዲሽን እንደምሳሌ ላሳያችሁና ሻለቃው የሚሉትንት ተርም እና ኮንዲሽን በዚያው አገናዝቡት።
Jonny Cash ይባላል የታወቀ የአሜሪካኖች country - and –western የሚበለው የባለገሮች ዘፈን ዘፋኝ ነው። ከመሞቱ በፊት በብዙ ሺሕ የሚቆጠር አፍቃሪዎቹ በተጋበዙበት የሙዚቃ ድግስ በመገኘት ፤ ሰላም እንዴት ናችሁ “Ragged Old Flag” (ያረጀ የወለል መጥረጊያ ጨርቅ) በማለት በምጸት እየተናገረ ትልቁ የአሜሪካ ሰንደቃላማ እያውለበለ መድረኩን ከፈተው። ሕዝቡ በቁጣ በጩኸት አስተጋባው፡ ማቆሚያ የሌለው ስድብ ወረደበት። ውረድ ! ጥፋ! ይሉታል። አድምጡኝ እማ! አንዴ ጸጥታ! ሲል የተቆጣውን አድማጭ ጠየቀ። አድማጩም “ምን አባቱ ሊሰድበን ሊለን ነው ከዚህ ወዲያ ውርደት” እያለ ዕድል ሰጠውና ሕዝቡ ጽጥ አለ።
“But, I will tell you what. We have also got a right to bear arms and if you burn my flag I will shoot you!!” (“ግን፣ እኮ ደግሞም ልንገረችሁ! ሰንደቃላማየን የማቃጠል መብት አለህ፤ ግን እኔም መሳሪያ የመታጠቅ መብት ስለተሰጠኝ ፤ ባንዲራዬን ካቃጥልክ የህይወትህ ፍጻሜ ይሆናል!!) እያለ ሰንደቃላማዋን እየሳመ ሲነግራቸው፤ ምድር ሰማዩን ያናጋ የደስተና የኩራት ጩኸት ለበርካታ ደቂቃዎች አስተጋቡለት።
ይህ የተርምና የኮንዲሽን ሰንደቃላማየን መስደብና ማቃጠል መብት አለህ፤
ስታቃጥላትን ከጫንቃየና ካንገቴ ስትነጥቀኝ ግን በታጠቅኩት ነፍጥ የህወትህ ፍጻሜ ይሆናል። የሚል ነው የሻለቃው ተርማና ኮንዲሽን
ለማጽደቅ የፈለጉት። ይህ እንዴት ያሳክካል?
ወደ 2ኛው ነጥብ ልግባና ልሰናበታችሁ፡
<<እኛ ነን እዚህ ያደረስናት ታሪካችን ባህላችን “ሰንተር” ማዕከል ሆነን እዚህ ድረስ ያመጣናት ኢትዮጵያ እኛ ነን።>>
አዎ ልክ ነው።
በንጉሥ አምደጽዮን በራሱ ጽሑፍ ልደምድም፡-
ቤተክርስትያን የታቦት ማዕከል እንደሆነ ሁሉ ንጉሥ የ12 ዳኞች መሃለኛ (13ኛ) እንደሆነው ሁሉ አማራው አገር በመምራት፤በማስፋትና በማስተዳዳር ማዕከል ነበር።በዚህ ረገድ “ሰለሞናዉያን” የሚል የመካከለኛው ዘመን ታሪክ መጽሐፍ ጸሓፊ ተመራማሪው ዶ/ር ደረሰ አያናቸው ሰለሞናዊው አምሐራው ንጉሥ አምደጽዮን የጻፈው ሰነድ ኮንቲ ሮዚኒ እና ታደሰ ታምራት የዘገቡት በመጠቀስና በራሳቸው ምርምር ያገኙት ሰነድ አምሓራው ንጉሥ አምደ ጽዮን በራሱ ጽሑፍ እንዲህ ዘግቦታል ይላሉ፡--
የቃላቶች ማብራሪያ፡
ንጉሥ ውድም ርእድ የአምደ ጽዮን አባት ነው። ( ) ውስጥ የገቡ በደራሲው የተጨመሩ አንባቢው እንዲረዳው ላመድረግ የተጨመሩ ቃላቶች ናቸው። “እንትርታ” ብሎ የተጻፈው የጥንት ስሙ ሲሆን የዛሬው የትግራይ “እንደርታ” ነው።
<<እኔ አምደ ጽዮን በ498 በጸጋ ዓመት ነገሥኩ። ከዚያም በ499 በጸጋ ዓመት የእስጢፋኖስ (ገዳም) ጉልት በውድም ርእድ የተነጠቀውን የተነጠቀውን መልሼ ሰጠሁ። ከዚያም በሁለት ዓመታት ውስጥ (አባ) እስጢፋኖስና የአባ ክርስቶስ (ተስፋነ የወቅቱ ዓቃቤ ሰዓት) ታምኜ ወደ ጦርነት ሄድኩኝ። እግዚአብሔርም የዳሞትን ሕዝብ በእጄ ሰጠኝ።ልዑላኑን፤ገዥዎችንና ሕዝብን ወንድና ሴቶችን በብዙ ቁጥር የሰጠኝን ወደ ሌላ ስፍራ አጋዝኳቸው።በመቀጠል እግዚአብሔር የሐድያን ሕዝብ ሰጠኝ፤ ብዙ ወንዶችና ሴቶችን ሰጠኝ። ከዚያም የጐጃምን መንግሥት በእጄ ሰጠኝ። ከእነ ወታደሮቹ (የጦር ሠራዊቱ) ልዑካኑን፤ከገዢዎችና ብዙ ቁጥር ወንድና ሴቶችን ሰጠኝ ከዚያም እግዚአብሔር የእንትርታን ከእነ ሠራዊቱ ከእነ ሕዝቡ ከእነ ወገኖቹ፤ ከእነ ግዛቱ እስከ የአክሱም ገበዝ ድረስ በእጄ ሰጠኝ። እንዲሁም እኔ ንጉሥ አምደ ጽዮን ወደ ኤርትራ ባሕር ሄድኩኝ። እዚያው ስደርስ በዝሆን ላይ ወጥቼ ወደ በሕሩ ደረስኩኝ። ከዚያም ቀስቴንና ጦሬን አንስቼ ጠላቶቼን ገድዬ ሕዝቤን አዳንኩኝ>>
ገጽ 50-51 (ሰሎሞናውያን የኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ ከ1262-1521) ደራሲ ዶ/ር ደረሰ አየናቸው።
በማለት ጦረኛው ሰለሞናዊው አምሐራው ንጉሥ አምደ ጽዮን ምፅዋ ድረስ በመሄድ ቱርኮችን ያሸነፈበትን ሰላም ያሰፈነበትን እና ዳር ድምበሩን እንዴት ማእከል ሆኖ በሃይሉ ሳይመካ እንደ እነ ንጉሥ ኢዛና “እግዚአብሔር በእጄ ሰጠኝ” በማለት አማራዊው ንጉሥ አስኳልነቱ ምን ያህል እንደነበር ከንጉሡ ሰነድ መረዳት ይቻላል።
ስለዚህ ሻለቃ ዳዊት <<እኛ ነን እዚህ ያደረስናት ታሪካችን ባህላችን “ሰንተር” ማዕከል ሆነን እዚህ ድረስ ያመጣናት ኢትዮጵያ እኛ ነን።>> የሚለው ንግግራቸው “ለዋጭ ዋጭ ጉጅሌው” ባይዋጥለትም ሰነዶቹ የሚነግሩን ሰንተር ማዕከል ሆነው ኢትዮጵያን ከዚያ እስከዚህ ድረስ ያደረሰው ጉዞ ሲፈተሽ ‘ቤተክርሰትያን የታቦት ማዕክል እንደሆነቺው ሁሉ አምሐራዎቹ በሃይማኖት ባስተዳዳርና በአገር አስፊነት ማዕከሎች ነበሩ።
ጌታቸው ረዳ
No comments:
Post a Comment