የዳመናው አገር
ጌታቸው
ረዳ
Ethiopian Semay
6/5/22
ይህ ግጥም ወያነ ትግራይ ወደ መንበረ ሥልጣን ወጥቶ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ
በኋላ የጎሳ ፖለቲካ ነድፎ እርስ በርሳችን በጥላቻና በቂም በቀል የጎሪጥ እየተያየን የቋንቋ አደረጃጀት “በተከተሉና ባልተከተልነው”
መሃል ሲታይ የነበረ እጅግ አሳዛኝና አስፈሪ የጥላቻና የመሰዳደብ ዓየር ሰፍኖ በነበረበት የመጀመሪያው ዓመት እና በተለይም ከዚያ
ተከትሎ ለ7 ዓመታት ወያኔዎች ከኤርትራ ባንዳዎች ጋር በመሻረክ አማራውንና የኢትዮጵያ ሰንደቃላማና ታሪክ ጸሓፊዎችን እንዲሁም በተለይም
አፄ ምኒሊክንና አማራውን በጠላትነት እንዲታዩ ወያኔ ትግራይ በረሃ ውስጥ (1) ተጋድሎ ትግራይ በልዎ ነቲ ዓሻ ኣምሓራይ (2)
ንዓወሽ በሉዎ እዚ ኣድጊ ኣምሓራይ (3) ይኺድ ንዓዱ… የመሳሰሉ
ፀረ አማራ የወያኔ ዘፈኖችን በግልፅ ሲያሰራጫቸው የነበረውን የጥላቻ ቅስቀሳው በተግባር በመተርጎም አጀንዳቸው አደርገው የተነሱት
የትግሬ ወያኔዎች መንግሥት ከሆኑ ወዲህ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ
አማራዎች በወያኔ የደህንነት አፋኝ አባሎች እየተገደሉ፤ ከሥራ እየተባረሩ እንዲሁም በር በከፈተላቸው በተለያዩ እስላማዊ አክራሪ አማራ እና ክርስትያን ጠሊታ እንዲሁም በ “ኦብነግ እና ኦነግ” ነጻ ውጪ ቡድኖች በቆጨራ አንገታቸው እየተቀነጠሰ ዕርጉዞች በካራ እየተቀደዱ ለዘመናት በኖሩበት አካባቢዎች ወደ ትውልድ መንደራችሁ ሂዱ እየተባሉ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል። በወቅቱ የሻዕቢያ ሥራ አስፈጻሚ የነበረው “ወያነ” ስንቃወም የነበርን ትግሬዎች ትግሬነታችን ተገፎ “የሸዋ ትግሬዎች” (ሽዋውያን ተጋሩ) የሚል ቅጥያ ስም ተሰጥቶን ትግሬነታችን ሲነጥቀን እንደነበር ይታወሳል።
በአንፃሩ
ከወያኔ ያልተናነሱ አንዳንድ ጠባብ አማራዎችና የኦነግና የመሳሰሉ ዘረኞች የትግራይን ሕዝብ ሲዘረጥጡ አልፎም “በየፓልቶክ ክፍል”
“ከትግሬ ጋር ጋብቻ እንዳታደርጉ” የሚል ቅስቃሳ ሲደረግ እነሱንም በግልፅ ስቃወም ትግሬ በመሆኔ እኔኑም አብረው “ትግሬ ‘ትግሬ’
ነው” እያሉ “የወያኔ የሻዕቢያ ዘር” እያሉ በየሚዲያው ሲሰድቡኝ በመሃል ለሃቅ በመቆሜ “አንተም ተው አንተም ተው” ባልኩኝ ቁጥር
የደረሰብኝ ዘለፋ እጅግ ኣሳዛኝ ስለነበር፤የተሰማኝን ብቸኝነትና ቅሬታ ለታሪክ የዘገብኩት የዳመናው አገር የሚለው ግጥም ነው። በከነዚህ
ዘረኞችጋር ያበሩ ተቃዋሚ ነን ሲሉ የነበሩ “ኦነግ” ወይንም “ሻዕቢያ” ወይንም “ወያኔ/ትግሬዎችንም የሚተች ጽሑፌን” ስልክላቸው
ድረገጾችም ጽሑፌን ላለማሳትም ያግዱኝ እንደነበር እዚህ ለመጥቀስ አውዳለሁ። የተቃዋሚው ድምፅ እንደዛሬ ሳይበረታ ድምጻችን እጅግ
በጣም ትንሽ ስለነበር፤ በወቅቱ የነበረው ትግሉ ሁኔታ “ተስፋ አስቆራጭ” “ብቻህን በትዝታ ፈረስ ስቅስቅ ብለህ የምታለቅስበት”
እና “ሁኔታው በጣም ጨካኝ” ( cruel) ስለመነር እንደ ዛሬው
ቀላል እንዳይመስላችሁ እግረመንገዴን ላስታውሳችሁም እፈልጋሁ።
ግጥሙም አገር ውስጥ በትላልቅ መጽሄቶች ታትሞ ነበር። ዛሬ በራሴ መጽሓፍ ለማስረጃ ተካትቷል። ግጥሙም እነሆ። ለጎሳ እና ላጥንት ለሥጋ ዝምድና ላገር ልጅ ለወንዝ ልጅነት ሳይሆን “ለሰብአዊነትና ለኢትዮጵያዊነት” በመቆሜ ሞት አይቀርምና እኔ በሥጋ ብሞትም ታሪክ ዘግቦታልና የቆምኩላትን አገሬ ኢትዮጵያን ግን ለጊዜው ቢያዳክሟትና ቢዘልፏትም መግደል ግን ከቶ አይቻላቸውምና ብየ ሌሊት ከአልጋየ ተነስቼ ለማስታወሻ የምትሆን ወያኔ ወደ አገር በገባ 6 ወይንም 7 አመቱ ለሕትምት ሳትገባ ይዣት የነበረች በኋላ ስድቡ ሲበዛብኝ ለሕትመት ልክያት ብዙ ሰው ያነበባት ሆኖም ግን እኔን ዛሬ ላወቃችሁኝ ወንድሞችና እህቶች ይህችን “ሰም እና ወርቅ” በተቀባች ግጥሜ እነሆ እንደገና ላስተዋውቃችሁ።
የዳመናው አገር (ጌታቸው ረዳ)
አንተም ታገስ አንተም ተው ባልኩኝ ቁጥር፤
ይጠሩኛል በነሱ ጎን ለምስክር።
ለሓቅ ስናገር አያምራቸው፤
ይመድቡኛል “ሸዋዊያን-ተጋሩ” ከሚሏቸው፤
ሌላኛውም ካልሄድኩ በመንገዱ፤
ያወርድብኛል የስድብ ንዳዱ።
”የወያኔ የሻዕቢያ” ዘር ይለኛል፤
መድረኩ ሁሉ ይዘጋብኛል፤
የቋንቋ ፍራቻም አገር አጥቅቶታል፤
ትግሬና አማራው ሌላዉም ሌላውም በሩቅ ይተያያል
መዞር አልተቻለም፤መንደር በዘር ታጥሯል።
ንቡም ቢሆን ጨንቆት እምባ ቋጥሯል ዓይኑ፤
አይዞህ እንዳልለው ዓይኔ ብሷል ካይኑ።
በዚህ ናፈቅኩኝ፤
አገር እንዳለው ሰው አገሬን ናፈቅኩኝ፤
ቀና ስል ወደላይ የጭጋግ ጉም ታየኝ፤
ልቤ አስሬ መታ ማመንም አቃተኝ፤
አየሁኝ ዳመና የጥንት የሚመስል፤
ይዞ ያገር ካርታ አብሮ የሰው ስዕል፤
ባተኮርኩኝ ቁጥር ይጠጋኛል፤
ደብዘዝ ይልና አንዳንዴም ይጎላል፤
ልዝነብ! ልዝነብ! ይላል፤
ዘንቦ ላይዘንብ ጠብ! … ጠብ!.... ጠብ!... ጠብ! ይላል፤
ቀዝቃዛም አይደለም ቆዳ ያቃጥላል።
ቆዳየን ለማየት ዞር ብል ላንዳፍታ፤
ተሰወረ ጉሙ ካይኔ በእፍታ።
አሻቅቤ ሰማዩን ብቃኝ በአንክሮ
ሳይታወቀኝ አየሁት መሬት ወርዶ እፊቴ ላይ ተገትሮ፤
የሰዉ እግር በእግረሙቅ ተሸንክሮ።
ብጎነታትለው ልፈታው
እግረሙቁን ልሰብረው
ጮኹብኝ በገደል ማሚቶ ከበቡኝ በግራ ቀኝ መጥተው
አትንካው አሉኝ እኔም መነካካት አልተው።
ነፃ አውጡት ፍቱለት ወይ ልፍታው ብየ በጠየቅኩኝ
ትግሬ ነህ አማራ? አሉኝ ማንን እምስላለሁ? አልኩኝ።
አይመስልም እንዴ ቆዳየ ቆዳችሁ?
ለምን እንዲህ ጠየቃችሁ?
ብየ ጥያቄያቸውን በጥያቄ መለስኩኝ
ማመን ሲያቅተኝ የምለውን ሲጨንቀኝ፤
ገርገጭ ሲል እግረሙቁ ተሰማኝ
በግራ ጎተቱት፤በቀኝ አዋከቡት፤አጋር የለው አማኝ።
አለቀሰ! አብሮት ያለው ካርታም ተላቀሰ
አለቀሰ! አለቀሰ! አለቀሰና እኔኑም ጭምር አስለቀሰ።
ተሰናበተኝ እንደታሰረ ”በጉም” ወጣ ታጅቦ ወደ ሰማይ
አብሮት ጭልጥ አለ ካርታውም አይታይ።
በዝግታ ይጓዛል፤
አንዴ ወደፊት አንዴ ወደ ኋላ
ይዋልላል።
ኮበለለ ኦሮማይ! ሄዷል ስል እንደገና ተሰበሰበ
ይዘንብ እና አብሮት ይወርድ ይሆን ስለው አልዘነበ።
”በጉም” ይጎተታል
አየሁት ደብዛውን እንዴ ይከስላል
አንዴ ይጎላል
ወይ አይሟሟ ወይ አይረጋ፤ ጎልቶ ላይጎላ ባየር፤
ይዋልላል በጉም የደመናው አገር።///-///
ገግጥም
ጌታቸው ረዳ (አሜሪካ)
Ethiopiansemay
www.ethiopiansemay.blogspot.com
No comments:
Post a Comment