Tuesday, February 16, 2010

እየየ በይ ትግራይ! የካቲት 11/2002 (ጌታቸዉ ረዳ www.ethiopiansemay.blogspot.com) በመንግስት ስልጣን ላይ ተደላድሎ ኢትዮጵያን በመግዛት ላይ ያለዉ ኤርትራዊዉ «ህወሓት»፤ ሕሊናቸዉ በጥቅም፤በወንዜ ልጅነት እና በጋብቻ ትስስር በተጋረዱ የትግራይ ተወላጆች ካድሬዎቹ አማካይነት ራዲዮኖቹ ፤ድረገጾቹ እና ጋዜጦቹ የካቲት 11 ቀን እያሉ የሚጠሩት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በር ከፋች የሆነላቸዉ ድርጅታቸዉ የተመሰረተበት ወርሃ የካቲት በየአገሩ የሚገኙትን የትግራይ ተወላጆች፤አምባሳደሮች፤ሚሊታሪ አታሼዎቹ እና ለነሱ ያደሩ ከትግራይ ያልሆኑ አንዳንድ አገልጋየቻቸዉ በድምቀትና በደስታ እንዲያከብሩት ሆድ አደር ዘፋኞቻቸዉንም በአሜሪካ በአዉሮጳ እና በየዓረብ አገሮች በመላክ ድርጅቱ ለሰብአዊነት እና ለኢትዮጵያ መጎልበት በመከታነት የቆመ ለማስመሰል ካሁኑኑ የተለመደዉ የቅጥፈት ዘመቻዉ እያጧጧፈዉ ነዉ። ኢትዮጵያን በዘዴና በገሃድ ለማዉደም ከተነሱት ጠላቶቿ ጥቂቶቹ እነ ኦነግ እና እነ ወያነ ትግራይ መሪዎች በሰብአዊ መብት አከባበር ማሕደራቸዉ የተጨማለቀ፤ሞረላቸዉ የላሸቀ፤ቡኩኖች ዛሬም ሆነ በታሪክ ፊት ለወደፊቱ ከመወቀስ አይድኑም። የወያነ ትግራይም ሆነ የኦነግ መሪዎች ትግል በሰዉ ልጆች ደም የተጨማለቁ እጆቻቸዉ፤ ዛሬም ብንል፤ ብንል፤ብንል ያልገባቸዉ “ደናቁርት ምሁራን” በጥብቅና ሲቆሙላቸዉ ታዝበናል። አንዳንዶቹ ወንጀሎቻቸዉን በጥሁፍ ደረጃ ሲከላከሉላቸዉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በአካል በሕዝባዊ መድረኮች እየተሳተፉ የነኚህ ወረዳ መሪዎቹ ርካሽና አሳፋሪ ታሪክ እንደ አኩሪ ታሪክ ባንጸባራቂነት ለማድመቅ ሌት ተቀን እየጣሩ ይስተወላሉ። ለማንኛዉም የድርጅቶቹን ወንጀል ለመሸፈን የቱን ያክል ቢጥሩ በሰዉ ልጆች ደም የተቀቡ እጆች ስላሏቸዉ የታፈነዉ የንጹሃን ደም እንደምንም ብሎ ጮሆ የፍርድ ያለህ ጩሆቱን ከማሰማት ሊያፍኑት አይቻላቸዉም እና እነሆ ፍርዳቸዉን እስኪያገኙ ድረስ ዛሬም በድጋሚ በየአመቱ በወርሃ የካቲት 11 ቀን በዊስኪ እና በቁርጥ ግብዣ ሲፈነጩ “ከሕዝቡ ጀሮ ለመደበቅ የሞከሩት ወንጀሎቻቸዉ” ገመናቸዉና እርኩስ ባሕሪያቸዉ ዛሬም አብሮ በየአመቱ በየካቲት ወር «የፍትሕ ያለህ!» ጩሆቱን ያስተጋባል። ወንጀለኞቹ ላስቀያሚ ታሪካቸዉ ተመጣጣኝ ፍትሕ እስኪያገኙ ድረስ የኢትዮጵያ ምድር እና ሰማይ ከወያኔ ሰለባዎች ጋር ፍትሕ ፍለጋ ዛሬም ለወደፊቱም ጩሆቱን አብሮ ያስተጋባል። ክቡራን የኢትዬጵያ ሰማይ የህዋ ሰሌዳ አንባቢዎች ዛሬ በዚህ የካቲት ወር በተከታታይ የሚቀርበዉ የወያነ ትግራይ ገመና አንዱ በአቶ ግደይ ባሕሪ ሹም የተጻፈዉ «አሞራ» ከሚለዉ መጽሃፍ ዉስጥ የወያነ ትግራይ ድርጅት በትግራይ ሕዝብ ላይ ሲፈጽማቸዉ ከነበሩት ግፎች ጥቂቶቹን ለናሙና እንድታነብቡት ሳቀርብላችሁ፤ በዲሞክራሲ እና ባገር ወዳድ እንዲሁም በትግራዋይነት እና ሰብአዊ ተማጔችነት ድርጅቱ ሲመጻደቅ የምትሰሙት እና በየሚድያዉ ያለ ለከት የሚዋሸዉ ዉሸት፤ከዚህ በታች የምታነብቡት ዘገባ ስታነብቡ ድርጅቱ ለሕዝብ የመቆርቆር መንፈስ አለኝ ከሚለዉ ቅጥፈቱ እና የዲሞክራሲ ጥያቄም ሆነ ተቃዉሞ ላቀረቡ ዜጎች ዓይናቸዉ እያየ በሕይወት እያሉ ከነ ነብሳቸዉ ሰለባዎቹ በቆፈሩት ጉድጔድ ዉስጥ እየከተተ በአፈር ትል አጥንታቸዉ እየተፈረከሰ ሥጋቸዉ ተልቶ እዛዉ እንዲሞቱ በማድረግ እና ከጥቃቱ ሊያመልጡ የሞከሩ ሰለባዎቹም እንደሚዳቌ እያባረረ በጥይት ሲገላቸዉ የተዘገቡት የወያነ ትግራይ ልዩ ልዩ ገበናዎች በየተራ በዚህ ወር አምዳቸዉን እየጠበቁ ይቀርባሉ። ለዛሬ የተዘጋጀዉ የየካቲት 11 ቀን 1966 ዓ.ም የወያነ ትግራይ ምስረታ በትግራይ ኗሪዎች ላይ ያስከተለዉ ሰቆቃ እና ምሬት ገመናዉ እነሆ ። በሚቀጥለዉ ሰሞን ደግሞ በትግርኛ ለትግርኛ አንባቢዎች ተርጒሜ ያቀረብኩትን ተሓህቶችን የተቃወመ የትግራይ ተወላጅ አንዳንዴ በሕይወቱ እያለ መቃብር ጉድጓድ ዉስጥ በመክተት የቁም ስቃዩን እያሳዩ እንዴት እንደሚገድሉት የሚገልጽ ይቀርባል። በዚህ ገጽ ግን ለአማርኛ አንባቢዎቼ የማቀርበዉ ከትግርኛዉ ለየት ያለና ሰፋ ያለ ደርጅቱን እና የኤርትራዉ ሻዕቢያ በመመሳጠር በሕዝቡ ላይ እና በታጋዮቹም ጭምር የተፈጸሙ ወንጀሎች በቦታዉ ከነበሩ ወያኔን ከተዋጉ ግለሰብ የዘገቡልንን ታሪክ እንድታነብቡ እጋብዛለሁ። በግደይ ባሕሪሹም (ከአሞራ መጽሃፋቸዉ የተገኘ) “ …ሴቶች ለማገዳ እንጨት ለቀማ ከሠፈራቸዉ ወጣ ብለዉ ወደጫካ ሲሄዱ፤በክረምት ወራት በጎርፍ የተጠራቀመዉን በደረቀዉ ወንዝ አፋፍ ላይ ዳሰሳ ጭራሮዉንና ጉቶዉን መምዘዝ ሲጀምሩ፤ጎርፍ ካጠራቀመዉ ቅርፊትና ግንድ ጋር የተቀላቀለ፤ የሰዉ አጽምና ያልፈረሰ የራስ ቅል፤ደጋግመዉ ያገኛሉ። በተለይ በትግራይ ክፈለ ሃገር፤በሽሬ አዉራጃ፤ በሰየምት አድያቦ ወረዳዎች ዉስጥ፤የሰዉ አጽም ያልተበተነበት በረሃ’ና ቋጥኝ የለም። ከሰላሳ ሁለት ጊዜ የወያኔ እና ኢዲህ ጦርነት እልቂት ልላ፤አካባቢው በወያኔ ቁጥጥር ከዋለ በሗላ፤ የኢዲህ ደጋፊ ነበርክ፤ነበርሽ ተብለዉ በወያኔ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በሗላ ፤በተሓህት አፈሙዝ እየተረሸኑ፤ በየፈፋዉና በየጋምስቱ የተደፉት፤ አፈር ተነፍጓቸዉ ፤ ፀረ ትግራይ “<ኮራኹር አምሐሩ”> ( የአማራ ቡችላ) እየተባሉ ለአሞራ ቀለብ የሆኑት ትግራይ ተወላጆች፤ በዓይናቸዉ ያዩ፤በድርጊታቸዉ የተሸማቀቀዉ ቤት ጎረቤት ይቁጠረዉ።በእርስ በርስ ጦርነት ካለቀዉ ይለቅ፤ በጥርጠራና በጥቆማ ተይዘዉ፤ ለዘርና ለታሪክ እንዳይተርፍ፤ በስዉር (በወያነ ትግራይ/የሻዕቢያ ባንዳዎች) ያለቀዉ የትግራይ ሕዝብ እጥፍ ድርብ ነዉ።ከክፍለሃገርዋ ከመቀሌ ከተማ ጀምሮ፤ በስምንቱ አዉራጃዎችና በአምሳ ሁለት ወረዳዎች ያለዉ ሕዝብ፤ፈጠን ብሎ ለእነሱ በርከክ ካላለና “ትግሬና አማራ” ወይም “ኢትዮጵያና ትግራይ” በሚለዉ መሰረታዊ መፈክራቸዉ ላይ፤ ጥያቄ ያቀረበ ሰዉ ሁሉ “ኢዲህ” ነዉ፤ እየተባለ ወላጅ በልጁ አጅ እንዲመታ እና አንዲረሸን ያደረጉት እነኚህ ለትግራይ ቆመናል የሚሉ የሻዕቢያ ባንዳዎች፤ በግማሽ ከኤርትራ ክፍለ ሃገር በመወለዳቸዉ፤ለነገዉ ትዉልድ ጥቁር ታሪከና የማይደርቅ ደም አተረፉ እንጂ፤ በተተኪዉ የትግራይ ትዉልድማ ለልጆቻቸዉ ቂም አትርፈዉ፤አመላቸዉን ይዘዉ በተራቸዉ ማለፋቸዉ አይቀርም። ደግ ይሁን ክፉ ሰዉ መቸም እንደ ድንጋይ ለዘላለም አይኖርም። ከናዚ ጀምሮ የነበረ አረመኔ ሁሉ አላለፍም ብሎ ዛላለም የኖረ ሰዉ የለም። ይህች የአረመኔዎችና የካሃዲዎች የትምክህተኞችና የቂመኞች ዘመን በተራዋ ሳትወድ በግዷ ታልፋለች። ትዉልድና ታሪክ ግን ይቀየራሉ።“ቁጥቋጦና ታሪክ ከመቃብር በላይ ነዉ” ይባል የለ!። ደርግ በቀይ ሽብር የከተማዉን ወጣት ሊጠርግ ፤ የሻዕቢያ ቅጥረኛ የሆነዉ ወያኔም፤ ትግራይ ዉስጥ በገጠሩ፤ ኢትዮጵያዊነቱን ያልካደና እምነታቸዉን ያላመነ ገበሬዉንና ወዛደሩን <ኮራኹር አምሐሩ፤ ሽዋዉያን ተጋሩ> (ያማራ ቡችሎች - የሸዋ ትግሬዎች) እያለች የ “ኢዲህ” ታጋይ ቤተሰብ ዘመድና አዝማድ የተባለ ሁሉ በጠቅላላ፤በሬና ላሙን፤በግ አና ፍየሉን፤ አህያዉን በቅሎዉን፤ ደሮዉንና ጎተራ እህሉን፤ ማርና ቅቤዉን፤እየወረሰች ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር ፤ ለሐማሴኖች መደሰቻ ተብሎ፤ላሻዕቢያ አልሰግድም ያለ ምስኪን የትግራይ አራሽ ገበሬ፤ “ዘር ማንዘሩ” ከምድር እንዲጠፋ እየረሸነች፤ ለሌሎች መቀጣጫ ተብሎም በወጉ በቤተዘመድና በጎረቤት እንዳይቀበር፤ለንቃተ ህሊና ትምህርት ወደ በረሃ ተልኳል እየተባለ፤ ሳይመለስ የቀረዉ የቤትና ጎረቤት ሰዉ ታዝቢ ይቁጠረዉ።ሻዕቢያ የተባለዉ የኤርትራዉ ድርጅት፤ በግማሽ ትግራይ ተወላጅ የሆኑትን ዘመዶቹን፤ ወየኔ ትግራይ ድርጅት “ቁንጮ” ላይ አስቀምጦ፤በንጹህ የትግራይ ዘርና ትዉልድ ላይ ግፍ የፈጸመበት “በሃያኛዉ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጊዜ” እንደነበር፤ ለተተኪዉ የትግራይ ትዉልድ ታሪክ መጥቀስና ማዉረስ የተቆርቋሪ ወገን ግዴታ ነዉ።ሻዕቢያዎች በወያኔ ትግራይ ስም ተሰይመዉ፤አመራሩን በወኪሎቻቸዉ ተቆጣጥረዉ፤ገበሬዉንና አገር ወዳዱን የትግራይን ሕዝብ፤ወጣቱንና ሕጻናቱን አሰባስበዉ (ትግራይ ዓደይ በል!!) <ላገሬ ለትግራይ በል!!> እያሉ፤ የራሳቸዉን ፍላጎት ለሟሟላት የጦርነት ምሽግና ተገን እንዲሆንላቸዉ አታልለዉና አሞኝተዉ፤ ባልተወለደ አንጀታቸዉ በገዛ ጓሮዉ ኢትዮጵያዊነቱንና አንድነቱን በሚያስከብር የጠራናፊት ሠራዊት (ኢዲህ) እግር እንዳይተክል ትግራይ ወጣት እርስ በርሱ ወንድም በወንድሙ ላይ ሰይፍ እንዲማዘዝ አደረጉ።ትግርኛ በመናገራቸዉና ወላጆቻቸዉ ትግራይ ዉስጥ ተወልደዉ የትግራይን መሬት ፍሬና እህል በልተዉ በማደጋቸዉ፤ትግሬዎች ነን በማለት፤ “ለነጻነትህ ብርሃን ነን” እያሉ የትግራይን ህዝብ በማታለል፤ በዘር ወገናቸዉ ለሆነዉ ለሻዕቢያ በተንኮል ተወክለዉ፤የትግራይን ሕዝብ ወገኑ ከሆነዉ የመሃል አገር ያማራና የኦሮሞ ሕዝብ ዝምድናዉ እንዲሻክር ወዳጅነቱንም ለዘላለም እንዳይኖረዉ ፤በኤርትራዊያን ተጨቁኖ፤ በአማራዉም ተጠልቶና ተራርቆ እንዲኖር፤ በተንኮል ወደ ገሃነም ጨለማ መሩት።በእነሱ አቌም - <ዓጋሜ የአማራ ሰላይ>በአማራዉም - <ባንዳ አስገንጣይ ተገንጣይ ታሪክ ሻጭ> እየተባለ እንዲወቀስ፤ ዘላለም እንዲከሰስና በታሪክ እንዲኮነን አደረጉት። በሻዕቢያ መሠረተ ዓላማ የተጠመቁ ሃማሴኖች፤ የትግራይ ሕዝብ በመሀል አገር ሕዝብ እንዲሞገስና እንዲመሰገን አይፈልጉም። ይልቁንም በትግሬዉና በአማራዉ መካከል የከረረ ጠብ ተፈጥሮ የትግራይ ሕዝብ ከመሀል አገር ያኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እየተጋጨና እየተነጫነጨ እንዲኖር፤እነሱ ግን ከሗላ <ግፋ በል -ጠቡን አታብርደዉ> እያሉ ተራርቆ በጠላትነት እንዲኖር ሕልማቸዉ ነዉ። ከጥንቱ ከጥዋቱ ትዉልድዳቸዉ ከሓማሴን የሆኑ የወያኔ መስራቾች እነ መለስ ተኽለ ፤ ሙሴ ባራኺ/ማሓሪ ተኽለ (ጫዓ መስከበት ጦርነት ላይ በኢድህ የተገደለ) ፤ የማነ ጃማይካ፤ ለገሰ ዜናዊ፤ግደይ ዘርአጽዬን፤,,,, ሲሆኑ በሗላም በብዛት ሌሎችም ተጨመሩበት። እነዚህ ሐማሴኖች ጥቂት ትግሬዎችን እነ አረጋዊ በርሄንና በጠራናፊት (በኢዲህ ሰራዊት) የተገዱልትን አቶ ገሰሰ አየለን “በሸራሮ የእርሻ ልማት ሰራተኛ” የነበረዉን አቶ በርሄን እና አቶ መረሳ አለማዮህን በማሞኘት፤ እነ ወልደስላሴ ነጋን፤ እነ ተኽሉ ሃዋዝንና ገብሩ አስራትንም በቀላሉ በማሳመን የወያኔ አባላት አደረጔቸዉ። እነዚህ ሰዎች የትግራይን ሕዝብ ጥያቄ በማንሳት ፈንታ አማራን እንደጠላት በመኮነን፤ሐማሴኖችን እንደ እንደታቦት ማክበርን ቀዳሚ የትግሉ ዓላማቸዉ አድርገዉ የሻዕብያ አገልጋዬች ሆኑ። ወዲያዉ ሻዕቢያ የላከቻቸዉ ተንኮሎኞች የድርጅቱ መሪ አዛዥነት ቦታ በመዉሰድ በድርጅቱ ዉስጥ ያሉት የትግራይ ተወላጆች ታዛዥ በሆኑበት ሰራዊቱ የሻዕብያ ሜዳ ለመጥረግ በአፄ ኢሳያስ አፈወርቂ አዋጅና በጦር ሚኒስትሩ በስብሓት ኤፍሬም (ወዲ ኤፍሬም) ትእዛዝ ወደ ኤርትራ ዘመቱ። የወያኔ ትግራይ ሠራዊት የሆኑት የትግራይ ወጣት ህፃናት አንድ ቀን በትምሕርት ገበታ ለመሳተፍ ዕድል ያላገኙ፤ ከጥጃ ጥበቃቸዉና ከወላጆቻቸዉ ጉያ ተገድደዉ የተለቀሙ ናቸዉ።ለሻዕቢያ ስልጣን ጥማት ሲባል ከእርስ በእርሱ ጦርት ሌላ፤መረብ ተሻግሮ፣በ አንጋፋ የኤርትራዉ ድርጅት በጀብሓ (ተሓኤ) ላይ ወረራ እና ዘመቻ እንድያደርግ ተገደደ። የትግራይ ወጣት ታጋዬች ባልተወለዱበትና ባላደጉበት መንደር በሳሕል እና በናቕፋ ገደል በቃሩራና በባርካ በረሃ ጥንት አባቶቻቸዉ ራስ አሉላ አባ ነጋ ጠላት ሲያስበረጉጉበት እና ሲያባሩሩበት በነበረዉ ሜዳ እየዳከሩ ምንም በማይገዳቸዉ ጉዳይ ገብተዉ በጀብሃ ላይ እንዲዘምቱ ተደረጉ። ሻዕቢያ ለብዙ አመታት ታግላ ተሳክቶላት የማታዉቀዉን ድል በአርበኝነትና በፊታዉራሪነት ጀብሃን እንደታዘዙት ጨፍጭፈዉ ከምድረ ኤርትራ ከክፍለሃገር አባረሩት። ሻዕብያ ሱዳን ለመመለስ ሳሕልን ዙራ ወደ ፖርት ሱዳን ሰትጓዝ እንዳልነበር ሁሉ፤በትግራይ ልጆች ሱሪ (ብስረ ወዲ ትግራይ) ወኔ እና አርበኝነት ያገኘቺዉን የከሰላ በር ዘግታ ልክ በአመቱ የትግራይ ሕዝብ በረሃብ ሲረግፍ፤በበጎ አድራጊ ድርጅቶች የዉጭ ዕርዳታ የተገኘዉን እህል፤ተጭኖ ወደ ምዕራብ ትግራይ እንዳይገባ ከለከለች።ሻዕብያ ለትግራይ ሕዝብ የተለገሰ የነብስ አድን የዕርዳታ እህል በመሬቴ በኩል አላሳልፍም ብላ መንገድ ስትዘጋ፤በወኪሎቿ በወያነ ትግራይ በኩል የተወሰደዉ “ከባድ” እርምጃ ግን “ሻዕብያ በከሰላ በኩል በር የዉጭ እርዳታ አላሳልፍም አለችን” የሚል የቃል መርዶ ነበር። በትግራዊነት ወኔ እማ ቢሆን ኖሮ ፤የወያነ ትግራይ መሪዎች ሁሉም ሙሉ በሙሉ የትግራይ ተወላጆች ቢሆኑማ ኖሮ “ጀብሃን በቀጡበት ጅራፍ ሻዕቢያን እየገረፉ ወስደዉ ከሰላ ከዘመዶቻቸዉ ከጀብሃ ሰራዊት ጋር ይቀላቅሉዋቸዉ ነበር”። ዳሩ ምን ይሁን! ትግራይ “ስንዴ እኔ ሟሽላ” እየመገበች ያሳደገቻቸዉ ዘረኞች ትግሬ መስለዉ ገብተዉ እንደተባይ ከትግራይ ሕዝብ ራስ ላይ ሰፍረዉ፤ እንዲያዉም ለግላቸዉ ምቾት የሚያማግጡበትን ገንዘብ ለማግኘት እንዲያመቻቸዉ በገበሬዉ ሕዝብ ስም እርዳታ የሚያገኙበትን የልመና ስልት ቀይሰዉ የተራበዉ ሕዝብ ሰብስበዉ “እርዳታ የምታገኝበትን “ጥርጊያ መንገድ ጥረግ” እያሉ ፤ በመለስ ዜናዊ መሃንዲስነት ቀን በጸሃይ ብርሃን ሌሊትም በችቦ እያጣደፉ ጋራዉን ከመሃል ትግራይ ከተምቤን ጀምሮ ምዕራብ ትግራይን አቋርጦ በጎንደር ወልቃይት ጠገዴንና የአርማጭሆ በረሃን አቋርጦ እስከ ምስራቃዊ ሱዳን በር ወዲ ኸዉሊ ድረስ በዶማና አካፋ አስቆፈሩት። ያንን በእርዳታ ያገኙትን እህል ቃል በገቡበት መሰረት ቦታዉ ድረስ ወስደዉ ለተቸገረዉ እንዳያከፋፍሉት ሕዝቡ ራሱ በጠረገዉ ጥርጊያ እየመሩ በጅምላ ሱዳን በር ድረስ አድርሰዉ እንዲሰደድ አስገደዱት። የወያኔ መሪዎች “የቀረቺህ ላም ፍየል ካለችህም እኛ እንጠብቅልሃለን” ብለዉ ከቀሙት በሗላ፤ያለፍላጎቱ ስደት የዳረጉት ሕዝብ ህፃን ሽማግሌ ሳይቀረ፤ወዲ ኸዉሊ ከተባለዉ በረሃ በበሽታና በረሃብ በሆድ ቁርጠትና በተቅማጥ እየተነዳ እንደ ቅጠል በጅምላ ባሰቃቂ ሁኔታ ረገፈ። እነዚህ “መሪዎች” የተባሉ “ሻዕብያዊ ወያኔዎች” ይህን ሲያዩ የዓለም ጋዜጠኞችን ጋብዘዉ በእነሱ ቃል አቀባይነት፤ ለበጎ አድራጊ ድርጅቶች “ለህዝብ የሰጣችሁን የእህል እርዳታ አልበቃ ብሎ፤ይኼዉ ሕዝባችን በረሃብ ረገፈ። ከዚሁ መጥታችሁ ማየት ትችላላችሁ” እያሉ መለመኛ አደረጉት። ያንን ዘዴ ተጠቅመዉ እርዳታ በብዛት ጎረፈ። ያንን ሕዝቡ ሽታዉን ብቻ እየሰጡ በቶን ለሱዳን ሀብታም ነጋዴዎች ቸብችበዉ ገንዘቡን ተሽሞነሞኑበት። ንምዕባለ ሃገርና(ላገራችን ዕድገት) ተብሎ ተገድዶ ወደ ሱዳን ጠረፍ በጅምላ እየተገፋ የተሰደደ ቤተሰብ፤ከመንደርና ከጎረቤት ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር በቀን ከሁለት መቶ እስከ ሶስት መቶ ሲሞት፤ከሗላ ለወያኔ አደራ የተዋቸዉ ጥቂት ከብቶቹ ደግሞ፤ ለወያኔ መሪዎች ቀለብ ሆኑ። ወገኔ በረሃብ በጠራራዉ “ወዲኸዉሊ ሜዳ” በሐሩር ሲቆላ፤ወያኔዎች ግን በአደራ የተወላቸዉን ጥቂት ከብቶቹ ጮማ ሲቀናጡ ነበር። ሰሚ ይፍረደዉ! የበደል በደል ነዉ። ሐማሴኖች (የኤርትራ ትግሬዎች) የትግራይ ሕዝብ ለዘር እንዳይተርፍ የፈጸሙት ተንኮል በየፈርጁ እና በየወቅቱ በተለያየ ስልትና ብልሃት ነዉ። እንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል፦ 1ኛ - ወያነ ትግራይ እና ጠራናፊት ኮሚቴ (ኢደህ) እንዲዋጉ አደረጉ። 2ኛ - የትግራይ ወጣት ትዉልድ ከሁለት ድርጅት ተከፍሎ በተለያየ ጦርነት እየተማገደ ሲያልቅ ለተተኪዉ ትዉልድ ዘር እንዳይተርፍ በወያኔ ትግራይ የተደራጀ ወጣት ሠራዊት እንዳይወልድ ወይም እንዳትወልድ በሞት ፍርድ ደንግገዉ እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ (ከሴት ደርሷል ተብሎ) የተጠረጠረዉን ተራ ታጋይ አባላቸዉን እየረሸኑ፤ መሪዎቹ (ቆንስሎቹ) ግን ለራሳቸዉ በየጎጡ በምስጢር ቅምጥ መልምለዉ የትግራይን “ንጹህ ዘር” የሚተካ ጋብቻ ከለከሉ። 3ኛ - የሻዕቢያ ሠራዊት እንዳያልቅና እንዳይሞት፤ የትግራይ ወጣት ግን ሳሕል፤ናቕፋ፤ቃሩራ፤ምፅዋ፤ባርካና ሰቲት ሄዶ እንደ ጤዛ እንዲረግፍ፤ከደርግና ከጀብሃ ሠራዊት ጋር ተዋግቶ እንዲሞት አደረጉ፡ 4ኛ - ልጆቹን ሲነጥቁት ሞት ፈርቶ ያልተነፈሰዉ ወላጅ፤ልጆቹን ለማሳደግ በደርግና በእነሱ መካከል ከሚወረወረዉ ጥይት እየተሳቀቀ ጓሮዉን ጭሮ ከሚኖርበት ጎጆዉ አስገድደዉ ልጆቻቸዉን እየያዙ አባት እንኮኮ ብሎ፤ እናት አዝላና እንጠልጥላ፤ቤት ንብረታቸዉን ገርበብ አድርገዉ ላምና ፍየሎቻቸዉን ለወያኔ አስረክበዉ ሱዳን ሄደዉ በጅምላ እንዲያልቁ አደረጉ። 5ኛ - የሻዕቢያ ሠራዊት አስመራ ሲገባ የደርግን ወታደር በጅምላ እንደረሸኑት እናስታዉሳለን። የአስመራ ነዋሪ የነበረዉንም ጥቂት የመሀል አገር (የ አማራዉ ሕዝብ) እስከ ትግራይ ጠረፍ ድረስ አባረሩት። ትግርኛ ተናጋሪዉን ኢትዬጵያዊ የትግራይ ሕዝብ ግን የት ያለ ቅጣት ቀጡት። ሰኞ አስመራ ከገባን ማክሰኞ ዓጋሜን እናባርራለን” ብለዉ በ1969 ዓ.ም ባወጁት ቃል መሠረት፤ ያማራ ሰላይ (ጃሱስ) እያሉ “ማይበላ” በተባለዉ ከተማ ዉስጥ በሚገኘዉ የመዝናኛ ፏፏቴ ሰብስበዉ ረሸኑት። በዚህ ቅጣት የፈጁት የሰዉ ቁጥር ብዙ ነዉ። ድርጊቱም ምስጢር አይደለም። ይህ ሁሉ በትግራይ ሕዝብ ላይ የተበየነ ፍዳ ድርጊቱ ሲፈፀም ሻዕቢያ አስሠርጎ ወደ ወደ ወያኔ ድርጅት ባሰማራቸዉ የሻዕቢያ ሰላዬች በሆኑት በወያኔ ትግራይ መሪዎችና ለነሱ ያደሩ የትግራይ ተወላጆች በጎ ፈቃደኝነትና ቆሞ ተመለካችነት ነዉ። የደርግን ሰራዊት ድል ነስቶ ሻዕቢያን ለሰላሳ አመት ሳሕል በረሃ ከተወሸቀዉ “የበረሃ ቤተመንግሥት” የጨለማ ኑሮ አላቅቆ “ቀን’ ያወጣለት “ግመል ጎታቹ” ሠራዊቷ ሳይሆን “ነፍጠኛዉና ዝነኛዉ የትግራይ ልጅ መሆኑን ማንም አስተዋይ የሚያዉቀዉ ያደባባይ ምስጢር ነዉ”። የሻዕቢያ ሱሪ ምንግዜም ሻዕቢያ ነዉ። ጀብሃ ታወቀዋለች። ታዲያ በየትኛዉ የዉግያ ታሪኩ ነዉ የሻዕቢያ ሠራዊት በጀግንነቱ አስመራን ከደርግ ሰራዊት አስለቅቆ አስመራን ነፃ አዉጥቶ የሚያወቀዉ? “እንኳንስ አስመራን ማስለቀቅ ቀርቶ የትግራይ ልጆች እስኪዘምቱበት ድረስ የሳሕልና የባርካ በረሃ እንኳ በጀብሃ ቁጥጥር ሥር ነበር”። ታድያ “ወርቅ ላበደረ ጠጠር መለሱለት” እንዲሉ ሻዕቢያ በትግራይ ልጆች ደም ምኞቷን ስታገኝ የተቀረዉ ከሞት ለተረፈዉ የትግራይ ሕዝብ፤- ታጋይ ልጆቹ እና ዘመዶቹ ለሻዕቢያ ያደረጉለትን ዉለታ ምስጋናዉና ብድሩን መመለስ ቀርቶ፤ ሻዕቢያዎች ወያኔ ነፃ ያወጣላቸዉ ኤርትራን ከተረከቡ በሗላ ኤርትራ ዉስጥ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ያፈሩትን ሀብትና ንብረት መያዝ ቀርቶ፤ መለወጫ ልብስ እንኳ ሳይዙ፤በሳንጃና በሰደፍ እያጣደፉ፤በራማ በር በኩል ነበር ወደ ትግራይ ያባረሩት። 6ኛ - ወያኔዎችም ቢሆኑ ታሪክ ይዉቀሳቸዉ እንጂ ፤ ኢትዬጵያን እንደያዙ፤ አዲስ የትግራይ ክልል ብለዉ ደጋግመዉ በአወጡት የመለክዓ ምድር (ካርታ) ላይ ከአማራዉ ጋር ለማቀያየም፤ ወልቃይትንና ጠገዴን ተሻግሮ አዲስ ድንበር ከመጠየቅ ይልቅ፤ትናንት ደጃዝማች ገብረ ሥላሴ “በወጨፎ ጠመንጃ” የሸጡትን የአዉጋሮን የእምኒ ሓጀርን፤ የጉልጅን፤ የተሰነይንና የከሰላን በር፤ የኤርትራ ክፍለ ሃገር ኩታ ገጠም ድንበር ጉዳይ (ለማስመለስም ሆነ ለታሪክ ትዝብት) ለምን አላነሱትም?” ለምስክር የአያታቸዉን “የገብረሥላሴን ዓይነት” ወጨፎ ጠመንጃ ወያኔዎች ትግል እንደመሠረቱበት እናዉቃለን። ይህ የሆነዉ “የወጨፎ ብረት-ባለዉለታችን ነዉ” ተብሎ ይሆን? “ሕዝቡ እኛ ካልነዉ ከደነገግነዉ ሕግ አይወጣም” ተብሎ ይሆን? በጣም ቂሎች ናቸዉ። “የትግራይ ሕዝብ የሚንቃቸዉን ያህል በበኩላቸዉ ሕዘቡን ሲንቁት ማየት ይገርማል።” እነሱም በዘመናቸዉ የሚያልደፉና ፤ይህ ለጊዜዉ ላሁኑ የሚመኩበትና የተቆጣጠሩበት ሠራዊት፤ በሌላ አዲስ ትዉልድ ሠራዊት ተተክቶ፤ አንድ ቀን ንብረቱን፤ታሪኩና መሬቱን የሚጠይቅ፤ ሌላ የትግራይ ሠራዊት የሚነሳ መሆኑን አልተገነዘቡም። መቼም በእነሱ ቤት ያለነሱ ሌላ ብልህ የለምና ነዉ። ዘመኑ የመጀመርያ እና የመጨረሻ ዘመን መስሏቸዋል።የትግራይ ሕዝብ ለጊዜዉ አፉና እጁ ታስሮ ዝም ይበል እንጂ ፤ አንድ ትዉልድ በወያኔዎች የተበላሸዉን ታሪኩን እንደሚያስመልስ ታረክ ምስክር ነዉ። ከ1968 እስከ 1970 ዓ.ም ድረስ የወያኔ ሠራዊት ጥቂትና ደካማ ስለነበረ ከኢደህ ጋር በሚደረገዉ ጦርነት ከሠራዊቱ ሰዉ ሲቆስል በእግሩ ሮጦ ማምለጥ የማይችለዉን ተሸክመዉ አያሸሹትም። ጠራናፊት አባርራ ከምትይዘን ቁስለኛችንን “እንሸኝ” የሚል ፈሊጥ ነበራቸዉ። ባልተወለደ አንጀታቸዉ እነ ግደይ ዘርአጽዬን ለመልእክታቸዉ ተሰልፎ የቆሰለዉን ብፃያቸዉን (ጓደኛቸዉን) ተሸክመዉ ከአስተማማኝ ዋሻ ደብቀዉ ከማስታመም ፈንታ “መድሃኒት ነዉ” ብለዉ ለትግራይ ወጧት በልቡ ስር የሚሰጡት መርፌ “የጓንዴ ጥይት” ነበር። ታዲያ አመላቸዉን የሚያዉቅ ቁስለኛ እንዳይጨርሱት “ደህና ነኝ” እያለ ለሞራል ያህል “ላሎየ! ላሎየ! ላሎየ ወይ ትግራይ ዓደየ” ብሎ ባስጠኑት መዝሙር ራሱን ማጽናናት ሲጀምር “ብፃይ (ጋድ) አታጭበርብረን፤ደክመሃል፤አትድንም፤ዘፈንህ የጣረሞት ዘፈን ነዉ” ይሉና የተለመደዉን ጥይታቸዉን ሰጥተዉና አሰናብተዉ ካንድ አፋፍ ጋምሰት “ሣር ቅጠል” አልብሰዉት ይሄዳሉ። ይህ የአገዳደል ፍልስፍና አንዲት ቀን በጦርነት ግንባር ተሰልፈዉ የማያዉቁት በሁለትና በሦስት ሰዓት መንገድ ርቀት ላይ ከሓላ አሻግረዉ ጦሩነቱን የሚከታተሉ፤ ተባራሪ ጥይት እንኳ ኳ ቢል የሚያስበረግጋቸዉ የቀድሞ የወያኔ የጦር መሪዎችና የሻዕቢያ ወኪሎች እነ ግደይ ዘርአጽየን ሲፈላሰፉበት የነበረ የአገዳደል ተግባር ነዉ። በግደይ ዘርአጽየንና በመኮንን ዘለለዉ ነገረ ሠሪነት፤ ጥንብ አንሳ አሞራ በሰየምት አድያቦ በረሃ ጦም አድሮ አያዉቅም ነበር። እንኳን የግራ ቀኙ ሠራዊት፤ያስታራቂ ሽማግሌዎችም ደም ተመሳሳይ ዕድል ገጥሞታል። ለምሳሌ ከዓዲ ሀገራይ ሰየምት አድያቦ ዉስጥ እነ አቶ አበበ ለማስታረቅ በቅንነት በመድከማቸዉ በእነዚህ ሰበበኞች ሕይወታቸዉ ለመቅሰፍት፤ሥጋቸዉ ለአራዊት ተዳርጓል። ከላይ የተጠቀሱት ወያኔዎች በዚህ ተግባር ሲጠቀሱ ሌሎቹ የወያኔ አመራሮች “ቅዱሳን” ናቸዉ ማለቴ አይደለም። በነገረ ሠሪነታቸዉና በግብራቸዉ በትግራይ ሕዝብ ደመንና አጽም ታሪክ በቅድሚያ የሚወቅሳቸዉ ግን እንዚህ ናቸዉ።” ግደይ ባሕሪሹም - አሞራ” ጌታቸዉ ረዳ www.ethiopiansemay.blogspot.com San Jose, California USA

1 comment:

Anonymous said...

እጅግ፡በሚዘገንን፡ሁኔታ፡ሀገር፡እና፡ወገኖቻችንን፡እያሰቃዩ፡መሆናቸው፡
ለማንም፡ግልጽ፡ነው።ነገር፡ግን፡የትግራይ፡ተወላጆች፡ይኸን፡ሁሉ፡ስቃይ፡
ለደረሰባቸው፡ወገኖቻቸው፡ከቀሩት፡ኢትዮጵያውያን፡ወገኖቻቸው፡ጋራ፡
አብሮ፡በመታገል፡ፈንታ፤አሁንም፡በትግራይ፡ተወላጅነታቸው፡ብቻ፡ለብ
ቻቸው፡ድርጅት፡ሲያቋቁሙ፡ነው፡የማየው።ስለዚህ፡እርስ፡በእርስ፡ለማፋ
ጀት፡የትግሬ፡ወያኔ፡አምባ፡ገነኖች፡ያቀዱትን፡በተግባር፡ቀጭቶ፡አንድነት
ን፡የመፍጠር፡ዕቅዳቸውን፡የሚጀምሩት፡መቸ፡ነው?።እንደ፡ጌታቸው፡
ረዳ፡መረረን፣አሳፈራችሁን፣እኛ፡ከኢትዮጵያውያን፡ወገኖቻችን፡በምንም፡
ዓይነት፡መከፋፈል፡እና፡መበጣበጥ፡ስለማንፈልግ፡በቃችሁ፡ወግዱልን፡ሲ ሉ፡ለምን፡አይታዩም?። ቸር፡ነገር፡ያምጣልን።

ሞገስ፡ታምሩ፣
ሰሜን፡አመሪካ።