Friday, March 1, 2024

ለፋሺሰት ትግሬ ምሁራን ዓድዋን በሚመለክት የተሰጠ መልስ ከጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay 3/1/24

 

ለፋሺሰት ትግሬ ምሁራን  ዋን በሚመለክት የተሰጠ መልስ

ከጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay

3/1/24

ሰሞኑን የዓድዋን በዓል አስመልክተው የትግሬ ፋሺሰቶች የትግሬ ነገሥታ አገር ወዳዶች አጼ ምኒሊክ ግን የጣሊያን ባንዳና “የአባት አገር” ፍቅር የሌላቸው  ናቸው (ተስፋኪሮስ የተባለ የታሪክ ምሁር ነው እንዲህ የሚለው- ገበታ ለሃሳብ ሚዲያ ቀርቦ የተናገረው፡፡ ሎቹም እንዲሁ ይላሉ) ከማለት አልፈው “ዓድዋ በትግሬዎች ግምባር ቀደም የተካሄደ የትግሬዎች ድል ብቻ ነው ፡ ትግሬ ባይኖር ጣሊያን ያሸንፍ ነበር እያሉ ሆኖም <<ምኒሊክ ባይኖር ጣሊያን ይገዛን ነበር>> የምትለዋ መራራ ሃቅ ግን ይደብቋታል፡፡ ፊደሉም፤ ድሉም፤ሃውልቱም ሁሉም የኛ ነው እያሉ በየሚዲያው ይለፍፋሉ። የትግሬ ምሁራን ሲዋሹ ደፋር ዋሾች ናቸው።ሲዋሹ  ወደ ላ አይሉም።

ዓድዋ ላይ ወራሪውን ፋሺሰት ጣሊያን ቅስሙን የሰበረው በምኒሊክ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር ነው ሲስሙ ያቃዣቸዋል። ሌላ ቀርቶ አፍቃሬ ወያኔ የሆነው ይሁዲው ሓጋይ ኤርሊክ አንኳ ሳይቀር “አሉላ” በሚል መጽሐፉ ላይ ራስ አሉላ ዓድዋ ውስጥ <<የተጫወቱት ሚና አይታወቅም>>ብሏል። ምክንያቱም አሉላ እራሳቸው፤ ከመተማ መልስ ፤ ጦራቸው የተበታተነ ፤ ምግብ የሌለው  የተመናመነ ጦር ይዘው ነበር ካገር አገር ከመንደር መንደር ሲዞሩ የነበሩት። ስለዚህ ታሪክ በታሪክነቱ ስንመለከት ዓድዋ የጋራ እንጂ የትግሬዎች ብቻ አይደለም።ትግሬዎች ብቻቸው ዓደዋ ላይ የማሽነፍ ብቃት ክነበራቸው ራስ መንገሻ ለምን እርዳታ ጠየቁ?

ምኒሊክን በባንዳነት መክሰስ የትግሬዎች በሽታ ሆኖ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ነው። እነሆ ዛሬ እዚህ ደርሰን እንደ አውነት ተወስዶ ዮሀንስና አሉላ አገር ወዳዶች፤ ምኒሊክ ግን አገር ፈቅር አልባ ተደርገው በባንዳነት ተስለዋል።

እስኪ ዶሴውን እንፈትሽ፡

ከመጀመሪያ እንጀምር፤

አጼ ዮሐንስ “በዝብዝ ካሳ” ከመባላቸው በፊት ከሽፍታነት ወጥተው ወደ ንግሥና ለመምጣት የተጠቀሙባት ሜላ >በባንዳነት< እንግሊዝን ማገልገል ነበር። አጼ ቴዎድሮስን ለመጣል የተጠቀሙበት የወንጀል ስልት ደራሲና ጋዜጠኛ አቶ ተክሌ የሻው “ሥልጣን ተሻሚ ትግሬዎችና የኢትዮጵያ አንድነት” መጽሐፍ (በገጽ 301 – 320) ስለአፄ ዮሐንስ ያሰፈሩት እንዲህ ይነበባል። “በዝብዝ ካሳ ምርጫ በንጉሠ ነገሥታቸው ዘመን ጊዜ ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝብ አብሮ መኖር ያበረከቱት መልካም ተግባር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ አለው። ቢሆንም የንጉሠ ነገሥት ዘውድ ከመቀዳጃቸው በፊት ወደ ሥልጣን ለመውጣትና ሥልጣናቸውንም ለማጠናከር ሲሉ የተከተሉት ዲፕሎማሲያዊ ወታደራዊና ሃይማኖታዊ መንገድ ግን በኢትዮጵያ ነፃነት አገራዊ አንድነት በሕዝቡ የአብሮነት ስሜትና ሰላማዊ የአገር ግምባታ ሂደት ላይ አፍራሽ ሚና ተጫውቷል። ለአብነት ያህል የሚከተሉትን የታሪክ ጭብጦች መጥቀስ ይቻላል።

በራስ ስሑል ሚካኤል መንገድ ጠራጊነት የተጀመረውን የኢትዮጵያን መከፋፈል፣ የንጉሦችን ሥልጣን፣ ተሰሚነትና ወሳኝነት ያደከመውን የዘመነ መሳፍንት አገዛዝ በጽኑ ኮንነው የኢትዮጵያን ጥንታዊ አገራዊነትና አንድነት አረጋግጠዉ የተነሱት አጼ ቴዎድሮስ፤ በናፒር በተመራው የእንግሊዝ ጦር ድል ሆነው፣ የራሳቸውም ሕይወት እንዲያልፍና ውጥናቸው ሁሉ ህልም ሆኖ እንዲቀር የአጥፊነት ተግባር ከፈጸሙበት አካባቢያዊ የጦር አበጋዞች ደጃዝማች ካሳ ምርጫ ግንባር ቀደሙ ናቸው።

በአጼ ቴዎድሮስ ላይ ያካሄዱት ዘመቻ ታሪክን ያላገናዘበ ታሪክን በኢትዮጵያውያን መሐል ጸንቶ የቆየውን ነባሩንና መልካሙን የጭንቅ ወቅት የትበብር ባሕል በመጣስ ከአውሮፓዊ ወራሪ ኃይል ጋር ተመሳጥረው በአገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም በሕዝቡ ሉዓላዊነትና ሰላማዊ የተከበረ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ደንቃራ የሆነ ተግባር የፈጸሙ መሆናቸውን በአሳዛኝ መልኩ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ነው።

ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች የተውጣጣውና በጀኔራል ናፔር የተመራው ጦር የደጃዝማች ካሣ ምርጫን የመረጃ መንገድ ምሪት፣ የውሃውንና የስንቅ አቅርቦት እንዲሁም የአገር ተወላጅ ተዋጊ ኃይል ድጋፍ ባይኖር ኖሮ የናፒየር ተልዕኮ የተለየ መልክ ሊይዝ ይችል እንደነበር አያጠያይቅም።” ሲሉ ገልጸውታል። (አቶ ተክሌ የሻው እላይ በተገለጸዉ መጽሐፋቸው ገጽ 298)

የላስታው ዋግ ሹም ጎበዜና የትግሬው ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ የአጼ ቴዎድሮስን ንጉሠ ነገሥትነት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ክብር፣ የሕዝቡን ነጻነትና ሉዓላዊነት ሊያዋርድና ሊገፋ ከመጣው የናፒየር ጦር ጋር ያደረጉትን ህብረት አቶ ተክለጻዲቅ መኩሪያም በበኩላቸው በእንዲህ ይገልጹታል።

<…በናፒየር የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ከህንድ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞ በጀመረበት ወቅት ቀደም ብሎ በቴዎድሮስ ላይ ካመጹት የላስታው ዋግ ስዩም ጎበዜ ይገኙበታል። የናፒየር ጦር ቴዎድሮስን ለመያዝ ከነዚህ ሰዎች ጋር ግንኙነት ፈጠረ፣ መንገድ በመምራት፣ ስንቅና ውሃ በማቅረብ፣ መረጃ በመስጠትም ተባበሩት። ይህም በመሆኑ የናፒየር ጦር በ1860 ከዙላ እስከ ሰንዓፈ ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ ወደ ውስጥ ሲገባ የገጠመው አንድም መሰናክል አልነበረም።

ጄኔራል ናፔር ሰንዓፈ ሆኖ ከትግሬና ከላስታ ሹማምንት ጋር ስምመነቱን ከፈጸመ በኋላ በእነሱ እየተረዳ ከሰንዓፌ በዓጋሜ እና በአሸንጌ በኩል አድርጎ በዋድላ አጠገብ ካለው ሳንሳራ ከሚባለው ቦታ ደረሰ…> (ተክለጻዲቅ መኩርያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ቴዎድሮስ እስለከ ቀዳመማዊ ኃይለ ሥላሴ-ገጽ 33) በደጃዝማች ካሳ ምርጫና በዋግ ሥዩም ጎበዜ ድጋፍ የናፔር ያላንዳች ችግር ከዘይላ የትግራይና የወሎን መሬት ሰንጥቆ ዋድላ ሲገባ፣ (ይድረስ ለጎጠኛው መምህር -ከጌታቸው ረዳ ሐምሌ 2002 ዓ.ም. 190)

“ጊዜ እንደ ንገሡ አዉድማ እንደ አግማሱ” እንዲሉ፣ በካሳ ምርጫ ፊታውራሪነት በተወጠነው መሠረት ቴዎድሮስንና ጥልቅና ሰፊ ራዕያቸዉን ለማዳፈን ያቆበቆቡ ግለሰቦችና ቡድኖች የወራሪዉ ኃይል አጋዥ ሆነው ተሰለፉ።

ላገሩ ባዕድ ለሕዝቡና ለባህሉ እንግዳ የነበረው የናፒየር ሠራዊት ባሕርና ውቅያኖስ አቋርጦና አሕጉር ሰንጥቆ መቅደላ መድረስንና ቴዎድሮስን ድል ማድረግ የቻለዉ በታጠቀው የጦር መሣርያ የበላይነት በወታደራዊ ቁጥርና ወታደራዊ ጥበብ ብቻ ሳይሆን ለአሸናፊነቱ ሰፊውን በር የከፈተለት ከብሔራዊ ጥቅምና የአገር ክብር በላይ ለግል ሥልጣን የቋመጠዉ ደጃዝማች ካሳ ምርጫና ዋግ ስዩም ጎበዜ የሰሩት የባንዳነት ተግባር እንደሆነ ታሪክ ተመራማሪዎች ይስማማሉ።

ደጃዝማች ካሳ ለናፔር ድል ላበረከቱት የአገርንና የወገንን ምስጢር አሳልፎ መስጠትና ተግባርና፤ ለቋመጡለት ሥልጣን መወጣጫ ዓይነተኛ መሰላል፣ ለተቀናቃኞቻቸው ቅስም መስበሪያ ይሆናቸው ዘንድ ናፒየር የጦር መሣሪያንና የወታደራዊ ጥበብ አስተማሪ ሰጥቷቸው መመለሱ ይታወቃል (12 ዘመናዊ መድፍ 900 የሚሆን ሰናድር ጠብመንጃና ሽጉጥ ከብዙ ጥይት ጋር ሰጣቸው። (ተክሌ የሻው 299)። (191 ይድረስ ለጎጠኛው መምህር ---ከጌታቸው ረዳ- ሐምሌ 2002 ዓ.ም.191 ) <<ሸዋዊ ብሔረተኛነትና በጥንታዊት ኢትዮጵያ ሃገራዊነት፣ ሉኡላዊነትና አንድነት አያምኑም።አንኮበራውያን ትምክሕተኞች ሸዋዊ ልዕልና የተረጋገጠበት ፤።… አንኮበር ላይ የመነጨውን ሥርዓታቸውን ለማስጠበቅና ህልውናቸውን ለዘላቂነት ለማረጋገጥም ከማንም የኢትዮጵያ ጠላትና ወራሪ ኃይል ጋር ግንባር ፈጥረው አገርን ለማስማማት ወደ ኋላ አይሉም። ይህም ካሁን በፊትም በታሪክ የተረጋገጠ ነው። በሌላ አነጋገር ትምክሕተኞች ሥልጣንና የበላይነትን ማዕከል ያደረገ ኢትዮጵያዊነትንና ሀገራዊ ስሜት ብቻ ነው ያላቸው ።>>(ገ/ኪ/ደ ገጽ 18)

ህዝብ የማንነት መግለጫ ነው። የትግራይ ህዝብ ታሪክ እንደሚያረጋግጠው ለኢትዮጵያዊነቱ፣ ለርስቱ፣ ለዳር ድንበሩና ለሀገራዊ ክብሩ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ይሰጣል።እንደ ትምክሕተኞች <<…ኢትዮጵያዊ ሀጋራዊነት በተግባር እንጂ በፉከራ በቀረርቶ በሽለላና በማስመሰል አይገለጽም። ኢትዮጵያዊ ሀገራዊነት የትግራይ ሥልጣን ለመጨበጥ ሲባል አንድ ክፍለ ሃገር ሙሉ ሸንሽኖ ለወራሪ ኃይሎች ገጸ-በረከት አያቀርብም። ለዚህም ነው አንኮበራውያን ትምክህተኞች ለኢትዮጵያ ሀገራዊነትና አንድነት ጸር ናቸው የምንለው።>> ገ/ኪ/ደ ገጽ 32 )

ገብረኪዳን ደስታም ሆነ እነ ተስፋኪሮስ፤ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም፤አክሱማዊው አታኽልቲ ሓጎሰ (የልጅንት ጓደኛ አብሮ አደግ ነበርን) ወዘተ የመሳሰሉ የፋሺሰት ትግሬ ምሁራን ከላይ ያነበብናቸውን ትምክህትና ውሸት በአማራው በተለይም “ሸዌ”፣ “አንኮበራውያን” እያለ በሚጠራቸው በሸዋ ህዝብ፣ መኳንንትና ንጉሥ ላይ ያነጣጠረ፤ ጸረ አንድነትና መርዘኛ የሆነ፤ ዘርን፣ ጎሳን፣ ቋንቋን መለኪያ በማድረግ ትግሬዎች ከኢትዮጵያዊነት ለመገንጠል ያላደረጉት ሴራ ትናንትም ዛሬም የለም።

የመንደርተኛነት አሉባልታና ክስ ስንፈትሽ ምኒሊክ የሰሩት ከጠላት መመሳጠር ዮሃንስም አሉላም፤ መንገሻም፤ደበብም ሁሉም ፈጽመውታል።ንጉሥ ዮሐንስም ሆኑ የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ መስዋዕትንና ጀግንነትን እንደፈጸሙ የሚጠራጠር ኢትዮጵያዊ የለም”።

ድሮ በምኒልክም ሆነ በትግራዩ ዮሐንስ ዘመነ መነግሥት የትግራይ ህዝብም ይሁን የሸዋ ሕዝብ አንድን ሰፊ ክፍለሃገር ከነ ወደቡ ፈርሞ ወድዶ ከ30 ሺሕ በላይ የትግሬ ወያኔ ተዋጊዎች ኤርትራ ምድር ኢትዮጵያ ወታደር እንዲዋጉ ተደርጎ (እንደ ትግሬዎች ለጠላት) ያስረከበ አናውቅም። ትግሬዎች መላዋን ኤርትራን ለኢሳያስ ሲያስረክቡት የትግሬ ሕዝብ በጭብጨባውና በዳንኪራው ተካፋይ ነበር። (ገጽ 196 ይድረስ ለጎጠኛው መምህር-ከጌታቸው ረዳ-ሐምሌ 2002 ዓ.ም. 196) በጥንት እና በቅርብ ታሪካችን የነበሩ ገዢዎች ሁኔታዎች ካቅም በላይ ሆኖባቸው ሁኔታዎች አላመች ብለውት ተገድደው ሆኖ እንደሆነ እንጂ እንደ “የወያኔ ትግሬዎች” ፈቅዶ ታግሎ ግምባር ቀደም የጠላት ጠበቃ በመሆን የአገር ሉዓላዊነት ለጠላት የሰጠ በታሪክ አልተመዘገበም። አለማፈር!!!

ኢስኪ ወደ ጣሊያኑ ጊዜ እንመለስ፡

ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር የማዋል ዕቅዱን በተግባር ለመተርጎም የተከተለው ስልት ሚሲዮናውያንን ወደ አገሪቱ አስሰርጎ በማስገባት በወንጌል ሰበካ ስም የሕዝቡን ባሕል ቋንቋና ታሪክ በማጥናት ለቅኝ አገዛዝ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ነበር። በዚህ ስልት መሰረትም ጁሴፔ ሳፔቶ የተባለዉ የላዛሪስት ሚሲዮን ባልደረባ ወደ ኢትዮጵያ ተልኮ ዓሰብ በመቀመጥ የአካባቢውን ሕዝብ ባሕል ቋንቋ ወግና ታሪክ በማጥናት መላ አገሪቱ የጣሊያን ቅኝ ተገዥ የምትሆንበትን ስልት ባሕል ወግና ስልት ያውጠነጥን ጀመረ። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ የአጼ ቴዎድሮስን ሞት ተከትሎ በተነሳው የሥልጣን ሽምያና ሽኩቻ ያስከተለው ጦርነትና መፋጠጥ የአገሪቱ ዳር ድንበር የሆኑትን ክፍሎች በተለይም ቀይ ባሕርና ወደቦቿ ደህንነታቸውን የሚጠብቅ ጠንካራ ማዕከል አጡ። ጁሴፔ ሳፔቶ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ “አብራሂምና ሐሰን መሐመድ” ከተባሉት የዓሰብና የራሒታ ሡልጣኖች አሰብን ገዛ።>> (ተክሌ የሻው 301)

የግዢውንም አፈጻጸም ተክለ ጻዲቅ መኩሪያ እንደዚህ ሲል ገልጸውታል።

<<…ጁሴፔ ሳፔቶ ግዢ እንዳረጋገጠ ወደ ጣሊያን ሃገር ሄዶ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ከበርካታ የንግድ ማህበር ፕረዚዳንት ከሆነው ሩባርቲኖ ጋር በመነጋገር ለወደቡ መግዣየሚሆነውን 8100 ብር ሰጥተው ላኩት። ጁሴፔም ዓሰብ እንደተመለሰ ከባሕር ወደ ዋናው የመሬት አካል ሰባት ኪሎሜትር የሚደርሰውን መሬት በ8100 ብር ሩባርቲኒ በሚባለው የንግድ መርከብ ማሕበር ስም ተፈራረሙ። በማግስቱ 21 ጊዜ መድፍ ተተኮሰ። የጣሊያን ባንዴራ ተሰቀለ >>። (ተክለጻዲቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአጼ ቴዎድሮስ ዕትም 1961 -55)

ይህ ከሆነ በኋላ ይላሉ አቶ ተክሌ የሻው “የሥልጣን ተሻሚ ትግሬዎችና የኢትዮጵያ አንድነት” ደራሲ “የጣሊያን መንግሥት አሰብን የገዛውና የራሱንም ባንዴራ የሰቀለ መሆኑን በወቅቱ ከነበሩት የሥልጣን ተሻሚዎች ይበልጥ ለደጃዝማች ካሳ ምርጫ የተደበቀ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ይቻላል። ምክንያቱም ድርጊቱ የተከናወነበት ቦታ ለእርሳቸው የሥልጣን መሰረት ከሆነው ክልል አቅራቢያ ከመሆኑም በላይ የባለቤታቸው አባት የዓፋሩ ባላባት በመሆናቸው ለመረጃው እሩቅ አያደርጋቸውምና ነው። ይሁን እንጂ ደጃዝማች ምርጫ ያሳዩት ተቃውሞ አልነበረም። ድርጊቱን በጸጋ ተቀብለውታል።>> (ተክሌ የሻው ገጽ 302)

ካሉ በኋላ፣ <<በዛ ወቅት የደጃዝማች ካሳ ምርጫ ትኩረት ያነጣጠረዉ በአሰብ መያዝና በእርሱም መረማመጃነት ወደ ፊት በመላ አገሪቱ ላይ ሊከተል የሚችለዉን አገራዊ ችግር ላይ ሳይሆን ….>> ይላሉ ደራሲዉ አቶ ተክሌ የሻው፤

<< አጼ ዮሃንስ አማቻቸዉን አጼ ተክለጊዮርጊስን ጠልፈው ከሥልጣናቸዉ ለመጣልና በቦታዉ ራሳቸዉን በመተካት በሚያስችላቸዉ ሁኔታ ላይ ብቻ ነበር። (ተክሌ የሻው -ከላይ በተገለጸው መጽሃፋቸዉ ገጽ 302) አጼ ተክለጊዮርጊስን አሰም ወንዝ ዳርቻ ጦርነት ገጥመው ድል በመንሳት ከአገር አንድነት ክብርና ብሔራዊ ጥቅም አብልጠው የቋመጡለትን ሥልጣን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ከጨበጡት በኋላም የጣሊያን መንግሥት ወታደር አምጥቶ ዓሰብ ላይ ሲያሰፍርም በመጀመሪያው ውል ያልተካተቱ ቦታዎችን ሲይዝ (ተክለጻድቅ መኩሪያ አስቀድሞ ከላይ ከተጠቀሰው መጽሃፍ ገጽ 57) የወሰዱት ዲፕሎማሲያዊ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ተቃውሞ አልነበረም (ተክሌ የሻው ገጽ 302) ሌላዉን የአጼ ዮሐንስ ጥፋት በመዘርዘር ሲቀጥሉ <በሌላ በኩል ግብጾች በ1863 በሙስንጅር ፓሻ መረታት ከምጽዋ አልፈው በጎስንና ሓባብን እንዲሁም በ1867 ዜይላንና ሐረርን ሲይዙ በአጼ ዮሐንስ በኩል የተወሰደ አገርን ከተስፋፊ ወራሪዎች የመከላለክል እርምጃ አልነበረም> (ተክለጻድቅ መኩሪያ አጼ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት ገጽ 111)

እነዚህ ድርጊቶች ሲጠቃለሉ በጉንደት፣ በጉራዕ፣ በዶጋሊ፣ በሳሓጢ፣ በዓድዋ፣ በእንዳባጉና፣ በተምቤን፣ በማይጨው በተካሄዱት ጦርነቶች የጠፋው ሕይወትና የወደመው ንብረት ከዚያም ወዲህ በቅርቡ ከ30 ዓመታት በላይ ለወሰደው ኤርትራን የመገንጠልና የማስገንጠል ጦርነት መነሻ ምክንያቱን የሚስበው አጼ ዮሐንስ ዓሰብና ምፅዋ በባዕዳን ተስፋፊዎችና ቅኝ ገዢዎች እጅ እንዲገቡ ዕድል ከሰጡበት ወቅት ጀምሮ ነው።ግብፆችም ሆኑ ጣሊያኖች ታሪኩን ባህሉንና ቋንቋውን በማያዉቁት ሕዝብ መሃል ገብተው የኢትዮጵያውያንን አንድነት በሚያናጋ፤ የሕዝቡን ነፃነት በሚጋፋ፤ ብሔራዊ ጥቅምንና መብቱን በሚያሳጣ ተግባር ላይ ተሰማርተው የራሳቸው ፍላጎት ተገዢና አራማጅ ለማድረግ ሌት ተቀን ሲጥሩ አጼ የሐንስ ይህን ተግባር ለመግታት አንድም እርምጃ አልወሰዱም (ተክሌ የሻዉ ገጽ 302) በጉንዲትና በጉሯዕ ጦርነት ድል የአጼ ዮሐንስ ቢሆንም>> ይላሉ አቶ ተክለጻድቅ መኩርያ << አስከ መጨረሻው ተዋግተው ራቲቭ ፓሻንና ልዑል ሐሰንን ከምሽጉ አውጥተው የግብፅን ጦር ከበጎስና ከሓባብ በማባረር ወደ ምጥዋ አልሸኙም። ምጥዋንም የኔ ነው አላሉም።>> (ተክለጻድቅ መኩሪያ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት ገጽ 146)

እንዲያውም ይላሉ ሲቀጥሉ በላይኛው መጽሃፋቸው በገጽ 149 <<እንዲያውም አጼ ዮሐንስ የጉራዕን ዕድል ሳይጠቀሙበት ወደ ኋላ በመመለሳቸው ራቲቭ ፓሻ ከምሽጉ ወጥቶ ሓማሴንን ለመያዝ ሁለተኛ ዕድል ተሰጠው>>። (146)

በበኩላቸዉ አቶ ተክሌ የሻዉም እንዲህ ሲሉ አክለውበታል <<አጼ ዮሐንስ ባገኙት ወታደራዊ ድል ተጠቅመዉ ወደ ፊት ተጉዘዉ ግብፆችን ከቦጎስና ሓባብ በመጨረሻም ከምፅዋ ለመገፍትር ያለመሞከራቸው መሰረታዊ ምክንያት እርሳቸው ወደ ፊት ከዉጭ ጠላት ጋር ሲጋፈጡ፤ ከመሃል አገር ባሉ የሥልጣን ተሻሚዎች ሥልጣኔን እነጠቃለሁ የሚለው ሥጋታቸው በማየሉ እንደሆነ ይታመናል>>። (ገጽ 203 ይድረስ ለጎጠኛው መምህር ---ከጌታቸው ረዳ----- ተጻፈ ሐምሌ 2002 ዓ.ም.) አቶ ተክሌ የሻው ለዚህ ማጠናከሪያ ማስረጃ ሲጠቅሱ <<የዚህም ማረጋገጫው በወቅቱ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ሆነው በመላ አገሪቱ ላይ ለመንገሥ የአካባቢው የጦር አበጋዞችን ከጎናቸው ለማሰለፍ በመጣር ላይ መሆናቸው ለአጼ ዮሐንስ የተሰወረ ስላልነበረ፤ እሳቸውም በበኩላቸው የወሎን፣ የቤጌምድርን፣ የየጁን፣ የጎጃምን፣ የላስታንና የሰሜንን ባላባቶች እና የጦር አበጋዞች ታማኝነት ለማግኘት በትጋት ይራወጡ እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው። እራሳቸዉ ይህን በማድረጋቸው አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም ላይ ተጻራሪ የሆነ ሥራ ሰሩ፤ ዛሬ በኢትዮያ ሰላም ላይ ደንቃራ የሆኑ ችግሮች ዘራቸውን ዘርተው ብቅለታቸውን የጀመሩት በአጼ ዮሐንስ አመራር ነው።ከፍ ብሎ እንደተገለጸው አጼ ዮሐንስ ከጉንዲት ድል በኋላ ወደ ፊት ገፍተው የግብፅን ጦር ገፍትረው ምፅዋን ለመቆጣጠር ያልሞከሩበት ሁለተኛው ምክንያት፣ ከሌሎች መንግሥታት ጋር ጦርነት ይፈጥራል በሚል ስጋት እንደሆነና ጉዳዩን ዓዲዃላ ሁነው ከመኳንንቶቻቸው ጋር መክረው ወደ ፊት ከመግፋት ይልቅ ወደ ኋላ መመለስ እንደሚሻል በማመናቸው ነበር። ዓድዋ እንደገቡም ለግብፁ እስማኢል በቀድሞው ወሰኑ (ቀደም ብሎ በያዛቸው የኢትዮጵያ መሬቶች) እንዲረጋ የሚማፀን ደብዳቤ ልከዋል።

አጼ ዮሐንስ ለእስማኢል በጻፉት ድበዳቤ ካሰፈሯቸው ሃሳቦች መካከል አቶ ተክሌ የሻው ሲገልፁት <<በቀድሞው ወሰንህ ቁም>> የሚለው አሳባቸውን ሲያብራሩ <<በጎስና ምፅዋን ፈቅጄልሃለሁ>> የሚል ቀጥተኛ ትርጉም የሚሰጥ ነው። ይህም አጼ ዮሐንስ የጠቀሱዋቸው የአገሪቱ ቀይ ባሕር ቦታዎች ተገድደው ሳይሆን ፈቅደው ለግብፅ የለቀቁ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

በሌላ በኩል በ1871 የሱዳን ገዥ የነበረዉ ጀኔራል ጎርደን በግብፅና በኢትዮጵያ (ከዲቭ እስማኢልና አጼ ዮሐንስ አራተኛ) መካካል የተፈጠረውን ጠብ እንዲያበርድ በእስማኢልና በእንግሊዝ ተወክሎ ወደ አጼ ዮሐንስ ተላከ፤ ጀኔራሉም ወደ ደብረታቦር ሄደ፤ በግብፅና በእንግሊዝ በኩል ያለዉን ሃሳብ ለአጼ ዮሐንስ በማስረዳት ከግብፅ ጋር እንዲስማሙ አግባቧቸዉ። አጼ ዮሐንስ የጄኔራል ጎረዶንን ሃሳብ ካዳመጡ በኋላ ያላቸዉን ፍላጎት እንደሚከተለው ገለጹ፣ ይላሉ አቶ ተክሌ የሻው <<…ከሱዳን ወሰን አካባቢ ያሉት ጋላባት፣ መተማ፣ ከረን፣ በምጥዋ አካባቢ የሚገኙት ሓባብና በጎስ ሰሓጢና ዶጋሊ…የኢትዮጵያ ታሪካዊ ግዛቶች ናቸው። ለኔ መመለስ አለባቸው አላሉም። (ተ/ጻ/መ አጼ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት ገጽ 239

አቶ ተክሌ የሻውም እንዲሁ ሲያክሉበት፣- <<ቢሆንም ምጽዋን የኢትዮጵያ ታሪካዊ ተፈጥሮአዊና ባሕላዊ በር (መዉጪያ መግቢያ) አንስተው ለእኔ ይገባኛል የሚል ጥያቄ ለጄኔራል ጎርደን አላቀረቡም። ይህም አጼ ዮሐንስ አራተኛ ምፅዋ የኢትዮጵያ አካል አለመሆንዋን አምነው የተቀበሉና ለግብፅ ፈቅደው የሰጡ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ታሪካዊ ጭብጥ ነው።>>

በተመሳሳይ ንጉሡ (አጼ ዮሓንስ) ከእንግሊዞች ጋር ያደረጉት ውል ዘርዘር ባለ ሁኔታ የታሪክ ባለ ሞያው አቶ ተክለጻዲቅ መኩርያ መዝግበዉታል፣

እንዲህ ሲሉ፡

<<በተመሳሳይ-ሁኔታ መሐዲስቶች ጦር ከሰላና ጋላባት ላይ የተከበበውን የግብፅና የእንግሊዝ ጦር ለማስለቀቅ ሲባል እንግሊዞች ባደሩት/በሰሩት ተንኮል፣ ድርና በሸረቡት ሴራ መሰረት “የሄዊት ስምምነት” የተባለው ውል በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካካል ግንቦት 26 ቀን 1876 ዓድዋ ውስጥ መፈረሙ ይታወቃል። እኤአ ሜይ 28 እና 31 ቀን 1884 አጼ ዮሐንስና ሪር አድሚራል ሄይዊት በመሸሻ ወርቄ አስተርጓሚነት ባደረጉት ዉይይት በአጼ ዮሐንስ በኩል የቀረቡት የስምምነት ሃሳቦች፡

1- ከሰላ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እንዲጠቃለል

2- በምፅዋ ወደብ ከሚሰበሰበው ቀረጥ ከግብፅ ዕኩል የመከፋፈል መብት ይኑረኝ የሚል ነበሩ።

አጼ ዮሐንስ ወደቡን ወይንም መሬቱን ምፅዋን ሳይሆን ቀረጡን ከማይመለከታቸው ወገኖች ጋር ለመካፈል ላቀረቡት "ከእጅ አይሻል ዶማ" የልመና ሃሳብ አድሚራል ሔዊት የሰጠው መልስ የሚከተለው ነው፡

1- ከሰላን እንዲወስዱ ለመፍቀድ ከመንግሥቴ ሥልጣን አልተቀበልኩም

2- የምፅዋን የገቢ ቀረጥ በተመለከተ ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልካቸው

ሸቀጦች በነፃ እንዲያልፉ ከማድረግ ውጭ ከቀረጡ ገቢ የመካፈል ፍላጎት ጨርሶ የማይታሰብ እንደሆነና አጼ ዮሐንስ የቀረጥ ገቢ ከፈለጉ ከምፅዋ ወደብ ወደ መሃል ኢትዮጵያ አልፎ ወደ ራሳቸው ግዛት የሚገባውን ሸቀጥ ኬላ በማቋቋም መቅረጥ ይችላሉ የሚል ነበር >>(ተ/ጻድቅ መኩሪያ አጼ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት 269)

አጼ ዮሐንስ ያቀረቡት የድርድር ሃሳብ ደካማ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን የባለቤትነት የድርድር የኢትጵያን የባለቤትንትን መብት ለግብፅ አሳልፎ የሰጠ በመሆኑ ያቀረቡትን እጅግ በጣም ትንሽ የቀረጥ ክፍያ መታሰብ እንደሌለበት ሔዌት ከማስገደዱም በላይ ኢትዮጵያ ወደ ዉጭ የምትልካቸውን ሸቀጥ በነፃ የማስወጣት ዕድል እንዲኖራቸው አላነሳም። ንጉሡም መጠየቃቸው አልተመለከተም። የኢትዮጵያ አንድነትና የሥልጣን ተሻሚ ትግሬዎች መጽሃፍ ደራሲ አቶ ተክሌ የሻው በመጽሐፋቸው <<ከሔዊት ስምምነት መንደርደርያ ሃሳቦች መገንዘብ የሚቻለው ምንም እንኳን በዚያን ወቅት ቀርቶ ዛሬም በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የዲፕሎማሲ ጥበብ ቴክንዮሎጂና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሰፊ ልዩነት ያለው መሆኑ ቢታወቅም በሃሳብ በዕምነትና በፍላጎት ደረጃ እንኳን አጼ ዮሐንስ 'ምፅዋ የኢትዮጵያ ናት፣ ወደ ኢትዮጵያ መጠቃለል አለባት፣ በምፅዋ ለሚገባውም ሆነ ለሚወጣው ሸቀጥ ቀረጥ ብቸኛ ባለቤት ኢትዮጵያ ልትሆን ይገባታል፣’ አለማለታቸው ምፅዋን ለግብፅ ወደው መስጠታቸውን የሚያሳይ ነው>> በማለት አንድምታውን ያቀርባሉ።


እንግዲህ አንባቢዎች እንዲገነዘቡት የምፈልገው ዮሃንስ መተማ ባይሄድ ኖሮ ዓድዋ ኤኢከሰትም ነበር፤ ዮሃንስና አሉላ  ተሞዳማጅ አልነበሩም ምኒለክ ግን ወደብና መሬት አሳልፎ የሚሰጥ ነው እያሉ የትግሬ ምሁራን ሁሌም የሙጥኝ የሚሉት የውሸት ፕሮፓጋንዳቸው ልብ አንድትሉት ነው።

ትግራዋይ/ወገኔ የሚሏቸው አጼ ዮሐንስንና አሉላን እንከን የሌላቸው ንጉሥ አድርገው ግማሽ ታሪካቸውን በመደበቅ በጎ፣ በጎ ሥራቸውን ብቻ በማድመቅ፤ ታሪክ ይደፍራሉ።

(ጌታቸው ረዳ ሐምሌ 2002 ዓ.ም. ገጽ-209)

ከላይ እንደተመለከትነው የንጉሥ ዮሐንስ ደካማነትና የንጉሥ ምኒልክም ዳካማ ጎን ተመሳሳይነታቸው ዕኩል መሆናቸውን ለማሳየት ነው። ሁሉም ያችን ሥልጣን አንዴት ልቆናጠጣት በሚል እሳቤ እንጂ አገርን በመክዳት አይደለም፤፡ አገርን በመክዳት ከሆነ ራስ አሉላ እጅግ አደጋ ጎጠኛ እና ጸረ አማራ ሸዋ ተገንጣይ ነበሩ። በዚህ ላይ አዲሱ ትውልድ በወያኔ ካድሬ ጸሓፍቶች እንዳይሳሳቱ ማገናዘቢያ እንዲሆን በማስብ ነው - በዚሁ እንቀጥል።

የትግሬ ፋሺት ምሁራን እንዲህ ይላሉ፦

<< ዮሐንስ የትግራይን ሕዝብ አስታጥቀው ድምበሩንና እራሱን ከጠላት ጥቃት እንዴት ሲጠብቅ እንደነበረና፣ አፄ ምኒሊክን ግን ጸረ ትግራይ እንደነበሩ በማይታይና በማይዳሰስ ማስረጃ ሲወነጅሏቸው እንዲህ ይላል፣

<< በኤርትራ በኩል ወደ ትግራይ (የመሳርያ ትጥቅ) እንዳይገባ አጼ ምኒልክና ኢጣሊያ እገዳ አድርገውበታል። ስለሆነም የትግራይ ሕዝብ ትጥቅ መፍታቱን እገዳ አደርገው የሚወጉት ጠላቶች እንጂ፣ ትጥቅ እሚያስታጥቅና አለሁልህ የሚለው የራሱ መንግሥት አልነበረውም>> ይላሉ።

ከመነሻው ንጉሥ ምኒልክም ሆኑ ዮሐንስና ተከታዮቻቸው የመሳርያ ትጥቅ የሚያገኙት ሌላውን ተቃዋሚ ወገናቸውን በባዕድ ጦር በማስገደል/በማዳከምወይንም በማስወገድ/ወይንም ምስጢሮችንና ብሔራዊ ጉዳዮችን ድምበሮችን ለጠላት ክፍት እንዲሆኑ እንዲሁም በብሐራዊ ጥቅሞች ላይ በመደራደር መሳርያ ከሚያመርት የውጭ ጠላት ጋር በመመሳጠር፣ በመተዋወቅ፣ በመወዳጀት እንደነበር ከሞላ ጎደል በታሪክ የተዘገበ ነው። መሳሪያውንም የሚፈልጉት አስቀድሜ እንደገለጽኩት የውስጥ ሥልጣን ተሻሚ፣ ተቀናቃኛቸውን ለማዳከም/ለማጥፋት እንጂ የውጭ ጠላት ለመምታት ቀዳሚ ዓላማቸው እንዳልነበረ የታወቀ ነው።ተቀናቃኛቸዉን ለማዳከም ደግሞ በአካባቢው መሳርያ እንዳይኖር/እንዳይባዛ በማድረግ ሲጠቀሙበት የነበረው ሌላው ስልት ነበር።

ይህ ስልት በሁሉም ነገሥታት/ገዢዎች የታየ በመሆኑ በንጉሥ ምኒልክ ልዩ የሚሆንበት መንገድ የለም። ዛሬም ወያኔ ተቀናቃኝ ቡድኑን ለማስፈታት መሯሯጡ ብቻ ሳይሆን ጭራሽኑ ህዝቡ መሳርያ እንዲፈታ በሕግ አዉጇል። መሳርያ የመታጠቅ መብት ያለው ቡድንና ግለሰብ ወያኔና የወያኔ አጃቢ እንደሆነ ከዛሬው እውነታ መረዳት ይቻላል። ነገሥቶቹ ትጥቅን ሲያስፈቱና ሲያስታጥቁ በነበረው የወቅቱ የቀማኛ ብዛትና ጥንካሬ ወይንም ያካባቢው ተወላጅ አልገዛም ባይ አፈንጋጭነት ሁኔታዎች ላይ በመመርኮዝ ነበር እንጂ፣ ትጥቅ ሲያስፈቱ ገብረኪዳን ደስታና መሰል ወያኔዎች እንደሚያምታቱት ሆን ብለው አገርን ለመክዳት በሚል ዓላማ ተነሳስተው ግን አልነበረም። ባካባቢው ተቀናቃኝ ብቻ ሲያቶኩሩ በኋላ የሚያስከትለውን ሰበብ ባለማወቅ ብሔራው ሉዓላዊነት እሚባሉ ትላልቅ ክብሮች ከጊዜ በኋላ ቀስ በቀስ ሲነኩ የምንገነዘበውም በዛው ምክንያት ነበር።

ነገሥታቱ <<አምላክ እንድገዛው የሰጠኝን ግዛቴን…>> ሲሉ የሚነበቡት ህዝባዊ እሴት ሳይሆን ተባርኮ ከሰማይ የተሰጣቸው የግላቸው ንብረት እንደሆነ ስለሚያዩት ለሥልጣናቸው ሲሉ በሕዝባዊ እሴቶች ላይ ማለትም ለምሳሌ በሉዓላዊነት ከጠላት ጋር ሲደራደሩ እናያለን።

ከሁኔታው.የምንረዳው“ሥልጣናቸውን እስካላረጋገጡ ድረስ ለሕዝብ፤ለድምበር፤ ለአገር ሉዓላዊነት ክብርና መከላከል፣… ለመሳሰሉት ቅድሚያ አይሰጡም (ወያኔ ከሱዳንና ከኤርትራኖች ጋር የደረጋቸዉን ድርድሮች ተመልከት)። ንጉሦቹ ሲነጋገሩ፣ ሲጽፉ ስለራሳቸው ግል ንብረትና ሥልጣን በዋናነት ባዛዥነትና ናዛዥነት አምላክ የሰጣቸው ንብረት፣ መሬት መሆኑን አንጂ ሕዝቡ ይጎዳል ወይንም አገር ይበታተናል፣ የሚል ቅድሚያ አስተሳሰብ የላቸውም። በትግሬ ፋሺሰቶች ክስ መሰረት ምኒልክ ወደ ትግራይ መሳርያ እንዳይገባ ትገሬን ለመጨፍለቅ ነው የከለከሉት የሚሉትን ውንጀላ ስንመለከት መሰረት የሌለው ክስ ነው።

መሳርያ የማስገባትም የማስወጣትም ሥልጣን ጣሊያኖች እጅ ነበር። ዮሐንስ የተደራደሩት ውልም ከዛ የተነሳ ነበር። ወደቡም፣ ሥልጣኑም አልነበራቸውም። ሁሉም መሳፍንቱም ሆኑ ነገሥታቱ አምሃ/እጅ-መንሻ በመስጠት ነበር መሳርያ የሚያገኙት። ለምሳሌ ዮሐንስም፣ ልጃቸው ራስ መንገሻም ሁሉም ገጸ በረከት በመስጠት ነበር መሳሪያዎቻቸውን ከሚያገኙበት አንደኛው ዘዴያቸው። ለምሳሌ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ያባታቸውን የወርቅ ኮረቻ ለባዕዳን በስጦታ እያበረከቱ ጦር መሳርያም ይሁን እውቅና የሚያገኙትና የሚያድጉት የነበር።

አጼ ዮሐንስ በገዛ ወደባቸውና መሬታቸው/አገራቸው መሳሪያ ሲያገኙ በእንግሊዝ (ስር) መልካም ፈቃድና ቁጥጥር ነበር። ምኒልክም እንዲሁ ነበሩ። ለምሳሌ የአጼ ዮሐንስን ውል ስንመለከት

<<ይህ ውል ከታተመበት ቀን ዠምሮ በምጥዋ ወደ ሓበሻ የሚገባ ከሓበሻም የሚወጣ ዕቃ ሁሉ የመሳርያ ነፍጥና መድፍ ጥይትም ቢሆን በእንግሊዝ ውክልና ነጻ እንዲወጣና እንዲገባ ተፈቅዷል>> (አጼ ዮሐንስና የኢትጵያ አንድነት ገጽ 370)

ዮሐንስ ራሳቸው የሚያስገቡት መሳርያ በእንግሊዝ ችሮታ እንደነበር። መሳርያ ቀርቶ የፍጆታ ዕቃም ቢሆን ፈቃጁ እንግሊዝ ነበር። ንጉሡ በውክልና ያወቁትም ጠላት የሚባለው እንግሊዝ ነው። ሳልጠቅስ የማላልፈው ከላይ ባየነው ስምምነት ላይ አንድ ነገር ልጨምር

<<ይህን ውል የተረጎመው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ>> ይላሉ አቶ ተ/ጻ/መኩርያ በተጠቀሰው ገጽ <<ከአማርኛ ትርጉም ግርጌ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ቃል አስፍሯል >> ካሉ በኋላ ተርጓሚው የተወልንን ማሳሰቢያውም አነሆ፤

<<ማሳሰቢያ - ይህ ውል በታተመ በስድስተኛው ወር እንግሊዞች ምጥዋን ለጣሊያን ሰጡና ውሉን አፍርሰው አጼ ዮሐንስን አዋጉዋቸው። አጼ ዮሐንስ ግን በውላቸው ቁመው ከድርቡሾች ጋር እየተዋጉ በሱዳን የተከበበውን የምስር ወታደር ወደ አገሩ አስገቡት>> (271)

እንግዲህ ዮሐንስም ሆኑ ምኒልክ በገዛ ወደባቸውና ሃገራቸው በጥገኝነት ተማምነው የሚቸሩላቸውን መሳርያ እየተቀበሉ እርስ በርስ ሲቀናቀኑ እንደነበር እየታወቀ ምኒልክ ለትግራይ ሕዝብ መሳርያ ከለከለ፣ ማለት ሚዛንን ያልጠበቀ ፍርድ ነው። ቢያደርጉም ለሥልጣን ሲሉ ነገሥታቱ ያላደረጉት ነገር አልነበረምና በሸዋው ንጉሥ ብቻ ልዩ ሊሆን አይባገም ማለቴ ነው።

የአባት ኮርቻ ለጠላት

የወያኔዎች ሴራ ከትናንት አስከ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያን ህልውናና ክብር የሚነካ አደገኛ ቅጥረኛ ሴራዎቹ ያደረሳቸው ጉዳቶች ተዘርዝሮ እንደማያልቅ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ይስማማሉ። አለመታደል ሆኖ አገሪቱ ጦር ባነገቱ ልበ ቢሶችና ለሥልጣን በሚቋምጡ ቡድኖች እየተመራች ሕዝቧ ለስቃይ ተዳርጓል። በጣም አሳዛኙ ነገር፣ የዛሬው የወያኔ መንግሥት ተብየው በመዋሸት እጅግ የተካነ በመሆኑ፣የዋህ ዜጎችን በማሳሳት አንዳንድ ተከታዮች አላጣም።

ከሚዋሻቸው መርሆዎቹ አንዱ፣ ከነበሩት ነገሥታት በተለይም ቀንደኛ ጠላቴ ብሎ ከሚጠራቸው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነገሥታትን ከጠላት ጋር ይሞዳሞዳሉ እያለ ሲከስ የትግሬ መሳፍንትና ነገሥታት ግን አገር ወዳዶች እያደረጉ በመሳል በየሚዲያው ሰሞኑ እየተረባረቡ ናቸው።በዚህ ምዕራፍ ለአንባቢያን ግልጽ እንዲሆን በማስረጃ አስደግፌ ላቅርብ። ልመሳልይ የገብረኪዳን ደስታ በመጽሐፉ በገጽ 3 ያለውን ስንመለከት <<….የግብጽና የኢጣሊያ ወራሪዎች ፖለቲካዊ ሥልጣን ከአጼ ዮሐንስ እጅ ወጥቶ ወደ ምኒልክ ካልተዛወረ በስተቀር በሰሜን ኢትዮጵያ ቅንጣት መሬት መቆጣጣር አይቻልም ማለታቸው ያለምክንያት አይደለም>> ይላል።

ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት በሚል የአቶ ተክለ ጻድቅ መኩርያ መጽሃፍ እንዲህ ይላል

<<…ከአንቶኖሊ መመለስ ወዲህ የኢጣሊያኖች አያያዝና የራስ መንገሻ የጀኔራል ጋንዶልፊ የመረብ ላይ ስምምነታቸው እንዲህ ይነበበባል

<<የኢጣሊያ አገር ጠቅላይ ሚኒስቴር ፍራንቼስኮ ክርስፒ ተሽሮ ማርኮዚ ዲሩዲኒ አንቶኒዮ ሰትራባ ተሹሞ ነበር። እርሱም አጭር ጊዜ እንደሰራ ተሽሮ እ ኤ አ ግንቦት 15ቀን 1892 ዓ.ም ጄዎቫኒ ጃዎለቲ ጠ/ሚ ከተመለሱ ወዲህ፣ የኢጣሊያ ባለሥልጣኖች በኤርትራ የሚገኙ ወኪሎቻቸው ምኒልክ በፊት የሸዋ ንጉሥ በነበሩ ጊዜ ገራገር፣ የዋህና የጣሊያኖችን ወደጅ የነበሩ፣ አሁን የንጉሠ ነገሥት ዘውድ ሲጭኑ ተለውጠው ጥብቅና ክፉ ሆኑ። የቀድሞውን የኛ ወዳጅነት ትተው ጉዳያቸው ከተሟላና የጦር መሳሪያ ከሰበሰቡ በኋላ ከፈረንሳይና ከመስኮብ መንግስታት ይወዳጁ ዠመር። ይህን ለማድረግ የሚገፋፉዋቸው ጠላቶች የሆኑትና አዲስ አበባ የሚቀመጡት የፈረንሳይ የስዊስና የሞስኮ ተወላጆች ናቸው።>> እያሉ ያሙ ዠመር።

ቀጥለውም አቶ ተክለጻድቅ ዶ/ር ትራቪሰቲ ስለ ምኒልክ የተቸበትን በቅንፍ እንደሚከተለው ዘግበውታል።

<<ሁልጊዜ የሸዋን ሐቀኝነት እጠራጠር ነበር። ምኒልክ አሁን የፈለጉትን አግኝተዋል። ለኛ በመልክ ውበት መለዋወጥ የሐበሻ ጠባይ የሚለወጥበት ምክንያት የለም። በሟቹ ንጉሥና ባሁኑ ንጉሠ ነገሥት መካከል ልዩነት የለም። በመካከላቸው ያለው ልዩነት ይኸኛው ዮሐንስ ይኸኛው ምኒልከ በመባል የስያሜ ልዩነት ብቻ ነው።>> ሲል ጽፋል። (Let-Marefia –L Travesi P.38)

ትግሬም ሆነ ሸዋ በኢጣሊያኖች ፊት የሁለቱም ነገሥታት ኃጢያት የኢትዮጵያን ወደብና አውራጃ ስንወር፣ ወሰናችን እስከመረብ ይድረስ ስንል ለምን ዝም ብለው አይመለከቱም? ለምንስ ይከራከራሉ ነው፤ የጣሊያኖች ቁጣ። ለዚህም አቶ ተከለጻድቅ መኩሪያ ከላይ በጠቀስኩት መጽሐፋቸው በገጽ 113 ስለ ነገሥቶቻችን ባሕሪ በግል እንዲህ ሲሉ ያስቀምጡታል።

<< ባለሥልጣኖቹ አንድ ጊዜ እርስ በርሳቸው የተጻጻፉበት ሰነድ ዛሬ ሲነበብ በእነርሱ ዘንድ እገሌ የሚባለው ራስ ወይም ደጃዝማች ኢጣሊያንን ይቃወማልን? >> በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አንዱን ወኪሉን ሲጠይቅ ወኪሉም አዎን ብሎ ሲመልስ፣ ትርጓሜው ይሄ ራስ ወይንም ደጃዝማች - ኢጣሊያ አንዱን አውራጃ ቆርሳ ብትወስድ መላውን አገር ብትወርስ ዝም ይላል? በዚህ የተነሳ የኢጣልያ መንግሥት ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ እኛ ዞሮ ሊሰለፍ ይችላል? የሚል የቂል ስሜት ነው። እገሌ ጣሊያን አይወድም ፣ ሲሉ አገሩን ብንወርር ሊወጋን ይችላል >>(ተ/ጻ/መ ገጽ 113-114 አስቀድሞ ከላይ ከጠቀስኩት መጽሐፋቸው)

እንግዲህ ይህን ስንመለከት ወያኔ የተባለው ጸረ ታሪክ እና የትግሬ ምሁራን የተባሉት የፋሺሰት ተውሳኮች የሌለ የማይመስል ወሬ እየጻፉ፣ የተደረገውንም ታሪክና ድርጊት በትክክል ከመጻፍ ይልቅ እያጣመሙ ለራሳቸው ለዘረኞቹ እንሚያመች በማቅረብ ሰውን ለማሳሳት መመኮራቸው አሳዛኙ ድረጊት ቢሆንም፣ ከነሱ የሚጠበቅ ነውና እንደ አመጣጣቸው የተደረጉትን ትከክለኛ ድርጊቶች በማቅረብ የተዛባ ሕሊናቸው የሚስተካከልበትን መፈለግ የሁላችንም አገር ወዳዶች ኃላፊነት ነው።

ለማጠቃለል፤

የሸዋ ነገሥታትንና መኳንንትን በተለይም ምኒልክን ትምክህተኛ፣ ከሃዲ፣ ጸረ-ትግሬ በማለት የዚህ የዛሬ አመት የዓድዋን በዓል ተንተርሰው ሥራ ፈት የወያኔ ምሁራን  በተለያዩ ሚዲያዎች በመወንጀል ምኒልክን ለመሳርያ ሲሉ ከጣሊያን አገር እየተመሳጠሩ የአገርንና የሕዝቡን ነፃነት ለሥልጣን ሲሉ በስጦታነት ለማበርከትም ሆን ብለው ፈቅደው የዉጫሌን ውል ተዋውለው በመፈረም ያገሪቱን ክብር ሸጠዋል በማለት ይከስዋቸዋል።

እንደሚታወቀው ጣሊያኖች ምኒልክን የውጫውን ውል አሳስተው በብልጣብልጥነት የዋሁን ንጉሥ ለማታለል ሞክረው በማታለልም ለነሱ እንደሚመች አድርገው እንደተረጎሙት ይታወሳል። ይህም ምኒልክ የኋላ ኋላ ተንኰሉ ስለገባቸው ውሉንም ስላልተቀበሉት በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ ይኖሩ የነበሩት እነ አንቶኖሊ የተባሉ ተወካዮቻቸው የጣሊያንን ተንኮል እውን ለማድረግ በገንዘብ በመደለል፣ በማግባባትም ይሁን በማስፈራራት ቢጥሩም አልሆን ስላላቸው ተስፋ ቆረጡ። “በዚህም እነ አንቶኖሊ ወደ አገራቸው እንደተመለሱ አስቀድመው…” ይላሉ አቶ ተክለጻድቅ መኩርያ በ“አጼ ዮሐንስና የኢትዮያ አንድነት” መጽሃፋቸው <<…አንቀጹ ካልጸደቀ መንገሻና አሉላ ቢሸፍቱብዎ መደገፍ አይቻለንም… >> እያሉ ያስፈራሩበትን አሳብ እነርሱም ራሳቸው መሳፍንቱን ማሸፈቱን በሥራ ለመተርጎም ሚኒስትር መሥርተው ተነሳሱ።

በነዚህ ከኢትዮጵያ በተመለሱት ወኪሎችና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀነባብሮ የኢጣሊያኑ ንጉሥ ኡምቤርቶ በአጼ ምኒልክ ላይ ለማስነሳት ከመደባቸው ውስጥ ለዋናውና ለቀንደኛው ለራስ መንገሻ፦

<<ማናቸውንም የሚያስፈልገዎትን ነገር ምጥዋ ወዳለው የበላይ ሃላፊያችን ቢልኩ ይከናወንለዎታል >> የሚል ደብዳቤ በሰው እጅ በመላክ ራስ መንገሻን ለማሸፈት መቀስቀስ ዠመረ። እርሳቸውም የአጼ ዮሐንስ አልጋወራሽነት ከልባቸው ስላልጠፋ ነገሩን በደስታ ተቀብለው መልስ ሰጡ። እነ አንቶኖሊ በየካቲት ወር የስንብት ደብዳቤ ጽፈው ወደ አገራቸው እንደተመለሱ፣ ቀድሞ ምኒልክን በአጼ ዮሐንስና በኢጣሊያኖች ጠብ አስታከው የተጠቀሙበትን አሁን ደግሞ ራስ መንገሻን በፈንታቸው በምንልክና በኢጣልያኖች ጠብ አስታከው ለመጠቀም ሲሉ በሐምሌ ወር መዠመሪያ ላይ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ከአፄ ምኒልክ ደብቀው ከጣሊያን ንጉሥ ለመጣላቸው ደብዳቤ መልስ ሰጡ። ደብዳቤውም እንዲህ ይላል።

<<በእግዚአብሔር ቸርነት በአገር ፈቃድ የንጉሥ 1ኛ ኡምቤርቶ የኢጣሊያን ንጉሥ…እኔ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ደህና ነኝ። ባለፈው መልክታችሁ አንድ ነገር ከኔ ብትፈልጉ ምፅዋ ወዳለው ወደኔ ሹመኛ ጸሐፊ አመልክቱ ብላችሁ ጽፋችሁልኛል። ልዑል ሆይ ከናንተ ፍቅር ለማድረግ ነው እንጂ ሌላ ነገር የምፈልገው ነገር የለኝም። ፍቅራችሁም ለዘላለማዊ ፍቅር እንድትሆን በልቤ ያለ ቅን አሳቤን በዚሁ ደብዳቤ እገልጽላችኋለሁ።ነገር ግን እኔ የምፈልገው ፍቅራችን ለጊዜው ብቻ አይደለም።ለትዉልድ ትውልዳችን እንድትሆን ነው። እንደ ሃሳቤም ሊሆንልኝም ተስፋ አለኝ (ሐምሌ 6 ቀን 1882 ዓ.ም)>> (አቶ ገብረሚካኤል ጉርሙ ያጠናቀሩት በዩኒቨርሲቲ የጥናት ክፍል ቁ-344 - (ተ/ጻ/መ)

ለላይኛው ድብዳቤ መልስ ከንጉሥ ኡመቤርቶ ለራስ መንገሻ ዮሐንስ የተጻፈ እንደሚከተለው ይነበባል።

<<ራስ መንገሻ የንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ልጅ ጤና ይስጥልኝ። የጻፉልኝ ድብዳቤ ደረሰኝ። እጅግ ደስ አለኝ። በኢትዮጵያ ሁሉ በዳግማዊ ምኒልክ የናንተ ንጉሠ ነገሥት ብዙ ተስፋ አለኝ፣ ነገር ግን የናንተ አሳብና የኔ አሳብ ይስማማ እንደሆነ ለመመርመርና ለማስረገጥ እሙን አሸከር ዶክተር ነራዚኒ ከወዳጃችሁ ዲማርቲኒ ጋር ከናንተ ሊዋዋሉ እሰድላችኋለሁ። ሁሉንም ነገር እንደአሳቤ ልትስማሙ ተስፋ አለኝ። የበለጠ ነገር ግን ከዠኔራል ጋንደልፊ የምጥዋ ገዥ ጋር አንድ ትልቅ ጉባኤ አድርጋችሁ እንድትገናኙ ለሁላችሁም የሚጠቅም ውል እንድተዋዋሉ። ፍቅራችንም በሁላችን ተጠብቃ ረዥም ዘመን እንድትኖር እግዜርን እለምናለሁ። ተጻፈ በኢጣሊያ መንግስት ቤት 15 መስከረም 1891 መስከረም 5 ቀን 1884 ዓ.ም - ፌ. ኡምቤርቶ >>(አቶ ገብረሚካኤል ጉርሙ ያጠናቀሩት ከላይ የተገለጸው ጥናት ገጽ 324)

ከመቀጠላችን በፊት ኔራሲኒ እና ማርቲኖ አንባቢ ማን እንደሆኑ ግራ እንዳይገባው ለማብራራት አቶ ተክለጻድቅ መኩርያ ኔራሲኒ ማን እንደነበር እንዲህ ይገልጹታል።

<<ዶክተር ቺዛሮ ኔራሲኒ የተባለው ተቀማጭነቱ በሐረር ሆኖ የራስ መኮንንንና የሐረርጌን ሁኔታ የሚሰልል ነው። በዛ በኩል የዜይላን እያጠና ወደፊት ቢያስፈልግ ወደ ሐረር በኩል የጦር ግምባር ለመክፈት የሚያስችለውን መንገድ የሚመረምርና ራስ መኮንንንም ከአፄ ምኒልክ የሚለዩበትን መንገድ ሲያውጠነጥን የቆየ ነው። አሁንም በመጨረሻ የራስ መኮንን ለክዳት አለመበገር ሲታወቅ ከሐረር ወደ ሮማ ከተመለሰ ወዲህ ራስ መኮንንንም ከአጼ ምኒልከ ለማስከዳት የታቀደውን ዓላማ ፍጻሜ ለማድረስ ተመርጦ የመጣ ነው።

ዶክተር ዲማርቲኖ አንጀሎ ካሁን በፊት ከመሐመድ አንፍሪ ዘንድ አራት ዓመት አውሳ ላይ ሆኖ ባላባቶቹን ከምኒልክ ለማስከዳት ብዙ ሰርቷል። ዓድዋ ላይም የኢጣሊያ ወኪል ሆኖ ከነራስ መንገሻ ጋር ተዋውቆ በጣም የተለማመደና የተወዳጀ የትግራይን ጸባይ ያዉቃል ተብሎ እንደ እነ ኔራሲኒ የተመረጠ ነው። ራሳቸው ራስ መንገሻ “እሱ ይምጣልኝ” (ዲማርቲኖ) ብለው ነበር። ለዚህ የመለያየትና ምንልክን የማዳከም ተግባር መመርያ ተቀብሎ ወደ መቀሌ የመጣ ነው። ራስ መንገሻ ዮሐንስ ለጣሊያኖች ሲጽፉ "ከወዳጅነት በቀር ምንም አልፈልግም" ሲሉ የኢጣሊያ ንጉሥ ደግሞ “ከዳግማዊ ምኒልክ ከናንተ ንጉሠ ነገሥት ጋር ወዳጅነት ለማድረግ ተስፋ አለኝ” በሚል አነጋገር ለመሸፋፈን ሞክሯል።ድንገት ደብዳቤው ወድቆ ቢገኝ ችግር ላለመፍጠር ነው። ይላሉ የታሪክ ጸሐፊው አቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ።ሆኖም የጣሊያኖቹና በራስ መንገሻ የደብዳቤ ልውውጥ ወደ ተግባር ተለውጦ <<ምጥዋ የሚቀመጠው ዋናው አገረገዥ ዤኔራል ጁሴፔ ጋንዶልፊና ራስ መንገሻ በንጉሥ ኡምቤርቶ ደብዳቤ ላይ እንደተጠቀሰው ተገናኝተው እንዲዋዋሉ አደረጉ። ግንኙነቱ በመጀመሪያ የታሰበው ዓድዋ ላይ ነበር። በኋላ ግን ባንድ ወገን ምስጢር እንዲጠበቅ በሌላም ወገን ዤኔራል ጋንዶልፊ ከመረብ ወንዝ አጠገብ ዓዲ ዃላ አጠገብ እንዲሆንለት ስለጠየቀ፣ ራስ መንገሻም በራስ አሉላም እና በሌሎቹ መኳንንትና ሠራዊት ታጅበው ወደ መረብ ሄዱ። በዚያም ሁለቱ ባለሥልጣኖች በወዳጅነት መልክ ተገናኝተው አሳባቸውን ከተለዋወጡ በኋላ ከዚያው ላይ እንደ ዘላለማዊ የጣሊያኖች ጠላት ይቆጠሩ የነበሩት ራስ አሉላም በራስ መንገሻ ዮሐንስ አማካይነት ከዤኔራል ጋር እጅ ለእጅ ተጨባብጠው በጣሊያኖችና በነራስ መንገሻ መካከል ጠቡ ቆሞ ፍቅር መተካቱ ተነገረ።>> (Italia and Ethiopia p.62,No.1)

ቀጥሎ ወንጌልና መስቀል ቀርቦ ራስ መንገሻና ዤኔራል ጋንዶልፊ ከዚህ እንደሚከተለዉ በመሐላ ስምምነት አደረጉ።

1-     ራስ መንገሻን የሚጠላ ለጣሊያን መንግሥት ጠላት ነው።ራስ መንገሻን የሚወድ ወዳጄ ነው። የጣሊያን መንገሥት ራስ መንገሻን ይወደዋል፤ያከብረዋል። የኢትዮጵያም ንጉሥ ልጅ እንደመሆኑም ያውቃል። ራስ መንገሻን የሚያሳዝን ምንም ነገር እንዳያደርግ ምሏል። 2- የኢጣሊያን መንግሥት የሚጠላ ለራስ መንገሻ ጠላት ነው። የኢጣሊያን መንግሥት የሚወደው ወዳጅ ነው። ራስ መንገሻ የኢጣሊያ መንግሥት ይወደዋልና ያከብረዋል። ህዳር29 ቀን 1884 ዓ.ም>> (Historica Diplomatica…Rosetti PP.108-111 –

ምንጭ ተክለጻድቅ መኩርያ ከላይ በተጠቀሰዉ መጽሐፋቸው)።

ይህንን ሰነድ ላሳይ የፈለግኩበት ምክንያት ከላይ በምዕራፉ መግቢያ እንደተገለጸው ገብረኪዳን ደስታ ደግሞ ደጋግሞ ስለ የሸዋ መኳንንትና ንጉሥ ለጸረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ መቆማቸውን፤ በከዳተኛነት እየከሰሰ ከጠላት ጋር ይመሳጠሩ ነበር እያለ በመመጻደቁ የትግራይ መኳንንትም ከማንኛቸውም መኳንንት ባልተናነሰ ሁኔታ ገብረኪዳን የኮነነውን ተግባር እንደፈጸሙ ለማሳየትና “ኩሩዎቹ የትግራይ መኳንንት” በማለት የሚያቆለጳጵሳቸዉ መኳንንትም ገብረኪዳን በንጉሥ ምኒልክ እና በሌሎቹ ከሚያወግዘው ሥነ ምግባር ነጻ እንዳልነበሩ ለማሳየት ነው።

ያውም ገፋ ብለን የስምምነቱን ሰነድ ስንመረምር በጣም ጉልህ የሆነ ጎጂ ድርጊት የተዋዋሉ መሆናቸውን እንገነዘባለን። ክረስፒ የተባለው ኢጣሊያዊ ስለስምምነቱ “ምኒልክ” በተባለው ሰነዱ የዘገበውን ሰነድ ስንመለክት እንዲህ ይላል፣-

1- ስለ አካለጉዛይና ሰራየ አስተዳዳሪዎች የሚሾሙት በራስ መንገሻና በምጥዋው

ገዥ ስምምነት እንዲሆን፤

2- እነዚህ ሁለቱ አውራጃዎች በውስጥ አስተዳደር ነጻ ሆነው ግብር ለኢጣሊያም ለኢትዮጵያም ግብር እንዳይከፍሉ።

3- በሁለቱ አውራጃዎች ሹማምንት ዘንድ ተቀማጭ የሚሆኑ የጦር መሳሪያ የያዙ የኢጣሊያ ሹማምንት ለመሾም የጣሊያን መንግሥት መብቱ እንዲታወቅለት’

4- በሁለቱ አውራጃዎች ላይ ምንም ዓይነት ዘረፋ እንዳይደረግ የሚል ነው>> Crisp.e Menelich… P.293.No 8 (ቀደም ብሎ ከላይ በተክለጻድቅ መኩርያ በተጠቀሰው መጽሐፍ ውስጥ)።

ገብረኪዳን ደስታ “የዶጋሊና የመተማ ጦርነት ለከሃዲዎችና ለወራሪዎች ለትምክህተኞች ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋለል” እያሉ ንዙዎቹ የትገሬ ምሁራን  የሸዋ ነገሥታትንና መኳንንትን እንደወራሪዎችና ከጠላት ጋር በመመሳጠር ያውም ከጣሊያን ጋር መመሳጠራቸውን እየኮነኑ ራሳቸው የትግራይ መስፍኑ ራስ መንገሻ ዮሐንስና አሉላ ግን መረብ ድረስ ሄደው የተዋዋሉትን ሰነድ ለጠላት ምቹ ሁኔታ ማን ይፈጥር እንደነበረ አንባቢ ከሰነዱ ማየት ይቻላል።

ከስምምነቱ በኋላ የሚያስገርመው ነገር ራሳቸው ራስ ሆነው የንጉሠ ነገሥት ማዕረግ ሳያገኙ ዉሉን ተዋውለው ከጨረሱ በኋላ ራስ መንገሻ ለዤኔራል ጋንዶልፊ የራስነት ማዕረግ፣ ለዶክተር ኔራሲኒ የቀኛዝማችነት ማዕረግ ከልዩ የኒሻን ሽልማት ጋር ስለሰጡ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ መሸፈታቸውን ራሳቸው አስታወቁ ማለት ነው።

ቀጥለውም ጣሊያኖችን ተገን አድርገው፣ ባላንጣቸው የነበሩት በፊት ከጣሊያን ጋር ተጠግተው የነበሩት ደጃዝማች ደበብ አርዓያን “ይሓ” ላይ ወግተው ከገደሉ በኋላ ጉልበት አግኝተው ጣሊያኖችም የኤርትራ ቅኝ ግዛት ከምጥዋ አስከ መረብ ወንዝ እንዲደርስ የተመኙትን እንደሚያገኙ ብቻ ሳይሆን በሰሜን በኢትዮጵያ እንደልባቸው ለመስፋፋት እንደሚችሉ እንደቆጠሩት አቶ ተክለጻድቅ ይገልጻሉ። ሌላው አስገራሚ ደብዳቤ ለጣሊያን የጻፉት;

<<ደበብን የገደልኩት ጣሊያንን ዉደድልኝ ብየ ብጠይቀው ተዋጋኝ>> ብለው መጻፋቸው ነው። እንግዲህ የትግራይ ምሁራን ሁለት ዓይናቸውን ከፍተው እንዲያዩ የሚከተለውን ደብዳቤ ልጋብዛቸው።

ደብዳቤው እንዲህ ይላል።

<< ደጃች ደበብ ኢጣሊያኖች ወዳጆቼ ናቸውና ዉደድልኝ ብየ ብላቸው እንቢ ብለው፣ ስጓዝ ካንገት በር (መግቢያ በር) ላይ ቆይተው ተሰልፈው ተዋጉኝ፤ በእግዚአብሔር ቸርነት በእመ ጽዮን አማላጅነት በእርስዎ ጸሎት ድል አደረግኋቸው፣ እርሳቸውም ሞቱ። >> (Archivio Storic? (Ethiopia) XV 1895 -Roma ) በማለት የምስራች ደብዳቤ ለኢጣሊያ ንጉሥ ጻፉ።

ራሱ በደብዳቤ መላላክ፤ በውል መፈራረም፤ ለጣሊያን ሲሉ የገዛ ወገናቸውን በመግደል አልተወሰኑም ነበር። ቀደም ብሎ በ1884 ዓ.ም መስከረም 13 ለንጉሥ እምቤርቶ ያቀረቡትን ገጸ በረከትም ጋር አብሮ የተላከው ከሚከተለው ሸኚ ደበዳቤ ጋር ላይ እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ።

<< ይድረስ ሃበ ዓብይ ወክብር ንጉሥ አበርቶ (ኡምቤርቶ)… ገጸ በረከት ያባቴን የጃንሆይ (ያጼ ዮሐንስ) የነበረ የወርቅ ኮርቻ ለፍቅር ምልክት እንዲሆን ሰድጃዋለሁ…>>Archivio Storico XV 1857-1895 (Roma) በማለት የወላጃቸውን የወርቅ ኮርቻ ለወራሪው ጣሊያን ለንጉሥ ኡምቤርቶ በስጦታ አበርክተዋል።

ታዲያ ምንሊክ እንዴት ሲሆን ነው ከጣሊያን የሚሞዳሞዱ የሚመሳጠሩ እያሉ የትግሬ ምሁራን ንጉሡን ለይተው የዓድዋ በዓል በመጣ ቁጥር ልሃጫቸውን የሚያዝረከርኩባቸው?

ፍርዱን ለናንተው ትቻለሁ።

ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay

 

 

 

 

No comments: