ከአባይ ጀርባ ያለው ደባ!
በአገሬ አዲስ
ግንቦት 5 ቀን 2012ዓም(13-05-2020)
አሁን የሚታዬው የአባይን ግድብ ተከትሎ የተነሳው የግብጾች ተቃውሞና ዛቻ በቅርብ
ጊዜ ውስጥ የተጀመረ ሳይሆን ከብዙ ዘመናት በፊት በሰጭና በተቀባይ መካከል የነበረ ግንኙነት ተከትሎ የመጣ ጠብና ስምምነት ያስተናገደ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥታዊ ተቋምና ስርዓት ባለቤት ሆና በከባቢው በሥልጣኔ ቀድማ በነበረችበት በአክሱም ዘመነ መንግሥት ጊዜም ሆነ ከዚያ ወዲህ በርቀትና በቅርበት
ባሉ መንግሥታት ተከብራና ታፍራ
እንደኖረች ታሪክ ይመሰክራል።ከጠንካራው መንግሥታዊ ስርዓት በተጨማሪ ከመሬቱዋ ፈልቆ አገር ሰንጥቆ የሚያልፈው የአባይ ወንዝ ለአሁኑዋ
ሱዳንና ግብጽ የህይወት ገንዳ ከመሆኑ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ የክብርና
የጥቅም መሳሪያ በመሆን አገልግሉዋል።
በተለይም በ13ኛው ክፍለዘመን ግብጾች ክርስቲያኖችን በተዳፈሩበት ጊዜ የኢትዮጵያ
ንጉስ የነበሩት አጼ አምደጽዮን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አለበለዚያ ግን አባይን እንደሚያግዱ አስፈራርተው ክርስቲያኖችን ከጥፋት
አድንዋል።ከዚያም ንጉስ ዳዊት እንዲሁ የክርስቲያኖችን መብት ለማስከበር ጦር ይዞ እስከመዝመት ድረስ አቅደው እንደነበርና የክርስቲያኖችንም
መብት እንዳረጋገጠ ታሪክ ይመሰክራል።
ግብጽ 1570 በኦቶማን ቱርክ ስር ከወደቀችበት ጊዜ ጀምሮ ቱርኮች ለአባይ ውሃ ኪራይ ይክፍሉ እንደነበር የታሪክ ማስረጃ ያሳያል።ቱርኮች
ከባቢውንና የአባይንም ወንዝ ለመቆጣጠር ተደጋጋሚ በቀጥታና በተዘዋዋሪ
መንገድ ወታደራዊና ሃይማኖታዊ ዘመቻ ቢያደርጉም በኢትዮጵያውያን ጀግንነትና ትግል ያሰቡት ሳይሳካላቸው ቀርቱዋል።የግራኝ አህመድ
መነሳትም ከዚሁ ከቱርኮች ዓላማ ጋር የተቆራኘ ነበር።
አውሮፓውያን አፍሪካን በመቀራመት ግብጽ በእንግሊዞች መዳፍ ስር ስትወድቅ በአባይ
ላይ የነበረው የይገባኛል ጥያቄ መልኩን ሳይለውጥ ይበልጥ ትኩረት የተሰጠው የእንግሊዞች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሆነ። እንግሊዞች በከባቢው
ላስፋፉት የጥጥ እርሻ የአባይ ውሃ ዋናው መጋቢ ስለሆነ ያንንም ላለማጣትና በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ብሎም ኢትዮጵያን ለመውረር
በቀጥታና በእጅአዙር ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ እንደ ቱርኮቹ ሳይሳካላቸው ቀርቱዋል።የመቅደላም ውጊያ የዚያው መሰሪ ተንኮል
ተቀጽላ ነበር።ሆኖም ግን ምንም እንኳን ለመውረር ያደረጉት ሙከራ ሁሉ ባይሳካላቸውም በየጊዜው ኢትዮጵያ የምትዳከምበትን ሴራ ከማውጠንጠን
አርፈው አያውቁም።በጎሳ ለመበታተን ያቀዱት መሰሪ ዓላማ ከብዙ ዓመታት በዃላ ከሞላ ጎደል በተሳካ መልኩ በተከሉት የጎሰኞች መርዘኛ
ስርዓት ከሰላሳ ዓመት ወዲህ የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታዋ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሆኑዋል።
ግብጾችም ከእንግሊዞች ቀጥተኛ ቅኝ ግዛት ነጻ ቢሆኑም በዬጊዜው የገዙዋቸውን የቱርክንና
የእንግሊዞችን ኮቴ ተከትለው የአባይን ወንዝ እስከምንጩ ለመቆጣጠር ብዙ ያልተሳኩ ሙከራዎችን አድርገዋል፤አሁንም
እያደረጉ ነው።የአሁኑን ለዬት የሚያደርገው ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑትን አገር በቀል ሃይሎች በመርዳት በባንዳነት ከጎናቸው ለማሰለፍ በመቻላቸውና አገራችን በተገንጣዮችና አስገንጣዮች የጎሳ ቡድኖች መዳፍ ሥር መውደቋን በመተማመን
ነው።
በአባይ ዙሪያ የግብጾች የባለቤትነት ጥያቄና የመያዝ ሙከራ በየዘመናቱ ሳይቀዬር
እስካሁኑ ድረስ የዘለቀ ነው።የግብጾች ዓላማ በምንም መንገድ ቢሆን በሰላምም ሆነ በወረራ የዓባይን ወንዝ መቆጣጠር ነው።ሙዋቹ የግብጽ
መሪ የነበረው አንዋር ሳዳት “የአባይን የውሃ ፍሰት የሚነካ ወይም የሚያዳክም ማንኛውንም እርምጃ ካስፈለገ በጦር ሃይልም ቢሆን
እንቀለብሳለን” በማለት ጣቱን ወደ ኢትዮጵያ ሲቀስር፤አያይዞም “የሶስተኛው ዓለም ጦርነት መነሻው የውሃ ምክንያት ሊሆን ይችላል”
ብሎ ነበር።
እሱም ብቻ ሳይሆን ከሱ በፊት የነበሩት የግብጽ መሪዎች ከዚህ የተለዬ አመለካከትና
ምኞት አልነበራቸውም።
የአባይ ወንዝ ውሃ ብቻ ሳይሆን ለም አፈርንም ወስዶ ስለሚያስረክብ ለሱዳኖችና
ለግብጾች ለሚያካሂዱት ስኬታማ የእርሻ ውጤት ዋና መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የዳቦ ቅርጫትም ተደርጎ ይቆጠራል።ለዚያም ነው ከክርስቶስ
ልደት በፊት በ486-425 ዓ ዓ ይኖር የነበረው የግሪክ ፈላስፋ ሄሮዱትስ “ግብጽ የአባይ ስጦታ ወይም አባይ የፈጠራት አገር ነች”
ሲል የመሰከረው።
እውነት ነው 90% የሆነው ምድሩዋ በረሃማና አሸዋማ ሲሆን ከ60ሚሊዮን በላይ
የሚሆነው ሕዝቡዋ የሚኖረው በአባይ ወንዝ ዳርቻ በለመለመው ና በቀይ ባሕር ዳርቻ ባላት ቀጭንና ጠባብ የወደብ መሬት ላይ ነው።በዓመት
የምታገኘው የዝናም መጠን ቢለካ በአንድ ቀን ውስጥ የኢትዮጵያ የቀንድ ከብቶች ከሚጠጡት ውሃ ቢያንስ እንጂ አይበልጥም።እንደው በደፈናው
ምድረበዳ ነች ማለቱ ይቀላል።ታዲያ ለህይወቱዋ ቋሚ ዋስትናዋ በክረምት ጊዜ 95% ፣በበጋ ጊዜ 86% ውሃ የሚዳርጋት የአባይ ወንዝ
ነው።ለዚያም ነው ለግብጾች አባይ የሞት የሽረት ጥያቄ የሚሆነው።የዘነጉትና የማይቀበሉት ግን ከመሬቱዋ ፈልቆ በሚሄደው የአባይ ወንዝ
ኢትዮጵያ የመጠቀም መብት እንዳላት ለማዬት የሚችል ህሊና እንዳልዳረጋቸው ነው።
ሙሃመድ አሊ (1769-1849)የተባለው መሪ የግብጽ ህልውናና ብልጽግና የሚረጋገጠው
ዓባይ የሚፈልቅበትንና የሚፈስባቸውን የኢትዮጵያ ግዛቶች ወሮ በመያዝ ነው የሚል እምነት ነበረው።ይህንንም በተግባር ለመግለጽ ኢትዮጵያ
የጣና ሃይቅንና አካባቢውን በውድ አሳልፋ እንድትሰጥ ያደረገው ሙከራ ስላልተሳካለት በእብሪት ተነሳስቶ የጦር ሃይሉን በማዝመት በ1820 ሱዳንን በመያዝ መረማመጃ አድርጎ በ1834
የኢትዮጵያ ግዛት የነበረውን ከሰላን፣በ1838 መተማን፣በ1846 ምጽዋን፣በ1869 ኩናማን፣በ1875 ሐረርን ለመያዝ ችላ ነበር።
ከዲፍ ኢስማኤል(1863-1879)የተባለውም ይህንኑ በማጠናከር ተንቀሳቀሰ።ወርነር
ሙዢንገር(1832-1875) የተባለው የስዊስ ተወላጅ የሆነው አማካሪው የሰጠው ምክር “ኢትዮጵያ በተረጋጋና ስነሥርዓት ባለው አስተዳደር
ስለምትመራ፣ጠንካራ ወታደራዊ አቋምና ከአውሮፓውያን ሃይሎችም ጋር የቆዬ ግንኙነት ስላላት ለግብጽ አደገኛ ነች፤ለግብጽ ያላት ዕድል
ከተቻለ ኢትዮጵያን በሃይል አንበርክኮ ይዞ እስላማዊ አገር ማድረግ፣ካልሆነም ቀውስና ችግር ውስጥ እንድትገባ የሚያደርግ ተግባር
ማከናወን የተሻለ አማራጭ ነው”የሚል ነበር። የመጀመሪያውን ምክር ተቀብሎ ካዲፍ ኢስማኤል በ1875 እና በ1876 ባደረገው የወረራ
ሙከራ በጉንደት 2500፣በጉራ 12000 ወታደሮቹን አጥቶ ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ።የሚገርመው ነገር ግብጾች
ያሰለፉት ያገራቸውን ዜጋ ብቻ ሳይሆን ቅጥረኛ የአውሮፓ ወታደሮችንም
ጭምር ነበር።ግን ሁሉም የጦር ሜዳ እራት ሆነው ቀሩ።ከመካከላቸው
አንድ እንኳ መርዶ ነጋሪ አልተረፈም።አማካሪው ሙዚንገር ሳይቀር በስሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ወታደራዊ የስለላ ሥራ ላይ ተሰማርቶ በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን የአፋር ተወላጆች
በወሰዱት እርምጃ አገሩ ሳይመለስ እስከወዲያኛው አሸልቦ ቀረ።
የግብጾች መረን የለቀቀ ተስፋፊነትና ፍላጎት በዓባይ ወንዝ ብቻ ላይ የተወሰነ
ሳይሆን መላ የቀይ ባህርን የአረብ ሃይቅ ለማድረግ ጭምር ነው።ከእንግሊዞች
ቅኝ ግዛትነት ሥር ከወጣች በዃላ በሥልጣን ላይ የተቀመጡት መሪዎች፣ገማል አብደል ናስር፣አንዋር ሳዳት፣ሁስኒ ሙባረክና የአሁኑም
አል ሲሲ የሚከተሉት መስመር ከ150 ዓመት በፊት የከዲር ኢስማኢል አማካሪ የነበረው የስዊስ ተወላጁ ሙዢንገር ከአቀረበው ሃሳብ
የመነጨ ነው።
የአገር አነሳስ፣እድገትና ውድቀት የነበረና እስከአሁንም ድረስ የዘለቀ እውነታ
ነው።ኢትዮጵያም በነዚህ ሂደቶች ውስጥ አልፋለች።ከፍ ብላ ከነበረችበት
የእድገትና የሥልጣኔ ማማ ቀስ በቀስ እዬወረደች አሁን ህልውናዋ ጥያቄ ውስጥ ከገባበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅታለች።
ለእድገቱዋ ምክንያት እንዳለው ሁሉ ለውድቀቱዋም እንዲሁ ምክንያት አለው።ለእድገትዋ
ምክንያት የሆነው ቆራጥና አገር ወዳድ፣ጥቅሙዋን አሳልፈው የማይሰጡ፣ታታሪና ጀግና ፣ሕዝቡን ከጎናቸው ሊያሰልፉ የቻሉ መሪዎች በነበሩዋት
ወቅት ሲሆን፤ ለውድቀቱዋም ደግሞ የዚያ ተቃራኒ የሆኑ፣ ብሔራዊ ስሜት የሌላቸው፣ ለባዕዳን ጥቅም የቆሙ ቅጥረኞች፣ ሥልጣኑን በጉልበት
በመያዝና የሕዝቡን አገራዊ ስሜት በጎሳ ተዋረድ በመሰባበር ለድህነት፣ለተስፋ መቁረጥና በራስ ላለመተማመን፣ለስደትና ለእርስ በርስ
ግጭት የዳረጉ ወሮበሎች የሥልጣኑ ባለቤት የሆኑበት የአሁኑ ወቅት ነው።
ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑት አገሮች በተለይም ግብጽና የአረቡ ዓለም ጸረ አንድነት የሆኑትን የሻእብያን፣የወያኔንና የኦነግን ታጣቂ ቡድኖች በማሰልጠንና ወታደራዊ፣ኤኮኖሚካዊና
ፖለቲካዊ ድጋፍ በመስጠት ኤርትራ እንድትገነጠልና ኢትዮጵያ ወደብ አልባ እንድትሆን ሲያደርጉ ለዚያ መሣሪያ የሆኑዋቸውን ወያኔና
ኦነግ የተባሉትን ለሥልጣን እንዲበቁ አድርገዋቸዋል።
በጎረቤት አገርም በኩል ተመሳሳይ ፈተና እንዲገጥማት ሶማሊያን አስታጥቀውና ከጎኑዋ
ተሰልፈው ጦርነት እንድትከፍትባት ማድረጋቸው የትናንትና ትዝታ ነው።የሶማሊያ መሰባበር አዳከመው እንጂ ዛሬም ቢሆን በተገኘው አጋጣሚ
ሁሉ ተመሳሳይ ትንኮሳ አልቀረም፤ለወደፊቱም የሚቀር አይመስልም።
አገር(መሬት)ሲያረጅ ጃርት ይፈላበታል እንዲሉ፣ የረጅም ጊዜ የነጻነት ታሪክ የነበራት፣ለሌሎች
አገሮች ነጻነት ምልክትና ምሳሌ የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ ታሪክ ሠሪ ሳይሆኑ ታሪክ አፍራሽ በሆኑ አገር በቀል ከሃዲዎች
መዳፍ ሥር ወድቃ ሲያከብሩን የነበሩ ደቃቃ አገሮች ሳይቀሩ እንዲንቁን ከዚያም አልፈው እያስፈራሩ የፈለጉትን ለማድረግ እንዲችሉ
ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።በእርዳታና በብድር ስም በቀላሉና በቀጥታ ሰርገው ለሚገቡበት በር ተከፍቶላቸዋል። የአገራችን አንጡራ ሃብት
እዬተቸበቸበ ለግልና ለቡድን ጥቅም መዋሉ የተለመደ ሆኑዋል።ያለፉት 30 ዓመታት አገራችንም ሕዝባችንም ታግተው የኖሩበት ስርዓት
የሰፈነበት ጊዜ ነው ቢባል ከውነት መራቅ አይሆንም።።
በሥልጣን ላይ ያሉት
የሚነዙት የማጭበርበሪያ ወሬና ፕሮፓጋንዳ የሚሠሩት ግንባታዎች ሁሉ ለሕዝብ ኑሮ መሻሻልና ለአገር እድገት እንደሆነ ተደርጎ ነው።ሃቁ
ግን ነገ ገንጥዬ የምይዘውን መሬት ዛሬ በኢትዮጵያ ስም በሚገባ ብድርና
እርዳታ ልገንባ የሚል ውድድር ይመስላል።ዘመናዊና ትልልቅ ሆቴልና መዝናኛ ቦታ ቢከፈት፣የእርሻና የፋብሪካ ተቋም ቢዘረጋ ለባለሥልጣኖቹና ለተባባሪዎቻቸው ጥቅም የሚውል፣ብሔራዊ ኤኮኖሚ የሚገነባና የሚያሳድግ
ሳይሆን ለውጭ ባለሃብቶች(አገሮች)ፈርጥጦ ከአገር ለሚወጣ ካፒታል ምንጭ ከመሆን አያልፍም።የከተማ ዕድገት ተብዬውም ዕቅድ ከተማዎችን
በተለይም አዲስ አበባን የባለጌ ሃብታሞችና የውጭ ዜጎች መዝናኛና ቅጥ ያጣ የወሲብና የሌሎችም ጎጂ ባህሎች መናኸሪያ አደረጋት እንጂ
በሕዝቡ ኑሮ ላይ መልካም ለውጥ አላመጣም።ያመጣው ለውጥ ቢኖር በኑሮ ውድነት የሚቀጣ፣በመፈናቀል ቤት አልባ የሚያደርግ፣ ወጣቱን ትውልድ
ሥራፈት አድርጎ በጎጂ ባህል፣ በሴት አዳሪነትና በግብረሰዶም ተላላፊ በሽታዎች፣ልማድና ሱስ መበከሉ ነው።የተገኘው ውጤት ለገንዘብ ሲባል ሰብአዊነት፣ብሔራዊ ስሜት፣ኢትዮጵያዊ ባሕልና ስነምግባር
እዬተረሳ መሄዱ ነው።ለጥቅም ሌላውን ቀርቶ እራስን አሳልፎ የመሸጥ ባህል እንደ ሥልጣኔ መቆጠሩ ነው።ከሰውነት ይልቅ የአውሬነት
ጸባይ እዬተስፋፋ መሄዱ ነው።
ወደ ጽሁፉ እርእስ ከሆነው የአባይ ወንዝና የግድብ ሥራ ስንመለስ
አባይን የመገደብ ፍላጎት አሁን በቅርቡ በወያኔ ዘመነ-መንግሥት የታሰበ ሳይሆን
በቀድሞ ጊዜ በነበሩት መሪዎች የታሰበና የታቀደ ነበር።የሩቁን ትተን የቅርቡን የአጼ ሃይለሥላሴን መንግሥት ጥረትና ፍላጎት ብንመለከት
ብዙ እቅዶች ተነድፈው እንደነበሩ እንረዳለን።
1-በጣና ሃይቅ ላይ ግድብ ለመሥራት በ1927 ዓም ከአሜሪካኑ J.G.White
Engineering Corporation of New York ከተባለው ኩባንያ ጋር በ20 ሚሊዮን ዶላር ግድብ ለማሠራት ታቅዶ ነበር።
2-ሌላው U.S.Bureau Of Reclamation ከተባለው ድርጅት ጋር በ1956-1964 በተደረገው ስምምነት አራት ግዙፍ ግድቦችን መሥራት እንደሚቻል ጥናቱን አቅርቦ
ነበር።
3- በ1962 ላህሜይር የተባለው የጀርመኖች ግንባታ ድርጅት በግልገል አባይ ዙሪያ
ጥናቱን ጨርሶ አቅርቦ ነበር።
እነዚህ ሁሉ እቅዶች ተግባራዊ ቢሆኑ ኖሮ ኢትዮጵያ አገራችን ሱዳንና ግብጽ በጥምረት
አሁን ካላቸው የኤሌክትሪክ፣የመስኖና የልዩ ልዩ ኢንዱስትሪ አቅም የበለጠ ይኖራት ነበር።ይህ በአሃዝ ሲገለጽ 172 ቢሊዮን ኪሎዋት የኤሌክትሪክ፣35 የልዩ ልዩ ተግባራት ፕሮጀክቶች፣16
እረጃጅምና ሰፊ የመስኖ መስመሮች፣440 ሽህ ሄክታር መሬት በማልማት
4- ሚሊዮን የአርሶ አደር ቤተሰቦች ሊሰፍሩ ይችሉ ነበር።ይህ
በተጨማሪ 12 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ሳይጨምር ነው።
በጥናቱ የተረጋገጠው ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያ እነዚህን እቅዶች ብታጠናቅቅ በሱዳንና
በግብጽ ላይ ምንም አይነት ጫናና ችግር እንደማይፈጥር ሲሆን እንደውም ተጠቃሚዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው። ያም ሆነ ይህ ዕቅዶቹ በተወሳሰበ ችግርና በተቀነባበረ ዓለም አቀፍ ሴራ በተግባር
ሳይተረጎሙ ቀርተዋል።
ቀዳማዊ ሃይለሥላሴ በአባይ ውሃ ላይ የመጀመሪያውን የግድብ መሠረት በአውሮፓውያኑ
ዘመን አቆጣጠር በ1945 በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1937 ዓም ያስቀመጡ ከመሆናቸውም በላይ በግንባታው ዙሪያ አገራችን የገጠማትንና ሊገጥማት የሚችለውን ችግር በመገንዘብ የወደፊቱ ትውልድ በገዛ ጉልበቱና ገንዘቡ በተግባር እንደሚገልጸው
ያላቸውን እምነት ከዚህ በታች የቀረበው የታሪክ ማስረጃ እንደሚያሳዬው ትንቢታዊ መልእክት አስተላልፈው ነበር።
አሁን በመካሄድ ላይ ያለው የአባይ ግድብ ግንባታ ብዙ መልስ ያላገኙ ጥያቄዎችን
የሚጭር ቢሆንም፤ መለስ ዜናዊ ቅጽበታዊ ውሳኔ በማድረግ ሥራው እንዲጀመር ማድረጉ ከዓላማው በስከጀርባ ያለውን ትተን ሊመሰገን ይገባዋል።ለከይሲ
ዓላማው የወጠነው የባይን የመገደብ ፍላጎት አሁን ላይ ላልጠበቀው ለሕዝቡ ብሔራዊ ስሜት ማብሰሪያና የአንድነቱ መግለጫ ሆንዋል።ፈረንጆች
A Blessing in Disguise በአማርኛ ቋንቋችን ከሞላ ጎደል ስውር ምህረት እንዲሉ። ከግንባታው ጀርባ መኖሩ
የሚታመንበት ጥርጣሬ በቦታው አመራረጥ ተከትሎ፣በመለስ ዜናዊ ድርጅት የፖለቲካ አቅጣጫ አንጻር ሊከሰት የሚችለውን ሂደት በመንተራስ
የሚሰነዘረው ስጋት ነው።ይኸውም ኢትዮጵያን በጎሳ የመከፋፈሉን እቅድ ተከትሎ ትግራይ ከኤርትራ ጋር ሆና ትልቅ አገር የመመስረቱ ዓላማ እንዲሳካና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት የማድረጉ
ፍላጎት የአባይን ውሃ ከሚመነጭበት ከአማራው መሬት አርቆ የትግራይ ክልል በቀላሉ ሊቆጣጠረው ብሎም ፌዴሬሽን በሚል ማጭበርበር ሊጠቀልለው
የሚችል አዲስና ደካማ የቤኒሻንጉል የተባለ ክልል ፈጥሮ ግድቡ እንዲሠራ ማድረግ የሚል ድብቅ የመሰሪ ፖለቲካ ጥንስስ እንደሆነ ውጥኑ በጉልህ ያሳያል።ይህ እቅድ ለወደፊቱ ይሆናል አይሆንም የሚለው
ስጋት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ምክንያቱም አሁን የተንሰራፋው ጎሰኝነትና
የጎሳ ፖለቲካው እስካልተወገደ ድረስ የአገራችን ህልውናና አንድነት
አደጋ ውስጥ መግባቱ ስለማይቀር ነው።ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ካለው ብሔራዊ ስሜትና ፍላጎት አንጻር የእኔ ነው ባይነት ኩራት
አድሮበት ለግንባታው የሚችለውን ሁሉ አበርክቱዋል፣ለማበርከትም ዝግጁ ነው።ምንም እንኳን በግንባታው ዙሪያ የወያኔ ዘራፊዎች ያባከኑት ገንዘብ መጠን ዬት እዬለሌ ቢሆንም ፣አሁንም ሕዝቡ ተስፋ
ሳይቆርጥና ሳይሰለች የግድቡን ሥራ ለማጠናቀቅ በሚያስችለው ሁሉ ለመሳተፍ ቁርጠኛነቱ አልቀዘቀዘም።ስሜቱ የሚነካው ግድቡ ተጠናቆ
የሚሰጠው ጥቅም ሲታወቅ ይሆናል።
የዓባይንም ሆነ የሌሎቹን ብሔራዊ አንጡራ ሓብቶች ለሕዝቡ ጥቅም እንዲውሉ ማድረግ
የሚቻለው እውነተኛ አገር ወዳድና፣ጎሰኝነትን የሚቃወም፣የክልልን ጎሰኛ አስተዳደር የሚንድ፣አሁን ከገባንበት መቀመቅ ሊያወጣን የሚችል፣
ሕዝብ የመረጠው ኢትዮጵያዊ መንግሥት ሲኖር ብቻ ነው።
ግብጽ በአባይ ውሃ ተፋሰስ ላይ አሁን ሳይሆን ቀደም ያለ የይገባኛል ጥያቄ እንዳነሳች
ቀደም ሲል በተገለጸው የታሪክ ማስረጃ አይተናል ። የበረገገላት የለም እንጂ አካኪ ዘራፍ ስትል ኖራለች።አሁን ላይ ግን በኢትዮጵያ
የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋትና ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ያለው የጎሰኞች ቡድን የመንግሥቱን እርከን በተቆጣጠረበት ወቅት አመቺ ሆኖ
ስላገኘችው በአባይ ወንዝ ና በግድቡ ሥራ ላይ እንቅፋት በመፍጠር ተባባሪዎችዋን አሰልፋ በመንቀሳቀስ ላይ ነች።
ለግብጽ ግትርና ለጸረ አባይ ግድብ አቋም ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።
1- እያደገ የመጣው ሕዝቡዋ ሕይወቱና የኑሮ ደረጃው በአባይ ላይ የተንጠለጠለ ስለሆነ ያንን በዘላቂ ባለቤትነት
ማረጋገጥ ለህልውናዋ ዋስትና በመሆኑ፣
2- ለሳውዲ ዓረቢያና ለኢሚራት አገሮች ሰፊ የእርሻ መሬት ስለሸጠች የአባይ ውሃን
መቆጣጠር የሁሉም አረቦች የጋራ ጥቅም በመሆኑና ካለአባይ ውሃ ያሰቡት ሰፊ የእርሻ ሥራ መከናወን ስለማይችል፣
3 ከአባይ የሚፈሰውን ውሃ አቅጣጫውን ቀይረው ለሳይናይ በረሃማ መሬት የልማት
እንቅስቃሴ እያዋሉ በመሆናቸው እጥረት በመከሰቱ፣
4 -ጥንታዊ ካይሮ ከተማ ልትሸከም የምትችለው የሕዝብ ብዛት ጥግ ላይ ስለደረሰ፣የዘመኑም
መሰረታዊ ተቋማት ለመዘርጋት አስቸጋሪ በመሆኑ ሌላ ከተማ የመገንባት ላይ በመሆናቸው ለዚሁ አዲስ ከተማ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል መስመርና ፣የቱሪዝም እንቅስቃሴዎችን ለመዘርጋት
አባይ ከፍተኛና ወሳኝ ድርሻ ስለሚኖረው።
የአባይን ግድብ ቢቻል ለማደናቀፍ አለያም በመቆጣጠር የተመናመነ ጥቅም ለኢትዮጵያ
እንዲሰጥ ተደርጎ የአንበሳውን ድርሻ ለመውሰድ የሚከተሉትን ስልቶች ነድፋለች።
1 ኢትዮጵያ ያወጣችውን የአባይ ግድብ አሞላል መመሪያ የጊዜ ገደቡን እንድታራዝም
በሚል ሰበብ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣በአረብ አገሮች የጋራ ማህበር፣በአሜሪካና በተከታዮችዋ በኩል የፖለቲካ፣የዲፕሎማሲና የገንዘብ
ተአቅቦና ጫና ማድረግና የማስፈራራት ዛቻ በመርጨት፣
2- የውሃ ሙሊቱን
ለመቀነስ የቀረበውን ሃሳብ ኢትዮጵያ እንድትቀበልና ለምታደርገው ትብብር የገንዘብ ድጎማ እንድታገኝ የሚል የሽምግልና ሃሳብ የያዙ
የአውሮፓ አገሮች በጉዳዩ እንዲገቡበት ማድረግ።ይህንን ሃሳብ የነደፉበት ምክንያት በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ለገንዘብ ፍቅር ያለውን
ደካማ ጎን ስለሚያውቁና አሳልፎ የሰጣቸውን የአገር ሃብቶችንና ንብረቶች በማዬት ይህም ይሳካል የሚል እምነት ስላደረባቸው ነው።
እዚህ ላይ በሁለቱም በኩል ኢትዮጵያ የምታጣው ነገር ቢኖር በገንዘብ የማይተመነውን
ልዑላዊነትዋን ነው።በተራዘመም ኪሳራ ኢትዮጵያ የአባይ ባለቤትነትዋን ብቻ ሳይሆን ነጻነትዋን ያጣች፣እንደ አገር ሳይሆን የተከፋፈለች
ጎሰኞች የሚያዙባት መንደር፣በግጭትና በጦርነት የምትታመስ፣ለሰርጎ ገብ የውጭ ሃገር ወራሪዎች ወደሌሎቹ ያፍሪካ አገሮች መረማመጃ
የሆነች ባለቤት አልባ መሬት ትሆናለች።
አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀነባበረው የግብጽን ፍላጎት ለማስከበር የተሰለፈው
ሃይል አሜሪካኖችንና አውሮፓውያኑን ጨምሮ፣ የአረብ አገሮችን፣የቅርብ አገሮች ሱዳንንና ጅቡቲን ሳይቀር ያሰለፈ ነው።የሌሎቹም የአፍሪካና
ጎረቤት አገሮች አቋም ግልጽ አይደለም፤እንደ ሌሎቹ በዶላርና በፖለቲካ ሥልጣን ድጋፍ በኢትዮጵያ ላይ ላለመነሳታቸው ዋስትና የለም።ሌሎቹ
መገንዘብ ያለባቸው ጉዳይ ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ የተመዘዘው የቅኝ አገዛዝ ሰይፍ ነገ በነሱም ላይ ሊሰነዘር እንደሚችል ነው። ኢትዮጵያ
ለዚያ የሙከራ ቤት መሆኑዋ ሊታወቅ ይገባል።
የእስልምና ሃይማኖትንም ተገን አድርገው የሚረጩት ፕሮፓጋንዳ የሙስሊሙን መብት
ለማስከበር ሳይሆን የአገሩን ጉዳይ እንዳይመለከትና ከቀረው ወገኑ ጎን እንዳይሰለፍ ለማድረግ ነው።ለእስላም ማህበረሰብ የሚያስቡ
ቢሆንማ ኖሮ የአገራቸውን ሙስሊም መብት ባከበሩና በዬጊዜው ደሙን
ባላፈሰሱ ነበር።
ዱሮም ሆነ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመካከሉ የጎሳና የሃይማኖት ልዩነት ሳይለያዬው ብቻውን ሆኖ ነው የመጣበትን ጠላትና አደጋ የተቋቋመውና
በአሸናፊነት የዘለቀው፤አሁንም ሆነ ወደፊትም ቢሆን ብቻውን ክብርና ነጻነቱን አስከብሮ ይኖራል።
ኢትዮጵያ ሱዳንም ሆነች ግብጽ በአገራቸው መሬት ላይ በሚፈሰው የውሃ ሃብት ያሻቸውን
ሲያደርጉ ተቃውማ አታውቅም፤እሱዋም ተመሳሳይ መብትዋ እንዲከበርላት ትፈልጋለች። ለምሳሌም ሱዳን
1 በላይኛው አትባራ ሰቲት፣
2 ካሸሞ አል ጊርባ፣
3 ጀበል አውሊያ፣
4 መሮዌ የሚባሉ የሃይል ማመንጫና የመስኖ ግድቦችን ሰርታ ስትጠቀም ኢትዮጵያ
ጣልቃ አልገባችም።ግብጽም ቢሆን የውሃ መጠኔ ይቀንሳል ብላ በሱዳን ላይ የከረረ አቋም ይዛ አካኪ ዘራፍ አላለችም ወይም አሁን በኢትዮጵያ
ላይ እንደሰነዘረችው ዛቻና ዓለም አቀፍ ጫና አልፈጠረችም።
በግብጽም በኩል
1 ዝቅተኛ አስዋንና ከፍተኛ አስዋን
2 ኤዝና(ኤስና)፣
3አዲሱ ሻማ ሃማዲ፣
4 አዲሱ አሱዊት ባራጌ የተባሉትን ግድቦች ስትገነባ የተቃወማት አልነበረም።አሁንም
የቀይ ባህርን በሚያመነምን ደረጃ ውሃ በመቋጠር 15 ኪሎሜትር ስፋት የሚሸፍን ውሃ በትነት እንዲባክን የሚያደርግ “ የናስር ሃይቅ
” የሚል ሰው ሰራሽ ሃይቅ ስራዎችን ስታከናውን ለምን ያላት አገር
የለም።
ኢትዮጵያ ላይ ሲሆን ግን ሁሉም ተረባረቡባት።ለምን ቢባል ነገሩ ከአባይ በላይ
ነው።የነጻነት ተምሳሌት የሆነች፣ቅኝ ገዥዎችን ያንበረከከች አገር በመሆንዋ ነው።ለዚያ ሂሳብ ማወራረጃው ከአሁኑ ጊዜ ያመቼ የለም
ብለው ያምናሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ አንድነቱን አጠናክሮ ቀድሞ ሊወሩትና መብቱን
ሊገፉት መጥተው የነበሩትን ጠላቶቹን አሳፍሮ እንደመለሳቸው ሁሉ የዘመኑንም ጠላቶቹን እንዲሁ ማንበርከክ ይኖርበታል።
አባይና አገር ዘመን ተሻጋሪዎች ናቸው፣ትውልድ እየተቀባበለ የሚያሻግራቸው የጋራ
ንብረቶች እንጂ የአንድ መንግሥት ይዞታዎች አይደሉም።መንግሥት ይወጣል ይወርዳል ሕዝብና አገር ግን እዬተወራረሱ ይቀጥላሉ።
ምንም እንኳን በሥልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ዴሞክራሲያዊ ባይሆንም፣ አገራችንን
ለዚህ አይነቱ ምስቅልቅል ሁኔታና ለግብጾች ድንፋታ አጋልጦ የሰጠንን ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ የጎሰኞች የፖለቲካ መስመር የሚያራምድ ቢሆንም፣ የአባይንና የአገራችንን ልዑላዊነት ጥያቄ ከመንግሥት
ጥያቄ ጋር ማስተሳሰር አይኖርብንም።አጀማመሩና ውጤቱ ላይ ጥያቄና ጥርጣሬ ቢኖረንም ሕዝብ አምኖበት ፣ሃብትና ጉልበቱን ብሎም ሕይወቱን
የገበረበትን የአባይ ግድብ ግንባታ ማስፈጸም ይኖርብናል።
በራስ መተማመን መርሆ የማንንም የውጭ ሃይል ጣልቃ ሳናስገባ በራሳችን አባይ ላይ
ለመወሰን መብትና አቅም እንዳለን ማሳዬት ይኖርብናል።ግብጽና አበሮቹዋ በመጡበት መንገድ ለመመለስ እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንቆምበት
ጊዜው አሁን ነው።ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባበታል እንዲሉ ክፍተት እንዲኖር መፍቀድ የለብንም።
በክልል የተዋቀረችው ኢትዮጵያ ስትፈርስ በክልሌ ያለውን ሃብትና ንብረት እንደ
ኤርትራው ሻብያ ነጥቄ አስቀራለሁ የሚል ህልም ያላቸውን ጸረ አንድነትና ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑ አገር በቀል ቡድኖች ምኞታቸው እንዳይሳካ
ማድረግ ከአባይ ጎን ከምናደርገው ትግል ተነጥሎ መታዬት የለበትም።
በሌላውም በኩል አገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ
ነቅቶ መጠበቅ የሚኖርበት ጉዳይ ከግብጽና ሱዳን ጋር የሚደረገው
ውል መብቱን እንዳያሳጣው መከታተል ይሆናል።የኢትዮጵያ ሕዝብ የተከሰተው ችግር በሰላማዊና ፍትሓዊ በሆነ መንገድ ቢፈታ ፈቃደኛ ነው።የኢትዮጵያ
ሕዝብ በሌሎች አገሮች ሕዝቦች ጉዳትና ኪሳራ ላይ መበልጸግን አይሻም።ይህ ሰላምና ፍትሕ መውደዱ እንደፍርሃት ከተቆጠረበትና ነጻነቱን
የሚገፈው ከሆነ ግን እጁን ሰጥቶ አይቀመጥም። ከመፈረሙም በፊት ሕዝባዊ ውይይት እንዲደረግበትና ውሳኔ እንዲሰጥበት ማድረግ ይገባል።ለመሪዎቹና
ለተደራዳሪዎቹ ብሎም ለውጭ ሃይሎች ውሳኔ አሳልፎ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልሆነ ጠንቅቆ ማወቅ ተገቢ ነው።ዛሬ በአጎብዳጅነት
የሚፈጸም ስህተት ነገ በታሪክና ትውልድም እንደሚያስጠይቅ ማወቅ ይገባል።
ከመቼውም በበለጠ አንድነቱን አጠንክሮ በጎሳ፣በቋንቋና በሃይማኖት ሊለያዩት የሚሞክሩትን አገር በቀል ከሃዲዎችን በማሶገድ የአባይ ወንዝና ውሃ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያ ዳርድንበርና የተፈጥሮ ሃብት ባለቤትነቱን ማረጋገጥ የአሁኑ
ትውልድ ታሪካዊ አደራ ነው።
ተፎካካሪ ነን ብለው ለሥልጣን ቅርጫ የተሰለፉት የፖለቲካ ድርጅቶች ለዚህ አገራዊ
ጥያቄ ቅድሚያና ትኩረት ሊሰጡት ይገባል።ይህ ማንነታቸው የሚታወቅበት ትልቅ ፈተና ነው።
ኢትዮጵያ በነጻነትና በአንድነት ለዘለዓለም ትኑር!
አባይን በገንዘባችን ብቻ ሳይሆን ካስፈለገ በአጥንታችን እንገነባለን!!
አገሬ አዲስ
ለዚህ ጽሑፍ መጋቢ አድርጌ የተጠቀምኩት
በፕሮፌሰር ዳንኤል ክንዴ የቀረበውን ጥናት ሲሆን ጽሑፉን በሚከተለው አመላካች
ሊያገኙ ይችላሉ።ጽሁፉ ብዙ ጠቃሚ ታሪካዊ ማስረጃዎችን ያካተተ ነው።ጥቂቶቹን የጠቃቀስኩት የአንባቢን ጊዜ ላለመጋራትና ላለማሰልቸት
በማለት ነው።እውቀት የሚሻ ሰው ግን ሳይሰለች ጊዜውን ወስዶ እንደሚመለከተው እተማመናለሁ።
በዚህ አጋጣሚ ፕሮፌሰር ዳንኤል ክንዴን ላመሰግን እወዳለሁ። ዕድሜና ጤና እንዳይለያቸውም
ምኞቴ ነው።
Egypt and the Hydro-Politics of the Blue Nile River
Daniel
Kendie
Henderson State University
No comments:
Post a Comment