Sunday, July 17, 2022

እያነባሁ ያነበብኩት የተከዳው የሰሜን ዕዝ መጽሐፍ ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay 7/17/2022


እያነባሁ ያነበብኩት የተከዳው የሰሜን ዕዝ መጽሐፍ

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay

7/17/2022

በሕግ የተጠበቀውን የደራሲው መብት ላለመጋፋት በጣም እጅግ በጣም አንድ ገጽ ብቻ ቀንጭቤ እንዴት ይህን ሁሉ ሰራዊት ትጥቅ ሊፈታ ቻለ? በሚል ደራሲው ያቀረበው ጥያቄ ጦሩ አምበጣ ሲያባርር እና የትግራይ ድሃ ተማሪዎች ደብተር መግዣ ሲያዋጣ ውሎ ደክሞት በተኛበት ወቅት አዘናግተው በድንገት በጭካኔ እንዴት እንደጨፈጨፉት እና በዚህ ጭፍጨፋ የትግራይ ሕዝብ ሱታፌ ምን እንደነበር ከጭፍጨፋው በተአምር የዳነው የዓይን ምስክር ደራሲ የአምሳ አለቃ ጋሻዬ ጤናው (ቻቻው) ከጻፈው መጽሐፍ አጋራችሗለሁ።

የመጽሐፉ ገጽ 393 ሲሆን ገጽ 101 ብቻ አንብቤአለሁ። ከደረስኩበት ገጽ ወደፊት ብዙ አሳዛኝ፤የሚያበሳጭ እና አስለቃሽ ታሪክ እንዳለ ተነግሮኛል። ለዛሬ ግን ደራሰውን እያመሰገንኩ ይህ መጽሐፍ እንዳነበው ከአገርቤት ሰው አስልኮ በማሰመጣት  በስጦታ ያበረከተኝ የልብ ወዳጄና ወንድሜ የሳንሆዜው ደ/ር ግርማ በቀለ ከልብ አመሰግናለሁ።              

አሁን ወደ ታሪኩ ልግባ፤-

ከዚህ ጽሑፍ በታች “ልዩ ኃይል” እያለ የሚተርከው ወያኔ ያሰለጠነው “የትግራይ ልዩ ኃይልን” ነው፦

“….. ልዩ ኃይሉ ከተተኮሰበት የሚደነብር፤ በልምምድም ሆነ በስልጣና ያልበቃ በመሳሪያና በፕሮፓጋንዳ ብቻ ማሸነፉን አልሞ የተነሳ ፈሪ ኃይል ነው።ሚሊሽያው ግን የዋዛ አይደለም። ምሽጉን ከያዘ መድፍ ቢተኮስበት ይሞታታል እንጂ ከምሽጉ ንቅንቅ አይልም።

በዋነኛነት ሠራዊቱ እጅ እንዲሰጥ ያደረገ ይኼ ያሰለጠኑት ብዙ ቁጥር ያለው ታጣቂ ነው። ታጣቂው ብዙ ቁጥር ያለው ስለሆነ የተሟላ ትጥቅ ሳይኖራትና 2 መቶ የማይሞላ የሰው ኃይል ላላት ሻለቃ 8 መቶ እና 1 ሺ ታጣቂ ይከባታል። ከሠራዊቱ በቁጥር ሦስት አራት ጊዜ የሚበልጥ ታጣቂ ጁንታው ያሰማራል። አንድ ሰው በሞተበት ቁጥር አንድ መኪና ሰው አምጥቶ ይደፋል።

ሌላው ጉዳይ የጁንታው ደጋፉዎች ሠራዊቱን በእጅጉ ያስደነገጡ ነበሩ። እንዴት መቶ ለማይሞላ አንድ ሻምበል ሠራዊት ከተሰለፈው ሚሊሽያና ከልዩ ኃይል በተጨማሪ ሦስት አራት ተሳቢ መኪና ድምፅ አልባ መሳሪያ የታጠቀ ሲቪል ሰው ይመጣል? የሚመጣው ሰው ደግሞ መጥረቢያ፤ USA ጩቤ፤ ካራ፤ገጀራ፤ሚስማር የተመታበት ጣውላ፤ ሠራዊቱ ዓይን ላይ የሚበተን በርበሬ… የያዘ ነው። ድንጋይ መሬቱን ሞልቶታል። ብሔርን መሰረት ያደረገ ስድባቸው አጥንት ይሰብራል። ሕሊና ያደማል።

በእርግጥ በወቅቱ የነበረ የትግራይ ሕዝብ ሦስት አራት አይነት ነው። ግማሹ የጁንታው ደጋፊ ሆኖ ሠራዊቱ እንደ አባቱ ገዳይ በክፉ ዓይኑ የሚያይ ነው። ዕድል ሲያገኝ  በገጀራና በመጥረቢያ እየቆረጠና እየፈለጠ፤በካራ እየባረከ፤ በድንጋይ እየወገረ እና በጩቤ እየወጋ፤በርበሬ ዓይኑ ላይ እየበተነ፤ጣውላ ላይ በተመታ ሚስማር ጭንቅላቱን እየሰነጠቀ ገድሏል፤ አቁስሏል።

በጣም ጥቂት ሕዝብ የሠራዊቱ ደጋፊ ነው። የጁንታው ደጋፊዎች ሠራዊቱን እንደ ጉንዳን ሲወሩት በግልጽ ይቃወማል።ተቃውሞ መከላከል ሳይችል ሲቀር ይለምናቸዋል። “ለዚህ ሠራዊት ይኼ አይገባውም ፤ አረ እባካችሁ የታሪክ ተወቃሽ አታድርጉን…?!” ይላል። ልመናው አላዋጣ ሲለው ያለቅሳል። ደረቱን እየደቃ “ወዮ”ይላል።  

ሌላው ሕዝብ ደግሞ ከማንም ያልሆነ መሀል ሰፋሪ ነው።ሠታዊቱን የሚቀጠቅጠውንም ፤ ለሠራዊቱ የሚያለቅሰውንም ዝም ብሎ ያያል። እንዲህ አይነት ሰው ግን አያበሽቅም? ይኼ እኮ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም። ይኼ እኮ የብሔር ወይንም የክልል ጉዳይ አይደለም። የሰብአዊነት ጉዳይ ነው። ሰው እንዴት በሰብአዊነት ጉዳይ መሀል ሰፋሪ ይሆናል?

የሆነው ሆኖ በኛ ሠራዊት ላይ ጥቃት  እንዲፈጸም ያዘዙና የመሩ የጁንታው ባለሥልጣናት ቢሆኑም፤ ሠራዊቱን እጅግ ዘግናኝና አሰቃቂ በሆነ መንገድ የገደሉ ግን ልዩ ኃይል ወይም ሚሊሽያ ሳይሆን የጁንታው ደጋፊ ሕዝብ እና እኛን የከዱ የሠራዊቱ አባሎች ናቸው።

ልዩ ኃይሉና ሚሊሽያው የያዘው መሳሪያ  ብቻ ነው፤የሚገድለውም በጥይት ነው። በካራ ያረዱ፤በጩቤ የወጉ፤ በገጀራ የቆረጡ ፤ በመጥረቢያ የፈለጡ፤  በድንጋይ የቀጠቀጡ አብዛኛዎቹ የጁንታው ደጋፊዎች ናቸው።ሌላኛው አስከሬንን በመኪና የረገጡ፤ ቁስለኛን በታንክ የጨፈለቁ የፍጥኝ አስረው ገደል የለቀቁ…ከኛ የከዱ የትግራይ ተወለጆች የሠራዊቱ አባላት ናቸው።

ይህ የጁንታ ኃይል ነው እንግዲህ የሠራዊቱን የግንኙነት መረቦች ቆራርጦና መንገድ ዘግቶ ካምፑን የከበበ። ሠራዊቱ ከአቅም በላይ ተዋግቷል (ሁሉም አንድ ባይሆንም ዘጠኝ ቀን ሙሉ ርሀብና ውኃ ጥሙ ሳያሸንፈው የተዋጋ አለ። አምስት ቀን ሌሊትም ቀንም ከምሽጉ ሳይወጣ ጥይቱ እስከሚያልቅ የተዋጋ አለ። ሰባት ቀን ሙሉ ያለምንም ዳቦና ውኃ የተዋጋ አለ።አምስት ቀን ሌሊትም ቀንም ከምሽጉ ሳይወጣ ጥይት እስከሚያልቅ የተዋጋ አለ። ለሦስት ቀን በእልህና ወኔ ከጁንታው ኃይል የተፋለመ አለ። ማንም የሚደርስለት አልነበረም።

ሠራዊቱ ምግብና ውኃ የለውም። የጁንታው ኃይል እንደፈለገ ምግብና መጠጥ ይቀርብለታል። ሠራዊቱ ጥይት እየቆጠበ ካልሆነ ካለቀበት ዕጣው በጁንታው እጅ መውደቅ ነው። ለጁንታው ኃይል ጥይት እንደ አፈርና ጭቃ ነው። ሁለት መቶእና ሦስት መቶ የሚሆን ሠራዊት 1 ሺ 5 መቶ እና ከዚያ በላይ የታጠቀ ኃይል ያሰልፋል። ከ    ደግሞ ተራራ የሚሸፍን ሕዝብ አለ።

ሠራዊቱ አንድ ሰው ሲቆስልበትና ሲሞትበት የሰው ኃይሉ ይቀንሳል። ጁንታው ስለሰው አይጨነቅም። አምስት ታጣቂ ቢሞትበት አምሰት አውቶብስ ሰው አምጥቶ ይደፋል። ታዲያ እንዴት ይሄ ሠራዊት ትጥቅ አይፈታም?

እያለ ወያኔ መጀመሪያ በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሲፈጽም ደራሲው በግል ማስታወሻው በምስጢር እየመዘገበ ያየውን የተፈጸመው አገራዊና ሰብአዊ ወንጀል ባስጨናቂ ሁኔታ በነበረበት ወቅት  ብርታትን የተሞላበት  የእልህ ግብግብ ያየውን ለኛ አቅርቦልናል።

ይህ የሚያሳየን የትግሬዎች ፋሺስዝም ብሎ ብሎ ወደ እዚህ ወንጀል እንዴት እንደተሻገረና ሕዝቡ ወደ ጭለማ እየተጓዘ እንደሆነ የምናይበት መስተዋት ነው። ይህ ሁሉ ወንጀል ፈጽመው ሲያበቁ ፤ በድርጊታቸው ሳይጸጸቱና ሳያፍሩ ፤ይህ አረመኔ ወንጀላቸው ደብቀው አሁን ደግሞ  “ትግራይ ሪፑብሊክ አንመሰርታለን” እየተባለ እየተፎከረ በሌላ መልኩ ደግሞ “ባንክ ክፈቱልን፤ ጤፍ ላኩልን፤ስልክ ጀምሩልን” እየተባለ እየተጮኸ ያለው። ከአማራ ሕዝብ ላይ ጠብ የለንም ይላሉ በሌላ በኩል ደግሞ የአማራን ልጆች ከጦሩ እየለዩ ሲረሽኑ ነበር። አምሳለቃ ጋሻዬ አንኳን ተረፍክና ይህንን ጉድ ነገርከን! ወጣም ወረደ ግን አብይ አሕመድና ወያኔ ሁለቱም ለዚህ ሁሉ ወንጀል ተጠያቂዎች ናቸው!!

መጽሐፉ ስጨርስ ለግምገማ እመለሳለሁ። እስከዚያው ድረስ ግን እንደተለመዳችሁት እንለምናችሀና ይህ ጽሑፍ ሕዝብ እንዲያውቀው ተቀባበሉት።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay

 

 

No comments: