Tuesday, February 23, 2010

የተሳሳተዉ የኤርትራ የራስ ምስል እብጠት ያስከተለዉ መዘዝ

የተሳሳተዉ የኤርትራ የራስ ምስል እብጠት ያስከተለዉ መዘዝ ጌታቸዉ ረዳ www.Ethiopiansemay.blogspot.com ባለፈዉ ምርጫ የተለያዩ ተቃዋሚ ድረጅቶች “ቅንጅት” ብለዉ የጋራ ጥምረት በማቀናጀት በሕዝብ ድምፅ ተደግፈዉ በሥልጣን ላይ ያለዉ የወያኔን ቡድን ያርበደበዱትን ያህል በዉስጣቸዉ በተነሳዉ አለመረዳዳት ወደ ተለያዩ ድርጅቶች ተበትነዉ ካየናቸዉ በሗላ አብሮ የተከተለ ሌላ ክስተት ደግሞ በእዛዉ ድርጅት ዉስጥ ተካትተዉ የነበሩ ደጋፊዎች እና አባል ግለሰቦች ፊታቸዉን ወደ ኤርትራዉ ሻዕቢያ በማዞር የሻዕቢያ አፈቀላጤዎች በመሆን የራሱ ሕዝብ እና የዓለም መንግሥታት ያወገዘዉ የኤርትራዉ ኢሳያስ አፈወርቅ “የአመቱ ሰዉ”በማለት እያጋነኑ ያላቸዉን አድናቆት እና ፍቅር ወደ መግለጽ የተሸጋገሩበት ክስተት ታዝበናል። ወያኔን ለማስወገድ ከሰይጣንም ቢሆን እርዳታና ምክር እንሻለን በማለት፤ ዓለም ካወገዘዉ ጋኔል ጋር ከመወዳጀታቸዉ አልፈዉ፤ ሰሞኑን ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት በኤርትራዉ ጋኔል ላይ እና ለሱ ባጎበደዱ ባለሥልጣኖች ላይ ያስተላለፈዉ ባለ ብዙ ፈርጅ ማዕቀብ በመቃወም ለኢሳያስ አፈወርቅ እና በዙርያዉ ላሉት አገልጋዬች ድጋፍ ሰላማዊ ሠልፍ እንዉጣ በማለት አንዳንድ ኢትዬጵያዊያን ሰለማዊ ሰልፍ ከሚያደርጉት ኤርትራዊያን የሻዕቢያ አማኞች ጋር በመሆን በድጋፍ እንዉጣ በማለት ያስተላለፉትን ጥሪ እዉን በማድረግ ከሻዕቢያዊያን ጋር አንድነታቸዉንና ድጋፋቸዉን አሳይተዋል። ይኸም ብዙዎቹን አስደምሟል። በ18 ዓመታት ዉስጥ ካስደመሙን የጥቂት ሰዎች ልክስክስነት የባሕሪ ክስተቶች ዉስጥ ይሄኛዉ ቀዳሚ መስመር የሚይዝ አሳፋሪ ክስተት ነዉ የሚል እምነትም አለኝ። ኢትዬጵያ ሁሉም በየሚናዉ እወዳታለሁ፤ለኔም አገሬ ናትና ያሻኝን መንገድ በመከተል ማአከላዊ ጠላትዋን ለማስወገድ በሚመቸኝ፤በመሰለኝ የትግል ስልት ተጠቅሜ ነፃ አወጣታለሁ የሙሉ አልታጡም /ብዛትም አላቸዉ። ወያኔም እኔም ዜጋ ነኝ እና ስለ ኢትዬጵያ እቆሮቆራለሁ ማለቱን አልቀረም፤ አብረዉ ከሱ እኩል የሱን ያህል ወይንም የባሰ ጸረ ኢትዬጵያ ከሆኑ ክፍሎች ጋራ አብረዉ ኢትዬጵያን ያመሳት የወያኔን ቡድን በመወዳጀት ኢትዬጵያን በመሰላቸዉ ራዕይ ለመዉሰድ ስልታቸዉን እየቀየሱ ነዉ። ነግር ግን ሙሶሎኒን ለመጣል ከሂትለር ጋር መወገን ማለት የሁለቱም ሰዎች ድርጅቶች ባሕሪ እና ዓላማ አለማወቅ አልያም ሆን ብሎ ዓላማቸዉን ለማካሄድ የተደረገ ዉሰጠ ሴራ ነዉ የሚል ድምዳሜ መድረስ ያስችላል።አገር መዉደድ ማለት ከለየላቸዉ ኢትዬጵያን “ከሚጠሉ” ቡድኖች እና መሪዎች ጋር መጎዳኘት አይደልም፤ ይልቁንም ከሃዲነት ነዉ።ወዳጅ የሚሏቸዉ እና ዓለም ሲያወግዛቸዉ ከተወገዙት ጋር አብረዉ የሚያለቅሱ ቡቡ ሆዶች እንድያዉቁት የምንሻዉ የሚወገዙት ክፍሎች ለእኛ ጠላቶች ናቸዉ። የኢትዬጵያ ጠላቶች ብዙዎች ናቸዉ። በተለይም ሻዕቢያ በኢትዬጵያ ጠላትነቱ የምስክር ወረቀት የያዘ በኢትዬጵያ ልብ ሕዝብ በጠላትነት የተመዘገበ ጠላታችን ነዉ። ብዙ በደል እና ጉዳት አድርሶብናል። የሻዕቢያን ጠላትነት መዘርዘሩ ነግቶ የሚያመስ በመሆኑ ያስከተለብን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ያወረደብነ ጥቃትና የልብ ሐዘን ስናስታዉስ አገሪቱን በከፋ መልኩ ለብርቱ ጥቃት ያጋለጧት ቡድኖች የገዛ ራሷ ዜጎች እንደሆኑ በተደጋጋሚ በታሪክ የታየ ነዉ።ከዓረቦች፤ትርኮች፤ጣሊያኖች፤እንግሊዞች አሜሪካኖች፤ሩሲያኖች ወዘተ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በመመሳጠር እና በመዋዋል ዉስጠ ሥራ እየሰሩ አገሪቷ ለቅኝ ግዛት እና ለእጅ አዙር ምዝበራ ያገለጧት ማን ነዉ ብለን ብንጠይቅ የኛዎቹ ኢትዬጵያዉያን ተብየዎች ናቸዉ።ይህ የባንዳነት በሽታ ከልጅ ልጅ እየተላለፈ ከትዉልድ ወደ ትዉልድ እየተላለፈ ወደ እኛዉ ወርዶ ዛሬ የምናየዉ የዘመናችን አሳፋሪ የባንዳነት ባሕሪ የቆየ የጥንት በሽታችን ክፉ ልክፍት ነዉ።ሰሞኑን ኤርትራን ብቻ ሳይሆን ኢትዬጵያን እና ጎረቡቶቿን ሁሉ ያበጣበጠዉ ሻዕቢያ የተባለዉ ጸረ ኢትዬጵያ ቡድን፤ ለመጥፎ ባሕርያቱ ማገጃ ይሆን ዘንድ የተባበሩት የዓለም መንግሥታት ያሳለፉትን ማዕቀብ በመቃወም የሻዕቢያ አገልጋዮች/አማኞች ሰልፍ ወጥተዉ እንደነበር በዜና ማሰራጫዎች ተላልፏል። ከሻሽብያ አገልጋዬች አብረዉ የወጡ ለሻዕቢያ ባለስልጣኖች የባባ ሆድ ያላቸዉ አንዳንድ ዉጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዬጵያዉያንም አብረዉ እንደተሰለፉ ተከታትለናል።ይህ ዜና ስንሰማ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንዳሉት “የክሕደት ቁልቁለቱን” ከካሃዲዎች ጋር አብሮ መጋራትን ያመለክታል። በጣም የሚገርመዉ ማዕቀቡ በባለስልጣኖች ዙርያ ያጠነጠነ እና የመሳርያ መተላለፍ እገዳ የሚመለከት መሆኑን እና የሻዕቢያ ባለሥልጣኖች በእገዳዉ/በማእቀቡ ላይ ያላቸዉ አስተሳሰብ አስመልክተዉ በሰጡት ቃለ መጠይቅ (የትግርኛዉ ቪ ኦ ኤን ያጠነዋል) ኤርትራን እንደማይጎዳ በሰጡት መልስ ማረጋገጥ ይቻላል። በቅርቡ የሻዕቢያ ፕረዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቅ ከአልጀዚራ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ጋዜጠኞች ጋር ባደረገዉ ቃለ መጠይቅም እንደገለጸዉ (አድማጭ ባስገረመ ሁኔታ) “ኤርትራዊ ስደተኛ በሱዳንም ሆነ በሌሎች ሃገሮች ከኤርትራ እየሸሹ የሚጠፉ ዜጎች የሉንም፤ሕዝባችን የምግብ ችግር የለዉም፤ ምግብ አያስፈልገንም፤በቂ ምግብ አለን፤ተርቦ ሚያደር ዜጋ የለንም፤ እርዱን አላልናችሁም….” በማለት የቆየ የወባ በሽታ ባቃወሰዉ ሕሊናዉ የኤርትራ መሪዎች ሕዝባቸዉን የመመገብ ጥበብ እና አስተዳዳር ብቁነት በመኩረራት ለተጠየቀዉ ጥያቄ መልስ እንደሰጠ ዓለም አድምጧል። ታዲያ ሻዕቢያዎች ማዕቀቡ እሚነት ችግር “በሕዝቡ ላይ የሚያመጣዉ ችግር የለም” እያሉ ሲናገሩ፤ ኢትዬጵያዊያን ነን የሚሉ ዜጎች ምን ተገኘ ብለዉ ነዉ የሻዕቢያ ሰልፍ አባሪዎችና አድማቂዎች ሆነዉ ማዕቀቡን በመቃወም ሰልፍ የወጡት? በቀወሰ ሕሊና ኤርትራን ኤርትራን ደፍጥጦ እየገዛ ያለዉ የሻዕቢያዉ መሪ ማዕቀቡን በማጣጣል “ፌዝ ነዉ” ፤”ቧልት ነዉ”፤ “እሚንት ጉዳት አያመጣም ካለ”፤ እነዚህ ሰዎች ምን ለመጠየቅ ነዉ ከሻዕቢያ አማኞች ጋር ሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ ድረስ በመዉጣት በብዙ ሚሊዬን የኢትዬጵያዊያን ደም እጆቹን ያጠበዉ ዓለም ሰማይና መሬት ካወቁት ዕዉቅ ጠላታችንን ድጋፋቸዉን ለመስጠት የደፈሩት ? በእዉነቱ እኔም እናንተም ዓለምም ኤርትራን የሚያዉቀዉ ህዝቧ በረሃብ፤በእርዛት በፖለቲካ ነፃነት እጦት የዜጋ መብት እጦት፤ ሙሉ ሰዉ ሆኖ በራስ የማሰብ እና የመንሳቀስ መብት ተነፈገባት በወረበሎች የማፍዬዚ ዓይነት አሰራር እና አደረጃጀት ባህሪ በሚከተል ቡድን የምትሰቃይ ምጢጢ መሬት ነች።ሕዝቡ ከማንኛዉም የታሪክ (ባለፉት አስተዳደሮች) ወቅት ዛሬ ከመቸዉም ጊዜ በከፋ መልኩ እየተሰቃየ እንደሆነ ራሳቸዉ ኤርኢራዊያን አምነዉ የዘገቡት እዉነታ ነዉ። ሕዝቡ በ ኤርትራ ህዝባዊ ሓርንት ግንባር መሪዎች ፋሽስታዊ /ማፊዬዚ አስተዳዳር የደረሰበት በደል ህይወቱ ከእስራት፤ከድብደባ፤ከስደት እስከሞት ከመንገላታት እስከ የሰዉ ሰዉነት ማጣት ርሃብ እና የሕሊና ጭንቀት፤እንዲሁም በከፋ መልኩ የኤርትራ ምሁራን (አብዛኛዎቹ ሙሁራኖቻቸዉ) በፈጠሩት “የተሳሳተ የራስ ምስል የበላይነት እብጠት” ወደ ህዝቡ በመተላለፍ ያስከተለዉ መዘዝ በቅዠት ‘ከፈጠሩት የበላይነት ባህሪ’ ባንነዉ “ራስን ፈልጎ የማጣት” ያስከተለዉ “የሃፍረት ስሜት” በመሰቃት ላይ ይገኛሉ። ይሄ እየታየ ያለዉ ኪሳራ ሊያስተባብል የሚችል ክፍል ካለ የኪሳራዉ ፈጣሪዎች እና ለክስተቱ ምክንያቶች የሆኑት ኤርትራዊያን ምሁራን ካልሆኑ በተቀር ሌላዉ ኤርትራዊ ዜጋ አሌ ሊለዉ የማይቻለዉ ነባራዊ ተጫባጭ ሁኔታ በየቀኑ እየገጠመዉ ያለዉ ክስተት ነዉ። ምሁሩ እና ቀለም ቀሰም ከተሜዉን በስፋት ያዳረሰዉ ይህ የህሊና ቀዉስ፤ በሰዉ ልጆች ታሪክ ዉስጥ እንዲህ ያለ አስገራሚ ትርኢት ሲታይ ምናልባትም በዓነቱ የመጀርያ እንደሆነ አምናለሁ። ኤርትራዊአኖቹ ሲሹት ነበረዉን ነፃነት ከተቀዳጁ በሗላ ይህ የሕሊና መሸማቀቅ፤ የጀብደኝነት እና ሥርዓተ አልባ መሆንን፤ ራስን ችሎ የዓለም ሕግጋትን አክብሮ አለመቆም ባህሪ ባጭር ጊዜ ዉስጥ እንዴት እና ለምን ሊሰከሰቱ እንደቻሉ ምክንያቶች አሉ። አነሆ ምክንያቶቹ ከዚህ በታች አንዳስሳቸዋለን ። የኢትዬጵያ ሕዝብ አካል የነበረዉ የኤርትራ ሕዝብ በሁተኛ የዓለም ጦርነት በቅኝ ግዛት አስፋፊዎች በጣሊያኖች ከተያዘ በሗላ፤ ጣሊያኖች የተሳሳተ የራሰ ምስል የበላይነት እና የስልጡንነትን እብጠት ካስተማራቸዉ ወዲህ ያ የተሳሳተዉ የራስ ምስል ከሽማግሌዎቹ ጀምሮ (ጥቂት የሰከኑትን አይጨምርም) እስከ ወጣት ጎረምሶቹ ድረስ ያዳረሰ አዲስ ባሕሪ እንደተላበሱ በቂ ትምሕርት እና ጥናት እንዲሁም ከማሕበራዊ ግንኙነት ዝምድና እና የሃሳብ ልዉዉጥ ልምድ እና ጥናት ካደረጉ አንዳንድ የኢትዬጵያ እና የዉጭ ሃገር የማሕበረሰብ ጥናት ሊቃዉንት ገልጸዉታል። ይህ የሕሊና የባላይነት እብጠት ከልጅ ልጅ/ካካባቢ ወደ አካባቢ በራሱ በኤርትራ ማሕበረሰብ ዉስጥም በሃይማኖት እና ባስተዳዳር ልዩነት በመከሰቱ ከመጠላላት ከመናናቅ አልፎ እስከ መገዳደል ድረስ የደረሱበት ሁኔታ እንዳለ ታሪክ ያነበባችሁ ታዉቀታላችሁ። (ያ በሽታ ዛሬም በ እስላሙ እና በክርስትያኑ ክፍል በደጋዉና በቆላዉ እና በአዉራጃ ልዩነቶች በምሁሩ እና በሕብረተሰቡ ዉስጥ እና በኤርትራ ተቃዋሚ ድርጅቶች ዉስጥ ይፋ የሆነ የመዘላለፍ ባሕሪዎች በየኢንተርኔቱ ተለጥፎ እያነበብን ነዉ)።ቅኝ ገዢዎች በይበልጥ ያስፋፉትን ይህ የራስ ምስል በተሳሳተ የመገንባት “ዕብደት”በወጣት ኤርትራ ተማሪዎች ተስፋፍቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ዉስጥ ይፋ የሆነ ቡድናዊ የተምክሕት፤የጥበት እና የጀብደኝነት ባሕሪ ያንጸባርቁ እንደነበር እና የተወጠረዉ ትምክሕታዊ ባህሪአቸዉ በአማራዎች እና በትግራይ ተማሪዎች ላይም በከፋ መልኩ የጥላቻ እና የንቀት ነፀብራቆች ያሳዩ እንደነበር የታወቀ መዝገብ/ሪኮርድ ነዉ። አብዛኛዎቹ ኤርትራዊያን ምሁራን የተማሩት በኢትዬጵያ ድካም እና ዜግነት ሲሆን፤ የኤርትራ ምሁራን እንደዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ከዜጎችም አስበልጣ የተንከባከበቻቸዉ ኢትዬጵያን እንደጠላት መመለክት ያዙት።ለይግረምም ድሃይቷ ኢትዬጵያ ታጀሯን ኤርትራን እንደበዘበዘቻት በመጽሃፍም በየጋዜጦች እና ቤድርጅቶቻቸዉ ያስጠኑና ይከስሱ ነበር። ኤርትራዊያን ምሁራን ያ የተሳሳተ የራስ ምስል ከሌሎቹ በተሻለ መንገድ የመጠቁ እና ልዩ ችሎታ እና ለዓለም የሚተርፍ ልዩ ተምሳሌት ልያበረክቱ የሚችሉ ልዩ ፍጥረት እንደሆኑ ሳይሸፋፍኑ በየሚዲያዉ በስትራተጂ /እንደ ዋነኛ የመርሆ አትኩሮት በመረባረብ ዓለም እንዲያምናቸዉ ወትዉተዋል። ኤርትራዊያን ልዩ ከሌላ የዓለም ሕዝብ ልዩ ፍጥረትና የላቀ ችሎታ አለን ብለዉ ስለሚመኩ በተግባር እንጂ በቃል /ፅሑፍ የማያምኑ መሆናቸዉን የኢሳያስ አፈወርቂ ሎሌ የነበረዉ ኢትዬጵያ የአስተማረቺዉ አዛዉንቱ ዶ/ር በረኸት ሃፍተስላሰ ከሻዕቢያዉ “ሕዉየት” መጽሄት ጋር እሱ ራሱ ባዋቀረዉ/በጻፈዉ የኤርትራ ሕገ መንግሥት ተብየዉ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ አዋጅ ለምን በጥቂት ቅጠሎች /ገጾች ተጽፎ እንደታተመ ተጠይቆ ሲመልስ “እኛ (ኤርትራዊያን) የተለየን ስለሆንን በብዛኛዉ የምናተኩረዉ ተግባር ላይ ነዉ” ሲል በጥልቀት/በዝርዝር ያልተደነገጉ ሕጎች እና በሕገ መንግሥቱ ያልተጠቀሱ መብቶች እና ክስተቶች እንዴት በተግባር ላይ እንደሚያዉሏቸዉ ልዩ ፍጡርነታቸዉን በመተማመን በወረቀት ያልሰፈሩ ሕጎችና ክስተቶች በተግባር ማዋል እንችላለን ሲል ከምሑር የማይጠበቅ መልስ ሲሰጥ አንብበናል (የትግርኛዉ ቃለ መጠይቅ ጊዜ ሲገኝ እተረጉምላችሗለሁ)።እሱ ብቻ ሳይሆን ዓንደብርሃን የተባለዉ የሻዕብያ ባለስልጣንም እንደዚሁ እንደተቀሩት የተሳሳተ ምስል የተከተሉ አብዛኛዎቹ ኤርትራዊያን ምሁራን ፤ ከኤርትራ ዘልቆ ኢትዬጵያን፤ሱዳንን ጅቡቲን የመንን ሶማሌን ተሻግሮ እስከ ኮንጎ እና ኡጋንዳ ከዛም ዳስሶ በጥልቀት ወደ ዓለም የሚደርስ ልዩ ዲሞክራሲ እና ስትራተጂ እንዳላቸዉ ገልጿል። በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመዉ “ፕሮፋይል” የተባለዉ ሻዕቢአዊ ሚዲያ እንደዚሁ “ተዋጊዎቻችን በክልሉ የላቀ የዉጊያ ብቃት እና ርቀት ያላቸዉ በመሆናቸዉ ለነጻነት ባደረጉት ብቻ ሳይሆን በመርሆቻቸዉ ዙርያ ያለማወላወል በመቆማቸዉ በአፍሪካ ሃያልነታቸዉ ተሞግሰዋል።” (ፕሮፋይል 1989፡ሕዳር-15) ምንጭ መድሃኔ ታደሰ (የኤርትራና የኢትዬጵያ ጦርነት የግጭቱ መነሻና መድረሻ)። ኢትዬጵያዊዉ የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ መድሃኔ ታደሰ ስለ ኤርትራዉያን የተሳሳተዉ የራስ ምስል ቀረጻን አስመልክቶ ሁኔታዉ ሲያብራራ፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ስለ ተሳሳተዉ ኤርትራዊ ትምክሕተኛነት በራሱ ትምክሕታዊ አንደበት እንዲህ ሲል ይገልጸዋል ሲል መድሃኔ ኢሳያስ አፈወርቂ ተናገረዉ ኤርትራዊያን ዓለምን ያሸነፉ ብቸኛ ልዕለ ሃያል ፍጥረት መሆናቸዉ የኢሳያስ አንደበት በጥቅስ አቅርቦታል” ዓለም በሙሉ የኤርትራን ሕዝብ በመቃወም ቢቆምም በድል አድራጊነት ወጥተነዋል።”(አሰር 1989 ሰኔ።) ሲል አሰር ከተባለዉ ከወያኔ መጽሄት ጋር ባደረገዉ ቃለመጠይቅ ልዩ ፍጥረትነታቸዉን ይገልጻል። መድሃኔ ለዚህ እንዲህ ይላል “(ለኤርትራ ነፃነት) ሌሎች ላደረጉት አስተዋጽኦ ብዙዎቹ ኤርትራዊያን ተገቢዉን አክብሮት ባለመስጠት እና ሃቁን በመካድ “ኢትዬጵያን እና ዓለሙን በሙሉ በማሸነፍ ታምር የፈጠሩ መሆናቸዉን አመኑ።” (መድሃኔ)። ይህ ዓለም በሙሉ ሲክደን ብቻችንን ዓለምን አሸንፍን የሚሉት የኤርትራ ምሁራን የፈጡት “ተረት-ተረት” ሃያልነት፤ የኤርትራ ፖሊሲ ከኤርትራ ድምበሮች ዘልቆ ወደ አፍሪካ ቀንድ ባሻገርም መላይቷን ዓለም የቃኘ እብደት ከልብ አምነዉ ሲነዙት የነበረ ለዛሬዉ ኪሳራ ዋነኘዉ ሰበብ ነዉ።የኤርትራ ባለሥልጣኖች በተደጋጋሚ “ለአፍሪካ ፕሮብሌሞች በሙሉ የተለያዩ መፍትሄዎች ነበሩን” ሲሉ ተደምጠዋል። (መድሃኔ)። ለተለያዩ የአፍሪካ ፕሮብሌሞች መፍትሄ አሉን ሲሉት የነበረዉን ቅዠት በሱዳን በየመን ከግብፅ፤ ጅቡቲ ፤በኢትዬጵያ፤ በኡጋንዳ በሶማሌ እና ኮንጎ ጉዳዬች ጣልቃ እየገቡ ካብዛኛዎቹ ጎረቤቶች ጋር ተጋጭተዋል። ይህ ፍሪካምንም ሆነ ዓለምን ያምበረከከዉ የሃያልነት ቅዠታቸዉ ልዩ ስም በመስጠት “የአፍሪካ ሲንጋፖር” እና አፍሪካዊት እስራል” ወደ መሆን ተሰይመዉ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ አከፋፋይ ማዕከል ለመሆን ባጭር ጊዜ ዉስጥ ያካባቢ ጎረቤት ሃገር ህዝቦች በመዳፋቸዉ ስር ለማስገባት በግልጽ እና በመርሆ ደረጃ የተስፋፊነት ነጸብራቅ አሳይተዋል። ይህንን የተሳሳተ የራስ ምስል እብጥት እዉን ለማድረግ ሕዝቡ “በልጅነ ት” የሻዕቢያ ድርጀት እና ባለስልጣኖች ደግሞ ወደ “አባታዊ መለኮትነት” በመሰየም የዕዝ ሰንሰለቱ ከሕዝቡ ከምንጩ መሆኑ ቀርቶ ኤርትራን በአባትነት የሚመራዉ ከኢሳያስ አፈወርቂ እና በዙርያዉ ከተኮለኮሉ ለስልጣን እና ለሆዳቸዉ ያደሩ “ሰነፍ ምሁራን” በሚሰጡት ትዕዛዝ እና ዕቅድ ብቻ እንዲተዳደር ሆነ። ይህ እብደት የተላበሰ ትምክሕተኛ ቡድን ሕዝቡን በመዳፉ ሥር ለማስገባት የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት “አገር እና ሕዝብ በሁለት መደብ /ካታጎሪ ለይቶ “ኤርትራ የሚባል መሬት/አገር” ቀዳሚ እንክብካቤ እንዲደረግለት “ሕዝብ የሚባል የኤርትራዉ ሕዝብ” ደግሞ “በሁለተኛ” መደብ በማስቀመጥ” ሕግ አልባ በሆነ ያገር መስዋእትነት እና ትርጉም የለሽ የሕይወት ኪሳራ በማድረስ የሕዝቡን ሰብአዊ ዜግነት እየተነጠቀ “ለመሬቱ ተገዥ” እንዲሆን (በሌላ አነጋጋር ሀጋር ለገዢዎች መከበርያ ዉስጠ ሴራ መሣርያ አድርገዉ በማዘጋጀት) ሕዝቡን ለማገልገል የተከለለዉ መሬት ልዩ ትኩረት በመስጠት ራሱ የፈጠራቸዉ ጠላቶች የሚላቸዉ የማይዳሰሱ ግምታዊ ‘ኢማጂናሪ’ ጠላቶችን እየፈጠረ ከጠላት ጥቃት ጥበቃ እንዲደረግለት በሚል ሽፋን ኗሪዎችን በአደናጋሪ ሰበካ እያምታታ፤ አፈሪካዊት እስራኤል (በወታደራዊ ሃይል መስክ) እና በምጣኔ ሃብትም ሁሉም መመመገብ የምትችል የአፍሪካዊ ሲንጋፖራዊነት ለመፍጠር በሚል አባዜአቸዉ ለሕዝቡ መርገጫ መሣርያ እንደ ምክንያት አበጅተዉ “ሁሉም ነገር በሻዕብያ የልብ ትርታ እየተመራ አንድ ልብ ኖሮት በአንድ ልብ እንዲንቀሳቀስ በሻዕብያ “የልብ ሸምቦቆ” መተላለፍያ ለሁሉም እንዲዳረስ ፋሽስታዊ አንድነት እና ትምክሕታዊ ብሔረተኛነት እንዲነግሥ በማስተማር እና በመደንገግ የሕዝቡ ኑሮ ከማሽቆልቆሉ አልፎ ሕዝቡ ከሻዕብያ የሚቀዳለትን የዘረኛነት እና ጠብለልተኛ ኤርትራዊ ብሕረተኛ ሕብረተሰቡን በሞላ ጥብቅ በሆነ “ወታደራዊ መዳፍ” አስገብቶ ገደብ የለሽ ለብሄራዊ ወታደርነት አገልግሎት እየመለመለ፤ እምቢ ያሉትን በግድ ፤ሊሸሹ የሞከሩትን ነብሰገዳየዮችን አሰማርቶ እያፈነ በማሰቃየቱ ዜጎቹ ከሚኖሩት መሬት እየሸሹ መሬቱ ባዳ እየሆነ ለስደት እና ለመከራ ዳርጎታል። ሕዝቡ ምንም እንኳ የከፋ ኑሮ እያሳላፈ ቢቀጥልም ለከፋ ኑሮ እንደመነሻ እና ተወቃሽ ሆኖ ከገዢዎቹ የሚነገረዉ ኢትዬጵያዊያን የፈጠሩብን ችግር ነዉ፤ የሚል ነዉ። አንዴ አማራዎች ሌላ ጊዜ ዓጋሜዎች ብለዉ በንቀት ለሚጠሩት በተለይም ለነፃነታቸዉ ከራሳቸዉ ምሑራን እና ተጋዬች ይልቅ ከፍተኛ እጅ ያበረከቱትን ትግሬዎችን (ወያኔዎችን) እንቅፋት ሆኑብን ብለዉ በመክሰስ፤በአጉል ትምክሕት አብጦ የተሳሳተዉ ኤርታራዊ ብሔረተኛነት ለኪሳራቸዉ መሸፈኛ ጣቶቻቸዉን ሲከስሱም ይደመጣሉ። (ዛሬ ደግሞ ከኢትዬጵያ አልፈዉ አሜሪካን በዋነነት ለኪሳራቸዉ ተጠያቂነት ይከስሳሉ)። ይህ ዕብደት ዞሮ ዞሮ እተነፈሰ በመሄዱ ኤርትራን መመገብና ማስተዳደር ቀርቶ ለዓለም ሕብረተሰብ የሚተርፍ ዲሞክራሲ እና ሃያልነት አለን ያሉትን “ተረታቸዉ” የመጨረሻ የሃያልነታቸዉ መሳያ ቤተሙካራ አድርገዉ የመረጧት መንግሥት አልባዋ ሶማሌ በመሆኗ፤ ወደ አካባቢዉ በመዝለቅ ባሸባሪነት የታወቁትን ጸረ ኢትዬጵያ የሆኑት ሃይላትን (ኦነግን) እና የሶማሊ አሸባሪዎችን እንዲሁም የኢትዬጵያ የኦጋዴን ሶማሌ ነፃ አዉጪ ድርጅቶችን እና የመሳሰሉት አክራሪ ሃይላትን መሳርያ በማስታጠቅ እና በማሰልጠን የኬንያን፤ኢትዬጵያን እና ኡጋንዳን ሰላም እንዲናጋ ሰላዬቹና ወታደራዊ አዋጊዎች/ተዋጊዎችን በአካል ወደ ሶማሌ በመላክ ለአካባቢዉ መቃወስ ምክንያት ወደ መሆን ተሸጋግሯል። እንደምታዉቁት ወደ እዛዉ ቀዉስ ሊገባ የተገደደበት ዋናዉ ምክንያት ደግሞ ‘ኢትዬጵያ” ጋር ያለ አቅሙ ጦር ጭሮ ከኢትዬጵያ በጥቁር ገበያም/በሕጋዊም ሲመዘብርበት የነበረዉን የሕዝቡ መጠወርያ ምንጭ በመድረቁ ከፍተኛ ቀዉስ ዉስጥ ተዘፍቆ ራሱን ከቀዉሱ ማዉጣት የማያስችለዉን ያ አቅመቢስ የጠብ ጫሪነት የትምክሕት ባሕሪዉ ኢትዬጵያን በጦር ሃይል መደፈር እንደማያዋጣዉ በተግባር ስላየዉ፤ በእጅ አዙር ጸረ ኢትዬጵያ የሆኑትን ሃይላትን በኤርትራ ምድር እያሰለጠነ ወደ ሶማሌም እየላከ “ለአፍሪካ ፕሮብሌሞች በሙሉ የተለያዩ መፍትሔዎች አሉን” የሚሉትን የእብሪት እና የትምክሕት አባዜአቸዉ በመክሸፉ የመጨረሻ ሙከራ ለማድረግ ሶማሌ ዉስጥ ጣልቃ ቢገባም፤ ያሰለጠናቸዉ ተዋጊዎችም የተመኘዉን ኢትዬጵያ ባጭር ጊዜ ፈርሳ የማየት ምኞቱ ባይሳካም የሽብር ሥራ የሚፈጽሙ ሰዎች ወደ ኢትዬጵያ አስሰርጎ በመላክ አንዳንድ ዘግናኝ የሆነ የሽብር ተግባር ፈጽሟል። ኢትዬጵአን ብቻ ሳይሆን ያካባቢ አገሮች ሕብረተሰብ ጭምር በፍርሃት እንዲናወጥ ሞክሯል። ይህ አልሳካ ሲለዉ ከኢሳያስ ተቃዋሚ ሃይሎች ማለትም ከኤርትራዊያን ራሳቸዉ የተላለፈዉ ዘገባ እንደሚያመለክተዉ የሻዕቢያ ቡድን በየዓለማቱ የራሱን ሰዎች በማሰራጨት የጥቁር ገበያ ንግድ ከማንቀሳቀሱ እና ያንዳንድ አገሮች ኢኮኖሚ ከመበዝበዙ አልፎ የባሕር ሃይል ልዩ ኮማንዶ በማሰልጠን እና በማሰማራት በሶማሌ እና በኤርትራ አካባቢ በሕንድ ዉቅያኖስ ዙርያ እና በመሳሰሉት የባሕር ቀጠናዎች የሚተላለፉትን የነግድ መርከቦች የባሕር መርከብ ዉንብድና የጠለፋዎች ተግባር እንደተሚታማ ከኤርትራ ድረገጾች የሚተላለፉት ዘገባዎች ያመለክታሉ። ይህ ሁሉ የተሳሳተ የራስ ምስል ሃያልነት በተግባር ሲፈተን ጦር አጫሪነት እና ከዓለም ሕብረተሰብና በጎረቤት አገሮች/ሕዝቦች መገለለን እና መወገዝን በማስከተሉ ፤ትንሺቷ ሃያልዋ ኤርትራ ከኢትዬጵያ በመለየት ሕዝቧን ማስተዳደር እና መመገብ አቅም ሲያጥራት አሜሪካን ኡጋንዳን እና ኢትዬጵያን ከዚያ አልፎ የዓለም ሕዝብ ለቀዉሱ ሰበብ አድርጎ መመጎት “ኤርትራዊያን ምሁራን ራሳቸዉን ከሰቀሉበት የተሳሳተ የራስ ምስል እብጠት በጥሰዉ” ራሳቸዉን አላቅቀዉ ወደ ነባራዊዉ ዓለም ወርደዉ የመጨረሻ የኤርትራ ዉድቀት እና መበታተን ካላዳኑ፤የ ኤርትራ ፖሊሲ ከኤርትራ ድንበሮች ዘልቆ ወደ ሌላዉ ዓለም በማዳረስ ዓለምን በታምራት ሰሪነታችን ሁሉንም ነጻ እናወጣለን እያሉ ሽብር ፈጣሪዎችን ከማሰልጠን እና ለሕዝባቸዉ ያልፈቀዱትን ዲሞክራሲ፤ለአካባቢ አገሮች ሰላም እና ዲሞክራሲ እናመጣለን የማለት ቅዘታቸዉን ከላቆሙ አሁን ኤርትራ ዉስጥ ከሚታየዉ ቀዉስ አሳዛዥ ክስተት በባሰ መልኩ እንደሚከተል መጠራጠር አይቻልም። መድሀኔ ታደሰ እንደገለጸዉ ወታደራዊዉ ቡድን በኤርትራ ሕዝብ እና በወደፊት ዕድሉ ላይ አባታዊ አገዛዝ ማስንሰራፋቱን አቁሞ፤ ሕዝቡ ባግባቡ ራሱን የመምራት ንቃት እንደሌለዉ እኛ ያዘዝንህን አድርግ የሚሉትን “አዛዥ ናዘዥ” የሽምቅ ተዋጊ ባህላቸዉ እና በሕዝቡ ስም ሁሉንም ነገር መወሰኑን ባስቸኳይ ማቆም ይኖርባቸዋል። በመጨረሻ ላይ “አፍቃሬ ሻዕቢያ ኢትዬጵያዊያንን በሚመለከት” የማስተላልፈዉ መልክት፤- ሻዕቢያን እንደግፋለን ብለዉ ባሳፋሪዉ ሰለማዊ ሰልፍ ራሳቸዉ የቀላቀሉ አፍቃሪ ሻዕቢያ ኢትዬጵያዊያን ዜጎቻች ለማስተላለፍ የምፈልገዉ ወንድማዊ መልክት ‘ሁኔታና ተጨባጭን ያላገናዘበ ኤርትራዊ ብሔረተኛ ትምክሕት’ (ባብዛኛዉ ኤርትራዊዉ ምሑር አስተሳሰብ በራስ ምስል የተቃኘ ነዉ) እጅግ ጠባብ እና “በጥላቻ የተለወሰ ብሔረተኛነት” በመሆኑ ኢትዬጵያን መጠላትነት በመመልክት ለኤርትራዊ ብሄረተኛነትን መነሻ እና መድረሻ፤ማጠናከሪያ እና ለቀዉሳቸዉ እና ሰቆቃቸዉ የማዘናጊያ እና ለሽንፈታቸዉ የመሸፈኛ መንገድ አድርገዉ ስለሚመለከቱት ለሻዕቢያ የምታሳዩት የባባ አንጀት “ፀረ-ኢትዬጵያዊነት” መሆኑን እንድታዉቁት ለመግለጽ እወዳለሁ። ሕዘብ እና ሻዕቢያ ለይታችሁ ካላያችሁ፤ ሻዕቢያን በመደገፍ ድጋፋችን ለኤርትራ ሕዝብ ነዉ የምትሉት አባዜ ካላቆማችሁ፤ ወታደራዊዉ የሻዕቢያዉ ቡድን በሕዝቡ ላይ ከ30 ዓመታት በላይ እያሳደረ ያለዉ ከባድ ጭቆና እና “አባታዊነት” ካልተገነዘባችሁ፤ስለ ሕዝብ ስለ ዲሞክራሲ ስለወንደማማችነት እና ስለፍትሕ እያላችሁ የምትዘላብዱት አባዜ በቅጡ እንድታጠኑት መልከቴን አስተላልፋለሁ። ሕዘብን ለማገናኘት ከፈለጋችሁም ከሻዕቢያ እና ከወያኔ አደራጅነት ዉጭ የሚንቀሳቀሱ የወያኔን እና የሻዕቢያን አጀንዳ የማያራምዱ ክፍሎች ተቀናጅቶ ለችግሮቹ መፍትሔ መሻት እንጂ ጀብደኝነቱን እንዲቀጥል በሻዕቢያ ላይ የተጣለዉ የመሳርያ እገዳ ይነሳ ማለት ከጀብደኞቹ ጋር መጎዳኘት መሆኑን እወቁ። ሰላም ለመላ አፍሪካ ሕዝቦች አንዲመጣ ምሁራን ከጀብደኞች እና ከትምክሕተኞች ራሳቸዉን ማላቀቅ ይጠበቅባቸዋል። ጌታቸዉ ረዳ ኢትዬጵያ ሰማይ ፤- አዘጋጅ። የካቲት 2002 ሳንሆዘ ካሊፎርኒያ አሜሪካ www.Ethiopiansemay.blogspot.com

4 comments:

Unknown said...

በጅምርዎ ባጠቃላይ ብስማማም፥ ከወያኔ ጋራ ለሚደረገው ፍልሚያ ያግዛሉ ተብለው ኤርትራ ላይ ለሚሰበሰቡት ተቃዋሚዎች ምንም መፍትሄ አልጠቆሙም።
ኢሳያስን ደግፉ የሚሉን ለዚህ ነውና።

Anonymous said...

ለ፡Phoebe:"ኤርትራ ላይ ለሚሰበሰቡት ተቃዋሚዎች ምንም መፍትሄ አልጠቆሙም"። ላሉት ተሰብሳቢዎችም ጠባብ ብሄረተኞች ስለሆኑ ለኢትዮጵያ አንድነት ፋይዳ ሊያመጡ የማይችሉ ለሥልጣን ጥማቸው እርካታ የሚሯሯጡ በመሆናቸው ለሀገራችን አሳቢ አለመሆናቸውን ያመለክታል። ኢሳያስን ደግፉ የሚሉትም እንደሱ አምባገነን ለመሆን ስለከጀላቸው ነው። እርስዎስ ምን ዓይነት መፍትሔ መጠቆም ይሻሉ?።

Anonymous said...

ጢና ይስጥልኝ አቶ ጌታቸው ለእብጠታቸው ምክንየት ጣሊያን ሳይሆን በወያኒ መሪነት የትግራይ ሕዝብ ነው ለአመታት ከኖሩበት ከሳህል በርህ እንዲወጡ ብቻ ሳይሆን አሀዙ በማይታወቅ የትግራይ ወጣት መሰዋትነት ምጅዋን ሲያስረክቡ ነው እብሪቱ የጅመረው ጣሊያን ከ ፬ኛ በላይ አያስተምርም ለእውቀቱ አውድማ ኢትዮጵያ ናት የነዻናት ባርነት አሽማቀቃቸው. የውሸቱ የ እብሪት እብጠት በባድሚ ጦርነት ወሰፊ እንደነካው እባጭ እሰከወዲያኛው ተንፍሶ ቀርቶል. እኔን የጨነቀኝ ኢትዮጵያ ወይም ሞት በማለት እስከ መጨረሻው ላለፍት ኤርትራዊ አርበኞች ማእቀቡን በመቃወም ባለ መካፍሊ አዽማቸው ልጅቻቸውሰ ምን ይሉኝ?ዜግነቴን እኔ እንዼ ማንም አይናግርልኝም የሚሉትን ኤርትራዊ ጉደኞቸን ፣በመእራባዊ ቆላ ከሻቢያ ጋር ሲዋደቁ ኖረው እንደትብያ ለተጣሉት ወገኖቸ ምን ልበላቸው አቶ ጌታቸው ማእቀቡ ሕዝቡን አይጎዳውም?የሚጎሱምተን ከበሮ በአንድነት እንዴት አድርገን እናሸብሸብ?

Anonymous said...

መፍትሄን አስመልክቶ የግዜ ጉዳይ አልመቸኝ ብሎ ነውና ሌላ ግዜ እመለሳለሁ ክላይ የለጠፍኩት አሰተያየቴን በቅን ልቦና ይመልከቱልኝ.
አለማየሁ ገበቲት